‹ተወዳጅ ሚድያ› 22ኛ ዓመቱን ሌሎችን በማመስገን እያከበረ ይገኛል!


 
በታሪክ ስነዳ፣ በመጽሐፎችና በኹነት ዝግጅት በጋዜጣ ሥራና በሌሎችም  የሚታወቀው ‹ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን › 22ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን፣ በየወቅቱ ዐብረው የነበሩ ባለሙያዎችንና ተቋማትን በማመስገን ሊያሳልፍ ነው።
 
‹ማክበር መሠልጠን ነው› በሚል መሪ አርእስት ከፊት፣ ከጐንና ከጀርባ የነበሩትን የሥራውን ዋና አንቀሳቃሾች ማመስገን ግድና ተገቢ ነው›› ሲል የድርጅቱ መሥራች ጋዜጠኛ ዕዝራ እጅጉ ተናግሯል።
 
ሰው ሕልም ቢኖረውም፣ እግዚአብሔር  ግን ትክክለኛ ዐቅም ያላቸውን ሰዎች ለባለሕልመኛ  እንደሚሰጠው የሚያምነው ዕዝራ እጅጉ፣ በእነዚህ ሰዎች ምክንያት  ‹ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን › ለዚህ ደረጃ መብቃቱን ይናገራል። ‹ተወዳጅ ሚድያ›፣ በተለይ ባለፉት 9 ዓመታት፣ ለ25 ሰዎች ወቅታዊ የሥራ ዕድሎች የፈጠረ ሲኾን፣ ብዙዎችም ዐቅማቸውን እንዲያውቁ፣ እንዲጠቀሙና እንዲያውቁ አድርጓል።
 
የካቲት 2፣ 1996 ዓ.ም በይፋ ሕጋዊ ሰውነቱን አግኝቶ ሥራውን የጀመረው ‹ተወዳጅ ሚድያ›፣ ‹‹ተወዳጅ›› የተሠኘ በነፃ የሚሠራጭ የማስታወቂያ ጋዜጣ በማሳተም ወደ ሚድያው ሥራ ዘልቋል፡፡ ‹‹በጊዜው ሥራው ሲጀምር፣ በየሱቁ እየዞሩ የማስታወቂያ ደንበኞች መፈለጉ ፈታኝ ነበር›› የምትለው የ‹ተወዳጅ› የመጀመሪያዋ ደሞዝ ተከፋይ የሽያጭ ባለሙያ ቅድስት ደበበ ናት። ቅድስት በጊዜው በ500 ብር ደሞዝ ሥራ መጀመሯን የምትናገር ሲኾን፣ ‹‹ከ22  ዓመታት በኋላ ‹ተወዳጅ› ሚድያ ዐዲስ ዐሳብ፣ ብቃትና ዐቅም ያላቸውን ባለሙያዎች አፍርቶ በማየቴ ርካታ ይሰማኛል›› ብላለች።


 
በአኹኑ ሰዓት ‹ተወዳጅ› ሚድያ ታሪክ በመሰነድ ሥራ ላይ ትኵረት ሰጥቶ ከ23 በላይ መጻሕፍትን ለአንባቢ ማቅረብ ችሏል። በዚህ ብቻ ሳይወሰን፣ 45 ታሪኮችን በሲዲና በዲቪዲ ያቀረበ ሲኾን፣ ልዩ-ልዩ ኹነቶችንም በማዘጋጀት አሻራ ማኖር ችሏል።
 
‹ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን›፣ በተለይ የሰዎች የሕይወት ታሪክ ከጉግል ላይ በቀላሉ ተፈልጎ እንዲገኝ ሲያደርግ፣ ለዚህ ጥረቱም ዳላስ ከሚገኘው ‹የአርኣያ ሰው› ሽልማት ለማግኘት በቅቷል። እንደ ‹ቻት ጂፒቲ› ያሉ ዘመኑ የወለዳቸው  የመረጃ ምንጮችም የ‹ተወዳጅ› ሚድያን ታሪኮች እንደ ተአማኒ የመረጃ ምንጭ አድርገው ይወስዷቸዋል።
 
‹ተወዳጅ› ሚድያ ለባለሙያ ዕድል በመስጠት የሚያምን ድርጅት መኾኑን መሥራቹ ዕዝራ ያስረዳል፣ ‹‹ልዩ-ልዩ ተቋማትና ግለሰቦች የሚያግዙት፣ ትብብር ለማሳየት ኹሌም ዐብረውት የሚኾኑ ተቋም ነው›› ሲልም ሀሣቡን ገልጿል።
 
በተለይ ተወዳጅ ከ2009 ዓ.ም ወዲህ ባለፉት 9 ዓመታት ትኵረቱን ሙሉ በሙሉ ታሪክ ላይ በማድረግ ዐዲስ አካኼድና ስልት በመንደፍ የበኩሉን የአገር አሻራ እያኖረ የሚገኝ ድርጅት ነው።


 
‹ተወዳጅ›፣ ኅትመቶችን ወደ ድምፅ በመቀየር ‹‹የኤርትራ ጕዳይ››ን (አምባሳደር ዘውዴ) የመሰሉ ከ30 በላይ መጽሐፎችንም በትረካ መልክ በማቅረብ በቀላሉ ሰዎች ሥራ እየሠሩና መንገድ ላይ እየኼዱ ማዳመጥ የሚችሉበትን ስልት ነድፏል።
 
ሚድያው  የኢንሳይክሎፒዲያ ፕሮጀክት በመቅረፅ ከሚያዝያ 13፣ 2013 ዓ.ም  ጀምሮ ‹‹መዝገበ አእምሮ›› የተሠኘውን መጽሐፍ በ2 ቅጽ ያሳተመ ሲኾን፣ በአጠቃላይ የ400 የሚድያና የጥበብ ሰዎችን ታሪክ ይዘዋል፡፡


 
የአባት የእናቶቻቸው ታሪክ እንዲጻፍ የሚፈልጉ በአገር ውስጥና በባሕር ማዶ የሚገኙ ደንበኞችም ‹ተወዳጅ›ን መርጠው የቤተሰቦቻቸው ታሪክ እንዲሰነድ ያደረጉ ሲኾን፣ እስከ ዛሬም 23 መጽሐፎች ለኅትመት በቅተዋል።መፅሀፍ ከመፃፍ ባሻገርም ደረጃውን የጠበቀ የአርትኦት ተግባር እያከናወነ ይገኛል።

አንድ የቈየ ምስል፣ ሰነድ ወይም ታሪክ አመላካች ወረቀት የቤት ሥርቻ ስር ከሚቀመጥ፣ በ‹ተወዳጅ› ዲጂታይዝ እየተደረገ ሲኾን፣ እስከ ዛሬም ከ10,000 በላይ ፋይሎች በቀላሉ ለትውልድ ተደራሽ እንዲኾኑ ተደርጓል።
 
‹‹ማክበር መሠልጠን ነው›› በሚል መሪ ዐሳብ ‹ተወዳጅ› ሚድያ እዚህ ለመድረሱ ምስጋና የሚቸራቸው ከ140 በላይ የሚኾኑ ባለሙያዎች፣ ግለሰቦችና ተቋማት በtewedajewikipedia.com ድረ ገጽ በtewedajemedia የፌስ  ቡክ ገጽ ላይ ስማቸው በዝርዝር የተቀመጠ ሲኾን፣ የ22ኛ ዓመት ክብረ በዓሉም ያለምንም ድግስ በማኅበራዊ ድረ ገጾችና በተመረጡ ሬድዮ ጣቢያዎች መረጃዎችን መጥኖና ከፍ አድርጎ በማስተላለፍ እንደሚከበር ታውቋል።


 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *