ጀሚል ሸሪፍ ሠዒድ

ሚል ሸሪፍ ሠዒድ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያው እና በጋዜጠኝነት ዘርፍ የማይረሳ አሻራ ያኖሩ ሰዎችን የህይወት ታሪክ እያሰባሰበ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ባለፉት 1አመት ከ5 ወር ጊዜ ውስጥ ከ200 በላይ የሚድያ ሰዎችን ታሪክ ያሰባሰብን ሲሆን 180 ያህሉንም መዝገበ-አእምሮ በሚል በጠንካራ ሽፋን ለማሳተም ችለናል፡፡ በቀጣይ ታሪካቸው ከሚሰነድላቸው ባለሙያዎች አንዱ ጀሚል ሸሪፍ ሲሆን እርሱም ከ19 አመት በፊት ህይወቱ እንዳለፈች ይታወቃል፡፡ ጀሚል ይርጋ የጀሚል ሸሪፍን ታሪክ እንዲህ ሰንዶታል፡፡ ጀሚል ሸሪፍ ሠዒድ- አይረሴው የብዕር ዘንገኛ!

“ጀሚል ከፍልውሃ”

በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሰማይ ላይ ደምቀው ከታዩ ኮከብ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ነበር – ጀሚል ሸሪፍ። በብዙዎች አንባቢያን ዘንድም ሆነ ቀድሞ የኢትዮጵያ ሬድዮን (በተለይም “የወጣቶች ፕሮግራም”ን) ይከታተሉ በነበሩ አድማጮች ዘንድ የሚታወቅበት የብዕር ስሙም “ጀሚል ከፍልውሃ” ይሰኛል። ከተመሠረተ ሰማኒያ አምስት ዓመታትን የተሻገረው “አረጋዊው” ኢትዮጵያ ሬድዮ ከ1970ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ የተከተላቸው ዘመናዊ አሠራሮችና የአሳታፊነት ባህል እጅግ ተወዳጅነትን ያተረፈለት ከመሆኑ ባሻገር ጀሚልንና እርሱን መሰል ምርጥ ብዕረኞችን ማፍራት ያስቻለ አዲስ መንገድ ነበር።

በዚያን ዘመን ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለመጻፍ ከቶም የማይታሰብ የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ማኅበራዊና ኪናዊ ጉዳዮች ላይ የብዕር ስም በመጠቀም ጎራ ለይቶ ጠንከር ያሉ “ምይይጦችን” ማካሄድ አንዱ መንገድ ነበርና ጀሚልም ይህን ተከትሎ ባደረገው የብዕር ጉዞ እስከ ዛሬ ድረስ ባሰቡት ቁጥር በአድናቆት ከሚዘክሩት አድማጮቹ ጋር ተገናኘ። የትዝታቸው አካል ሆኖም ይወሳል።

ጀሚል – ከልደት እስከ ዕውቀት

ጀሚል የተወለደው እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ ነው – ከአዲሱ ገበያ ከፍ ብሎ በሚገኘውና በተለምዶ “ቶታል” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ። የልደት ዘመኑን በተመለከተ ከ“ጽጌሬዳ መጽሔት” እና ሌሎች ሰዎች የሰጡን መረጃዎች ሰፊ ልዩነት የሚታይባቸውና የማይገናኙ ነበሩ። የ“ጽጌሬዳ” መጽሔት መረጃ የልደት ዘመኑን 1952 ሲያደርገው፣ ጓደኛው አበበ ለማ ደግሞ “1954 ነው” ይላል። ከሁለቱም የተሻለና ተአማኒነት ያለው መረጃ ሆኖ ያገኘሁት ግን የወላጅ እናቱን ነው።

“ጀሚልን የወለድኩበት ዘመን መቼ እንደነበር አላውቀውም። ግን እርሱን ወልጄ አራስ ቤት እያለሁ ‘ልዑል መኮንን ሞቱ’ ተብሎ ይወራ እንደነበር አስታውሳለሁ” በማለት የሰጡትን መረጃ ስንከተል የልደት ዘመኑ 1949 ዓ.ል. መሆኑን እንደርስበታለን። ምክንያቱም የልዑሉ ኅልፈተ-ሕይወት የተሰማው ግንቦት 5 /1949 ዓ.ል ነውና።

የጀሚል ወላጅ አባት ስም “ሸሪፍ ሠዒድ” ይሰኛል። የእናቱ ደግሞ ኸይሪያ ሠዒድ። በአባቱ ወገን የቀጥበሬ፣ በእናቱ በኩል ደግሞ የአብሬት ሼኾች ቤተሰብ መሆኑን ከእናቱ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል። ለአያቱ (ለእናቱ እናት) ሷሊሃ ጁሃር እጅግ ጥልቅ ፍቅር የነበረው ጀሚል ነፍስ ካወቀ በኋላ ከእርሳቸው ጋር መኖርን ምርጫው አድርጎ ፍልውሃ አካባቢ አደገ። እርሳቸውም “እንደ እናንተ አጣና እየቆረጠና እንጨት እየፈለጠ አይኖርም” ብለው በአያት እንክብካቤ አቀማጥለው ያዙት። አብሯቸው እየኖረም ነበር የአባቱን ከዚህ ዓለም በሞት መለየት የሰማው።

ቤተሰባቸውን ሽሮሜዳ (ቁስቋም አካባቢ) በአጣና ንግድ ያስተዳድሩ የነበሩት አባቱ አቶ ሸሪፍ ሠዒድ አንድ ግለሰብ የሌላን ሰው ድንበር አልፎ የሸጠላቸውን ዛፍ ባለማወቅ በመቁረጣቸው ተከሰው ከርቸሌ በታሰሩበት ነበር የሞቱት። ጀሚል የዕድገቱ ሰፈር በሆነው ፍልውሃ የኖረው አያቱ ዘንድ ብቻ አልነበረም፤ የእናቱ ወንድም ከሆኑት አጎቱ አቶ ገብረእግዚአብሔር ሠዒድ ጋር “ሮተሪ ክለብ አጠገብ” በሚገኝ ቤታቸው አብሮ ይኖር ነበር።

የትምህርት ሕይወት

ለመጀመሪያ ጊዜ ቀለም የቀመሰው ከእናትና አባቱ ጋር ሽሮ ሜዳ ይኖር በነበረበት ጊዜ በ”ማቴዎስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ሲሆን በመቀጠል በ”ሥላሴ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነበር። ሽሮ ሜዳን ለቅቆ ፍልውሃ መኖር ሲጀምር ደግሞ የደጃዝማች በየነ መርዕድ ትምህርት ቤት ተማሪ ለመሆን በቃ።

አብሮ አደጉና “አብዛኛውን የልጅነት ዕድሜያችንን እንደ ቤተሰብ ሆነን ነው ያሳለፍነው” የሚለው አበበ ለማ ሲናገር “ጀሚል በትምህርቱ ጎበዝ እና ‘ከ1ኛ እስከ ሦስተኛ’ ደረጃ ነበር የሚወጣው” በማለት ስለ“ቀለሜዋ”ነቱ ይመሰክራል። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲያገባድዱም በቀድሞው ልዑል መኮንን በአሁኑ አዲስ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመደቡ። ይሁን እንጂ በዘመኑ ያረበበው የፖለቲካ መንፈስና ያስከተለው ቀውስ በትምህርታቸው ላይ ሙሉ በሙሉ እንዳያተኩሩ ስላደረጋቸው በቀድሞው የትምህርት ፍቅርና ተነሳሽነት ለመማር አልቻሉም ነበር። እናም ከትምህርታቸው ጎን ለጎን እነርሱንና እነርሱን መሰል የዚያን ዘመን ወጣቶች ልብ የገዛውን “የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)”ን ተቀላቅለው ወታደራዊውን የደርግ መንግስት ለማስወገድ ትግል ጀመሩ።

ጀሚልና የፖለቲካ ሕይወቱ

“ኢሕአፓን ከተቀላቀልን በኋላ የተደራጀነው በአንድ ሕዋስ ሥር ነበር” የሚለው አበበ ለማ የሕዋሷ መሪ ከፖስታ ቤት ጀርባ ይኖር የነበረ ሰሎሞን ሙሉጌታ የተባለ ወጣት እንደነበር ያስታውሳል። የፖለቲካ ንቃታቸውን ለማዳበር ፓርቲው ከሚሰጣቸው የጥናትና የውይይት ፕሮግራሞች በተጨማሪ ንባብን ዋነኛ መንገዳቸው አድርገው ተያያዙት። በዲያሌክቲካዊ ማቴሪያሊዝም ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ጽሑፎችን የንባብ ትኩረታቸው አደረጉ። ፓርቲው የሚሰጣቸውን ተልዕኮም ጎን ለጎን መወጣት ጀመሩ። ጨርቆስ፣ ካዛንቺስ፣ ፍልውሃ፣ መርካቶና ሌሎች አካባቢዎች ጭምር በመዟዟር ጨለማን ተገን አድርገው ጽሑፍ ማዘጋጀት፣ መበተን፣ መፈክር መጻፍ፣ የፓርቲውን አርማ በየግድግዳና አጥር ላይም መሣሉን ተያያዙት።

በፓርቲው መዋቅር ላይ መንግስት ኃይለኛ ጡንቻውን ሲያሳርፍም ሰፈራቸው ላይ “ሚስጥራዊ ወጣቶች ማህበር (ሚወማ) የተሰኘ የወጣቶች አደረጃጀትን በመፍጠር ፓርቲያቸውንና መንግስታዊ አደን የበረታባቸውን የትግል ጓዶቻቸውን ለመታደግ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመሩ። ይሁን እንጂ ተራቸው ደርሶ እነርሱም መታሰሩ አልቀረላቸውም ነበር። በአንዱ ሌሊት ሰፈራቸው ተከብቦ ብዙ ወጣቶች ተያዙ። “ለማምለጥ የሞከሩ ናቸው” ተብለው ብዙዎች ተገደሉም። በወቅቱ አጎቱ ቤት ይኖር የነበረው ጀሚል የቤታቸው በር ሲንኳኳ በጓሮ በኩል ወጥቶ ከቤታቸው ጀርባ (ኦርማ ጋራዥ አካባቢ) የሚገኘውን ወንዝ በመሻገር ሊያመልጥ ሲል የአብዮት ጥበቃዎች እጅ ላይ ወደቀ። ወስደውም አሰሩት።

በመጀመሪያ ለተወሰኑ ወራት ከፍተኛ 14 ቀበሌ 22 ውስጥ ነበር የታሰሩት። በዚያም እርሱና ታሪኩ የተባለ የሰፈራቸው ልጅ እጅግ ስቃይ የተመላ የእስር ጊዜ ነበር ያሳለፉት። ጀርባቸው እስኪተለተል ከተገረፉ በኋላ ቁስላቸው ላይ ጋዜጣ ያቀጣጥሉባቸው ነበር። በዚህም ምክንያት ያሳለፈውን አሰቃቂ ጊዜ የሚያስታውሱትን ጠባሳዎች ጀርባው ላይ አጋድሞ ለመዞር ተገዶ ነበር። “ደርግ የተወልኝ ማስታወሻዬ ነው” ይል እንደነበር ወዳጁ ዳንኤል ድርሻ አጫውቶናል። አብረውት ከታሰሩት አንዱ የነበረውና በአሁኑ ጊዜ በሀገር ፍቅር የዘመናዊ ውዝዋዜ አሰልጣኝ የሆነው ከድር ዓሊ ከእርሱ ጋር በእስር ስላሳለፉት ጊዜ ሲናገር “እኛ በዕድሜ ትናንሾች ስለነበርን ቀላል የሆነ ግርፊያ ነበር የሚፈጸምብን። ጀሚል ግርፊያና ቃጠሎ ጭምር ተካሂዶበት ወደ እስር ክፍላችን ሲመለስ የደረሰበትን ስቃይ ዋጥ አድርጎ እኛን ነበር የሚጽናናን” በማለት ስላለፉበት የስቃይ ሁኔታና ስለጀሚል ጽንአት ገልጿል።

በአሁኑ ጊዜ በፖለቲከኛነቱ የምናውቀው ጓደኛውና የሥራ ባልደረባው የነበረው አብዱረህማን አሕመዲን “ጀሚል የእስር ጊዜን ያሳለፈው በከፍተኛ 14 ቀበሌ 22 ብቻ አልነበረም። ፓርላማ ጊቢ ውስጥ ሰዓቱ ካለበት ሕንፃ በታች በሚገኝ Underground እስር ቤት ጭምር ታስሮ ፍዳውን እንደ ቆጠረ ከገዛ አንደበቱ ሰምቻለሁ” ይላል። እናቱ ወ/ሮ ኸይሪያ ሠዒድ እና እህቱ ፋንቱ ሸሪፍ ሲናገሩም “ያሳለፈው ስቃይ ካሳደረበት ተጽእኖ (Trauma) የተነሳ ከእስር ቤት ከወጣ በኋላ እስከ ዕለተ-ሞቱ ድረስ ሌሊት፣ ሌሊት እየባነነ ጮሆ ይነሳ ነበር” በማለት ስላሳለፈው የመከራ ጊዜ ይተርካሉ።

የሥራ ሕይወቱ

ከእስር ከተፈታ በኋላ ከትምህርቱ ጎን ለጎን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በላይብረሪያንነት ተቀጥሮ መሥራት ጀመረ። በዚሁ ዘርፍም (Library Science) በዲፕሎማ ተመርቋል። እስከ ‘70ዎቹ አጋማሽ ድረስም በትጋት ሲያገለግል ከቆየ በኋላ በፈቃዱ ሥራውን ለቅቆ በለገዳዲ ሬድዮ የመዝናኛ ዝግጅቶችን ማቅረብ ጀመረ። በዚያም ሳለ የተለያዩ ማኅበራዊና ኪናዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱ መጣጥፎችን ከማቅረብ በተጨማሪ ከ12 በላይ የሬድዮ ድራማዎችን ጽፎ ለአድማጮች ጆሮ አብቅቷል።

በአሁኑ ጊዜ ታዋቂ ተዋናይና የማስታወቂያ ባለሙያ የሆነው ሠራዊት ፍቅሬ በወጣትነቱ ዕድሜ ተክለሃይማኖት አካባቢ በሚገኝ የቀበሌ አዳራሽ ውስጥ አማተር ክበባቸው ባዘጋጀው ቲያትር ላይ ሲተውን ጀሚል አይቶት በጻፋቸው የተለያዩ የሬድዮ ድራማዎች ላይ ይተውን ዘንድ ወደ ለገዳዲ ሬድዮ ጣቢያ በመውሰድ ከአድማጮች ጋር እንዲተዋወቅ ማድረጉን ገልፆልኛል። “ለመጀመሪያ ጊዜ የተወንኩትም ‘ዜሮ ለዜሮ’ በተሰኘ ጀሚል በተረጎመው ድራማ ላይ አንቶኒዮ የተሰኘውን ገፀ-ባህሪ ወክዬ ነበር” ሲልም አክሏል።

ከለገዳዲ ሬድዮ በኋላ በፍሪላንሰርነት መሥራት የጀመረው በኢትዮጵያ ሬድዮ ነው – በተለይም “የወጣቶች ፕሮግራም” ላይ። “ጀሚል ከፍል ውሃ” በተሰኘ የብዕር ስሙ ድንቅ ድንቅ ሃሳቦችን ያጋራ ነበር። ይጽፋቸው በነበሩት ደፋር ጽሑፎች ሰበብ ሊደርሱበት ከነበሩት ትንኮሳዎች ይታደገው የነበረው አለቃቸው በቀለ ተሾመ እንደነበር ዳንኤል ድርሻ ከራሱ የሰማው እንደሆነ ገልፆ በጻፈው ማስታወሻ አስነብቧል።

ጋዜጠኛ ሳምሶን ማሞ ስለጀሚል ለጽጌሬዳ መጽሔት በ1995 ዓ.ል በሰጠው አስተያየት ከ1977 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ ሬድዮ አብሮት እንደሠራና “ጀሚል በችሎታው ፍፁም የተካነ ከመሆኑም በላይ የራሱ ስታይልና አድማጭ የነበረው ጋዜጠኛ ነበር። … ቁጥብና እዩኝ፣ እዩኝ የማይል በመሆኑ እንጂ ችሎታውና ሥራው ዛሬ ላይ አሉ ከሚባሉ ጋዜጠኞች በላይ የሚያደርገው ነበር” ብሏል። የብዙ ጊዜ ጓደኛውና የሥራ ባልደረባው ከነበረው ሙሐመድ ሳኒ በተሰጠኝ ዝርዝር መረጃም “ጀሚል ከ‘ለገዳዲ’ እና ‘ኢትዮጵያ ሬድዮ’ በተጨማሪ በሬድዮ ፋና የመጀመሪያዎቹ የምሥረታ ሰሞናት ለአጭር ጊዜያት አገልግሏል። በሬድዮ ጣቢያው ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን ‘ዕጣ-ፈንታ’ የተሰኘ ድራማው በቅዳሜ የረፋድ ሰዓት የመዝናኛ ዝግጅት ላይ ተላልፎ አድናቆት አግኝቶለታል።”

ጀሚል በህትመት ሚዲያው ዘርፍ

ጀሚል ወደ ህትመት ሚዲያው ዘርፍ ጎራ ያለው የ“ቢላል” መጽሔት ምክትል አዘጋጅ በመሆን ነበር። የ“ቢላል” መጽሔት ባለቤትና አሳታሚ አቶ ሠዒድ ሙሐመድ ኑርዬ በአንድ ወቅት የፕሮግራሙ ተሸላሚ በሆኑበት “ምርኩዝ” 02 ዝግጅት ላይ ባደረጉት ንግግር “የ‘ነጃሺ አሳታሚ’ እና የ‘ቢላል’ መጽሔት መጀመር ሰበብ ጀሚል ሸሪፍ ነው። ከዕለታት በአንዱ ቀን የሐጅ ሙሐመድ ወሌን ሀዲስ በካሴት ቀድቼ በምሸጥበት ሱቅ በኩል ሲያልፍ ሰምቶት ገባና ‘ለምን ይህን በመጽሔት መልክ አናዘጋጀውም?’ የሚል ሃሳብ አቀረበልኝ። እኔም ‘የአንተ ዓይነቱን ሰው አይደል እንዴ የምፈልገው?!’ ብዬ ሥራውን ጀመርን። …” ነበር ያሉት። ከቢላል መጽሔት ከለቀቀ በኋላም በመጅሊስ ሥር ይታተም የነበረውን “አል-መናር” መጽሔ አዘጋጅቷል። በግለሰቦች ባለቤትነት ይታተሙ በነበሩት “ኢቅራእ” እና “አል-ነጃሺ” ላይ ከመሥራቱ ባሻገር ከጓደኛው ጋዜጠኛ አክሊሉ ታደሰ ፍቃድ በመከራየት በእርሱ ባለቤትነት ሥር “አል-ከውሰር” የምትሰኝ ጋዜጣ ማሳተም ጀምሮ እንደነበር በዚያን ዘመን የነፃው ፕሬስ ሰዎች ከነበሩት መካከል አንዱ ነስሩ በሽር ለዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ አውግቶታል።

ከ“ኢስላማዊ” ሚዲያዎች ከራቀ በኋላ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ መፍቀሬ-ኢሕአፓ በነበረችው “ጎሕ” ጋዜጣና መጽሔት ውስጥ በአዘጋጅነትና በማኔጂንግ ኤዲተርነት ከማገልገሉ በተጨማሪ “ሞረሽ” የተሰኘች የ“ጎሕ” እህት ጋዜጣ ለንባብ እንድትበቃም አድርጓል። አብረውት ከሠሩትና ስለእርሱ አስተያየት ከሰጡት ሰዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ “በዚያን ዘመን ለንባብ ይበቁ ከነበሩ ጋዜጦችና መጽሔቶች መካከል የእርሱ እጅ ያላረፈባቸው ጥቂቶች እንደነበሩ” ይገልጻሉ።

ጀሚል፤ “ጀሚል ከፍልውሃ” ከተሰኘው የብዕር ስሙ በተጨማሪ “በልዩ”፣ “አልማዝና አልማዝ”፣ “አሌፍ”፣ “ጀሚል ጀማል”፣ “አተረ ጌተረ”፣ “ቬኪዮ”፣ “ዶቅማስ”፣ “ኢማን ጀሚል” በተሰኙ የብዕር ስሞች የተለያዩ ጽሑፎችን ያስነብብ ነበር። “ኢስላማዊ” ይዘት በነበራቸው የኅትመት ውጤቶች ላይም “ነጃት አብዱልቃድር” እና “ሼኽ ሩኃኒይ” በተሰኙ የብዕር ስሞች ያስተላልፋቸው በነበሩት ሃሳቦቹ የሀገራችንን ሙስሊም ለማንቃት እጅጉን ተግቷል። ለሌሎችም የሀገራችን “ነፃ ፕሬስ” ውጤቶች ተነባቢነት ያደርጋቸው የነበሩት ሙያዊ አስተዋጽኦዎች እንደዋዛ የሚገለጡ አለመሆናቸውን ብዙዎቹ የሙያ አጋሮቹ ይናገራሉ።

ጀሚል በሥነ-ጽሑፉ ረገድ

በልጅነቱ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን “እቴጌ መስክ የዕድገት ጣቢያ” የተሰኘ የኪነ-ጥበብ ክበብ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን መሥርቶ ብዙ ቲያትሮችን፣ አጫጭር ልብ-ወለዶችንና ግጥሞችን ጽፎ ለታዳሚያኑ ያቀርብ እንደነበር ሌላኛው አብሮ አደጉ አእምሮ ኃይሌ ተናግሯል። ይህም ለወደፊቱ የጋዜጠኝነትና የሥነ-ጽሑፍ ሕይወቱ ታላቅ መሠረት ጥሎለታል። “ብዙ” ሊባሉ የሚችሉ አጫጭር ልብ-ወለዶቹንም በተለያዩ መጽሔቶችና ጋዜጦች ላይ አስነብቧል። እንደ ምሳሌም የ“ቱሉ ፎርሳ” ተከታይ አድርጎ የጻፈው “ፎርጃ ቱሉ ፎርሳ” የተሰኘው “ጎሕ” ላይ ይወጣ የነበረው ተከታታይ ልብ-ወለድ ጽሑፉ በማሳያነት ይጠቀስለታል።

ግላዊ ጠባይ

ለዚህ ጽሑፍ መረጃ ፈልጌ ያነጋገርኳቸው ታዋቂ ጋዜጠኞችና ሌሎች አብሮ አደግ ጓደኞቹ በሙሉ ብሎ መደምደም በሚያስችል መልኩ ስለ ጠባየ-መልካምነቱ፣ ረጋ ያለ ስለመሆኑና ዝምተኛነቱ ተናግረዋል። “አይቆጣም፣ ትሁትና ሰውን ተናግሮ የማያስቀይም ሰው ነበር” ሲሉም መስክረውለታል። “በባህሪው ዝምተኛ በመሆኑ ‘ኩራተኛ’ አድርገው የሚያስቡት አሉ። ግን ተሳስተዋል። እጅግ ተግባቢና ተጫዋች ሰው ነበር – ጀሚል። ዓይኖቹ በራሳቸው የሚናገሩ ናቸው። ከፈለጉ ይረግሙሃል፣ ይመርቁሃል። ሲስቁም ሆነ ሲያዝኑ ልታገኛቸው ትችላለህ” የሚል አስተያየቱን የሰጠን አብሮ አደጉ አበበ ለማ ነው።

የ“አል-ነጃሺ” ጋዜጣ ባለቤትና አሳታሚ የነበረው አቶ ዓሪፍ አብዱል ቃድር ደግሞ “ጀሚል ለተጎዳ ሰው ተቆርቋሪ፣ ሰውን የማያስቸግር፣ ቃሉን አክባሪ፣ ሥራውን ለዓላማ የሚሠራ ነበር። ነፃነቱን ለድርድር የማያቀርብና በችግር ታጥፎ ‘ሸብረክ’ የማይል ሰው ነበር” ይላል። ከምግብ ጉበት “ነፍሱ” እንደነበረና ከዚያ በተረፈ ምግብ ብዙም እንደማይበላ፣ እንዲሁም በጧት ሥራ መግባት የማይሆንለት ግን ደግሞ ሥራውን አድምቶና አሟጥጦ የሚሠራ ጎበዝ ጸሐፊ ነበር” ብሎ ይገልጸዋል።

“ከቀደመ ሕይወቱ ሁሌም የሚሸሸው ጠባሳ ያተረፈ ሰው ይመስልም ነበር። ቤቱ ውስጥ የሚገኙ የቆዩ ዕቃዎችን፣ ብርድልብስ መቀየር አይፈልግም ነበር። ከበስተጎኑ ደግሞ የአንዲት ሴት ፎቶ ተሰቅሎ ይታይ ነበር” ይላል። “ለሴቶች ትልቅ አክብሮት፣ ፍቅርና ስሱነት የሚስተዋልበት ቢሆንም ሲቀርባቸው ግን አታይም” ሲል ያክላል። የይቅር ባይነቱም ልክ እስር ቤት ላይ ያስገረፈውን ሰው ይቅር እስከማለት የሚደርስ ነበር።

የትዳር ሕይወት

ጀሚል የረጋ የትዳር ሕይወት የነበረው ሰው አልነበረም። ከልጅነት ዕድሜያቸው ጀምሮ ይዋደዱ ከነበረችው የሰፈሩ ልጅ አሰገደች ንጉሤ ጋር ለውሱን ጊዜያት አብረው የቆዩ ሲሆን ቤተሰቦቿ ከእርሱ ጋር መሆኗን የማይፈልጉ በመሆናቸው በእነርሱ ጣልቃ ገብነት ምክንያት ትዳራቸው መፍረሱን የአክስቱ ልጅ በልዩ ገብረእግዚአብሔር ተናግራለች። በአሁኑ ጊዜ ኑሮዋን በሀገረ-ካናዳ ካደረገችው አሰገደች “ሚልካ” የምትባል ልጅ እንዳለው ነግሮን ነበር ብላ አጫውታናለች – እህቱ ፋንቱ ሸሪፍ። በ1980ዎቹ አጋማሽ ላይም ዕፀገነት ከተባለች ሴት ጋር ትዳር መሥርቶ ነበር። ከእርሷም “ኢማን” የሚባል ልጅ በ1986 ወልዶ የነበር ቢሆንም ገና በአራስነቱ ሆስፒታል ውስጥ እንደሞተበት ቤተሰቦቹ ይናገራሉ። “ባለቤቱም እንዲሁ ብዙም በሕይወት አልቆየችም ነበር” ይላሉ። “በስተመጨረሻ አካባቢ ኑሮውን በአግባቡ እንዲመራ፣ ልጅ ወልዶ ራሱን እንዲተካ ፈልገን ‘ሽቱ’ የምትባል ቆንጅዬ ሴት ድረነው የነበረ ቢሆን ከስምንት ወራት በላይ አብረው አልቆዩም ነበር” ትላለች ታናሽ እህቱ ፋንቱ ሸሪፍ ሠዒድ – እርጋታ ስለተለየው የትዳር ሕይወቱ ስታወጋ።

ጀሚል በሕይወቱ መጨረሻ ላይ

ጀሚል በሕይወቱ መጨረሻ ሰሞናት ይሠራ የነበረው በ“ጽጌሬዳ” መጽሔት ማኔጂንግ ኤዲተርነት ነበር። የራሷን የተለየ ቀለም (መንገድ) ይዛ በመጣችው በዚህች መጽሔት ዝግጅት የሚታወቅበት ትጋቱ እና ብቃቱ አልተለዩትም ነበር። በግልጽ ባይናገረውም፤ በልጅነት ዕድሜው አባቱን በወኅኒ ቤት ውስጥ በሞት ማጣቱ ከፈጠረበት ሀዘንና ክፍተት በተጨማሪ ስኬታማ የፍቅርና የትዳር ሕይወትን መምራት ያለመቻሉ በውስጡ የማይሽር ጠባሳ አኑሮበታል ተብሎ ይገመታል። የብቸኝነት ኑሮው የበዛ ነበር። “አንድ ነገር እንዳይሆን” ብለው የሰጉት እናትና እህቱ የወንድሙን ልጅ አብሮት እንዲኖር ቢያደርጉም ሊሆን አልቻለም። በዚህም ምክንያት በቅርብ የሚንከባከበው አልነበረም። ምግቡንም በቅጡ አይመገብም ነበር። እናም በጠና ታመመ። ሕመሙ ቲቢ ነበር። በወቅቱ የእናቱ ቤት ምቹ ስላልነበረ ጓደኛው ሰሎሞን አዳሙ አስኮ ወደሚገኘው ቤቱ ወስዶት ያስታምመው ጀመር። ምግብ በደንብ አይመገብ ስለነበር ጤናው መሻሻል ባለማሳየቱ ሆስፒታል እንዲገባ ተደረገ። ከዚያ በሕይወት መውጣት አልቻለም። እናም በዕድሜው መጨረሻ ላይ ከጎኑ ያልተለዩትን አቶ ሰሎሞን አዳሙንና ባለቤቱን፣ ኢልሃም ሙሐመድ አወል ረጃን፣ ጋዜጠኛ ኢድሪስ ዋበላንና ተማሪ ውብሸት እምሩን አመስግኖ ሐምሌ 14/ 1995 ዓ.ል. በሞት ይህችን ዓለም ተሰናበታት። ቀብሩም በኮልፌ ሙስሊም መካነ-መቃብር ተከናወነ።

ጀሚልን በፀፀት

“ጀሚልን እጅግ ጎድተነዋል። ዝም ብለን ማሠራታችን ላይ ብቻ አተኩረን በተገቢ ሁኔታ አልተከባከብነውም፤ በሕይወት እንዲቆይልን አላደረግነውም” ይህም ስለ እርሱ ሳስብ ወይም ትዝ ሲለኝ የሚያሳዝነኝና የሚጸጽተኝ ነገር ነው ይላል – ነስሩ በሽር። የዓሪፍ አብዱልቃድርም ስሜት እንዲሁ ተመሳሳይ ነው። “በሕይወት እያለ ብዙ ልናደርግለት ስንችል ባለማድረጋችን ይቆረቁረኛል” በማለት ጸጸቱን ይገልጻል።

ታዋቂው ጋዜጠኛ ደረጀ ኃይሌ ደግሞ የዛሬ ሁለት ዓመት ግድም ለዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ስለጀሚል ሸሪፍ በስልክ የሚከተለውን አጫውቶት ነበር።
“በኢትዮጵያ ሬድዮ የወጣቶች ፕሮግራም ላይ ስሠራ ሦስት ምርጥ ጸሐፍት የዝግጅታችን ድምቀቶች ነበሩ – መስፍን ገብረማሪያም፣ ሙላቱ ገብሩ እና ጀሚል ከፍል ውሃ። ድንቅ ሰዎች ነበሩ። እነዚህ ሰዎች ትዝ ሲሉኝ “የባከኑብን ሰዎቻችን” የሚል ርዕስ ነበር የሚታየኝ። እናም ከዛሬ ነገ እጽፈዋለሁ እያልኩ ሳላደርገው ቀረ እንጂ ስለ እነርሱ ብዙ ማለት እሻ ነበር” በማለት ቁጭት-አዘል ስሜቱን አንጸባርቋል።

ዓሪፍ አብዱልቃድር እንዳለው ጀሚል የሚጽፈው ለዓላማ እንጂ የተዝናኖትን ስሜት ለመፍጠር አልነበረም። ብዕሩም አምባገነኖችን የሚፋለምበት፣ በደልን የሚያወግዝበትና ኢ-ፍትሐዊነትን የሚቃወምበት መሣሪያው ሆና ነበር የዘለቀችው – የአይረሴው ሰው የጀሚል ሸሪፍ ሠዒድ መንጎል!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *