ዶክተር ያየህይራድ ቅጣው ማናቸው?

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን፣ መዝገበ-አእምሮ (የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ) ፕሮጀክቱ ለአገር የሠሩ ሰዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል።

ይህ ታሪክ በዲጂታል ሚድያዎች፣ በመጽሐፍ፣ በድምፅ ትረካና በሌሎችም መንገዶች እየቀረበ እንደሆነ ይታወቃል። ባለፉት 4 ዓመታት ከ5 ወር ጊዜ ውስጥ የ423 ሰዎችን የሕይወትና የሥራ ታሪክ ለመሰነድ የቻልን ሲሆን 600 ገፅ ባላቸው ሁለት የተለያዩ መጽሐፎች ላይም ታሪኮቹ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው እንዲቀመጡ አድርገናል።በተለይ ታሪኮቹ በዲጂታል ሚድያዎቻችን ላይ ተደራሽ የሚደረጉ(የሚጫኑ) በመሆኑ ጎግል ላይ በቀላሉ ሲፈለጉ የሚገኙ ናቸው።

ቅፅ 3 መዝገበ አእምሮ መፅሐፍ ፣ከ20 በላይ ዘርፎች ይኖሩታል። ከእነዚህም ዘርፎች የትምህርት ዘርፍ የሚለው ይገኝበታል። በዚህ ዘርፍ ትልቅ አሻራ አኑረዋል በሚል የመዝገበ አእምሮ ቦርድ ከመረጣቸው ባለውለታዎች አንዱ ዶክተር ያየህይራድ ቅጣው ይጠቀሳሉ። ዶክተር ያየህይራድ ቅጣው በደርግ ዘመን የትምህርት ሚኒስትር በመሆን ያገለገሉ ሲሆን ለአገራቸውም ልዩ ፍቅር አላቸው።

የዶክተር ያየህይራድ ቅጣው የሕይወት ታሪክ የፊታችን ጥር 9 2018 ይመረቃል።

“ከእናት እቅፍ እስከ ልጅ ልጅ ምርኲዝ ትዝታዎቼ ” የሚል ርዕስ የተሰጠው ይህ መፅሐፍ 350 ገፆች አሉት፡፡ የመፅሐፍ ዝግጅቱን እና ምረቃውን የሚያከናውነው ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን ( እዝራ እጅጉ) ሲሆን አርትኦቱም በናይእግዚ ኅሩይ ተሠርቷል።

በዕለቱ በዶክተር ያየህይራድ ቅጣው ላይ ያተኮረ የ3 ሰዓት የድምፅ ዶክመንተሪ በይፋ የሚመረቅ ሲሆን ሳቤህ ዞንና ተወዳጅ ሚድያ በትብብር እንዳሰናዱት ለማወቅ ተችሏል።

ዶክተር ያየህይራድ ቅጣው ከጄነራል ዊንጌት ብርቱ ተማሪዎች አንዱ የነበሩ ሲሆን በፈረንሳይ አገርም የህክምና ትምህርታቸውን ለመከታተል የቻሉ ናቸው፡፡

የዕድገት በሕብረት ዘመቻ ላይ የማይዘነጋ አሻራ ያኖሩት ዶክተር ያየህይራድ ቅጣው፣ የህይወት ታሪካቸው አጠር ብሎ እንዲቀርብ አድርገናል። ቤርሳቤህ ጌቴ እንደሚከተለው ታሪኩን ሰንዳዋለች።

         ትውልድ እና የልጅነት ጊዜ

ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ ከተባሉ ምሁራን መካከል ተጠቃሽ ናቸው። ዶክተር ያየህይራድ ቅጣው። ትውልዳቸው መጋቢት 22፣ 1932 ዓ.ም በአዲስ አበባ ልዩ ስሙ “ሐኪም ቦራ” ተብሎ ይታወቅ በነበረው በአሁኑ ራስ ደስታ ሆስፒታል ቅርብ ርቀት ላይ በምትገኝ መንደር ነው። ” የተወለድኩት ቤት ውስጥ ነው — ግራዚያኒ በየካቲት 12 ሲቈስል የታከመበት የዛሬው ራስደስታ ሆስፒታል ከቤታችን 100 ሜትር እንኳን አይርቅም። ስወለድ እንደሌሎች ጨቅላዎች ባለማልቀሴና ከእኔ በፊት የተወለዱ ወንዶች ሁሉ በመሞታቸው መቼም ወንድ አይወጣላቸውም! በሚል ተስፋ በተቆረጠበት ሁኔታ ነበር ታላቅ እኅቴ (እቴቴ) – ኧረ ይነቃነቃል!! ብላ በህይወት መኖሬን ያበሰረችው።” ይላሉ እርሳቸው።

በህይወት መኖራቸው ሲታወቅ ቤቱ ደስታ በደስታ፣ እልልታ በልልታ ሆነ። እስከ ሰባት ዓመታቸውም በልዩ እንክብካቤ ስም ሳይወጣላቸው ‹ማሚቱ› ተብለው እየተጠሩ ነው ያደጉት። “ጥቍር ቀሚስ ለብሼ ከሰውም ከ‹‹እግዚአብሔር››ም ተደብቄ ነው ያደግሁት፡፡ ጠጕሬም — አልፎ አልፎ በመቀስ ከመከርከም ባለፈ ምላጭ ነክቶት አያውቅም — ተፈጥሮ ወደ 25 ዓመቴ ላይ እሰኪላጨው ድረስ!!” ሲሉም ያስረዳሉ።

ዶክተር ያየህይራድ በሰፊ ቤተሰብ ውስጥ ነው ያደጉት። ከልጆች ውጪ በቤት ውስጥ ያደጉት የዘመድ ልጆችና አገልጋዮች በጋራ በመከባበርና ፍቅር በነገሰበት ቤት ውስጥ ነበር ያደጉት። ዶክተር ያየህ ይራድ የተከበሩ አፈንጉስ ልጅ ናቸው። ሀገራቸውን በታማኝነት ያገለገሉ የተወደዱና የተከበሩ አባት ነበሯቸው። ታዲያ ዶክተር ያየህይራድ ስለ አባታቸው ብቻ ሳይሆን የእናታቸውም ተናግረው አይጠግቡም። “የቤቱ መሪ ናት” ብለው ይገልጿቸዋል።

ትንሹ ያየህይራድ የቄስ ትምህርት ቤት ደጃፍና አርጩሜ አላየም። ፊደል መቁጠር የተጀመረው እቤት ውስጥ በእቴቴ አማካኝነት ነበር። ሰባት (7) ዓመት ከሞላው በኋላም ከመንገድ ማዶ በሚገኘው የስዊድሽ ሚሽን ትምህርት ቤት ገብቶ ለሁለት አመት ተማረ። ወደ ሦስተኛ ክፍል እንደተዛወረም ትምህርት ቤት ተቀይሮለት በአርበኞች ትምህርት ቤት መማሩን ቀጠለ። የአርበኞች ትምህርት ቤት ትዝታ መቼም ብዙ ነው። ትንሽ ሜዳ ላይ በክፍል ሲሰለፉ ‘ደሙን ያፈሰሰው” እያሉ ሰንደቅ አላማ በሚሰቅሉበት ሰዓት ከሰልፉ ሥርአት ወጣ ብሎ የሚገኝ ተማሪ፣ በስሙ ተጠርቶ፣ የሥነምግባር/ኮንዳክት ነጥብ ይቀነስበት እንደነበር መች ይዘነጋና።

     የትምህርት ቤት ጉዳይ

የወቅቱን የቁጥር መረጃ ዶክተር ያየህይራድ እንደሚጠቅሱት (1948 አም)፤ በኢትዮጵያ በሙሉ የመንግስት ትምህርት ቤቶች አራትመቶ ሰላሳ አንድ(431) አንደኛ ደረጃ፤ አስራአንድ (11) ሁለተኛ ደረጃ (አብዛኛዎቹ አዲስ አበባ ውስጥ)፤ አንድ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅና አንድ ኢንጂነሪግ ኮሌጅ ብቻ ነበሩ፡፡ ጠቅላላው የአንደኛ ደረጃ (1-8) ተማሪ 93,623 ሲሆን፤ የ8ኛ ክፍል 1,896 ብቻ ነበር፡፡ የሁለተኛ ደረጃ (9-12) ተማሪ፡ አካደሚ18 1,831፤ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ 1,379፤ ድምር ከ3,500 በታች ነበር፡፡ እኛ በ1949አም ወደ ሁለተኛ ደረጃ ስንገባ ከጠቅላላው ወደ 4,300 ተማሪ ወደ 2,300 (53%) በአስራ አንድ (11) አካደሚ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ነበሩ፡፡ ከዚህ ውሰጥ የ9ኛ ክፍል ተማሪ ከ1,020 አይበልጥም፡፡

     ትምህርት ወዳዱ ያየህይራድ

ዶክተር ያየህይራድ ቅጣው የትምህርት ልህቀት ከልጅነታቸው የጀመረ ነው። “ሳያጠና ጥሩ ውጤት ያመጣል” የሚል ተቀጥላ እስኪሰጥ ድረስ ፈጣን እድገት ነበራቸው። በአመት ሁለት ክፍል ለመማር በመቻላቸው ከእድሜያቸውም ፈጥነው በ1948 የ8ኛ ክፍል የመጀመርያ ደረጃ መልቀቅያ ፈተና ለመውሰድ ቻሉ። ወደ ሁለተኛ ደረጃ ሲያልፉም እንደ ዝንባሌያቸውና ውጤታቸው ምርጫ አደረጉ። በ1949 ወደ ሁለተኛ ደረጃ ሲገቡ በጠቅላላ ካለው 4,300 የተማሪ ቁጥር የ9ኛ ክፍል ተማሪው ከ1,020 አይበልጥም ነበር።

በዊንጌት በዘጠነኛ D ክፍል ተማሪ የነበሩት ዶክተር ያየህ ይራድ ፤ ክፍሉ በጥባጭ የበዛም ቢሆን፤አብዛኛው ተማሪ በሚገባ መከታተል የሚችል ነበር፡፡ በትምህርት ሥርአቱም ከአማርኛና ከግብረገብ በቀር ትምህርቱ ሁሉ በእንግሊዘኛ ነበር፡፡ የዊንጌት አንዱ ዋና ጉዳይ ሥነስርአት ማክበር ነበር፡፡ ሁሉንም ነገር በደውል ይግባቡበታል። ደውል ሲደወል ከእንቅልፍ መነሳቱ፣የትምህርትና የምግብ ሰዓቱ እስከ መኝታው ድረስ የታወቀ ነው። ‘ደሙን ያፈሰሰ’ የሚለውን ዘምረው ሰንደቅ ዓላማ ይሰቅሉና የዳይሬክተሩን መልዕክት ሰምተው ክፍል ከሚገቡበት ጀምሮ ምሽት አልጋ ላይ እስከሚወጡበት ሰዓት ድረስ ያለው ተግባር ዝንፍ የማይል የየእለት ተግባር ነበር።

  ነፃ የትምህርት ዕድል-ፓሪስ

ኮሌጅ፣ ሁለተኛ አመት መጨረሻ ላይ፣ አንድ ቀን፣ ወደ ባህር ሃይል ቢሮ ተጠርተው “በስምምነታችን መሠረት፣ ለህክምና ትምህርት፣ እስኮላርሽፕ ተገኝቶልሃልና ለመሄድ ተዘጋጅ” ተባሉ። እርሳቸውም ያለ አንዳች ማመንታት ተቀብለው ጉዳዩን ለሳይንስ ፋከልቲ ዲን፤ ሚስተር ማክፋርሌን፤ ነገሯቸው። እነርሱ ፊዚክስ እንዲያጠኑ ካናዳ ወይም አሜሪካ ሊልኳቸው ቢፈልጉም ዶክተር ያየህይራድ ግን በውሳኔያቸው ፀንተው ፈረንሳይን መረጡ።ቤተሰብና ጎረቤት ሁሉ ተደሰተ። ለትምህርት ወደ ውጭ በመሄድ የመጀመርያ ከሚባሉት መካከል በመሆናቸውም የሰፈሩ ወሬ እርሳቸው ብቻ ሆኑ። “

ዶክተር ያየህ ይራድ ወደ ፓሪስ ካቀኑ በኋላ የህክምና ትምህርትን ወደሚከታተሉበት ቦታ ሲሄዱ የገጠማቸውን እንዲህ ያስታውሱናል። “… በባቡር፣ ወደ ቦርዶ አቀናሁ፡፡ ከባቡር ጣቢያ ታክሲ ይዤ፣ ሳልጠይቀው፣ ከተማውን አዙሮ ካሳየኝ በኃላ “እንዴት እሩቅ ነው” እያልኩ፤ ትምህርት ቤቱ አደረሰኝ፡፡ በኃላ ሳውቅ፣ ጣቢያው ከትምህርት ቤቱ ከ400ሜትር በላይም አይርቅ፡፡ የህክምና ትምህርት (ቦርዶ) ወደ ትምህርት ቤቱ ስገባ፣ ዪኒፎርም የለበሰ ዘብ፣ በላቀ አክብሮት ተቀብሎ፣ ወደ ኃላፊው ቢሮ ወሰደኝ፡፡” ብለው ጊዜውን የአሁን ያህል ያስታውሱታል።

            ጉብዝና በፓሪስ

በፓሪስ የህክምና ትምህርታቸውን ሲከታተሉ በተለይም መጀመሪያ ዓመት ላይ ከቋንቋ አለመቻል ጋር ተያይዞ በብዙዎች ተስፋ ቢቆረጥባቸውም ለራሳቸው እረፍት ሳይሰጡ ቀን ከሌት አጥንተው በሚያስገርም ውጤት ሁሉን አስደምመዋል። እረፍት ማጣታቸው ለህመም ዳርጓቸው እንደነበረም አይዘነጋም። የሆነው ሆኖ ከዓመት በኋላ ሀገሩም ቋንቋውም ተለምዶ በጥሩ ውጤት ትምህርታቸውን ከዳር ለማድረስ ተችሏቸዋል። በነገራችን ላይ ፓሪስ ከህክምና እውቀት ጋር ብቻ ሳይሆን ከጎናቸው አጥንት ጋርም አገናኝታቸዋለች። በአንድ መንደር ተወልደው አድገው መገናኛቸው ሌላኛው አለም ላይ ሆነ። ወይዘሮ ሀና ዶክተር ያየህይራድን በሰፈራቸው በዝና ከማወቅ በዘለለ የጠለቀ ዕውቅና አልነበራቸውም። ነገር ግን ለትምህርት በሄዱበት ስፍራ ላይ ሊገናኙ የግድ ሆነ። ወይዘሮ ሀና ጉተማ በትምህርታቸው የላቀ ደረጃ ላይ መድረስ የቻሉ፤ ጥንካሬና ትጋትን ከወላጆቻቸው ወርሰው ያደጉ ብርቱ እመቤት ናቸው። የማይዘነጉ መልካም የፍቅር ጊዜያትንና ደማቅ የጋብቻ ስነስርአትን በማካሄድ ወደ ትዳር የገቡት ጥንዶቹ ዛሬም ድረስ በስስት የሚተያዩ መከባበርና መደማመጥ የነገሰበት ቤተሰብን እንደመሰረቱ የተመለከተ ሁሉ ሊመሰክረው የሚችል ነው።

   ከፈረንሣይ መልስ

በ1971 ዓ.ም ከፈረንሳይ ከተመለሱ በኋላ የዩኒቨርስቲ አስተማሪ ሆነው በሳምንት ሁለት ቀን ከ10 እስከ 12 ሰዓት በባህር ሀይል ክሊኒክ የህክምና አገልግሎት ይሰጡ ነበር። አብዛኛው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ወታደር እና የወታደር ቤተሰቦች መሰረት ለነበሩ ሥራው ውስብስብ የጤና ችግር እምብዛም ያልነበረበት ነው። ከበድ ያለ የጤና ችግር ያለበት ከተገኘ ደግሞ ወደ ጦርኃይሎች ሆስፒታል ሪፈር ይፅፋሉ። በዚህ አገልግሎት ላይ በነበሩበት በሻለቃ አጥናፉ አባተ በተፃፈ ደብዳቤ የዕድገት በህብረት ዘመቻን ከሻለቃ ኪሮስ ዓለማየሁ ጋር በመሆን እንዲመሩት ተደረገ። በዚህም ውጤታማ ሥራን ሠርተው ተገኙ። ዶክተር ያየህይራድ ቅጣው የተሰጧቸውን ኃላፊነቶች በልዩ ትጋትና ጥራት የሚሠሩ በመሆኑ ውጤት ሳያስመዘግቡ የቀሩበት ጊዜ አልነበረም። ለምሳሌ በሀገሪቱ ከነበረው የጦርነት ዘመቻ ጋር ግብግብ የገጠመው የትምህርት ሥርዓት በተቻለ መጠን ውድቀትን እንዳያስመዘግብ ያደርጉት የነበረው ጥረት ሊደነቅ የሚገባው ነው።

ዶክተር ያየህይራድ ቅጣው፣ በፈረንሳይ የነበራቸው የትምህርት ቆይታ እንደተጠናቀቀ ወደ ሀገራቸው በመመለስ ወደላካቸው ነበር ያመሩት። በትምህርት ላይ በነበሩበት ጊዜ ከሀገራቸው ጋር የነበራቸውን ግንኙነት አላቋረጡም ነበርና በእውቀት ደርጅተው ለመጡት ዜጋ የሥራ በር ፈጥኖ ነበር የተከፈተላቸው። በመንግስታዊ ኃላፊነት ላይ ከገቡ ጊዜ አንስቶም በተለያየ ተልዕኮ ላይ ተሰልፈው ውጤታማ ሥራ ለመሥራታቸው አስተዋፅኦዋቸው በራሱ ምስክር ሆኖ ሊቀርብ ይችላል።

ዛሬ በብዙ ተደጋጋሚነት ለመሰልቸትና ለመፈራት የበቃው ‘ ብሔር’
የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ በተቋም ደረጃ በመምራት ዶክተር ያየህይራድ የሚቀድሙ ይመስላል። የዛሬው የጤና ጥበቃ ትምህርት ቤትም ዶክተር ያየህይራድ ጥርሳቸውን የነቀሉበት ነው።

      ተመራማሪው ዶክተር ያየህይራድ ቅጣው

ዶክተር ያየህ ይራድ ቅጣው በኃላፊነቶቻቸው ውጤት ከማስመዝገባቸው ጎን ለጎን በጥናትና ምርምር ሥራቸውም የተመሰከረላቸው ምሁር ናቸው። በተለያዩ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ላይ እየተጋበዙ ሙያዊ አስተዋፅኦዋቸውን ሲያበረክቱ የቆዩ ሲሆን ለቀጣይ 50 አመት ሀገሪቷ በጤና ረገድ የሚገጥማት ውጣውረድና የመፍትሔ ሀሳብ ላይ ሲያደርጉት የነበረው ረዥም ጊዜን የፈጀው ጥናትም በቅርቡ ነው ወደ መጠቃለሉ የደረሰው።

የሙያ ማህበራት እና አለምአቀፍ ተቋማት

ከሙያ ማኅበራት አባልነት አንፃር ከፈረንሳይ ከተመለሱበት ከ1971 ጀምሮ የኢትዮጵያ ህክምና ማኅበር አባልና ለተወሰኑ ዓመታትም የቦርድ አባል በመሆን የሠሩ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ሰፊ ስራ ሲሰሩ ቆይተዋል። ለምሳሌ ሐኪሞችን ገጠር በማቆየት ፣ ምርምርን በማትጊያ(ኢንሴንቲቭ) ለማበረታታት እንዲቻል ያደረጉት አስተዋፅኦ ሊጠቀስ የሚችል ነው።

ዓለምአቀፍ ግንኙነትን በማጠናከር ረገድ፣ በዩኔስኮ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት ከመደበኛ ተልዕኳቸው ባሻገር የኢትዮጵያን ዋና ዋና ቅርሶች በአለም ቅርስነት በማስመዝገብ የራሳቸውን አስተዋፅኦ ያበረከቱት ዶክተር ያየህይራድ ከ1993 ጀምሮ ደግሞ በጤና ዕድገት ዙሪያ የማማከር ሥራን ሲሠሩ ቆይተዋል። በአማካሪነት UNFPA, WHO, UNDP, UNAIDS የመሰሉ ትላልቅ ዓለምአቀፍ ተቋማት ላይ እና በአገር ውስጥ ደግሞ እንደ AHRI, CRDA, EGLDAM, EMA, EPHA, ESOG ላይ ሰፊ አስተዋፅኦ አበርክተዋል። በ‹ተባበሩት መንግሥታት ኤድስ ፕሮግራም› (UNAIDS) አማካኝነት፣ የኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኤችአይቪ/ኤድስ ስትራቴጂክ ዕቅድ (2000) ዝግጅት መሪ አማካሪ ነበሩ። በጤናው ረገድ የተሻለ እንቅስቃሴ የተደረገበት የጤና ኤክስቴንሽን አገልግሎትም ላይ ድርሻ ነበራቸው።

         የመሠረተ ትምህርት አባት

በህይወት ውስጥ ውጣ ውረድ መኖር የግድ ነውና በዶክተር ያየህይራድ የሥራ ዘመንም ቢሆን ቀላል የማይባሉ ተግዳሮቶች ተጋርጠው እንደነበረ የሚካድ አይደለም። ልዩነቱ ግን ዶክተር ያየህይራድ የሚመጣባቸውን ውጣ ውረድ እንደአመጣጡ የመቀበል ልዩ ፀጋን የተቸሩ መሆናቸው ላይ ነው።

የትምህርት ሚኒስትር በመሆን አገራቸውን ያገለገሉት ዶክተር ያየህይራድ የመሠረተ ትምህርት እንዲስፈፈም ትልቁን አሻራ ለማኖር የቻሉ ናቸው።

     ዛሬም ዶክተሩ ይመራመራሉ

ዶክተር ያየህይራድ ዛሬም ለጡረታ እጃቸውን አልሰጡም። ይልቁን በቤታቸው በሚያሳልፉበት ጊዜ ከላፕቶፓቸው ሳይላቀቁ በመፃፍና በማንበብ ትልቅ አስተዋፅኦ ያላቸውን የፅሁፍ ሥራዎች በማበርከት ሥራ ተጠምደው ይገኛሉ።

ዶክተር ያየህ ይራድ ከመደበኛ ስራቸው ጎን ለጎን በበጎ ፍቃድ በሙያቸው በበርካታ ፕሮጀክቶችና የጥናት ስራዎች ላይ በመሳተፍ ሀገራቸውን በቀናነት ያገለገሉ ታላቅ የሀገር ባለውለታ ናቸው። ሀገሪቷ በጤናው ዘርፍ በቀጣይ 50 አመታት የምትደርስበት ደረጃ ምን እንደሚሆን ያደረጉት ጥልቅ ጥናትና ትንታኔ ዘመን ተሻጋሪ ለትውልድ የተቸረ አበርክቷቸው ነው።

      ስፖርት፣ ሙዚቃ

ዶክተር ያየህይራድ ለስፖርትና ለሙዚቃ ያላቸው ፍቅር ደግሞ የሚያስደንቅ ነው። ዛሬም ድረስ ቤት ውስጥ የትዳር አጋራቸውን እያቀነቀኑ ማዝናናት ያስደስታቸዋል። ጥላሁን ገሰሰ፣መሀሙድ አህመድ ይበልጡን የሚመርጧቸው ሙዚቀኞች ናቸው። ለሴት ልጃቸውም ሰርግ መድረክ ላይ በማቀንቀን ቤተሰቡን በደስታ ያስለቀሱ ለጥበብ ቅርብ የሆኑ ሰው ናቸው። እስፖርቱም ላይ ንቁ ተሳታፊ ነበሩ። በተማሪነት ዘመናቸው ለቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ለሁለት አመት ተጫውተዋል። የስፖርት ህክምና በሀገራችን ሳይታወቅ ገና ስልጠናውን በመውሰድና በሀገራችን እንዲጀመር የሰሩ ሰው ናቸው።የካፍ ህክምና ኮሚቴ አባልም ነበሩ።

  ስለዶክተር ያየህይራድ ቅጣው የቅርቦች ምንአሉ?

ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ፣ ዶክተር ያየህ ይራድን የሚያውቋቸው በሳይንስ ፋኩልቲ እርሳቸው የሁለተኛ አመት ተማሪ ዶክተር ያየህይራድ ደግሞ የመጀመሪያ አመት ተማሪ ሆነው የተማሪነት የእግርኳስ ጨዋታ ላይ የ9 ቁጥር ማሊያ ልብሳቸውን መቼም አይዘነጉትም። የተፈጥሮ ሳይንስ ተመራማሪና የስነ-ህይወት ወይም ባዮሎጂ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ ከተማሪነት ዘመናቸው ጀምሮ የሚያውቋቸውን ዶክተር ያየህይራድን ሲገልጿቸው። ” ቅን፣ እራሱ ያፈለቀውን አስደናቂ ሀሳብ ከሌሎች ጋር በጋራ የመጣ ሀሳብ በማስመሰል ለራሱ መውሰድ የሚገባውን አድናቆች ለሌሎች የሚያካፍል፣ በእውቀቱ የሚታወቅ ሰው ነው” ብለው ይገልጿቸዋል። “በትምህርቱ ጎበዝ ነው የእድገት በህብረት ዘመቻ ላይ የሰራውን ሥራ አደንቃለሁ። የትምህርት ሚንስቴር ሆኖ ዩኒቨርስቲው ያለበትን የአሰራር ችግር በቅርበት ስለሚያውቀው ችግሮችን ለመቅረፍ እናደርግ የነበረው ጥረት እንዲሳካ ያየህይራድ ቦታው ላይ መሆኑ ጠቅሞናል።” ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርትና ምክትል ፕሬዘዳንትም የሆኑት ፕሮፌሰር ምትኬ ሞላ በበኩላቸው ዶክተር ያየህይራድን ስልጣን ላይ ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ በሩቁም ቢሆን ቢያውቋቸውም በስራው አለም በቅርበት ያወቋቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በጤና ጥበቃ ይመራና የ20 አመት ውል በነበረው ‘የኢትዮጵያ የጤና ልማት ፕሮግራም’ ላይ ሲሆን በጊዜው የውጪ አማካሪዎች ቢኖሩበትም ዶክተር ያየህይራድም በዚህ ስራ ውስጥ እንደነበሩ ያስታውሳሉ። ይበልጡን ያወቋቸው ደግሞ የኩፍኝ ክትባትን በተመለከተ አብረው ሢሠሩ ነው። ” ደከመኝ ሰለቸኝ አይልም ለእኔ ሮል ሞዴሌ ነው ስራ እንዴት እንደሚሰራ የተማርኩበት ሰው ነው። ስራ ሰጥቶኝ የሚሰጠኝ አስተያየት የሚያበረታታ ነው። ጥሩ ነው ብሎ አድንቆኝ የሰጠሁትን ፅሁፍ መልሶ ሲሰጠኝ ግን ከሰጠሁት ፈፅሞ የተለየና ከፍ ያለ ሆኖ አገኘዋለሁ። እውቀቱን ለማጋራት የማይሰስት፤ ለትውልድ አሳቢ ሰው ነው። ዶክተር ያየህይራድ ለእኔ ሮል ሞዴል ነው። ” ብለዋል።

        ቤተሰብ 

ዶክተር ያየህይራድ ቅጣው ከባለቤታቸው ወይዘሮ ሐና ጉተማ፣4 ልጆችን የወለዱ ሲሆን እነርሱም አቶ ቅጣው ፣ ዶክተር ማሪት፣ አቶ ብሩህ እና አቶ ቢንያም ናቸው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *