ትእግስት ይልማ

ትእግስት ይልማ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ‹‹መዝገበ-አእምሮ›› በሚል ርዕስ የ180 የሚድያ ሰዎችን ታሪክ በጠንካራ ሽፋን መጽሀፍ አሳትሞ ማስመረቁ ይታወቃል፡፡በዚህ መጽሀፍ ውስጥ ታሪካቸው ከተሰነደላቸው የሚድያ ሰዎች አንዷ ትእግስት ይልማ ናት፡፡ትዕግስት ከዛሬ 25 አመት ቀደም ብሎ የተመሰረተው ካፒታል ጋዜጣ እንዲመሰረት እና አሁን ላለበት ደረጃ እንዲበቃ ካደረጉት መካከል አንዷ ናት፡፡ ትእግስት ይልማ በአሁኑ ሰአት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባኤ ሊቀመንበር ናት፡፡ በሥራ ትጋቷ በብዙዎች የተመሰከረላት ትእግስት ይልማ በየት መንገድ አለፈች፡፡ ባንቺአየሁ አሰፋ እና እዝራ እጅጉ ታሪኳን እንደሚከተለው ሰንደውታል፡፡

የኢትዮጵያ የህትመት ጋዜጠኝነት ሲነሳ የእሁድ ጋዜጣ ይታወሳል። ከእሁድ ጋዜጣ ጋር ተያይዘው ሦስቱ ጋዜጦች ይመጣሉ። ከሦስቱ ጋዜጦች አንዱ ደግሞ “ካፒታል” ነው። ካፒታልን ላይ ከመሥራት ጀምሮ አሁን ላለበት ደረጃ ያበቃችው ትእግስት ይልማ በሚድያው ዘርፍ የራሳቸውን አሻራ ካኖሩት መካከል አንደኛዋ ነች፡፡

ካፒታል ጋዜጣ ተመስርቶ ማደግ እንደጀመረ እድገቱ በአጭር ሊቀጭ ሲል ትእግስት እንደእናት ፈጥና ተቀብላ ታድጋዋለች። በቢዝነስ እና ኢኮኖሚ ጋዜጦች ላይ ቁልቁል የሚሰነዘሩ ጫናዎችን ተቋቁማ ጋዜጣውን ከማስተዋወቅ እስከ ማስተዳደር ድፍን 25 ዓመታትን ዘልቃለች፤ ትዕግሥት ይልማ ቡልቻ።

ልጅነት እና ትምህርት

ትውልድ እና እድገቷ በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ ሲሆን በሰፊ ቤተሰብ ውስጥም ያደገች ናት፡፡ አባቷ አቶ ይልማ ቡልቻ የቢዝነስ ሰው ሲሆኑ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የግል የድንኳን እና ተጓዳኝ ዕቃዎች ማምረቻን ያቋቋሙ ሰው ነበሩ። ትዕግሥት ሥራን ማክበር ከወላጅ አባቷ ተምራለች፡፡ ያሰቡትን መልካም ነገር በይደር ማስቀረት በህይወት መንገድ ወደኋላ እንደሚያስቀር ቅርብ ሆና ተምራለች፡፡ የትምህርትን አስፈላጊነት ገና በልጅነት የተረዳች በመሆኑ ለዚህም ወላጅ አባቷ ቀዳሚ ተመስጋኝ ናቸው፡፡ ያኔ ትዕግሥት የተረዳችው አንድ ትልቅ ቁምነገር የሰው ልጅ አእምሮውን በደንብ ካሰራ ብዙ ነገር መፍጠር እንደሚችል ነው፡፡

ትዕግሥት ከመዋለ ህጻናት እስከ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ድረስ የተማረችው በሊሴ ገ/ማርያም ት/ቤት ውስጥ ሲሆን የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቷን በህንድ ሀገር ፑኔ ከተማ በላቁ ጥናቶች ማዕከል በሚታወቀው ጎህካሌ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚክስ ተቋም (Gohkale Institute of Politics and Economics) በማስተርስ ኦፍ ኢኮኖሚክስ ተመርቃለች፡፡ በዚህም በርካታ የጥናት ምርምሮችን ማድረግ ከመቻሏ ባለፈ በጥሩ ውጤት ትምህርቷን አጠናቃለች፡፡ ምንም እንኳን በልጅነቷ ታላላቅ ጋዜጠኞች የዘገቧቸውን ዜናዎች፣ ተዘዋውረው የሚሰሯቸውን ፕሮግራሞች ስትመለከት በውስጧ ጥሩ መነሳሳት የሚፈጥርባት ቢሆንም ጋዜጠኛ እሆናለሁ ብላ አልማም ፣ አስባም አታውቅም ነበር።

ወደ ስራ አለም

በ1984 ዓ.ም ትምህርቷን ጨርሳ ወደ አገሯ እንደተመለሰች በቀጥታ ወደ ሥራ መስክ ስትሰማራ የመጀመሪያ ሥራዋን በተማረችበት ሊሴ ገ/ማርያም ትምህርት ቤት አንድ ዓመት ያህል አስተምራለች። ይሁን እንጂ መምህርነት መልካም ቢሆንም የበለጠ መስራት ወደምትችልበት ስፍራ አቀናች፡፡ ወደ አልካቴል ገብታ አንዳንድ ልምዶችን መቅሰም ችላለች፡፡

በቴክኖሎጂ እና ኢንፎርሜንሽን ቴክኖሎጂ በአገራችን በቀዳሚነት ከሚጠሩት የግል ተቋማት መካከል ከሆነው INFOTEC PLC ተቀጥራም በሽያጭ ስራ አስኪያጅነትና ቴሌኮም ኃላፊነት ድርጅቱን አገልግላለች። በስራዋም በርካታ ውጤቶችን ለተቋሙ ማበርከት ችላለች፡፡ ከዛም በዘለለ ለህይወቷ የሚጠቅሙ ልምዶችን መቅሰም ችላለች ። ትዕግሥት በቴክኖሎጂው ዘርፍ የላቀ ዕውቀት የነበራት ሲሆን የሳተላይት ተከላ፣ የቴሌኮም መስመር ዝርጋታዎችን በማስተባበር ልምድና እውቀት መቅሰም ችላለች፡፡

የሲስኮም ምስረታ

በመቀጠል SYSCOM PLC የሚባል የኢንፎርሜንሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያ በ1989 ዓ.ም መመስረት ቻለች፡፡ ይህም ኩባንያ እጅግ ውጤታማ ሊባል በሚችል እና በወቅቱ በሀገራችን ዘመናዊ አስተዳደርን ከሚከተሉ ተቋማት መካከል እንዲሆን አድርጋለች፡፡ ቁርጥ የሆነ የአመራር ስልት፣ ጥርት ያለና የተቀላጠፈ አሰራር፣ በማምጣትና በመሞከር በሥራዋ ላይ ለውጥ ለማምጣት ሞክራለች፡፡

ትዕግሥት ይልማ የሥራ እንቅስቃሴዋን በማስፋት ክራውን ፐብሊሺንግ የሚባል የካፒታል ጋዜጣ አሳታሚ ድርጅትን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በመምራት ለአገሯ በሚዲያው ዘርፍ በርካታ አስተዋፅኦ ስታበረክት ቆይታለች፡፡ በዚህ የጎላ ሚናዋ ለረዥም ጊዜ የቆየች ሲሆን ዘርፉ ላይ ካሉ ጥቂት ሴት አመራሮች አንዷ በመሆኗም ይበልጥ እንድትሰራ ብርታት እና ጥንካሬ ሆኗታል፡፡ትዕግስት ካፒታል ጋዜጣን እንደ አዲስ በማዋቀር ውስብስብ በነበረ የአሰራር ሂደት ውስጥ እንደ ስሟ ትእግስትን ተላብሳ የሥራውን ስርአት ማስቀጠል መቻሏ በተለይ ለህትመት ኢንዱስትሪው ትልቅ ውለታ ውላለች፡፡

ትእግስት እና ካፒታል

ካፒታልን በክንዶቿ ላይ አንጥፋ በየቢሮዎቹ እየዞረች አንባቢ በመፈለግ፣ ጋዜጣው እንዲታወቅ የተቻላትን ስታደርግ ሥራውን የእውነትም እየወደደችውና እያወቀችው ነበር፡፡ የቢዝነስ ተቋማት ምርትና አገልግሎታቸውን በጋዜጣው ላይ እንዲያትሙ በማሳመን፣ ህትመቶች በየጊዜው እንዲወጡ፣ ፎርማቶቹ በጥሩ ሁኔታ እንዲቀጥሉ፣ ኤዲቶሪያል በመስራት፣ በህትመት፣ ፣ በፊደላት መሸራረፍ ፣ በህትመት የሰዓት መዘግየት፣ ግራፊክስና ዲዛይኑን በመገምገም እስከ መምራት ድረስ በርካታ ደረጃዎችን ተጋፍጣ አልፋለች።

ፈተናዎች የቱንም ያህል ቢከብዱ ትእግስት ግን እየተሞረደች ተንገዳግዳ የአንድ ትውልድ ዕድሜ ያህል ተሻግራ ለመቆም በቅታለች። ከሀገር ውጪ ያሉ የህትመት ጋዜጠኞችን በማስመጣት ተሞክሮዎችን በመቅሰም፤ የጋዜጣ ገጽ ከነበረው እንዲጨምር፣ አዳዲስ አምዶች እንዲካተቱ፣ጋዜጣው በቀለም እንዲታተም እንዲሁም በርካታ ባለሙያዎች እንዲሳተፉ አድርጋለች። የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ የሚዘወረው በታላላቅ የንግድ ኩባንያዎችና የቢዝነስ ተቋማት እንደመሆኑ መጠን መረጃዎችን በማጋራት የቢዝነስ ጥናቶችን በማዘጋጀት በሀገር ውስጥ የኢንቨሰትመንት ሥራ እንዲከናወን፣ መነሳሳቱ እንዲፈጠር ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትል የአቅሟን ያህል ሰርታለች፡፡

እንደሀገር ለግልም ሆነ ለመንግሥት ዘርፍ ክንድ በመሆን ካፒታል በማገልገል ላይ ነው። ተሞክሮን በማስተዋወቅ ደረጃም እንዲሁ ። በሀገር ውስጥ ያሉ የኢንቨስትመንት ዕድሎች እና ተግዳሮቶችን ነቅሶ በማውጣት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ላይ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡት በማድረግም ብዙ ተግባራትን አከናውናለች፡፡ ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ትኩረታቸውን ወደ ሀገራቸው በማድረግ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ እንዲሳተፉ ኢኮኖሚውን የማረጋጋት ሥራ ላይ በጋዜጣዋ በኩል ወሳኝ ጉዳዮችን አንስታለች፡፡ በልዩ ልዩ የማህበረሰብ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ በተለይ ኢትዮጲያ ከፖሊዮ ነፃ እንድትሆን ለረጅም ዘመን ማለትም ከ24 ዓመታት በላይ ያለማሰለስ በካፒታል ጋዜጣ ላይ ያደረገችው ጥረት እጅግ ትልቅ የነበረና በጣም ደስተኛ የሚያደርጋት ስራዋ እንደሆነ ትናገራለች።

ጋዜጣው የምስረታ ዓመቱን በሚያከብርበት ወቅት ወጣት ጋዜጠኞች ስለጋዜጠኝነት ግንዛቤ እንዲኖራቸውም ትእግስት የበኩሏን ጥረት ታደርግ ነበር፡፡ ሳምንታዊ የፓናል ውይይት በማዘጋጀት የሀሳብ እና የልምድ ልውውጥ እንዲኖር ጥረት ማድረጓ አልቀረም፡፡ በኪነ-ጥበብ ዘርፉ የማይታወቁ ባለሙያዎችን ከህዝብና ከአርቱ ማህበረሰብ ጋር ለማስተዋወቅ የስዕል ኤግዚቢሽን በማዘጋጀት ለእይታ አብቅተዋል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ዓለምን ጠፍሮ በደቆሰበት ወቅት፣ ሁሉም ቤቱ በከተመበት ጊዜ፣ ካፒታልን በፒዲኤፍ መልክ በማድረግ ለደንበኞቿ የኢሜል አድራሻ በመላክ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ የሚያስብል ስራን ሰርታለች። ይህም ማለት የኮሮና ቫይረስን የስርጭት አድማስ በመግታት እና ሰዎች ከመረጃ እንዳይርቁ በማድረግ ነው።

በጥያ አካባቢ የህፃናት እና የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት እንዲሰራ ከብዙ የአካባቢው ህብረተሰብ እና ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አስተዋፅኦዋ ትልቅ ነው። ህፃናትና ወጣቶች ሲማሩ ለበለጠ የትምህርት ደረጃ ሲታጩ ለማየት ተችሏል። በተለይም በሀገሪቱ የበርካታ ሀገራት ኤምባሲዎች፣ ድርጅቶች እና ትልልቅ ተቋማት እንደመኖራቸው መጠን በራሳቸው ቋንቋ ስለ ሀገሪቱ ኢኮኖሚና ቢዝነስ እውቀት እንዲኖራቸው እንዲይዙ በማድረግ ካፒታል ወሳኝ ሚና መጫወት ችሏል፡፡

Entrepreneur profile ወይም የስራ ፈጣሪዎች መድረክ የተሰኘ አምድ በመክፈትም ስራ ፈጣሪዎች አቅማቸውን እንዲያወጡ ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ በማሰብ ትእግስት ከባልደረቦቿ ጋር በመሆን ትልቅ ስራ ሰርታለች፡፡ Art & Culture የተሰኘው የካፒታል ጋዜጣ አምድም እንዲሁ የሀገሪቱን ባህል በማስተዋወቅ የራሱን ጉልህ ሚና ያበረከተ ነው፡፡ የጋዜጣውን ገጽታ ከመቀየር ጀምሮ በበርካታ ኹነቶች ውስጥ በህትመት ሚዲያው ዘርፍ ትዕግሥት እና ካፒታል ፈር ቀዳጆች ናቸው።

በተለይም ዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት እና ትጋት የሚጠይቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ደረጃውን እንደጠበቀ ማህበረሰቡን ለ24 አመታት በቢዝነስ እና ኢኮኖሚ ዙሪያ እንዲያገለግል ማስቻል ለእርሷ ትልቅ ኩራት ነው፡፡ በዚህም በርካታ እውቅናዎችን ማግኘት በመቻሏ እርካታ ይሰማታል፡፡ ትዕግሥት ይልማ ያገኘቻቸው ማዕረጎችንም እንደሚከተለው ተቀምጠዋል።

  1. Rotary People of Action Champion of Health April 2021Received from Rotary International the “Rotary People of Action Champion of Health Award” in recognition of work to ensure communities maintained access to basic Health services during Covid-19 pandemic.
  2. Regional Service Award for a Polio-Free World 2016 Received the Regional Service Award for a Polio-Free World from the Rotary Foundation Trustees 2015-16 in recognition of significant active personal service toward the goal of polio eradication
  3. Chevalier dans L’Ordre National de La Legion d’Honneur Jan. 2016 Received the ‘Chevalier dans l’Ordre National de la Légion d’Honneur; the highest honourAttributed to civilians by the Government of France
  4. ECX Champion Award Addis Ababa, Feb. 2011 Received the Ethiopian Commodity Exchange Champion Award at its 1000 days celebration for media support.

በመደበኛ ትምህርቷ እና ሥራዋ ያገኘቻቸውን ልምዶች እና እውቀቶች ተጠቅማ ባላት ማህበረሰቡን የማገልገል ጽኑ ፍላጎት በርካታ የሚድያ ተቋማት ውስጥ በላቀ ሁኔታ ትሳተፋለች፡፡ በአመራርነት ጭምር በርካታ በጎ ሥራዎችን እያከናወነችም ትገኛለች፡፡ ይህ ተግባር ለእርሷ ከመደበኛው ስራዋ እና ማህበራዊ ህይወቷ ተጨማሪ ጫና የሚፈጥርባት ቢሆንም ማህበረሰቧን በማገልገሏ ያላት እርካታ የጎላ እና የበለጠ እንደሚያመዝንባትም ትናገራለች፡፡ ይህ ያላሰለሰ ልፋቷ እና ጥረቷ በርካታ ብሄራዊ እና አለምዓቀፋዊ እውቅናን አስገኝቶላታል፡፡

ትዕግሥት ይልማ በቦርድ አባልነትና በተለያዩ መደቦች ያበረከተቻቸው ዘርፈ ብዙ ክንውኖች ያሏት ሲሆን ከሞላ ጎደል ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል።

  1. Initiative Africa – August 2002Initiative Africa, non-profit organization, founding & board member
  2. Mena – August 2004 Mena, non-profit organization, founding & board Member
  3. Rotary Club of A.A. Entoto Jul. 2004 – July 2005 President of the RC of A.A Entoto; Founding Member
  4. RYLA Ethiopia June 2006 – July 2007 Rotary Youth Leadership Awards (RYLA) and Retractors chair for 2006/07

በተጨማሪም በበርካታ ስራዎች ውስጥ ተሳትፎዋ እጅጉን የበዛ ነው። በርካታ ተቋማትን በተለያዩ መልኩ ታገለግላለች። በኃላፊነትም እየሰራች ትገኛለች። ሥራዎቿን ለማየት ያክል

  1. ካፒታል በተሰኘው ሳምንታዊ የእንግሊዘኛ ጋዜጣ ላይ በማኔጂንግ ኤዲተርነት፣
  2. በሲስኮም ኃ/የተ/የግ/ማህበር በማኔጂንግ ዳሬክተርነት፣ በእነዚህ ሁለት ድርጅቶች ውስጥ በአጠቃላይ ከ40 ሰራተኛ በላይ በማስተዳደር
  3. በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባኤ በሊቀመንበርነት፣ ምክር ቤቱ ከ 60 በላይ የሚዲያ ተቋማት አባላት ያሉበት ሲሆን በሚዲያው፣ በጋዜጠኞች፣ በህዝብና በመንግስት መካከል ጤናማ ግንኙነት እንዲኖር እና የጋዜጠኞችን ስነ-ምግባር ደንብ ከማስጠበቁም በላይ በሀገሪቱ መሰረታዊ የሆነው ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ፣ የህግ የበላይነት እንዲከበር፣ ሰላምና ዲሞክራሲ እንዲያብብ የበኩሉን አስተዋፅኦ የሚያደርግ ተቋም ነው፡፡
  4. የኤስ ኤም ኤል ኤች – ኦ ኤን ኤም (SMLH-ONM ETHIOPIA)በፕሬዝዳንትነት የፈረንሳይ ከፍተኛ የሽልማት ማህበር የተመሰረተበት ዋንኛ አላማ የድጋፍ ስራዎችን ለሚገባቸው ማቅረብ እንዲሁም በፈረንሳይ እና በኢትዮጵያውያን መካከል ወዳጅነት እና ትብብርን ለማጠናከር ነው፡፡ በ2005 ዓ.ም የተቋቋመ ማህበር ሲሆን ከዚህ ቀደም በጋራ በመረዳዳት የመኖር መርህ መሰረት በአገራችን የተለያዩ የድጋፍ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል፡፡
  5. አሊያንስ ኢትዮ-ፍራንሣይዝ (Alliance Ethio-Française) በፕሬዝዳንትነትአሊያንስ ኢትዮ-ፍራንሣይዝ ከ1899 ዓ.ም ጀምሮ በፈረንሳይ እና በኢትዮጵያ መካከል የባህልና የቋንቋ ልውውጦችን የሚያበረታታ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ሲሆን ይህም የተሳካ እንዲሆን የአቅሟን እየሰራች ትገኛለች፡፡
  6. ሮታሪ ኢንተርናሽናል – ናሽናል ፖሊዮ ፕላስ ኮሚቴ ሰብሳቢ (Rotary International, National PolioPlus Committee Chairperson)

ሮታሪ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የ1.2 ሚሊዮን ባለሙያዎች እና መሪዎች ዓለም አቀፋዊ ማህበር ሲሆን፣ በማኅበረሰቦቻቸው ውስጥ ሰዎች አንድነት የሚፈጥሩበት እና ዘላቂ ለውጥ ለመፍጠር የሚጥሩበት ማህበር ነው፡፡ ፖሊዮን ጨርሶ ለማጥፋት ትእግስት ከምታከናውናቸው ተግባሮች ዋና ዋናዎቹ ህብረተሰባችንን የመደበኛ ክትባት ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ፣ ከፖሊዮ ነፃ የሆነ አካባቢን መፍጠር፣ እንዲሁም የፖሊዮ ወረርሽኝን የመከላከል አቅምን ማሳደግ እና ለሚሰሩ ስራዎች ሃብት ማሰባሰብን ያካትታል፡፡

ግሩም አባተ ÷ የካፒታል ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሲሆን ትእግስት ለምትሰራው ስራ ያላት ጽኑ ፍቅርና መሰጠት ይደንቀዋል፡፡ በተለይ ጋዜጣው ወደ ማተሚያ ቤት በሚላክበት ጊዜ ሁሉን አይታ ካልሆነ ወደ ቤት መግባት የሚሉትን ነገር ፈጽሞ አታስበውም ሲል ትእግስት ከስራው ጋር ያላትን ጥብቅ ትስስር ሊያሳይ ይሞክራል፡፡

ግሩም እንደሚናገረው ትእግስት ትጋትን ለሚያሳያት ሰው ጥሩ ታበረታታለች፤ ነገር ግን ከሰነፍ ጋር በፍጹም ስምምነት የላትም፡፡ ከትእግስት ጋር ላለፉት 15 አመታት ያገለገለው ግሩም በአንድ በኩል እንደ ታላቅ እህት ባልደረቦች ሲቸገሩ ዝም ብላ አታይም፡፡ ለሰው የሚያዝን ልብ እንዳላት ግሩም ይናገራል፡፡ ከስራ ባለፈም ሰው የግል እክል ሲደርስበት አብራ በመሆን አለኝታነቷን ታሳያለች ሲል ዋና አዘጋጁ ግሩም ይናገራል፡፡

እነዚህን እና የመሳሰሉ ሥራዎችን እየሰራች ያለች ሲሆን ለወደፊቱም በሁሉም ዘርፍ የላቀ ደረጃ ለመድረስ ጥረቷ የላቀ እርምጃዋም የፈጠነ እንዲሆን እየተጋች ትገኛለች፡፡ ለካፒታል ጋዜጣ እዚህ መድረስ ብዙ የጠቆሩና የፈኩ ፊቶችን አይታለች አልደነገጠችም። ብዙ ሳቅና ስላቆች ገጥመዋታል አልተሸማቀቀችም። ይልቁንም እኒያን ሁሉ ፈተናዎች አልፋ ዛሬ ሀገር ማገልገል ላይ ጊዜዋን እየሰጠች ነው፡፡

ከራስ በላይ ለሌሎች መዋል (‘Service Above Self’ – Rotary) ለሁሉም ጊዜ መስጠት፣ ስራን አለማሳደር ወይም ጨርሶ መስራት፣ የህይወት ፍልስፍናዋ እንደሆነ ከተወዳጅ ሚዲያ ጋር በነበረት የቃለመጠይቅ ወቅት ትናገራለች። የካፒታል ጋዜጣ መስራች እና አስተዳዳሪ ትዕግሥት ይልማ ቡልቻ፡፡ትእግስት እርሷ ጋር ሲሰሩ የነበሩ ባለሙያዎች በተለያዩ ሙያ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው ሀገራቸውን እያገለገሉ መሆናቸውን ስታስብ ታላቅ ርካታ ይሰማታል፡፡ ትእግስት ካፒታል አሁን ላለበት እንዲደርስ ትልቁን ድርሻ የሚወስዱትን ታምሩ ገዳን፤ ሙሉቀን የወንድወሰንን እንዲሁም ግሩም አባተን ማመስገን ትፈልጋለች፡፡ ወደፊት ሚድያውን ከዚህ በላይ የማሳደግ ራእይንም ሰንቃለች፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *