የሸዋሉል መንግስቱ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ፣ የሚድያ እና የድርሰት ሠዎችን የህይወት ታሪክ በመሠነድ ላይ እንደሆነ ይታወቃል። ከዚህ ቀደም መዝገበ- አእምሮ በሚል ርዕስ የ180 የሚድያ ሰዎችን ታሪክ በመጽሀፍ ለህትመት አብቅተን ማሠራጨታችን አይዘነጋም ። ቅፅ 2 ላይ የህይወት ታሪካቸው ከሚሰነድላቸው መካከል የሸዋሉል አንዷ ነች።
የሸዋሉል መንግስቱ ገጣሚ እና ዜማ ደራሲ ጋዜጠኛ እንዲሁም ፀሃፊ ተውኔት ነበረች፡፡ገና በ32 ዓመት ዕድሜዋ ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለየችው።
ውልደት በያኔው አጠራር ምሥራቅ ሃረርጌ ጃርሶ (ኤጀርሳ ጎሮ) አካባቢ በ1937 ዓ.ም ነው ፡፡የሸዋሉል ለእናቷ ብርቅዬ እና ብቸኛ ልጅ ነበረች፡፡ ይሄም የሆነበት ምክንያት ምን እንደሆነ ሲገለፅ የፈረንሳዊው ተመራማሪ ፍሬደሪክ ማርቴል ደረስኩበት እንዳለው የሸዋሉል እናት ልጅ መውለድ ተስኗቸው ከቆዩ በኋላ በአርባ ስድስተኛ ዓመታቸው ላይ ማህፀናቸው ለምልሞ ሴት ልጅ እንደ አገኙ ስሟንም ‹‹ የሸዋሉል ›› እንዳሏት ይገልፃል፡፡ብዙዎች በስሟ አጠራር ዙሪያ ጥያቄዎችን ያነሱ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ አንድም ሴት በወቅቱ በዚህ ስም የማትጠራ በመሆኑ ነው፡፡ልዑል የሚለው ስያሜ የሚሰጠው ለወንድ እንጂ ለሴት ባለመሆኑ ነው ብዙዎች ሲጠሯት ‹‹የሸዋልዑል መንግስቱ›› እያሉ ሲሆን እርሷግን ስሟን በፅሁፍ በምታሰፍርበት ጊዜ ‹‹የሸዋሉል መንግስቱ›› በማለት ነበር።
ትምህርቷን ተወልዳ ባደገችበት ምሥራቅ ሀረርጌ ጃርሶ (ኤጀርሳ ጎሮ) አካባቢ ሲሆን ከሥነ-ፅሁፍ ጋር የነበራት ትውውቅም ገና በ10 ዓመቷ ነበር፡፡የመጀመሪያው የድርሰት ሥራዋም ‹‹ የኢዮብ ትዕግስት›› የተሰኘ ድርሰቷ ሲሆን ከ 9 ዓመታት በኋላ ማለትም በ19 ዓመት እድሜዋ ጥቂት መሻሻያ ተደርጎበት በኢትዮጵያ ሬዲዮ ‹‹ የትያትር ጊዜ›› በተባለ ፕሮግራም ላይ ተላልፎላታል፡፡ይህ ሥራም በድርሰት ዓለም የመጀመሪያው ሥራዋ ነው፡፡ሌላኛው ፈረንሳዊው ተመራማሪ ፍሬድሪክ ማርቴል ደግሞ እንዲህ ይለናል፡፡”..የሸዋሉል.. ግጥም ፅፋ ህዝብ በተሰበሰበበት ያቀረበችው ገና በስምንት አመቷ ነበር፡፡አጋጣሚውን ሲገልፅም የቀዳማዊ ኃይለስላሴ የትወልድ ሃገራቸው የሀረርጌ ኤጀርሳ ጎሮ ጉብኝት ነበር፡፡ የሸዋሉል ንጉሱ ፊት ቀርባ ግጥም አንብባ የሃምሳ ብር ሽልማት አግኝታለች በማለት ይገልፃል፡፡ ወይ ሆቢ ሆቢ ለድምፃዊ አሊ ቢራ ያበረከተችው ብዙዎች የወደዱላት አይረሴ የሙዚቃ የግጥም ስራዎቿ ነው፡፡የሸዋሉል መንግስቱ ሙዚቃ ዘሃረር የተባለ መፅሄትንም በማዘጋጀት ትታወቃለች። በጊዜውም የ27 ዓመት ወጣት ነበረች፡፡
የሸዋሉል መንግስቱ ብዙ ጊዜዋን ያሳለፈችው በሀረርጌ ፖሊስ ማስታወቂያ ክፍል በየሁለት ወሩ የሚታተመውን “የምስራቅ በረኛ” መፅሄትን በማዘጋጀት ነበር፡፡በዚህ ክፍል ለሀረር ምስራቃዊ ሰጎን ኦርኬስትራ አያሌ ግጥሞች እና ዜማዎችን ቲያትሮች እና ዝማሬዎችን ታዘጋጅ ነበር፡፡ካዘጋጀቻቸው ቲያትሮች ውስጥም ‹‹ሰው መልዓክ ሆነ እንዴ?›› የሚል ሥራዋን ብዙዎች ያስታውሱታል፡፡በሀረር ቆይታዋ በትርፍ ጊዜዋ ለኢትዮጵያ ሬዲዮ መረጃዎችን በማከፈል የምታገለግል የነበረ ሲሆን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ፅሁፎችን ትልክም ነበር፡፡
በ1962 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የታተመላት ፅሁፍ ‹‹ሴቶች ብሄራዊ ስሜት ይኑራቸው›› የሚል ነበር፡፡የሸዋሉል መንግስቱ የመፅሐፍ ደራሲም ነበረች። በ1962 ዓ.ም ተፅፎ በ1968 ዓ.ም የታተመው ‹‹ እስከመቼ ወንደላጤ›› የተሰኘ ሥራዋ በዚህ ዘመን እምብዛም የሚታወቅ ባይሆንም በዘመኑ ብዙ የተነበበ ነው፡፡ከተፃፈ 6 ዓመት በኋላ የታተተመው መፅሃፉ በብዙዎች ከመነበብ አልፎም ብዙዎችን ያነጋገረ መፅሃፍ ለመሆን በቅቶ ነበር። ይሄም ሊሆን የቻለበት ምክንያት በወቅቱ አይነሱም አይደፈሩም የተባሉ ርዕሶችን ያነሳችበት ነበር፡፡የመፅሃፉ ዋና ጭብጥ በዋናነት ስለ ጋብቻ እና ፍቺ ስለ ጾታዊ ግንኙነት እና ወንደ ላጤነት በነፃነት ያተተችበት ነው፡፡በመጽሀፏ መግቢያዎች ላይ 3 መሰረታዊ ጥያቄዎችን በማንሳት ትጀምራለች1. በወንዴ ላጤነት እስከመቼ እንሰቃያለን? 2. እጮኛነትን ምክንያት በማድረግ እስከ መቼ ማን ዘራሾች እና የሀገር ስም ሰባሪዎች የወላጆቻች አሳዛኞች እንሆናለን? 3. መግባባትን ሳናውቅ ዕድልን በማማረር እስከመቼ እንኖራለን? የሚሉ ሲሆኑ በእነዚህ ሶስት ጥያቄዎች ላይ ተመርኩዛ የራሷን ትንታኔዎች ለመስጠት ትሞክራለች።አያሌ አባባሎችና ጥቅሶችም የመፅሃፉ አንድ አካል ናቸው።
ሙዚቃና የሸዋሉል መንግስቱ
የሸዋሉል መንግስቱ በሙዚቃው ዓለም ብዙ ሰርታለች። ዘመን ተሻጋሪ የግጥም እና ዜማ ሥራዎቿ ህያው ምስክሮቿ ናቸው፡፡ለወንዶች በሰጠቻቸው ድንቅ የዘፈን ግጥሞች ምክንያት ወንዶችን ለሴቶች የፍቅር ዘፈን የምታዘፍን ይሏታል፡፡ ሴት ሆና ሳለ የአንድን አፍቃሪ ወንድ ልብ በዚህ ደረጃ መረዳት እንዴት ተቻላት? ሲሉ ብዙዎች ይገረማሉ፡፡
የሸዋሉል በትውልድ ዥረት ውስት በአንዱ የተከሰተች ልዩ የግጥም እና ዜማ ደራሲ ነበረች፡፡ የባህል ጨዋታዎችን ወደ ዘመናዊ ዘፈን ስትቀይር ደግሞ ወደር አልነበራትም።በሀገራችን የባህል ስራዎችን በዘመናዊ ግጥም እና ዜማ አድሶ የማቅረብ ብልሃትን ያሳየችን ድንቅ ከያኒ እንደሆነችም ብዙዎች መስክረውላታል፡፡በጥላሁን ገሰሰ፣ በአሊ ቢራ እና በሌሎችም እውቅ የሙዚቃ ስራዎች ውስጥ የብዕር ቀለሞቿ ደምቀው የሚታዩ ናቸው፡፡የሸዋሉል ግጥም እና ዜማ ሰጥታቸው እጅግ ከተወደዱ ስራዎቿ መካከልም የጥላሁን ገሰሰ አካም ነጉማ አንዱ ነው፡፡ሌላው የሸዋሉል የግጥም እና ዜማ ስራዎ ማደሪያ አንጋፋው ድምፀዊ መሀሙድ አህመድ ነው፡፡ እርሱ ከተጫወታቸው ሙዚቃዎች ውስጥ በግጥም ስራ የተሳተፈችባቸው ስራዎች ትዝታ ግጥም ሆሆ ገዳማይ ግጥም ስደተኛሽ ነኝ ፣ እንዴት ነው ገዳሆ ፣ አሸወይና ዜማ፣ ኧረ መላ መቼ ነው ? አታውሩልኝ ሌላ ግጥም ፣ የሸዋሉል የድርስት ውጤቶች ናቸው፡፡የሸዋሉል መንግስቱ የአንጋፋው ድምጻዊ አሊ ቢራ እና የክራሯ ንግስት የአስናቀች ወርቁን ስራዎች የመድረስ ዕድል ነበራት።
ከአሊ ቢራ ሥራዎች ውስጥም ወይ ዮቢ ዮቢ እና አዋሽ የሚሉትን ስትደርስ እህ ልበና ፣ ሰላ በልልኝ ለአስናቀች ወርቁ ሰርታለች፡፡ሌላው ትልቁ የግጥም እና የዜማ ስራዋ በዳህላክ ባንድ አጃቢነት የተሰራው እና በሙሉቀን መለሰ በ1969 ዓ.ም ዓልበም ነው፡፡በዚህ አልበም ውስጥ የተካተቱት 10 ዘፈኖች ሁሉም የሸዋሉል መንግስቱ ድርሰቶች ናቸው፡፡ዘፈኖችንም ጀመረን ፣ ህልም ሆነሽ አትቅሪ ፣ ጉብል ቀዘባ ፣ የምንጃር ሸጋ ፣ ውብ አበባ ፣ በኔ ሞት ፣ውብ አበባ ፣ ባይሽ ደስ ይለኛል መወደድሽን ብታውቂ ፣ ከሴት እሷ ብቻ ፣ ትዝታ የሚሉት ናቸው፡፡በሸዋሉል የግጥም እና ዜማ ደራሲነት ፣ በጥላዬ ገብሬ አቀናባሪነት እንዲሁም በዳህላክ ባንድ አጃቢነት እንዲሁም በታንጎ ሙዚቃ አሳታሚነት ሙዚቃው ለአድማጭ ደርሷል፡፡ በዚህ የአልበም ሙዚቃ ሽፋን ላይ የሸዋሉል መንግስቱ እንዲህ ስትል መልዕክቷን አስፍራለች ‹‹ሕይወት ሞት፣ ሃዘን፣ ደስታ፣ ፍቅር ፣ ጠብ ፣ ትዝታ ፣ ሰላም ፣ ጦርነት፣ ትግል እና ድል ብሎም ዓለም ሁለንተናዋ ይስበኛል ዜማ እንድደርስ ግጥም እንድፅፍ ይጋብዘኛል። ስለሆነም እኔና ብዕሬ የትም መቼም ከሰፊው ህዝብ ጋር ነን ›› ብዙውን ጊዜ ስትጠየቅ የምጠላው ብላ የምትናገረው ነገር አንድን ነገር ነገ አደርገዋለው ማለት ነው፡፡
የሸዋሉል ስራዎች ከሀረር እና ከአካባቢዋ አልፎ አዲስ አበባን ድፍን ኢትዮጵያን ለማዳረስ በጣት የሚቆጠሩ አመታትን አልፈጀባትም ። ሙዚቃን በሀረር በተባለ መጽሄቷ ላይ እንዲህ ትላለች ‹‹ ለዚህ መፅሄት ቁም ነገሩ ሁለት ነው። አንደኛ ልፋታችን ድካማችን በህዝብ ዘንድ አልታወቀልንም ለሚሉ የሙዚቃው አለም ሰዎች የከበረ የሕሊና ድጋፍ ለማበርከት ሁለተኛው ደግሞ የሙዚቃ ሙያ ክቡርነት በመጠኑም ቢሆን ለአንባቢያን ለማስታወስ ነው ፡፡በዚህ መጽሄት ውስጥ ከተካተቱት ድምፃውያን መካከል መርሐዊ ዮሃንስ ፣ ሲሳይ ገሰሰ ፣ ወጋየሁ ደግነቱ ፣ተስፋዬ ለሜሳ እና ሌሎች በርካቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡የሸዋሉል በአዲስ አበባ በቆየችባቸው ጥቂት ጊዜያቶች ውስጥ በርካታ ሥራዎችን ሠርታለች። በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን በዜና አንባቢነት በፕሮግራም አዘጋጅነት እና በሬዲዮ ድራማ ፀሃፊነት ሰርታለች፡፡በደርግ ዘመን በቀበሌ ሊቀ መንበርነት ያገለገለች ሲሆን በወቅቱም የመኢሶን አባል ነበረች፡፡እረጅሙ ጉዞዋን በአጭሩ የቀጨባትም የያኔው ትውልድ የፖለቲካ እንካ ሰላምታ ነው ።የሸዋሉል መንስግቱ የ5 ልጆች እናት ስትሆን ግንቦት 1969 ዓ.ም ነው ከዚህ ዓለም በሞት የተለየችው።