ቁጥር አንድ ኤዲተር ከውድነህ ዘነበ- ስለ ታምራት ገብረጊዮርጊስ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የፎርቹን ጋዜጣ መስራች ስለሆነው ስለ ታምራት ገብረጊዮርጊስ የስራ እና የህይወት ታሪክ ረዘም ያለ ጽሁፍ ከዚህ ቀደም ማውጣታችን ይታወሳል፡፡ ከወጡት ጽሁፎች መካከል የውድነህ ዘነበ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡ ሀሙስ ሰኔ 1997 ዓም ለኔ ልዩ ቀን ነበር ። ጠዋት ነበር ሃያ ሁለት አካባቢ በሚገኘው የ Fortune ጋዜጣ አሳታሚ ወደ ሆነው Independent news and media pls ቢሮ የደረስኩት ። ታምራት ገ/ጊዮርጊስን አገኘሁት – ፎርቹን ጋዜጣ ላይ መስራት እንደምፈልግ ነገርኩት ። በአግራሞት እያየኝ አንዳንድ ጥያቄዎች ጠይቆኝ ሲያበቃ – ዛሬ ጀምር አለኝ ።
ተዘጋጅቼ ያመጣሁት ሁለት ዜናዎች አሉኝ – እያቸው አልኩት ። እየተገረመ በወቅቱ የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ለነበረው አየነው ኃይለስላሴ አሳልፎ ሰጠኝ። በዚያው ሳምንት ነበር አንዱ ዜና ፊት ለፊት ገፅ አንዱ ዜና ደግሞ ገፅ አስር ላይ የታተመልኝ ። ይህን እድል ማግኘት ለኔ ተአምር ነበር ። የታምራት ቢሮ መስራት ለሚፈልግ ማንኛውም ሰው ክፍት ነበር ። አለመታደል ሆኖ ልበልና የፎርቹን ጋዜጣ ቢሮ የስራ ከባቢ ትጋት ፣ ንቃት ፣ ትኩረት የሚፈልግ በመሆኑ ሰው አይበረክትም – ቢሮው በውጥረት የተሞላ ነው። እኔ እንኳን በአምስት አመት ቆይታዬ የነበሩኝ ባልደረቦች ቢሰለፉ ወልመራ ይደርሳሉ ። ገብተን የወጣን የፎርቹን ሰዎች ሁሉ የማንክደው ሃቅ ቢኖር ስራ አውቀን መውጣታችንን ነው ። ታምራት በኔ እይታ በኢትዮጵያ ቁጥር ፩ ኤዲተር ነው ።
ዜና ፅፈን እሱ ቢሮ ገብተን ስንወጣ ዜናችን ተገለባብጦ ፣ ተደበላልቆ ፣ ተቆርጦ ፣ ረዝሞ በአስገራሚ ጥራት ኤዲት ተደርጎ እናገኘዋለን ። የመጨረሻውን ኮፒ ስናየው የራሳችን መሆኑን እንጠራጠር ሁሉ ነበር ። ዜና ይዘን ታምራት ቢሮ በገባን ቁጥር ረመጥላይ ቆመን ፣ ተለብልበን ፣ ነደን ፣ ግለን ፎርቹን የገባንበትን ቀን ረግመን እንወጣለን – አንዳንድ ልጆች ሸልለው ገብተው አመድ መስለው ይወጡ ነበር ። እኔ ከግለቴ በረድ ስል ብዙ እየተማርኩ መሆኑን አስባለሁ – ለአዲስ ስራም እነሳለሁ ። ምክንያቱም እሁድ ጠዋት አራት ኪሎ ኢንተር ሜዞ ቁጭ ብዬ ቡናዬን እየላፍኩ ጋዜጣዬን ሳነብ ልዩ ስሜት ይሰማኛል – የሚደወሉልኝ ስልኮች ኢነርጂ ይሰጡኛል። የአርብ ወይም የቅዳሜ ምሽቱ ንዴት ይረሳኛል ።
ፎርቹን የገባሁት በታሪከኛው ምርጫ 1997 ዓም ማግስት በመሆኑ ወቅቱ ውጥረት የተሞላበት ነበር ። አንድ ረቡዕ ጠዋት ሁሌም እንደምናደርገው ኤዲቶሪያል ተቀምጠን የደረስንበትን የስራ ደረጃ እየተያየን እያለ በአዲስ አበባ ከተማ ከባድ ደም አፋሳሽ ግጭት ተነሳ ። በወቅቱ ታምራት ያቀረበልን ሃሳብ ዛሬም አይረሳኝም ። እስካሁን የሰራነውን እሁድ አናትመውም – አዲስ ስራ እንስራ ወይስ ትተን ቤታችን እንግባ በማለት ጠየቀ ። የተወሰንን ጋዜጠኞች እንስራ አልን። መስራት የማይፈልግ አይገደድም ። የተፈጠረው ከባቢ ለሕይወት አስጊ ስለሆነ አስቡበት በማለት ጊዜ ሰጠን ። እኛም እንሰራለን የሚል ታሪካዊ ውሳኔ አሳልፈን ። ለሚያልፍ ዝናብ አልበሰብስም ያሉ ጋዜጠኞች ወደ ቤታቸው ሲከቱ ታምራት እና የተወሰንን ጋዜጠኞች ስራ ላይ እንደነበርን በታሪክ ተፅፏል ። ለአራት ይመስለኛል አዲስ አበባን አስምረን ተከፋፍለን ከሕይወት ጋር ግብግብ ፈጥረን – አዲስ አበባ ስታነባ – የኢህአዴግና የቅንጅት ፖለቲካ ሰው ሲበላ ተመለከትን – ለአንባቢዎቻችን ታማኝ በመሆን ጉደኛ ጋዜጣ አትመን አስነበብን። የታምራት ፎርቹን ጋዜጣ ለኤዲቶሪያል ስራዎች ከፍተኛ ገንዘብ ያፈሳል።
ከከተማ ወጣ ባሉ ቦታዋች ዜና ሲፈጠር በድርጅቱ ተሽከርካሪ እና በጀት ከማንም ቀድመን ቦታው እንደርሳለን ። እኔ ከአንድ ሽህ ብር በታች በሆነ ደሞዝ ጀምሬ በኢትዮጵያ ፕሬስ ዘርፍ ትልቁ ተከፋይ እስከመሆን ደርሼ ነበር። የተወሰንን ጋዜጠኞች ከድርጅቱ ጠቅላላ ወርሃዊ ገቢ የሆነ ፐርሰንት ከደሞዛችን በተጨማሪ ይከፈለን ነበር። ታምራት እንደ አሰሪ ዳር ሆኖ ወይም እንደ ባለሃብት ከፍታ ላይ ሆኖ አይደለም ተቋሙን የሚመራው ። የእያንዳንዱን ጋዜጠኛ እንቅስቃሴ ይከታተላል – በአገሪቱ እየተካሄደ የሚገኘው ክስተት እንዲያመልጠው አይፈልግም ። ከሱ ጋር ዜና መስራት አስደሳች ነው ። አንዳንድ ዜናዎችን ባይ ላይን መካፈል እያለበት ይተውልናል ። ለምን ስንለው ኤዲት ማድረግ ስራዬ ነው በማለት ይመልሳል። በፎርቹን ጋዜጣ ላይ ብዙ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ፅፈናል ። የአገሪቱን ማክሮ ኢኮኖሚ ፣ መሠረተ ልማት ፣ የግብርና ዘርፍ ፣ የአካባቢ ጥበቃ ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ፣ የአገሪቱ ገቢ እና ወጭ ንግድ ፣ የፌደራል መንግስት በጀት ፣ የኢንዶመንት ድርጅቶች ግዝፈት ፣ የውጭና የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ትኩረት ፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር እንቅስቃሴ … በትኩስ ትኩሱ ልፈናል – ለሚዛናዊው የፎርቹን አንባቢ በሰንበት ምድር አድርሰናል። የዚህን ሁሉ ክሬዲት የአንበሳው ድርሻ የታምራት ገ/ጊዮርጊስ ነው። በዚህ ሂደት ከግዙፍ ኩባንያዎች ዛቻ ፣ ማስፈራሪያ አልፎ ተርፎም ክስ ቀርቦብን በፍርድ ቤት መድረክ በዝረራ አሸንፈናል ።ይህም በኢትዮጵያ የፕሬስ ታሪክ ከግል ኩባንያ ክስ የቀረበብን እና ያሸነፍን የመጀመሪያዎቹ ሆነን በታሪክ ተመዝግበናል ።
ታምራት ለጋዜጣ አንባቢው ማህበረሰብ ሃብት ነው ፣ ታማኝ ነው ፣ ለጋዜጠኞቹም ጥላ ነው ። እሱ ከማንም ጋር ጠብ የለውም ፣ ከማንም ጋር በፍቅር አይወድቅም ። የመርህ ሰው ነው። በኢትዮጵያ በኢንግሊዝኛ ቋንቋ የሚታተመውን ትልቁን ፎርቹን ጋዜጣ በብዙ ችግር ውስጥ ይዞ መቆየቱ ያስመሰግነዋል ። የታምራት የሊደር ሽፕ ፍልስፍና አነጋጋሪ መሆኑ እንዳለ ሆኖ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ከሁለት አስርት አመታት በላይ ጋዜጣውን ይዞ የመጣበት መንገድ ተጠንቶ መማሪያ ቢሆን እላለሁ። ታሜ መዝናናትም ያውቅበታል – ከሱ ጋር የአዲስ አበባን በተለይም የካዛንቺስን የምሽት በረከት መቋደስ መታደል ነው። ታምራት – ለሠጠኸኝ ዕድል – ላሳለፍናቸው መልካም ዓመታት አመሠግናለሁ። ውድነህ በአሁኑ ሰአት ግሪን ሚድያና ኮሚኒኬሽን የተባለ ድርጅት ከፍቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ ውድነህ ታምራት ጋር ሲሰራ የቀሰማቸውን በጎ ልምዶች በራሱ ድርጅት ላይ ተግባራዊ ያደርጋል፡፡ ውድነህ ሀገራዊ ሪፎርም ዳግም የተወለደው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የተሰኘ ባለ 200 ገጽ መጽሀፍ ጽፎ ያሳተመ ሲሆን ጽናትን ከፎርቹን በማግኘቱ ታምራትን ደግሞ ማመስገን ይወዳል፡፡