አንተነህ ድፋባቸው
ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እናስተዋውቃለን፡፡ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡
ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ6 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ከድርሰት እና ስነጽሁፍ ዘርፍ ታሪኩ የሚቀርብለት ሰው አንተነህ ድፋባቸው ይሆናል፡፡
ትውልድና ልጅነት
አንተነህ ድፋባቸው ይባላል፡፡ የተወለደው በአዲስ አበባ ልዩ ቦታው የካ ሚካኤል በሚባለው አካባቢ ሲሆን ከእናቱ ከወ/ሮ አልጋነሽ ይመር እና ወልዶ ካሳደገው አባቱ ከአቶ ድፋባቸው ወልዴ ነበር ወደዚህች ምድር የተቀላቀለው፡፡
የልጅነት ኑሮ
እናቱ ወ/ሮ አልጋነሽ የተረጋጋ የትዳር ህይወት አልነበራቸውም፡፡ከባለቤታቸው ከአቶ ድፋባቸው ጋርም የነበራቸው የትዳር ህይወት ባለመዝለቁ ምክንያት በማይመች ሁኔታ በአዲስ ሠፈር መብራትና ውሀ በሌለበት አካባቢ (ቤት) የዱር አራዊት (ጅብ) በሚንቀሳቀስበት አካባቢ አጥር በሌለው ሁኔታ የተመቸ ሥራ ባልነበራት እናት ሥራ ስትሄድ ልጅዋን የሚጠብቅላት ባልነበረበት ሁኔታ አቶ ድፋባቸው ከአልጋነሽ ያገኙትን የአንድ ወር ጨቅላ ጥሎላት ጠፋ፡፡
የአንተነህ እናት ወ/ሮ አልጋነሽ በጊዜው የሚሠሩት በምግብ ማደራጃ ውስጥ የፅዳት ሥራ በመሆኑ ይከፈላቸው የነበረው ደመወዝ በወር ብር 40 ብቻ በመሆኑ ሁለት ልጅ ለማሣደግ ችግር ሆነባቸው፡፡ በጊዜው አንተነህን ከሌላ ለተወለደው የስድስት ዓመት ልጅ ለታምሩ ትተው መሄድ ግድ ይላቸው ነበር፡፡
በችግር ውስጥ ማደግ
አንተነህ በብዙ ችግር ውስጥ እያደገ ወንድሙን ጨዋታ ሲያታልለው ትቶት ሲሄድ ህፃን አንተነህ እየጠፋበት ቁጥቋጦ ውስጥ እንቅልፍ እያንቀላፋ ከቤታቸው ጀርባ ባለው የድንጋይ ካባ ውስጥ እየተኛ ዳዴ እያለ የኮሽም አጥር ውስጥ እየተኛ ዝናብ ሲመጣም እየተደበደበ እናቱ ከሥራ ስትመጣም በቁጥቋጦው ፈልጋ እያገኘችው በዚህ ሁኔታ ማደጉን ቀጥሎ መጠንከር ሲጀምርም በብዙ ችግርና ስቃይ አደገ፡፡
አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ቤት
እድሜው አራት ዓመት ሲሆን በአቅራቢያው ወደሚገኝ የቄስ ትምህርት ቤት ገብቶ መከታተሉን ቀጠለና የቄስ ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ እድሜው ሰባት ዓመት ሲሆነው መገናኛ በሚገኘው ዘርፈሽዋል (ምስራቅ በር ቁጥር 1) የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት መማር ጀመረ፡፡ ከዘርፈሽዋል ት/ቤት እስከ ስምንተኛ ክፍል ከተማረ በኋላ የስምንተኛ ክፍልን የብሄራዊ ፈተና ውጤቱ ጥሩ ባለመሆኑ ወደ ዘጠነኛ ክፍል መዘዋወር ባለመቻሉ ምክንያት ስምንተኛ ክፍልን ደገመ፡፡ ስምንተኛ ክፍልን በድጋሚ የተማረው ዘርፈሽዋል ሳይሆን እንግሊዝ ኤምባሲ አካባቢ በሚገኘው ደጃዝማች ቢትወደድ ት/ቤት ነበረ፡፡
በደጃዝማች ቢትወደድ ት/ቤት ለአንድ ዓመት ያህል ትምህርቱን ከተከታተለ በኋላ በድጋሚ የብሔራዊ ፈተና ተፈትኖ ጥሩ ውጤት በማምጣት ወደ ዘጠነኛ ክፍል ተዘዋወረ፡፡ አንተነህ ዘጠነኛ ክፍል (ሃይ ስኩል) ትምህርቱን ለመከታተል ወደ ምስራቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተመድቦ ለአንድ ዓመት ያህል ትምህርቱን ከተከታተለ በኋላ በኢትዮጵያ አዲስ የትምህርት ፖሊሲ በመቀየሩ ምክንያት በ1992 ከምስራቅ አጠቃላይ ት/ቤት ወደ ኮከበ ፅባህ ትምህርት ቤት በመቀየር የ10ኛ ክፍል ትምህርቱን በ1993 ዓ.ም በኮከበ ፅባህ ት/ቤት በመከታተል በጊዜው የትምህርት ፖሊሲው በመቀየሩ የሁለተኛ ደረጃ የብሄራዊ ፈተና ከ10ኛ ክፍል በመደረጉ ምክንያት በ1993 ዓ.ም የብሔራዊ ፈተናውን ወስዷል፡፡
ራስን ለመቻል የተደረገ ሙከራ
የሁለተኛ ደረጃ የብሄራዊ ውጤት ሲጠባበቅም ከቆየ በኋላ ውጤቱ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ባለመሆኑ ምክንያት ራሱን ለመለወጥ በመንፈሳዊ ህይወት ውስጥ ከሚያውቀው አንድ ጓደኛው ጋር ዶሮ ለማርባት ተነጋግረው ተስማሙ፡፡ በሀሳብ የተነጋገሩትን በተግባር ለመቀየር በመስማማታቸው የዶሮ ቤትን በጓደኛው በአሸናፊ ቤት ለመሥራት ዝግጅታቸውን አጠናቅቀው የአሸናፊ ቤት ከአዲስ አበባ ወጣ ያለ ቦታ በመሆኑ ብዙ ዋጋ ከፍለው ከጫካ እንጨት እየቆረጡና ከሠዎች የተወሰነ የ300 ብር ድጋፍ አግኝተው የዶሮ ቤቱን ሰሩ፡፡ የዶሮ እርባታው እንደጠበቁት ሳይሳካ በመቅረቱ ወይም ዶሮዎቹ በሸለመጥማና በዶሮ በሽታ በማለቃቸው ምክንያት አንተነህ ሌላ ሥራ ለመፈለግ ወሰነ፡፡
በረዳት ኬክ ጋጋሪነት ተቀጥሮ ለመሥራት በወር 130 ብር ለመሥራት ተስማማ፡፡ በዚህ ኬክ ቤት፤ ኬክ ጋጋሪው ሙያ ሊያስተምረው ፈቃደኛ ባለመሆኑ ሌላ ሥራ ለመቀየር ወስኖ በጊዜው በማያውቃቸው ባልና ሚስቶች ቤት በቤት ሠራተኝነት በወር 260 ብር ለመቀጠር ወሰነ፡፡ ይህን የቤት ሠራተኝነት የሠራው የምግብ ዝግጅት ትምህርት ለመማር ጅማሮ ስለነበረ ለትምህርት ቤቱ ክፍያ እንዲያግዘው ስለፈለገ ነበር ዋጋ የከፈለው፡፡
ለአራት ወራት ያህል የግለሰቦች ቤት በቤት ሠራተኝነት ከሠራ በኋላ ትምህርቱንም በማታው ፈረቃ ይከታተል ስለነበረ በኤል ኤም ኢንተርናሽናል ኮሌጅ በ1996 ዓ.ም አጠናቅቆ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ ልደት አዳራሽ በዲፕሎማ ተመረቀ፡፡
የምግብ ስራ እና ግለ-ታሪክን ማሳተም
ከኤልኤም ኢንተርናሽናል ኮሌጅ በምግብ ዝግጅት ዲፕሎማውን ከያዘ በኋላ የተግባር ልምምድ ለማድረግ (አፓረንትሺፕ) ወደተለያዩ ሆቴል በመጠየቅ በአክሱም ሆቴል አዲስ አበባ አክሱም ሆቴል በወር 450 ብር እየተከፈለው እንዲሠራ እድሉን በማግኘቱ ለአንድ ዓመት ያህል ከሠራ በኋላ በአክሱም የነበረውን ቆይታውን በሰላም ጨርሶ ሌላ ሥራ በማፈላለግ ወደ አርኮባሊኖ ሬስቶራንት በተባለ ሬስቶራንት በዋና ሼፍነት እየሠራ ባለበት ሁኔታ በዛው በአርኮባሊኖ ውስጥ በተፈጠረ እድል ወደ አፍሪካ ህብረት በመዘዋወር ለተወሰነ ዓመታት ከሠራ በኋላ የተሻለ እድል አግኝቶ ወደ አንድ አዲስ ወደተከፈተ ሆቴል በማቅናት ልምዱን በአዶት ቲና ሆቴል በጁፒተርና በተለያዩ ሆቴልና ሬስቶራንቶችን በማደራጀት በማሰልጠን ቅዳሜና እሁድን ደግሞ ኬተሪንግ አገልግሎት በመስጠት ገቢውን ለማሳደግና እውቀቱንም ለማዳበር ችለዋል፡፡
አንተነህ በዚህ ሁኔታ ከገፋ በኋላ በተለያዩ ቦታዎች ባገኘው እድል ምክንያት የራሱን ሬስቶራንት በአዲስ አበባ ውስጥ ሜክሲኮ (ገነት ሆቴል) አካባቢ ከፍቶ የተወሰነ ሠራተኞችም ቀጥሮ መሥራት ጀምሮ ነበረ፡፡ የሬስቶራንቱ ሁኔታ ሰላሙን የነሳውና ነገሮች ባልጠበቁት ሁኔታ በመወሳሰባቸው ምክንያት ሥራው በእጅጉ አማሮት የግል ህይወቱም ላይ ችግር ስለፈጠረበት ሬስቶራንቱን ትቶት ሆቴል ላይ ተዋውቋቸው ወዳጅ በሆኑት አንድ ቤተሰብ ምክንያት ወደ ስፔን አቀና፡፡
ስፔን ባርሴሎና ለሁለት ሳምንታት ከቆየ በኋላ ወደ ሀገሩ ላለመመለስ በመወሰኑ ጉዞውን ወደ ጀርመን በማቅናትና በጀርመን የጥገኝነት ጥያቄ በመጠየቅ ጉዳዩን ሲከታተል ቆይቶ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ትምህርቱን በመማርና ከኢትዮጵያ የያዘውን ዶክመንት ወደ ጀርመንኛ በማስለወጥ ተሳክቶለት አሁን በጀርመን ሀገር በፊረንበርግ ከተማ አለም አቀፍ ሆቴል ውስጥ እየሠራ ይገኛል፡፡
የኮሮና ቫይረስ በዓለማችን በወረርሺኝ መልክ በመከሰቱ ምክንያት በእድሜ ዘመኑ ይመኘው የነበረውን የግለ- ታሪኩን የመፃፍ እድል (ጊዜ) በምቹ ሁኔታ በማግኘቱ ቤት የመቀመጥ ዘመቻ ላይ አንተነህ ድፋባቸው የህይወቱን ታሪክ ድንቅ አስተማሪ መፅሀፍ ፅፎ ለአንባቢ አብቅቷል፡፡ የመጽሐፉም ስያሜ ስደተኛው ሼፍ በሚል አርዕስት ባማረ ሁኔታ አበርክቶታል፡፡
ለአንተነህ ከፈጣሪም ዘንድ ልጆችም ተሰጥተውታል፡፡ ይህን ሁሉ ላደረገለት ለፈጣሪው እግዚአብሔር በህይወቱ ሁሉ በምህረት ለመራው የራራለትን ያገዘውን የረዳውን ሞገስ የሰጠውን አምላኩን እግዚአብሔርን ከልቡ አመስግኖ እንዳልጠገበ ብዙ ጊዜ ይናገራል፡፡ አሁንም ለዚህ ክብር ላበቃው ፈጣሪ ሞገስ ለሰጠው ክርስቶስ ክብር ምስጋና ይሁንለት፡፡