የ7ኛው የዕንቁ እና ንቁ ሴት ተሸላሚ

ተዋናይ፣ ገጣሚ፣ ደራሲና አዘጋጅ ዓለም ፀሐይ ወዳጆ ገና የ13 ዓመት ልጅ ሆና ነው ወደ ጥበቡ ዓለም የዘለቀችው። 

ወደ መድኃኒ ዓለም ሁለተኛ ደረጃ ትቤት ስትዛወር ከትወናና ከሥነ-ፅሑፍ በተጨማሪ የተማሪዎች መማክርት ጉባዔን በመምራት ትምህርት ቤቷንና ሀገሯን በመወከል ውድድርና ስብሰባዎችን በመሳተፍ ውጤት ታስመዘግብ ነበር።
በብሔራዊ ቴአትር ቤት የሚሰጠውን የቴአትር ጥበብ ትምህርት በመሳተፍ ከህዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊነት የቴአትር ክፍል ኃላፊ እንዲሁም የፕሮግራምና ፕሮዳክሽን የሥራ መሪ በመሆን አገልግላለች። የተውኔት ሙያተኞች ማህበርን በመመሥረትና በመምራትም ከፍተኛ አስተዋፅዎ አድርጋለች።

በኢትዮጵያ የሕፃናት ቴአትርን አስፈላጊነት በመግለፅና በመመሥረት የውጭ ባለሙያዎችን በመጋበዝና ለመጀመሪያ ጊዜ የሕፃናት ቴአትርን በማቅረብ የተለያዩ ጥናቶች እንዲደረጉና ክፍሉ እንዲጠናከርም አድርጋለች። 

በሕፃናት ማሳደጊያ ለሚገኙ ሕፃናት የኪነ-ጥበብ ሥልጠና በመስጠትና በኋላም የሕፃናት አምባ ሲቋቋም ወደሥፍራው በመመላለስ ሕፃናቱ ከመደበኛ ትምህርት በተጨማሪ በኪነ-ጥበብ ታንፀው እንዲያድጉ አድርጋለች። ሕፃናቱንም ለአገር አቀፍና ዓለምአቀፍ ዝግጅቶች እንዲሳተፉ አብቅታለች።

በትወና ሙያ እጅግ በርካታ ተውኔቶችን ከመጫወቷ ባሻገር፣ የመድረክ ሙሉ ቴአትሮችን ፅፋ ለእይታ ያበቃችና የመጀመሪያዋ የሴት የመድረክ ቴአትር አዘጋጅም ናት።

በአገሪቷ ስመ ጥር ለሆኑ ድምፃውያን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የዘፈን ግጥሞች የፃፈች ስትሆን የእራሷን  ሁለት የግጥም መድብሎች፣ አንድ የግጥም CD ፣ ሁለት የመድረክ ቴአትሮች ቪዲዮ፣ እንዲሁም በአራት የጋራ የፀሐፊያን ስብስብ ሥራዎች ( ሁለቱ በእንግሊዘኛ) ተሳትፋለች። ከተውኔት የፅሑፍ ሥራዎቿም ውስጥ አንዱ በእንግሊዝኛ ተተርጉሞ  በደቡብ ካሊፎርንያ ዩኒቨርሲቲ በዕውቅ ተዋንያን ለመድረክ ዕይታ ቀርቧል። 

በሰሜን አሜሪካ ቆይታዋም የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ማህበርን በመመሥረት ቀጥሎም ጣይቱ የባሕልና የትምህርት ማዕከልን በማቋቋም ከፍተኛ ውጤት ያስገኙ የጥበብ ሥራዎችን ከማበርከቷም በተጨማሪ ወጣት ተዋንያንንና ገጣሚያን ለውጤት አብቅታለች።ድርጅቱ ከኢትዮጵያውያን አልፎ የአፍሪካንና ዓለም አቀፍ ገጣሚያንን በመድረክነት አገልግሏል ። የመጀመሪያውን የአማርኛ ቤተ-መፃሕፍት በመክፈትና ከ60 በላይ ቴአትሮችን በማዘጋጀት በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች፣ በካናዳ በአውሮፓና በአውስትራሊያ በመዘዋወር ለጥበብ አፍቃሪው በማቅረብና መሰል ድርጅቶችን በማቋቋምና ድጋፍ በመስጠት ዕድሜዋን ለሙያዋ ያዋለች ናት። በእነዚህም ታላላቅ ተግባራት ምክንያት ከመንግሥት ተቋማት፣ ከሕዝባዊ ድርጅቶች ከ63 በላይ ሽልማቶችንና የምሥክር ወረቀቶችን አግኝታለች።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *