መስፍን አሸብር

መስፍን አሸብር

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 200 የሚድያ ፤ የስነ-ጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል ገጣሚና ጋዜጠኛ መስፍን አሸብር ይጠቀሳል፡፡ መስፍን አሸብር ‹‹ጠብታ ፍቅር›› በተሰኘ የግጥም መድበሉ የሚታወቅ ሲሆን በበሳል ሂሳዊ ምልከታውም ይታወቃል፡፡

የአሁኑ ፋና ብሮድካስቲንግ የቀድሞ ሬድዮ ፋና ሲጀመር ከመስራች ጋዜጠኞቹ አንዱ የነበረው መስፍን በጥበባት አለም መሰናዶው ይታወቃል፡፡ በ31 አመቱ በ1990 ህይወቱ ያለፈው መስፍን በቅርብ ጓደኞቹ የሚወደድ እና በሙያው ላይም ትልቅ አሻራ ያኖረ ነበር፡፡ ቅድስት ወልዴ የህይወት ታሪኩን እንደሚከተለው አሰናድታዋለች፡፡ ይህን የህይወት ታሪክ በዚህ መልኩ ስናጠናክር ዶክተር ተሻገር ሽፈራው እና የመስፍን እህት መንበረ አሸብር ላደረጉልን ትብብር ማመስገን እንወዳለን፡፡ መስፍን አሸብር ጋዜጠኛ እና ገጣሚ ሲሆን በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በፋና ራዲዮ ድምፃቸው በአየር ከናኘ ቀደምት ጋዜጠኞች አንዱ ነው፡፡በጓደኞቹ ዘንድ ‹‹አባ ስሜቶ›› በመባል የሚታወቀው መስፍን ‹‹ጠብታ ፍቅር›› የተሠኘ የግጥም መድብል ህይወቱ ካለፈ በኋላ በጓደኛው ስንዱ አበበ አሳታሚነት በ1999 ዓ.ም ለአንባቢያን አድርሷል፡፡

ውልደት

ጋዜጠኛ እና ገጣሚ መስፍን አሸብር በ1958 መርካቶ ጨው በረንዳ አካባቢ ነው የተወለደው፡፡ሶስት እህቶች እና ሁለት ወንድሞች ያሉት ሲሆን ለቤቱ የመጀመሪያ ልጅ ነው፡፡

ትምህርትና የስነፅሁፍ ጅማሮ

ለስነ- ፅሁፍ ልዩ ፍቅር በማሳደሩ በሰፈራቸው አቅራቢያ በሚገኘው አፍሪካ አንድነት ትምህርት ቤት ግጥሞችን፣ስነ ጽሁፎችን ያቀርብ ነበር፡፡ ጓደኞቹ እንደሚናገሩት ይህ ትምህርት ቤት የመስፍን የስነጽሁፍ ህይወት መነሻ ነው፡፡ በትምህርቱም ጎበዝ በመሆኑ በተማሪዎች እና በመምህራኑም ዘንድ የታወቀ ነበር፡፡ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱ በኃላ የልጅነት ጓደኛው ተሻገር ሽፈራው እንደሚገልጸው ጭምቱ መስፍን የመጣበት ትልቁ ትኩረቱ ማንበብ እና ማንበብ የሆነበት ጊዜ ነበር፡፡ ወ-መዘክር በመሄድ አንድ ልብ ወለድ መፅሀፍ ሲያነብ ውሎ አመሻሹን ጓደኞቹን ሰብስቦ ይተርክላቸውም ነበር፡፡ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሲማር በተለይም የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ አያለ የሚያስታውሰው የአማርኛ መምህሩ ይሰጠው የነበረው አስተያየት ለመስፍን የግጥም መፃፍ ፍላጎት እና ብርታት ሆኖታል፡፡

ብላቴ ዘመቻ እና መስፍን

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እየተማረ ባለበት ወቅት የመመረቂያው ዓመት በነበረበት በ1983 ዓ.ም የብላቴ ዘመቻ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ወታደራዊ ስልጠና ሲወስዱ አብሮ ዘምቷል፡፡የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች በሙሉ በገቡበት ብላቴ መስፍን ታዋቂ መሆን ችሎ ነበር፡፡አርቲስት አለማየሁ ታደሰ የሁለተኛ ዓመት ታማሪ ሳለ አብረው ወደ ብላቴ ተጉዘው ነበር፤በተለይ በዚያ ወቅት አጋጥሞን የነበረውን የምግብ መመረዝ ምክንያት ተማሪው በሙሉ ታሞ ነበር ያንን ታሪክ ‹‹ሸርተቴ›› ሲል ቁልጭ አድርጎ በግጥም ፅፎታል ሲል ያስታውሰዋል፤በጣም የምወደው ግጥም ነው የሚለውን ይሄን የመስፍን አሸብር ግጥምንም በተለያዩ መድረኮችም አቅርቦታል፡፡

‹‹ሸርተቴ››

እንቅልፍ የምትነሳ ፤ሌት የማታስተኛ
ህሊና ሞጋቹ፤ክፉ ወንጀለኛ
መቼም አንላቀቅ፤ አንተ ተንኮለኛ
ክስ አቅርቤያለሁኝ ፤ለፈራጁ ዳኛ
ሳትታይ አድፍጠህ፤ተሰውረህ ከ’ኛ
ገብተህ የተገኘህ ፤ከዚህ ከብላቴ
በላ ልበልሀ፤ተጠየቅ ሸርተቴ!
እያለ የሚቀጥለው ይህ ግጥም በኃላ በታተመው ‹‹ጠብታ ፍቅር›› በተሰኘው መፅሀፉ ውስጥ የተካተተ ሲሆን የብዙዎችም ትዝታ ነው፡፡ ከብላቴ ከተመለሱም በኃላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስታትስቲክስ ትምህርት ክፍል የቀረውን ትምህርት አጠናቆ ተመርቋል፡፡መስፍን ‹‹መነሳነስ›› የሚል ርዕስ የሰጠው አጭር ልብወለድም ፅፎ በመመረቂያ መፅሄታቸው ላይ ሊታተምለት ችሏል፡፡

የስራ ህይወት

መስፍን በቀበሌ የወጣቶች ማህበር የስነ-ጽሁፍ መድረኮች ላይ ግጥሞችን፣ ልብ-ወለድ እና መጣጥፎችን በማቅረብ የስነ-ጽሁፍ ክህሎቱን አዳብሯል፡፡ አብሮ አደጉ ተሻገር ሽፈራው ‹‹የስሜት እና የአዕምሮ ጉልበት ነው መስፍን ውስጥ የሚታየው ያም ይመስለኛል ለገጣሚነት ህይወቱ አስተዋፅኦ ያደረገው ››ሲል ይገልፀዋል፡፡ መስፍን አንድን ነገር ለመፃፍ ከተቀመጠ ትኩረቱ ወረቀት እና መፃፊያ ላይ ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ ቢያወሩት ቢጠሩት አይሰማም፡፡በተመለከተው እና ፣በቅርቡ ያለውን ነገር በፍጥነት ወደ ግጥም ቀይሮ በመፃፍም ይታወቃል፤አንድ ቀን ወደ ቤታቸው ጎረቤታቸው እንጨት ተሸክመው ልብሳቸውን ሳይቀይሩ ቢመጡ ውሻው አላስገባ ይላቸዋል፤ሌላ ቀን ይገቡ የነበሩት ያን ቀን አላስገባ ቢላቸው ወዲያው ‹‹ፕሮቶኮል›› የተሰኘውን ግጥም ፃፈ፡፡

ፕሮቶኮል
የነጌቶች ውሻ ፤የትልቁ ግቢ
የዘመኑ ቦቢ፤
አመዛዛኝ ኖሮ፤አርቆ አሳቢ
የሰው ጠረን ገማች፤የሰው ፊት አንባቢ
የነተበ ሸማ፤አዳፋ ቡቱቶ
መልበሴን ገምቶ
ወልጋዳ ጫማዬን፤ሲያስተውል ቆይቶ
አዳዲሱን ለባሽ ፤ወፋፍራሙን ትቶ
እኔ ላይ ቡ አለ፤ለገላጋይ ታክቶ
‹‹ፕሮቶኮል›› አውቆ ፤ውሻ እንኳ ለይቶ፡፡1985

መስፍን ስሜቱን መደበቅና መቆጣጠር ፣የማይችል ጮክ ብሎ የሚያወራ እጅግ ተመስጦ ያለው ቅን ሰው ነው የሚለው ጓደኛው ጋዜጠኛ ዘከርያ መሃመድ ‹‹አባ ስሜቶ ››በማለት ነበር የሚጠራው፡፡ከተመረቀ በኃላ ወደ ኬንያ በስደት በሄደበት ጊዜ በርካታ ግጥሞችን ይጽፍ ነበር፤አንድ ቀን ግን ተነስቶ ‹‹እኔን ብሎ ገጣሚ›› በማለት ግጥሞቹን በሙሉ ሰብስቦ አቃጥሏቸዋል፤በቅርብ የነበሩም ይህንን ከመስፍን ስሜታዊነቱ ጋር ያያይዙታል፡፡በ‹‹ጠብታ ፍቅር››መፅሀፉ መግቢያ ላይ ያለው መንደርደሪያ የተሰኘው ግጥሙ በኋላ ያንን አልፎ እንደገና ግጥም መፃፍ መጀመሩን ያሳየበት ነው፡፡

መንደርደርያ

እስቲ እንግዲህ ልጀምረው ፤መጀመር ይሻላል አሉ
መጨረስ ካልታደሉ፤
ቢጨረስስ ለራስ እንጂ፤ልቦና ቀልቡን ለማጠር
ስሜት ውሉን ለመቋጠር፤ህሊና እግሩ እንዲታሰር
ድሮስ ቢሆን የታለና፤የሚጨረስ ነገር አይኖር፡፡(1984-ዋልዳ -ኬንያ )

የጋዜጠኝነት መንገድ

መስፍን አሸብር ከኬንያ (ዋልዳ) ከስደተኛነት መልስ በአዲሱ የሬድዮ ፋና ጋዜጠኛ ሆኖ ፋና ገና የአየር ስርጭት ሳይጀምር ጀምሮ ተቋሙ ዕውቅና አግኝቶ እስኪቋቋም ድረስ መስፍን አሻራውን አሳርፏል፡፡ ብቸኛው በጋዜጠኝነት በሰራበት ተቋም የራሱ አዳዲስ ፎርማቶች በመቅረፅም በመስራት ከቀዳሚያኑ የፋና ራዲዮ ጋዜጠኞች ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ለራዲዮ ተመራጭ የሆነ ባለ ድምጸ ጎርናናው መስፍን በፍቅር በሚሰራበት ራዲዮ ላይ በድምጹ ብቻ በአድማጮች የሚለይ ነበር፡፡

መስፍን ስራውን በትኩረት የሚሰራ ከስራ ውጪ ደግሞ ጥርስ የማያስከድን ቀልድ እና ጨዋታ አዋቂ በብዙዎች ተወዳጅ እርሱ ባለበት መገኘት ደስ የሚያሰኝ የሚሉለት አይነት ሰው ነው፡፡ በፋና ራዲዮ አብረው ይሰሩ ከነበሩት ውስጥ ጋዜጠኛ እማዋይሽ ዘውዱ ‹‹ሊፅፋቸው ያሰባቸውን ነገሮች እና የፃፋቸው ነገሮች እዚያው አጠገባችን ያለውን ነገር በልዩ ዕይታ እና ምልከታ ማየትን በጋዜጠኝነት መንገዴ ከመስፍን ያገኘሁት እና የጨመረልኝ ነገር ነው›› ትላለች፡፡

‹‹ከጥበባት ዓለም›› የተሰኘውን ፕሮግራም የመስፍን በፋና ራዲዮ መለያው ነበር፡፡መስፍን አንድን ነገር ለማግኘት ካሰበ ሳያገኘው አያርፍም ፤በአንድ ወቅት ‹‹ከጥበባት ዓለም›› የተሰኘውን ፕሮግራም ማዘጋጀት ከጀመረ በኋላ በደራሲ በዓሉ ግርማ ‹ኦሮማይ› መጽሀፍ ውስጥ የፊያሜታ ጊላይ ገጸ-ባህሪይ መነሻ ነች ትባል የነበረችውን ወጣትና ሌሎችንም ፈልጎ ቃለ-መጠይቅ ለማድረግ አስመራ ድረስም ሄዶ ነበር፡፡

በፋና ራዲዮ ቆይታው ከጋዜጠኝነቱ ባሻገር የተለያዩ የራዲዮ ድራማዎችን በመፃፍ ለአየር አብቅቷል፡፡ የመስፍን ጋዜጠኝነት መጀመሪያውም ማብቂያውም ሬድዮ ፋና ነበር፡፡ አምስት ዓመታት ባልሞላ አጭር (1986-1990) የሥራ ቆይታው “ከጥበባት ዓለም” በተሰኘ ሳምንታዊ ዝግጅት በሬድዮ ጣብያው አድማጮች ለመወደድ የበቁ ይዘቶችን በማቅረብ ሙያዊ ተሰጥኦውን አሳይቷል፡፡ በየሳምንቱ ዓርብ ከማምሻ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት ይቀርብ በነበረው “ከጥበባት ዓለም” ዝግጅቱ ብዙ ገጣምያንን፣ የአጭርና ረዥም ልቦለድ ደራስያንን፣ ጸሐፍያነ ተውኔትን፣ የሙዚቃ ሰዎችን፣ ሰዓልያንን፣ ቀራጽያንንና የፈጠራ ስራዎች ሀያስያንን በማወያየት ለአድማጮቹ አቅርቧል፡፡

የዝግጅቱ ይዘቶች ወቅታዊ የኪነጥበብ ሁነቶችንና ዝንባሌዎችን የሚከተሉና በፈጠራ ሥራዎች ዓላማ ላይ የሚያተኩሩ አወዛጋቢ ሀሳቦችን የሚያስተነትኑ ነበሩ፡፡ ስለ ስነጽሁፍ መድረኮች፣ በመታየት ላይ ስላሉ ተውኔቶችና የሥነ-ሥዕል አውደ-ርዕዮች ከሚያቀርባቸው ዘገባዎቹ ጋር የይዘት ትንታኔንና የኪነ-ጥበብ ፍልስፍናን ያካትት ነበር፡፡ የዝግጅቱን እንግዶች ለምን እንደሚጽፉ፣ እንደሚገጥሙ፣ እንደሚያዜሙ፣ እንደሚስሉ … ደጋግሞ ጠይቋል፡፡ አወያይቷል፡፡ “የኪነጥበብ ዓላማ ምንድነው?” በሚለው መሰረታዊ ጥያቄም ላይ ሀሳብ አለዋውጧል፡፡

መስፍን በሳምንታዊ የሬድዮ ዝግጅቱ ለብዙ የኪነጥበብ ሰዎችና ሀያስያን መድረክ ከመፍጠሩም በተጨማሪ “ከጥበባት ዓለም” ወቅታዊ ፍላጎቶች ጋር የሚዛመዱ የግጥም ስራዎቹን በማቅረብ ተደማጭነት አትርፏል፡፡ የራሱን አጫጭር የሬድዮ ተውኔቶች አዘጋጅቶ በማቅረብ ሳምንታዊ ዝግጅቱን አዝናኝና አስተማሪ ለማድረግ ችሏል፡፡ ይህም ተሞክሮው በኪነ-ጥበብ ጋዜጠኝነት ዘርፍ ላይ በማተኮር አስተዋጽኦ ካበረከቱ የአገራችን ጋዜጠኞች አንዱ ያደርገዋል፡፡

በሬድዮ ጣብያው ውስጥ የነበረው ቆይታ አጭር ቢሆንም የስነጽሁፍ ተሰጥኦውና ልምዱ ከዘጋቢ ጋዜጠኝነት ባሻገር ለጀማሪ ጋዜጠኞች ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ የአርታኢነት ሚና ለመያዝ አብቅቶታል፡፡ “ከጥበባት ዓለም” ዝግጅቱ በተጨማሪ በሚሳተፍበት የዜና ስራ ለወጣት ጋዜጠኞች የዘገባ መነሻ ሀሳብ የመስጠትና የማነሳሳት ችሎታውን ባልደረቦቹ ያደንቁለት ነበር፡፡ ከህልፈቱ በኋላ የታተመው የግጥም መጽሀፉ በተመረቀ ዕለት የተናገሩ ባልደረቦቹ እንዳሉት “መስፍን ጋዜጠኝነት ስለ ድሆች መዘገብ አለበት ይላል፡፡ ስለዚህ ደሀው ወደሚገኝበት የጉልት ገበያና ጠጅ ቤት ብቅ በሉ ይላል”፡፡

መስፍን ካበረታታቸው ወጣት ባለሙያዎች አንዱ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ባለቤት እና መስራች እዝራ እጅጉ ይገኘበታል፡፡ እዝራ በ1989 የአካፑልኮ ቤይን ፊልም ለቦሌ ሀይስኩል ተማሪዎች እየተረጎመ ባቀረበበት ጊዜ መስፍን አሸብር የሚድያ ሽፋን እንዲያገኝ በማድረግ የ17አመቱ እዝራ በፋና ሬድዮ ትርጉሙን እንዲያቀርብ አግዞታል፡፡ እዝራም መስፍንን ምን ጊዜም ያመሰግነዋል፡፡

የመስፍን ስንብት

መስፍን ባጋጠመው ህመም ምክንያት በ31 ዓመቱ በ1990 ዓ.ም ህይወቱ አለፈ፡፡ለሞቱ ቀናት ቀርተውት እንኳን ከህመሙ ጋር እየታገለ ግጥምን፣መጣጥፍ እና ወግን ይጽፍ ነበር፡፡ጓደኞቹ እና የቅርብ ሰዎቹ የመስፍንን የግጥም ችሎታ ያውቁ ነበር እና መፅሀፍ ሳያሳትም ህይወቱ ማለፉ ይቆጫቸው ነበር፤በዚህ መነሻነት የፃፋቸውን ግጥሞች ከያሉበት አሰባስበው ከዘጠኝ ዓመታት በኃላ በቅርብ ጓደኛው ስንዱ አበበ አሳታሚነት ግጥሞቹ‹‹ጠብታ ፍቅር›› በተሰኘ ርዕስ ለመታተም በቅተዋል፡፡ ጋዜጠኛ ዘከርያ መሀመድ‹‹ጠብታ ፍቅር መጽሀፍ እንደ ጂጂ እኔን የራበኝ ፍቅር ነው ሙዚቃ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ግን ቀድሞ የተጻፈ ነው፡፡የቃላቱ ስዕል ገለፃው ፣ቋንቋው የሚደንቅ ነው፡፡›› በማለት መፅሀፉን ይገልፀዋል፡፡

መዝጊያ

ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የመዝገበ-አእምሮ የቦርድ አባላት አቋምን የሚያንጸባርቅ ነው፡፡ መስፍን 31 አመቱ ላይ ነው ያረፈው፡፡ ግን ያኖረው አሻራ ትልቅ ነው፡፡ ትልቅ አሻራ ለማኖር ብዙ እድሜ ማካበት ግድ አይደለም፡፡ እነዚያ ምስል ከሳች ግጥሞቹ ዘመን ተሻጋሪ ፈጽሞ ሊሰራ የማይቻል ገጣሚ አድርገውታል፡፡ በህይወት ሳለ አየር ላይ ያዋላቸው መሰናዶዎች ዛሬም ሲደመጡ በእውቀት የተሰሩ ለመሆኑ ያስታውቃሉ፡፡ መስፍን አሸብር ዲግሪውን ካገኘ ከ6 አመት ቆይታ በኃላ ነው ያረፈው፡፡ ነገር ግን ያቺን 6 አመት ትልቅ አሻራ ለማኖር ተጠቅሞባታል፡፡ እኛ ደግሞ ታሪክ ሰናጅ እንደመሆናችን የ1980ዎችን ጀግናዎች መዘከራችን እንደ አቋም እምነት ይዘን የምናራምደው እሳቤ ነው፡፡ በድሮ ገጣሚና በድሮ ከያኒ ብቻ እየተንጠለጠሉ ከመኖር ለድሮውም ክብር እየሰጡ አዳዲሱንም ወደ መድረክ ማምጣት የተመሰረትንበት ቀዳሚው ግብ ነው፡፡ ከመስፍን በፊት ብዙ ገጣሚዎች ቢኖሩም መስፍን ደግሞ ዘመኑን መስሎ ረቂቅ ሀሳቦችን ያነሳ ነው፡፡ በመሆኑም በዘመኑ ልክ ልናከብረውና ስራዎቹን እያነሳሳን ልናወድሰው ይገባል፡፡ ይህ የህይወት ታሪክ መስፍንን ሙሉ ለሙሉ ይገልጸዋል ባንልም ማነው ለሚሉ ግን ትክክለኛ ምላሽ እንደሚሰጥ እናምናለን፡፡ ይህ አጭር የህይወት ታሪክ በዋናነት በቅድስት ወልዴ ተዘጋጅቶ በእዝራ እጅጉ አርትኦት የተሰራለት ሲሆን በተወዳጅ ሚድያ ዲጂታል ሚድያዎች ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ይህ ጽሁፍ ዛሬ ነሀሴ 7 2015 አ.ም የተጫነ ሲሆን በቅርቡ ታትሞ ለንባብ በሚበቃው መዝገበ- አእምሮ ላይም የሚካተት ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *