ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን፣ መዝገበ-አእምሮ (የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ) ፕሮጀክቱ ለአገር የሠሩ ሰዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል።
ይህ ታሪክ በዲጂታል ሚድያዎች፣ በመጽሐፍ፣ በድምፅ ትረካና በሌሎችም መንገዶች እየቀረበ እንደሆነ ይታወቃል። ባለፉት 4 ዓመታት ከ5 ወር ጊዜ ውስጥ የ423 ሰዎችን የሕይወትና የሥራ ታሪክ ለመሰነድ የቻልን ሲሆን 600 ገፅ ባላቸው ሁለት የተለያዩ መጽሐፎች ላይም ታሪኮቹ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው እንዲቀመጡ አድርገናል።
በድርሰት ዘርፍ የሕይወት ታሪካቸው ከሚሰነድላቸው መካከል ደራሲ ጌታቸው በለጠ ይጠቀሳል። ደራሲ ጌታቸው ታሪኩን ለተወዳጅ ሚድያ ፈቅዶ የሰጠ ሲሆን ፅሑፉንም ዕዝራ እጅጉ እንደሚከተለው ሰንዶታል።
ማንነት በአጭሩ
ጌታቸው በለጠ ታህሳስ 7 ቀን 1953 ዓ.ም በደብረ ማርቆስ ተወልዶ አዲስ አበባ ኮልፌ አደገ፡፡ ወደ ሥራ ከተሠማራ በኋላም በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ በኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ብሔራዊ ጽሕፈት ቤት፣ በአስቴር ነጋ አሳታሚ ድርጅት፣ በተለያዩ የኃላፊነት እርከኖች ላይ ሠርቷል፡፡ በመጨረሻም “ዮቤግ ኮሚዩኒኬሽን፣ ሚዲያና ፐብሊሺንግ ኃ.የተ.የግል ማኅበር” የተሰኘ ድርጅት ከጓደኞቹ ጋር በማቋቁም ወደ ግል ሥራ ዞሯል፡፡
የትምህርትዝግጅት
ሁለተኛ ዲግሪ፡- በድንበር ዘለል ኮሚዩኒኬሽን፣ በአሜሪካ ሀገር ሚኒሶታ ክፍለ ግዛት ከሚገኘው ከአንጋፋው ቤቴል ዩኒቨርስቲ፣ የመጀመሪያ ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ፣ በቲዮሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪ ከኢቫንጀሊካል ቲዮሎጂካል ኮሌጅ (አዲስ አበባ)፣ በሊደርሺፕ አድቫንስድ ዲፕሎማ በአሜሪካ ሐዋይ ክፍለ ግዛት ከሚገኘው ጆን ሐጋይ ኢንስቲቲዩት አግኝቷል፡፡
የንባብ ቁርኝት እና የአባት ምኞት
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በኮሜርስ የትምህርት ዘርፍ ከዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ከኮልፌ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (አዲስ አበባ) ተከታትሏል፡፡ በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ መሠረት የጣለለትን የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው አዲስ አበባ ይገኝ በነበረው የብርሃነ ዩኒቨርሳል ሥነ ጥበባት ት/ቤት እና አራት ኪሎ በሚገኘው የወጣቶች ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (ወ.ወ.ክ.ማ) ነው፡፡
ጌታቸው በለጠ የተወለደው ከመጻሕፍት ንባብ ጋር የቅርብ ትሥሥር ባለው ቤተሰብ መሐል ነው፡፡ አባቱ የጦር ሠራዊት መኮንን ሲሆኑ እናቱ ደግሞ ለዘመናዊ ትምህርት ያልታደሉ የቤት እመቤትና ልጆቻቸውን በትምህርት አንፀውና ኮትኩተው ለቁም ነገር ለማብቃት እጅግ የተጉና በአካባቢው ማኅበረሰብም ዘንድ በመልካም አርአያነት የሚጠቀሱ እናት ነበሩ፡፡
አባቱ በነበራቸው ወታደራዊ ኃላፊነት ምክንያት በሀገር ውስጥ በሚገኙባቸው ጊዜያት በተለያዩ ወታደራዊ ግዳጆች በዓመት ውስጥ ከቤተሰባቸው ጋር የሚያሳልፉት ጥቂት ቀናት ብቻ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ለወታደራዊ ሙያ ሥልጠና፣ ለሥራና ሙያዊ ለሆነ ግዳጅ በተለያዩ ውጭ ሀገራት ይጓዙ ስለነበር የቤተሰባቸውን ናፍቆት ለማለዘብ ዘዴ ብለው የያዙት ራሳቸውን ከመጻሕፍት ንባብ ጋር ማቆራኘት ነበር፡፡ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ታትመው ያነበቧቸውን መጻሕፍትና መጽሔቶችም ልጆቻቸው እንዲያነቡ ከፍተኛ ጉጉት ስለነበራቸው ያበረታቷቸው እንደነበር ታላላቆቹ ይተርኩለት ነበር፡፡
ከሦስቱ ታላላቅ እህቶቹና አንድ ወንድሙ ቀጥሎ ወንድ ልጅ እንዲወለድ ከፍተኛ ጉጉት ስለነበራቸው ገና በእናቱ ማኅፀን እንዳለ ወንድ ልጅ እንደሚወለድ ተስፋ አድርገው በጉጉት ለሚጠበቀው ለዛሬው ጌታቸው በለጠ አባቱ “ናፖሊዮን” ብለው ስም ያወጡለት ገና ይህንን ዓለም ሳይተዋወቅ ነበር፡፡
ይህም ብቻ አይደለም ገና ላልተወለደ ልጃቸው አንድ የሰነድ ማስቀመጫ አቃፊ በማዘጋጀትም “ለልጄ ለናፖሊዮን” እያሉ ከመጽሔቶችና ከጋዜጦች ላይ የሚያገኟቸውን ጠቃሚ ጽሑፎችን እየቆረጡ ፋይል በማድረግ ያስቀምጡለት ነበር፡፡ “ይሄው በጉጉትና በተስፋ የሚጠበቀው ወንድ ልጅ ‹ናፖሊዮን› አድጎ ነፍስ ሲያውቅ “ጽሑፎቹን እንድታስረክቢልኝ” በማለት ለእናቱ አደራ ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ “ናፖሊዮን ሲያድግ ጋዜጠኛ ወይንም ደራሲ እንዲሆንም” ምኞታቸውን በማስታወሻ ጽሑፍ ማኖር ብቻም ሳይሆን አዘውትረው ለልጆቻቸውና ለእናቱ ይነግሯቸው ነበር፡፡ እናቱም የአባቱን አደራ በጥንቃቄ ጠብቀው በማኖር እንደተመኙትም ጌታቸው ነፍስ እንዳወቀ በአንድ አረንጓዴ ክላሴር ውስጥ የተከማቹ በውጭ ሀገራትና በሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ተጽፈው የታተሙ ቁርጥራጮች ጽሑፎችን አስረክበውታል፡፡
ከጽሑፎቹ በተጨማሪም “አባትህ ጋዜጠኛ ወይም ደራሲ እንድትሆንለት በጽኑ ይፈልግ ነበር፡፡ ወታደር ቢሆንልኝ እያለም ምኞቱን ሲገልጽ ነበር” በማለት ከአባቱ የተረከቡትን አደራ በውስጡ እንዲሰርፅ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ ስሙን ግን አባቱ እንደተመኙለት ‹‹ናፖሊዮን›› ሳይሆን እንደራሳቸው ስሜትና ፍላጎት ‹‹በሴቶች መካከል መገኘቱን በማስታወስ ጌታቸው የሚለውን ስም በማውጣት አጸኑለት፡፡
የልጃቸውን መጨረሻ ለማየት ይጓጉ የነበሩት አባቱ በወታደራዊ ግዳጅ ላይ እያሉ ገና በልጅነት ዕድሜው ከበርካታ መኮንኖች ጋር በመስዋዕትነት ስላለፉ የአባትነት ምክራቸውንና “ለልጄ” ይሉ የነበረውን መልካም ምኞታቸውን ለማገናዘብ፣ አደራቸውን ለመቀበልና ምክራቸውን ለማድመጥ ጨቅላ ዕድሜው አልፈቀደለትም ነበር፡፡ ዛሬ በሕይወት የሌለው የሦስት ጊዜ ታላቅ ወንድሙ ግርማ በለጠ አባቱ ለልጆቻቸው የተመኙላቸውን ምክርና ጉጉት ተግባራዊ በማድረግ ከመጻሕፍት ንባብ ጋር ሕይወቱን በማቆራኘቱ ጥሩ አንባቢ፣ ጥሩ ገጣሚ፣ ጥሩ የቴአትር ደራሲና ተዋናይ በመሆን በትምህርት ቤቱና በአደገበት ኮልፌ አካባቢ የተዋጣለት የጥበብ ሰው ለመባል በቅቷል፡፡ በዘመኑ “ግርማ በለጠ” የሚለው ስም በአደጉበት አካባቢ በኮልፌ በስፋት ይታወቅ ነበር፡፡ በየጊዜውም መጻሕፍት የመግዛት ልማድም ነበረው፡፡
ጌታቸው ንባብን ወደደ ወደ ፅሑፍም ተሳበ
ጌታቸው የከበደ ሚካኤልን የ”ታሪክና ምሳሌ” መጻሕፍት፣ የያሬድ ገብረ ሚካኤልን “የእንስሳት አገልግሎት”፣ የጃለታ ጃፈሮንና የገብሬ ወዳጆን መጻሕፍት ያነበባቸውና አብዛኞቹን በቃሉ ሸምድዶ ያንበለብላቸው የነበረው ገና መደበኛ ትምህርት ቤት ሳይገባ ነበር፡፡ ቄስ ትምህርት ቤት ገብቶ እጅግም ሳይቆይ “ብርሃነ ዩኒቨርሳል ሥነ ጥበባት” በሚባል መደበኛ ትምህርት ቤት 2ኛ ክፍል ገባ፡፡
የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች እንደየፍላጎታቸው በልዩ ልዩ ክበባት ውስጥ ሲደለደሉ፣ እሱም ከእናቱ የተረከበው የአባቱ ምክር ነፍስ ዘርቶበት ተሽቀዳድሞ የትምህርት ቤቱ ጋዜጠኛ መሆን እንደሚፈልግ ገለፀ፡፡ ይህንን ፍላጎቱን የተረዱት የትምህርት ቤት ባለቤትና ዲሬክተር አቶ ጌታቸው ደምሴ ለፍላጎቱ ተፈጻሚነት ያሳዩት ቀናነት በእጅጉ ይገርመዋል፡፡ ለ2 ዓመት ብቻ በተማረበት በዚያ ትምህርት ቤት ውስጥ የተዘራበት የጋዜጠኛነት ሙያ ሳይሆን የግጥም መጻፍ ችሎታም ጭምር ነበር፡፡
ይህንን የገጣሚነት ችሎታ ሊያገኝ የቻለው ግን በአንድ አስገራሚ አጋጣሚ ነበር፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው፡- የ2ኛ ክፍል ተማሪና የትምህርት ቤቱ “ታዋቂ” ጋዜጠኛ በነበረበት አንድ ዕለት በትምህርት ቤታቸው ውስጥ የግጥም ውድድር እንደሚደረግ ማስታወቂያ ተነገረ፡፡ በውድድሩ ለማሸነፍ ከፍተኛ ጉጉት ስላደረበት ከአባቱ እኩል የሚያከብረውንና የሚያደንቀውን ታላቅ ወንድሙን ግርማ በለጠን ለውድድሩ በተሰጠው ሐሳብ መሠረት “የበሬ አገልግሎት” በሚል ርዕስ ግጥም እንዲጽፍለት አጥብቆ ለመነው፡፡
ግጥሙ ለውድድር የሚቀርብ መሆኑን ግን አልገለጸለትም፡፡ ወንድሙ ጥያቄውን ተቀብሎ ድንቅ ግጥም ጽፎ ሰጠው፡፡ ጌታቸው፣ የራሱ ሥራ ለማስመሰል በራሱ የእጅ ጽሑፍ ገልብጦ ለውድድር አቀረበ፡፡ ግጥሙም በከፍተኛ አድናቆት ተመርጦ በጠዋቱ የሠልፍ ሥነ ሥርዓት ላይ ለተማሪዎች እንዲያነበው ተወሰነ፡፡ በጓደኞቹ ጭብጨባ ታጅቦ ንባቡን ጨርሶ ወደ ሠልፉ ሲያመራ ከተማሪዎቹ መሐል አንድ ተማሪ “ውሸቱን ነው…! የእሱ ግጥም አይደለም…! ወንድሙ ነው የጻፈለት…!” ብሎ እሪታውን አቀለጠ፡፡ ነገሩ በዚሁ አላበቃም፡፡ “ወንድሙ የጻፈው ግጥም ደብተሩ ውስጥ ሊገኝ ስለሚችል ይፈተሽ” በማለት ያ ሞገደኛ ጓደኛው አቤቱታውን አጠናከረ፡፡
እውነትም ጌታቸው ወንድሙ የጻፈለትን ግጥም በራሱ የእጅ ጽሑፍ ሲገለብጥ ይኸ ሞጋች ጓደኛው አይቶት ኖሯል፡፡ የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ደምሴም የዚህኑ ልጅ ክስ አድምጠው የጌታቸው ደብተር በሙሉ በተማሪዎች ፊት ተዘርግፎ እንዲፈተሽ አዘዙ፡፡ አምላክ ከውርደት ሲታደገው ደብተሩ ውስጥ ወሽቆት የነበረው የወንድሙ ጽሑፍ አልተገኘም፡፡ ጓደኛው እንደ “ቀናተኛና ውሸታም”፤ እሱ ደግሞ እንደ “ጀግና” ተቆጥሮ አሳዛኙ የቅሌት ቴአትር በዚሁ ተደምድሞ ጌታቸው በጓደኞቹ ዘንድ የ“ዝነኛ ገጣሚ”ነትን ስም ተጎናፀፈ፡፡ ያንን ሐፍረቱን ለመሸፈን ሲልም ሥራው ቀንና ሌሊት ግጥም መጻፍ ሆነና ወደ ትክክለኛው ጎዳና ለመግባት ቻለ፡፡ ዛሬ ምሥጋናው ለዚያ “አጋላጭ ጓደኛዬ ይድረስልኝ” በማለት በጸጸት ይናገራል፡፡ ይህንን ምስክርነት የመሰከረው “የትዝታዬ ማኅደር” በሚል ርዕስ ያሳተመው ግለ ታሪኩ በተመረቀበት ዕለት የልጅነት መምህሩን አቶ ጌታቸው ደምሴን ፊት ለፊት አስቀምጦ ሚያዝያ 5 ቀን 2018 ዓ.ም ነበር፡፡
በዚህ አጋጣሚ በውስጡ ያለውን ተሰጥዖ ማውጣት ከቻለ በኋላ በየተማረባቸው ትምህርት ቤቶች ወይ የትምህርት ቤቱ ጋዜጠኛ፣ አለያም በሥነ ጽሑፍ ክበብ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የአባቱን አደራ ለማሳካት ጥረቱን ቀጠለ፡፡ በተለይም በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ሲማር፣ የሰባተኛና የስምንተኛ ክፍል የአማርኛ መምህሩ የነበሩት መምህር ሰውነት ጥበቡ፣ የትምህርት ቤቱ “ዝነኛ ገጣሚ” ተብሎ ከፍ ያለ ሽልማትና ክብር እንዲጎናፀፍ ያደረጉለትን እገዛ እና ክትትል የማይረሳው ውለታ እንደሆነ ይናገራል፡፡ እኚህን መምህሩንም መጽሐፉ በተመረቀበት ዕለት የክብር እንግዳ አድርጎ በእንግዶቹ ፊት አመስግኗቸዋል፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ ለሳይንስ ትምህርት በጭራሽ ፍላጎት አልነበረውም፡፡ ምርጫው የቴክኒክ፣ አለያም የንግድ ሥራ ዘርፍ ቢሆን ይመርጥ ነበር፡፡ ከፊዚክስና ከኬሚስትሪ ትምህርት ለመሸሽ ስለፈለገም የንግድ ሥራን ለመማር ተገደደ፡፡ ሆኖም በውስጡ ሥር የሰደደው የሥነ ጽሑፍ ፍላጎት ትክክለኛ ቦታውን ያገኘው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በገባ ጊዜ ነበር፡፡
ጌታቸው በለጠ በዩኒቨርስቲ
የመጀመሪያ ዓመት የመሰናዶ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ለቀጣዮቹ ክፍሎች በዋና የሙያ ዘርፍ (Major Discipline) ለሁሉም ተማሪዎች ለምርጫ የቀረቡላቸው 14 ያህል የትምህርት ዘርፎች ነበሩ፡፡ የእሱ ፍላጎት ቀድሞውንም የተወሰነ ስለነበር የምርጫውን ቅፅ ከመሙላቱ አስቀድሞ በቀጥታ ያመራው ወደ ኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍል ነበር፡፡ በወቅቱ የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ የነበሩት መምህር ይልማ ከበደ ምርጫው እርሳቸው የሚመሩት ክፍል መሆኑን ሲገልጽላቸው ከደስታቸው ብዛት የተነሳ ቆመው እንደጨበጡትና በየመምህራኑ ቢሮ ወስደውም ከመምህራኑ ጋር እንዳስተዋወቁት ያስታውሳል፡፡
ከመምህራኑ መካከልም አቶ ደበበ ሰይፉ፣ ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ፣ አቶ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው፣ አቶ መስፍን ሀብተ ማርያም እና ሌሎቹም የተቀበሉት ከማበረታቻ ቃል ጋር በትልቅ ደስታ ነበር፡፡ በዚያ ዓመት በዚህ የትምህርት ዘርፍ ብዙ ተማሪዎች ያለውዴታቸው በመመደባቸው ደስተኛ አልነበሩም፡፡ ከፊሎቹ ከመመዝገባቸው በፊት፣ ከፊሎቹም ከተመዘገቡ በኋላ “ለአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ጊዜአችንን አናጠፋም” እያሉ ትምህርቱን አቋርጠዋል፡፡
ጌታቸው ግን በዚያ የትምህርት ክፍል በፈቃደኛነት መመዝገቡ ለብዙዎች መምህራን ደስታ የፈጠረው በዚሁ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም ብሎ ይገምታል፡፡
#አስደንጋጩአጋጣሚ
በ1976 ዓ.ም የ4ኛ ዓመት ተማሪ በነበረበት ጊዜ በፅኑ ከሚያፈቅረው የሥነ ጽሑፍ ሙያ ጋር የተያያዘ አንድ አስደንጋጭ አጋጣሚ ተፈጥሮበት ነበር፡፡ ጉዳዩ እንዲህ ነው፡- በ‹‹ቋንቋዎች ጥናት ኢንስቲትዩት›› ይገኙ የነበሩ የአራት የትምህርት ዘርፍ (የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ፣ የእንግሊዘኛ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ፣ የሥነ ልሳን እና የቴአትር ጥበባት) ዲፓርትመንት ተመራቂ ተማሪዎች በጋራ አንድ የመመረቂያ መጽሔት ለማሳተም ተስማምተው ሥራውን ይጀምራሉ፡፡ የምረቃ ማስታወሻ መጽሔት ማዘጋጀት በወቅቱ እጅግም የተለመደ ስላልነበረ በመጽሔቱ ላይ የሚወጡትን ጽሑፎች ማሰባሰቡና የማሳተሚያ ገንዘቡን ማፈላለጉ በኮሚቴ ውስጥ ለነበሩት አባላት ቀላል ተግዳሮት አልነበረም፡፡
የሆነው ሆኖ ጽሑፎቹ እንደምንም ተሰባስበው ከኅትመት በፊት ወደ ሳንሱር ክፍል ለምርመራ ይላካሉ፡፡ በዚያን ጊዜ እንኳንስ መጽሔትና መጻሕፍትን ያህል ከፍ ከፍ ያሉ የኅትመት ውጤቶችን ቀርቶ ከእነዚህ ያነሱት ጽሑፎች ለምሳሌ፡- የስምና የማዕረግ ገላጭ ቲተርና ካርድ፣ የሠርግና የአርባ ቀን መታሰቢያ መጥሪያዎች የመሳሰሉት የኅትመት ውጤቶችም ሳይቀሩ ከሳንሱር ክፍል ፈቃድ ካልተገኘ በስተቀር ሊታተሙ አይችሉም ነበር፡፡ ወደ ሳንሱር ክፍል ከተላኩት የመጽሔቱ ጽሑፎች መሐል “ሺህ ውበት” በሚል ርዕስ ጌታቸው የጻፈው አንድ ግጥም ነበረበት፡፡
የግጥሙ ቅርፅ የተራኪነት ባሕርይ ያለው ሆኖ በአንድ ታዳጊ ወጣትና በአያቱ መካከል የተደረገ ውይይት መሰል ይዘት ነበረው፡፡ ከሳንሱር ክፍሉ ጋር ያላተመውና ያስደነገጠው የ“ሺህ ውበት” ግጥም ይዘት በአጭሩ የሚከተለውን ይመስል ነበር፡፡ አንድ አዘውንት አባት መደብ ላይ ጋደም እንዳሉ የልጃቸው ልጅ የሆነ አንድ ታዳጊ ከመደቡ ጠርዝ ላይ አረፍ ብሎ የራስ ፀጉራቸውን በፍቅር በሚያሻሽበት ወቅት የአንደኛው ጣቱ ጥፍር ስንጥቅ ኖሮ ድንገት እጁን ከፍ ሲያደርግ 5 ያህል የአያቱ ሽበቶች በስንጥቅ ጥፍሩ ውስጥ ገብተው ይነቀላሉ፡፡
ሽማግሌውም ታዳጊውን ልጅ “አ! አ! ሽበቴን ነቀልክ እኮ?” ብለው ይገስጹታል፡፡ ወጣቱም ይቅርታ በመጠየቅ “አራት ሽበት፣ አምስት ሽበት! ምን ይጎዳል በሚዶስ ይረግፍ የለ ስታበጥረው ለማማር” በማለት ይመልስላቸዋል፡፡ እሳቸውም “እኒህ አምስት ሽበቶች ሽበት ብቻ ሳይሆኑ ሺህ ውበትም ናቸው፡፡ ትናንትን ማስታወሻ ፎቶግራፎቼም ቅርሴም ናቸው፡፡ የሽበት ሽበት እማ እንጨትም እኮ ሽበት አለው እሳት ወደ እርሱ ሲጠጋ አላስጣለውም እንጂ፡፡” ብለው ይመልሱለታል፡፡ ልጁም “አያቴ ለስንፍናዬ ይቅር በለኝ! የእኔስ ጥቁር ዞማ ፀጉር ለሀገር በሚጠቅም ተግባር ይነጣ ይሆን ወይንስ እንደ ጠቆረ ወደ መቃብር ይወርዳል፡፡” በማለት ይጸጸትና ይቆጫል፡፡ ይህ ነበር የግጥሙ ይዘት፡፡ ያለመታደል ሆኖ ግን “ፀጉር እንዲሰነጥቁ” ከፍ ያለ ሥልጣን በተሰጣቸው የወቅቱ የሳንሱር ኃላፊዎች ግጥሙ በደግ አልተተረጎመም ነበር፡፡
በመሆኑም ለዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት በተሰጠ ቀጭን የስልክ ትዕዛዝ መሠረት ጌታቸውና የቋንቋዎች ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዲን የነበሩት ዶክተር ደጀኔ ለታ በአስቸኳይ አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት አጠገብ ወደሚገኘው የሳንሱር ጽሕፈት ቤት ተጠርተው ሄዱ፡፡ ከሳንሱር ኃላፊው ዘንድ እንደቀረቡም ጌታቸውን በስድብ ውርጅብኝ ብቻ አልተውትም “መንግሥትን የሚቀናቀኑ አደገኛ” ተብለው ከተፈረጁ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ውስጥ አንዱ ተደርጎ ክትትል እንደሚደረግበት ገለጹለት፡፡ በክፉ ዐይን የሚታዩ ጸሐፊዎች ከሚመዘገቡበት “ጥቁር መዝገብ ውስጥም ስሙ እንደሚመዘገብ” የተወሰነ መሆኑን አረዱት፡፡ ረዳት ዲኑን ዶ/ር ደጀኔ ለታንም እንዲሁ በንዝህላልነት ወቀሷቸው፡፡
የሳንሱር መ/ቤቱ ዋና የክስ ምክንያት በወቅቱ የሀገሪቱ የፖለቲካ ሥልጣን ውስጥ “ጋንግ ኦፍ ፎር” የሚባሉ አራት ሰዎች ያሉበት የምሁራን አንጃ በደርግ ውስጥ ተፈጥሯል እየተባለ ይታማ ነበር፡፡ በእነዚህ “ጋንግ ኦፍ ፎር” እና በመለዮ ለባሽ የደርግ አባላት መካከል የጎሪጥ መተያየት መከሰቱ በስፋት ይወራ ነበር፡፡ በተነቀሉት የሽማግሌው ሽበቶች አስመስሎ “አራቱ ጋንግ ኦፍ ፎር እና ፕሬዚዳንት መንግስቱ ተነቅለው ይወገዱ” የሚል መልዕክት ግጥሙ እንዳስተላለፈ በመተርጎሙ ነበር፡፡ አራቱ “ጋንግ ኦፍ ፎር” ተብለው የተፈረጁት የወቅቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጓድ ፋሲካ ሲደልል፣ ጓድ ዶ/ር ዓለሙ አበበ፣ ጓድ ሽመልስ ማዘንጊያና ጓድ ሸዋንዳኝ በለጠ ነበሩ፡፡ በአምስተኛነት ደግሞ አብረው ይነቀሉ ተብሎ በግጥሙ ውስጥ የተመሳጠረው ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ነው” የሚል ክስ ነበር፡፡
ለማንኛውም ዶ/ር ደጀኔ ለታ ባደረጉት ከፍ ያለ የርኅራኄ ተማፅኖ ግጥሙ ውስጥ የተጠቀሱት “አምስት ሽበቶች” ብዛታቸው ከ5 በላይ እንዲሆኑና አንዳንድ ቃላትም እንዲለዝቡ ትዕዛዝ ተሰጥቶ በመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ነገሩ ረግቦ “ሺህ ውበት” የሚለው ግጥም ነፃ ሊወጣ ችሏል፡፡ ይሄው መዘዘኛ ግጥም “ስሞተኛው” በሚለው የጌታቸው የመጀመሪያ መጽሐፍ ውስጥ ታትሟል፡፡
“እባብ ያ’ዬ በልጥ በረዬ” እንዲሉ ያን መሰል ክፉ ገጠመኝ ዳግመኛ እንዳይከሰት በመስጋት ጌታቸው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተመርቆ ሥራ ላይ እንደተመደበ “ማንነቴን ይደብቅልኝ እንደሆን” ብሎ በማሰብ በብዕር ስም መጠቀም ጀመረ፡፡ ስለዚህ በወቅቱ በብዙ የጋዜጣ አንባቢያንና የሬዲዮ ፕሮግራም ተከታታዮች ዘንድ ጥሩ ተቀባይነት አግኝቶ በነበረው “ዳግላስ ጴጥሮስ“፣ “ዳኘው”፣ “መኃልይ” በሚሉ ሦስት የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በሚጠቀምባቸው የብዕር ስሞቹ አማካይነት ከሌሎች ታላላቆቹና የሚያከብራቸው ብዕረኞች ጎራ ለብዕር ፍልሚያ ተሰለፈ፡፡
ደራሲው መፅሐፍ አሳተመ
ዳግላስ ጴጥሮስ በሚለው የብዕር ስሙ የመጀመሪያውን የአጫጭር ልብ ወለዶችና የግጥም መድበል መጽሐፉን “ስሞተኛው” በሚል ርዕስ አሳተመ፡፡ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ጽሑፎችንም ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር አንባቢዎች አቀረበ፡፡ “ዳግላስ ጴጥሮስ” በሚለው የብዕር ስም ከ1977 – 2017 ዓ.ም በአዲስ ዘመን፤ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ በየካቲት መጽሔት፣ በኢትዮጵያ ሬዲዮ “የእሁድ ፕሮግራም” እና በኋላም “በአዲስ አድማስ ጋዜጣ” ላይ፣ እንዲሁም በውጭ ሀገር በትምህርት ላይ በነበረባቸው ዓመታት “መስታወት” በሚል ርዕስ ይታተም በነበረ የኢትዮጵያውያን መጽሔት ላይ ቁጥራቸው በሺህ የሚቆጠር ሥነ ጽሑፋዊና ማኅበራዊ ሂስ ላይ ያተኮሩ ርዕሰ ጉዳዮችን ለአንባብያን አበርክቷል፡፡
“መኃልይ” በሚለው የብዕር ስሙ ደግሞ በዋና አዘጋጅነት ባገለገለበት “የቃለ ሕይወት መጽሔት” ላይ በርካታ አርቲክሎችን አስነብቧል፡፡ ከመደበኛ ስሙ ይልቅ ዕውቅናን ባተረፈለት ዳግላስ ጴጥሮስ በሚለው የብዕር ስሙ በተለያዩ የኅትመት ውጤቶች ላይ ለ39 ዓመታት ያህል መደበኛ ሙያው ጋዜጠኛ ሳይሆን በግል ተነሳሽነት ሐሳቡን ሲገልጽ መኖሩ ምናልባትም የአባቱን “ትንቢት” በጽናት ለመፈጸም መጨከኑ ሳይሆን እንዳልቀረ ይገመታል፤ “ልጄ ናፖሊዮን ጋዜጠኛና ደራሲ እንዲሆን እመኛለሁ” የሚለውን አባታዊ የቃል አደራ ለማስፈጸም፡፡
በወቅቱ በአዲስ ዘመንና በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦች፣ በብዕር ስም ይፋለሙ ከነበሩት ከነአሸናፊ ዘደቡብ አዲስ አበባ፣ ዳንዴው ሰርቤሎ፣ ተርቡ፣ መድፉ፣ አፈሊቅ አክሊሉ፣ ባጎር፣ መርቆሪዎስ፣ ጎርጎሪዮስ፣ ዝማሙ ሊበን፣ ማኅተመ ጌጡ ወዘተ…. ከመሳሰሉት ታላላቅ ጸሐፍት ጋር ይደረግ የነበረው ሙያ ነክ የሂስ ጦርነት የወቅቱን መንግሥት በከፍተኛ ሁኔታ ሳያሳስበው አልቀረም፡፡
ተጽእኖ ፈጣሪ ናቸው የተባሉ የተወሰኑ የብዕር ተሟጋቾች ወደ ኢሠፓ ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት ተጠርተው ከፍተኛ ግሳፄ ደርሶባቸዋል፡፡ ጌታቸውም ለሁለተኛ ጊዜ በወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር በነበሩት በዶክተር ኮሎኔል ፈለቀ ገድለ ጊዮርጊስ ጠቋሚነት “ስማቸውን እየለዋወጡ በመጻፍ ሕዝቡን ግራ እያጋቡ ነው” በማለት ከተወነጀሉት አንዱና ዋነኛው ነበር፡፡ ለተወሰነ ጊዜ ከሥራ አካባቢ ዞር ብሎ እንዲቆይና ለጊዜው ማንኛውንም ጽሑፍ እንዳይጽፍ ከገጣሚ ሻለቃ ክፍሌ አቦቸርና ከደራሲ ሻለቃ ዓባይነህ አበራ በተሰጠው የጓደኝነት ምክር ከአደጋ መሹለኩንም ያስታውሳል፡፡
መንትዮች
ሌላውና በሦስተኛነት ከፍ ያለ ችግር ያስከተለበት “መንትዮች” በሚል ርዕስ ያሳተመው 2ኛው መጽሐፉ ነበር፡፡ ይህንን መጽሐፍ በ1982 ዓ.ም በ15,000 ቅጂ ያሳተመው የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ባልደረባ እያለ ነበር፡፡ መጽሐፉን ያሳተመው ከተቋሙ የቁጠባና ብድር ማኅበር ብር 9,000 (ዘጠኝ ሺህ ብር) ተበድሮና በአጭር ጊዜ ውስጥ ሸጦ ብድሩን ለመመልስ ቃል ገብቶ ነበር፡፡ ሆኖም መጽሐፉ ታትሞ እንደተረከበ ከፊሉን በግሉ፣ በርከት ያለውን ቁጥር ደግሞ ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት እንዲያሰራጭለት የውል ግዴታ ተፈራርሞ በአደራ ሽያጭ አስረከበ፡፡ ይህ ከሆነ ከጥቂት ቀናት በኋላ እሱና የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት የቁጠባ ማኅበር ሊቀ መንበር የነበሩት አቶ ዳምጠው መላኩ ወደ አዲስ አበባ ኢሠፓ ጽሕፈት ቤት ተጠሩ፡፡ ከዚያም የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በሰይጣናዊ ቁጣ እየተንቀጠቀጡ “ወዛደሩ ለችግሬ” ብሎ ያጠራቀመውን ገንዘብ እንደምን ለተረት ተረት መጽሐፍ ማሳተሚያ ለመበደር እንደ ደፈርክና ሊቀ መንበሩም እንዴትና በምን አግባብ ብድሩን እንደፈቀደ ማብራሪያ ስጡ ተብለው ተጠየቁ፡፡
ሁለቱም ጉዳዩን በትህትና ቢያስረዱም ኃላፊው ግን ምክንያታቸውን በቀና ልቦና ሊረዱ አልፈቀዱም፡፡ ስለሆነም ገንዘቡን በሦስት ቀናት ውስጥ እንዲመለስ ከማስጠንቀቂያ ጋር ቁርጥ ውሳኔያቸውን አሳወቁ፡፡
ጌታቸው ይህንን አደጋ ለመቋቋም የነበረው መፍትሔ አንድ ብቻ ነበር፡፡ ያለውን ንብረት ሸጦ በተሰጡት ሦስት ቀናት ውስጥ ዕዳውን መክፈል፡፡ ስለዚህ የመኖሪያ ቤት ሠርቶ ለጎጆ መውጫ ያሰበውን መሬቱን በአንድ ሌሊት ያልተጠና ውሳኔ በብር አሥራ አራት ሺህ ሸጦ እዳውን ከፈለ፡፡ ይህንን ፈጣን ውሳኔ በመወሰኑም ራሱንም ሆነ የክፉ ቀን ወዳጁ የሆኑትን የቁጠባ ማኅበሩን ሊቀ መንበር አቶ ዳምጠው መላኩን ከችግር ለመታደግ ችሏል፡፡ የአደራ ሽያጭ እንዲያከናውንለት ለኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ያስረከበውን በሺህ የሚቆጠር መጻሕፍትም፣ በእርስ በእርሱ ጦርነት ማክተሚያ አካባቢ የኢህአዴግ አማፂያን ዋና ዋና ከተሞችን ሲቆጣጠሩ “የሽያጭ ሱቆቹ ተዘርፈዋል” በሚል ምክንያት ገንዘቡን ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ “ሁሉም ሙያ አነሰም በዛ፣ እንደየባህርያቸው መሥዋዕት ማስከፈላቸው እውነት ቢሆንም በተለየ ሁኔታ ግን ‹ለኪሳራ የጣፈው ቢነግድ አይተርፈው› እንዲሉ የሥነ ጽሑፍ ሙያ የሚያስከፍለው መሥዋዕትነት ግን በብዙ አቅጣጫ የከፋ መሆኑን” ጌታቸው ደጋግሞ ይናገራል፡፡
#የጌታቸውበለጠሥራዎች
‹‹የሥነ ጽሑፍ ሕይወቴ ብዙ መስዋዕትነት አስከፍሎኛል›› ቢልም፣ ዛሬም ድረስ መጻፉን ሳያቋርጥ ለንባብ ያበቃቸው በርካታ ሥራዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡ 1. “ስሞተኛው”፡- አጭር ልብ ወለድ፣ በ1981 ዓ.ም፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ (ዳግላስ ጴጥሮስ በሚል የብዕር ስሙ)፣ 2. “መንትዮች”፡- ረጂም ልብ ወለድ፤ የመጀመሪያ ኅትመት በ1982 ዓ.ም፤ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፤ ድጋሚ ኅትመት 2002 ዓ.ም ርሆቦት አሳታሚዎች፣ 3. ኤሎሄና ሃሌ ሉያ፡- ኢልብ ወለድ፣ በ1992 ዓ.ም፣ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፣ በዘመነ ደርግ የነበረውን አስከፊ የሃይማኖት ጥላቻና የክርስቲያኖችን ስደት በዝርዝር የሚተርክ መጽሐፍ፤ 4. የአመራር ጥበብ፡- ኢልቦለድ፣ ከ2002 – 2005 ዓ.ም፣ ርሆቦት አሳታሚዎች፣ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ለአምስት ተከታታይ ጊዜያት የታተመና በአንባብያን ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፈ፣ 5. የጥበባት ጉባዔ፡- ኢልብ ወለድ፣ 2004 ዓ.ም፣ ርኆቦት አሳታሚዎች፣ ለሁለተኛ ደረጃ እና ለኮሌጅ ተማሪዎች የሚያግዝ የሥነ ጽሑፍ ማስተማሪያ መጽሐፍ፤ 6. የአማርኛ ቋንቋ መማሪያ፡- ኢልብ ወለድ፣ መጀመሪያ 2005 ዓ.ም፣ ድጋሚ 2007 ዓ.ም፣ በህንድ አገር ደረጃውን ጠብቆ በቀለማት የታተመ የዘጠነኛና የአሥረኛ ክፍሎች መርጃ መጽሐፍ፤ 7. ሦስት የአፀደ ሕፃጻናት የአማርኛ መማሪያ፡- በ2006 ዓ.ም፣ በማራኪ ቀለማት የተዘጋጁና በህንድ አገር የታተሙ፤ (መጽሐፍ አንድ፣ መጽሐፍ ሁለት፣ መጽሐፍ ሦስት)፣ 8. ሦስት የሕጻናት የታሪክ መጻሕፍት፡- ‹‹ሳቂታዋ ጽጌሬዳ››፣ ‹‹ዳማና ቡሎ›› እና ‹‹ጭልፊትና ሲላ›› የተሰኙ በሙሉ ቀለማት የተዘጋጁና በህንድ ሀገር በ2007 ዓ.ም የታተሙ፡፡
ከእነዚህ ሥራዎቹ በተጨማሪ ከሌሎች የሥነ ጽሑፍ አጋሮቹ ጋር ሆኖ፡- የዘመን ቀለማት፡- የግጥም መድበል፣ የጥላሁን ገሠሠ ግለ ታሪክ፣ የትምህርት ሚኒስቴር በሀገር ዓቀፍ ደረጃ በሥራ ላይ ያዋላቸው ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍሎች አራት “የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር” ማስተማሪያ መጻሕፍት፣ እንዲሁም፣ ለ3ኛና ለ4ኛ ክፍሎች የአካባቢ ሳይንስ መርጃ መጻሕፍትን በማዘጋጀት ከፍተኛ ግምት ያላቸውን የእውቀት ትሩፋት አበርክቷል፡፡
ጌታቸው፣ ከራሱ የሥነ ፅሑፍ ሥራዎች በተጨማሪ ለሌሎችም የዘርፉ ባለሙያዎች የምክርና የአርትዖት እገዛ በማድረግ ይታወቃል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ፡- “በመከራ ውስጥ ያበበች ቤተክርስቲያን”፡- ደራሲ ወንድዬ ዓሊ፣ “የአዲስ ኪዳን ቅኝት”፡- በርካታ ተርጓሚዎች የተሳተፉበትና ከ11 ዓመታት በላይ የፈጀ ትልቅ የትርጉም ሥራ ሲሆን፤ የሀገሪቱ የሥነ መለኮት ተቋማት ለማስተማሪያነት የሚጠቀሙበት መጽሐፍ ነው፡፡ እንደ ታላቅ ስራ ከሚቆጥራቸው ስኬቶቹ መካከል በጳውሎስ ኞኞ የተዘጋጁት “ዳግማዊ አጤ ምኒልክ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የተጻጻፏቸው ደብደቤዎች” በሚሉ አርእስት የተዘጋጁ ሁለት ቅጽ መጻሕፍትን በአርታኢነትና ከቤተሰቡ ጋር በመተባበር የኅትመት ብርሃን እንዲያዩ ያደረገው ጥረት በእጅጉ ያስደስተዋል፡፡ በ1948 ዓ.ም መታተም የጀመረውንና በደርግ መንግሥት ለረጂም ዓመታት ተቋርጦ የቆየውን የ“ቃለ ሕይወት” መጽሔት እንደገና እንዲታተም በማድረግ ለ14 ዓመታት ያህል በዋና አዘጋጅነት በርካታ ቅጾች እንዲታተሙ ማድረጉም ሌላው የስኬቱ መገለጫ ነው፡፡
#የትዝታዬማኅደር
ጌታቸው ከጥቂት ወራት በፊት ያሳተመው “የትዝታዬ ማኅደር” የሚለው ዳጎስ ያለው መጽሐፉ በብዙዎች ዘንድ በመነበብ ላይ ይገኛል፡፡ መጽሐፉ ከግለ -ታሪክነት ከፍ ያሉ ሀገራዊ ጉዳዮች እንደተከታቱበት በምረቃው ዕለት ዳሰሳ ባደረጉ ምሁራን ተመስክሮለታል፡፡
ይሄው “የትዝታዬ ማኅደር” መጽሐፍ በተለያዩ ዓለማት ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንዲዳረስ ታስቦ በአማዞን በኩል የአማርኛው ኅትመት በሂደት ላይ ይገኛል፡፡ በተጓዳኝነትም ለእንግሊዘኛ ቋንቋ ተናጋሪ ዓለም አቀፍ አንባቢያን በዚያው በአማዞን በኩል የትርጉም ሥራው እየተፋጠነ ይገኛል፡፡
ጌታቸው በለጠ፣ በገጣሚነት፣ በጋዜጣ ዓምደኛነት፣ በመጽሐፍ ደራሲነት፣ በአርታዒነት በመጽሔት አዘጋጅነት ወዘተ. የሥነ ጽሑፍ ክህሎቱን ከማሳየቱና ለተተኪው ትውልድ እውቀትን ለማሸጋገር ከመጣሩ ባሻገር ከ1997 ዓ.ም እስከ 2005 ዓ.ም ድረስ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ፕሬዝደንት ሆኖ በማገልገል ለማኅበሩ ከፍታና ለሥነ ጽሑፍ እድገት የማይናቅ አስተዋፅዖ አበርክቷል፡፡ ከሥነ ጽሑፍ ሙያው በተጨማሪም የኢትዮጵያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባል፣ የምሁራን ቲንክ ታንክ ቡድን ም/የቦርድ ሊቀመንበር፣ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ ሊቀመንበር፣ የአሜሪካ ተማሪዎች ማኅበር የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና በበርካታ ሀገራዊ ቦርዶችና ኮሚቴዎች ውስጥ በመሳተፍ ሀገሩንና ሕዝቡን እያገለገለ የዜግነት አሻራውን በደማቁ እያሳረፈ ይገኛል”።