መሠለ ገ/ህይወት
ውልደትና እድገቱ የፍቅር ከተማ በሆነችው ደሴ ከተማ ነው፡፡የልጅነት ዘመኑን ያሳለፈው፣ የ1ኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው ደሴ በሚገኘው በወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት ነው፡፡የነፍስ ጥሪው ጋዜጠኝነት እንደሆነ ያወቀውና የተረዳው ገና ብላቴና ሆኖ ነው፡፡
ከመደበኛ ትምህርቱ ጎን ለጎን በወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት ሚኒ ሚዲያ ውስጥ አጫጭር ግጥሞችንና የተለያዩ መጣጥፎችን ማቅረብ፣በሰንበት ት/ቤት እና በሰናይ አማተር የጋዜጠኞች ክበብ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የተጀመረው የሙያ ጉዞ ደሞዝ የሚቆረጥለት ባለሙያ ወደ መሆን ያሸጋገረው በ1991 ዓ.ም ነበር፡፡
እስከ 2002 ዓ.ም ድረስ ባሉት ጊዚያት በተለያዩ ጋዜጦች ላይ ከጀማሪ ሪፖርተርነት እስከ ዋና አዘጋጅነት ድረስ ሰርቷል።
ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በግሉ በሚያሳትመው የሽግግር መፅሔት ዋና አዘጋጅ ነው፡፡
ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ታዋቂ ዜና አቅራቢዎች መካከል አንዱ የሆነው መሰለ ገብረ ህይወት የኢቢሲ ቤተሰብ የሆነው ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡”ለሙዚቃ የተለየ ፍቅር አለኝ” የሚለው ጋዜጠኛ መሰለ በአንድ ወቅት የመልካሙ ተበጀን እና የንዋይ ደበበን ሙዚቃዎች በመጫወቱ በብዙዎች ዘንድ ከፍተኛ መነጋሪያ ሆኖ ነበር፡፡
በቀድሞው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በህትመት ጋዜጠኝነት ዲፕሎማ ፣ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቴሌቪዥን ጋዜጠኝነት የመጀመሪያ ዲግሪውን እንዲሁም በጋዜጠኝነት እና ኮሙኒኬሽን ደግሞ ሁለተኛ ዲግሪውን ሰርቷል፡፡
በቅርቡም “ የሚዲያ አመራር ”የሚል አዲስ መፅሐፍ አዘጋጅቶ ለንባብ አብቅቷል፡፡የረዥም አመት የሙያ ልምዱንም በተለያዩ የስልጠና መድረኮች እየተገኘ ለጀማሪ ጋዜጠኞች እያካፈለ ይገኛል፡፡
‹‹በጣም የወደዳቸውና የምንጊዜም ምርጫዎቼ ናቸው” ያላቸውን ሶስት መፅሃፍቶች መርጧል፡፡
1. ታላቁ ተቃርኖ ….. ሐብታሙ አለባቸው
2. አጥቢያ…… አለማየሁ ገላጋይ
3. ጋዜጠኝነት ያለአስተማሪ…..ላዕከማርያም ደምሴ