የፊልም ባለሙያው ቴዎድሮስ ተሾመ ታኅሳስ 29 ቀን 1962 ዓ.ም ጅማ ከተማ ተወለደ።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በጅማ ከተማ ሄርማታ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። የ16 ዓመት ልጅ እያለ፥ ወጣቶች በግዳጅ የሚወሰዱበትን ብሔራዊ ውትድርና ሽሽት አየር ወለድን ተቀላቀለ። ነገር ግን አንድ ዓመት ሳይቆይ አምልጦ ወጣ። በኋላም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ትምህርቱን ቀጥሎ ሽመልስ ሀብቴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብቷል። ከዛም ተሻግሮ በአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ የኮሌጅ ትምህርቱን አጠናቀቀ።
ሥራ የጀመረው በፎቶግራፍ ባለሞያነት ነው። ይህም ነው ለፊልም ጥበብ ፍቅር ያሳደረበት። ከዛም ይሠራበት ከነበረው ፎቶ ቤት በተዋሰው የሰርግ ካሜራ፥ በጅማ ከተማ የተቀረጸ ‘ግልብጥ ዓለም’ የተሰኘ የመጀመሪያ ፊልሙን ጽፎ፣ አዘጋጅቶና ፕሮድዩስ አድርጎ ለዕይታ አበቃ።
ከኹለት ዓመታት በኋላ በ1990 ‘ሲኦል’ የተሰኘ ሁለተኛ ፊልሙን ሠራ። ይህም ሥራው የሚድሮክ ኢትዮጵያን ትኩረት መሳብ በመቻሉ፥ በኩባንያው የሙሉ ጊዜ የዘጋቢ ፊልም አዘጋጅ ሆኖ ተቀጠረ። በዛ መደበኛ ሥራውን እየሠራ ሳለ ነው ‘ቀዝቃዛ ወላፈን’ የተሰኘውን ፊልም ያዘጋጀው። ከዚህ በኋላም ሙሉ ጊዜውን ለፊልም ሙያ በመስጠት ‘ቀዝቃዛ ወላፈን’፣ ቀጥሎም ራሱ መሪ ተዋናይ ሆኖ የተሳተፈበትን ‘ፍቅር ሲፈርድ’ ፊልሞች ያዘጋጀው። “እንደተመኘሁት ስኬታማ አልሆነልኝም” የሚለው ’ቀይ ስህተት’ የተሰኘ ፊልሙን የሠራው ከዚህ በኋላ ነበር።
አላበቃም፥ ስኬታማ ዕይታና ውጤት ያመጣለት ‘ዐባይ ወይስ ቬጋስ’ን ለዕይታ አበቃ። በኋላም ‘ሦስት ማዕዘን’ የተሰኘ ፊልም በኹለት ክፍሎች ለዕይታ አቀረበ።
ቴዎድሮስ በተለይ በ’ሦስት ማዕዘን’ ፊልም ከሀገር ውጭ በርከት ያሉ ሽልማቶችን አግኝቷል። በሀገር ውስጥ ደግሞ ዝምታዬ በተሰኘው ፊልም በ2017ቱ የጉማ ሽልማት በምርጥ ረዳት ተዋናይነት ተሸልሟል።
የኢትዮጵያ የኦድዮ ቪዥዋል ፕሮድዮሰሮች ማኅበር ፕሬዝዳንት ሆኖ ያገለገለው ቴዎድሮስ፥ በ90ዎቹ ከፍቶ ይሠራበት ከነበረው ከቴዲ ስቱድዮ ጀምሮ፣ አሁን ላይ እስካለው ሴባስቶፖል ሲኒማ፥ በኢትዮጵያ ፊልም ውስጥ ጉልህ ድርሻ አለው። አሁን ላይ በግሮቭ ጋርደን ዎክ ያዘጋጀው ለፊልም ቀረጻ ምቹ የሆነ አውድም ለዚህ ምስክር መሆን ይችላል።