ገፀ-ብዙው ባለራዕይ ክብረት አበበ ( አቤቤ ) እና የጠብታ አምቡላንስ ጉዞ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን ፣ መዝገበ-አእምሮ ( የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ ) ፕሮጀክቱ ለአገር የሠሩ ሰዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ታሪክ በዲጂታል ሚድያዎች ፣በመፅሀፍ፣በድምፅ ትረካና በሌሎችም መንገዶች እየቀረበ እንደሆነ ይታወቃል።በተለይ ጉግል ላይ ታሪካቸው ሲፈለግ የማይገኝ ሰዎች አሁን የሙያ አበርክቷቸው በቀላሉ ኢንተርኔት ላይ በግልፅ ተቀምጦ ይገኛልደ ባለፉት 4 ዓመት ከ 5 ወር ጊዜ ውስጥ የ423 ሰዎችን የሕይወትና የሥራ ታሪክ ለመሰነድ የቻልን ሲሆን 600 ገፅ ባላቸው ሁለት የተለያዩ መፅሐፎች ላይም ታሪኮቹ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው እንዲቀመጡ አድርገናል።
በዚህ የስነዳ ሥራችን ውስጥ በቅፅ 3 ከተካተቱት 20 ዘርፎች ውስጥ የሥራ ዘርፎች ውስጥ ሥራ ፈጠራ አንዱ ነው። ሥራ ፈጠራ ብቻ ሳይሆንየሚድያ ሰዎችም፣ የቴአትር ባለሙያዎች እየተሰነዱ ይገኛሉ። አጠቃላይ 74 ከፍተኛ የሚድያ አመራሮች፣ሚኒስትሮች ፣ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የግል ሚድያ መሥራቾች፣ዋና አዘጋጆች እና መካከለኛ አመራሮች ተካተዋል። 35 ያህሉ በዋና ሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ያሉ ሲሆን የሁሉም ታሪክ በተሟላ ደረጃ ለመሰነድ ተችሏል። የእነዚህን ሰዎች ታሪክ ሰንዶ ለአንባቢ ተደራሽ ማድረግ ፈታኝ ቢሆንም አሳክተነዋል። በዚህ ተግባራችንም ተጠናክረን እንቀጥላለን።
በዚህ ፅሑፍ የሕይወት ጉዞውን የምናይለት ባለ ራዕይ ሥራ ፈጣሪ የጠብታ አምቡላንስ መሥራች ክብረት አበበ ነው። ክብረት ከሰሞኑ ስዊዘርላንድ አቅንቶ በአለም የኢኮኖሚ ፎረም ላይ ታድሞ ዓለም አቀፍ ዕውቅና አግኝቷል። እኛም በቅፅ 3 የመዝገበ አእምሮ መፅሀፍ ላይ የክብረት ታሪክ እንዲሰነድ አድርገናል። እስከዚያው ግን በተወዳጅ ሚድያ ዲጂታል መንገዶች ከእነ ምስክርነቱ እንዲያነቡ ተጋብዘዋል። ታደሰ ማሞ እና ዕዝራ እጅጉ የሕይወት ታሪኩን አጠናክረውታል።
ክብረት አበበ የጠብታ አምቡላንስ መስራችና ስራውን በዋና ስራ አስፈፃሚነት የሚመሩ ታታሪ ሰው ናቸው፡፡
አቶ ክብረት አበበ ቱፋ ይባላሉ፡፡‹‹እኔ በተማርኩትና ኋላም በስራና በህይወት ልምድ ባዳበርኩት ዕውቀቴ ለራሴም ሆነ ለማህበረሰቡ ያዋጣሁት ጠብታ ምንድነው? በሚል ሞጋች ጥያቄ ተነሳስቼ ነው ጠብታ አምቡላንስን የመሰረትኩት›› ይላሉ፡፡
ማንኛውም የራሱን የግል ስራ ፈጥሮ ለመስራት የሚነሳ ሰው በቅድሚያ እኔ ምን ዕውቀት አለኝ? እንዴትስ ዕውቀቴን ተጠቅሜ በምሰራው ስራ ህይወቴን የሚቀይር ገቢ ማግኘት እችላለሁ? ብሎ ራሱን መጠየቅ አለበት የሚሉት አቶ ክብረት አበበ አሁን ያላቸውን ድፍረትና ጥንካሬ የወረሱት ከአባታቸው እንደሆነ ዘወትር ይናገራሉ።
በራሳቸው የስራ ፈጠራ ተነሳስተው ከብቶችና ዶሮዎች በማርባት፣ወይን በመትከል እና ማር በማነብ ውጤታማ ከነበሩት አባታቸው የሥራ ፈጠራ ክህሎትን እንደወረሱም ይናገራሉ፡፡
ትውልድ እና ልጅነት
የኮሪያ ዘማች ከነበሩት አባታቸው ሻምበል አቤቤ ቱፋ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ንጋቷ አጀቢ በአዲስ አበባ ከተማ ጃን ሜዳ አካባቢ በሚገኘው በኮሪያ ሰፈር በ1962 ዓ.ም ተወለዱ፡፡
12 ልጆችን ላፈሩት እናትና አባታቸው ስድስተኛ ልጅ ናቸው፡፡‹‹እንደማንኛውም የወታደር ልጅ በብዙ ዕጥረት፤ሆኖም ግን በተሟላ የቤተሰብ ፍቅር ነው ያደኩት››የሚሉት ነርስ ክብረት አበበ የጃን ሜዳ ልጅ እንደመሆናቸው መጠን አብዛኛውን ጊዜያቸውን በጨዋታ ነበር የሚያሳልፉት።የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ኮሪያ ሰፈር በሚገኘው ህብረት ፍሬ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በኮከበ ፅባህ ት/ቤት አጠናቀዋል፡፡
#ጉዞ ወደ ዩኒቨርሲቲ – ወደ ሥራ ዓለም
ጥቂት ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ፈተናን በሚያልፉበትና የኮሌጅ ተሳትፎ ብርቅ በሆነበት በዚያ ዘመን በልጆቻቸው የትምህርት ጉዳይ በማይደራደሩት አባታቸው ጥብቅ ክትትል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት አግኝተው የጅማ ጤና ሳይንስ ኢንስቲቲዩት (የአሁኑ ጅማ ዩንቨርሲቲን) ተቀላቀሉ፡፡
በ1981 ዓ.ም ከጅማ ጤና ሳይንስ በነርሲንግ ሙያ በዲፕሎማ ከተመረቁ በኋላም ለአምስት ዓመታት ያህል በባሌ ክፍለ ሀገር በጊኒር ከተማ ተመድበው አገልግለዋል፡፡
#ጠብታ አምቡላንስ
ወደ አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆሰፒታል ተዛውረውና በአንስቴዚያ ትምህርት ቤት ተምረው ከተመረቁ በኋላ የማደንዘዣ ሙያተኛ (አንስቴቲስት) ሆነው ለ17 ዓመታት በዚሁ ሆስፒታል አገልግለዋል፡፡ኋላም የግል ስራቸውን ለመከወን የሚያስችላቸውን በትምህርት፣በንባብና በልምድ ጭምር ያዳበሩትን ዕውቀት ሰንቀው ጠብታ አምቡላንስን መሰረቱ፡፡
ከህክምና ዘርፍ ትምህርታቸው በተጨማሪ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ ከፋክሊቲ ኦፍ ቢዝነስ ኤንድ ኤኮኖሚክስ በማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪ ተቀብለዋል፡፡ጠብታ አምቡላንስን በመሰረቱ በሁለተኛው አመት ላይ በአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት አማካኝነት አዲስ አበባ፣ኪጋሊ እና ስቶክሆልም በሲዊዲኑ ግብረ ሰናይ ድርጅት ሲዳ (SIDA) አማካኝነት የአንድ አመት የቢዝነስ ስትራቴጂ ስልጠና ወስደዋል።ከዚህም ሌላ የአኩመን ኢስት አፍሪካ የ2015 የፌሎው ሺፕ ፕሮግራም ውስጥ በመሳተፍ ለአንድ አመት ያህል በተለያዩ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በመዘዋዘር የአመራርነት ስልጠና ወስደዋል።
#ማህበራዊ ሥራ ፈጣሪው ክብረት
አቶ ክብረት አበበ የኢትዮጵያ ማህበራዊ ሥራ ፈጣሪዎች ፕሬዘዳንት፣ የካታሊስት 2030 እና የአፍሪካ ፎርዋርድ የኢትዮጵያ ተወካይ እና ሮቴሪያን በመሆናቸው ከ60 ሀገራት በላይ ተጉዘዋል።
ተጉዘው ንግግር ካደረጉባቸው ትልልቅ ስብሰባዎች ውስጥ የ2016ቱ የአውሮፓ ዲቨሎፕመንት ደይስ (Europian Development Days, 2016, EDD, 2016 )በወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ከነበሩት ከጠቅላይ ሚ/ር ሐይለማርያም ደሳለኝ ጋር የመሳተፍ እድል አግኝተው ነበር፣በ2017 በአሜሪካን ሀገር በዋሽንግተን ከተማ ወርልድ ባንክ ስራቸውን የተመለከተ ፕረዘንቴሽን እንዲሁም በእንግሊዝ ፓርላማ የኢትዮጵያን የማህበራዊ ሥራ ፈጠራ ሥነ ምህዳርን በተመለከተ የመናገር እድል አግኝተዋል።
#ህልማቸውን ያሳኩ
ከልጅነታቸው ጀምሮ እንዲህ መሆን እፈልጋለሁ ብለው መናገራቸውን ባያስታውሱም በቂ ዕውቀትና ልምድ ከቀሰሙ በኋላ ግን የተፈላጊ ሙያ ባለቤት ሆኜ እስከመቼ በችግር እኖራለሁ የሚል ጥያቄ ራሳቸውን በመጠየቅና ለጥያቄው ፈጣን ውሳኔ በመስጠት ማንም በግል ባልደፈረው በድንገተኛ ህክምና ዘርፍ ጠብታ አምቡላንስን መስርተዋል፡፡
በወቅቱ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በተጨማሪ በሌሎች ስድስት ሆስፒታሎችም በአንስቴዚያ ህክምናው ሲኒየር አንስቴቲስት በመሆን ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም ከድህነት ራሳቸውን ለማውጣት ቢችሉም ህይወት ማለት መግዛትና መሸጥ ወይም ከድህነት ራስን ብቻ ነፃ ማውጣት አይደለም በሚል ፍልስፍናቸው ጧት ማታ ከራሳቸው ጋር ብዙ ተሟግተዋል፡፡
2001ላይ አምቡላንስ አምጠው ወለዱ
ምን ዓላማና ህልምስ ሊኖረኝ ይገባ ይሆን? ብለው ራሳቸውን ሲጠይቁም ከማንነታቸው ጋር በሚገባ ተመቻችቶ ያገኙት የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ስርዓትን በመዘርጋት ስራውን የገቢ ማስገኛ ማድረግ እንደሚቻል ተረድተው በ2001 ዓ.ም ጠብታ አምቡላንስን አምጠው ወልደዋል፡፡ሆኖም ስራውን መጀመርና መዝለቅ በአረንጓዴ መስክ ላይ እንደመራመድ ምቹና ቀላል አልነበረም ባይ ናቸው።
በኢትዮጵያ ደረጃ ብዙዎች የተለያዩ የስራ ዕድሎችን ፈጥረው ቢሞክሩም የእሳቸው ግን የማይገመትና የማይደፈር ነበር፡፡አምቡላንስ ሲባል ብዙዎች አናቱ ላይ ያለውን ቀይ መብራት ብልጭ ድርግም እያደረገና የሳይረን ድምፅ እያሰማ በተከለከለ መንገድ ሳይቀር በጥድፊያ የሚምዘገዘገው መኪና ይመስላቸዋል፡፡
አምቡላንስን አምቡላንስ የሚያስብሉት ሁለት መሰረታዊ ነገሮች ናቸው።የተገጠሙለት የድንገተኛ ህክምና መሳሪያዎች እና መሳሪያዎቹን ጠንቅቀው የሚያውቁ ሙያተኞች።አምቡላንሶች በውስጣቸው የያዙት የህክምና መሳሪያ ከመኪናው ዋጋ በላይ መሆኑን የሚያውቁ ቁጥራቸው ትንሽ ነው፡፡
አምቡላንስ በድንገተኛ አደጋ ተጎድተው የወደቁት አጥንታቸው ከመሰረቱ እንዳይናጋ የሚደግፍ፣ የሚፈስ ደምን የሚያቆም፣የፈሰሰ ደማቸውን በጊዜያዊነት ለመተካት የሚሞክር፣የልብ ምታቸው እንዳይቆም እና አየር እንዳያጥራቸው የሚያግዙ መሳሪያዎችን ያሟላና፤እንዲሁም ከሾፌሩ ጀርባ ሆነው የተሟላ የድንገተኛ ህክምና ዕርዳታ የሚሰጡ ባለሙያዎችን እና ታታሪ ሾፌርን ያካተተ ነው ይላሉ የጠብታ መስራቹ ክብረት አበበ፡፡
ጠብታ ሲጀመር
ጠብታን ለማቋቋምና በአዲስ ወኔ ወደ ስራቸው ለመግባት ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለቀው ፈቃድ ለማውጣት ወደ ጤና ጥበቃ ሲያመሩ የፈጠራ ሀሳባቸውን ብዙዎች አልተቀበሉትም።
ከዚህ ቀደም በስራው ላይ በግል የተሰማራ ተቋምም ሆነ ግለሰብ ስላልነበረ ወዲህም ስራውን ለመለካት የሚያስችል መለኪያ (ስታንዳርድ) የተዘጋጀለት ባለመሆኑ ፈቃዱን ለማግኘት አቀበት ሆኖባቸው ነበር፡፡
እናም አቶ ክብረት በራሳቸው ተነሳሸነት ለአሰራሩ መመዘኛ የሚሆን ስታንዳርድ አዘጋጅተው አቀረቡ፡፡ያቀረቡት የድንገተኛ ህክምና መመዘኛ ከታየ በኋላም ጥያቄው ከቀረበ ከስድስት ወር በኋላ የስራ ፈቃዱ ፀደቀላቸው፡፡
#Dead aid መፅሀፍን አነበቡ
አንዳንዶች ይህን ሀሳብህን ለምን መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በሚል አቋቁመህና በስራው ላይ አጋዥ አካላትን እያሳተፍክ ብትከውነው ይበጅ ነበር እያሉ ከወዲሁ የስራውን ክብደት መዝነው ቢወተውቷቸውም ጥልቅ ሀሳባቸውን ተረጋግተው በማስረዳት በድፍረት ወደ ስራቸው ገብተዋል፡፡
ይህን ሀሳብ ያለመቀበላቸው አንዱ ምክንያት በወቅቱ በተመስጦ ያነቡት የነበረው የታዋቂዋ አፍሪካዊት የደሚሳ ማዮ መፅሐፍ ነበር፡፡ዘ ዴድ ኤድ (Dead Aid) ፡፡በአጭሩ ደሚሳ ማዮ በመፅሐፍዋ ላይ ለማስረዳት የምትሞክረው እርዳታ እንዴት የአፍሪካን ህዝብ ለችግሮቹ ሁሉ መፍትሄ ምዕራብያውያኑ ጋር እንደሆነ እንዲያምኑ ለማድረግ እርዳታን እንደተጠቀሙበት በማስረዳት ነው።
ይህ ክብረት ከ15 አመት በፊት ጓደኞቹ ሲመክሩት የነበረን ሐሳብ ዛሬ ትልቁ የአሜሪካን ረጂ ድርጅት (USAID) በድንገት እርዳታውን ሲያቆም ያስከተለው ማህበራዊ ቀውስ ብቻውን የእርዳታን አገር እና ህዝብ ገዳይነት በተግባር ያሳየ ነው ይላሉ አቶ ክብረት አበበ።
ብዙዎች የድንገተኛ አደጋ የመጀመሪያ ህክምና ዕርዳታን በክፍያ መስራት የሚታሰብ አይደለም ብለው በሚያስቡበት አገር ስራውን በክፍያ ለማከናወን ክብረት ትግል ገጠሙ፡፡
‹‹በዕርግጥ ለወደፊቱም እንደ ሀገር ለእያንዳንዱ ሰው በቂ የጤና ኢንሹራንስ ሽፋን እንዲሟላ ካልተደረገ በዚህ መንገድ ብቻ ስራውን መከወን ፈታኝ ነው››የሚል ምክራቸውን ለሚመለከተው አካል እያሳሰቡ ዛሬም በስራው ላይ አሉ፡፡
አነሳሳቸው
አነሳሳቸውን ስናስታውስ ሌላው ፈቃድ ከማግኘት በኋላ አንስቴቲስት ክብረትን የፈተናቸው ጉዳይ ለስራው አስፈላጊ የሆነውን ገንዘብ ማሰባሰብ ነበር፡፡
ምንም እንኳን ባንኮች አቶ ክብረት ባቀረቡት አዲስ የስራ ፈጠራ ሃሳብ ቢደመሙም የወገኖችህን ህይወት ለማዳን አዲስ ሀሳብ በማፍለቅህ ብናደንቅህም ለዚህ ብለን የያዝነው የብድር ገንዘብ ስለሌለን እናዝናለን ብለው መለሷቸው፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት፡፡ብዙ ህዝብም አላት፡፡ድንገተኛ አደጋዎች እዚህም እዚያም ይከሰታሉ፡፡በኢትዮጵያ በየትኛውም ጎዳናም ይሁን በስራ ቦታዎች ወይም በቤት ውስጥ፣በድሃም ሆነ በሀብታም፣በተማረም ይሁን ባልተማረ፣በወንድም ይሁን በሴት፣በህፃንም ይሁን በአዋቂ ላይ ድንገተኛ አደጋ ሊከሰት ይችላል፡፡ሆኖም እንደኔ የነዚህ ሰዎች ጉዳይ አሳስቦት ወደዚህ ስራ ለመግባት የሚሞክርን ሰው በብድር ገንዘብ ለመደገፍ የተዘጋጀ የፋይናንስ ተቋም አለመኖሩ አስደንግጦኝ ነበር›› ይላሉ ትናንትን ሲያስታውሱ፡፡
ዛሬም ኢምፓክት ኢንቨስትመንት ወይም ፔሻንት ካፒታል የለም ይላሉ አቶ ክብረት። ባንኮች ህንፃ ይይዛሉ፣ገንዘብ ይሰጣሉ፤ሀብታም የነበረን የበለጠ ሀብታም ያደርጋሉ፡፡ይህው ነው የፋይናንስ ስርአቱ አካሄድ ።
ያኔ መውጣት መውረዱ አሰልቺ የሆነባቸው እኚህ ብርቱ ሰው ስለስራቸው ለሌሎች ማስረዳቱ ማገዶ መፍጀት ብቻ ሲሆንባቸው ወደ ቤታቸው ተመልሰውና ከውድ ባለቤታቸው ጋር መክረው በሚገባ በመተማመን የመኖሪያ ቤታቸውን ሸጠው የመጀመሪያዎቹን ሶስት አምቡላንስሶች ከዱባይ በመግዛት ወደ ስራ ገቡ፡፡ጨለማ የወረሰው ይመስል የነበረውን ረጅም መንገዳቸውንም የመጀመሪያውን ሻማ በመለኮስ ወገግ አደረጉት፡፡
ከሁሉም በላይ በመኪና አደጋ ብዙዎች ለድንገተኛ አደጋ ይዳረጋሉ፡፡ወደ ጠብታ አምቡላንስ ተደጋጋሚ ጥሪዎች የሚሰሙትም በዚሁ አደጋ ነው፡፡በኮንስትራክሽን ስራዎች አካባቢና በየቤቱ እንደ ስትሮክ የመሳሰሉ በሽታዎችም የድንገተኛ አደጋ መንስዔነታቸው ጨምሯል፡፡
እናም ድንገተኛ አደጋ ሲገጥም ሰዎች ለህልፈትና ለዕድሜ ልክ አካል ጉዳተኝነት የሚጋለጡት በዋናነት ከአደጋው መከሰት በኋላ ከወደቁበት ቦታ በአግባቡና በጥንቀቄ ተነስተው ፈጥነው ወደ ጤና ተቋም ባለመድረሳቸው መሆኑን የጠብታ ሰዎች በሚገባ ከተገነዘቡት ቆይተዋል፡፡
እንደ አቶ ክብረት አገላለፅ በድንገተኛ አደጋ የወደቁ ወገኖቻቸውን በባለሙያ በሳይንሳዊ መንገድ በጥንቃቄ ተነስተው ወደ ጤና ተቋም ሳያደርሱ እባካችሁ ወገኔን ወደ ቀድሞ አቋሙ ፈጥናችሁ መልሱልኝ ብለው የሚለምኑ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡
እናም ይህን ማንም ከሳቸው በፊት በግል ደረጃ ያልደፈረውንና ስራው የቀይ መስቀል ብቻ ነው ተብሎ በሚታሰብበት አገር የድንገተኛ አደጋ ወቅት የመጀመሪያ ህክምናን እና የአምቡላንስ አገልግሎትን በክፍያ ለመስራት ታጥቀውና አልመው የገቡት ከዚያ በፊት በሆስፒታል የስራ ላይ ቆይታቸው አደጋ የደረሰባቸው ሰዎች ከወደቁበት በሚነሱበት ወቅት እንደ ግኡዝ ነገር ታፍሰው ብቻ ወደ ሆሰፒታል የሚመጡት ከጥንቃቄ ጉድለት የተነሳ ለዘላቂ ችግር ሲዳረጉና ህይወታቸው ሲያልፍ በተደጋጋሚ በመመልከታቸው ነበር፡፡
ማንበብ ሙሉ ሰው ሲያደርግ-አሠራርን መፈተሽ
ታዲያ ዝም ብለው ወደ ስራው ዘው ብለው አልገቡም፡፡ብዙ አነበቡ፡፡በተለያዩ አጋጣሚዎችም የሌሎች አገሮችን የአሰራር ልምድ በሚገባ ፈተሹ፡፡በአይናቸውም አሰራራቸውን ተመለከቱ፡፡
በተለይ በአንድ ወቅት አንድ እንግሊዛዊ በኢትዮጵያ ሳለ የልብና የመተንፈስ ችግር ገጥሞት በአስቸኳይ ወደ ለንደን መብረር አለበት ተብሎ ይወሰናል፡፡አቶ ክብረትም ተገቢውን ሙያዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ ተመርጠው አብረው በመጓዝ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በአግባቡ ፈፅመው ለንደንን ሲረግጡ ያዩትን ማመን አቃታቸው፡፡
‹‹ድንገተኛ አደጋ የገጠመውን እንግሊዛዊ ይዤ ለንደን ስደርስ የአንድ ዜጋቸውን ነፍስ ለማትረፍ በአየርና በምድር ያደረጉትን ርብርብ ስመለከት ለካስ አንድ ሰው አንድ ሀገር ነው እንድልና የሰው ልጅን የህይወት ዋጋ ውድነት እንዳሰብ አድርገውኛል›› ብለዋል፡፡
ከዚያም በለንደን በነበራቸው የአምስት ቀን ቆይታ ለቀጣይ ስራቸው ስምሪት የሚያግዙ ልምዶችን ቀስመው ተመለሱና ለመስሪያ ቤታቸው የስራ መልቀቂያ አቅርበው ለአዲሱ ጉዞ ተዘጋጁ፡፡
ለንደን በስኬት የታመመውን ተጓዥ ከደረስኩ በኋላ እራሴን የጠየኩት ጥያቄ ይህንን ነው ይላሉ አቶ ክብረት፡፡”ከአዲስ አበባ ቦሌ ኢንተርናሽናል ኤርፓርት ወደ ለንደን አንድን ሰው በጤና ካደረስኩ ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቅርብ ከሆነው ፖስታ ቤት አስፋልት ላይ የመኪና አደጋ የደረሰበትን የራሴን ዜጋ እንዴት ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ማድረስ ያቅተኛል?”
የሰው ልጅ ህይወት ውድ በሆነባት የለንደን ከተማ ያየሁትንና የሰውን ነፍስ ለመታደግ የሚደረግን የጋራ የተቀናጀ ርብርብ አይቼና ተገርሜ ወዲህ ስመለስ፤ሰው ዝም ብሎስ ይሞት የለም ተብሎ በሚተረትበትና ህይወት ርካሽ በሆነበት አገር የድንገተኛ የመጀመሪያ ህክምና ዕርዳታን ለወደቁት በክፍያ ለመስጠት ማሰቤ ብዙዎቹን ማሰገረሙ አልደነቀኝም ይላሉ አቶ ክብረት፡፡
ሆኖም ይላሉ ሲቀጥሉ ሆኖም የድንገተኛ አደጋ ደርሶ ጥሪ ሲደርሰን እኛ ወደ ተጎጂዎች የምንቀርበው መክፈል ስለመቻላቸው እያሰብን ሣይሆን ህይወታቸውን ስለማዳን እየተጨነቅን ነው ካሉ በኋላ ስለክፍያ እያሰብን ብንሰራማ ኖሮ ገና ዱሮ ስራውን አቁመን ፈቃዳችንን መልሰን ጠብታን እንዘጋው ነበር ይላሉ፡፡
አንዱን ወጪ በአንዱ ገቢ በማካካስና (Cross Subsidy) ቅድሚያ ለሰው ልጆች ህይወት ዋጋ በመስጠት ፈታኙን ስራ ከጀመርነው 15 ዓመታት አልፈውናል ብለዋል፡፡
15አምቡላንስ በ15 ዓመት
ጠብታ አምቡላንስ አሁን 15 የሚሆኑ ደረጃቸውን ያሟሉ አምቡላንሶች አሉት፡፡ተቋሙ በእስከዛሬ ቆይታው ከ100 ሺህ በላይ ለሆኑ ሰዎች የአምቡላንስ አገልግሎት በመስጠት ወደተሻለ ህክምና ወደሚያገኙባቸው ቦታዎች አዘዋውሯል፡፡ቁጥራቸው ቀላል ላልሆኑና ወደ ውጪ ሀገር ሄደው ለመታከም ለወሰኑትም እስከ አየር አምቡላንሱ ድረስ የማዝለቅ ሚናውን ተወጥቷል፡፡
‹‹ተጎድተው ጎዳና ላይ የወደቁት ተጓጂዎች ሳይሆኑ እኛ ነን ፈጥነን ወደ ተጎጂዎቹ መድረስ ያለብን››የሚሉት ጠብታ አምቡላንሶች ስራቸውን በጀመሩበት የመጀመሪያ ሰሞን የነበረባቸውን የባለሙያ እጥረት ለመቅረፍ ከካናዳ ድረስ ልምድ ያላቸው ሙያተኞችን በበጎ ፍቃድ በማስመጣት በድንገተኛ ህክምና አሰጣጥ ዙሪያ በአሰልጣኞች ስልጠና አሰልጥነው በማሰማራት ለሌሎችም የስራ ዕድል ከፍተዋል፡፡
#ሥልጠና በጠብታ
በተለይ ታታሪው ክብረት ተግባራዊ ባደረጉትና ስራ ባስጀመሩት ጠብታ ፓራሜዲክ ኮሌጅ በመጀመሪያው ዙር16 ሰልጣኞችን በኢኮኖሚ ደረጃቸው ዝቅ ካሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በመመልመልና ፒ ኤፍ ሲ (PFC) ከተባለ የኖርዌጂያን አጋር ድርጅት ጋር በመተባበር ለ18 ወራት አሰልጥነው ወደ ስራ ማሰማራታቸው ትልቅ ውጤት መሆኑን ስራ አስፈፃሚው ይመሰክራሉ፡፡
ጠብታ ፓራሜዲክ ኮሌጅ ከመጀመሪያዎቹ ተማሪዎች ምረቃ በኋላ ያገኘውን ልምድ ተጠቅሞ ሦስት ዙር ሰልጣኞችን አስመርቆ ዛሬ አራተኛ ዙር ላይ ይገኛል።ከዚያ ወዲህ ነው አንግዲህ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም በዚህ ረገድ ያለውን ክፍተት ተገንዝቦና ባለሙያዎችን ማሰልጠን ተገቢ መሆኑን አምኖበት በመጀመሪያ እና በማስተርስ ዲግሪ ደረጃ እያሰለጠነ የሚገኘው፡፡
ጠብታ ወደ ከፍታ
‹‹በጠብታ አምቡላንስ ብቻ ተወስኜ አልቀርም›› የሚሉት አቶ ክብረት በቀጣይ የምስራቅ አፍሪካ የህክምና የአጫጭር ስልጠና (Continious professional Development, CPD) የልህቀት ማዕከልን የመመስረት ህልማቸውን ሰንቀው ለዚሁ ህልማቸው ማስፈፀሚያ በአራት ኪሎ አቧሬ አካባቢ ባለ 12 ወለል ህንፃ እየገነቡ የሚገኙት።
የያዙትን ችግር ፈቺ የአምቡላንስ አገልግሎት በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የጠብታ መለያ ቁጥር በሆነው 8035 የስልክ ጥሪ ስር በማቀናጀት የአምቡላንስ አገልግሎትን ለሁሉም ማቅረብን፣ለስራው የሚያገለግሉና ከውጪ እያስመጣናቸው ያሉትን የድንገተኛ ህክምና ግብአቶች በአገር ውስጥ በራሳቸው ፋብሪካ የማምረትን፣የአደጋ ጊዜ ተጎጂዎች የሚገለገሉበትን ሆስፒታል የመገንባትን፣የዲያግኖሲስ(ምርመራ) መስጫ ማዕከል የመክፈትን፣የአየር ላይ አምቡላንስ ሲስተምን ስራ የማስጀመርን፣የሰራተኞቻቸውን ቁጥር ከሺህ በላይ ማድረስንና ሌሎችንም ተያያዥ ስራዎች ለማስፋፋት የደነደነ ዕቅድ ተልመው በስራ ላይ ናቸው፡፡
ጠብታ የጎረቤት አገራት ተስፋ
በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች መድረስ የቻለው ይህ ተቋም ነገም ለሚሊዮኖች መድረስን ይሻል፡፡የሥራ ዘርፎቹን እያሰፋና ተገቢውን ክፍያ እየጠየቀ ከአገር ውስጥም አልፎ የጎረቤት አገራት ተስፋ ለመሆን ይታትራል፡፡
የመጀመሪያውን የግል አምቡላንስ አገልግሎት መስጫ መስርተው በስራ አስፈፃሚነት የዘለቁት፣በኢትዮጵያ የማህበራዊ ሥራ ፈጣሪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ሆነው ያገለገሉት ክብረት የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት የቦርድ አባልም ነበሩ።
ኃላፊነታቸውን በትጋት የተወጡትና የኢትዮጵያ የስራ ፈጠራ ኮሚሸን የአማካሪዎች የቦርድ አባሉ እንዲሁም የኢንጂባራ ዩንቨርሲቲ የቦርድ አባል፤በአፍሪካም ደረጃ የካታሊስት 2030 እና የአፍሪካ ፎርዋርድ የኢትዮጵያ ተጠሪ በመሆን እያገለገሉ ያሉት አቶ ክብረት አበበ ከረጅም ትልሞቻቸው ጋር ዛሬም በስራ ላይ ናቸው፡፡
ባለትዳርና የአንድ ወንድ ልጅ አባት የሆኑት አቶ ክብረት መጪውንም ጊዜ የብዙዎች ተስፋና አለኝታ ሆነው ለመቀጠል ይታትራሉ፡፡በኢትዮጵያ የማኅበራዊ ሥራ ፈጠራ ምሳሌ የሆነው የአቶ ክብረት ተቋም ማለትም ጠብታ አምቡላንስ በዓለም አቀፍ መድረክ ከሰሞኑ የክብር ሽልማት (Prestigious Award) ተችሮታል።
በኢትዮጵያ የጤናው ዘርፍ የመንግሥትን ጫና ለመቀነስ የግል ኢንቨስትመንት ሚና ወሳኝ ቢሆንም፣ የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎትን መዝለቅ ግን በከፍተኛ ወጪውና በአነስተኛ ትርፋማነቱ ምክንያት ለብዙዎች ተመራጭ አልነበረም።ይህንን ሰብረው ከታዩት ሥራ ፈጣሪዎች መካከል ግንባር ቀደሙ የጠብታ አምቡላንስ መስራችና ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ ክብረት አበበ ናቸው።ለዚህም በርካታ እውቅናዎችን አግኝተዋል።
ጥቂቱን ለመጥቀስ ከኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሦስት ሽልማቶች
1ኛ.የጤና ጀግና
2ኛ.የድንገተኛ ህክምና አምባሳደር
3ኛ.የተለየ ሥራ በድንገተኛ ህክምና አገልግሎት።
ከአሜሪካን ሀገር ከሜሪላንድ ስቴት የማህበራዊ ሥራ ፈር ቀዳጅ፤
በዘንድሮ ዓመትም በስዊዘርላንድ ዳቮስ በተካሄደው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ ጠብታ አምቡላንስ የሽዋብ ፋውንዴሽን የ2026 የዓመቱ ምርጥ የማኅበራዊ ሥራ ፈጣሪ ተሸላሚ በመሆን ተመርጧል።
ይህ ስኬት በኢትዮጵያ የፖሊሲ ክፍተት በሚታይበት በማኅበራዊ ሥራ ፈጠራ (Social Entrepreneurship) መስክ መገኘቱ ደግሞ ሽልማቱ ለአንድ ተቋም ብቻም ሳይሆን እንደ ሀገርም ብዙ ትምህርት የሚወሰድበት ጭምር ያደርገዋል።
ማኅበራዊ ሥራ ፈጠራ ትርፍን ማግኘት ላይ ብቻ ሳይሆን፣ማኅበረሰባዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚተገበር የንግድ ሞዴል ነውና።በኢትዮጵያ እንዲህ ያሉ ተቋማት በርካታ ፈተናዎች ይገጥሟቸዋል።ዘርፉ በንግድ ድርጅትና (Profit Maximization) በረድኤት ድርጅት (NGO) መካከል ያለ በመሆኑ፣ግልጽ የሆነ የሕግ ድርጅታዊ መዋቅር አለመኖሩ ለሥራ ፈጣሪዎች እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል።
ይህንን ዘርፍ በሀገራችን በህግ ማዕቀፍ ለመደገፍ ከፍተኛ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል።ጠብታ አምቡላንስ በዚህ ውስጥ ያለፈና ማኅበራዊ የሥራ ፈጠራ በኢትዮጵያ አስፈላጊነቱን ያሳየ ተቋም ነው።
በሽልማቱ ሥነ-ስርዓት ወቅት አቶ ክብረት አበበ እንደተናገሩት “አሁን ብቻዬን እንዳልሆንኩና እንዳላበድኩ አረጋግጫለሁ” ሲሉ ከዛሬ 15 ዓመት በፊት ይህንን ሥራ ቤታቸውን ሸጠው እና የሚመዘኑበትን ሚዛን (Standard) ራሳቸው ፅፈው ሲጀምሩ በኢትዮጵያ የተቀናጀ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት አለመኖሩንና 4 በመቶ የሚሆኑት ብቻ በአምቡላንስ ወደ ህክምና ተቋማት ይመጡ እንደነበር አስታውሰዋል።
እጅግ የሚገርመው አጋጣሚ ደግሞ ጠብታ አምብላንስ በሲዊዘርላንዷ ዳቮስ ከተማ በተሸለመበት በጥር 12 /2018 ዓ.ም (January 20/ 2026) የኢትዮጵያ ሚኒስትሮች ምክር ቤት የሥራ ፈጣሪዎች ፖሊሲን ማፅደቁ በብዙዎች ዘንድ ግርምትን ፈጥሯል።
አቶ ክብረት በጠብታ አምቡላንስ “ከ100ሺ በላይ ለሚሆኑ ተጎጂዎች የአምቡላንስ አገልግሎት ሰጥተናል ፤ከ300 ሺ በላይ ለሚሆኑ ሰልጣኞች የመጀመሪያ ህክምና እና የደህንነት ስልጠና ሰጥተናል ሚሊዮኖችን ባለፉት 10 አመታት በሸገር ኤፍ ኤም ሬዲዮ በየሳምንቱ በምናስተላልፈው የድንገተኛ ህመም እና የደህንነት የጥንቃቄ መልእክቶች ተፅኖ ፈጥረናል ያሉ ሲሆን “በቀጣይም በምሥራቅ አፍሪካ ፈጣንና አስተማማኝ የአየር አምቡላንስ አገልግሎትን እውን ለማድረግ አቅደናል” ሲሉ ተናግረዋል።
አሁን ላይ ጠብታ አምቡላንስ በአዲስ አበባ ባለ 12 ወለል ህንፃ የድንገተኛ ህክምና የልህቀት ማዕከል እየገነባ ሲሆን ይህም በእርግጠኝነት ሊሳካ እንደሚችል ባለራዕዩ ማህበራዊ ሥራ ፈጣሪ ያምኑበታል።
ስለ አቶ ክብረት ምስክርነት የሠጡት የአስተዳደር ዋና አማካሪ የሆኑት አቶ ደምሰው አበበ ይህን ብለዋል፡፡
‹‹ክብረት በሰው ልጆች መካከል የሚሰመሩ ሰው ሰራሽ ድንበሮችን የማይቀበል መሆኑን በድርጊቶቹ ሁሉ ያንጸባርቃል።የሰው ዜግነቱ ዓለም ነው የሚል የማይዋዥቅ ዕምነት ያለው እንደመሆኑ ለጉዞ፣ለሉላዊ (global) መስተጋብር፣ችግሮችን ለመፍታት የብዙዎችን ሀሳብ ስለመቀበል፣አዳዲስ ሀሳቦችን ለማወቅ እንዲሁም ተሞክሮዎችና ታሪኮችን ለመጋራት ትልቅ ቦታ ይሰጣል።ማህበራዊ ህጸጾችን ለመፍታት እንደሚተጋ ታታሪ ግለሰብ የህዝብ የአኗኗር ዘይቤ እንዲሻሻል ይሰራል፤በአዎንታዊ ትርክት ግንባታ እና ኢትዮጵያ ባላት የዕድገትና የመልማት ሰፊ አቅም በፅኑ ያምናል።››
የተሰጡ ምስክርነቶች
የባለቤቱ የወይዘሮ መሠረት ኃይሉ ምስክርነት
መሰረት ኃይሉ እባላለሁ። የአቶ ክብረት አበበ ባለቤት ነኝ። በትዳር 28 ዓመት ከተዋወቅን ደግሞ ወደ 35 ዓመት ገደማ ሆኗል።
ክብረት ትዳሩንና ቤቱን የሚወድ እና የሚያከብር ፣ ለእኔ ለባለቤቱ እና ለልጁ ሁለንተናውን አሳልፎ የሰጠ፣ በጣም ሰላማዊና የፍቅር ሰው ነው።
ሰው በጣም ይወዳል፣ ለብቻው መብላት መጠጣት አይወድም። ከአብሮ አደጎቹ፣ ከጓደኞቹ ፣ ከዘመዶቹ እና ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር በጋራ መብላት መጠጣት እና መሳቅ መጫወት ይወዳል። ለሰው ልጅ የተለየ ፍቅርና ክብር አለው። በተቻለው መጠን ሁሉ ከሰዎች ጋር በሰላም እና በፍቅር መኖርን ይመረጣል ።
ፀብን፣ ጭቅጭቅን፣ ጥላቻን፣ ፉክክርን፣ ክፋትና ተንኮልን ለማስተናገድ ልቡ ቦታ የለውም።
በሥራው ቀልድ አያውቅም ። በይበልጥም ድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ላይ አጥብቆ ነው የሚሠራው። ህልሙ ስለሆነ እንደወለደው ልጁ ነው በትኩረት ተከታትሎ አጥብቆ የሚሠራው። ህልሙን የሚያደናቅፍ ምንም ነገር ማስተናገድ አይሻም ።
ሁል ጊዜ አዲስ ነገር ለመፍጠር የተለየ እይታ አለው። አብዛኛው ሰው በማያይበት አቅጣጫ ነገሮችን ያያል። ያሰበውን ነገር ሳይፈፅም እንቅልፍ አይወስደውም ። ሌት ተቀን ይሠራል ። ተስፋ አይቆርጥም ። በመጨረሻም ያሳካዋል።
ከክብረት የማደንቅለት ባህሪዎች ውስጥ_
- ታታሪነቱን፣ ትጋቱን እና ተስፋ አለመቁረጡን
- ለይቅርታ ያለውን ቦታ
- ሁሉን የሰው ልጅ መውደዱ(ፍቅር ሁሉን ትበልጣለች ) ብሎ ማመኑ
- ነገሮችን በቀናነት እና በብርሀን ማየቱ፣ ነው።
” የሚለውን የሚኖር
የሚኖርለትን የሚሰራ “
#የተስፋዬ ለታ ምስክርነት(ከአስኮ)
ወዳጅ ክብረት የሩብ ክፍለ ዘመን ጎረቤቴና ጓደኛዬ ብል ማራቅ ይሆንብኛል ።
የአለም ኢኮኖሚክ ፎረም ሽልማት ይገባዋል ( Schwab foundation & World Economic Forum Award. Outstanding Social Enterprenuer of the Year, 2026 )
በዓለም ላይ የሚሉትን የሚኖሩና የሚኖሩለትን የሚሠሩ ሰዎች እጅግ ጥቂት ናቸው።
ከእነዚያ ጥቂት እጅግ የታደሉ ሰዎች ውስጥ አንዱ ይህ የኔ ወንድም ክብረት አቤቤ ቱፋ ነው። ይገባዋል የምለውም በምክንያት ነው።
ከብዙ በጥቂቱ ከዛሬ 8 ዓመት አስቀድሞ በእኔ መኖርያ ቤት ግቢ ውስጥ የገጠመንን ብቻ ላንሳ።
አስታውሳለሁ ቀኑ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት ቀን ነው።
ታድያ በየበዓሉ እንደምናደርገው ጎረቤቶች ሰብሰብ ብለን በሬ አርደን ቅርጫችንን ከተከፋፈልን በኃላ ግቢ ውስጥ ተቀምጠን ከሥጋውም ከመጠጡም እየቀማመስን ሳለ እጅግ የምናከብረው ታላቅ ወንድማችን በድንገት ህመም ተሰምቶት ይወድቃል።
ሁላችንም ተደናግጠን የወደቀውን ወንድማችንን ከወደቀበት ለማንሳት ስንቻኮል ክብረት ለእኔ ተዉት ለማንሳት እንዳትሞክሩ የሚል ትዕዛዝ ይሰጣል ።
እኔ ግን አልቻልኩም ይሄ ሰውዬ ምን እያለ ነው? ይልቅ እርዱኝ እናንሳው እያልኩ ለማንሳት እታገላለሁ። ይሄኔ ደጋግሞ ተው ቢለኝ አልሰማ ብለው በጣም ተቆጥቶ (ከዛነ ቀን በፊትም ከዛን ቀን በኃላም ሲቆጣ አይቼው አላውቅም) “ይህ መሬት መቁረጥ አይደለም” ለእኔ ተዉልኝ ( እኔ የመንገድ ግንባታ ሠራተኛ ነኝ)
ያለውና ለዚህ እጅግ ለምናከብረው ታላቅ ወንድማችን ከእግዚአብሔር ጋር ለተጨሜሪ ድፍን 8 አመት እስከዛሬ ሳይለየን በህይወት የመኖር ምክንያት በመሆኑ ለዚህ ነው
” የሚለውን የሚኖር የሚኖርለትን የሚሰራ” እጅግ የታደለ ሰው ነው ብዬ ለመግለፅ የወደድኩት ጎረቤቴ እና ወንድሜን ክብረት አቤቤ ቱፋን
የኢንጂነር ፍቃዱ ጣፋ ምስክርነት
የእኔና የክብረት ትውውቅ የሚጀምረው ካደግንበት የልጅነት የወታደር ሰፈር ጃንሜዳ አካባቢ ልዩ ስሙ “ዜሮ አምስት ቀበሌ” ነው።
ምንም እንኳን በእድሜ ብንለያይም እኔ በትንሹ ብበልጥም እና አብረን አንድ አካባቢ ብናድግም የህይወት አቅጣጫ በተለያየ መንገድ ስለወሰደን አብረን በልጅነት እየተጫወትን የማደግ እድሉ አልነበረንም:: በአንድ አካባቢ ማደጋችንና በተመሳሳይ ታሪክ ውስጥ ማለፋችን ግን ከረጅም ጊዜ በኃላ ቤተሰብ ከመሠረትን በኃላ በአጋጣሚ እንደገና (አስኮ ሊዝ ሠፈር) በዛው ሠፈር በሚኖርና የእኛ ታላቅ በሆነ የቀድሞ የኛ ሰፈር የኑሮ አምስት ( ጃንሜዳ) ልጅ ክብረትን የኛን ሰፈር ጤና ቡድን እንዲያይ ግብዣ አቅርቦለት ለመጀመሪያ ጊዜ በግንባር ተገናኝተን በአንድ ሰፈር ልጅነት ተዋውቀናል።
ከዚህ በኃላ እንግዲህ የጤና ቡድናችን ግንኙነት ጠንካራ ስለሆነና በተለይ የእግር ኳስ ውድድሩ ለእኛ ጃንሜዳ አካባቢ ለተወለድን ልጆች በጣም ያስደስተን ስለነበረ መቅረት የሚባል ነገር አልነበረም። በዚህም ምክንያት በጣም ስለተቀራረብን መኖሪያ አካባቢያችንም አንድ ላይ ስለነበረ በጣም ብዙ ከመተዋወቃችን በላይ የእሱን ራዕይ በደንብ በመገንዘብና ተካፋይ በመሆን የጠብታ አምቡላንስ ቅድመ ሆስፒታል ድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ውስጥ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆኜ በማገልገል ላይ እገኛለሁ::
ክብረትን እንዴት ትገልፀዋለህ ብባል:-
ቅን ፣ያመነበትን ለመሥራት ደፋር፣ ሰው አክባሪ፣የዋህ, የሚያደርገውን የሚያውቅ፣ የቅርቡን ሳይሆን የሩቁን ማየት የሚችል ሰው መሆኑን ነው።
ከእርሱ ምን ተማርክ ብትለኝ ፦
ስለ ችግሮች ሳይሆን ስለ መፍትሔያቸው የሚያስብና ችግሮችን ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ አጋጣሚዎች ናቸው እንጠቀምባቸው የሚል አመለካከት ያለው መሆኑ ነው።
በማህበራዊ ህይወቱ ተጫዋች ከመሆኑም በላይ ጨዋታው በራሱ የሕይወት ታሪክ እና በሌሎች ታሪክ ያለፈና ያሁኑን አካቶ የእውነቱን (የሚያስደንቀውንም የሚያሳፍረውንም) ታሪክ እያዋዛ ማጫወት የሚችል በእውነትና ስለ እውነት የሚኖር ሰው ነው።
ከእርሱ በተለየ ሁኔታ የተማርኩት ነገር ችግር እንዳያጋጥም መጣር ካጋጠመ ደግሞ መፍትሄ እንደሚኖረው በማሰብ አለመጨነቅ እንደሚያስፈልግ ነው።
###@@#@@@
#የወይዘሮ ተናኘ ደገፉ ምስክርነት
.
ክብርዬን የማውቀው ከባለቤቱ ከመሲ ጋር ፍትህ ሚኒስቴር ከተቀጠርኩበት ከ1996ዓ.ም. አንስቶ ነው፡፡ ጠብታን የመጀመሪያውን የግል አምቡላንስ አገልግሎት ሰጪ ድርጅት የመመሥረት ሃሳብ ሲጠነስስ አብሬው ነበርኩ፡፡ ከፍትሕ ሚኒስቴር ከለቀቅሁ በኃላም በተገናኘን ቁጥር ስለጠብታ ብዙ እናወራ ነበር፡፡ በተለይም ብዙ የሥራ ልምዴ በሰው ኃይል አስተዳደር ላይ ስለነበር በሥራው ላይ ያጋጠመውን ችግር ያወራኝና እባክሽ ደህና ጎበዝ የሚያግዘኝ ባለሙያ ፈልጊልኝ ይለኝ ነበር፡፡ ተወዳድሮ ያገኛቸውን ሽልማቶች ሲነግረኝ እጅግ እደሰታለሁ፡፡
የጡረታ መብቴን አስከብሬ ለአንድ ዓመት በእረፍት ላይ ሳለሁ አንድ ቅዳሜ ቀን ለጥቅምት መድኃኔ ዓለም ክብር ከታናሽ እህቴ ጋር በጧት ተነስተን በሎንቺና ተሳፍረን ወደ ደብረ ሊባኖስ እሄድን ስልኬ ጮኸ፡፡ አነሳሁት፡፡ መሲ ነበረች፡፡
“ሀሎ” ስላት
“ተኑዬ ደህና ነሽ?” አለችኝ፡፡ ደንገጥ ብዬ
“እኔ ደህና ነኝ አንቺ በደህና ነው በዚህ ሰዓት የምትደውይው?”
“አንቺ ምን አለብሽ ሥራ በቃኝ ብለሽ እቤትሽ ተቀምጠሻል፡፡ እኛ ወደ ቢሮ እሄድን ነው፡፡ ለማንኛውም ክብርዬ ይፈልግሻል፡፡ “ሰኞ ጧት በበርሽ ሳልፍ አብረን እንሄዳለን፡፡ እፈልግሻለሁ እንድትጠብቂኝ” ብሎሻል፡፡ አለችኝ፡፡
“እሺ” ብያት ስልኩ ተዘጋ፡፡
ሰኞ በጧት ተያይዘን 22 ማዞሪያ ወደነበረው የጠብታ ቢሮ ሄድን፡፡ አንዲት ትንሽ ክፍል ውስጥ ሁለት አነስተኛ ጠረጴዛና ሁለት ወንበሮች ባለቡት “በይ ከዛሬ ጀምሮ እዚህ ትቀመጫለሽ የአስተዳደር ኃላፊ ሆነሽ ትሠሪያለሽ፡፡ እኔ ሥራ ማቆምሽን መቼ ሰማሁ እዚህ ስንት ሥራ አለብን አለኝ፡፡” ክብርዬን በጠብታ ጉዳይ እንዴት ላግዘው እንደምችል ሁሌም በውስጤ አሰላስል ስለነበር በደስታ ትዕዛዙን ተቀብዬ ያለኝን ልምድን ዕውቀት ለጠብታ ለማዋል ለራሴ ቃል ገብቼ ሥራ ጀመርኩ፡፡ ይህ የሆነው ከዛሬ 10 ዓመታት በፊት ነበር፡፡ ዛሬም እዚያው አለሁ፡፡
ክብርዬ ሰው ወዳድና ሰው አክባሪ ነው፡፡ አዲስ ሠራተኛ ተቀጥሮ ቢሮ እያዞርኩ ሳስተዋውቅ ቢሮውን ከፍቼ ገብቼ ሥራ እንዳላስፈታው “እሱ የጠብታ ዋና ሥራ አስኪያጅና መሥራች ነው አሁን ሥራ ላይ ነው ሌላ ጊዜ በደንብ ትተዋወቁታላችሁ ስለጠብታ በደንብ ያወራላችኋል::” ብዬ ስወጣ ከተቀመጠበት ተነስቶ በፍቅርና በፈገግታ እጁን ዘርግቶ እየጨበጠ “ክብረት እባላለሁ ፡፡ እንኳን ደህና መጣህ/ሽ” ብሎ ሲተዋወቃቸው ስመለከት ለሰው ያለውን አክብሮትና ትህትና አደንቅለታለሁ፡፡
እንደ አለቃዬ ባከብረውም ሲሳሳት እንደ ልጅ እቆጣዋለሁ፡፡ “እሺ ተኑ” ከማለት ሌላ አይመልስልኝም፡፡ ሌላ ጊዜ ምክንያቱን ያስረዳኛል፡፡ ክብርዬ ሲበዛ ደግ ነው፡፡ ቸገረኝ ያለውን ሁሉ አያልፍም፡፡ ሰው ሲደሰት ማየት ያስደስተዋል፡፡ ሁሌ ቢደገስ፣ ሁሌ ቢበላ ደስታው ነው፡፡ ለዚህ መሲም ተባባሪ ናት፡፡ ባልና ሚስት ከአንድ ወንዝ ይቀዳል እንደሚባለው፡፡
ከምንም በላይ የሕይወት ማዳን ሙያውን እንደነፍሱ ይወደዋል፡፡ የነፍሱ ጥሪ ስለሆነም ብዙ ተፈትኖበታል፡፡ ለሚያጋጥመው ችግር እስከጫፍ ሄዶ ያለውን አማራጭ ሁሉ ተጠቅሞ መፍትሔ ይፈልጋል እንጂ ተስፋ አይቆርጥም፡፡ ሁሌም የሚያልመው ስኬትን መልካም ነገርን ብቻ ነው፡፡ ያመነበትን ለማድረግ ደፋር ነው፡፡ ማህበራዊ ተሳትፎውና መሠረቱ በጣም ሰፊ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ አውቆ እንዳላወቀ የሚያልፍበት ትዕግስተኛነቱ በእኔ ግምት ልክ ያልፍብኝና ያናድደኛል፡፡
ደስ የሚለው ነገር የሚጎዳውን ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ባልታሰበ መንገድ ከአጠገቡ ያርቅለታል፡፡ አዲስ ነገር ለመሥራትና ለመጀመር አስቦ ሲያማክረኝ “ተው ክብርዬ አስር ድስት በአንድ ጊዜ አትጣድ” ስለው “አንቺ ስለምትፈሪ እኮ ነው፡፡ እኔ ሥራ ፈጣሪ ነኝ አልፈራም” ይለኛል፡፡ በቅንነት ከልቡ የሚሠራው ሁሉ ይሳካለታል፡፡ በሕይወቴ ካሳለፍኳው የሥራ ዘመናት ሁሉ ከክብርዬ ጋር ለጠብታ እንደሠራሁባቸው ዓመታት የሚያስደስተኝ የለም፡፡
@@@@@@@@@
#የአቶ ዘሪሁን መኮንን ምስክርነት
ክብረትን ሳውቀው!
እንደ መነሻ
በአስኮ ሊዝ መንደር ነዋሪዎች ማህበር በአባልነት ተደራጅተን የመኖሪያ ቤት በመሥራታችን የመነሻ መተዋወቂያችን ሆኗል።
የዚህ ኅብረተሰብ ነዋሪ በአዲስ መንደር በመክተሙ ለመተዋወቅና ለአብሮነት ሁኔታዎች በመመቻቸታቸው ከ 600 በላይ አባዎራዎች ተሳስበን እንኖራለን ።
አብዛኛው ነዋሪ በእድር አባልነት የሚቀራረብ ሲሆን ሌሎች ደግሞ በጤና ስፖርት ክበብ በመሰባሰብ አብሮነታችን ጠንካራ እንዲሆን አግዞናል ።
እንግዲህ ለእኔና ለክብረትም ሆነ ለሌሎቹ ጓደኞቻችን ዋናው የመቀራረብያ መንገዳችን ከዚህ ይጀምራል ።
የጤና ቡድኑ ከ 50 በላይ አባላቱን በ4 ቡድኖች በመክፈል ዓመታዊ የእግር ኳስ ውድድር ስለሚያካሂድ ፉክክሩና ቅርርቡ የበለጠ አስተዋውቆናል ።
ክብረቴን ያቀፈው የዳቸና ቡድን የዘመኑን ዋንጫ በማሸነፉ ለተጫዋቾቹ የስፖርት ቱታ ከኮፍያ ጋር በራሱ ወጪ ገዝቶ በመሸለም ውድድሩን ከፍ አደረገው።በዚህም ምክንያት ቅን አሳቢነቱን በመረዳት ቀረብኩት።
ክብረት የጠብታ አምቡላንስን አገልግሎት ሲወጥን ቤቱን ሽጦ
እንደሆነ ሲናገር አልጋ በአልጋ የሆነ አጋጣሚ ተፈጥሮለት እንዳልሆነ ለማንም ግልጽ ነው።የመኪና አደጋ ሲከሰት የትራፊክ ፖሊሶች ተጎጂውን አፋፍሰው የሚወስዱበትን ሂደት ለመቀነስ ብሎም ለማስቀረተ ስልጠናን መሠረት ያደረገ የመነሻ ሀሳብ የአምቡላንስ አገልግሎት መስጠት አስችሎታል።ይህን ኩነት ለማሟላት አጋጣሚን በእልህ በመጋፈጥ እንዳሳካው በቅርብ ሆኜ ተገንዝቤአለሁ ።
ክብረት በዚህ ጅማሬ ረክቶ አልተቀመጠም ።በጥረት የታገዘ
እቅዱን ተዛማጅ በሆኑ ክንውኖች
ለመቀጠል ተንቀሳቅሷል። ከወጣቶች ተሳትፎ ጋር የአምቡላንሱን ሥራ ለማቀናጀት የፓራሜድክስ ሥልጠና በመስጠት ባለሙያዎችን ለሀገር
እንዲጠቅሙ የማስመረቅ ሥራውን ተያይዞታል ።
የመዳረሻ ግብ
ክብረት አቤቤ ጠብታ አምቡላንስን ብቻ በማደራጀት የሚረካ አልሆነም።ወጣቶችን በሥራ ፈጠራ መስክ ለማነቃቃት ማህበር በማደራጀትና መሰል አስተሳሰብ ካላቸው ጋር በመጣመር የመሪነቱን ቦታ በመያዝ በመንግስት ዘንድ የኢንተርፕርነርሽፕ ሀሳብ ተቀባይነት እንዲያገኝ የጣሩት ጥረት ተሳክቶ እነሆ በህግ እስከመጽደቅ ደርሷል።
የዚህ የኢንተርፕርነር አስተሳሰብ ከሀገር አልፎ በአፍሪካ ውስጥ አሸናፊነትን ለኢትዮጵያችን አጎናጽፏታል።
ክብረቴ በአገር አቀፍና በዓለም አቀፍ መድረኮች ተሳትፎውን በማስፋት በ አዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት በቦርድ አባልነትና በሮታሪ ክለብ መድረክም አንዱ የአገር ተጠሪ በመሆን በቅርቡ ወዳጅ ጓደኛና ቤተሰብ በተገኙበት መድረክ የፕሬዚዲየም ኃለፊነቱን ለመረከብ ችሏል።
በዚህ የተደራረበ ጥረት በተገኘው ውጤት ሳይረካ ለበለጠ ግብ ታጥቆ በመሥራቱ ራሱን ለዓለም አቀፍ የኢንተርፕርነርሽፕ ውድድር አብቅቶ በስዊዘርላንድ ዳቮስ ከተማ በተደረገው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ፎረም ስብሰባ ላይ አሸናፊ በመሆን ወገን እና አገሩን አኩርቷል።
የጠብታ አምቡላንስ ሥራውንም በተሟላ ስልጠና ለማከናወን እንዲቻል ባለ 12 ወለል ህንጻ በመሥራት ለቢሮና ለሥልጠና ማካሄጃ ህንፃ በማጠናቀቅ ላይ ተቃርቧል።
ኢትዮጵያንም በኩራት ሰገነት ላይ አስቀምጧታል ።
ይህን እድል መጎናፀፍ በእልህ ሳይታክቱ ከሚለፉት እንደ ክብረት አቤቤ ካሉ ሳተናዎች ውጭ ማን ያሳካዋል??!!
ክብረቴ ስላወኩህ እድለኛ ነኝ።
እንኳን ደስ ያለህ!!!
#የአቶ ይታገስ መንግስቱ ምስክርነት
ማስተዋልና ጥበብ የተሞላበት ግንኙነት ቋሚ ትስስርን ይፈጥራል ፡፡ እኔና አቶ ክብረት አበበ ግጥምጥሞሻችን ድርብርብ ነው፡፡ሁለት ተመሳሳይ ዩኒቭርስቲዎች አብረን ተምረናል፤ሁለት ድርጅቶች ተቀጥረን አብረን ሠርተናል፡፡ነገር ግን የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በደንብ እንድንተዋወቅ የጊዜዉ እርዝማኔና በአንድ ቡድን አብረን መሥራታችን ጥልቅ መተዋወቅና ስብእናችንንም እንድንረዳ ረድቶናል፡፡ አቶ ክብረት አበበ ጠብታን በመሰረቱ በሁለት ዓመት ያበራውን የቅድመ ሆስፒታል አገልግሎታችን አላማ ለማጋራት ደሞዜን 450% ቀንሼ ነበር የተቀላቀልኩት፡ ቢሮም እያደርን ሰርተናል ፈተናውን አልፈን እዚህ ደርሰናል፡፡
አቶ ክብረት አበበ በተፈጥሮ የተሰጠው የኢንተርፕርነር ችሎታውና የእኔ ደግሞ የኢንትራፕርነር ችሎታ ለጥምረታችን ትልቁ ሚስጢር ነው፡፡በ2026 አቶ ክብረት የተሸለሙት የ15 ዓመት በቅድመ ሆስፒታል ላይ የፈርቀዳጅነቱ ሚና ሀብት ለመሰብሰብ ሳይሆን ገና ጨቅላ የሆነዉን አገልግሎት ለማሻሻል ስለሆነ ከግለሰብ እስከ ሀገር አቀፍ የተሠሩ ሥራዎች ህያው ምስክሮች ናቸው፡፡ የጠብታ አምቡላንስም ያበረከተው አበርክቶ በመጽሀፍ ተሰንዶ መቀመጥ ያለበት ነዉ፡፡የዚህ ዓመት ሽልማት ደግሞ ኢትዮጲያን በዓለም መድረክ ያስጠራ ለመሆኑ ሀገራችንም ኮርታለች፡፡
አቶ ክብረት አበበ እናመሰግናለን፡፡
##@@@@@@
የመቶ አለቃ ሁነኛው ኪዳኔ ምስክርነት
የእኔና የክብረት ግንኙነት ጅማሬው በወላጆቻችን የተጀመረ ሲሆን የእኔና የእሱ ግንኙነት ከእነሱ የቀጠለ በመሆኑ ከአንድ እናት እና አባት አለመወለዳችን እንኳን ያወቅነው ካደግን እና ነፍስ ካወቅን በኋሏ ነው።ክብረት በልጅነቱ ጎበዝ የደረጃ ተማሪ፤ለትምህርቱም ትኩረት የሚሰጥ ፤ሁልጊዜም ለማወቅ የሚጥር ፤ እናት አባቱን በሥራ የሚያግዝ ታዛዥ የነበረ ሲሆን፤ ከስፖርት ዓይነቶች ደግሞ እግር ኳስን ጥሩ አድርጎ የሚጫወት ነበር።በባህሪውም ቀልደኛ ጨዋታ የሚያውቅ፤ ለሰው የሚያዝን ሩህሩህ ሲሆን ሥራ ፈጣሪ ሆኖ እዚህ ደረጃ ለመድረሱ ምክንያት የሆኑት የኮርያ ዘማቹ አባቱ ሻምበል አቤቤ ቱፋ ናቸው። አባቱ ጎበዝ የሥራ ሰው እና ሥራ ፈጣሪም ናቸው። አንድ ሥራ ብቻ የማይሠሩ የነበረ ሲሆን ዶሮ አርብተው እንቁላል ለገበያ የሚያቀርቡ፤ንቦች አንበው ማር ለገበያ የሚያቀርቡ፤ከብቶችን አርብተው ወተት እና የወተት ተዋዕፆችን ለገበያ የሚያቀርቡ፤በግቢያቸው ውስጥ የወይን ተክል ተክለው የወይን ፍሬ ለገበያ የሚያቀርቡ ጀግና የሥራ ፈጣሪ ናቸው።
ክብረትም የአባቱን ሥራ ፈጣሪነት እየተመለከተ በማደጉ ዛሬ ለእርሱ እዚህ መድረስ የአባቱ አስተዋፅኦ ትልቅ ቦታ አለው። ስለክብረት ብዙ ድንቅ ነገሮች አሉ። ብዙ ማለትም ይቻላል። እዚ ጋር ስለዳቮሱ ውድድር ላንሳ። ክብረት ብዙ ውድድሮችን በማህበራዊ ሥራ ፈጠራ ዘርፍ ተወዳድሮ ሲያሸንፍ አውቃለሁ።የዳቮሱን ግን አሸንፎ ለመውጣት ከባድ እንደነበር ነው ያጫወተኝ ምክንያቱም ውድድሩ የነበረው ከዓለም ጋር ነበር።