76 አመት የተሰናዳ የትምህርት ሚኒስቴር የሂሳብ መግለጫ ሪፖርት

የዛሬ 76 አመት የተሰናዳ የትምህርት ሚኒስቴር የሂሳብ መግለጫ ሪፖርት ከእጃችን ገባ

ይህ የሂሳብ መግለጫ ሪፖርት ሲሰናዳ ሀገራችን ገና ዩኒቨርሲቲ አላቋቋመችም፡፡ ጣሊያንም ተባሮ ከወጣ ገና 7 አመቱ ነበር፡፡ ይህ በታይፕ ራይተር የተተየበ የሂሳብ ሪፖርት 4 ገጽ የወሰደ ሲሆን የ76 አመት እድሜም አስቆጥሯል፡፡ ይህ ታሪካዊ ሰነድ ከማይፈለጉ ወረቀቶችና ህትመቶች ጋር በአንድ ወቅት ሊጣልና ሊቃጠል ሲል ታድገነው ከእጃችን አስገብተነዋል፡፡ ለሰነዶቻችን አምድ ስለሚመጥንም እነሆ ከአጭር መግለጫ ጋር አቅርበነዋል፡፡

ይህ የሂሳብ መግለጫ ስለ ጠቅላላው የ1940 የትምህርት ሚኒስቴር በጀት የሚያወሳ ነው፡፡ በየጠቅላይ ግዛቶች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ስለተመደበው በጀትም ዝርዝር የአሀዝ መረጃ ያስቀምጣል፡፡ሪፖርቱ ነሀሴ 16 1940 የተጻፈ ሲሆን ሪፖርቱንም ያሰናዱት አቶ ጳውሎስ ብርሀኔ እንደሆኑ ሰነዱ ይጠቁማል፡፡ 4ቱን ገጽ በጥራት ስካን ያደረግነው በመሆኑ በጥንቃቄ ታዩት ዘንድ እንጋብዛለን፡፡ ከዚህ ጽሁፍ ጋር አብሮ ፖስት የተደረገ በመሆኑም ኦሪጅናል ሰነድ እያያችሁ ታሪክ ማንበብ ትችላላችሁ፡፡

የዛሬ 76 አመት የነበረውን ሁኔታ የበለጠ ለማወቅ እንዲረዳችሁ አንዳንድ ታሪኮችን ጀባ እንበላችሁ፡፡ ከታች የቀረበውን ጽሁፍ ያገኘነው ዶክተር አክሊሉ ሀብቴ ከጻፉት ‹‹ የቀዳማዊ ሀይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ የከፍተኛ ትምህርት መቋቋምና መስፋፋት ጉዞ በኢትዮጵያ በሚል ርእስ በገጽ 125 ካሳፈሩት ሀሳብ አንዳንድ ነጥቦችን እናስቀምጣለን፡፡

‹‹…. ጦርነቱ እንዳለቀ ትምህርት እንደሚያስፈልግ በተደረገው ቅስቀሳ ወጣቱ ግልብጥ ብሎ መውጣት ጀመረ፡፡የወታደር መጋዘን፤የወታደር ፈረሶች የወታደር ክሊኒክ የመሳሰሉትን እንዳገኙ ወደ ትምህርት መስጫነት ማመቻቸት ግዴታ ነበር፡፡ ሳይሞቱ በተረፉት ውጭ ሀገር ኖረው በህይወት በተመለሱት ፤ አንዳንዴም ለኢጣሊያ በማገልገል መጠነኛ ዘመናዊ ትምህርትና ያገር ትምህርት እውቀት ባገኙ የውጭ ሀገር ሰዎች በየቦታው ትምህርት ቤት መከፈት ተጀመረ፡፡ ንጉሰ-ነገስቱም ለትምህርት መስፋፋት በጣም ይጥሩ ነበር፡፡ትምህርት ቤቶች በየቦታው እንዲከፈቱ ችግር ሲኖር ለማበረታታት አዳሪ ት/ቤት በማቋቋም ለተማሪዎቹ ዩኒፎርም በማሰፋት መምህራን ከልዩ ልዩ ሀገራት እንዲቀጠሩ በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *