ቦሌ ህብረተሰብ
መምህርት ስርጉት በቀለ
የመጀመሪያዋ የቦሌ ኮምዩኒቲ መምህርት
ቦሌ ኮምዩኒቲ በ1967 ዓ.ም አንድ ተብሎ ሲጀመር፣ ከተቀጠሩ መምህራን የሚጠቀሱት መምህርት ስርጉት በቀለ ናቸው፡፡ መምህርት ስርጉት በቀለ በአዲስ አበባ ጉለሌ አካባቢ በ1936 ዓ.ም የተወለዱ ሲሆን በአድቬንቲስት ሚሽን እና በእቴጌ መነን ተምረዋል፡፡ ቀጥለውም ፣ወደ ደብረብርሀን መምህራን ማሰልጠኛ ተጉዘው ሰልጥነዋል፡፡ በጅማ ለተወሱ ዓመታት ካስተማሩ በኋላም አዲስ አበባ በመድሀኒአለም እና በሲቢስቴ ነጋሲ ተማሪ ቤት አስተምረዋል፡፡ መምህርት ስርጉት ቤታቸውንም የገዙት ቦሌ ሆምስ ሲሆን ቦሌ ህብረተሰብ የአማርኛ መምህርት ሆነው ሲመደቡ የ31 ዓመት ወጣት ነበሩ፡፡ በአሁኑ ሰአት ባህር ማዶ የሚገኙት መምህርት ስርጉት ጎበዝ የአማርኛ መምህርት ነበሩ፡፡ ቦሌ ህብረተሰብ አንድ ብሎ ሲጀመር ከነበሩት መምህራን መካከል መምህር ትንሳኤ፣ ወንድወሰን ሀይሉ፣መምህርት አሰገደች ፣ መምህርት ፀሀይነሽ እና መምህር ሲላስ ዳዴቦ ይጠቀሳሉ፡፡
መምህርት ስርጉት በቀለ ፣ተማሪዎችን በቅጣት ሳይሆን በብልሀት እና በፍቅር በመያዝ ያምናሉ፡፡ አንድ ጊዜ ባቡ የሚባል ልጅ ክፍል ውስጥ በጣም እየረበሸ አስቸገራቸው፡፡ ከዚያም እንዲህ አሉ ፣‹‹ አሁን የዛሬውን ትምህርት ከመጀመራችን አስቀድሞ ባቡ ለ 2 ደቂቃ ያሻውን እንዲያደርግ እንፍቀድለት፡፡ ከዚያም ባቡ ወጥቶ ዘፈነ ለ2 ደቂቃ ያህል፡፡ ከዚያም የመማር ማስተማሩ ሂደት በስነስርአት ቀጠለ፡፡
መምህርት ስርጉት በቀለ፣ ተማሪዎቻቸው ዛሬም በክብር ያነሷቸዋል፡፡ ሲገቡ በ255 ብር ደሞዝ ሥራ የጀመሩት መምህርቷ ከደሞዙ ይልቅ የተከበረው ሙያ ለውስጣቸው ትልቅ ርካታ ያመጣላቸው ነበር።
ሲያስምሩ በደንብ ይዘጋጃሉ፡፡ ተማሪዎች ፊት ለፊት ወጥተው ክርክር እንዲያደርጉ ልቦለዶችን እንዲያነቡ ያበረታታሉ፡፡ ራሳቸውም ግጥም የመጻፍ ዝንባሌ አልፎ አልፎም ለራሳቸው የመጻፍ ውስጣዊ ፍላጎት ስለነበራቸው ተማሪዎቹን በወጉ ያስተምሩነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ ስለ ደራሲያን ማውራት ሲያምራቸው ከሂሳብ መምህሩ ወንድወሰን ሀይሉ ጋር በጣም ስለሚግባቡ በድርሰት ጉዳይ ላይ ይወያያሉ፡፡
መምህርት ስርጉት 7 ዓመት ለሚሆን ጊዜ ሲያስተምሩ ትምህርት ቤቱ ውስጣቸው ያስቀመጠላቸው ነገር እንዳለ ይገነዘባሉ፡፡የትምህርት ቤቱ አስተዳደር ለመምህራን እንደሚያስብ ወይዘሮ ስርጉት አጫውተውናል፡፡ አንዳንድ ተማሪዎቻቸው ትልቅ ቦታ ደርሰው ያገኟቸዋል፡፡ ሀኪም ሆነው ይገኛሉ፡፡ ታዲያ ሁሉም ‹‹ቲቸርዬ›› እያሉ በልዩ ፍቅር ይጠሯቸዋል፡፡ ለዚህ የስነዳ ስራ በሚል ያነጋገርኳቸው መምህርት ስርጉት በቀለ የ80 አመት አዛውንት አይመስሉም፡፡ልክ እንደ ኩል ጥርት ያለው ድምጻቸው እና ምስላቸወንም ሲልኩ ለካስ ከተማሪ ጋር የዋለ ሁሌም አፍላ ነው ለካ ያሰኛል፡፡
ከቦሌ ኮምዩኒቲ ቀጥሎ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ለ18 አመት ያገለገሉት ወይዘሮ ስርጉት የአስተማሪነት ሙያን ከምንም ሙያ በልጦ ይገኝባቸዋል፡፡ ከእኔ ጋር ስለ ቦሌ ኮምዩኒቲ ሲያወሩ በልዩ የሀሴት መንፈስ ተሞልተው ነበር፡፡ 50ኛ አመቱ ላይ እንድረስና ብዙ ሊያወጉን ይችላሉ፡፡
በትምህርት ቤቱ ታሪክ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊ ሴት ርዕሰ መምህርት
ቦሌ ኮምዩኒቲ ሲመሠረት የወጭ ዜጋ የሆነች ሴት ርዕሰ መምህርት እንደነበረች ታሪክ ቢነግረንም ትምህርት ሚኒስቴር ርዕሰ መምህር መመደበ ከጀመረ ወዲህ ወደ ቦሌ ኮምዩኒቲ የመጡ አንድ ርዕሰ- መምህርት ነበሩ። በነጭ ቮልስ ዋገን መኪናቸው ይታወቃሉ። ወይዘሮ ፍሰሀ ገብረየሱስ ።ወይዘሮ ፍሰሀ ቦሌ ኮምዩኒቲ የመጡት በ1972 ሲሆን ለ ሁለት አመትም አገልግለዋል።
ወይዘሮ ፍሰሀ በ1934 በሀረርጌ ሰቀሬ ቀበሌ የተወለዱ ሲሆን በኮከበ ጽባህ፣እና በናዝሬት ስኩል የቋንቋ መምህርት ነበሩ። ከዚያም በየነ መርዕድ አንደኛ ደረጃ ርዕሰ- መምህር ሆነው በማገልገል ላይ ሳሉ ቦሌ ኮምዩኒቲ ተመደቡ።
ወይዘሮ ፍሰሀ ከማልረሳቸው የወላጅ ኮሚቴ መካከል ኮሎኔል አብዲሳ አይረሱኝም ይላሉ። ተራማጅ የነበሩት ኮሎኔል አብዲሳ መምህራንን በመቆጣጠር አጠቃላይ የትምህርት ሂደቱን በመከታተል የተጣለባቸውን አደራ የተወጡ ናቸው።
ወይዘሮ ፍሰሀ እንዳጫወቱን የእጅ ሥራ መምህር ሻምበል ሸጋው እና ኮሎኔል አብዲሳ የትምህርት ቤቱን ወሰን በማካለልና ካርታ እንዲገኝ በማድረግ የማይተካ ሚና ነበራቸው ።
ወይዘሮ ፍሰሀ ከባህር ማዶ ሆነው በስልክ እንዳወሩን በ 2 ዓመት ቆይታቸው ትምህርት ቤቱ መሠረት እንዲኖረው የተቻላቸውን አድርገዋል። ከአስተማሪ ጋር በመተባበርና በፍቅር ሲሠሩ የነበሩት ወይዘሮ ፍሰሀ በሁሉም መምህራን የሚወደዱ እና የሚከበሩ ናቸው። ልጆቻቸውም እንደ አለን ጉደታ፣ ሰላማዊት ጉደታ ያሉት ቦሌ ኮምዩኒቲ የተማሩ ነበሩ ።
የወይዘሮ ፍሠሀ ባለቤት አቶ ጉደታ ቦሩም የወላጅ ኮሚቴ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በህይወት የሉም ።ወይዘሮ ፍሰሀ ለረዥም ዓመት ቦሌ ኮምዩኒቲ ባይሠሩም ትዝታው ግን ዛሬም ከህሊናቸው አልጠፋም። በዚህ ታሪክ ውስጥ በመካተታቸው ብሎም በመታወሳቸው ተወዳጅ ሚድያን መርቀዋል። እኛም አሜን ተቀብለናል ብለናል።
የየምስራች ትዝታ
የምስራች አብዬ እባላለሁ፡፡ከሁለተኛ ክፍል እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምሬያለሁ፡፡
ሒሩት አብዬ፣ በለጠች አብዬ እና ዳኛቸው አብዬ የሚባሉ አብረውኝ የሚማሩ እህቶችና ወንድም ነበረኝ፡፡
የት/ቤታችን መደበኛ ኳስ ተጫዋቾች የነበርነው የምስራች አብዬ፣አለማሽ አስፋው፣ዝናሽ ወልዴ፣ሉባባ ሙጂ፣አማላ መሃመድ፣ ሐለወያ እብዶ እና መሰረት ተፈሪ እንዲሁም አይዳ ሙህዲን ስንሆን አስተማሪያችን ቲቸር እሸቱ ነበር፡፡
የማይረሳኝ ለውድድር የምንሄድባቸው ት/ቤቶች ምስራቅ አጠቃላይ፣ኮከበ ፅብኃ፣ ወንድራድ የመሳሰሉት በእግራችን ጫካውን አቋርጠን ሄደን ፤አሸንፈን ዋንጫ ይዘን እየጨፈርን የምንመጣውን መንገድ ሳስበው ይገርመኛል፡፡ ዘውዱ የሚባል ከገርጂ የሚመጣ ጥቁር ሕንድ የሚመስል ፀጉሩ በጣም የሚያምር ትሁት ልጅ አሁን የእስፖርት አስተማሪ ሆኗል አሉ አብሮን ኳስ ይጫወት ነበር፡፡ ከእስፖርት አስተማሪያችን ከቲቸር እሸቱ ስር አይጠፋም ነበር በጣም ነበር የሚቀራረቡት፡፡
ሌላው የማይረሳኝ ሃይ ጃምፕ እና ሱዚ የሚባል ጨዋታ እንዲሁም ጢቢጢብ በጣም አዘወትር ነበር፡፡
በአንድ ወቅት ደግሞ ከት/ቤታችን ራቅ ያለ ቦታ ገርጂ አረንጓዴ ባህር ወይም ባርኔሮ ሜዳ የሚባል አካባቢ አይሮፕላን መሬት ላይ ወድቆ እየተመላለስን እናይ ነበር፡፡
ከቦሌ የማይረሳኝ ትዝታዎች አንዱ ደግሞ አብረውን ይማሩ የነበሩ እነ የምስራች ታዬ፣ዘላለም ታዬ፣አማረ ታዬ፣ታምራት ታዬ፣ተፈራ ታዬ፣ ትዝብት ታይ፣ሰላም ታዬ፣ ዲንኪላ ታዬ፣ ገሊላ ታዬ፣ በርታ ታዬ……. በጣም ብዙ ናቸው፤ የነሱ ቤት ከፍ ያለ ቦታ ላይ ነው ያለው፤ እና የጋሽ ታዬ ጥቁር መርሰዲስ ነበረቻቸው፤ መኪናዋ ስትታጠብ፤ ዋና መንገድ አስፋልቱ ላይ ውሃው ይፈሳል፤ እና ከሩቅ ስንመጣ ውሃውን ካየን አርፈደናል፡፡ መኪናዋ ካልታጠበች ውሃ የለም አላረፈድንም፤ በጣም የሚገርመኝ የጋሽ ታዬ መኪና የእኛ ሰዓት ነበረች፡፡ በዛ ጊዜ እጅ ላይ የሚታሰር ሰዓት ብርቅ ነበር፡፡
የማልረሳቸው የምወዳቸው፣ የማከብራቸው፣ ፍቅርን ትህትናን ቅንነትን እንድናቅ የቀረፁን ዳይሬከተራችን ወ/ሮ ፍሰሃ ገብረየሱስ፣ አቶ መረሳ ኮከቡ፣ አስተማሪዎቼን ቲቸር መስፍን፣ቲቸር ጌቱ፣ቲቸር አለማየሁ፣ቲቸር ወንዶሰን፣ ቲቸር ስርጉት፣ቲቸር ፀሐይ፣ ቲቸር የኋላሸት፣ቲቸር ሻመበል በእጅስራ ፔሬድ ያቺን የጎማ ቅጣት ያልቀመሰ የለም መቼም አልረሳቸውም፡፡ በሕይወቴ ደግሞ የእግዚያብሔር ፈቃዱ ሆኖ ማግኘት የምመኘው ቲቸር ወንዶሰን እና ቲቸር አለማየሁን ለማየት በጣም እጓጓለሁ፡፡ በተለይ ማትስ አስተማሪዬን ቲቸር ወንዶሰንን፡፡
በተረፈ ከላይ ልጀምርና የማስታውሳቸውን የቀድሞ ተማሪዎች ስም ልጥቀስላችሁ፡፡ መክሊት እሸቱ፣ ራሄል ስኳር፣እምነት ስኳር፣ መአዛ ኤሊያስ፣አስቴር ኤሊያስ፣አማን ገብረየሱስ፣ ዳፍላ ገብረየሱሰስ፣ አሉላ አብረሃ፣ቴድሮስ ሰለሞን፣ዳዊት ሰለሞን፣አበበ ቁራ በካልቾና በጠረባ የሚመታን ሂዱ ይሄን አምጡ፣ ሂዱ እከሌን ጥሩ ብሎ ከአንድ ካልቾ ጋር የሚልከን፤ አሁን ትልቅ ሰው ሆኗል ጣሊያን ሀገር ኢንጂነር ነው፡፡
ኮከብ ዘመድኩን ናይሮቢ በጣም ትልቅ ዲዛይነር ናት፣ ሄለን ገ/ንጉስ፣ ሱዛን ገ/ንጉስ፣ ኤደን በርሄ፣ ካቢው፣ በጣም ላያት የምጓጓው ሳሌም ሃብቱ፣ያፌት ሃብቱ፣ ሳራ ሃብቱ፣ ሊሄም ሃብቱ፣ ራምዚ መሃመድ፣ራሚ መሃመድ፣አማላ መሃመድ፣ኢብራሂም መሃመድ፣ የአስተማሪያችን የቲቸር ግርማዬ ወንድሞች አትክልትና፣ ይትባረክ ከነ አፍሮ ፀጉራቸው አይረሱኝም፤ ፍረወይኒ ገብረዋህድ በጣም የምትናፍቀኝ፣አማኑኤል፣ ሶፊያ አቡበከር፣ የምስራች ጀማል፣ ሳንታሌ ሃይሌ፣ ሎሾ ሃይሌ፣ ሚኪ ብርሃኔ፣ አባይ ብርሃኔ፣ ቤቴልሄም ፓንታሊዮን፣ ምስራቅ አባተ፣ አልጋነሽ አምባዬ፣ሚካኤን አንባዬ፣ ዳንኤል አምባዬ፣ ዮናስ አምባዬ፣ ፍሬህይወት ገብረሚካኤል፣ ፋና ማለደ፣ትዝታ ማለደ፣ የምወዳትና የምትናፍቀኝ ጓደኛዬ ራሄል ወጨፎ፣ ደመላሽ ወጨፎ፣ እሙዬ ወጨፎ፣ ናዝራዊት አማኑኤል፣ ሌዛ ሰብስቤ፣ራሄል ሰብስቤ፣ እስክንድር ሰብስቤ፣ የምትናፍቀኝ ሰሎሜ መስፍን፣ ሃና መስፍን፣
አምዴ ዘውዳለም፣ ስምኦን፣ የአቶ ይድነቃቸው ተሰማ ልጆች ትንሳኤ ይድነቃቸው፣ አልታዬ ይድነቃቸው፣ ስንታየሁ ይድነቃቸው፣ ቤላ፣ዮሳፋት፣ፌቨን ጊላጋብር፣የትምወርቅ በየነ፣ተዋበች፣ ሂሩት ተስፋሚካኤል፣ ሱዛን ጌታቸው፣ዮሀንስ ጌታቸው፣ ሰብለ ተጫኔ፣ጃራ ወልዱ፣ጃራ ግዛው፣ቤቴልሄም ብርሃኔ፣ የትናየት ግዛው፣የምወዳቸው ጓደኞቼ መሰረት ተፈሪ እና ገነት ተፈሪ አሁንም እንገናኛለን ሳባ ተፈሪ፣ ሃይለየሱስ ተፈሪ፣ ብሩክ አምዴ፣ ቅድስት አምዴ፣ ኢሳያስ ገ/ስላሴ ጊፍቲ ገ/ስላሴ፣ መነን ገ/ስላሴ፣ ጴጥሮስ ካሳሁን፣ ሃና ፍስሃ፣እስጢፋኖስ ብርሃኑ፣ ሰብለ ብርሃኑ፣ ቾምቤ፣ ፅጌ፣ ንጋቱ፣ ደስታ ይልማ፣ትግስት ይልማ፣ጌዲዮን ይልማ፣ የማትረሳኝ የምወዳት ፅዮን ጉደታ፣ሰላማዊት ጉደታ፣ ፀሐይነሽ ገ/ሚካኤል፣ እስካሁን ያልተለያየን እህቶቼ ሳራ ሃሰን፣ ሳራ ገ/ፃዲቅ፣ሉባባ ሙጂ፣ ዝናሽ ወልዴ ቢያንስ በሁለት ቀን እንደዋወላለን፤ አለምነሽ ወልዴ፣ አማረች ወልዴ፣ ሀለውያ አብዶ ቤተልሄም ጌታቸው፣ አድማሱ ጌታቸው፣ 2ቱ ትግስት ተስፋዬ ቱሉ፣ ፋንሽ ተስፋዬ፣ አስናቀች ደምሴ
ፀጋዬ ደምሴ ከትምህርት ቤት ሁሌም አንደኛ የሚወጣ የነበረ ተማሪ ደሞዝ ኧረ ስንቱ በጥቂቱ ይሔንን ይመስላል፡፡
የትምህርት ቤቱ የ8ተኛ ክፍል ፓርቲ ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘጋጁት ረባሿ እህቴ ሒሩት አብዬ፣ገነት ተፈሪ፣ የትናዬት ግዛው፣ ጴጥሮስ ካሳሁን፣ እንዲሁም የዳይሬክተራችን የቅርብ ቤተሰብ የሆነችው ቤተልሔም ብርሀኔ ሲሆኑ፤ የመክፈቻ ዳንስ ሲደነሱ ዳይሬክተራችን አቶ መረሳ ኮከቡ ቤቲ ዘመዱ ስለሆነች ተናዶ ሲያፈጥባት እንዳያስቆማት ፊቷን እያዞረች ትደንስ እንደነበር ሒሩት ያስታወሰችውን ነግራኛለች፡፡
በምሳ ሰዓታችን ደግሞ ከት/ቤታችን ፊት ለፊት ገባ ብሎ ጀላቲ ሄደን የምንገዛው አይረሳኝም፡፡ ፓስቲም ይሸጥ ነበር፡፡ አሁን ጮርናቄ የሚባለው፡፡ እንዲሁም ከላይኛው ሱቅ (ከልከል) የሚባል እንደ ዳቦቆሎ አይነት ነገር እየገዛን እንበላ ነበር፡፡
በተጨማሪም ከቦሌ ቁጠባ ወተን ቦሌ ሃይ ስኩል ተምረን የጨረስን ተማሪዎች ብዙዎቻችንን አሰባስቤ በሶስት ወር አንድ ቀን የምንገናኝበት ትልቅ ማህበር መስርቼ ይኸው ማህበራችን በአራት እግሩ ቆሞ በየሶስት ወሩ በናፍቆት እንገናኛለን፡፡ የማህበሩ ስም Bole Senior Secondary School (BSSS) ይባላል፡፡ የማህበራችንም ሊቀመንበር ነኝ፡፡ ገንዘብ ያዥ እኔና ዝናሽ ወልዴ በመሆን በየወሩ መዋጮም በባንክ አካውንት ይጠራቀማል፡፡ ወደፊት እንግዲህ ሌሎቹንም ያልሰሙትን አሰባስበን አንድ አክሲዮን እንደምናቋቁም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ስለነበረን ቆይታ እና አንተም አስታውሰህ ስለ ት/ቤታችን ስላዘጋጀኸው ፕሮግራም ከልብ እያመሰገንኩ እግዚያብሄር ሁላችንንም ባለነበት በእድሜና በጤና ያቆየን እያልኩ ሃሳቤን በዚሁ እቋጫለሁ፡፡
እግዚያብሔር አምላክ በሕይወት ያለነውን ይጠብቀን፣ በደስታ ያገናኘን፡፡ ያረፉትንም ነፍሳቸውን ከፃድቃን ከደጋጎቹ ጎን ያኑርልን ፡፡
ቲቸር ወንድወሰን ሀይሉ የቦሌ ኮምዩኒቲ የመጀመሪያው የሂሳብ መምህር
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ስለ ቦሌ ኮምዩኒቲ የትም ቦታ የማይገኙ ታሪካዊ መረጃዎችን እያካፈለ እንደሆነ ይታወቃል ። የቀድሞው ተማሪዎችም በዚህ ሥራችን ደስ መሰኘታቸውን ገልጸውልናል ። እኛም በዚህ ሥራችን ተጠናክረን እንቀጥላለን ። ትዝታችሁን ከፎቶ ጋር አብራችሁ ላኩልን ባልነው መሠረትም እየላካችሁ ስለሆነ ልባዊ ምስጋናችን ይድረስ ።
አሁን የምናቀርበው ታሪክ የቲቸር ወንድወሰንን ነው። ቲቸር ወንድወሰን በአሁኑ ሰዓት የ70 ዓመት ሰው ሲሆኑ ከደቂቃዎች በፊት አነጋግረናቸው ነበር ። ቲቸር ወንድወሰንን እንድናገኝ የማፈላለጉን ሥራ ሠርቶ ያገናኘንን ደስታ ይልማን ማመስገን እንፈልጋለን ። በዕዝራ እጅጉ የተሰነደውን የመምህር ወንድወሰንን አጭር ታሪክ በጥሞና ይከታተሉ።
መምህር ወንድወሰን ሀይሉ ዋቅጅራ በ1946 በወንጂ ተወልደው አደጉ። የአንደኛ እና የሁለተኛ የትምህርታቸውን በወንጂ እና በናዝሬቱ ተማሩ።
ከዚያም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስ አስተዳደር እስከ 2ኛ ዓመት ድረስ ተምረዋል። በኋላም ትምህርታቸውን አጠናቀዋል።
ከዚያም በ1967 ዓ.ም የ 21 ዓመት ተማሪ ሳሉ ቦሌ ኦሎምፒያ በሚገኘው መሠረተ ክርስቶስ ትምህርት ቤት ለ አንድ ዓመት ያህል አስተምረዋል ።
ወደ ቦሌ ኮምዩኒቲ የገቡት በመስከረም 1968ዓ.ም ሲሆን እንዲገቡ ምክንያት የሆኗቸው ሰው ደግሞ አቶ ዮሴፍ ወልደሚካኤል የሚባሉ የወላጅ ኮሚቴ አባል ነበሩ።እናም በ1968 የ4ኛ እና የ5ኛ ክፍል ሂሣብ መምህር ሆነው ተቀጠሩ። በጊዜው የወር ደሞዛቸው 275 ብር ነው።
መምህር ወንድወሰን አንዳንድ አስተማሪዎችን ያስታውሳሉ ። የአማርኛ መምህር የነበረው ትንሣኤ ማሞን አይዘነጉትም። ሁለቱ አብረውም ይኖሩ ነበር ። አቶ ትንሳኤ በአሁኑ ሰዓት ካሊፎርኒያ ይገኛሉ።ቤተሰብም መስርተዋል።
ሌላዋ የማይረሷት አስተማሪ ቲቸር ስርጉት በቀለን ነው። ከቲቸር በመጽሐፍ ጉዳይ ይወያዩ ነበር። መምህር ወንድወሰን በጊዜው በዕድሜ ገና 22 ዓመታቸው ስለነበር በትኩስ ጉልበት ያስተምሩ ነበር።
ቲቸር ወንድወሰን በብዙ ተማሪዎች የሚወደዱ ስማቸው ጎልቶ የሚነሳ ተወዳጅ መምህር ነበሩ ።
ቲቸር ወንድወሰን ከማይረሱት ተማሪ አንዱ ሜካኒካል ኢንጂነር ደስታ ይልማ ነው። ደስታ ይልማ ያኔ ጎበዝ እንደነበር ቲቸር ወንድወሰን ያስታውሳሉ ።
“..ደስታ…. ጋር በየጊዜው እንገናኛለን። አክባሪዬ ነው ” ሲሉ ቲቸር ወንድወሰን ትዝታቸውን አውግተውናል ። እንደ ቤተልሔም መኮንን፣ ማህሌት መኮንን ያሉ ጎበዝ ተማሪዎችንም ነበሩ ብለውናል።
ቲቸር ወንድወሰን፣ በጊዜያቸው ከነበሩት የወላጅ ኮሚቴ መካከል አቶ ዮሴፍ ወልደሚካኤል ፣ አቶ አበበ ታፈሰ፣አቶ ሚካኤል ደምሴን ያስታውሳሉ።
መምህር ወንድወሰን፣ በጊዜው የተማሪዎች ቁጥር አነስተኛ እንደነበር ነግረውናል ። እናም በጥራት ለማስተማር ሁኔታው አመቺ ነበር ይላሉ።
ቲቸር ወንድወሰን ሀይሉ ሂሣብን ወደውት ነበር የሚያስተምሩት። በጊዜው በተማሪዎች እና በአስተማሪ መካከል የቤተሰባዊነት ስሜት ስለነበር የመማር ማስተማር ሂደቱ የተሳካ ነበር ።
መምህር ወንድወሰን በጊዜው 4 ኪሎ ነበር የሚኖሩት። እናም የቀኑን ሙሉ ውሏቸው ቦሌ ኮምዩኒቲ ነበር ።
ቲቸር ወንድወሰን እንደሚናገሩት በወቅቱ የሥራ ጫና አልነበረባቸውም ። እናም በቂ ዝግጅት አድርገው ወደ ክፍል ይገቡ ነበር ።
ቲቸር ወንድወሰን ተማሪዎቹ ሳያውቁ ኩዊዝ በመፈተን ይታወቁ ነበር ። ይህንንም የሚያደርጉት ተማሪዎች ሳይጨናነቁ እንዲፈተኑ ለማድረግ አስበው ነው።
“….ተማሪዎች በራስ የመተማመን ችሎታቸው የዳበረ ነበር ። ወላጅም ቢሆን ብዙዎቹ የተማሩ ስለነበሩ ካስተማርን በኋላ የልጆቻቸውን ደብተር እየተመለከቱ ይህ ምንድነው ?እያሉ ይጠይቁ ነበር ። እኛም በቂ ዝግጅት እናደርግ ነበር ።” በማለት የዚያን ጊዜ ትዝታቸውን አጫውተውናል ።
ቲቸር ወንድወሰን በመጋረፍ አይታወቁም። አልፎ አልፎ የሚረብሹ ተማሪዎች አይጠፉም። እነዚህን የሚረብሹ ተማሪዎች በሥነ ምግባር ለማነጽ የተቻላቸውን አድርገዋል። ልጆቹ ካደጉም በኋላ አግኝተዋቸው ያውቃሉ።
ቲቸር ወንድወሰን ሀይሉ ከ1968 እስከ 1970 ነሀሴ ድረስ ለ3 ተከታታይ ዓመታት ቦሌ ህብረተሰብ በሂሳብ አስተማሪነት ዘልቀዋል።
ቲቸር ወንድወሰን በ1970 ከቦሌ ህብረተሰብ ለመልቀቅ ሲያስቡ መምህርነትን ጠልተው ሳይሆን የተሻለ ኑሮ ፍለጋ በሚል ነበር ። የወላጅ ኮሚቴው ቲቸር ወንድወሰንን ለማግባባት ታላቅ ጥረት አድርገው ነበር ። እንዲሁም የርዕሰ – መምህር ቦታ እንስጥዎት ተብለው ነበር ። ቲቸር ወንድወሰን ሀይሉ ግን የሥራ ልምዳቸውን አጽፈው በ 1971 መስከረም ወር ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ተቀላቀሉ ። ከ 30 ዓመት በላይም በኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግለዋል።
ቲቸር ወንድወሰን ማስተማር ከምንም በላይ ርካታ ይሰጣቸዋል።ዛሬ በእርሳቸው የተማሩ ልጆች ዶክተር ፣ኢንጂነር ሆነው ሲመለከቱ እንኳንም መምህር ሆንኩ ይላሉ። አስተማሪ የሁሉም አባት የሚለውን አሰብ ሲያደርጉ ደግሞ መንፈሳዊ ርካታቸው ጨምሮ ይገኛል ።
ቲቸር አለማየሁ ጎሹ የቦሌ ኮምዩኒቲ የጂዮግራፊ ፣ የታሪክና የአማርኛ መምህር
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ስለ ቦሌ ኮምዩኒቲ የትም ቦታ የማይገኙ ታሪካዊ መረጃዎችን እያካፈለ እንደሆነ ይታወቃል ። የቀድሞው ተማሪዎችም በዚህ ሥራችን ደስ መሰኘታቸውን ገልጸውልናል ። እኛም በዚህ ሥራችን ተጠናክረን እንቀጥላለን ። ትዝታችሁን ከፎቶ ጋር አብራችሁ ላኩልን ባልነው መሠረትም እየላካችሁ ስለሆነ ልባዊ ምስጋናችን ይድረስ ።
አሁን የምናቀርበው ታሪክ የቲቸር አለማየሁ ጎሹን ነው። እርሳቸውም ለ 11 ዓመታት ቦሌ ኮምዩኒቲ አስተምረዋል።
በአሁኑ ሰዓት የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ይዘዋል።ቲቸር አለማየሁ የ70 ዓመት ሰው ሲሆኑ አነጋግረናቸው ነበር ።
በዕዝራ እጅጉ የተሰነደውን የመምህር ዶክተር አለማየሁ ጎሹን አጭር ታሪክ በጥሞና ይከታተሉ።
ዓለማየሁ ጎሹ የተወለዱት በ1946 አምቦ ከተማ ሲሆን ከአምስት አመት እድሜያቸው ጀምሮ ደግሞ እስከ 1961 ያደጉትና እስከ ስድስተኛ የተማሩት ምዕራብ ኢትዮጵያ ግንደበረት በሚባል ስፍራ ነበር ፡፡ የአንደኛ ደረጃን የተማሩት በግንደበረት ት/ቤት ሲሆን በ1961 ስድስተኛ ክፍልን ከጨረሱ በኋላ በአጎታቸው አማካይነት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት
7ኛ ክፍል በፍሬ ሕይወት ት/ቤት
8ኛ ክፍል በተስፋ ኮከብ ት/ቤት
ከ9-12 በሽመልስ ሀብቴ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የተማሩ ሲሆን በ1966 አስራ አንደኛ ክፍል ሁለተኛ ሴሚስተር ላይ ትምህርት በተማሪዎች የንጉሱን አገዛዘ መቃወም ምክንያት ስለተቋረጠ ቤታቸው ተቀምጠው ነበር ፡፡ በኋላም በ1967 ደርግ ስልጣን በመያዙ ከ10ኛ ክፍል በላይ ያሉ ተማሪዎች በሙሉ ገበሬውን እንዲያስተምሩ የመሬት አዋጅ ለማስፈጸም በየክፍለአገሩ አዝምተዋቸው ስለነበር እስከ 1968 ግንቦት በዛ ቆይተው ሲመለሱ በ1969 11 እና 12 በአንድ አመት ጨርሰው ብሄራዊ ፈተና እንዲወስዱ ተደርጓል ፡፡
“…ከዚህ በኋላ እኔ የአንድ አመት የመምህርነት ስልጠና በመውሰድ በመምህርነት በቦሌ ሕብረተሰብ ትምህርት ቤት 1971 ጥር ወር ላይ ተቀጠርኩ። የመጀመሪያ ደሞዜ 153ብር ሲሆን መስከረም ላይ ለአስተማሪዎች ሲጨመር ለኔም 10 ብር ተጨምሮ 163 አገኝ ነበር፡፡በዚህን ጊዜ አስተምር የነበረዉ ከዛም ለ8 አመት ያስተማርኩት 6፣7፣እና 8ኛ ክፍል ጂኦግራፊና ታሪክ ነበር፡፡ ከ8 አመት በኃላ በሀይማኖት ምክንያት ከ6-8 ካሉት ክፍሎች በማንሳት 1-3 አማርኛ እንዳስተምር ተደረኩኝ። ይህም አእምሮዬን ለመጉዳት የታሰበ ነበር ለእኔ ግን እረፍት ነበር፡፡ደሞዜ አልተነካም ብዙ የሚያስከፋኝ አልነበረም። ሆኖም እየከፋ ተጽእኖ እየበዛ ሲመጣ ስራዉን ብወደውም ለመልቀቅ ተግድጄ ነበር፡፡ ” ሲሉ የቀድሞው የቦሌ ኮምዩኒቲ መምህር አለማየሁ ጎሹ ትዝታቸውን ያወጋሉ።
በ 1981 ግንቦት ላይ ሥራውን በመልቀቅ ወደ ሌላ መስሪያቤት በመግባት ስራ ጀመሩ ፡፡ከዚህ በኋላ ከመምህርነት ከለቀቁ በኋላ እየሰሩ መማራቸውን በመቀጠል ፡-
– ከተግባረ ዕድ ት/ቤት በነዳፊ ምህንደስና (Draftsman)
– ከኢቫንጀሊካል ቲዎሎጂካል ኮሌጅ በዲፕሎማ (Diploma of Theology)
– ከኢቫንጀሊካል ቲዎሎጂካል ኮሌጅ በባችለር ዲግሪ (Bachelor of Theology )
ከዛም ወደ ዚምባቡዌ በመሄድ
– በአፍሪካን ሊደርሺፕ ማኔጅመንት አካዳሚ (ALMA) ማስተርስ ዲግሪ (MA Master of Art in leadership management
– ከቴሎ ዩኒቨርሲቴ (USA) ማስተርስ ዲግሪ (master of Divinity)
– ከቴሎ ዩኒቨርሲቲ የዶክተር ዲግሪ ( Doctor of Ministry) ለመማር ችለዋል።
የቦሌ ሕብረተሰብ ት/ቤት የመጀመሪያ ከሁለተኛ ደረጃ ከጨረሱ በኋላ ስራ ተቀጥረው የሰሩበት ቦታ ሲሆን አስራ አንድ አመት መምህር ሆነው ሲያገለግሉ ለአጭር ጊዜ ተጠባባቂ ዳሬክተር በመሆን ሰርተዋል። እርሳየው ሲቀጠሩ የነበሩት ዳይሬክተር አቶ ሲላስ ዳዴቦ ሲሆኑ ሌሎች አብረዋቸው ከሠሯቸው ዳይሬክተሮች የሚያስታውሷቸው አቶ ፍስሀ ክፍሌ ፤ ወ/ሮ ፍስሀ ገብረየሱስ አቶ ዘውዴ አቶ ታደሰ፣ አቶ ብርሀን ሙላት ሲሆኑ መምህራን ወንድወሰን ፤ትንሳኤ ማሞ ፤ ወ/ሮ ፀሐይ፤ ስርጉት፤ አማረች ፤አየለች ፤በልዩ ፤ ጌጡ ተፈራ ፤ አቶ ከበደ ፤አቶ በለጠ አወቀ ፡አቶ ተሾመ መረጭ፤ አቶ ታደሰ (መምህር)፤ የኋላሸት ካሳ ፡ አቶ ብሻዉ ነበሩ፡፡
“…በትምህርት ቤቱ ቆይታዬ ተማሪዎችን በፍቅር ለማረም ለማስተካከል እቀጣ ነበር ።አካል የሚጎዳ ሳይሆን ማረሚያ ቅጣት እቀጣ ነበር፡፡ በመሆኑ በወላጅ ተከስሼ አላዉቅም ፡፡ አቅም በፈቀደው ሁሉ ከክፍል ማስተማር መቅረት አልፈልግም ፡፡ ክፍል ከገባሁ የምገባው ለማስተማር እንጂ ሰአት ለማሳለፍ አልነበረም፡፡ መምህርነት ወላጅነት ነዉ ብዬ አምን ስለነበረ እንደወላጅ ሃላፊነቴን ለመወጣት እጥር ነበር። ለውጤቱ ምስክሮች ተማሪዎች ናቸው፡፡
ለተማሪዎች በታሪክ ትምህርት ክፍለ-ጊዜ ስለሀገር ስለእናት ስለቤተሰብ የተጻፉ ትምህርቶችን ታሪኮችን በማንበብና በማስነበብ ማስተማር እወድ ነበር ። በጎንዮሽ በመንግስት ቢከለከልም ሥለ ሐይማኖት እምነት እግዚአብሔር አወያያቸዉ ነበር፡፡ አንድ ወቅት የሙዚቃ አስተማሪ ተደርጌ ስመደብ ይህን ግጥም ጽፌ ዜማ ሰጥቼ እንዲዘምሩ አድርጌ ነበር ።ምን ያህሎቹ እንደሚያስታውሱት ባላዉቅም፡-
እምዬ እናቴ የኔ ወዳጄ
አትለይብኝ ሁሌ ከደጄ
እንዴት ይረሳል የናት ዉለታ
በሀዘን በችግር ስትንገላታ የሚል ነበር
እኔ ማስተማርን በጣም እወዳለሁ ፡፡ ሳስተምር ፍላጎቴ እዉቀት መስጠት ነዉ ስለሆነም ለዛ እጥር ነበር ፡፡ ዛሬም ከማስተማር ጋር በተያያዘ ስራ ላይ እገኛለሁ፡፡ በአብዛኛዉ አመራርና አስተዳደር (Leadership management ) ስልጠና በመላዉ ኢትዮጵያና በምስራቅ አፍሪካ አገሮች በመስጠት ላይ እገኛለሁ ፡፡
በመምህርነቴ ጎበዝ ተማሪዎችን እወዳለሁ ።አደንቃለሁ ከማስታውሳቸው ተማሪዎች ይበልጣል ጌታቸዉ ፤ ሜሮን ሚካኤል፤ ርብቃ ጸጋዬ፤ ማሪያማዊት ጉደታ አልረሳቸዉም ፡፡ ደስ የሚለኝ ጎበዞችን መከተል ብቻ ሳይሆን ደከም ያሉትን ወደ ጎበዞች ደረጃ ማምጣት ፍላጎቴና አደርገዉ የነበረ ስራዬ ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ ተማሪዎችን ማዳመጥ እንዲናገሩ እንዲጠይቁ ማድረግ እወዳለሁ፡፡ ተማሪዎች የግል ችግራቸዉን ሳይፈሩ እንዲነግሩኝ አደርግ ነበር ከቻልኩ እረዳለሁ ካልቻልኩ ወላጅ ጠርቼ አናግራለሁ፡፡
በ1974 ትዳር ስመሰርት ተማሪዎች የሰጡኝ ስጦታዎች ዛሬም ትምህርትቤቱን ያስታውሱኛል፡፡ ዛሬ 70 አመቴ ላይ ነኝ 4 ልጆቼ አስተምሬ ድሬ 8 የልጅ ልጆች አያት ነኝ ክብሩ ሁሉ ለእግዚአብሔር ይሁን” በማለት መምህር አለማየሁ ታሪካቸውን አውግተውናል ።
ቲቸር የኋላእሸት ካሣ – የትምህርት ቤቱ ጎበዝ ሰዓሊ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ባለፉት 9 ቀናት ብቻ በ8 ተከታታይ ክፍሎች የቦሌ ኮምዩኒቲን ታሪክ ከቀድሞ ተማሪዎችና አስተማሪዎች እየጨለፍን ስናቀርብ ነበር ። እስካሁን አብዛኛው ያቀረብነው፣ ከ1967-1980 መካከል በትምህርት ቤቱ ውስጥ የተማሩና ያስተማሩ ሰዎችን ትዝታ ነው። በ 9 ቀናት ውስጥ 200 የሚጠጉ ትዝታ ቀስቃሽ፣ የትም ያልታዩ ምስሎችን ያጋራን ሲሆን እነዚህም ምስሎች የቀድሞውን የተረሳ ትዝታ ለማምጣት ዓይነተኛ ሚና ነበራቸው። ብዙዎች ጓዳቸውን ፈትሸዋል። የድሮ ዕቃዎች የሚቀመጡበትን ስፍራ ዳግም አራግፈዋል። ይህን ነበር የምንሻው። ታሪክ ነጋሪ ምስል ካርቶን እና ኮመዲኖ ውስጥ ከሚቀመጥ አርነት ቢወጣ አይሻልም? አርነት የወጡ ሰነዶች እና ምስሎች በአሁኑ ሰዓት በመላ ዓለም ከአንዱ ስልክ ወደ ሌላው እየተንሸራሸሩ ይገኛሉ። ደስ ሲል። ቦሌ ህብረተሰብ ተሰነደ ይሏል እንዲህ ነው። በተጨማሪም ፣እስካሁን በቻልነው ዐቅም በየዘመኑ(በየባቹ) የነበሩ ተማሪና መምህራን እንዲጠቀሱ እያደረግን ነው። አስተማሪዎች ተገቢውን ክብር እንዲያገኙም ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ ታሪካቸውን እያስቀመጥን እንገኛለን።
በዛሬው ክፍል 8 የሚያጫውቱን መምህር የኋላእሸት ካሣ አባገላን ናቸው።
እኒህ መምህር በርካታ መጻህፍትም የአርትዖት ሥራ ሠርተዋል። አሁን በቅርቡ ወደ ማተሚያ ቤት የሚላክ የራዕይ መጽሐፍ ትርጓሜ አለ። የኮሙኒኬሽን መጽሐፍ ጽፈውም ጨርሰዋል። ሌሎች ያለቁ መጻህፍት ወደ 13 ደርሰዋል። መ ምህር የኋላእሸት ቦሌ ህብረተሰብ ለ4 ዓመት ያስተማሩ ሲሆን በኪነ- ጥበብ ክህሎታቸውም ይታወቃሉ። እኒህ መ ምህር በ 1975 ለአንዲት የ8ኛ ክፍል ተማሪያቸው ገንቢ አስተያየታቸውን ጽፈውላት ነበር ። ተማሪዋ ኤደን በዕደማሪያም ስትባል ፣8ኛ ክፍል ስታጠናቅቅ አስተማሪዎቿ አውቶግራፏ ላይ ሀሣብ እንዲሰጧት ጠይቃ ረዘም አድርገው ከጻፉት ውስጥ መምህር የኋላእሸት አንዱ ነበሩ። ይህን አውቶግራፍ ባህር ማዶ የምትገኘው ኤደን በዕደማርያም ለ41 ዓመታት ጠብቃ አቆይታው ነበር። ለእኛም ልካልናለች። ሙሉውን ታነቡት ዘንድ ጋብዘናል። ከዚህ ጽሁፍ ጋር አብረን ፖስት አድርገነዋል።ኤደን ከልብ እናመሠግናለን ። ያንቺም ትዝታ ይቀጥላል። መምህር የኋላእሸት በምክራቸው” ብልህ ልጅ የአባቱን ተግሳፅ ይሰማል። ሰነፍ ግን ይንቀዋል” ብለው ምክራዊ ጽሁፋቸውን ይቀጥላሉ። በመቀጠልም መጽሐፍ ቅዱስ የህይወት ዋና መርህ መሆኑን ሊነበቡ የሚገባቸውንም ጥቅሶች አክለው ጽፈውላታል።
ቲቸር የኋላእሸት ማናቸው?
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ንጉሥ ወልደጊዮርጊስ ሠፈር ት/ቤት አሁን ዕድገት በሥራ በሚባለው ተከታተሉ። ሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በመድሃኔዓለም አጠቃላይ ተምረዋል። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ1975 ዓ.ም እስከ 1980 ተከታትለው በቋንቋ እና ሥነ- ጽሁፍ ዲግሪያቸውን ተቀበሉ ። ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበረውም በማታው የትምህርት ክፍል ነበር።
የአራት ዓመት የቦሌ ሕብረተሰብ ቆይታቸው በደስታ የታጀበ ነበር ።
ወደ መምህርነት ሙያ ሲዘልቁ፣ ገና የሃያ ዐመት ኮበሌ ነበሩ ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንደጨረሱ ነበር ወደ መምህርነት ሙያ የገቡት፡፡ ጊዜው 1975 ዓ.ም ነበር፡፡ ለትምህርት ቤቱ ባስገቡት የትምህርት ማስረጃ መሠረት ተጠርተው ቃለ -መጠይቅ የተደረገላቸው በወላጅ ኮሚቴው ሰብሳቢ በአቶ መላከ ሰላም ሞገስ ነበር፡፡ ሜክሲኮ በነበረው የማዕድን ሚኒስቴር ቢሯቸው ድረስ ተጠርተው አንዳንድ ቃለ-መጠይቅ ተደርጎላቸው ብር 182 የወር ደሞዝ ተቆርጦላቸው የማስተማር ሥራቸውን በማግስቱ ጀመሩ፡፡
“…በቦሌ ሕብረተሰብ ማህበረሰብ ውስጥ በዕድሜ ትንሹ መምህር ነበርኩ፡፡ ከስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች በዕድሜ ከስድስትና ከሰባት ዓመት እምብዛም አልበልጥም ነበር፡፡ ተማሪዎች ተለቅቀው ሲወጡ ከመሃከላቸው ከተገኘሁ የሚታዘብ ሰው ከተማሪዎቹ አንዱ እንጂ እኔን እንደ መምህር የሚቆጥረኝ አልነበረም፡፡ ” ይላሉ መምህር የኋላ እሸት ካሳ።
የተቀጠሩት የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎችን አማርኛ፣ እንግሊዝኛና የሳይንስ ትምህርት እንዲያስተምሩ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ፣ከተመደቡበት ጊዜ አንስቶ እነዚያን ዛሬ ትላልቅ የሆኑትን ያኔ ገና ህጻናት የነበሩትን ልጆች ለማስተማር በፍቅርና በስሜት ሲታትሩ እንደነበር አይዘነጉትም፡፡
“… በተፈጥሮዬ የኪነ -ጥበብ ዝንባሌው ስለነበረኝ ሥዕልም ሙዚቃም ሥነ- ጽሑፍም እሞክር ነበር፡፡ የሥነ-ጽሑፍ ተሰጥዖዬን ለማጎላመስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎች የመጀመሪያ ዲግሪዬን በማታው የትምህርት ክፍል እየተማርኩ ነበር ፡፡ የነበረኝን የሥዕልና ጥሩ የካሌግራፊክ ተሰጥዖ ለማስተምራቸው ተማሪዎች የማስተማሪያ መርጃ ዝግጅት ተጠቅሜበታለሁ፡፡ የእንግሊዝኛ ፊደላትንና አንዳንድ ቃላትን እንዳስተምርበት የተለያዩ ፍሊፕ ቻርቶች አዘጋጅቼ እጠቀም ነበር፡፡ እነዚህ ፍሊፕ ቻርቶች በመምህራን ማረፊያ ተደርድረው በተለያየ ጊዜ ከዞን ትምህርት ቤት ለሚመጡት ሱፐርቫይዘሮች እንዲታይ ይደረግ ነበር፡፡ በዚህ ሥራዬ ከሚያበረታቱኝና ጎሽ ከሚሉት መካከል በወቅቱ የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር የነበሩት አቶ መረሳ ኮከብ ምንም ጊዜ አይረሱኝም፡፡
ከእኔ ጋር የቀረበ ወዳጅነት የነበረው መምህር ተስፋዬ ዓለሙ አሁን በሕይወት የሌለ፣ አአዩ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ምሩቅ ስለነበር ሰባተኛና ስምንተኛ ተማሪዎችን እንግሊዝኛ የሚያስተምረው እርሱ ነበር፡፡ በተጨማሪም መምህር አለማየሁ ጎሹ ፤ በቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት በልጅነቴ ያስተማረኝ፣ አብረንም በአንድ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ስለነበርን፣ እንደገናም አብረን ስናስተምር የሥራ ባልደረባ ሆንን። ለእኔ እንደ ታላቅ ወንድም ነበር፡፡ በተጨማሪም የአምስተኛና የአራተኛ ክፍል ተማሪዎችን ሳይንስ የሚያስተምረው መምህር አሥራት መንገሻ ሌላው የልብ ወዳጄ ነበር፡፡ በተረፈ ከእኔ በፊት ትምህርት ቤቱ ውስጥ ተቀጥረው ሲሰሩ የነበሩት እነ ሻምበል ሸጋው፣ (እሸቱቸስፋዬ፣ ጌጡ ተፈራ፣ ጋሽ በለጠ አወቀ፣ ቢሻው ተፈራ እኒህ ሁሉ አሁን በህይወት የሉም) እንደ ታላቅነታቸው ከህይወታቸውም ከአብሮነታቸውም ብዙ የተማርኩና ተወዳጅ ባልደረቦቼ ነበሩ፡፡ ” በማለት መምህር የኋላ እሸት ትዝታቸውን ያወጋሉ።
ቀረቤታቸው ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጋር ስለሆነ ዛሬ ብዙም ስማቸውን የማያስታውሷቸው እንቁ የነበሩት ተማሪዎችን ከቶም አይረሷቸውም፡፡
አንድ ጊዜ በጊዜው የመንግሥት ሥራ ላይ ስለነበሩ ከመንግሥት ልዑክ አንዱ ሆነው ወደ አሜሪካ በረራ ላይ እያሉ አንዲት መልኳን የት እንደሚያውቋት እርግጠኛ ያልሆኑባት ልጅ በአውሮፕላን ላይ ስታስተናግድ ነበር፡፡ጉዞው ረጅም ስለነበር ልጅቷን የት ይሆን የማውቃት? እያሉ በማሰላሰል ላይ ሳሉ በመጨረሻ መጣችላቸው፡፡ ለካ በቦሌ ሕብረተሰብ አንደኛ ይሁን ሁለተኛ ክፍል ያስተማሯት ልጅ ነበረች፡፡ በረራቸው ከባለሥልጣን ጋር ነበረ፤ ልጅቷን ጠርተው ሲያነጋግሯት አብረዋቸው የነበሩት ባለሥልጣናት ምቾት አልነበራቸውም፡፡ ሆኖም ቲቸር የኋላእሸት ግን ጠርተዋት የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን የት እንደተማረች ጠየቋት፣ እርሷም ተናገረች። ከዚያ በኋላ ለመሆኑ ቲቸር የኋላእሸትን ታስታውሻቸዋለሽ ወይ? ብለው ጠየቋት። ፊቷ በርቶ አዎ ብላ ትኩር ብላ ስትመለከታቸው ምስላቸው መጣላት እና እርስዎ ነዎት አይደል? አለች ፤ መልክሽን እንጂ ስምሽን ማስታወስ አልቻልኩም ማን ትባያለሽ? አሏት። ማሪያማዊት እባላለሁ ብላ መለሰች፡፡
መምህር የኋላእሸት ያን አጋጣሚ ሲያስታውሱ ብዙ ትዝታ ውስጣቸው ተመላለሰ ። እንዲህ ይላሉ፦
“… በጣም ደስ አለኝ፡፡ ወልዶ ልጁ ለወግ ማዕረግ እንደበቃችለት አባት ሆኜ ታላቅ ርካታ ተሰማኝ፡፡ ከዚያም ምቾት አጥተው የነበሩት ከእኔ ጋር የነበሩት ባለሥልጣናት ሁኔታውን ስነግራቸው በጣም ተገርመዋል፡፡ የመምህር ትልቁ ደሞዝ ይህ ነው፡፡ ልጆቹ ፣ተማሪዎቹ ቁምነገር ላይ ደርሰውና ራሳቸውን ችለው ማየት፡፡ ለዚህ ነው ሃዋሪያው ዮሐንስ ‹‹ልጆቼ በእውነት እንዲሄዱ ከመስማት ይልቅ የሚበልጥ ደስታ የለኝም።›› ያለው፡፡
በአጠቃላይ ቦሌ ሕብረተሰብ የቆየሁት ለአራት ዓመታት ነው፡፡ አራተኛውና የመጨረሻውን ዓመት የትምህርት ቤቱ የማዕከል ኃላፊ ሆኜ ሰርቻለሁ፡፡ ይህም 1978 ዓ/ም ነው፡፡ በዚያን ዓመት በትምህርት ቤቱ ውስጥ እስከተወሰኑ ዓመታት አሻራ ሆነው የቆዩ ሥራዎቼን እንደተውኩ አስታውሳለሁ፡፡ ትምህርት ቤቱ ከነበራቸው ሁለት ብሎኮች ውስጥ በመተላለፊያዎቹ ግድግዳ ላይ ለተማሪዎች ማስተማሪያ መርጃነት የሚገለግሉ ሥዕሎችን መስራቴን አስታውሳለሁ፡፡ ትምህርት ቤቱ ከውጭ በሚታየው ግንብ ላይ በትልቁ ከውጭ እንዲታይ የትምህርት ቤቱን ሥምና አርማ መሥራቴንም አልዘነጋውም፡፡
ከዚህ ዓመት በኋላ ቀደም ብዬ ጀምሬው የነበርኩትን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋዜጠኝነት ለመቀጠል ከመምህርነት ሙያ ተሰናብቼ ለቀቅኩ፡፡ በዚያም በፍሪላንሰርነት ለሦስት ዓመታት ያህል በፕሮግራም አዘጋጅነት ቆይቼ በወቅቱ አገሪቱ እንደ መመሪያ አድርጋ የያዘችው ርዕዮተ ዓለም ጸረ- እግዚአብሔር የነበረው የማርክሲዝምና የሌኒንዝም አመለካከት ስለነበር፣ ጣቢያውም በዚህ ርዕዮት የተቃኘ ስለነበር እዚያ መሥራት እንደማልችል ተገልጾልኝ ሥራዬን እንዳቆም ተደረገ፡፡ እኔም በማገባደድ ላይ የነበርኩትን የሥነ- ጽሑፍ ትምህርቴን በመቀጠል ጨረስኩ፡፡
ከዚያም ብዙ ሳልቆይ ለሌላ ከፍተኛ ትምህርት ወደ ናይሮቢ ኬንያ በማቅናት በወቅቱ በአፍሪካ ውስጥ ከነበሩት ሁለት የኮሙኒኬሽን ኮሌጆች መካከል አንዱ በሆነው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተጨማሪ የኮሙኒኬሽን ዲግሪዬን ተምሬ ጨረስኩ፡፡
ትምህርቴን እንደጨረስኩ በወቅቱ በአገራችን ወንጌልን መስበክ ክልክል ስለነበር ለዚህ ዓላማ ተቋቁሞ የነበረውም ዝነኛውና አንጋፋው የብስራተ ወንጌል ሬዲዮ ጣቢያም በመንግሥት ተወርሶ ስለነበር፣ ይህንኑ ወንጌል በመገናኛ ብዙሃን ለማሰራጨት የነበረው ብቸኛ አማራጭ ከውጭ አገር በሚዘጋጁ የሬዲዮ ፕሮግራሞች ነበር፡፡ እኔም ከሲሼልስ በሚሰራጨው የሬዲዮ ጣቢያ ውስጥ የአማርኛው ክፍል ኃላፊና ከፍተኛ የፕሮግራም አዘጋጅ ሆኜ ለሦስት ዓመታት
ሰራሁና በናይሮቢ የነበረኝን የስድስት ዓመታት ቆይታ አጠናቅቄ ወደ አገሬ ተመለስኩ፡፡ ከዚያም የግሬት ኮሚሽን ሚኒስትሪ በሚባል መንፈሳዊ ድርጅት ውስጥ የኢየሱስ ፊልም ፕሮጄክት ዳይሬክተር በመሆን 5 ዓመታት አገልግያለሁ፡፡
በዚያ የነበረኝን ቆይታ ጨርሼ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራም ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን አቅም ግንባታ ፕሮጄክት ሥራ አስኪያጅ ሆኜ ለ2 ዓመታት ሰርቻለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ለቀጠሉት 23 ዓመታት በተለያዩ ባንኮች ማለትም በዳሸን ፣ በንብና በብርሃን ባንኮች ውስጥ የማርኬቲንግና የሕዝብ ግንኙነት ሥራ አስኪያጅ በመሆን አገልግዬ በጡረታ ከተገለልኩ አንድ ዓመት አልፎኛል፡፡
ሆኖም አሁንም በአንድ የቢዝነስ የግል ኩባንያ አማካሪና የዋናው ሥራ አስኪያጅ ረዳት በመሆን እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ እኔ የአንዲት ሚስት ባል የሁለት ልጆች አባት ስሆን የመጀመሪያ ልጄን ድሬአለሁ፡፡ ሁለተኛው ልጄ የኮሌጅ ተማሪ ነው፡፡
በዚህ አጋጣሚ የቦሌ ሕብረተሰብ በሕይወት ላሉት ማህበረሰብ በአጠቃላይ እንኳን ለትምህርት ቤቱ ሃምሣኛ ዓመት ኢዩቤልዩ ምሥረታ አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቴን ከልብ እገልጻለሁ፡፡ የቀድሞ ተማሪዎቼ ዛሬ ትላልቅ ሆናችሁ ቤተሰብ የመሰረታችሁና የልጆች አባት የሆናችሁ ሁሉ እግዚአብሔር እናንተንና ቤታችሁን ይባርክ ፡፡ ለመዝጊያ እንዲሆን ይህንን በረከት እንደ አባት ልባርካችሁ እወዳለሁ፡፡
በመከራ ቀን እግዚአብሔር ይስማችሁ የያዕቆብ አምላክ ስም ያቁማችሁ። ከመቅደሱ ረድኤትን ይላክላችሁ፥ ከጽዮንም ያጥናችሁ። ቍርባናችሁን ሁሉ ያስብላችሁ፣ የሚቃጠል መሥዋዕታችሁን ያለምልምላችሁ። እንደ ልባችሁ ይስጣችሁ ፣ ፈቃዳችሁንም ሁሉ ይፈጽምላችሁ። መዝሙር 19፡1-4″ በማለት መምህር የኋላ እሸት ካሣ ትዝታቸውን፣ አሁን የደረሱበትን እንዲሁም ለተማሪዎቻቸው ያላቸውን ምርቃት አድርሰዋል።
ቲቸር አስራት መንገሻ(ዶክተር) ጎበዝ የሳይንስ አስተማሪ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ባለፉት 11ቀናት ብቻ በ8 ተከታታይ ክፍሎች የቦሌ ኮምዩኒቲን ታሪክ ከቀድሞ ተማሪዎችና አስተማሪዎች እየጨለፍን ስናቀርብ ነበር ። እስካሁን አብዛኛው ያቀረብነው፣ ከ1967-1980 መካከል በትምህርት ቤቱ ውስጥ የተማሩና ያስተማሩ ሰዎችን ትዝታ ነው። በ 9 ቀናት ውስጥ 200 የሚጠጉ ትዝታ ቀስቃሽ፣ የትም ያልታዩ ምስሎችን ያጋራን ሲሆን እነዚህም ምስሎች የቀድሞውን የተረሳ ትዝታ ለማምጣት ዓይነተኛ ሚና ነበራቸው። ብዙዎች ጓዳቸውን ፈትሸዋል። የድሮ ዕቃዎች የሚቀመጡበትን ስፍራ ዳግም አራግፈዋል። ይህን ነበር የምንሻው። ታሪክ ነጋሪ ምስል ካርቶን እና ኮመዲኖ ውስጥ ከሚቀመጥ አርነት ቢወጣ አይሻልም? አርነት የወጡ ሰነዶች እና ምስሎች በአሁኑ ሰዓት በመላ ዓለም ከአንዱ ስልክ ወደ ሌላው እየተንሸራሸሩ ይገኛሉ። ደስ ሲል። ቦሌ ህብረተሰብ ተሰነደ ይሏል እንዲህ ነው። በተጨማሪም ፣እስካሁን በቻልነው ዐቅም በየዘመኑ(በየባቹ) የነበሩ ተማሪና መምህራን እንዲጠቀሱ እያደረግን ነው። አስተማሪዎች ተገቢውን ክብር እንዲያገኙም ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ ታሪካቸውን እያስቀመጥን እንገኛለን።
በዛሬው ክፍል 9 የሚያጫውቱን መምህር አስራት መንገሻ (ዶክተር) ናቸው።
መምህር አስራት መንገሻ፣ በሳይንስና በእንግሊዝኛ አስተማሪነታቸው ይታወቃሉ። ቦሌ ኮምዩኒቲ ፣ ከ1975-1978ዓ.ም ከ 5-8 ክፍል የተማረ ሊያስታውሳቸው ይችላል።
ቲቸር አስራት መንገሻ፣ በ1956 ዓ.ም በሰላሌ ተወለዱ። ሰላሌ አጋምሶ ተወልደው ያደጉት ቲቸር አስራት መንገሻ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም በፊታውራሪ ማሞ ስዩም ትምህርት ቤት ተምረዋል። ከዚያም የ6ኛ ክፍል ትምህርታቸውን በራስ ስዩም መንገሻ ተከታተሉ።በመቀጠልም ከ 7-12 በተፈሪ መኮንን እና በደብረ ዘይት ትምህርት ቤት ተማሩ። የዩኒቨርስቲ ቆይታቸው ደግሞ በወንዶ ገነት የተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ነበር። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከዚያ ነው የተቀበሉት።
ቲቸር አስራት 20 ዓመታቸውን ባከበሩ ማግስት ነበር የቦሌ ኮምዩኒቲ አስተማሪ ለመሆን የበቁት። በጊዜው ተማሪዎቹ ፣ ለዕውቀት ያላቸው ጥማት የሚደንቅ እንደነበር ቲቸር አስራት ያስታውሳሉ። ቦሌ ህብረተሰብ ማህበራዊ ግንኙነትን የተማርኩበት ፣ ጥሩ ትዝታ ያሳለፍኩበት ቤት ነውም ይላሉ መምህሩ።
በጊዜው ቲቸር አስራት መኖሪያቸው ፈረንሣይ ሌጋሲዮን አካባቢ ነበር ። እናም ያ ዘመን ለእኔ ወርቃማ ነው ሲሉ ነግረውናል ።
ቲቸር አስራት በወጣትነት ዕድሜያቸው ቦሌ ኮምዩኒቲ ሲያስተምሩ በወላጆች ኮሚቴ እና በተማሪዎች ዘንድ ይከበሩ ነበር። ምን እንደሚያስተምሩ በሚገባ ያውቃሉና። ተማሪ ላይ አካላዊ ቅጣት ከማድረስ ይልቅ መምከር ይቀናቸዋል ። ከተማሪያቸው አንዷ እና በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ባህር ማዶ የምትገኘው ካቢው መኮንን ሸገኔ ይህንን አስተያየት ሰጥታለች”….
ቲቸር አስራት ሳይንስ አስተምረውናል፤ 5ኛ ወይም 6ኛይመስለኛል።በጣም ትዕግስተኛና ረጋ ያሉ አስተማሪ ነበሩ።ስናጠፋ ከመቅጣት ይልቅ በምክር እንዲሁም ከመፅሀፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ሲጠቀሙ አስታውሳለሁ።ለእኔ ልዩ ትዝታዬ ስለአባቴ(መኮንን ሸገነ) ያላቸውን አድናቆትና እኔም ልኮራ እንደሚገባኝ በተደጋጋሚ የነገሩኝን ነው። ” በማለት ሀሣቧን ሰጥታ ነበር ።
መአዛ ይትባረክ የተባለች ተማሪም አሜሪካ አገር ስትሄድ ፣ እንደቲቸር አስራት ዓይነት አስተማሪ ገጠመኝ ብላ መናገሯ ይታወቃል።
ቲቸር አስራት መንገሻ ከርዕሰ- መምህር አቶ መረሳ ኮከቡን አይዘነጓቸውም።”….. አቶ መረሳ የማልረሳቸው ርዕሰ- መምህር ናቸው።የበለጠ እንድማር ይገፋፉኝ ነበር።” በማለትም አስተያየታቸውን ለግሰዋል።
ቲቸር አስራት መንገሻ ቦሌ ኮምዩኒቲ ሲቀጠሩ ወርሀዊ ደሞዛቸው 275 ብር ብቻ ነበር ። ተማሪን በማገዝ ግን ያምናሉ። ከሳይንስ ውጭ ተማሪዎች የቤት ሥራ ሲሰጣቸው ቀለል ብሏቸው ወደ ቲቸር አስራት ይሄዳሉ። ቲቸር አስራትም ደስ ብሏቸው ተማሪዎችን ይረዱ ነበር ። ይህም ትልቅ የመንፈስ ርካታ ያመጣላቸው ነበር።
ቲቸር አስራት ቦሌ ኮምዩኒቲ ለ 4 ዓመት ብቻ ነው የሠሩት። ከዚያ በኋላ ፉድ ፎር ዘ ሀንግሪ ወደተባለ ግብረ- ሠናይ ድርጅት በመግባት አገልግለዋል። ትምህርታቸውንም በመቀጠል የማስተርስ እና የፒኤችዲ ዲግሪያቸውን ይዘዋል።
ቲቸር አስራት ፣ በ 1975ዓ.ም 8ኛ ክፍል የነበረች ተማሪ አውቶግራፏ ላይ አስተያየት እንዲያሰፍሩላት ጠይቃቸው ነበር። ተማሪዋ አለማሽ አስፋው ስትባል ከቲቸር አስራት የተጻፈላት አስተያየት እንዲህ የሚል ነበር”….ከሰው ጋር ያለሽን ተግባቢነት ሳላደንቅ አላልፍም። ከአስተማሪዎች እና ከተማሪዎች ጋር ጥሩ ወዳጅነት አለሽ። ይህም ለወደፊቱ የሚጠቅምሽ ባህሪ ነው።አዳዲስ ነገሮችን ለመማር እና ለማወቅ የምታደርጊውን ያላሰለሰ ጥረት ማድነቅ አለብኝ ። ሌላ የምጨምረው ሀሣብ አይኖረኝም። ይህንኑ መልካም ባህሪ ለወደፊቱ ህይወትሽ ጠብቀሽ ብታቆይው ጥሩ ይመስለኛል ” በማለት በእንግሊዝኛ ጽፈውላት ነበር ። መምህሩ፣ ከዛሬ 41 ዓመት በፊት የጻፉትን አስተያየት ወይም የእጅ ጽሁፋቸውን አሁን ፖስት ስለሚደረግ ያነቡታል። መምህር ምንጊዜም ደግ ነው። ዕውቀቱን ብቻ ሳይሆን መልካም ምኞቱንም ያለአንዳች ስስት ይሰጣል።