ተካበች አሰፋ

የሚድያ ሰው ተካበች አሰፋ

ተካበች አሰፋ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ፣ባለፉት 3 ዓመታት በሚድያው ዘርፍ የተሠማሩ ባለሙያዎችን የህይወት ታሪክ ሲያስነብብ እንደነበር ይታወቃል ።አንዳንዶቹን በመጽሐፍ ሌሎችን በድረ- ገጽ እያደረግን የግለ- ታሪክ ክፍተትን ለመሙላት የተቻለንን ጥረት አድርገናል ። የሽልማት ውድድሮች ሲዘጋጁም የዕጩዎችን ማንነት ስንነግር ቆይተናል።

ይህ ሥራችን ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን ድርጅታችንም ቡድን አቋቁሞ እና ስርዐት ዘርግቶ የስነዳ ተግባሩን ሲያከናውን ቆይቷል። በሐምሌ 30 2014 ዓ.ም በጠንካራ ሽፋን የወጣው እና 600 ገፆችን የያዘው፣ ” መዝገበ- አእምሮ የ180 የሚድያ ሰዎችን ታሪክ የሚተርክ ነው። ይህ መጽሐፍ 11 የቦርድ አባላት ባሉት ቡድን የተሠናዳ ሲሆን ቅፅ 2 እየተዘጋጀ ይገኛል።

በቅጽ 2 የህይወት ታሪካቸው በመጽሐፍ ውስጥ ከሚካተትላቸው መካከል የሚድያ ሰው ወይዘሮ ተካበች አሰፋ ናቸው።

የሚድያ ባለሙያ ተካበች አሰፋ ሳህሌ ይባላሉ ፡፡ አባታቸው አቶ አሰፋ ሳህሌ ገብረ ሕይወት እናታቸው ደግሞ ወ/ሮ ላቀች ዘውዴ አሰግዴ በመባል ይታወቃሉ።

የሚድያ ሰው ተካበች አሰፋ ሐምሌ 5ቀን 1938ዓ.ም በአዲስ አበባ ተወለዱ። በልጅነታቸው የአባታቸው እናት አያታቸው ወደሚኖሩበት አዲስ ዓለም ወሰዷቸው። እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም ወላጆቻቸው እነርሱ ዘንድ አመጧቸው ። ወይዘሮ ተካበች ሲያስረዱ እንዲህ ይላሉ፦

“….አዲስ ዓለም የጀመርኩትን የቄስ ትምህርት እድቀጥል በማድረግ እስከ መልዕክተ ዮሐንስ ድረስ ተማርኩ። በኋላም ዘመኑን ባላስታውስም ካዛንቺስ በሚገኘው አሰፋወሰን የአሁኑ ምስራቅ ጎህ ትምህርት ቤት ገብቼ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ተምሬ በ1956 ዓ.ም የአንደኛ ደረጃ ት ዓ.ምት ምህርቴን አጠናቅቄያለሁ፡፡

በ1956 ክረምት ትምህርት ቤት ሲዘጋ በዚያን ጊዜ የመንበረ ፀባዖት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል አስተዳዳሪ የነበሩት አባት ወጣት ሴቶችን ብቻ በማሰባሰብ ልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ትምህርት እንድንማር አደረጉን። ይህም ከዚህ በፊት አልፎ አልፎ ቤተክርስቲያን ከመሄድ ያለፈ ምንም እውቀት ያልነበረንን ከፍተኛ እውቀት እንድናገኝ አድርጎናል፡፡ እኔም ስለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት የጠለቀ እውቀትና የጠነከረ እምነት እንዲኖረኝ አድርጓኛል፡፡

አስፋወሰን ትምህርት ቤት አንደኛ ደረጃ ብቻ እንዲሆን ስለተወሰነ ሁለተኛ ደረጃው ወደ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ኮከበ ጽባሐ ትምህርት ቤት ተዘዋወረ። እኔም በ1957ዓ.ም የጀመርኩትን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በ1961ዓ.ም አጠናቀቅኹ፡፡ የማትሪክ ውጤቴ ግን ዩኒቨርሲቲ የሚያስቀጥለኝ አልሆነም። ሆኖም በወቅቱ ሰበታ በሚገኘው ጌቴሴማኒ ማርያም የሴቶች ገዳም ተቀጥሬ የክረምት ሥራ ስሰራ ነበር። ክረምቱ ሲያበቃም ከሌሎች ሁለት ሰዎች ጋር በመሆን በገዳሙ ውስጥ መደበኛ ትምህርት ቤት በማቋቋም መነኮሳቱንና በአመክሮ ላይ ነበሩትን ወጣት ሴቶች ለአንድ ዓመት ተኩል አስተምሬያለሁ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ትምህርት ቤቱ ተስፋፍቶና ደረጃውን አሳድጎ እየሰራ ይገኛል፡፡” በማለት ይተርካሉ።

የሚድያ ሰው ተካበች አሰፋ በ1963 ዓ.ም ትምህርት ሚኒስቴር በመምህርነት ተቀጥ አዲስ አበባ በሚገኘው በየነመርዕድ ( ዕድገት በህብረት)አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የኅብረት ትምህርት (social studies ) ለ13 ዓመታት አስተምረዋል፡፡ በእነዚህ አመታት ለኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ተመርጠው ለአዲስ አበባ ቅርንጫፍ በገንዘብ ያዥነት አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ “መምህርነት የሰው ልጅ የሚቀረፅበትና የሚስተካከልበት ሙያ ስለሆነ አሁንም በጣም እወደዋለሁ አከብረዋለሁ፡፡” ሲሉ ወይዘሮ ተካበች አሰፋ ይናገራሉ።

እርሳቸው በ1976 ዓ.ም፣ የውጪ ሀገር የትምህርት ዕድል አግኝተው በቀድሞው ቼኮዝሎቫኪያ አካል በነበረችው ስሎቫኪያ በተባለው ሀገር በብራትስላቫ ከተማ በታዋቂውና ጥንታዊው ኮሚዩንስ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ተከታትለው በሁለተኛ ድግሪ ተመርቀዋል፡፡

በ1982 ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ በወቅቱ ስራ የሚመድበው ሲፔኤ ስለነበር ቶሎ ሳይመደቡ ቀሩ።ከአስር ወር ቆይታ በኋላም በ1983 ዓ.ም በማስታወቂያ ሚኒስቴር ተቀጥረው በፕሬስ መምሪያ የካቲት መጽሔት ላይ ተመድበው ሲሠሩ ቆዩ ። በኋላም ወደ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ተዘዋውው በዋናነት የሴቶች ዓምድ አዘጋጅ ሆነው ሲሠሩ ሌሎች ጉዳዮችንም የተመለከቱ ፅሁፎችን ያቀርቡ ነበር፡፡

የኢሕአዴግ መንግስት በሁሉም ክፍለ ሀገሮችና የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የሴቶች ጉዳይ መምሪያ የተባለ አዲስ መዋቅር እንዲቋቋም አደረገ፡፡ በመሆኑም በ1986ዓ.ም በማስታወቂያ ሚኒስቴር በአገሪቱ ቀዳሚ የሆነው የሴቶች ጉዳይ መምሪያ ሲቋቋም ወይዘሮ ተካበች የመጀመሪያዋ ኃላፊ ሆነው ተመደቡ። መዋቅሩ አዲስ በመሆኑም ለተመደበለት የሰው ሀይል የሥራ ዝርዝር በማዘጋጀት ተገቢውን ሥራ ሲያካሄድ ቆየ ።በዚህም ጊዜ ውስጥ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ሥር ካሉት አራት የሚዲያ ድርጅቶችና በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ውስጥ ለሚሰሩ ሴት ሠራተኞች ሴቶችን የተመለከተ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን በማዘጋጀት ሥልጠናዎችን ሲሰጥ ነበር፡፡

በ1987 ሕገመንግስሥት ጸድቆ አዲስ ፓርላማ ሥራ ሲጀመር ማስታወቂያና ባህል ተጣምረው ማስታወቂያና ባህል ሚኒስቴር ተብሎ ተዋቀሩ ።በዚህም የማስታወቂያው የሴቶች ጉዳይ መምሪያ ተዘግቶ የባህሉ ብቻ ጠቅልሎ እንዲይዘው ተደረገ፡፡ የማስታወቂያ የሴቶች ጉዳይ መምሪያ አባላትም ወደ መጡበት ድርጅት ተመለሱ። ወይዘሮ ተካበችም ወደፕሬስ ድርጅቱ ተመልሰው የዜና ማዕከል ኃላፊ ሆነው ተመደቡ። በኋላም ወደ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ተዘዋውረው በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ሲፅፉ ቆዩ ።በመጨረሻም ከነሐሴ 1 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ የጡረታ መብታቸውን አስከብረው ከድርጅቱ ተሰናበቱ፡፡

“…ከአንድ ዓመት እረፍት በኋላ 2005ዓ.ም በትግል በአቋቋምነው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያ ሴቶች ማህበር (ኢትመባሴማ) ተቀጥሬ(ለስሙ) ጽሕፈት ቤቱ እንዳይዘጋና ማኅበሩ እንዳይፈርስ ከፍተኛ ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ ከ2010 የመንግስት ለውጥ በኋላ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ሕግ በመለወጡ ማኅበራችን ራሱን አሻሽሎና ተጠናክሮ ሥራውን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በ2014ዓ.ም በተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ አዲስ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ተመርጠው ተግባራቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡ እኔም በክብር በማዕረግ ለመሸኘት በቅቻለሁ፡፡የማህበሩ አባልነቴ ግን አልተቋረጠም አይቋረጥምም፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያ ሴቶች ማህበርን ለማቋቋም ብዙ ችግርና ፈተና አጋጥሟል፡፡ የነገሩ መነሻ በ1988 ዓ.ም ቤጂንግ ላይ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የሴቶች ጉባኤ ከቀረቡት 12 የመነጋገሪያ ነጥቦች አንዱ “ ሴቶችና ሚዲያ“ የሚለው ርዕሰ -ጉዳይ ነበር፡፡ መምሪያው ሴት ጋዜጠኞችን ስብሰባ ጠርቶ እንዴት ነው መስራት ያለብን በማለት ውይይት እያካሄደ ነበር በዚህ መሀል የሴት ጋዜጠኞችን ማህበር ማቋቋም አለብን የሚለው ሐሳብ ቀርቦ አስተያየት ተሰጠበት ይህም ጉዳይ ለአለቆች ሹክ ተብሎ ከፍተኛ መተራመስን ፈጠረ።

የድርጅቶቹ ኃላፊዎች ሚኒስቴሮቹም መምሪያውን እንደጠላት አዩት፡፡ በመብት መሆኑም ቀርቶ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማህበር (ኢጋማ) እያለ ሌላ ማቋቋም ለምን አስፈለገ ?የሚል ሃሳብ ከሚዲያ ሃላፊዎች ይሰነዝር ነበር እንደውም ከተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ያገናኙትም አልጠፉም አንዳንድ አባላትም ከአለቆቻቸው ወቀሳና ግልምጫ ደርሶባቸዋል፡፡ በጣም የሚገርመውና የሚያሳዝነው ይህቺ አገር አለእኔ ማን አላት? የሚሉ አንዳንድ ኃላፊዎች ተደብቀው ሀገር ጥለው መኮብለላቸው ነው፡፡

በዚህ ግዜ ነው “ ሲሻኝ ጢስ ወጋኝ “ እንዲሉ ማስታወቂያና ባህል ሲጣመሩ የማስታወቂያ ሚኒስቴርን የሴቶች ጉዳይ መምሪያ በማፍረስ እኛን ወደየመጣንት ድርጅት እንድንመለስ ተደረገ፡፡” በማለት የሚድያ ሰው ተካበች አሰፋ ይናገራሉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *