አስናቀዉ ሲሳይ ተገኘ
‹‹የማይዘነጉ ባለውለታዎች›› ለወጣቱ ትውልድ አርአያ እና መንገድ አመላካች ናቸው
የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1970ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡
በ tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ይህ አጭር ግለ-ታሪክ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡ ከ36 አመት በላይ አፍሪካዊነት ላይ የሰሩ በርካታ መጽሀፍትን የደረሱና ያሳተሙም ናቸው፡፡ እኒህ ሰው አቶ አስናቀው ሲሳይ ተገኘ ይባላሉ፡፡
ለጸረ-አፓርታይድ ንቅናቄ ውለታ የዋሉ ታላቅ ኢትዮጵያዊ
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሊመሰረት ሰሞን ግርማዊ ቀዳማዊ ሀይለስላሴ አፍሪካን አንድ ለማድረግ ወገባቸውን ታጥቀው ተነሱ፡፡ እነ አቶ ከተማ ይፍሩን በደንብ አድርገው ካስረዱ በኋላ የአህጉሪቱ አባት በመሆናቸው እርሳቸውም የበኩላቸውን ሊያደርጉ ቃል ገቡ፡፡ መስከረም 1954፡፡
ያኔ ኮንጎ ዘምተው የነበሩት ሻምበል ሲሳይ ተገኘ ደግሞ ከኮንጎ መልስ ወንድ ልጅ ባለቤታቸው ስለወለደች ይህንን እንደ ትልቅ ሲሳይ በመቁጠር ፈገግ አሉ፡፡ ልጁ መስከረም 29 1954 ሲወለድ አፍሪካን አንድ የማድረጉ ስራ በስፋት ተጠናክሮ ነበር፡፡
የልጁ ስም አስናቀው ሲሳይ ተባለ፡፡ ይህ ልጅ የአፍሪካዊ መአዛ በታወደበት ዘመን በመወለዱ አፍሪካን ወዶ አደገ፡፡ 24 አመቱ ላይም የደቡብ አፍሪካ የነጻነት ታጋዮችን የእጅ እጅ ውጊያ ለማሰልጠን ዛምቢያ አቀና፡፡ ዛሬ ሜይ 25 የአፍሪካ አንድነት 58ኛ አመት በሚታሰብበት እለት የማይዘነጋ ውለታ ለአፍሪካ ስለዋለው አንድ ሰው እንተርካለን፡፡ አስናቀው ሲሳይ ተገኘ፡፡
በጎንደር ከተማ አዘዞ በሚገኘዉ የጦር ካምፕ መስከረም 29 1954 አ.ም ተወለዱ፡፡
አባታቸው ሻምበል ሲሳይ ተገኘ ይባላሉ፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ- ስላሴ ሰራዊትን ሲያገለግሉ የቆዩ እና በፈቃዳቸው መልቀቂያ አስገብተው የሻምበልነት ማዕረጉን ይዘው የጡረታ መብት ሳይጠበቅላቸው ወደ ሲቪል ስራ የዞሩ ነበሩ፡፡ እናም የአባት ጦር ሰራዊትን አደራጅተው ነበር፡፡ ሻምበል ሲሳይ ዘመናዊ እርሻን በጊዜዉ ያስገቡ አዲስ አስተሳሰብ የነበራቸው የ5 ኒሻን ተሸላሚ ፣ የአምስት ወንድ እና የአምስት ሴት ልጅ አባትም ነበሩ ። እናት አገሪቱ ተሰማ በአካባቢዉ በበጎ ስራቸው እና ማኀበራዊ አገልግሎታቸው የሚታወቁ ነበሩ፡፡
ባለታሪኩ አስናቀው ስለ ኢትዮጵያዊነትና አፍሪካዊነት አስተሳሰባቸው ብሎም እምነታቸው ሲያስረዱ እንዲህ ይላሉ
‹‹……….የተወለድኩበት አዘዞ በኢትዮጵያዊነት ላይ ያለዉ አመለካከት እና ግንዛቤ በመላዉ አገሪቱ በቂ እና ትልቅ ምሳሌ የሚሆን ነው፡፡ የእኔም ፍጹም ኢትዮጵያዊነት ከቤተሰቤ እና ከአካባቢዬ የተላበስኩት ነዉ ። ከሁሉም በላይ የማንጸባርቀው አፍሪካዊነቴን ሲወራ አዳምጠውዉ የነበረው የኮንጎ ዘመቻ ጉዳይ ሁሌም በአይምሮዬ ውስጥ የሚገኝ እና የምንኰራበት ገድል ጋር አብሬ አድጌበታለሁ ። አባቴ በኮንጎ ዘመቻ ሰላም አስከባሪ በሻምበል አዛዥነት የዘመተ ነበር።›› በማለት ባለታሪኩ አቶ አስናቀው ይናገራሉ፡፡ ከዚያም ትምህርት በአጼ ፋሲል ተማሪ ቤት መጀመሩን ይተርካሉ፡፡
‹‹………በአፄ ፋሲል ትምህርት ቤት አዘዞ እስከ አምስተኛ ክፍል ተማርኩ ፤ ስድስተኛ ክፍል መሰረተ- ትምህርት ቤት ከተማርኩ በኋላ በፋሲለደስ ትምህርት ቤት መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ እና እስከ አስረኛ ክፍል ድረስ ትምህርቴን ተከታትዬ በጊዜው ውጤታቸው ከፍተኛ የሆነ አስር ልጆች ተመርጠን ወደ አዲስ አበባ ተግባረ- ዕድ ትምህርት ቤት በመግባት የሁለት ዓመት የቴክኒክ ትምህርት እና መደበኛ የአስራ አንደኛ እና የአስራ ሁለተኛ ትምህርቴን አጠናቅቄያለሁ ።
9ኛ ክፍል እያለሁ በአካባቢዉ በነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት በጎንደር ከተማ በሚገኘው የባታ ወህኒ ቤት ለአንድ ዓመት ከሁለት ቀን በእስር ቆይቻለሁ። ገና በልጅነት የመቋቋም ፣ የአልበገሬነት እና ከፍተኛ የጓዳዊ ስርዓትን ተምሬበታለሁ ። በዚያ ዕድሜዬ በእስር በነበርኩበት ወቅት በምርመራ ጊዜ ግርፋት ስቃይ እና መከራንም ተቀብያለሁ ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማታው ክፍለ- ጊዜ የሲቪል ኢንጅነሪንግ አምስት ኪሎ ካምፓስ እስከ 3 ዓመት ድረስ ተከታትዬ በስራ ምክንያት አቋርጫለሁ ፡፡ በአገር ውስጥ እና በውጭ በርካታ የረጅም እና የአጭር ጊዜ ኮርሶችን በሚገባ ተምሬ አጠናቅቄያለሁ ። የተለያዩ የኢንተለጀንስ እና የማስ ኰሙኒኬሽን ኮርሶችንም በሚገባ ወስጃለሁ ።›› በማለት ታሪካቸውን ይናገራሉ፡፡
አቶ አስናቀው በግላቸው ራስን የመከላከል ስልጠና ይሰጡ ነበር፡፡ ጊዜውም 1977 ነበር፡፡ ያኔ በደቡብ አፍሪካ የጸረ-አፓርታይድ ንቅናቄ ይደረግ ነበር፡፡ እናም የእጅ በእጅ ውጊያ ስልጠና ለመስጠት አቶ አስናቀው በነጻ አውጭዎቹ ፓርቲ በኤም ኬ ይመረጣሉ፡፡ እናም ጉዞ ወደ ዛምቢያ ይደረጋል፡፡ በጊዜው ይህን ኤምኬ የተሰኘ ፓርቲ የመሰረቱት እነ ኦሊቨር ታምቦ ነበሩ፡፡ ታዲያ ይህን የጸረ-አፓርታይድ ንቅናቄ ለመደገፍና ስልጠናውን ለመስጠት ወደዚያው ሲያቀኑ አፍሪካዊነት የሚለው ሀሳብ ውስጣቸው ሰርጾ ገብቶ ነበር፡፡ 36 አመት ወደ ኋላ ሄደው አቶ አስናቀው ሲያስታውሱ እንዲህ ይላሉ………….
‹‹……በኢትዮጵያ ዉስጥ በስትራቴጅክ ጥናት ኢንስቲትዩት ዉስጥ በማሰልጠን እና ስልጠናን ድጋፍ በመስጠት ለአምስት ዓመት አገልግያለሁ ፡፡ በዚሁ ኢንስትቲዩት ከዉጭ የሚመጡ የአፍሪካ ነፃ አዉጭዎችን በአገር ዉስጥ እና በዉጭ አገር የማሰልጠን እና አብሮ የመስራት ዕድል ገጥሞኛል ። በዚህም ስራ ላይ እያለሁ ለመጀመሪያ ጊዜ የመሰናክል እና የብቃት ኮርስ ማኑዋል በማዘጋጀት በመሬት ላይ ተግባራዊ በማድረግ ለሰልጣኞች አገልግሎት እንዲዉል አድርጌያለሁ ፤ ይህን የማሰልጠኛ ማኑዋል በዛምቢያ በሚገኘው ጐንደር ወታደራዊ ካምፕ ላይ በመተግበር የኤም ኬ እና የስዋፖ ነፃ አዉጭዎች እንዲሰለጥኑበት አድርጌያለሁ ።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የደቡብ ሱዳን እና የሱማሌ ነፃ አዉጭዎችን በማሰልጠን ለዉጤት አብቅቻለሁ ፤ በተለይ ለደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ መንግስት ከኤም ኬ ጋር በመሆን በተለይ ከክሪስ ሃኒ ዋና ኮማንደር ጋር በመሆን የእግር እሳት ሆነንባቸው ነበር ።›› በማለት 4 አመት የቆዩበት ህይወት ብዙ ቁምነገር እንዳስተማራቸው ይናገራሉ፡፡
ፈታኝ የነበረውን ይህን የማሰልጠን ስራ የተረከቡት አቶ አስናቀው በመጀመሪያ የደረሱት ታንዛንያ ነበር፡፡ ነገር ግን ቦታው ለማሰልጠንና ለውጊያም አመቺ ስላልነበር ለጥንቃቄ ሲባል ቦታ መቀየር ነበረበት፡፡ እናም የስልጠናው ቦታ ዛምቢያ እንዲሆን ተደረገ፡፡ ዛምቢያ ለዚህ ትግል ታላቅ ሚና ማበርከቱዋን አቶ አስናቀው ያስታውሳሉ፡፡ ለተከታታይ 4 አመት ከ2000 በላይ የነጻነት ታጋዮችን የእጅ በእጅ ውጊያ ያሰለጠኑት እኒህ ብዙም ያልተነገረላቸው ሰው መጠነኛ ደሞዝ ከፓርቲው ይቆረጥላቸው ነበር፡፡ከደሞዙ ይልቅ ለደቡብ አፍሪካ ነጻነት አንድ ጡብ ማኖር ወጣቱን አሰልጣኝ ያረካቸው ነበር፡፡ ታዲያ እኒህ አሰልጣኝ አልፎ አልፎም ውጊያው ስፍራ ይሄዱ ነበር፡፡ ማንዴላ ሲፈቱም አሰልጣኙ አቶ አስናቀው ወደ እናት ሀገራቸው መጡ-ጊዜውም 1984 መሆኑ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ያለውን ታሪክ ሲተርኩም………..
‹‹………….ከጊዜ በኋላ በአሜሪካ እና በኢንግላንድ ኑሮዬን ጀምሬ የነበረ ቢሆንም በአገሬ ወይም በአፍሪካ ውስጥ ለመኖር ከነበረኝ ቁርጠኝነት የተነሳ በትውልድ አካባቢዬ ትምህርት ቤት በመስራት ፣ የተለያዩ በርካታ ማኀበራዊ አገልግሎቶችን በመስጠት ከዚህም አልፎ በአገር አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ ህዳሴ ማኀበርን በመመስረት በምክትል ፕሬዘዳንትነት በማገልገል ፣ በሲቪል ማኀበራት ጥምረት ስራ አስፈፃሚነት በመሆን የምርጫ ታዛቢነት ስራ ለመጀመሪያ ጊዜ በተደራጀ መልኩ በአመርቂ ሁኔታ ለአገሬ ሰርቻለሁ ። ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለመጀመሪያ ጊዜ የቴሌ ቶን ራት በማዘጋጀት ለኢትዮጵያ ህዝብ እና ለመንግስት ባለስልጣናት ግንዛቤ በማስጨበጥ ከፍተኛ ስራ ሰርቻለሁ፤ የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎችን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች እና አገርን በሚጠቅሙ መልኩ አዘጋጅቼ አቅርቤያለሁ ። በነዚህም ምክንያቶች ከኢትዮጵያ ፕሬዜዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ የወርቅ ሜዳልያ ፣ የወርቅ ዋንጫ እና የክብር ዲፕሎማ ተሸልሜያለሁ ።
ለኔ ፍልስፍናዬ ኢትዮጵያኒዝም ነዉ፡፡ ኢትዮጵያኒዝም ደግሞ የአፍሪካዊነት ነፃነት መርህ ከመሆኑ በላይ የፓን አፍሪካኒዝም መሰረት ነው ። ከነበረዉ የአገር ዉስጥ አስቸጋሪ የፖለቲካ ሽኩቻ አፍሪካዊነቴን አጉልቼ በማዉጣት አለም አቀፋዊ ስራ በመስራት የተሻለ አፈፃፀም መስራትን እመርጣለሁ ። ለኔ በብሄር ማሰብ ወይንም መደራጀት ያሳንሰኛል ብዬ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም በአህጉር ደረጃ እና ከዛም አልፎ ያለኝ አለም አቀፋዊ አመለካከቴ ፀረ -ቅኝ ግዛት ፣ ፀረ አፓርታይድ እና ፀረ ሽብርተኛ አመለካከት በመሆኑ ነው ።
ለዚህም ነው አጋጣሚዉን ተጠቅሜ የኤም ኬን(ኡሙኩሁንቶ ዊ ሲዝዌ)ን ፣ የስዋፖን ፣ የኤስ ፒ ኤል ኤን ፣ የሱማሌን ነፃ አዉጭ ሁለቱን ድርጅቶችን አገራቸዉን ነፃ ለማዉጣት በአደረጉት ትግል የሚገባኝን ሁሉ አድርጌያለሁ ፤ በተጨማሪም የጋና አየር መንገድ እና የዚምባብዌን አየር መንገድ የበረራ ደህንነት በትብብር አሰልጥኛለሁ ።
በደቡብ አፍሪካ የማንዴላን የቅርብ ጥበቃዎች በማሰልጠን እና በማብቃት የተሻለ ዉጤት በማብቃት ከነበረው የአፓርታይድ የተተበተበ የበላይነትን ማስወገድ ችያለሁ ። ከዛምቢያ እስከ ደቡብ አፍሪካ በእግር ከኤም ኬ ሰልጣኝ ሽምቅ ተዋጊዎች ጋር በመሆን የዛምቤዚን እና የሊምፖፖን ወንዞች በማቋረጥ በማቋረጥ አስፈላጊዉን ግዳጅ ለመፈጸም የሚያስችሉትን የቶፖግራፊ ስልጠና በመስጠት አፍሪካዊ ግዳጄን በብቃት ተወጥቻለሁ ።
ከስዋፖ ሽምቅ ተዋጊዎች ጋር በዛምቢያ ደንበር እና በአንጎላ ካሲንጋ በደረሰዉ ጭፍጨፋ አጸፋዊ መልስ ለማድረግ የተደረገው ግዳጅ ሙሉ በሙሉ ተሳትፌአለሁ ።
በሱማሌ ግዛት የኢትዮጵያ ፓይለት እና የኩባ ወታደር ከሌሎች የኢትዮጵያዊ ምርኰኞች ጋር የነበሩበትን አካባቢ ሞዴል በመስራት ለግዳጅ ያሰለጠንኩ ሲሆን ይህ እስር ቤት ባልታሰበ መልኩ ቦታዉን በመቀየሩ ለውጤት ሳይበቃ ቀርቷል ። ›› በማለት ትረካቸውን ያሳርጋሉ፡፡
እኒህን ብዙ ያልተነገረላቸውን ሰው በርካታ አፍሪካዊያን ጀነራል እያሉ በአክብሮት ይጠሯቸዋል፡፡ ላቲኖቹ ደግሞ ኰማንዳንት የሚል መጠርያ ሰጥተዋቸዋል፡፡ አሰልጣኝ አስናቀው በግል የወታደራዊ ስልጠናን እና ማሰልጠኛን በበቂ ሁኔታ የገነቡ እና ከአገር አልፈው አህጉራቸውን በማገልገል ብዙ ጀነራሎች ያፈሩ በመሆኑ ደስተኛ ናቸው፡፡ ነገር ግን እናት እና አባታቸው ያወጡላቸውን ስም አስናቀውን ይወዱታል ። እንዲህ ይላሉ……
‹‹…..ስለእኔ ብዙ ማውዉራት አልወድም ነገር ግን እውነታው በመጽሃፍ የተዘጋጀ በመሆኑ ለትውልድ ተቀርፆ ይተላለፋል ። አሁን ብዙ እውነታዎችን መግለጽ እና የምናዉቀዉን ነገር ለትውልድ ለማስተላለፍ በማሰብ አፍሪካን በሚመለከት 12 መጸሀፍ መካከለኛዉ ምስራቅን በተመለከተ ደግሞ 6 መጽሀፍ በአጠቃላይ 18 መጽሀፍ ፅፌ አዘጋጅቻለሁ ። የመጀመሪያዉ አፍሪካ ፩ እና የሰቆቃዉ ምድር ፍልስጥኤም የሚሉት መጽሀፎች የታተሙ ሲሆን ሌሎች ተራቸውን እየጠበቁ ይገኛሉ ።.››
‹‹…..የደቡብ አፍሪካው አምባሳደር በኢትዮጵያ አምባሳደር ኤድዋርድ በተገኙበት የደቡብ አፍሪካን ቀን በማስመልከት የመጽ ሀፍ ምረቃዬን በአደረኩበት ጊዜ ባደረጉት ንግግራቸው እዉነታዉን አስቀምጠውታል “ እኛ አስናቀዉን የምንጠራዉ ጀነራል ብለን ነው ፤ ነገር ግን አፓርታይድ እና ቅኝ ገዥ አስተሳሰብ ያልተላቀቁት ቴሬሪስት ብለው ይጠሩታል “ ሲሉ ገልጸዉታል፡፡ አፍሪካን የሚወዱት አስናቀው››