ተድባበ ጥላሁን
ተወዳጅ ሚድያ እና የኮሚኒኬሽን ማእከል በሚድያው ዘርፍ ልዩ አሻራ ያላቸውን እና የነበራቸውን ባለሙያዎች ታሪክ እየሰነደ ሲያቀርብ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ከዚህ ቀደም የ180 የሚድያ ሰዎችን የህይወት ታሪክ መዝገበ አእምሮ በሚል ርእስ በመጽሀፍ ማውጣታችን ይታወሳል። አሁን ደግሞ በቀጣይነት የ200 የጥበብ እና የሚድያ ሰዎችን የህይወት ታሪክ አሰባስበን በአንድ መጽሀፍ አድርገን ለማውጣት መሰናዶ አጠናቀናል።
አሁን በዚህ ጽሁፍ ታሪኩን የምናይለት ሰው የሚድያ ሰው ተድባበ ጥላሁን ይባላል።ተድባበ በነጻው ፕሬስ ጉልህ አሻራ ከነበራቸው ባለሙያዎች አንዱ ነው፡፡ በቤዛ፣ በአእምሮ እና በሪፖርተር ጋዜጦች የሠራው ተድባበ በበሳል እይታው ይታወቃል፡፡ እዝራ እጅጉ እና አማረ ደገፋው የተድባበን ታሪክ እንደሚከተለው ሰንደውታል፡፡
ገና የ6ኛ ክፍል ብላቴና እያለ….
ጎበዝ አንባቢ እና ጥሩ ጸሐፊ የነበሩት አባቱ ወደ ቤት ካመጧቸው መጽሐፍት መካከል አንዱን መርጦ አነበበ፤ አሳዘነው፤ ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ። እንባ የቋጠሩ የልጅ አይኖቹ ሳይደርቁ ከቤት ትምህርት ቤት ደረሰ።
ብላቴናውን ከሀዘኑ ለማፅናናት፣ እንባውንም ለማበስ የያኔው አማርኛ መምህሩ ተጠርተው ያነበበው መጽሐፍ እውነት የሚመስል ግን እውነት ያይደለ ልቦለድ እንደሆነ ቢያብራሩለትም አላመናቸውም።
ይህ አጋጣሚ የያኔው ብላቴና የዛሬው ጎልማሳ ዛሬ ላይ ሆኖ የሚያስታውሰው የመጀመሪያ የሥነ ጽሑፍ ትውውቁ ነው። ከዚያ በኋላ በልቦለድ እና በእውነተኛዋ ዓለም ያለውን ልዩነት ጥንቅቅ አድርጎ ለይቶ ትልልቅ የህይወት መስመር እጥፋቶችን አስተናግዷል፤ የሀገራችን ግዙፍ ጋዜጣና መጽሔቶች ላይም ፅፏል፤ ተደጋግሞ የታተመና የተነበበ መጽሐፍንም እንዲሁ ከትቧል።
ይህ ሰው ተድባበ ጥላሁን ይባላል። አዲስ አበባ ካዛንችስ የተባለው አካባቢ ህዳር 5 ቀን 1957 ዓ.ም ነው ውልደቱ፤ በለጋ እድሜው ያስለቀሰውን ጨምሮ ከንባብ ጋር ሕይወቱ እንዲጎራበት ያደረጉት አባቱ ጥላሁን ዘለቀ በሻህ ይባላሉ። እናቱ ደግሞ ወይዘሮ ሙሉነሽ ታፈሰ ገብሬ።
ተድባበ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን አስፋወሰን እየተማረ ጎን ለጎን የቤተክርስቲያን ትምህርትን ቅርቡ በነበረ ደብር ቀስሟል። ጧት ጧት አስፋወሰን ከሰዓት ከሰዓት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በምስራቅ አጠቃላይ ካጠቃለለ በኋላ በዘመኑ ህግ መሰረት ለመሰረተ ትምህርት ዘመቻ ከአዲስ አበባ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጦ ተጓዘ።
በያኔው አጠራር በወረሂመኖ አውራጃ ተንታ ወረዳ ውስጥ ወዳለች መንደር ዘልቆ 3 ወራትን ቆዬ፤ ከዚህ ሁሉ ዓመት በኋላ ዛሬም የሚያስታውሰው ተንታ በነበረው ቆይታው መቅደላን ጎብኝቷል። አስቀድሞ ጎንደር አካባቢ ይመስለው የነበረንና የአፄ ቴዎድሮስ የመጨረሻ ዳና ያረፈበትን ቦታ ተመላልሶበታል።
ከዘመቻው ተመልሶ ተግባረ ዕድ ገባ። የተግባረ ዕድ ቆይታውን ካጠናቀቀ በኋላ ደግሞ በድጋሜ በሌላ ዘመቻ ወደ ወለጋ አቀና – ለብሔራዊ ውትድርና። በዚያም ለሁለት ዓመታት የተጠጋ ጊዜን ካሳለፈ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ።
ከቆይታዎች በኋላ ደግሞ ባህር ትራንስፖርት ባለስልጣን ውስጥ ስራ አግኝቶ ወደ ምፅዋ ዘለቀ። በቀይ ባህር ዳርቻ ዓመታትን ከቆየ በኋላ ስፍራው ከኢትዮጵያ ግዛትነት ሲወጣ ተመለሰ።
ተንታ፣ ወለጋ እና ምፅዋ ተድባበ ለህይወት ያለውን አተያይ ቀርፆባቸዋል። ከአዲስ አበባ የመሃል ከተማ ኑሮ ተነስቶ ከአርሶ አደሩ ጋር ሲመላለስ፣ ጠላት ቢሆን ለተባለው ኢላማ ቃታውን ሲስብ፣ ደመወዝ ተከፋይ ሁኖ በቀይ ባህር ዳርቻ ሲመላለስ… ያላየውን አይቷል፣ ይሆናል ብሎ ያላሰበው ገጥሞታል፤ ህይወት ለካ እንደዚህም ናት አስብሎታል።
1984 ዓ.ም ሲሆን ጋዜጠኛ ሁኖ፤ እየፃፈ በህትመት ሚዲያው በኩል ተገለጠ። ወግ ያለው ንባብን በወጉ በተሰደረ መጽሐፍ ነው የጀመረው – 6ኛ ክፍል ሆኖ ባነበበው እና በነባበት ልቦለድ። ንባቡ ቀጥሎ 8ኛ ክፍል ሲደርስ ወደ መፃፍ አደገ። በትምህርት ቤታቸው በተደረገ ውድድር አሸንፎ የፃፈውን በተማሪዎች ፊት ጮክ ብሎ አነብቧል።
ህይወት ተንታ ወስዳ ስትመልሰው፣ ወለጋ አድርሳ ድጋሜ አዲስ አበባ ስታመጣው፣ ደሞ ምፅዋም ስታደርሰው እያነበበ ነበር። በተለይ በምፅዋ ንባቡን ከመፃፍ ጋር አስተባብሯል። ከዚህ በኋላ ነው ጋዜጠኛ የሆነው።
‹‹አዲስ ድምፅ›› ለተባለ ጋዜጣ ሲሰራ የመጀመሪያ ያመጣው ዜና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መታፈሳቸውን የተመለከተ ነበር። የዩኒቨርስቲ ተማሪ መስሎ ታፈሱ የተባሉት ተማሪዎች ያሉበት ቦታ ድረስ ሄዶ እንደሰራው ዛሬም አይዘነጋው።
እዚያው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በማታው መርሃ ግብር የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን እየተማረ ቤዛ የተሰኘ መጽሔት ላይ ለ3 ዓመታት ሰራ፤ አስቀድሞም አዕምሮ የተባለ ጋዜጣ ላይ 3 ዓመታት ሰርቷል።
እነዚህ ዓመታት በሀገራችን የግሉ ፕሬስ ማለዳ ነበሩ። ተድባበ መለስ ብሎ ሲያስታውሳቸው “ያኔ አልበሰልንም ነበር” ይላል። የግል ፕሬስ ማለት መንግስትን መቃወም እና የተቃዋሚዎችን ሃሳብ ሳይፈትሹ ማስተጋባት ብቻ ይመስለን ነበር ብሎ ራሱን እና ዘመን ተጋሪዎቹን ይሄሳል።
ይህን ግለ ሂስ ለማረቅ በሚመስል መንገድ አዕምሮን ለቆ ለድጋሜ ትምህርት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን በቀን መርሃ ግብሩ በድጋሜ ተቀላቀለ። በዚህ ጊዜ ትልልቅ መምህራንን ዛሬም ድረስ ከማይረሳቸው የክፍል ተጋሪዎች ጋር አገኘ።
ዶክተር ፈቃደ አዘዘ ለሚያስተምሩት አንድ የትምህርት ዓይነት በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶች የሚግባቡበትን የተለዬ ቋንቋ ፍለጋ ወቶ ዳጎስ ያለ ጥራዝ ይዞ ተመልሷል። በዚሁ ጥራዝ ዙሪያ ከሌላኛው መምህሩ ዶክተር ዮናስ ጋር ተማክሮበት ጉዳዩ ከመማሪያ ክፍል አልፎ ለህዝብ የሚደርስበትን መላ ሲያስቡ ቆይተው በመጽሐፍ በኩል መጣ።
የኤች አይ ቪ ኤድስ ነገር ተደጋግሞ በሚለፈፍበት የ1990ዎቹ አጋማሽ “መኃልየ መኃልይ ዘካሳንችስ” ብሎ ያየውን የሰማውን ለአንባቢ አደረሰ።
3 ዓመት የፈጀውን እና “በኢትዮጵያ የግሉ ፕሬስ እድገት እና ችግሮች” በሚል ርዕስ ያጠናውን ጥናት ጽፎ የቀን ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ ሪፖርተር ገባ። የጋዜጣው ዋና ሰው ሁኖ 3 ዓመታትን ሰራ። አስቀድሞ ራሱንና የዘመኑ ተጋሪዎቹን የወቀሰበትን በኋላም ጥናት የሰራበትን ጥፋት ላለመድገም በእጅጉ ጥሯል። ለዛም ነው ሪፖርተር እያለ የምርመራ ጋዜጠኝነት ላይ አብዝቶ የለፋው።
ከልፋቱ በኋላ ከሪፖርተር ለቆ ከወዳጆቹ ጋር ዕለታዊ አዲስ የምትል ጋዜጣ መስርተው ለዘጠኝ ወር ሰሩ። ከዘጠኝ ወር ቆይታ በኋላ ከሀገር መውጣት የሚል ሃሳብ አምጦ ወለደ፤ እናም ተድባበ ባህር አቋረጠ። ጥሪ ነው እና አሜሪካም ሆኖ ዘ ፕሬስ ላይ ለአንድ ዓመት ያህል ሀበሻ በአሜሪካ እያለ ፅፏል።
ከሀገር ርቆ ሲኖር ወገን አገኘ። ብሔራዊ ውትድርና እያለ ለእረፍት ወደ አዲስ አበባ በተመለሰ ጊዜ ከጓደኛው ይዞት የመጣውን መልዕክት ለቤተሰቦቹ ሊያደርስ ቤታቸው ሲሄድ በር የከፈተችለት እመቤት ጌታቸው ቀድማው አሜሪካ ገብታ ኖሮ አገኛት፤ ሀገር ቤት የጀመሩት ፍቅራቸውን በሰው ሃገር ቀጥለው ከትዳር ከፍታ አደረሱት፤ ትዳራቸው አሁን ላይ ሁለት ሴት ልጆችን ያፈራ እና 3 አስርታርን የተሻገረ ሁኖ በአሜሪካ ቴክሳስ ይኖራሉ።