የመጀመሪያው የፋና ሥራ አስኪያጅ የኣቶ ሙልጌታ ገሰሰ የሕይወት ታሪክ 

ክፍል 1

ኣቶ ሙልጌታ ገሰሰ ኣብርሃ ታህሳስ 08/1951 ዓ/ም ከኣባታቸው ኣቶ ገሰሰ ኣብርሃ ከወላጅ እናታቸው ወይዘሮ መብራት ገብረማርያም በኩሃ ከተማ ተወለዱ ። የኣንደኛ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኩሃ ከተማ ተምረዋል ። ከ 1966 እሰከ 1969 ዓ/ም በመቐለ ሃፀይ ዮሃንስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ተከታትለው ፈፅመዋል።

ከ1968 እሰከ 1970 ዓ/ም በከተማ ህዋስ የህዋህት ኣባል ሆነው ታግለዋል ገና በወጣትነት ዘመናቸው ትግሉን የተቀላቀሉት ኣቶ ሙልጌታ ህይወትን በሚበላ ፈታኝ ሕቡእ ትግል ውስጥ ተደራጅተው በእሳት ተፈትነዋል ።

በ 1970 ዓ.ም በደርግ በተካሄደው የቀይ ሽብር ዘመቻ ታስረው ከፍተኛ ስቃዮችን በፅናት ኣሳልፈዋል ።

ከእስር ቤት እንደወጡ የኮሌጅ ትምህርታቸውን ተከታትለው ከጨረሱ በኃላ በኣጋርፋ  የእርሻ ማሰልጠኛ ማእከል ተከታትለው የእርሻ ባለሞያ ሆነው ለኣገራቸው ኣገልግለዋል። በስራ ላይ እያሉ ኣሁንም ዳግማይ በደርግ ስርኣት በ1976 ዓ/ም በኣዲስ ኣበባ እና መቐለ ለእስር ተዳርገው ከቆዩ በሓላ በ 1978 ዓ/ም በኣግኣዚ ኦፕሬሽን የእስር ቤቱን ሰንሰለት ሰብረው ነፃነታቸውን ተጎናፅፈዋል ። በመቀጠልም፣ የደርግን ሥርኣት ለመደምሰስ በተካሄደው የትጥቅ ትግል ውስጥ ተሳትፈው በከፍተኛ ጅግንነት እና ፅናት ህዝባዊ ግዴታቸውን ተወጥተዋል።

በትጥቅ ትግሉ ውስጥ በተሰለፉበት ወቅት የኣግኣዚ ስልጠናቸውን ጨርሰው ከተመረቁ በሓላ በ 1979 ዓ/ም በፕሮፖጋንዳ መእከል የጥናት እና ትርጉም ክፍል ተመድበው የተለያዩ ሳይንሳዊ መፅሃፍቶችን ከእንግሊዘኛ ወደ ትግርኛ እና ኣማርኛ በመተርጎም ስራ ላይ ተሰማርተው ግዳቻቸውን ተወጥተዋል ። ከዚሁ በተጨማሪ በኣማርኛ እና ትግርኛ በሚዘጋጁ ጋዜጦች ወይን እና የካቲት ኣዘጋጅ ሆነው ትምህርትን ኣሰንቀዋል።

በስነ ጥበባዊ ስራቸው የላቀ ክህሎት ያላቸው ታጋይ ሙሉጌታ ገሰሰ ኣጫጭር ልበወለዶች ግጥሞች ሃተታዎች ትንታኔዎችን በመፃፍ የሰላ የታጋይ ብእራቸውን በማሳረፍ የታወቁ ነበሩ። ከዚሁ በተጨማሪ የሩስያ መሳጭ ኣጫጭር ልበወለዶችን ከእንግሊዘኛ ወደ ኣማርኛ በመተርጎም የትግሉ ጋዜጦች በይበልጥ ተወዳጆች ሆነው እንዲነበቡ ብርቱ ጥረት ካደረጉ ታጋዮች ግንባር ቀደም ሆነው የሚታወሱ ናቸው ።

ታጋይ ሙልጌታ ገሰሰ በጥናት እና ትርጉም ማእከል ሆነው በተለያዩ ስልጠናዎች በ ስነ ሃሳብ እና ጋዜጠኝነት ተሳትፈው በፖለቲካ ብቃታቸው በቆራጥነታቸው በሰላ የጥበብ ብእራቸው እና በብርቱ ኣንደበታቸው እና ድምፃቸው ተመርጠው በድምፅ ወያነ ሬድዮ በዋና ኣዘጋጅነት ለኣማርኛ ፕሮግራም ተመርጠዋል ታጋይ ሙሉጌታ ገሰሰ በወርቃዊ ግዚያቸው የድምፅ ወያነ ጋዜጠኛ በመሆን ከሳቸው የሚጠበቀውን የላቀ ታጋይ በመሀን የጋዜጠኝነትን ሞያ በትግሉ ውስጥ ከፍተኛ ስራቸውን ኣበርክተዋል ።

ከ 1980 እሰከ 1983 ዓ/ም በነበረው ብርቱ ትግል ፕሮፖጋንዳን መርተው የመሪ ሚናቸውን የተጫወቱት ታጋይ ሙሉጌታ የድምፅ ወያነ ፕሮግራሞች እሳቸው በፃፍዋቸው ሃተታዎች ልብወለዶች የሬዲዮ ድራማዎች ግጥሞች እና ቃለ መጠይቆችን ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገሩ አድረገዋል። ከንባብ ተለይተው የማያውቁ ታጋይ ሙሉጌታ የላቀ ፖለቲካዊ ብስለት ያላቸው እና የትግል መድረክ ውይይቶች በሳቸው በሳል ተሳትፎ የመተንተን ብቃት እና ተከራክሮ የማሳመን ኣቅም የሁልግዜ ደማቅ ስራዎቻቸው ናቸው።

ደፋር የላቀ በራስ መተማመን ኣቅም ያላቸው ለሚያምኑባቸው ኣመለካከቶች በግልፅ የሚያራምዱ ወደ ሓላ የማይሉ ተጋይ ሙሉጌታ በክርክር ወቅት የሚያነስዋቸው ነጥቦች በሳል እና ጥልቀት የተሞላባቸው እንዲሁም ልዩ ትኩረት የሚቸራቸው ናቸው።

የትጥቅ ትግል ኣብቅቶ በድል ኣዲስ ኣበባ ከተገባ በሓላ በኢትዮጽያ ሬዲዮ በዋና ስራ ኣስኪያጅነት ሆነው ሰርተዋል ። ቀጥለወም መስራች ኣርማ ሆነው እና ኣደራጅተው ላበቁት ሬድዮ ፋና ተመድበው ዋና ስራ ኣስኪያጅ ሆነው ኣገልግለዋል ።

የሬድዮ ፋና ድል  መስራቹ እና መሪው ሙልጌታ ገሰሰ ፈፅመው የማይለያዩ መሆናቸው ታሪክ ያወሳዋል ።በዘመናዊ የሬድዮ ድርጅት ግንባታ በኩልም ታጋይ ሙሉጌታ ስማቸው በወርቃዊ ቀለም ተፅፎ እንዲኖር ያደረጉ ናቸው። የሬዲዮ ፋና ዜናዎች ፕሮግራሞች የሰነጥበባት ስራዎች ወደ ላቀ ደረጃ መሸጋገራቸው ተከትሎ የታጋይ ሙሉጌታ ገሰሰ ስም በርቶ እና ደምቆ የሚታይ ነው።

የሬድዮ ጋዜጠኝነት የምትሰማው ብቻ ሳይሆን የምትሳተፍበት እንዲሆን የሰሩ ታጋይ ሙልጌታ ተሳታፊዎች በቀጥታ በስልክ እንዲሳተፉ በመጋበዝ  ሬዲዮን ወደ ህዝባዊ መስተጋብርነት የቀየሩ ታላቅ መሪ እና የህዝብ ልጅ ናቸው።

ኤች አይ ቪ ኤድስ ሕቡእ ሚስጢራዊ እና ልትናገረው ነውር እና ፅያፍ በነበረበት ወቅት ታጋይ ሙሉጌታ ባስጀመሩት የለውጥ ማእበል በቫይረሱ የተያዙ ወገኖችን ኣፍ ኣውጥተው ስለበሽታው ኣስከፊነት በድፍረት እንዲናገሩ እንዲያስተምሩ ድምፃቸው በሬዲዮ እንዲሰማ እና ኣስተምህሮ እንዲሰጡ ቀዋሚ የሬዲዮ ፕሮግራም እንዲኖራቸው ብርቱ ጥረትን ኣድርገዋል ።

ከ 1984 እሰከ 1992 ዓ/ም ሬዲዮ ፋናን በሃለፍነት የመሩት ኣቶ ሙልጌታ ለኣጭር ግዚያት የሜጋ ማከፋፈያ እና ህትመት ድርጅት ዋና ስራ ኣስኪያጅ ሆነው በመስራት ላይ እንዳሉ በህዋሕት ኣመራር ውስጥ በተፈጠረ መከፋፈል ምክንያት ስራቸውን በፍቃዳቸው ለመልቀቅ ተገደዋል  ።  ከዝያም በሓላ በኮንስትራክሽን ማህበር ዘርፍ ማህበር ውስጥ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው ሰርተዋል  ።  

በቢዝነስ ኣድሚኒስትሬሽን ትምህርታቸውን ተከታትለው ከሃገረ እንግሊዝ የማስተርስ ድግሪያቸውን ወስደዋል ።  ገና ለህትመት ያልበቁ በርካታ ግጥሞች እና ልበወለዶችን የደረሱት ታጋይ ሙሉጌታ በበርካታ የስነ ፅሑፎች መድረክ በቀጣይነት ሲሳተፉ ቆይተዋል  ።  

የላቀ የኮሚኒኬሽን ችሎታ የእንግሊዘኛ፣ ኣማርኛ ፣ትግርኛ ቋንቋ ርትኡ ኣንደበት የነበራቸው፣ሰብኣዊ፣ህዝባዊ እና ርሁሩሁ የሆኑት ኣቶ ሙልጌታ የላቀ ተወዳጅነትን የተላበሱ ኣክብሮትን የተጎናፀፉ ውድ የህዝብ ልጅ ነበሩ።

ከባለቤታቸው ታጋይ ኣኸዛ ኣለነ ኣንድ ሴት ልጅ እና ሁለት ወንድ ልጆችን ኣፍርተዋል ።ታጋይ ሙሉጌታ ገሰሰ ባደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ከቆዩ በሓላ ሃምሌ 25/2017/ዓ/ም በ 63 ኣመታቸው ከዚህ ኣለም ድካም ኣርፈዋል ።

ፅናት ለባለቤታቸው እና ለልጆቻቸው ፣

ፅናት ለወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው ለመላው ቤተሰቦቻቸው ለታጋይ ጉዶቻቸው፣ ጉደኞቻቸው እና ወዳጆቻቸው።

እግዚኣብሄር ኣምላክ ነፍሳቸውን  በኣፀደ ገነት ያንሩልን።

የሕይወት ታሪክ አዘጋጆች ፡

ቤርሳቤህ ጌቴ 

አሰፋ በቀለ 

ዕዝራ እጅጉ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *