የሚድያ መሪ ሙሉጌታ ገሰሰ

ክፍል 2

ሙሉጌታ ገሰሰ ትውልዱ ኲዊሃ ላይ በ1951 ዓ.ም ነበር።

በፋና ውስጥ  መሥራች ከሚባሉና በአመራርነት ፋናን በከፍታ ካራመዱ መካከል ግንባር ቀደሙ ነው። የፋና ሬድዮ መሥራች፣ የብሪፊንግ ባህል በሌሎች የሚድያ ተቋማትም ጭምር እንደ መልካም ተሞክሮ ከመወሰዱ በፊት በፋና ሬድዮ ላይ ሥራን በግልፅነት በጋራ የመገምገምና ለነገ የተሻለ ሆኖ መገኘት መሠረት የሚጥለውን ሥርአት በማስጀመር ፣ የተቋሙን መሪ ቃሎች በተለያዩ ጊዜያት ከ1987- 1997 የቆየውን መሪ ቃል በማስወጣትና ተቋሙን በይዘትም ሆነ በቴክኖሎጂ ለማዘመን ብልህ አመራርነቱን ያስመሰከረ ጠንካራ የሚድያ መሪ ነው። 

በፋና 25ኛ አመት ምሥረታ ላይ በቀለማት የቴሌቪዥን መዝናኛ ላይ የስቱዲዮ እንግዳ ሆኖ በቀረበበት ወቅት ያነሳው አንዱ ሀሳብ የተቋሙ የሥራ ባህልን ይመለከታል።

 እንደሚታወቀው ከበረሀ ጀምሮ የነበረ የሬድዮ ጣቢያ እንደመሆኑ ቀዳሚው የሥራ ሀይል በትግል ሜዳ ላይ የነበረው ነው። ታጋዩ በአኗኗሩ የሥራ ሰዓትም ሆነ ደሞዝ የሚያውቅ የንግግር ልምዱም ፊትለፊት ቁጣም ጭምር የተቀላቀለበት የሚመስል እና ሲወጣ ግን አብሮ ሻይ የሚጠጣ ቂምና በቀልን የማያውቅ የነበረ ሲሆን ከዚህ የሰው ሀይል ላይ ተጨማሪ ሆኖ የገባው ሲቪል ደግሞ ይሄንን ባህል ጨርሶ የማያውቅ በአስተዳደራዊ አሰራር የሚመራና መደበኛ የሥራ ሰዓትን የሚጠቀም ቁጭ ብሎ መነጋገር የሚባለውን ነገር የማያውቅ በመሆኑ ሁለት የተለያየ ባህልን በማጣመር ወደ አንድነት ማምጣት ይጠይቅ ነበር። በመሆኑም የጊዜው አመራሮች አስተዳደራዊ ማንዋልን በመዘርጋት ቤቱ መርህ እንዲኖረው ቢደረግም ግን ደግሞ ታጋዩ የለመደው የመነጋገር ባህል ግን ቀጣይ ስራን ለማስተካከል ጠቃሚ ነውና ይሄንን ለማስቀጠል የማለዳ ብሪፍ ተጀመረ። የሥራ ሰዓት በሚል በትግል ሜዳ የነበረው ሰው ከለመደው አኗኗር ውጪ እንዳይታሰር በማለትም ጋዜጠኛው የሰዓት ፊርማ ከሚቀመጥለት ይልቅ ይዞት የሚመጣው ጠቃሚ ሀሳብ ላይ ትኩረት ማድረጉ ተመረጠ፡፡ ስለዚህም ወጥቶ የሚቃርመውን ጠቃሚ ሀሳብ እያመጣ ቤቱን ለማሳደግ ሁሉም በየፊናው ይለፋ ነበር፡፡ ውጤቱም በአንድ ሰው ጥረት ብቻ ሳይሆን በሁሉም ድምር የመጣ ውጤት መሆኑን ያረጋግጣሉ።

ግዜው ላይ ጠንካራ የቦርድ አመራር መኖሩ ሌላው በጎ ነገር ሲሆን አዳዲስ የሰው ሀይል በመጨመር፣ የአሰራር ማኑዋሎችን በመስራት፣ ደካማና ጠንካራ ጎንን በመለየት ክፍተቱን ለመድፈን አብሮን ያለው የትኛው የህብረተሰብ ክፍል ነው የሚለውን ለማጥራት የጥናት ስራ በመሥራት አሰራሮችን ለማሻሻል ጥረት ተደርጓል ፡፡ይህም እርምጃውን እንዲጨምር ምክንያት ሆኖለት ነበር። 

ሰው ላይ የተለየ ትኩረት ይሰጥ እንደነበር የተናገረው ሙልጌታ አንድ ሠራተኛ በሥነምግባር ምክንያት ሳባረር ቤተሰቡ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ሚስትን ወይም ልጅን አምጥተን እስከመቅጠር እና የቤተሰቡ ኑሮ እንዲቀጥል ማድረጋችን የዚሁ ማሳያ ነው ብሏል። በዚህ የቅጥር ሒደት የቤተሰቡ አባል ሙያው ስላለው ብቻ ሳይሆን ባለው አቅም ከፅዳት ጀምሮ በሚችለው እንዲሠራ ነው ሁኔታው የሚመቻችለት። 

በፋና ውስጥ ሀሳብ ያለው ሰው ትልቅ ዋጋ ይሰጠው ነበር። ሁሉም በነፃነት የሚያስበውን እንዲያቀርብ ይበረታታል። እቅድም ከላይ ወደ ታች ሳይሆን ከታች ወደ ላይ ከጋዜጠኛው ወደ አመራሩ የሚቀርብ መሆኑ ጋዜጠኛው ሀሳቡን እንዲያንሸራሽር እድል ፈጥሮለታል። የሚሰሩ የነበሩት ዝግጅቶች በ3 መልኩ የተዋቀሩ ነበሩ ማለትም ኢንፎርማቲቭ፣ ኤዱኬሽን እና ኢንተርቴይመንት በሚል።

በዚህ መሠረት ህዝቡ ውስጥ የዘለቁ ትላልቅ ፎርማቶችን ይዞ መቅረብ ተችሏል። እነ ዳሰሳ፣ህዝቡ ምን ይላል እና በዜና ደግሞ በአለምነህ ይቀርብ የነበረው ጥበብ የታከለበት የግነት ዜና ተደማምሮ ፋናን ሊያገነው ችሏል። ፋና የሚለው በአንድ ቃል ሁለት ቋንቋን የሚገልፅ ሆኖ የቀረበው ከሰራተኛው በተዋጣ ሀሳብ ሲሆን ብሩክ ከበደ ይዞት የቀረበው ፋና የሚለው ቃል ብርሀንን እና መንገድን የሚገልፅ በመሆኑ አፅድቀነው የተቋሙ መጠሪያ ሊሆን በቅቷል በሚል ሙሉጌታ ጊዜውን አስታውሷል።

የፋናን ቴክኖሎጂ አቅሙ በሚደንቅ ፍጥነት እያደገ መምጣቱን ያስረዳው ሙሉጌታ በግዜው ጋዜጠኞች የጠዋት ዜና ለማቅረብ ለሊት 8 ሰዓት ቢሮ ገብተው መረጃዎችን ማፈላለግ ይጠበቅባቸው ነበር ያለው።

ፋና እራሱን በራሱ እየደጎመ የሚሠራ መሆኑንም በማንሳት በገቢ ማስገኛ ሥራ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ 80 ሺህ ብር የሚጠጋ ገንዘብ ከሜጋ አሳታሚ ድርጅት ነበር የተበደሩት ከዛም በተለያየ ሁኔታ ስቴት ኦዲየንስ የሚሉትን የመድረክና ስፖንሰር የሚያስገኙ ስራዎች ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመሆን ሰርተው ተቋሙን በገንዘብ ለመደገፍ ችለዋል። እሩቅ እያሰበ የራሱን ህንፃ ገንብቶ አቅሙን አግዝፎ እንዲገኝም ይህ አሰራር መሰረት ጥሎለት አልፏል።

ፋና ትምህርት ቤት ነው ተብሎ ሲነገር ይሰማል ምክንያቱ ደግሞ በሙያም ምንም ልምድ ያልነበራቸው ሰዎች ገብተው ዕውቀታቸውን አካብተው የሚወጡበት ቤት በመሆኑ ነው። በየጊዜው የነበሩ አመራሮች ይሄንን በኩራት ይናገሩታል አቶ ሙልጌታ ደግሞ ሠራተኛው በእውቀትም እራሱን ማሳደግ ካልቻለና የትምህርት ደረጃውን ካላሳደገ እርከን በመከልከል ጫና ልንፈጥርበት እንዲማርም ልናበረታታው እንጥር ነበር ብለው ያስታውሳሉ።

አዳዲስ የሚገቡትን ደግሞ በጠንካራ የማጣራት ሥራ ጥራቱን የጠበቀ ሙያተኛ እንዲገኝ ይሠራ ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ  የመፃፍ ችሎታ ያላቸው የተለያዩ ሙያተኞች ለምሳሌ ኢኮኖሚስት የሆኑ ወይም የህግ ባለሙያዎች፣ የጤና ባለሙያና መሰል ሙያተኛን በመፈለግ በአንድ ጉዳይ ስፔሻላይዜድ ያደረጉ ጋዜጠኞች እንዲኖሩት ይሠራ ነበር።

ሙሉጌታ በትምህርት እራሱን በማሳደግ ከእንግሊዝ ሀገር ተምሮ ማስተርሱን ለመቀበል የበቃ ሲሆን በመሪነት ብቃቱ የሚያውቁት ሁሉ የሚመሰክሩለት መሪ ነበር። ከሚድያው አለም ወጥተው በኮንስትራክሽን አሶሴሽን ውስጥ በመሥራት ላይ ነበር።  ሚድያዎች የሁሉንም ሀሳብ በሚዛናዊነት በአንድ መድረክ እያቀረቡ የማወያየትና ሀሳብ ገዢ ሆኖ እንዲወጣ መስራት ላይ ሊተጉ እንደሚገባቸው ሙሉጌታ በአፅንኦት መምከሩ የሚዘነጋ አይደለም፡፡


ሙሉጌታ ገሰሰ በወዳጆቹ አንደበት

ብሩክ ከበደ (የኤንቢሲ ዋና ሥራ አስፈፃሚ )

ሙሉጌታን ከፋና በፊት ነው የማውቀው። ጓደኛዬና ሚስጥረኛዬ የልብ ወዳጅ ገበና ከታች ነው ሙሉጌታ። ከአለቅነቱ በላይ ወዳጅነቱ ይበልጣል።  የፋና ምሥረታ ፕሮጀክት ላይ በ1986 ዓ.ም ነበር የሚያገኘን። መስፍን ዓለማየሁ የሺጥላ ኮከብን የመሰሉ ደራሲዎች ጓደኞቹ ነበሩ። ዘከሪያ መሀመድ መስፍን አሸብርና እኔን ያገኘን ነበር።  ያኔ እኛን የሚያገኘን ፋና ሬድዮን የመመስረት ሀሣብ ስለነበር ለዚያ ሥራ ይሆናሉ ብሎ ስላሰበን ነበር፡፡ ከእኛም ጋር በቀላሉ ይግባባ ስለነበር ተመችቶን ነበር። ሙልጌታ ገሠሠ ሁለገብ፣ ተግባቢ፣ቤተሰባዊነትን መፍጠር የሚችል፣ ሁሉም ሰው ባለው አቅም ልክ መሥራት እንዲችል ዕድል የሚፈጥር፣ ተቋማዊ ባህልን መፍጠር የቻለ ሰው ነው ። እያደረ ሁሉ የሚሠራ ባለሙያ ነው። የሥራ ቦታው ቢሮው ብቻ አልነበረም፤ ተቋማዊ የእኔነት ስሜትን በመፍጠር የማይናጋ መሠረት የጣለውም በዚሁ ምክንያት ነው። የሰብአዊነት ስብእናውም ላቅ ያለ ነው። ፋና ሲመሰረት 24 ሰዓት የሚያሰራን ሰው ነው። ፋና የሚለውን ስም ሳወጣ ወዲያው ነው የቀለባት “እኔ እንኳን አላሰብኩትም” በሚል ነበር የተቀበለኝ። እድል ይሰጣል እንድንፈጥር እንድናቅድ በእኔነት አቅማችንን እንድናወጣ ያደረገን ነው ሙሉጌታ። ወግ አጥባቂ ሰው ሳይሆን በተሳሳተ መንገድ ሰዎች የሚረዱት ነበሩ።

እንደ ወዳጅ የምናየው ሙልጌታ፣በአለቃነቱ አብረውት የሚሠሩትን ያደንቃል ያበረታታል። በአጠገቡ ሆነው በአመለካከትም ሆነ በቅናት ለውድቀቱ የማይመለሱለት ሰዎች መኖራቸውን እያወቀም ቢሆን አብሮ የመኖር አቅም የነበረው ሰው መሆኑን አደንቃለሁ። እኔ በግሌ ከእርሱ ብዙ ተምሬያለሁ “ሰውን በአዎንታዊነት አሳትፈው” የሚለውን የሥራ መርሁን አደንቅለታለሁ ተምሬበታለሁም። ሙልጌታ በባህሪውም አዎንታዊ ነው።የሰዎችን ተሰጥዖ ማውጣትን ያውቅበታል፡፡የኢትዮጵያ ሚድያ ካጣቻቸው ሰዎች አንዱ ሙልጌታ ገሠሠ ነው፡፡ ብዙ መሥራት ሲችል ከ 1993ቱ የህወሓት ክፍፍል በኃላ ከሚድያው ዓለም ራቀ፡፡ ለቤተሰቦቹ መፅናናት እመኛለሁ።

ዮሀንስ ገብረ መድህን 

ሙሉጌታ ከበረሀ ሬድዮ ጣቢያው ጀምሮ እስከ ፋና ድረስ አለቃዬ ነበረ። በቀደመው ጊዜ ሙሉጌታ የኢህአዴግ ሬድዮ ውስጥ በ1982 ስገባ ከተቀበሉኝ መካከል አንዱ ነው። ሙሉጌታ በአጋርፋ እርሻ ኮሌጅ ሲሠራ እንደነበር አውቃለሁ።  በመቀሌ ወህኒ ቤት ውስጥ ደግሞ ለእስር ተዳርጎ በአጋዚ ኦፕሬሽን ነበር የተፈታው። ሙሉጌታ ገሰሰ በባህሪው አቀራራቢና ተግባቢ ሰው ነው። ከሚድያ ከወጣ በኋላ በራሱ የሥራ መስመር ውስጥ ገብቶ በንግድና በኢንደስትሪ ትርኢቶችን በኤግዝቢሽን ያካሂድ ነበር።

ኦሀድ ቤንያሚን

ሙሉጌታን የማውቀው በ1988 ዓ.ም ሰላምና መቻቻል ኮንፍረንስ ሬድዮ ፋና ሲያዘጋጅ ነበር። በጣም ተግባቢ ቀጥተኛና ቀለል ያለ ስብዕና ያለው ሰው ነው። ፋና ስገባ ከእርሱ ጋር ተነጋግሬና ተደራድሬ ነው የገባሁት።እንደመሪ ከፍተኛ የስሜት ብልህነት ያለው፣ ጥሩ ልብ ያለው ሰው በመሆኑ በቁጣ እንኳን ቢናገረን የማንከፋበት፣ የማይታለፍ መስመር ያለው ብሎም በውሳኔ ሰጪነቱ የሚመሰከርለት መሪ ነው። ያኔ ፋና ሲመሰረት ሲቪሉንና ታጋዩ ሰውን በጋራ አዋህዶ በአንድ አይነት ባህል ሚዛን አስጠብቆ የቆየ ፣ ፋናን ማቆም የቻለ ጎበዝ መሪ ነበር።

ሙልጌታ፣ በእውቀቱ በከተሜነት አስተሳሰቡ ነገሮችን የሚረዳበት መንገድና ፕሮፌሽናልን በማስቀደም ወደ ኋላ የሚሉትን በመግራት የሚታወቅ መሪ ነው። ሙሉጌታ ቢጋጭም እንኳን ማንም ቂም አይዝበትም ምክንያቱም ቁጣው ማንነትን መሰረት ያደረገ ሳይሆን ሥራው ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ የሚሰጠው ትችት በመሆኑ የሚናገረው ሰው ራሱ የሙሉጌታ ንግግር ምክንያታዊ መሆኑን ስለሚረዳ ቅሬታ በመሀል ሳይፈጠር ነበር ሥራው የሚሠራው። ሙሉጌታ እጅግ በሳል ሰው ነው። ከማንኛውም ሰው ጋር ሚዛኑን ጠብቆ መኖር የሚችል ነው። 

ሙሉጌታ ከባለቤቱ አኸዛ የሦስት ልጆች አባት ሲሆን ‘ሚዘር’ የተባለችው የመጀመሪያ ልጁ በሚወደው በቀደምት የህወሀት ታጋይ ስም ነው የሰየማት።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *