ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የሚድያ መሪዎችን የሙያ እና የተሞክሮ ታሪክ ለትውልድ እያስቀመጠ እንደሆነ ይታወቃል። አንዳንድ የሚድያ መሪዎች ከጋዜጠኝነት እና ከሚድያ አመራርነት ከፍ ወዳለ የመንግስት የሥራ ኃላፊነት አድገው አገራቸውን እያገለገሉ ይገኛሉ። ታሪካቸውን ከሰነድንላቸው የመንግሥት የሚድያ ኃላፊዎች መካከል ዶክተር ፍሰሐ ይታገሱ፣ ረዳት ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬ፣ የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሣ፣ የኮምዩኒኬሽን ሚኒስትሯ እናትዓለም መለስ እና አቶ ጌትነት ታደሠ ይገኙበታል። ሌሎችንም መሥራታችን ይቀጥላል ።
አሁን በዚህ ፅሁፍ ታሪካቸውን የምንሰንደው የኢቢሲ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩትን የአቶ አብዱራህማን ሩቤን ነው። እርሳቸው ፣በህክምና ሲረዱ ቆይተው”፣ ታህሳስ 15 2018 ዓ.ም ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን የቅርብ ሰዎቻቸውን በማነጋገር የሙያ ታሪካቸውን ለትውልድ እንዲቀመጥ አድርገናል። ታሪኩንም ዕዝራ እጅጉ እንደሚከተለው ሰንዶታል።
አቶ አብዱራህማን ኢቲቪ ውስጥ የተቸገረ ባልደረባ ካዩ ማለፍ አይሆንላቸውም። ታመው በነበረበት ሰዓት እንኳን ሀሣባቸው ሥራ ላይ ነበር። ህንድ አገር ህክምናቸውን ተከታትለው ከመጡ በኃላም ሻል ሲላቸው ቢሮ ለመግባት ይሞክሩ ነበር። ይህም ሥራውን ለመሥራት ያላቸውን ልዩ ተነሳሽነት የሚያሳይ ነው።
ከአቶ አብዱራህማን ሩቤ ጋር አሰላ ከሁለተኛ ደረጃ ጀምሮ አብሮ የተማረው ሙክታር ከማል እንደሚናገረው አብሮ አደጉ ከልጅነቱ ጀምሮ ለሚድያ ልዩ ፍቅር ያሳደረ ነበረ። ከሚድያ ባሻገርም ሙዚቃ ይወድ ነበር። በትምህርቱም የደረጃ ተማሪ ነበር በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷል።
“አቶ አብዱራህማን ሩቤ እንደ አለቃ ራሱን ከመኮፈስ ይልቅ የአገልጋይነት መንፈስን በመላበስ ሥራውን በትህትና እና ሰውን በማክበር ያከናውን ነበር። ይህም ከልጅነቱ አንስቶ ያሳየው የነበረ ባህሪይ ነው።” በማለት አብሮ አደጉ ሙክታር ከማል ይናገራል።
አቶ አብዱራህማን ሩቤ ማናቸው?
አቶ አብዱራህማን ሩቤ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሎዴ ሄጦሳ ወረዳ ከአባታቸው አቶ ሩቤ ከድር እና ከእናታቸው ወ/ሮ መሬና ሀጂ ከድር በ1978 ዓ.ም ተወለዱ።
አቶ አብዱራህማን ሩቤ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአርሲ ዞን ሎዴ ሄጦሳ ወረዳ የተከታተሉ ሲሆን የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በውጭ ቋንቋዎች ጥናት(በአፋን ኦሮሞ) በ1998 ዓ.ም አግኝተዋል።
ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ በኮሙዩኒኬሽን እና ሚዲያ ጥናት ተቀብለዋል።
የሚድያ ሰው አቶ አብዱራህማን ከሙያው ጋር የተገናኙ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ሥልጠናዎችንም ወስደዋል።
አቶ አብዱራህማን ሩቤ በጋዜጠኝነት የሥራ ዓለምን የተቀላቀሉት በኢቢሲ ሪፖርተር በመሆን ነበር። ጊዜውም 1999 ዓ.ም ነበር። በጊዜው 1000 ሰዎች ተመዝግበው የነበረ ሲሆን 15 ለአፋን ኦሮሞ 15 ደግሞ ለአማርኛ ሲያልፉ ከ15ቱ የአፋን ኦሮሞ አላፊ ባልደረቦች መካከል አቶ አብዱራህማን ሩቤ ይጠቀሳሉ።
ከኢቲቪ በመቀጠልም በኦሮሚያ ብርድካስቲንግ ኔትዎርክ (ኦቢኤን) ከሪፖርተርነት ጀምሮ እስከ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚነት አገልግለዋል። በቅርበት የሚያውቋቸው እንደሚናገሩት የሚድያ መሪ አብዱራህማን ሩቤ ኦቢኤን የፎርማት ለውጥ እንዲያመጣ ብሎም አዳዲስ ፕሮግራሞች እንዲቀረፁ የመሠረት ድንጋይ ያስቀመጡ ናቸው። በተለይ ከዶክተር ብርሀኑ ዖላና ጋር አንድ ላይ በመሆን ያከናወኑት ሚድያውን የማሻሻል ሥራ(reform )ሊጠቀስ የሚገባው ነው።
ከሰዎች ጋር በቀላሉ ተግባብቶ በመሥራት ጥሩ የአመራር ክህሎት ያዳበሩት አቶ አብዱራህማን ሩቤ በባልደረቦቻቸው የሚወደዱ ሰው ነበሩ።
ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ የኢቢሲ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው በሙያው የሚጠበቅባቸውን ሁሉ አድርገዋል።
“አቶ አብዱራህማን ሰውን አድማጭ እና የመፍትሔ ሰው ነበሩ። አብረን በሠራንባቸው ጊዜያት ሰው የማድመጥ ልዩ ተሰጥዖውን ማየት ችያለው ስትል የቀድሞ የኢቲቪ የመዝናኛ ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ ሀቢባ ፋሪስ ትናገራለች።
አቶ አብዱራህማን ሩቤ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በ40 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም የተለዩ ሲሆን ታህሳስ 14 2018 ኮልፌ በሚገኘው መካነ መቃብር ቀብራቸው ተፈፅሟል ።
አቶ አብዱራህማን ሩቤ ባላትዳር እና የሦስት ልጆች አባት ነበሩ።
ምስክርነት
አቶ ሙክታር ሁሴን በኢቢሲ ምክትል ሥራ አስፈፃሚና የቋንቋዎች ዘርፍ ኃላፊ ናቸው። እርሳቸው ለተወዳጅ ሚድያ በሰጡት ምስክርነት የሚድያ ሰው አብዱራህማን ሩቤ በሥራው ቦታው ላይ የሚገኝ በትጋት ብዙዎች የመሰከሩለት ባለሙያ ነበር ብለዋል።
” አብዱራህማንን ለ20 ዓመት አውቀዋለሁ ። ከኦቢኤን ጀምሮ አብረን ሠርተናል ። አብዛኛውን የሥራ ዘመኑን 13 ዓመት ያህል ያሳለፈው ኦቢኤን ነው። ከ2001 ጀምሮ ኦቤኤን ላይ ከሪፖርተርነት ጀምሮ ሲሠራ ነበር። ዶክመንተሪ በመሥራትም አቅሙን የፈተሸ ነበር” ሲሉ አቶ ሙክታር መስክረዋል።
አቶ አብዱራህማን ሩቤ በተፈጥሮ ተቋማትን የመለወጥ ክህሎት ያዳበሩ ናቸው። አንድን ቡድን መርተው ለስኬት የማብቃት ችሎታንም ያዳበሩ መሆናቸው ይነገርላቸዋል ።
“የኦቢኤን ሥር ነቀል የመዋቅር ማሻሻያ በተደረገ ጊዜ የአቶ አብዱራህማን ሚና ትልቅ ነበር።ማሻሻያው ወደ ኃላ እንዳይመለስ ቁርጠኛ አመራር የሰጠ ሰው ነው። ኦቢኤን አሁን ያለበት ደረጃ እንዲደርስ የአቶ አብዱራህማን አስተዋፅኦ ታሪክ የሚያነሳው ነው። ኢቲቪ ዶክተር ፍሰሐ ይታገሱ ጋር ነው 2014 ላይ የመጣው። ፍሰሀ ጋር በጋራ ሆነው ነበር የመሥሪያ ቤቱን የማሻሻያ ሥራ የሠሩት። በተለይ ሸጉሌ ያለው የኢቲቪ ግቢ በተገቢው መልኩ እንዲደራጅ ለፍቷል። በመሥሪያ ቤቱ ባልደረቦች ዘንድም በጣም የሚወደድ ነበር። የታመመ ጊዜም አብዱራህማን ከህመሙ እንዲሻለው ስለት የተሳሉ የኢቲቪ ባልደረቦች ነበሩ። ” ሲሉ አቶ ሙክታር ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
አቶ ሰኢድ ዓለሙ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የዜና ዕቅድ ክትትል ክፍል ዋና አዘጋጅ ሲሆኑ አቶ አብዱራህማንን ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጀምሮ ያውቋቸዋል። እንደ አቶ ሰኢድ አባባል አቶ አብዱራህማን የማድመጥ እና የትህትና ባህሪው ከዩኒቨርስቲ አንድ ብሎ የጀመረ ነው።
” ያኔ ዩኒቨርሲቲ ሳለን የማይበትን ባህሪይ ኢቲቪ ከገባንም በኃላ አይቼበታለሁ። አመራር ሆኖ ሲመጣ ደግሞ የተሻለ ውሳኔ ሰጪ ሆኖ መጣ። እርሱ አመራር ሆኖ ከመጣ በኃላ የማድመጥ ልዩ ክህሎት አዳብሮ ነበር።ይህም እንደ አመራር ጠንካራ እንዲሆን የረዳው ይመስለኛል።” በማለት አቶ ሰኢድ ምስክርነት ሰጥተዋል።