ዶ/ር ምናሴ ኃይሌ (ከ1922-2018)

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን ፣ መዝገበ-አእምሮ ( የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ ) ፕሮጀክቱ ለአገር የሠሩ ሰዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ታሪክ በዲጂታል ሚድያዎች ፣በመፅሀፍ፣በድምፅ ትረካና በሌሎችም መንገዶች እየቀረበ እንደሆነ ይታወቃል። ባለፉት 4 ዓመት ከ 5 ወር ጊዜ ውስጥ የ423 ሰዎችን የሕይወትና የሥራ ታሪክ ለመሰነድ የቻልን ሲሆን 600 ገፅ ባላቸው ሁለት የተለያዩ መፅሐፎች ላይም ታሪኮቹ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው እንዲቀመጡ አድርገናል።

ቅፅ 3 መዝገበ አእምሮ ከ20 በላይ ዘርፎች ይኖሩታል። እዚህ ዘርፍ ውስጥ የሚገኙ የአገር ባለውለታዎችን መሰነዳችን ይቀጥላል። ዲፕሎማሲና የመንግስት ኃላፊነት በሚለው መደብ ታሪካቸውን የምንሰንድላቸው ዶክተር ምናሴ ኃይሌ ሲሆኑ ታሪካቸውንም ዕዝራ እጅጉና ሲሳይ ገብረማሪያም እንደሚከተለው አጠናክረውታል

ህልፈታቸው በዩናይትድስቴትስ ኒውጀርሲ እ.ኤ.አ መስከረም 2025 (ጳጉሜ 5, 2017 ዓ.ም) ነበር።እንደ አንድ የመንግስት ኃላፊ ፣ዲፕሎማት ፣የህግ ምሁር ለማይታረቁና ለተለያዩ የዓለም አስተሳሰቦች የሚጋሩትን ድልድይ በመገንባት ይህን ዓለም ተሠናብዋል። ከልጅነት እስከዕውቀት ዶ/ር ምናሴ ህይወትን እንዴት ኖሯት?

ልደት፣ ዕድገትና ትምህርት

ዶ/ር ምናሴ ኃይሌ ከእናታቸው ከወይዘሮ እሌኒ ኃይሌ እና ከአባታቸው ከአቶ ኃይሌ ድብነህ በ1922 ዓ.ም በሐረር ተወለዱ። የልጅነት ዘመናቸውን በሐረር ያሳለፉት የያኔው አዳጊው ምናሴ ቤተሰባቸው ኑሮውን በአዲስ አበባ ሲከትም የእርሳቸው የትምህርት ህይወት በኮተቤ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ቀጠለ። በኮተቤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ሳሉ በሀገረ- አሜሪካ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ የሚያስችላቸውን እድል አገኙ።

በአሜሪካ በቀጠለው ትምህርታቸው እ.ኤ.አ በ1950 ከዊስኮንሲን ማዲሰን ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አገኙ። እ.ኤ.አ በ1954 ደግሞ በኒውዮርክ ወደሚገኘው ኮሎምቢያ ዩንቨርስቲ በማቅናት የህግ ትምህርት ለማጥናት ጥርጊያውን ያመቻቸላቸውን ለህግ ትምህርት ቅድመ ዝግጅት ብቁ የሚያደርገውን የ (Juris Doctor) ወረቀት አገኙ። ባልተገታው የትምህርት ጉዟቸው እ.ኤ.አ በ1957 ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሲጎናፀፉ ከ4 አመት በኋላ በ1961 ሦስተኛው ዲግሪ (ፒ.ኤች.ዲ) ያዙ።

ሀገራዊ ኃላፊነት እና ሙያዊ አበርክቶ

በዛው ትምህርታቸውን ባጠናቀቁበት ዓመት ምቾት ይበልጥብኛል ሳይሉ እ.ኤ.አ በ1961 ወደ እናት ሀገራቸው ኢትዮጵያ ተመለሱ።

በተመለሱበት ቅፅበትም የኢትዮጵያን ፒስ ኮርፐስ ከአሜሪካ ጋር በጋራ እንዲሠሩ ሁለቱን ሀገራት ያፈራረሙት ዶክተር ምናሴ ነበሩ። በጊዜውም እርሳቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የህግ አማካሪ ሆነው በተቀጠሩበት ጊዜ ነው። ዶ/ር ምናሴ ኃይሌ በተመደቡበት የውጭ ጉዳይ ስራ ሳይታጠሩ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ደንብ የሚል ረቂቅ በማዘጋጀት በረቂቅ ደንቡ አማካይነት የኢትዮጵያ ፐርሶኔል አስተዳደራዊ ኤጀንሲ ተብሎ የሚጠራውን ተቋም አቋቋሙ ።

ከዚህ መንግስታዊ ኃላፊነት በኋላ እ.ኤ.አ በ1962 ዶ/ር ምናሴ የንጉሠ ነገስቱ የግል ካቢኔ አባል ተደርገው ተሾሙ። በዚሁ ኃላፊነታቸው የውጭ ፣የፍትህ ፣የኢኮኖሚ ፣የውጭ ደህንነት እና ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ቅኝት እንዲያደርጉ እና ስትራቴጂካዊ በሆኑ ሀሣቦች ዙሪያ እንዲያማክሩ በንጉሡ የግል ካቢኔ አባል ሆነው ሥራቸውን ቀጠሉ።
ከተሠጣቸው ስትራቴጂካዊ ጉዳዮችን ማማከር እና ቅኝት የማድረግ ኃላፊነት ባሻገር እ.ኤ.አ በ1964 ሌላ ድርብ ኃላፊነት ተጣለባቸው። የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሚንስትር ሆነው ተሾሙ። በዚህ ኃላፊነታቸው በሃገሪቱ በወቅቱ በነበሩት ሚዲያ ዎች ማለትም በኢትዮጵያ ሬድዬ ፣ቴሌቪዥን እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላይ ስርነቀል ለውጥ እንዲመጣ በማድረግ በእርሳቸው መሪነት ተቋማቱ የተሻለ ሙያዊ ነፃነት እንዲጎናፀፉ አድርገዋል።በተመሣሣይ ጊዜም በሀገሪቱ በተነባቢነት ሁለተኛ ደረጃነት ይዞ የነበረው የዛሬይቱን ኢትዮጵያ ጋዜጣን መስርተዋል።

እ.ኤ.አ ከ1969 እስከ 1971 የነበረው ወቅት የአሜሪካ ትኩረት በቬትናም ጦርነት እና የቀዝቃዛው ጦርነት ትኩረት ያየለበት ጊዜ ነበር።ለዶ/ር ምናሴ ይኸው ወቅት ቀጣይ የሙያ ማረፊያቸው ሆኖ በአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉበት ጊዜ ነበር።

ከአሜሪካ አምባሳደርነት መልስ እ.ኤ.አ በ1971 ዶ/ር ምናሴ ዳግም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚንስትር ሆነው ተሾሙ።በዚህ የውጭ ጉዳይ ቆይታቸው ቦታው የሚጠይቀውን ታላላቅ የዲፕሎማሲ ስራዎችን ያከናወኑ ሲሆን በዚሁ ጊዜ የኢትዮጵያን የውጭ ጉዳይ ልዑክ በተባበሩት መንግስታት ፣በአፍሪካ አንድነት፣ በወቅቱ የዓለም ገለልተኛ አባል ሃገራት ንቅናቄ እየተባለ ከሚጠራው ተቋምና እና በሌሎች የሁለትዮሽ ትብብር መድረኮች ኢትዮጵያ እንድትከብር አድርገዋል።

እ.ኤ.አ ከ1971 -1972 ባለው ጊዜም ሀገርን በሌላ ሙያዊ አቅም ወደሚያገለግሉበት ወደአፍሪካ አንድነት ድርጅት በማቅናት በድርጅቱ ውስጥ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባል አገልግሎታቸውን ቀጠሉ። እርሳቸው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባል በነበሩት ዘመንም አህጉሪቱ በታላቅ ተስፋ እና ስጋት ውስጥ ነበረች። ዶ/ር ምናሴም በድርጅቱ በነበራቸው ቆይታ ስጋትን ወደተስፋ በመቀየር ካሳኳቸው ተግባራት መካከል እ.ኤ.አ በ1972 በአዲስ አበባ የተካሄደው ስምምነት ሲሆን ስምምነቱም የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት እንዲቋጭ ያደረገ ነበር። ከዚሁ ጎን ለጎን ለረዥም ጊዜ አጨቃጫቂ የነበረው የኢትዮጵያና የሱዳን ድንበር እንዲካለል አድርገዋል። በተመሳሳይ ወቅት ከንጉሰ ነገስቱ ጋር ወደቻይና ተጉዘው ጉብኝት አድርገው ከወቅቱ የቻይና ጠቅላይ ሚኒስቴር ዞ ኔሊያ እና ከሊቀመንበሩ ማኦ ዜዱንግ ጋር ተገናኝተው ሁለቱ ሃገራት በጋራ ስለሚሠሩባቸው ጉዳዮች መክረዋል።

የጋራ እሳቤ መስራቹ ምናሴ ሀይሌ!

ሀሙስ ግንቦት 16 1965 ዓ.ም ፡፡ የአፍሪካ ሀገራት ርዕሳነ ብሔራት እና ርዕሳነ መንግስታት የወቅቱን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ 10ኛ አመት በአል ለማክበር በአዲስ አበባ ታድመዋል፡፡

ለአዲስ አበባ ይህ ክብረ በአል የድርጅቱ ጉዞ 10 ዓመት ላይ መድረሱ ብቻ አይደለም ትርጉሙ።ዕለቱን ልዩ ያደረገው በዚህ ቀን የተፃፈው አይረሴ ታሪክ ነው።

በአፍሪካ አንድነት ምስረታ 10ኛ ዓመት ላይ
ቅዳሜ ግንቦት 18 1965 ዓ.ም የድርጅቱን ምስረታ በማስመልከት የሚደረጉ ንግግሮች ቀጥለዋል፡፡በወቅቱ እንኳን አደረሰን አደረሳችሁ ከሚሉ መልዕክቶች ባሻገር የበዓሉን ዐውድ የሚለውጡ ንግግሮች መደመጥ ጀመሩ፡፡ ቀዳሚው ደግሞ ከሶማሌያው ተወካይ የተደመጠው ንግግር ነበር፡፡በአፍሪካ አንድነት 10ኛ አመት በዓል ላይ የወቅቱ የሀገራቸውን ፕሬዚዳንት የሆነትን ዚያድ ባሬን ወክለው የተገኙት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ኮለኔል ኢስማኤል አቡበከር ሲሆኑ ንግግራቸው ኢትዮጵያን በመክሰስ ጀመረ ፡፡በሶማሊያው ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ ተፅፎ በምክትሉ በቀረበው ንግግር ኢትዮጵያ ሶማሊያን ልትወር ነው የሚል ሀሜት ያዘለ ዲስኩርን አሰሙ፡፡ የሶማሌውን ምክትል ፕሬዚዳንት ተከትሎ መድረኩን ቀጥለው የተረከቡት ደግሞ የወቅቱ የሊቢያ ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር የሆኑት አቡ ዘይድ ነበሩ፡፡ አቡዘይድ “ኢትዮጵያ በአፍሪካ የጥቂት ነጭ ገዢዎች ስርዓት እንዲሰፍን ትፈልጋለች፡፡” በማለት ለሰደድ እሳቱ ክብሪቱን በመጫር

ንግግራቸውን ጀመሩ፡፡ በማስከተልም “ኢትዮጵያ በአፍሪካ የጥቂት ነጭ ገዢዎች ስርዓት እንዲሰፍን የምታደርገው እስራኤልን በመርዳት ነው፡፡” ሲሉ ክሳቸውን አጠናከሩ፡፡በዚህ ያልተገታው ተንኳሽ ንግግራቸው “ኢትዮጵያ ለአሜሪካ የጦር ሰፈር ፈቅዳለች፡፡ለሰሜን ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶም ትሰልላለች፡፡ይኸው የስለላ ሥራዋ በደቡብ አፍሪካ እና በሮዴዥያ ያለውን ሥርአት የሚመግብ ነው፡፡ይህ የኢትዮጵያ ተግባር ከአፍሪካ አንድነት ዓላማ ጋር የማይሄድ በመሆኑ ፤ በዚህ በዓል ላይ የታደማችሁ የአንድነት ድርጅቱ አባላት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መቀመጫ ከአዲስ አበባ እንዲነሳ” የሚል ክስ አቀረቡ፡፡ ይኸው ንግግር በአዳራሹ የነበረውን አውድ ቀየረው፡፡ ክብረ-በዓሉ ወደሃሣብ ጦርሜዳነት ተቀየረ። በወቅቱ ንጉሰ ነገስቱን ወክለው ለሶማሌ ፕሬዚዳንት እና ለሊቢያው ፕሬዚዳንትተወካዮች የወቅቱ
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር አክሊሉ ሀብተወልድ በፈረንሳይኛ መልስ ሰጡ።ነገሩ ግን በዚህ አልተቋጨም መሠል ጥያቄን በታሪክ ሲነሣም ሁሌም መልስ ሊሆን የሚችል ንግግር በሌላኛው የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ተሰማ፡፡

ስለሁኔታው በማግስቱ ጉዳዩን ለዓለም አንባብያን ያደረሠው “The New York Times” በዘጋቢ ቶማስ ጆንሰን ፅሁፍ እንዲህ ሲል ገለፀው። “AFRICAN NATIONS CLASH AT PARLEY” ወይም “በሰርግ መሀል የቀለጠው ጦርነት” የሚል ስሜት ያለው ፅሁፍ ፃፈ፡፡በዚሁ ግንቦት 19 1965 ዓ.ም ለንባብ ባዋለው ፅሁፍ በአፍሪካ አንድነት 10ኛ ዓመት ክብረ-በአል ላይ የኢትዮጵያ እና ሊቢያ ዱላ ቀረሽ ፀብ ማስተናገዳቸውን፡፡
የፀቡ ፊትአውራሪ የሊቢያው ተወካይ አቦዙድ ዱዋርዳ በአረበኛ ባደረገው ንግግር የኢትዮጵያን መሪዎች “ፅዮናውያን እና ቅኝ ገዢዎች” ብሎ መዝለፉን። “ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ከአሜሪካ እና ከፅዮናውያን ጋር ጥብቅ ቁርኝት” ያላቸው መሆኑን ይህን ተከትሎም “የአፍሪካ አንድነት ዋና መዲናነት ወደሌላ ሥፍራ ይዘዋወር” ብሎ መጠየቁ መሆኑን አትቷል፡፡

አፀፋዊ ምላሹ በጣም ትዕግስተኛ እና ሆደሰፊ እንደመሆናቸወ ከሚነገርላቸው ኢትዮጵያውያን የማይገመት ነበር ያለው “ዘ ኒውዮርከ ታይምስ” በወቅቱ መብረቃዊ የሆነ አፀፋዊ ምላሽ የሰጡትን የኢትዮጵያው የወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ምናሴ ሀኃይሌ ምላሽ ‘No Dictation From Libya’ ብለው ጀመሩ ይላል፡፡

“ቀድሞ ዲስኩር ያሰማው ሰው ንግግሩ የፈላስፋ መስሏችሁ ከቁብ እንዳትቆጥሩ፡፡…የአንድ የዞረበት እና ግራ የገባው ሰው ንግግር ነው፡፡” ሲሉ ቀጠሉ “በዚህ አዳራሽ ያላችሁ የአፍረካ ርዕሳነ ብሔራት እና ርዕሳነ መንግስታት፤በተነሣው ርዕስ ላይ ማናችሁም በሊቢያ ቀጥተኛ ትዕዛዝ ትቀበላላችሁ ብዬ አላምንም፡፡ሊቢያ የቱን ያህል አማላይና የተትረፈረፈ ሀብት ቢኖራትም አፍሪካ ለሽያጭ የቀረበች ቁስ አይደለችም። የሊቢያ ሀብት ለአፍሪካውያን ምናቸውም ነው፡፡ ” ሲሉ ጠንካራ ቅስም ሰባሪ ምላሽ ሰጡ፡፡አዳራሹ በጭብጨባና ጩኸት ተሞላ።

አክለውም የኢትዮጵያን አቋም በግልፅ እንዲህ በድፍረት አስቀመጡ “ሊቢያ ከነዳጅ የምታገኘው 13 ቢሊየን ዶላር ዓለምን ለመቀየር በቂ ይመስላታል።” በማለት የኢትዮጵያ የአፍሪካ መዲናነት መለወጥ እንደማይችል የወቅቱ ደፋር እና የአድዋ ልጅ መሆናቸውን ያስመሰከሩበትን ንግግር አደረጉ። ይህንኑ ታሪክም ዘ ኒውዮርከ ታይምስ ለታሪክ እንዲቀመጥ አድርጎታል።
ይህ የዶክተር ምናሴ መርህ አዘል ንግግር በመድረኩ ብቻ ተቀብሮ አልቀረም።የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ እንደሚባለው ኢትዮጵያ ዛሬም ድረስ በአፍሪካና በዓለም ጭቁን ህዝቦች ፊት በአርአያነት ለመታየትና ለአፍሪካውያንም የቁርጥ ቀን ቤታቸው ልትሆን የቻለችው ትናንት በተከፈለው ዋጋ ነው። የትናንቱ ዋጋ ለዛሬ መሰረት ሆኖ ነገ እንዲገነባባት አድርጓል፡፡ የአፍሪካ ህብረት መዲና መሆንም እንዲሁ በዋዛ ያልተገኘ እና በየጊዜው እጅግ የከበረ ዋጋ የሚከፈልበት መሆኑ በታሪክ አጋጣሚ የሚከሰቱ ክስተቶች ማሳያ ሆነው አልፈዋል፡፡ እዚህ ላይ ትናንት የህብረቱ መቀመጫ በኢትዮጵያ እንዲሆን ለማድረግ ዶ/ር ምናሴ ኃይሌ እና ጓዶቻቸው ገጥሟቸው የነበረው ፈተና ራሱን በታሪክ የደገመበትን አጋጣሚ እናንሳ፡፡

የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በቶጎ ሎሜ በ1991 ዓ.ም ለህብረቱ ስብሰባ ታድመዋል። ይኸው በትውልድ መፈራረቅ ያልተገታው ጥያቄ በቶጎ ሎሜ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ላይ ከመቃብር ተነስቶ ብቅ አለ። ለውይይት ከቀረቡ አጀንዳዎች በ24 ኛ ደረጃ ላይ የአፍሪካ ህብረት መዲናነትን ከአዲስ አበባ እንዲነሳ በወቅቱ አንድ ጉዳይ ሆኖ መጣ። ኢትዮጵያን ወክለው በመድረኩ የተገኙትት አቶ መለስም ለአጀንዳው መልሳቸው የእነዶክተር ምናሴ ኃይሌ አርአያነትን የተከተለ ነበር፡፡ “….በአፍሪካ ጉዳይ መንግስቱ ኃይለማርያም ልክ እንደቀዳማዊ ኃይለስላሴ ሁሉ የፀና አቋም ነበረው፡፡ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ያላት ቁርጠኝነት መንግስታት በተለዋወጡ ቁጥር የሚቀየር አይደለም፡፡” ሲሉ አፅንኦት ሰጥተው መድረኩ ላይ ተናገሩ።

ይህን የመለስ አባባል ከባለታሪኩ ዶ/ር ምናሴ ሀይሌ ስም ትርጉም ጋር ስናሰናኘው ስምና ግብራቸው የገጠመላቸው ሰው ያስብላቸዋል፡፡ በቅዱስ መፅሀፍ ምናሴ፦ማስረሻ የሚል ትርጉም አለው፡፡ ለዘመናት እኛ ኢትዮጵያውያን ስርአት መጥቶ ስርአት ሲተከል በውስጥ ጉዳያቸው መለያየታችን ያለና የኖረ ቢሆንም በአፍሪካ ጉዳይ ዶ/ር ምናሴ ኃይሌና ባልደረቦቻቸው በዘመናቸው ለሀገራቸው የከፈሉት ዋጋ በዓለም መድረክ የውስጥ ልዩነታችንን ያስረሳ ተብለው ቢገለፁ የሚያንስባቸው አይሆንም፡፡ ህያው ሥራቸው በርዕዮትም በግብርም በማይመስሏቸው የኢትዮጵያ መሪዎች መመስከሩም ይህንኑ ያስረዳል፡፡

ይህ ሁሉ ሀገራዊ አበርክቶ ግን በምስጋና አልተቋጨም። ጊዜ ሲለወጥ ነገሮችም አብረው ተቀየሩ። አንዱ ሾተል የሆነው የታሪክ አካልም በ1966 አብዮት ብቅ አለ። በወቅቱ በሀገራችን የተካሄደውን የ1966 ቱ አብዮት ተከትሎ ዶ/ር ምናሴ ከስልጣን ለቀቁ።

ከስልጣን በኋላ ዶ/ር ምናሴ ኃይሌ ስለነበሩበት ሁኔታ ቤተሰቡን በቅርበት የሚያውቁት ዶ/ር ጌታቸው ተድላ እንዲህ ያስታውሱታል።”በወቅቱ ዶ/ር ምናሴና ቤተሰባቸው ሜክሲኮ አካባቢ በሚገኘው ትምባሆ ሞኖፖል በታች ቪላ ተከራይተው ይኖሩ ነበር።እኔ ስለቤተሰቡ የማስታውሰው ልጅ እያለን ወ/ሮ አይሬስ ሀይሌ እሁድ እሁድ በራቸው ላይ ብስኩት ይሰጡን ነበር። ወይዘሮ አይሬስ መልከ መልካም ጥቁር አሜሪካዊት እናት ነበሩ።ሁለት መንታ ወንድ ፣አንድ ሴት እና ሌላ አንድ ወንድ ልጅ ነበራቸው።መንቶቹ ዴቪድ እና ዳንኤል ሲባሉ።ሴቷ ሱዛን የመጨረሻው ወንድ ልጅ ስም ማይክ ነው።ሶስቱም ወንዶች ፕሮፌሽናል ዶክተሮች ናቸው ።ሴት ልጃቸው ሱዛን የአባቷን ፈለግ በመከተል የጥብቅና ሙያ ላይ ታገለግላለች። ዶ/ር ምናሴን ደርግ አንድ አመት ከሁለት ወር አስሯቸዋል።ልክ መስከረም 1ቀን ተፈቱ።ኮሎኔል ዳንኤል አስፋው ከ4ኛ ክፍለጦር ወደቤተ-መንግስት ወሰዳቸው።ከዚያም ተፈቱ። እንደተፈቱም ኒውዮርክ መሄድ እፈልጋለሁ ሲሉ ልቀቋቸው ይሂዱ የተከበሩ ሰው ናቸው አለ።ወደአሜሪካ ሄዱ ።” በማለት ዶክተር ጌታቸው መስክረዋል።

ከእስር እንደተፈቱ ህይወታቸውን በስደት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ መምራት ቀጠሉ። በስደት እያሉ ህይወታቸውን በአላማ መምራታቸውን አላቆሙም።በተግባር የቀሰሙትን እውቀት በትምህርት ማካፈል ጀመሩ። በቀዳሚነት የማስተማር ስራ የጀመሩት ደግሞ በቪላኖቫ ዩንቨርስቲ ሲሆን ከጥቂት ቆይታ በኋላ ወደኒውዮርክ በማቅናት ካርዶዝ ዩኒቨርሲቲ ለ26 ዓመታት በማስተማር እና በተለያዩ የህግ፣በዲፕሎማሲ እና የአፍሪካ ሉአላዊነት ጉዳዮች ላይ ጥናቶችን ሲያሳትሙ ቆይተዋል።

ዶ/ር ምናሴ ኃይሌ እንዳሰቡት የኖሩ፣በታላቅ ክብር ፣በማይናወፅ ትጋት እና በኢትዮጵያ ጥልቅ ፍቅር እንደተነደፉ በ95 ዓመታቸው የህይወታቸው ጉዞ ተፈፅሟል።ዶ/ር ምናሴ ከወ/ሮ አይሪስ ሀይሌ ጋር 71 አመት የትዳር ህይወት ነበራቸው።ከትዳር አጋራቸውም አራት ልጆችን ያፈሩ ሲሆን ጠቃና የህግ ምሩቅ የሆነችው ሱዛን ሀይሌን ፣ዶ/ር ዳዊት ፣ዶ/ርዳንኤል ፣ዶ/ር ሚካኤል ሀይሌ እና 8 የልጅ ልጅ እና የአንድ የልጅ ልጅ ልጅ ቅድም አያት ነበሩ።

የአሁን ዲፕሎማቶች ከዶ/ር ምናሴ ሀይሌ ምን ይማሩ?

ክቡር አምባሳደር ነብዩ ተድላ

“አንድ ዲፕሎማት በየትኛውም ጊዜና ወቅት የሃገሩን ጥቅም ከማስከበር አኳያ ስትራቴጂክ የሆነ ትዕግስት ባለቤት ሊሆን ይገባል ተብሎ ይታሰባል። በዲፕሎማሲ አንዳንድ ጊዜ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች በአጭር ጊዜ የማይገለፅ ውጤት ላይኖራቸው ይችላል።ስለዚህ በዲፕሎማሲ ረዥሙን ጨዋታ መጫወት የሚችል ስትራቴጂክ ትዕግስት እንዲኖረው ከአንድ ዲፕሎማት ይጠበቃል።በዚህ ሂደት መቼ የወደፊት ርምጃ ማድረግ ያስፈልገኛል።
መቼስ ወደኋላ ልመለስ ያስፈልጋል።እርምጃ ማድረግ አለብኝ የለብኝም የሚለውን ማወቅ አስፈላጊ ነው ።

ሁለተኛ የታሪክና የባህል ጥልቅ ግንዛቤ ሊኖረውም ይገባል። ይህ ሲሆን አንድ ዲፕሎማት ውጤታማ ዲፕሎማሲ ይሰራል ተብሎ ይታመናል።

ሶስተኛው ከቋንቋ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ያሉ ክህሎቶችን መረዳት ነው።ዶ/ር ምናሴም ባየነው የድርድር መድረክ ላይ በአጭር አገላለፅ በተመጠነ ቋንቋ የሀገራቸውን ጥቅም ያስጠበቁበትን ሁኔታ ማየት ይችላሉ።

በመሠል የድርድር እና ምክክር መድረኮች የሀገርን ጥቅም ሊጎዱ የሚችሉ ነገሮች ሊከሰቱ ይችላሉ።ችግሮች ሲከሰቱ መደናገጥና ስሜታው መሆን ሳይሆን በተረጋጋ ሁኔታ ለተነሣ ጉዳይ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል።አስፈላጊ ሲሆን ተግሳጽ መስጠት ጭምር እንደሚያስፈልግ መማር ይቻላል።ይህን ከቀደሙ በሳል ዲፕሎማቶች መማር የምንችለው ነው።”ብለዋል

አምባሳደር ብዙነሽ መሠረት “ስለ ዶ/ር ምናሴ ኃይሌ ብዙ የምናነሳውቸው ነገሮች አሉ።በእርሳቸው ዘመን በነበረው ዲፕሎማሲ እና የውጭ ጉዳይ ሥራ አመራርነት ሁሉንም አንስቶ መጨረስ አይቻልም።የ10ኛውን የአፍሪካ አንድነት ክስተት መነሻ አድርገን ትውልድ ሊማር የሚችለው ከምንም ነገር በፊት የሀገርን ጥቅም ማስቀደም፣ ሀገርን ሊጎዳ የሚችል ነገር ሲገጥም ለሀገር ቆፍጠን ብሎ መቆምን አስተምረዋል።

በአሁኑ ጊዜ የሚነገር ነገር አለ። በሀገር ጉዳይ የሀገር ጥቅምን ቆፍጠን ብሎ መናገር እና ማስከበርን ብዙ እንማራለን ።ሌላው የሚፈጥረው ስሜት አለ መለስ ብሎ እንዲህ አይነት ጉዳይ ሲታይና ሲነበብ የሚፈጥረው ስሜትና የሀገር ፍቅር የበለጠ ይቀሰቅሳል።ትውልድም ከዶ/ር ምናሴ ይህን ይማራል ብዬ አምናለሁ።” ብለዋል አምባሳደር ብዙነሽ መሠረት።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *