ልጅ ይልማ ዴሬሳ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የሀገር ባለውለታዎች ታሪክ በወጎ ተጽፎ ለአዲሱ ትውልድ መሻገር አለበት ብሎ በጽኑ ያምናል፡፡ ግለ-ታሪካቸው በመጽሀፍ ሊጻፍ ከሚገባቸው ሰዎች አንዱ ልጅ ይልማ ዴሬሳ ናቸው፡፡ እኒህ ኢትዮጵያን ከማንም በላይ የሚያስቀድሙ ሰው በተለይ በገንዘብ ሚኒስትርነት በሌሎችም የመንግስት የስራ ሃላፊነት ሀገራቸውን በንቃት ያገለገሉ ናቸው፡፡ ስለ እኒህ ሰው ግለ-ታሪክ እነሆ፡፡
ትውልድ እና ትምህርት
ክቡር ልጅ ይልማ ከአባታቸው ከክቡር ብላታ ዴሬሣ አመንቴና ከእናታቸው ከወ/ሮ ጫልቱ ሶንቶ በመስከረም 14፣ 1900 ዓ.ም. ወለጋ ውስት ጩታ በምትባል ቀየ ተወለዱ። ብላታ ዴሬሣ የሌቃ ነቀምቴ መንግሥት መስራች ስመጥር ሞቲ በከሬ ጎዳና የልጅ ልጅ ነበሩ።
ብላታ ዴሬሣ፣ ልጃቸውን፣ወጣት ወንድሞቻቸውንና ጥቂት የወንድ ዘመዶቻቸውን ዘመናዊ ትምሕርት፣ስልትና አስተሳሰብ እንዲቀስሙ ስላሹ አዲስ አበባ ከዳግማዊ ምኒሊክ ት/ቤት የመጀመርያ ምሩቃን ከነበሩት መካከል ቀኛዝማች ዘውዴ ታደሰን እንደ አስተማሪ ቀጥረው ወደ ጩታ ወሰዷቸዉ። በዚህን ወቅት ልጅ ይልማና ወጣት ዘመዶቻቸው አባታቸው አጥር ግቢ በተሠራችው ት/ቤት ውስጥ ቀኛዝማች ዘውዴ፣ ሂሳብ፣ አማርኛ፣ እንግሊዘኛና ሳይንስ አስተማሯቸው። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ብላታ ዴሬሣ የራሳቸውን ገንዘብ ከፍለው የጩታ ተማሪዎቹን አዲስ አበባ ዳግማዊ ምኒሊክ ት/ቤት አስገቧቸው።
ልጃቸው ትምሕርታቸውን ዳግማዊ ምኒሊክ ት/ቤት በሚከታተሉበት ወቅት በኢትዮጵያ ታሪክና ባህል የላቀ ዕውቀት የነበራቸው ብላታ ዴሬሣ ስለ ዘመናዊ ትምሕርት፣ ኤኮኖሚ፣ ባህል፣ ፖለቲካ እና ህብረተሰባዊ ጉዳዮች «ብርሃንና ሰላም» ለሚባለው ጋዜጣ ብዙ ድርሰቶችና አስተያየቶች ያበረክቱ ነበር። ልጅ ይልማ የመጀመሪያ ደረጃ ትምሕርትታቸውን ከፈጸሙ በኋላ ከአጎቶቻቸው ከልጅ በላይና
ከልጅ ገብረግዚ እመንቴ ጋራ ሆነው ግብፅ አገር አስክንድሪያ በሚገኘው ቪክቶርያ ኮሌጅ የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርታቸውን አጠናቀቁ። ከዚያም ለከፍተኛ ትምሕርት ልጅ ይልማና አጎቶቻቸውን አባታቸው ወደ እንግሊዝ አገር ላኳቸው።
በመጀመሪያ ልጅ ይልማ በኬምብሪጅና በኦክስፎርድ «ስኩል ሰርቲፊኬት» ተቀበሉ። ከዚያም በበርክቤክ ኮሌጅ የሎንዶን ማትሪኩሌሽን/የሁለተኛ ደረጃ ዲፕሎማ/ ፈተና ካለፉ በኋላ፣ በሎንዶን ኤኮኖሚክስ ት/ቤት ትምሕርታቸውን ቀጥለው በኢኮኖሚክስ የባችለር ኦፍሳይንስ ዲግሪ በመአረግ ተቀበሉ። ከዚያም በኋላ፣ ዤኔቭ ሔደው ለአንድ ዓመት የኢንተርናሽናል ሕግ ተማሩ።
ልጅ ይልማ ትምሕርታቸውን ፈጽመው ወደ ሀገራቸው ከጠላት ወረራ ሁለት ዓመት በፊት ተመለሱ። በዚህን ጊዜ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ፣ የእስካንዲኔቪያን አገሮችና የሊግ ኦፍ ኔሽንስ (የዓለም መንግስታት መሐበር) ክፍል ኃላፊ ሆነው የጣልያን ጦርአዲስ አበባ እስኪገባ ድረስ አገለገሉ።
በተመለሱ በዓመታቸው ልጅ ይልማ ወ/ሮ ቅድስት ተሰማን አገቡ። ወ/ሮ ቅድስት የግርማዊት እቴጌ መነን ት/ቤት ሲመሰረት ከመጀመሪያዎቹ ተማሪዎች እንዷ ነበሩ። በትምህርታቸውም ባሳዩት ብርታት ከግርማዊት እቴጌ መነን የወርቅ ሰዓት ተሸልመው ነበር። ወ/ሮ ቅድስት የፊታውራሪ ተሰማ ባንቴና የወ/ሮ ፍሰሐ ያየህይራድ ልጅ ናቸው። ፊታውራሪ ተሰማ ከ1924 እስከ 1927 ዓ.ም.
በኢትዮጵያና በእንግሊዝ ሶማሌላንድ ወሰን ክልል ሥራ ዋና ተካላይ ነበሩ። በእናታቸው በወ/ሮ ፍሰሐ ወ/ሮ ቅድስት የደጅአዝማች ገርማሜ ወልደሐዋርያት ተወላጅ ነበሩ። ደጅአዝማች ገርማሜ አፄ ምኒሊክን አፄ ቴዎድሮስ ካሰሯቸው አምባ መቅደላ በስልት ወደ ሸዋአስኮብልለው ያባታቸውን የንጉሥ ሀይለመለኮትን አልጋ መልሰው እንዲይዙ የረዱ የወጣቱ ልዑል የተከበሩ አማካሪ ነበሩ።
ጣልያን አገራችንን በወረረ ጊዜ ልጅ ይልማ ከወጣት ምሁራንና የሆለታ እጩ መኮንኖች ጋራ ሆነው «ጥቁር አንበሳ» የሚባለውን የአርበኝነት ድርጅት ወለጋ ውስጥ አቋቋሙ። የመጀመሪያውም ፕሬዝደንት ሆነው ተመረጡ። እጩ መኮንኖቹ የጣልያን መንግሥት ወደ ነቀምቴ እርቅ ለመፍጠር የላካቸውንልዑካን ገደለውየመጡባቸውን ሶስት አውሮፕላን አቃጠሉ። ከዚህም በኋል ቂም ለመበቀል የግራዚያኒ አየር ሀይልነቀምቴን በቦንብ ደበደበ። በዚህን ወቅት ልጅ ይልማና የጥቁር አንበሳ አባላት ከልዑል ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ ጦር ጋራ ተቀላቅለው የጣልያን እጅ ገና ያልገባ አካባቢ ውስት ወደ ደቡብ ምስራቅ አመሩ። መንገድም ለይ ሲዋጉ ቆይተውከፋ ውስጥ በሚገኘው ጎጀብ በተባለው ወንዝ ላይ በጠላት እጅ ተያዙ። ከዚያም ጠላት ልዑል ራስ እምሩን፣ ደጃዝማች ታዬ ጉልላቴን ልጅ ይልማንና አቶ ሀዲስ ዓለምአየሁን ወደ ጣልያን አገር ልኳቸው ፖንዛና ሊፓሪ በተባሉ ደሴቶች አሰራቸው።
ልጅ ይልማ ጣልያን አገር በእስር በቆዩበት ወቅት አባታቸው ብላታ ዴሬሣ ሱዳን በስደተኝነት ኑሮ በንግድ ካካበቱት ገንዘብ ለአርበኞች ትጥቅና ስንቅ ወደ ኢትዮጵያ እየላኩ አዲስ አበባ የነበረውን የጣልያንን ኮሎንያል መንግሥት ሲያዋክቡ ቆዩ። አርበኞቹን መደገፍ ትተው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ የጣልያን መንግሥት ብላታ ዴሬሣን ለማማበል ልጅ ይልማን ከሶስት ዓመታት በኋላ ከእስር ፈቶ አገራቸው መለሳቸው። ብላታ ዴሬሣ ግን ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አገራቸው እስኪመለሱ ድረስ አርበኞቹን መርዳት ሳያቆሙ ሱዳን በስደት ቆዩ።
ልጅ ይልማ ከነፃነት መልስ በኋላ፣ በ1933 ዓ.ም. የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዋና ጸሐፊ ሆኑ። በዚያን ጊዜ ከመጀመሪያ ባለቤታቸው ከወ/ሮ ቅድስት ጋራ ተለያይተው ከወ/ሮ ኤልሳቤጥ ወርቅነህ ጋራ በመስከረም ወር 1933 ተጋቡ። ወ/ሮ ኤልሳቤጥ የአዛዥ ወርቅነህ እሸቴና የወ/ሮ ቀጸላወርቅ ቱሉ ልጅ ናቸው። ከጣልያን ጦርነት በፊት ወደ አውሮፓ ለትምሕርት ከተላኩ በጣት ከሚቆጠሩት ሴት ተማሪዎች አንዷ ነበሩ። አባታቸው አዛዥ ወርቅነህ የመጀመርያው ዘመናዊ ኢትዮጵያዊ ሐኪም፣ በተለያየ ጊዜ ደግሞየአፄ ምኒሊክ ሐኪም፣ የተፈሪ መኮንን ት/ቤት የመጀመሪያ ድሬክተር፣የጨርጨር አገረገዥና በጦርነቱ ወቅት በእንግሊዝ አገር የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሙሉ ሥልጣንአምባሳደር ሆነው አገልግለዋል። በእናታቸው በወ/ሮ ቀጸላወርቅ፣ ወ/ሮ ኤልሳቤጥ የንጉሥ ሣህለሥላሴ ተወላጅ ናቸው።
ከ1934 እስከ 1941 ዓ.ም. ልጅ ይልማ መጀመሪያ በዋና ዲሬክተርነት፣ ቀጥሎ በምክትል ሚንስትርነት የገንዘብ ሚኒስቴርን መሩ። በዚያን ወቅት በገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ የባጀት ክፍል፣ የግምጃ ቤትና የሒሳብ ክፍል፣ የመሬት ግብር ክፍል፣ የሥራና የሰው ግብር ክፍል፣ የክሬዲትና የፊናንስ ክፍል፣ የመንግሥት ንብረት ክፍልና ጉምሩኮች አቋቋሙ። ገንዘብ ሚኒስቴርን እየመሩ ልጅ ይልማ የኢትዮጵያን ያየር መንገድ እንዲመሰረትና እንዲቋቋሙ ትልቅ ሚና ተጫወቱ። በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ የተባለውንና የኢትዮጵያ ብር (ካረንሲ) ከነዋስትናው ማቋቋም። ኢትዮጵያ የብሬቶን ውድ ድርጅቶች (የዓለም ባንክና የሞነቴሪ ፋንድ የሚያጠቃቅል) አባል እንድትሆን ማድረግ። ታክስ ሁሉ በገንዘብ እንጂ በእቃ እንዲከፈል (ማለትም የገባር አገዛዝ) እና የገበያ ቀረት ማስቀረት። የ1939 የባጀት አዋጅ እንዲደነግና በዚህ አዋጅ ምክንያት የመንግሥት ሠራተኛ ሁሉ በእህል ወይም በቁሳቁስ መከፈሉ ቀርቶ ደመወዝ በገንዘብ እንዲከፈል ማድረግ። የለም፣ ለም ጠፍና ጠፍ መሬቶችን የመደበው የ1937 የመሬት ግብር አዋጅ እንዲደነገግና ሥራ ላይ እንዲውል ማድረግ። የዚህ የመሬት ግብር ዓላማ የማያርሰው እንዲያርስ ብዙ ጋሻ የነበራቸው በግብረ ጠል መሬቱ እንዲከፋፈል የሚያደርግ እንዲሆን ነበር።
ከ1941 እስከ 1945 ዓ.ም. ልጅ ይልማ የንግድና እንዱስትሪ ምክትል ሚንስትርና የፕላኒንግ ቦርድ ፕሬዝዳንት መሪ ሆነው ሚኒስቴሩን በውጭ ንግድ፣ ባገር ውስጥ ንግድ፣ የንዱስትሪ፣ የሕግ እና የፕላን ክፍል እንዲከናወን አደረጉ። ለኅብረተሰባዊና ኤኮኖሚያዊ ልማት መከናወን እስታቲስቲክ መረጃዋች አስፈላጊ ስለሆኑ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የእስታቲስቲክ ቢሮ እንዲቋቋም አደረጉ። ነጋዴዎችና ባለ እንዱስትሪዎች ሕጋዊ አቋም እንዲከተሉ ለማድረግ የሕግ ክፍል ባልደረቦቻቸው የንግድ ሕግ (ኮሜራሻል ኮድ) እንዲደነግጉ አድርገው ሕጉም እንዲታወጅ አደረጉ።
ልጅ ይልማ የአገሩ ኢንፍራስትራክቸር እንዲጠናከር አዲስ ከተቋቋመው ከዓለም ባንክ ጋር የመጀመሪያውን የኢንተርናሽናል ብድር መንግሥት እንዲዋዋል አደረጉ። በዚህም ብድር እርዳታ ያውራ ጎዳና ባለስልጣን፣ የቴሌ ኮሚዩኒኬሽን ቦርድ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ተቋቋሙ። በአገሩ ኤኮኖሚ ውስጥ ቡና ከፍ ያለ ቦታ መያዝ ስለጀመረ ወደ ውጭ አገር የሚላከውን ቡና ዓይነትና ጥራት የሚቆጣጠር ክፍል ለመጀመሪያ ጊዜ በሚኒስቴር ውስጥ አቋቋሙ። በተጨማሪም የኤክስፖርት እህሎች ጥራትና ደረጃ እንዲጠበቅ መበጠሪያዋች በየበሮቹ እንዲቆሙ ከማድረጋቸውም በላይ የእህል ቦርድ እንዲቋቋሙ አደረጉ።
ከ1945 እስከ 1950 ዓ.ም. ልጅ ይልማ በዩናይትድ ስቴትስ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርና የኢትዮጵያ መልክተኞች በዓለም መንግሥታት መሐበር ጉባዬ መሪ ሆነው ተሾሙ። ልጅ ይልማ ከተባበሩት መንግስታት መደበኛው ጉባዬ ሥራ ተካፋይ ከመሆናቸውም በላይ ሁለት ጊዜ የጉባኤው ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠው አገልግለዋል። አንደኛው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ትኩር ብሎ የተመለከተው ጉዳይ በኢትዮጵያና በአሜሪካ ጥቁር ሕዝብ መካከል ወዳጅነት ለመፍጠርና ግንኝነት ለማሻሻል ነበር። ይህን ለማከናወን ልጅ ይልማ ከሐዋርድ ዩኒቬርስቲ ፕሬዚዳንትና መምሕራን ጋር ወዳጅነት በማብጀት በነሱ አማካኝነት ከዋሽንግተን ውጭ ካሉትም ጥቁር መሪዎች ጋራ ለመተዋወቅ መንገዱን ከፈቱ። አገር ውስጥ የነበረውን የዘረኝነት ስርዓት በመቀበል ዋሺንግተን ዲሲ የነበሩ ኤምባሲዋች የብሔራዊ በዓል ቀናቸውን በግብዣ በሚያከብሩበት ወቅት የአሜሪካ ጥቁር እንግዶች ከነጭ እንግዶች እንዳይቀላቀሉ አይጋበዙም ነበር። የላይቤሪያ ኤምባሲ በብሔራዊ በዓል ቀናቸው ማግስት ለአሜሪካ ጥቁር እንግዶች ብቻ ግብዣ ያደርግ ነበር። ልጅ ይልማ በኢትዮጵያ ብሔራዊ በዓል ቀን ጥቁርና ነጭ እንግዶችን ሳይለዩ አንድ ላይ ይጋብዙ ነበር።
ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በ1947 ዓ.ም. አሜሪካን ለመጎብኘትመጥተው በነበረ ጊዜ ልጅ ይልማና ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ፕሬዝዳንት አይዘንሐዋርንና ያሜሪካ ካቢኔት አባላት ኢትዮጵያ ኤምባሲ በጋበዙ ምሽትአዳም ክሌትን ፖውል የሚባሉትን ዝነኛ የኮንግሬስ አባል የነበሩ ጥቁር ሰውና የሐዋርድ ዩኒቬርስቲ ፕሬዚዳንት ሞርድካይ ዋየት ጆንሰንን ጋበዙ። በዚህና በሌሎችም ልዩ ልዩ ዘዴ ኢትዮጵያ ጥቁሮችን አትወድም ተብሎ ሲሰበክ የነበረውንና ጥላቻም ፈጥሮ የቆየው ብዙ ተሻሻለ። ከአያሌ ዘመናት አንስቶ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖለቲካ ሲመለከት የቆየው የምዕራብ አውሮፓን ኃያል አገሮች ዝምድና ብቻ ነበር። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋራ የፖለቲካ ዝምድና ቢጀመርም ይህ አገርም የምዕራባውያን ቡድን ውስጥ ስለነበረ ፖለቲካችን ከነርሱ እምብዛም አይርቅም ነበር።
ብዙ የእሲያና ጥቂት የአፍሪካ አገሮች ነጻነታቸውን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከተጎናጸፉ በኋላ ለመደጋገፍና ጥቅማቸውንም ለማስከበር«ያፍሪካና የእስያ ቡድን» የሚባል ወገን ለመፍጠር በባንዱንግ ከተማ በ1947 ዓ.ም. ተሰበሰቡ። ልጅ ይልማም የኢትዮጵያ መንግሥት የዚህ አካል እንድትሆን ስላሹ የንጉሠ ነገሥቱን መንግሥት መከረው የኢትዮጵያ መንግሥት ልዑካን መሪ ሆነው በባንዱንግ ስብሰባ ላይ ከቻናው መሪ ቹ ኤን ላይ፣ ከግብፁ ፕሬዚዳንት ጀማል አብዱልናሰር፣ ከሕንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ጃዋሃራል ኔኅሩ እና ሌሎችም መሪዋች ጋራ ሆነው «ያፍሪካና የእስያ ቡድን» የሚባለውን ድርጅት በአገራችው ስም መሠረቱ።
ሕይወታቸውን በሙሉ የኢትዮጵያና የዓለም ታሪክን ለማወቅና ለመረዳት የሚወዱትና የሚሹት ልጅ ይልማ ብዙ መጽሐፍት ከማንበብ ሌላ አባታቸውን ብላታ ዴሬሣንና ሌሎች ብዙ የታሪክ አዋቂዎችን ያነጋግሩ ነበር። የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሽልማት ድርጅት ባላደራ በነበሩበት ወቅት የታሪክ አዋቂዋችን፣ ለምሳሌ ፕሮፌሰር ሊኦ ሀንስቤሪን ተሸላሚ እንዲሆኑ ድርጅቱን አሳውቀዋል።
አሜሪካ አምባሳደር በነበሩ ወቅት ልጅ ይልማ በታሪክ ማስትሬትአቸውን ለማግኘት ዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘውጆርጅታውን ዩኒቨርስቲ ተመዝግበው ይማሩ ነበር። በሥራ ምክንያት አገራቸው ስለተመለሱ ጨርሰው ለመመረቅ ባይችሉም «ቢዛንቲን ኤምፖየር ኤንድ ዘ ክሩሴድስ» የሚል ጥናት ጽፈው በ1957 ዓ.ም. በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ አሳትመዋል። በተከታዩ ዓመት «የኢትዮጵያ ታሪክ በአሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን» የሚባለውን ታዋቂ ጽሑፋቸውን ለሕዝብ አቅርበዋል። ይህ ጥናት በኢትዮጵያና በአዳል መንግሥታት በነበሩት ግጭቶችና በኦሮሞ ሕዝብ በአፍሪካ ቀንድ የብስ ላይ ስለነበረው እንቅስቃሴ የሚያተኩር ነው።
በመጋቢት 1950 ዓ.ም. ንጉሠ ነገሥቱ ልጅ ይልማን ከአሜሪካ ጠርተው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አድርገው ሾሟቸው። ሥራቸውን እንደጀመሩ የዘመናዊ ትምሕርት ያላቸውን ሠራተኞች ቀጥረውሥራ ላይ መደልደል የልጅ ይልማ የመጀመሪያው እርምጃቸው ነበር።ከነዚህም መካከል በኋላ ለአምባሳደርነትና ለሌሎችም ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ ብዙዎች ነበሩ። ለምሳሌልጅ ይልማ ዶ/ር ጌታቸው መካሻን ቀጥረው ለመጀመሪያ ጊዜ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ውስጥ የኢትዮጵያና የአፍሪካን ጉዳይ በተለይ የሚከታተል የአፍሪካ ዴስክ ወይም ክፍል ከፍተው ዶ/ር ጌታቸውን ሃላፊ አድርገው ሾሟቸው። በዚያኑ ወቅት አክራ ላይ በኳሜ ንክሩማ ሰብሳቢነት በሚደረጉት አንደኛ፣ በሚያዝያ 1950 ዓ.ም. «የነፃ አፍሪካ የመጀመሪያው ጉባዬ» ሁለተኛ፣ በታህሳስ 1950 ዓ.ም. «የመላው አፍሪካ ሕዝብ ጉባዬ» ኢትዮጵያ እንድትሳተፍ አድርገዋል።
በሰኔ 1951 ዓ.ም. ኢትዮጵያ «የነፃ አፍሪካ የሁለተኛው ጉባዬ» ሰብሳቢ በሆነች ጊዜ ልጅ ይልማ ሊቀመንበር ሆነው ጉባኤውን መርተዋል። እነዚህ የተለያዩ ስብሰባዎች ለነፃ አፍሪካ አገር ዲፕሎማቶች ለመተዋወቅ፣ ለመደማመጥና ለመተማመን ቦታና ጊዜ ስላበረከቱ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በግንቦት 1955 ዓ.ም. አዲስ አበባ ላይ ለተቋቋመው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሠረቱን ጥለው አጠናክረው አዳብረው አዘጋጅተዋል።
ለረጅም ጊዜ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርስቲ የቦርድ ሊቀመንበር ሆነው ያገለገሉት ልጅ ይልማ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት በየዓመቱ ከአፍሪካ አሃጉር ለሚመጡ ለሁለት መቶ ተማሪዎች ስኮላርሽፕ ሰጥቷቸው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርስቲ ተመዝግበው ለመማር ችለው ነበር። ከነዚህም ተማሪዎች መካከል ተመርቀውአገራቸው ከተመለሱ በኋላ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሰው ላገሮቻቸው ትልቅ አስተዋፆ ያደረጉጥቅቶች አይደሉም።
ኢትዮጵያ «ያፍሪካና የእስያ ቡድን» በ1947 ዓ.ም. አባል ለመሆን ስለበቃችፖለቲካዋ ከምዕራባዊያን ድንበር አልፎ ከሌሎችም መንግሥታት ጋር የተሻለ ዝምድና ለመፍጠር ቻለች። ይህን ዓላማ የበለጠ ለማዳበር ልጅ ይልማ ከመስኮብና ከሌሎችም የምስራቅ አውሮፓ አገሮች ጋራ ግንኙነታችንን ማሻሻል አስፈላጊ መስሎ ስለታያቸው በ1950ና 51 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስፈላጊ የነበሩትን እርምጃዎች ሲወስድ ቆይቶ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሶቭየት ሕብረትንና ቼኮዝላቫኪያን በሐምሌ1951 ዓ.ም. ለመጎብኘት በቁ። በዚህም ጉብኝት ምክንያት ኢትዮጵያ ከሶቭየት ሕብረትና ከቼኮዝላቫኪያ ለልማት የሚሆን ብድር ከማግኘቷምሌላ ከ«ምስራቅ ቡድን» ተብለውከሚጠሩት አገሮችጋራ ግኑኝነቷ እጅግ እየተሻሻለ ሄደ።
በ1953 ዓ.ም. ከተከሰተው ታህሣሥ ግርግር ጥቂት ወራት በፊት ንጉሠ ነገሥቱ ልጅ ይልማን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዘዋውረው የገንዘብ ሚኒስትር አድርገው ሾሟቸው። ልጅ ይልማ ይሄንን ሚኒስቴር ለሁለተኛ ጊዜ ሲመሩ ያተኮሩት በፊት ባልነበሩት አሁን በርካታ መሆን በጀመሩት በኤኮኖሚ በፊናንስና በሕግ ልምድ ያዳበሩና በነዚሁ ትምሕርቶች ከአዲሱ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርስቲ እውቀት ቀስመው የሚመረቁትን ኢትዮጵያውያን በብዛት ቀጥሮ የገንዘብ ሚኒስቴርን በዘመናዊ አወቃቀርና አሠራር ለመለወጥ ነበር።
ይሄንንም ዓላማ ለመጎናጸፍ ልጅ ይልማ ራዕያቸውን ለአዲስ ቅጥረኞቹ ካካፈሉ በኋላ የቴክኖክራቶቹ ዕለታዊ ሃላፊነትና ድርጊት ውስጥ ጣልቃ ሳይገቡ በሙሉ ዕምነት ድጋፍ ሰጥው ለውጡ እንዲፈጸም ማድረግ ነበር። ከነዚህም የዘመናዊ ለውጥ ሐዋርያ መካከል እነ አቶ ተፊሪ ለማን፣ እነ አቶ ቡልቻ ደመቅሳን፣ እነ አቶ ተድላ ተሾመን፣ እነ አቶ ዳምጤ በረደድን፣ እነ አቶ እሸቱ ሀብተጊዮርጊስን እና እነ አቶ አስፋው ዳምጤን በጥቂቱ መጥቀስ ይቻላል። የአገሪቷ ሕዝብ ቁጥር ቶሎ ቶሎ እየጨመረ፣ የመንግሥት ኢንፍራስታራክቸርና አስተዳደር እየተስፋፋ፣ ሕዝቡ ለተሻለ ኑሮ ፍላጎቱ እያደገና እየጓጓ እያለ ገንዘብ ሚኒስቴር ይሄንን አገራዊ ጥማትና እድገት ለማርካትና ፊናንስ ለማድረግ የሚሰበስበው ታክስ በየዓመቱ በተለያዩ ምክንያቶች ይፈራረቅ ነበር።
ስለዚህ ልጅ ይልማ የገንዘብ ሚኒስቴር በመጠኑም ቢሆን አስተማማኝ የገቢ ምንጭ እንዲኖረው ለትርፍ የቆሙ የተለያዩ የመንግሥት ድርጅቶች እንዲመሠረቱ አደረጉ። ለምሳሌ ብሔራዊ ሎተሪን፣ ሶደሬን፣ ፍልውኃን፣ 82 አፓርታማ ተብሎ የሚጠራውን ሕንጻን በጥቂቱ መጥቀስ ይቻላል። ነገር ግን ልማትና ዕድገትን በሰፊው ለማቀድ እና ለማስፋፋት አገሪቷ ውስጥ የነበረው ካፒታል የተመጠነ ስለነበረ ከውጭ አገር መንግሥታትና ድርጅቶች ብድር መበደር ግድ ይል ነበር።
ይህም ሆኖ የምዕራባውያን አገሮችመንግሥታትና ድርጅቶች በዚያን ወቅት «ሶስተኛ ዓለም» ተብለው ለሚጠሩት አገሮች ለሚያበድሩት ብድር ዋስትና ይሰጉ ስለነበረ ለልማት የሚደለድሉት ገንዘብ እጅግ የተወሰነ ነበረ። በተጨማሪም ለዚሁ ውስን ብድር ፈላጊ መንግሥታት ብዙ ነበሩ። በዚህ ውድድር ልጅ ይልማ ጥረታቸው ብድሩን ለማግኘት ብቻ ሳይሆን ገንዘቡን ለመቆጣጠርና ለማስተዳደር ከዚሁ ብድር ተቀንሶ ብዙ ብር ተከፍሏቸው ተያይዘውየሚላኩትን ኤክስፐርቶች ለመቀነስ ወይም ከተቻለ ለማስወገድ ነበር። ይህንን ለማድረግ ልጅ ይልማ በውሉ መሠረት ተፈፃሚ የሚሆኑ ግዴታዎችን በሰዓቱና በስርዓቱ እንዲከፈሉ ያደርጉ ነበር።
ይህ አሠራር በኢትዮጵያ መንግሥት ችሎታ ላይ ዕምነት ስላጠናከረ ልጅ ይልማና የገንዘብ ሚኒስቴር ባልደረቦቻቸው ከዓለም ባንክና ከአፍሪካ ልማት ባንክ በብድሮቹወለድና አስተዳደር ለአገሪቷ ተመቺ የሆኑ ውሎችን መዋዋል ችለዋል። ልጅ ይልማ ገንዘብ ሚኒስቴር ዘጠኝ ዓመት ካገለገሉ በኋላ በየካቲት 1961 ዓ.ም. ወደ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተዘዋወሩ። ከሁለት ዓመት ከስድስት ወር በኋላ ወደ ዘውድ አማካሪነት ተሸጋገሩ።
አብዮቱ በየካቲት 1966 ዓ.ም.እንደፈነዳና የክቡር ልጅ እንዳልካቸው መኮንን ካቢኔ እንደ ተመሰረተ ሕገ መንግሥቱን እንዲያሻሻል አዲሱ አስተዳደር በክቡር አቶ ተክለፃድቅ መኩሪያ ሰብሳብነት አንድ ጉባኤ አቋቋመ። ልጅ ይልማም ለዚሁ ጉባዔ ተመርጠው ለሕዝብ እንደራሴዎች ሕግ የሚደነግገውን ንዑስ ኮሚቴ አየመሩ እያለ ሰኔ 22 1966 ዓ.ም. የጊዜያዊ ወታደራዊ ደርግ ወታደሮች ልጅ ይልማን ከቤታቸው ወስደው አሰርዋቸው።
አጥፍተዋል ተብለው ክስ ሳይቀርብባቸው እንደሌሎቹ የቀድሞ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የአፄ ምኒልክ ታላቁ ቤተ መንግሥት ከምድር በታች በሚገኘው ክፍል ውስጥ የፖለቲካ እስረኛ ሆነው ታሰሩ። ማቀቁ። በዚያኑ ጊዜብዙ የረጅም ግዜ የሥራ ባልደረቦቻቸውና ጓደኞቻቸው አለ አግባብና አለፍርድ ተረሽነው ታንቀው ተገደሉ።
ከአራት ዓመት ተኩል እስራት በኋላ ልጅ ይልማ በሆድ ካንሰር ወህኒ ቤት ሲሰቃዩ ቤተሰቦቻቸው ወደ ሆስፒታል ተዘዋውረው የሚያስፈልገውን ህክምና በጥድፊያ እንዲያገኙ ለተለያዩ የወታደራዊ መንግሥት ባለሥልጣናት በስጋትና በጭንቀት ብዙ ግዜ እመለከቱ። ልጅ ይልማ የሞት አፋፍ ሲደርሱየወታደራዊ መንግሥት ወደ ሆስፒታል አዘዋወራቸው። ከሰባት ቀን በኋላ ጥር 13 1971 አረፉ።
ልጅ ይልማ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከፍተኛ ዕምነት እና ድጋፍ ሳይለያቸው በዕውቀታቸው፣ በሥራ ልምዳቸው፣ በብልህነታቸው፣ በራእይአቸውና በሀገር ፍቅራቸው የኢትዮጵያን ዘመናዊ ኢንፍራስትራክቸርና እስተዳደር መሠረት ከዘረጉ፣ ከተንከባከቡና ካበለጸጉ የሃኛው ክፍለ ዘመን ታላላቅ ኢትዮጵያዊ መሪዎች አንዱ ናቸው።
የልጅ ይልማ አስተዋፆ አሻራ በፊናንስ፣ በንግድና በኢንዱስትሪ፣ በትምሕርት፣ በአየር በየብስና በውኃ መጓጓዣ፣ በቴሌኮሙኒኬሽን፣ ባገር መከላከያ ጦር ኃይል እና በውጭ ፖለቲካ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት ሰነዶች ውስጥ ለጊዜው ተረስቶ ደብዝዞ ቢቀመጥም እንደነ አምባሳደር ዘወዴ ረታና ዶ/ር ታምራት ኃይሌ የታሪክ መርማሪዎችና ጸሐፊዋች ዕይታና ትችቶቻቸውን ጽፈውና አሳትመው ለሕዝብ ሲያቀርቡ የልጅ ይልማ ልፋትና ትጋት የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ተገቢ የሆነውን ቦታ መያዙ አይቀርም።