ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን፣ መዝገበ-አእምሮ (የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ) ፕሮጀክቱ ለአገር የሠሩ ሰዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል።
ይህ ታሪክ በዲጂታል ሚድያዎች፣ በመጽሐፍ፣ በድምፅ ትረካና በሌሎችም መንገዶች እየቀረበ እንደሆነ ይታወቃል። ባለፉት 4 ዓመታት ከ5 ወር ጊዜ ውስጥ የ423 ሰዎችን የሕይወትና የሥራ ታሪክ ለመሰነድ የቻልን ሲሆን 600 ገፅ ባላቸው ሁለት የተለያዩ መጽሐፎች ላይም ታሪኮቹ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው እንዲቀመጡ አድርገናል።
በቀጣይነት ፣መዝገበ አእምሮ ቅፅ 3 በልዩ ልዩ ዘርፍ ታትሞ ለንባብ የሚበቃ ሲሆን ከእነዚህ ልዩ ልዩ ዘርፎችም በጎ አድራጎት አንዱ ነው። በዚህ ዘርፍ ታሪካቸውን ከምንሰንድላቸው መካከል ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ አንዷ ናቸው። ሲስተር ዘቢደር ባለፉት 23 ዓመታት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት የተለያዩ የበጎ አድራጎት ተግባራትን ያከናወኑ ሲሆን ዕዝራ እጅጉም ታሪካቸውን እንደሚከተለው ሰንዶታል።
ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ፣ ጥር 16 ቀን 1955 ዓ.ም ከእናታቸው ወ/ሮ ናሲሴ ቦሽራ እና ከአባታቸው አቶ ዘውዴ ይታየው በአሁኑ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፤ በጋሞዞን ጨንቻ ከተማ የተወለዱ ሲሆን ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናትም ናቸው፡፡ ሲስተር ዘቢደር የ1ኛ እና የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጨንቻ እና አርባ ምንጭ ከተማ ከዚያ በኋላም በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ነርሲንግ ት/ቤት ተመርቀዋል፡፡
በሙያቸው ወገናቸውንና ሀገራቸውን ከማገልገል ጎን ለጎን ራሳቸውን በትምህርት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ከነበራቸው ፅኑ ፍላጎት በመነሳት ከአሜሪካን ሀገር ፕሪስተን ዩኒቨርሲቲ አድቫንስድ ዲፕሎማ፤ የባችለር ዲግሪ እና የማስተርስ ዲግሪ በቢዝነስ አድሚኒሰትሬሽን ተቀብለዋል፡፡ ላለፉት በርካታ ዓመታት የተለያዩ ድርጅቶች ባዘጋጁት በውጭ ሀገር እና በሀገር ውስጥ በርካታ አጫጭር ስልጠናዎች ላይም ተሳትፈዋል፡፡ ሲስተር ዘቢደር በነርስነት ሙያቸው በአርባ ምንጭ ሆስፒታል፤ በቅ/ጳውሎስ ሪፈራል ሆስፒታል ያገለገሉ ሲሆን በኖርዌይ የህፃናት አድን ድርጅት ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ለረጅም ዓመታት ሠርተዋል፡፡
ሜሪ ጆይ እንዴት ተጠነሰሰ?
ነገሩ እንዲህነው፡፡ ቀደም ብሎ ሲስተር ዘቢደር ሲሠሩበት ከነበረው የኖርዌይ ህፃናት አድን ድርጅት ከለቀቁ በኋላ የግል ክሊኒክ በማቋቋም ለተወሰነ ጊዜ የሠሩ ቢሆንም ለረጅም ዓመታት በልባቸው ሲመኙት የነበረውን የበጎ አድራጎት ሥራን የሚያከናውኑበት ድርጅት መመሥረት እንዳለባቸው የሚገፋቸው ውስጣዊ ፍላጎት እንዳላቸው በወቅቱ ይቀርቧቸው ለነበሩ ሰዎች ያማክራሉ፤ የእነዚህ ሰዎች ምላሽ በጣም ጥሩ ሃሳብ ነው በርቺ፤ ከጎንሽ ነን የሚል አልነበረም፤ ይልቁንም ይህ ከባድ ነገር ነው፤ በአንቺ አቅም በፍፁም አይታሰብም፤ቢቀርብሽ ይሻላል የሚል ነበር፡፡ ነገር ግን ሲስተር ዘቢደር ቁርጠኛ እና ልበ ሙሉ ሴት ነበሩና በግል ክሊኒካቸው የበጎ አድራጎት ሥራ ጀመሩ፡፡
ይህ የሆነው ከ32 ዓመታት በፊት በ1986 ዓ.ም በአዲስ አበባ “አስኮ “በሚባለው አካባቢ ነበር፡፡ በወቅቱ ምንም ዓይነት የመንግስትም ሆነ የግል የጤና አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም በአካባቢው ስላልነበር ማህበረሰቡ በተለይም ሴቶች እና ህፃናት ሲያጋጥማቸው የነበረውን ከፍተኛ ችግር በመገንዘብ ቅን ልቦና ያላቸው ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ የነበራቸውን የግል አነስተኛ ክሊኒክ ለበጎ አድራጎት ሥራ በማዋል ለአካባቢው ማህበረሰብ ነፃ የጤና አገልግሎት በመስጠት እና ለ100 ለችግር የተጋለጡ ህፃናት እና ሴቶች ድጋፍ በማድረግ ሜሪ ጆይ የበጎ አድራጎት ድርጅትን እውን አደረጉ፡፡
የድርጅቱ ስም ሜሪ ጆይ የተባለበት የራሱ ምክንያት ነበረው፡
ሲስተር ዘቢደር አፍንጫቸው ላይ በበቀለ እጢ ህመም ይሰቃዩ ነበር፤ ከህመማቸው ለመዳን በህክምና ብዙ ጥረት አድርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ በሃኪሞች በስተመጨረሻ ህመሙ ወደ ካንሰር እንደተቀየረባቸው እና ውጭ ሀገር ሄደሽ መታከም አለብሽ ተብሎ ይነገራቸዋል፡፡ ሲስተር ዘቢደር በተነገራቸው ነገር ሳይደነግጡና ተስፋ ሳይቆርጡ ሁሉን ነገር ለፈጣሪያቸው በመስጠት የኪዳነ ምህረትን ፀበል መከታተል ይጀምራሉ፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላም እጢው ጠፍቶ ሙሉ በሙሉ በመፈወሳቸው የበጎ አድራጎት ድርጅቱን ስም ሜሪ ጆይ ብለውታል፡፡
የድርጅቱ እድገት እና አገልግሎት መስፋፋት
በአንድ ወረዳ እና በውስን ተጠቃሚዎች የተጀመረው የሜሪ ጆይ የልማት ሥራ የህብረተሰቡ ፍላጎትና ጥያቄ በዓይነትና በመጠን እያደገ በመምጣቱ ከውጭ ለጋሽ ድርጅቶች እና ከሀገር ውስጥ ሃብት በማሰባሰብ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተደራሽነቱን በማስፋት በአሁኑ ሰዓት በአምስት ክልሎች እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ 73 ወረዳዎች እና 342 ቀበሌዎች በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የህብረተሰብ አባላትን ተጠቃሚ ማድረግ የቻለ፤ የተቀናጀ አገልግሎት የሚሰጥ፤የበርካቶችን ህይወት የቀየረ፤ የመኖር ተስፋቸውን ያለመለመ፤ በብዙዎች የሚወደድና የሚደገፍ፤ብዙ መሠረተ ልማቶችን እና ተቋማትን ለህዝብ አገልግሎት ያበቃ ጠንካራውን ሜሪ ጆይ ከአጋሮቻቸው እና ሠራተኞቻቸው ጋር በመሆን አሁን ያለበት ደረጃ ላይ አድርሰውታል፡፡
በመስራች ሲስተር ዘቢደር ሥራ አስኪያጅነት የሚመራው የሜሪ ጆይ የተቀናጀ የልማት ፕሮግራም ከውጭ ለጋሽ ድርጅቶች እና ከሀገር ውስጥ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት አና ከኢትዮጵያዊያን ዜጎች የበጀት እና የዓይነት ድጋፍ በማሰባሰብ እና የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ላይ በማዋል በትምህርት፤ በጤና፤ በኢኮኖሚ አቅም ግንባታ፤ በማህበራዊ ደህንነት ጥበቃ፤ የህፃናት፤ ወጣቶች እና አረጋዊያን አገልግሎት መስጫ ማእከላትን፤ የህክምና ማእከላትን የበርካታ ወገኖችን ህይወት እንዲቀየር በማድረግ ረገድ፤ ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል፡፡
በሲስተር ዘቢደር፤ ደጋፊዎቻቸው እና አጋሮቻቸው ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ለወገናችን ችግር መፍትሄው ከእኛው እንዳለ በማመን የኢትዮጵያዊያን ለኢትዮጵያዊያን ፕሮግራም ከ23 ዓመታት በፊት በመጀመር እና የሀገር ውስጥ ሃብትን ተቋማዊ በሆነና በተደራጀ መንገድ በማሰባሰብና ስራ ላይ በማዋል ፋና ወጊ ድርጅትን ፈጥረዋል፡፡
ሲስተር ዘቢደር የህፃናት፤ ሴቶች፤ አካል ጉዳተኞች እና ሌሎች ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች መብቶች እንዲከበሩ፤ ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ እና ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ በተለያዩ ትልልቅ መድረኮች ድምፅ ሆነዋቸዋል፤ በፖሊሲዎች ላይ ሞግተዋል፤በበርካታ ብዙሃን መገናኛ ሰፊውን የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎችን ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡
ያላቸውን ሁሉ ለመስጠት እና የሚችሉትን ለማድረግ ወደ ኋላ የማይሉት ሲስተር ዘቢደር ለተለያዩ ድርጅቶችና ተቋማት የበጎ ፈቃድ አምባሳደር በመሆን አገልግለዋል፤ በማገልገልም ላይ ናቸው፡፡ ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያክል፡፡
· በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የህይወት ዘመን የበጎ ፈቃድ አምባሳደር
· የቀይ መስቀል የህይወት ዘመን አምባሳደር
· በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የህይወት ዘመን የላቀ የነርሲንግ አገልግሎት አምባሳደር
· በብሪቲሽ ካውንስል የአየር ንብረት ለውጥ የህይወት ዘመን አምባሳደር
· ፕላን ፓረንትሁድ ፌደሬሽን ኦፍ አሜሪካ በስነተዋልዶ ጤና የምስራቅ አፍሪካ አምባሳደር
· የኮርድኤይድ በሴቶች የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር የበጎ ፈቃድ አምባሳደር
· የእናት ባንክ የህይወት ዘመን አምባሳደር፤ በስማቸው የባንኩ ላፍቶ ቅርንጫፍ የተሰየመላቸው
· በሆላንድ ድርጅት የሴቶች ካውንስል የህይወት ዘመን አምባሳደር
· የሺ ጋብቻ የህይወት ዘመን አምባሳደር
· የየም ዞን አስተዳደር የህይወት ዘመን አምባሳደር
በተጨማሪም በተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የቦርድ አባል በመሆን እና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጥተዋል፤ አሁንም በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ሲስተር ዘቢደር በቀይ መስቀል ለ37 ጊዜ ደም በመለገስ የበርካቶችን ህይወት በመታደግ ለሌሎች አርአያ በመሆን የላቀ የሰብዓዊነት ተግባር ፈፅመዋል፡፡ ከእንደዚህ ዓይነት የሞራል ልእልናን የሚያሳይ የሰብዓዊነት ስራ ለአፍታም ቢሆን መራቅ የማይፈልጉት ሲስተር ዘቢደር ለሌሎች ወገኖች ብርሃን ለመስጠት የአይን ባንክ ልገሳ አድርገዋል፡፡
የኢትዮጵያ ልብ ህሙማን ህፃናት ድጋፍ፤የጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል የቦርድ አባል በመሆን ያገለገሉ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማህበር እና የአዲስ አበባ ፅዱና አረንጓዴ ኢኒሼቲቭ አባልና ደጋፊ ነበሩ፡፡ እንዲሁም ለተለያዮ መሰል ሀገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅቶች አባል በመሆንና ድጋፍ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡
ሲስተር ዘቢደር ሰዎች ችግር በሚገጥማቸው ጊዜ በማማከር፤ መፍትሄ በማመቻቸት ለችግር ደራሽነታቸውን፤ አዛኝነታቸውን በተደጋጋሚ ያሳዩ መልካም ሰው ናቸው፡፡ ከዚህም በላይ ሰራተኞችን እንደ ጓደኛ በማቅረብ፤ ነፃነትን በመስጠት፤ አቅማቸውን አውጥተው እንዲጠቀሙ በጣም ያበረታታሉ፤ በማህበራዊ ህይወታቸውም ጨዋታ አዋቂ ናቸው፡፡
ሲስተር ዘቢደርና ድርጅታቸው ሜሪ ጆይ ላስመዘገቡት ውጤትና ላበረከቱት አስተዋፅኦ በተለያዩ ሚኒስቴር መ/ቤቶች፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ክልላዊ መንግስታት፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ ብሄራዊ የኤድስ ምክርቤት፤ የዲያስፖራው ማህበረሰብ፤ ሀገራዊ እና አለም አቀፍ ተቋማት፤ በዓለም ባንክ፤ በለጋሽ ድርጅቶች፤ በኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጤና ማህበር፤ የካናዳ ዓለም አቀፍ የኤድስ ጉባኤ የቀይ ሪቫን እውቅና እና ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ በተጨማሪም በአፍሪካ ህብረት የሞዴል ሴት መሪዎች እውቅና እና ሽልማት ተቀብለዋል፡፡