አረፈ ዓይኔ ሐጐስ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በመገናኛ ብዙሀን ዘርፍ አስተዋጽኦ ያላቸው እና የነበራቸውን ሰዎች የህይወት ታሪክ እየሰነደ ለምርምር ግብአት እንዲሆን እያደረገ ይገኛል፡፡ በሀምሌ 30 2015 ዓ.ም የ180 የሚድያ ሰዎችን የህይወት ታሪክ ‹‹መዝገበ-አእምሮ›› በተሰኘው ሰነድ ጽፎ ማስቀመጡ ይታወሳል፡፡ አሁን ደግሞ በ2ኛው ቅጽ በሚድያው ዘርፍ የተመሰከረላቸው ሰዎችን እያፈላለገ በተወዳጅ ሚድያ ማህበራዊ ሚድያ ላይ እየሰነደ ይገኛል፡፡ አሁን በዚህ ጽሁፍ የህይወት ታሪኩን የምናይለት ሰው አረፈ ዓይኔ ሐጎስ ይባላል፡፡ በህትመት ሚድያው ዘርፍ ባለፉት 40 አመታት የራሱን ጉልህ አሻራ ያኖረ ነው፡፡ ለህትመት ያበቃቸው መጽሀፎችም አሉት፡፡ ከባለታሪኩ ያገኘውን ታሪክ እዝራ እጅጉ እንደሚከተለው ሰንዶታል፡፡
የስለት ልጅ
የስለት ልጅ ነው። ጉራ ሲያምረው ታዲያ እንደናንተ በአጋጣሚ ሳይሆን ተለምኜ ነው ወደዚህ ዓለም የመጣሁት ይላል፡፡ የተወለደው ሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት ጉርሱም በሚባል ስፍራ ነበር፡፡ ወላጆቹ ከተጋቡ ከአስራ አንድ አመታት በኋላ ጥቅምት 4፣ 1947 ዓ᎐ም የተወለደውን ህፃንም የሴት አያቱ አረፈዓይኔ የሚል ስም አወጡለት፤ የሌሎችን ልጆች ሲያይ ይንከራተት የነበረው ዓይኔ አረፈ ለማለት ነው፡፡ እርሱ መንገዱን ከቀደደው በኋላ ግን በተከታታይ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ስለተወለዱ የተለየ እንክብካቤ ሳይደረግለት እንደማንኛውም ልጅ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በአፍደም፣ ቀጥሎም በድሬዳዋ፤ ከዚያም አምቦ ተከታትሎ ዩኒቨርሲቲ ገባ፡፡ አገራችንን እስካሁን የሚንጣት ፖለቲካ እያጎሸ የነበረበት ወቅት በመሆኑ እንደነገሩ የአንደኛ አመት ትምህርቱን በተፈጥሮ ሳይንስ መስክ ተከታትሎ በቀጣይ ለመማር የሚፈልገውን ትምህርት ለመምረጥ ተንቀሳቀሰ፡፡ ህልሙ ጋዜጠኛ መሆን ነበር፡፡ ሆኖም በወቅቱ ይህ የትምህርት መስክ በዩኒቨርሲቲው ባለመኖሩ የፍሬሽማን ዲን የነበሩት ጄ.ቢ.ማርሻል ተቀራራቢነት ያለውን የውጭ ቋንቋዎችና ሥነ ፅሁፍ እንዲያጠና መከሩት፡፡ ጓደኞቹ ግን ከተፈጥሮ ሳይንስ ወደ ማኅበራዊው ያደረገውን ለውጥ ተሳለቁበት፡፡ ያም ሆነ ይህ ተማሪው የውጭ ቋንቋዎችና ሥነ ፅሁፍ እና ፍልስፍናን ለመማር ተመዝግቦ ትምህርት ከመጀመሩ የአገሪቱ የፖለቲካ ትኩሳት በመጨመሩና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አድማ በመቀስቀሱ እርሱም ከአድማው ተቀላቅሎ በዚያው እንደወጣ ቀረ፡፡ ትምህርት የለ ፤ሥራ የለ፡፡
በ22 አመቱ ኢቲቪ
ዳሩ ግን በዚያ መሐል ማስታወቂያና መርሐ ብሄር ሚኒስቴር ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያ አወጣ፡፡ በተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት አስራ ሁለተኛ ክፍልን ያጠናቀቁና በተወሰኑ ትምህርቶች ጥሩ ውጤት ያላቸውን በረዳት ፊልም አንሺነት ለመቅጠር ነበር የተፈለገው፡፡ የጭንቅ ጊዜ ስለነበር በርካታ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ተመዝግበው አራት ሰዎች ተመረጡ፡፡ ከነርሱ አንዱ አረፈ ዓይኔ ነበር፡፡ እናም ግንቦት፣ 1969 ዓ᎐ም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መምሪያ ተቀጠረ፡፡ ሥራው ረዳት ፊልም አንሺነት ነበር፡፡ ቤት ውስጥ ምሥል በሚቀርፁበት ጊዜ ለፊልም አንሺው በሚመች መንገድ መብራት መያዝና በተጨማሪም የተቀረፀውን ፊልም በፈረቃ ማጠብ ነበር፡፡ ደመወዙ 182 ብር ሲሆን፣ ተጣርቶ ከ140 በላይ ይደርሰዋል፡፡ ዋናው ነገር ግን ጋዜጠኛ የመሆን ህልሙ ጭላንጭል ከሩቁ ይታየው ጀምሯል፡፡
በመሆኑም የደመወዙን ግማሽ እየከፈለ በርቀት ትምህርት ከእንግሊዝ ሀገር የጋዜጠኝነት ትምህርት ተከታትሎ ዲፕሎማ አገኘ፡፡ በቀጣዩ የትምህርት ዘመን ደግሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛ ተማሪነት ተመዝግቦ ትምህርት ጀመረ፡፡ ዳሩ ግን ወደ በኋላው በእድሜ የገፉት ፊልም አንሺዎች አንዳችም ጉዳት የማያስከትልባቸው ቢሆንም ከሰሱት፤ ቋሚ የመንግስት ሰራተኛ ሆኖ ሳለ መደበኛ ትምህርት ይከታተላል በማለት፡፡ የምናውቃት ያቺ ችግር (ምቀኝነት) ተቀስቅሳባቸው ይሆናል፡፡ ቢሆንም ክፉዎች ባሉበት ሁሉ ደጐች ስለማይጠፉ የቅርብ ሃላፊው የነበሩት አቶ ዳኜ እምቢ አለ እና የበላይ ሃላፊው አቶ አብዱ ሙዘይን ኦዳ ሥራውን በትጋትና በጥራት ከሚሠሩት ጥቂት ሠራተኞች አንዱ መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ መማሩ የሚያስከትለው ጉዳት ስላልታያቸው መማሩን የማያውቁ በመምሰል ትምህርቱን እንዲገፋበት አበረታቱት፡፡ ከዚያም ተመረቀ፡፡
ወደ ፕሬስ መምሪያ
ፍላጎቱ በዚያው በቴሌቪዥን መምሪያ ፕሮግራም ክፍል መሥራት ነበር፡፡ ሆኖም ለፕሮግራም የሚሆን ፅሁፍ (ስክሪፕት) እንዲያቀርብ ጠይቀውት ተቀባይነት ቢያገኝም እንኳን በጀት የሌለ በመሆኑ ወደ ሌላ መምሪያ ለመቀየር ፈቃደኛ መሆኑን ተጠየቀ፡፡ ፕሬስ መምሪያ ሲሄድ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ፅሁፎች እንዲያዘጋጅ ተደርጐ በመጨረሻ በ1974 ዓ᎐ም በእንግሊዝኛው ጋዜጣ “ ኢትዮፕያን ሄራልድ“ ዝግጅት ክፍል እንዲሰራ ተመደበ፡፡
ከዚያማ ለእንግሊዝኛው ጋዜጣ ብቻ ሳይሆን በራሱ ተነሳሽነት ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እና ለዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ፅሁፎችን ማቅረብ ጀመረ፡፡ ብዙም ሳይቆይ የእንግሊዝኛው ጋዜጣ ለባህል ገፁ (cultural Front) አዘጋጅ ይፈልግ ስለነበር ከሥነ ፅሁፍ ተማሪነቱ በስተቀር ልምድ ባይኖረውም እድል ተሰጠው፡፡ እልል በቅምጤ ሆነ፡፡ ጋዜጠኛው አምዱን ከማዘጋጀትም አልፎ ሥነ ጥበብና ባህል ነክ ጉዳዮችን ለአማርኛ ጋዜጦች ማቅረብ፣ ለዝግጅት ክፍሉም “ስፖት ላይት“ እና “ፕሮፋይል“ በሚል ይወጡ ለነበሩት አምዶች በተከታታይ ፅሁፍ ማቅረቡን ተያያዘው፡፡
የሚያቀርባቸው ፅሁፎች ተነባቢነትን በማግኘታቸው የሚሠራው በከፍተኛ ሞራል ነበር፡፡ በዚህ ሂደት ቁም ነገርን እና ቀልድን በማሰናሰል የሚቀርቡ ፅሁፎችን ተነባቢነት በመገንዘቡም የአዲስ ዘመን ጋዜጣ አዘጋጅ ወደ ነበሩት አቶ መርእድ በቀለ በመቅረብ “ቅምሻ“ የሚል ሣምንታዊ አምድ መጀመር እንዲፈቀድለት ጠየቀ፡፡ ከጎኑ መሆናቸውን ገለፁለት፡፡ አምዱ የአንባብያንን ተሳትፎ የሚጋብዝ ስለነበር ተወዳጅ ሆነ፡፡ እነዚህን ተደራራቢ ሥራዎች በፈቃደኝነት ቢሠራም ዋነኛ ሥራዎቹ የእንግሊዝኛው የባህል ገፅ፣ “ስፖት ላይት“ እና “ፕሮፋይል“ ነበሩ፡፡ በነዚያ አምዶች አማካይነት ስለ አገሪቱ ታዋቂ የጥበብ ሰዎችና ጉዳዮች የመፃፍ፣ የመተዋወቅና አልፎ ተርፎም አብሮ የመብላትና የመጠጣት እድልን ማግኘት ቻለ፡፡ ከአገር ውስጥ ጸጋዬ ገብረ መድህንን፣መንግስቱ ለማን ፣አፈወርቅ ተክሌን ፤ባጭሩ ከፖለቲከኞች በስተቀር ያገሪቱና ታዋቂ ሰዎች በሙሉ ማለት በሚቻል መልኩ፤ ከውጪ ታሪክ አዋቂው ፕሮፌሰር ኤርሊክ ሀጋይን፣ሉሲን ያገኘው ዶናልድ ጆሀንሰን እና ሌሎችንም ለጊዜው የዘነጋቸውን የማወቅ አጋጣሚ ስለተፈጠረለትም ብዙ ነገሮችን ማወቅ ቻለ፡፡ ሆኖም ግጭቶችና አለመግባባቶች ይፈጠሩ ነበር፡፡ ከነዚያ አንዱ የሚከተለው ነበር፡፡
“ጥርሳም…”
ረቡዕ ተስአት በኋላ ነበር፡፡ የጋዜጠኛው አምድ ወጥቶ ለቀጣዩ ዝግጅት የሚሆነውን እቅድ እያሰላሰለ ቡና በመጠጣት ላይ ሳለ ተላላኪዋ መምሪያ ሃላፊው (የአለቃው አለቃ) ቢሮ በአስቸኳይ እንደሚፈለግ ነገረችው፡፡ ቡናውን ባንድ ትንፋሽ ጨልጦ ሄደ፡፡ እንደደረሰ ፀሃፊዋን የተፈለገበትን ምክንያት ቢጠይቃት እንደማታውቅና ውስጥ ያሉት እንግዳ ግን አቶ ጸጋዬ ገብረ መድህን መሆናቸውን ነገረችው፡፡ ደስ ብሎት እየሳቀ ገባ፡፡ “ጥርሳም!“አሉ ጸጋዬ በቁጣ፤ መምሪያ ሃላፊው አቶ ጎሹ ሞገስ “ተቀመጥ፣ምንድነው የፃፍከው? “ አሉ በመቀጠል፡፡ ትውስ አለው፡፡ “መትፋት ያስነውራል!“የሚለው ግጥም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ራስ መኮንን አዳራሽ ተነቦ ነበር፡፡ ግጥሙ ውብ የነበረና በተፈሪ ዓለሙ አስገምጋሚ ድምፅ በተነበበም ጊዜም ክፍሉን የኤሌክትሪክ ሞገድ የመታው ይመስል ልዩ ስሜትን (ንዝረት) ፈጥሮ እንደነበር መፃፉንና ነገር ግን የራሳቸውን ፈጠራ ለማቅረብ ለሚውተረተሩ ተማሪ ታዳሚዎች ያንን ግጥም ማቅረብ ያሸማቅቃል የሚል ስጋት እንደተፈጠረበት ገልፆ መፃፉን ተናገረ፡፡ በርግጥ ገጣሚው በወቅቱ ገጣሚ ነን ባይ ካድሬዎች ይፈጽሙ የነበረውን ነውር (“መትፋት”) መገሰጻቸው ነበር፡፡ እውነት አላቸው፡፡ የጋዜጠኛው ስጋት ግን ታዳሚያቸውን አላገናዘቡም የሚል ብቻ ነበር፡፡ ጸጋዬ ለተናገረው ምላሽ ባይሰጡም በግልምጫ ከአፈር እየደባለቁት ነበር፡፡ አቶ ጎሹ “በል ሂድ አሁን፤ሰኞ ስምንት ሰአት ትመጣለህ“ በማለት አሰናበቱት፡፡
“ጥርሳም” መባሉ ሲከነክነው የከረመው አረፈ ዓይኔ በቀጠሮው ቀን እንደገባ “እርስዎ፣ ጥርሳም የሚሉኝ እኔ ከእርስዎ ጋር የቁንጅና ውድድር ልገጥም አልመጣሁ!“አለ፡፡ አልመለሱለትም፡፡ መምሪያ ሃላፊው “ጓድ ፀጋዬን የፕሮፋይል ገፅህ እንግዳ ታደርጋቸዋለህ!“ አሉት፡፡ ደስ አለው፡፡ በቀላሉ የማያገኛቸውን እንግዳ “እንዲክስ“ እየነገሩት ነው፡፡ “እሺ“ ብሎ ሳቀ፡፡ ጸጋዬ ቢያዩትም “ጥርሳም“ አላሉትም፡፡ ከዚያን ወዲህ ግን የሁለቱ ፍቅር ለየት ያለ ነበር፡፡ ሲያገኙት እጁን ይዘው ነጠል በማድረግ ያዋዩታል፤ ከማያውቁት ሰዎች ጋር “እቺን በደንብ እወቃት ፣እሺ!?“ በማለት ያስተዋውቁታል፤ወዘተ፡፡
በዚህ መልኩ ስለ ታላላቅ የአገሪቱና የውጭ አገር ሰዎች ሲፅፍ፣ ከነርሱ ሲማር እና የአምዶቹንም ብዛት በማበራከት እነ “ጀስት ኤ ፊው ፖይንትስ“ እና “ሰንዴይ ሰፕሊመንት“(ከኤፍሬም እንዳለ ጋር) ሲሠራ ቆየ፡፡ በዚያን ወቅት ከጋዜጠኝነቱ በተጨማሪ መጽሐፍት የማውጣት ፍላጎት ስለ ነበረው አራት መጽሐፎችን ለንባብ አብቅቶ ነበር፡፡ እነርሱም “ቀልዶች ከጋብሮቮ ምድር“፤ “አለቃ ገብርሐና እና አስቂኝ ቀልዶቻቸው“፤ “እሷና እሱ“፤ እና “እንዲህ ሆነላችሁ“ ነበሩ፡፡ ከነጋዴዎች ጋር በሽርክና መጽሐፍትን በግል በማሳተም ሥራ በፈር ቀዳጅነት ካስተዋወቀ ወዲህም የብዙ ደራስያንና ተርጓሚዎች ሥራዎች ለአደባባይ መብቃት ችለዋል፡፡ ነገር ግን ገንዘብ ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ ምክንያቱም የመጽሐፍ ነጋዴዎች አጭበርባሪዎች ናቸው፡፡
የመንግስት ለውጥ
በ1983 ዓ᎐ም መገባደጃ ላይ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለ ማርያም አገር ጥለው ስለጠፉ የአማፅያኑ ቡድን አገሪቱን ተቆጣጠረ፡፡ ከፕሬስ መምሪያ “የኢሠፓና የደህንነት ቀንደኛ አባሎችና የሥነ ምግባር ጉድለት አለባቸው“ የተባሉ ጋዜጠኞችና ሹፌሮች ሳይቀሩ ተባረሩ፡፡ ከእነርሱም መካከል የመምሪያ ሃላፊው አቶ ሙሉጌታ ሉሌ አንዱ ነበሩ፡፡ በቦታቸው ወጣቱ ታጋይ ተስፋዬ ገብረ አብ ተሾመ፡፡ እርሱም አረፈ ዓይኔን ቢሮው አስጠርቶ መፅሄት የመጀመር ሃሳብ ስላለ ታግዘናለህ አለው፡፡ በዚያ መሠረት “እፎይታ“ መፅሄት ሲጀመር፣ በጋዜጣ ሥራው ላይ ደርቦ የመፅሄቷ ዋና አዘጋጅ ሆነ፡፡
የመምሪያ ሃላፊው ከወራት በኋላ እንደገና አስጠርቶ የክልል 14 ማስታወቂያ ቢሮን ለማቋቋም ወደዚያ እንዲቀየር መወሰኑን ገለፀለት፡፡ ከጋዜጠኝነት ሙያው መለየትን ፈፅሞ አስቦ የማያውቀው ጋዜጠኛ ግራ እንደተጋባ ፈቃደኛ ባይሆን ምን ሊፈጠር እንደሚችል ጠየቀ፡፡ “ልትታሰር ትችላለህ“ የሚል አጭር መልስ ተሰጠው፡፡ ጥቅምት፣ 1985 ዓ᎐ም የዝውውር ደብዳቤ እንደደረሰው ከአራት የተለያዩ የማስታወቂያና መርሐ ብሄር ሚኒስቴር መምሪያዎች ከተመደቡ ባልደረቦቹ ጋር ወደ ማዘጋጃ ቤት ሄደ፡፡ ቢሮ የለም፡፡ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው ቢሮ እየተሰበሰቡ እንዲሠሩ ታዘዙ፡፡ አስቸጋሪ ሥራ ነበር፡፡ በዚያ ላይ በተደራቢ የመፅሄት ዝግጅት ሥራውን ቀጥሏል፡፡ ቢሮ የማቋቋሙን አስተባባሪነት ሥራ ጨርሶ መፅሄትና ጋዜጣ መውጣት እንደጀመረ ግን “እፎይታ” ወቅቱን ጠብቃ እየወጣች ስላልሆነ ወደዚያ ተዛውሮ እንዲሠራ ታዘዘ፡፡ ነሐሴ 10፣ 1986 ዓ᎐ም እየከፋው ቋሚ የመንግስት ሥራውን ለቆ የ”ግል” ወደነበረው ፋና ዴሞክራሲ ድርጅት ተቀየረ፡፡ ሆኖም ድርጅቱ ሲጠናከር ወደ መንግስት ሥራው መመለስ እንደሚፈልግ ገልፆና ቃል ተገብቶለት ስለነበር፤ እንዲሁም በፋና ዴሞክራሲም የእፎይታና በተጨማሪም ሣምንታዊ ጋዜጣ ተጀምሮ ሥራው መልክ እየያዘ ሲመጣ ጥያቄውን አነሳ፡፡
ከጥቂት ማንገራገር በኋላ የካቲት 1፣ 1989 ዓ᎐ም የቀድሞው ማስ ሚዲያ ማዕከል ተመደበ፡፡ በዚያ በጊዜያዊ ተቀጣሪነት (በፍሪላንስነት) የአካዳሚክ ዘርፉን እንዲያስተባብር ነበር የተመደበው፡፡ ነገር ግን የመምህር እጥረት አለ በመባሉ ደርቦ እንዲሠራ ተደረገ፡፡ በተቋሙ በነበረው ቆይታም የጋዜጠኝነት ትምህርትን የማስተማር እድል በማግኘቱ ነቢበ ቃላትን ከተግባር እያጣጣመ እውቀቱን ማካፈል ችሏል፡፡ በዚያ አጭር ቆይታውም እስከ ዛሬ ድረስ ማስተማሩን እንዲገፋበት የሚጐተጉቱት ጠንካራ ጋዜጠኛ ተማሪዎችን አፍርቷል፡፡
ጦርነት
ኢሕአዴግ በሥልጣን ላይ አሥር አመት እንኳን ሳይቆይ ጦርነት ተቀሰቀሰ፤ከኤርትራ ጋር፡፡ ሐረርጌ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ ከሶማሊያ ጋር ለሚደረገው ጦርነት ታንክ በባቡር ተጭኖ ሲጓጓዝ ላየውና የወረዳ ፖሊስ አዛዥ የነበሩት አባቱም በየጊዜው በአፋርና በኢሳ ጎሳዎች መካከል ግጭት ሲፈጠር ተወርዋሪ ጦር በመሆን ይንቀሳቀሱ ስለነበር ጦርነት አዲስ ጉዳይ ባይሆንበትም እጅግ በጣም የሚጠላው ነገር በመሆኑ አዘነ፡፡ በግሉ ሊያጋጥመው የሚችለውን ችግር እንኳን ፈፅሞ አላሰበውም፡፡ በርግጥ በህይወት ያልነበሩት አባቱ ሻምበል ሐጐስ ወልደ ጊዮርጊስ በተለምዶ “ስመጥር ሀማሴን“ ከሚባሉት ወገን ነበሩ፡፡ እናቱ ወይዘሮ አለማሽ እምባዬም የጀግናው ዘርአይ ደረስ ባለቤት ነበሩ፡፡ እናላችሁ ሐረርጌ ተወልዶ አሥረኛ ክፍል ሲደርስ አዋሽን የተሻገረው ጋዜጠኛና ደራሲ ከአገር እንዲባረር መወሰኑ ተነገረው፡፡ የቀበሌው ሊቀመንበር የሆኑት ወይዘሮ “ለአገሪቱ ደህንነት ከሚያሰጉ ኤርትራውያን” ጋር እንዲጋዝ ስለተወሰነ ማክሰኞ ለመሄድ እንዲዘጋጅ ቤቱ መልእክት ትተው ነበር፡፡ ከኔ በላይ ኢትዮጵያዊ ላሳር የሚለው ሰውዬ ወደ ማያውቀው አገር ሊጋዝ መሆኑን ሲሰማ እጢው ዱብ አለ፡፡ ለማን አቤት ይበል?
የእፎይታ ሥራ አስኪያጅ እና የርሱን ሃላፊነት በመደረብ ዋና አዘጋጅ ወደ ነበረው ተስፋዬ ገብረ አብ በመሄድ የደረሰበትን ካስረዳው በኋላ፣ የባለስልጣኖቹ ውሳኔ የሚፀናም ከሆነ በራሱ መንገድ ለመሄድ እንጂ ለመጋዝ ፈቃደኛ እንዳልሆነ ባፅንኦት ገለፀ፡፡ ነገር ግን በተደረገው ማጣራት እንዲጋዙ ከተወሰነባቸው ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ስለሌለ ተረጋግቶ ሥራውን እንዲሠራ ተነገረው፡፡ ምናልባት መኖሪያ ቤቱን የፈለጉት የቀበሌዋ ሊቀመንበር ያስተላለፉት ትእዛዝ ሊሆን እንደሚችል ተገምቶ ነበር፡፡
ዳሩ ግን ጉዳዩ በዚህ አልተቋጨም፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ሥራ ቦታው ተመሳሳይ ጥያቄ ተነሳ፡፡ የማስ ሚዲያ ማሰልጠኛው ማዕከል ሃላፊ ከሥራ ከመባረር ለመዳን ከፈለገ የሌላ ዘር ሀረግ ያለበት መሆኑን የሚያመለክት ማስረጃ ቢጤ እንዲያመጣ ጠየቁት፡፡ ሆኖም እውነቱን መናገርን በመምረጡ የውጭ አገር ተወላጆች በመንግስት መሥሪያ ቤት እንዳይሠሩ በተወሰነው መሰረት ከተቋሙ መሰናበቱን የሚገልፅ ደብዳቤ ሚያዝያ 30 ፣ 1991 ዓ᎐ም ደረሰው፡፡ ከሃያ ሁለት ዓመት በላይ መንግሥትንና አገሩን ያገለገለው ጋዜጠኛ እንደ አሮጌ ቁና ሜዳ ላይ ተጣለ፡፡
ይሁንና ክፉ ሰዎች በብዛት ባሉባት አገራችን ደግ ሰዎችም ስለነበሩ እና ስላሉም የዘርፉ የበላይ ሃላፊ የነበሩት አቶ ዓለም ሰገድ ገብረ አምላክ ጋዜጠኛው ጸሀፊም ስለሆነ ሊያግዝ ይችላል በማለት እ᎐ኤ᎐አ ሜይ 24፣ 1999 ዓ᎐ም ሜጋ አሳታሚ ድርጅት እንዲመደብ አደረጉ፡፡ አልከፋውም፡፡ በአሳታሚ ድርጅቱ አድካሚ የሆነውን የአርታኢነት ሥራ ቢሸከምም ብዙ እውቀት ማግኘት ከመቻሉም በተጨማሪ በርካታ ደራሲዎችና ተርጓሚዎችን በማገዝ የተለያዩ መጽሐፍትን ማሳተም እንዲችሉ ማድረግ ችሏል፡፡
አልለቅ ያለ አባዜ
ሆኖም የጋዜጠኝነት አባዜው አልለቅ ስላለው ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማእከል ለእንግሊዝኛ ዴስክ ዋና አዘጋጅ እንደሚፈልግ ማስታወቂያ ባወጣ ጊዜ ተወዳድሮ ጥር 6 ፣ 1996 ዓ᎐ም ወደ ቀድሞ ሙያው ተመለሰ፡፡ በዚያም ያለችውን እውቀት ሲያካፍል ቢቆይም ተጨማሪ ብቃትና ችሎታን ማዳበር የሚያስችል ምህዳር ያለው ሆኖ ስላላገኘው የእንግሊዝኛ ቋንቋ አርትኦትና ጥናታዊ ፅሁፎችን ወደ ማሳተም ሙያ አቀና፡፡ ከዚያን ወዲህ በነበረው ጊዜም ኮድ ኢትዮጵያ የሚባለው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ባቋቋመው የእንግሊዝኛ ልብወለድ መጽሐፍትን ለወጣቶች ለማዘጋጀት በተቋቋመ ኮሚቴ በዳኝነትና በአርታኢነት መሥራት ችሎ ነበር፡፡ በተጨማሪም “የእስያውያን ተአምራዊ ጉዞ“ ፣ “የስኮትላንዳውያን ቀልዶች”፣ “ወርቅ የማፍራት ጥበብ”፣ “ፖለቲከኞች እፈሩ” የተባሉ መጻሕፍትን ለአንባብያን አቅርቧል፡፡
እነሆ አረፈ ዓይኔ ዞሮ ዞሮ በመጨረሻ ወደ ጋዜጠኛነቱ ሙያ ተመልሷል፡፡ በትርፍ ጊዜው በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የውጭ ቋንቋዎች ዳይሬክቶሬት ውስጥ በአርታኢነት በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ እና አሁንም እየተማረ ነው፡፡ ዜግነቱን በተመለከተም በ1990ዎቹ መጨረሻ በሕግ የኢትዮጵያ ዜግነት ተሰጥቶታል፡፡ እንግዲህ ከረጅሙ ባጭሩ፤ ከብዙው በጥቂቱ የጋዜጠኛና ደራሲ አረፈ ዓይኔ ሐጐስ ታሪክ ይህን ይመስላል፡፡
ሆኖም ብዙዎች ጐፈሬ ጸጉሩንና አለባበሱን በማየት የሚያቀርቡለት ጥያቄ አለ ፤ ቤተሰብ መስርተሃል ወይ? የሚል። አዎን፣ አረፈ ዓይኔን ከምንም በላይ የሚያስደስተውና የሚኮራበት ቤተሰብ አለው። ከአርባ ዓመት በፊት ካገባት ባለቤቱና በአሁኑ ሰዓት በኮተቤ ትምሕርት ዩኒቨርሲቲ መምሕርት ከሆነችው እና ቀድሞ የኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት ከነበረችው ባለቤቱ ዶክተር አልማዝ ባራኪ ሦስት ልጆችን አፍርቷል፡፡ ባይወልደውም ያሳደገው አንድ ልጅም አለው፡፡ ይኸው ልጅ በአሁኑ ጊዜ በሕክምና ትምሕርት ስፔሽያሊስት ሆኗል፡፡ ሌላው ወንድ ልጁም በዚሁ የሕክምና ትምሕርት ተመርቆ ስፔሽያሊስት ለመሆን በመማር ላይ ነው፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ ይመረቃል፡፡ ከሴት ልጆቹ አንደኛዋ በሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ትምሕርት የማስተርስ ዲግሪዋን ከሚሺጋን ዩኒቨርሲቲ (አሜሪካ) አግኝታ በዚያው አገር በሙያዋ እየሠራች ትገኛለች፡፡ ሁለተኛ ሴት ልጁ ከፋርማሲ ትምሕርቷ በተጨማሪ በቅርቡ በፐብሊክ ሄልዝ በማስተርስ ዲግሪ ትመረቃለች፡፡ ይህ ቤተሰብ ከሁሉም በላይ በዲሲፕሊን የተቀረፀና የሚፋቀር ነው፡፡ ለአባት ታዲያ ከዚህ በላይየሚያስደስት ምን ነገር አለ?
አረፈ አይኔ በዶክተር ጌታቸው ድንቁ እይታ
ዶክተር ጌታቸው ድንቁ ከ 2 አመት በፊት የብሮድካስት ባለስልጣን ዳይሬክተር የነበሩ ሲሆን በአሁኑ ሰአት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ቤት መምህር በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ዶክተር ጌታቸው ድንቁ 2ኛ ዲግሪውን ይማር በነበረበት ጊዜ የስራ ላይ ልምምድ እንዲያደርግ የተመደበው ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማእከል ነበር፡፡ በ1997 በዋልታ የእንግሊዝኛ ዴስክ ሃላፊ የነበረው ደግሞ አረፈ አይኔ ሀጎስ ነበር፡፡ ታዲያ ዶክተር ጌታቸው የተመደበው በጋዜጠኛ አረፈ አይኔ ስር ነበር፡፡ ዶክተር ያን ዘመን አሁን ሲያስበው ከአረፈ አይኔ ጋር መመደቤ እድለኛ መሆኔን ያሳያል ይላል፡፡ ምክንያቱን ሲገልጽም አረፈ አይኔ ተማሪዎችን በወጉ እውቀት ማስታጠቅ የሚችል ብቁ ሰው ስለነበር ነው፡፡
‹‹ …አረፈ አይኔ ስር ገና ከመመደቤ ልዩ ችሎታውን ማድነቅ ጀመርኩ፡፡ ጽሁፎችን በሰላ መንገድ አርትኦት ሲያደርግ ነፍስ ይዘራባቸዋል፡፡ አንዳንድ ጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ ከጋዜጠኞች ጋር አብሮ ይልከኛል፡፡ እናም ምርጥ ዜና እንዴት እንደሚሰራ በትህትና እና ቀናነት በተሞላበት መልኩ ይነግረኛል፡፡›› በማለት ዶክተር ጌታቸው የአረፍአይኔ ክህሎት ልዩ እንደነበር ያስታውሳል፡፡
አረፈ አይኔ ስራውን መስራት እንጂ ብዙ ለመታየት እና ሰው እንዲያደንቀው የሚጓጓ እንዳልነበር ዶክተር ጌታቸው ይመሰክራል፡፡‹‹…. አረፍ አይኔ ብዙ አይናገርም፡፡ ነገር ግን በደሙ ውስጥ ያለው የጋዜጠኝነትና የስነ-ጽሁፍ ፍቅር ለብዙዎች የሚተርፍ ነበር፡፡ ለእኔም ተረፈ፡፡ እኔ ውጭ ሄጄ ከተማርኩ በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማስተማር ስጀምር አረፈ አይኔን እንደ አርአያ በመቁጠር ስሙን ሰርክ አነሳዋለሁ፡፡ ›› በማለት ዶክተር ጌታቸው ደስ እያለው ስለ ስለ አረፈ አይኔ ይመሰክራል፡፡ አረፈ አይኔ ዶክተር ጌታቸው ድንቁ ዋልታ የስራ ልምምድ ላይ ሳለ ያበረታታው ነበር፡፡ ሄራልድ ላይ ዜና እንዲሰራ ልኮት ነገር ግን ዜናው በጌታቸው ስም እንዲወጣ ያደርጋል፡፡ ይህም አረፈ አይኔ ለወጣቶች የሚሰጠውን ከበሬታ ብሎም ለራሱ ስም ብዙም የማይጓጓ እንደነበር የሚነግረን ሀቅ ነው፡፡
ዶክተር ጌታቸው የአረፈ አይኔ ታሪክ በተወዳጅ ሚድያ አማካይነት መሰራቱ ትልቅ ጀምር እንደሆነ ይናገራል፡፡ እንደ አረፍ አይኔ አይነት ሰዎች ጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት ውስጥ ማስተማር ያለባቸው ናቸው፡፡ በተለያየ ምክንያት ላያስተምሩ ቢችሉ እንኳን ታሪካቸው ለሌሎች መነቃቃት መፍጠሩ እንደማይቀር ዶክተር ጌታቸው ያስረዳሉ፡፡