የዛሬ 30 ዓመት ህይወቱ ያለፈው ጋዜጠኛ ጌታቸው ኃይለማርያም በሙያ ባልደረቦቹ የማስታወሻ ዝግጅት ሊደረግለት ነው፡፡
ጌታቸው ኃይለማርያም
የፊታችን እሁድ መስከረም 12 2017 ዓ.ም ከቀኑ 8 ሰአት ጀምሮ በወመዘክር አዳራሽ በሚከናወነው በዚህ ዝግጅት፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሬድዮ እና ቴሌቪዥን ባልደረቦች ይታደማሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡
የማስታወሻ ዝግጅቱ ሀሳብ አመንጪ እና አዘጋጅ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ሲሆን በዕለቱም ጋዜጠኝነትን የሚያጠኑ ተማሪዎች በመሰናዶው ላይ ይገኛሉ፡፡
አንጋፋው ጋዜጠኛ ጌታቸው ኃይለማርያም፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬድዮ በጠቅላላው ከ 24 ዓመታት በላይ ያገለገለ ጋዜጠኛ ነበር፡፡ በተለይም በዜና አቀራረብ እና አንባቢነት ለብዙዎች አርአያ የሆነም የሚከበር ጋዜጠኛ ነበር፡፡
በማስታወሻ ዝግጅቱ ላይ፣ ስለ ጌታቸው ምስክርነት የሚሰጡት ጋዜጠኛ ሚሊዮን ተረፈ ፤ ጋዜጠኛ ዋጋዬ በቀለ እና ጋዜጠኛ ታዬ በላቸው ሲሆኑ በተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን የተዘጋጀ የ20 ደቂቃ የድምጽ ዘጋቢ ሥራም እንደሚደመጥ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የሚድያ ሰው ጌታቸው ኃይለማርያም፣ አሁን በአንጋፋነታቸው እውቅና የተቸራቸውን እንደ ነጋሽ መሀመድ፣ አለምነህ ዋሴ፣ ንግስት ሰልፉ እና ብርቱካን ሀረገወይንን የመሰሉ ባለሙያዎች ለሙያዊ ብቃት እንዲደርሱ በማሰልጠን እና ልምዱን በማካፈል የበኩሉን የተወጣ ባለሙያ ነበር፡፡ ዜና ፋይል የተሰኘውን ፎርማት ለመጀመረያ ጊዜ እንዳስተዋወቀ እና እንደፈጠረ የሚነገርለት ይህ ሰው በብስራተ ወልጌል የሬድዮ ጣቢያም ሙያዊ አደራውን ሲወጣ ነበር፡፡
ታላቁ የሚድያ ሰው ጌታቸው፣ ከዚህ ቀደም ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ባሳተመው ‹‹መዝገበ አእምሮ የሚድያ ሰዎች ኢንሳይክሎፒዲያ›› ላይ ታሪኩ የተሰነደለት ሲሆን ከዚህ ቀደም ያነበባቸው ዜናዎች እና ምስሎቹም ወግ በያዘ መልኩ ለታሪክ እንዲቀመጥለት ተደርጓል፡፡
ይህ የማስታወሻ ዝግጅት እውን እንዲሆን የጋዜጠኝነት መምህር አብርሀም ጸሀዬ እና ስብሀቲዝም ቡድን አባላት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በተጨማሪም የተወዳጅ ሚድያን የስነዳ ሀሳቦች ምንግዜም የሚደግፈው ታሜሶል ኮምዩኒኬሽን (ሰለሞን ከበረ) የዝግጅቱ ተባባሪ በመሆን አለኝታነታቸውን አሳይተዋል፡፡
የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን መስራች ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ከዚህ ቀደም የ45 ሰዎችን ታሪክ በሲዲ፣ የ20 ሰዎችን የህይወት ታሪክ በመጽሀፍ ያዘጋጀ ሲሆን ባለሙያዎች በህይወት እያሉና ካለፉም በኋላ ስማቸው በድምቀት መነሳት አለበት የሚለውን ዓላማ አንግቦ በመነሳት እስከዛሬ ከ 30 በላይ ሁነቶችን ለማዘጋጀት በቅቷል፡፡