አለም ብርሃኔ ደስታ
ተወዳጅ ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን በሚዲያው ዘርፍ ጉልህ አሻራ የነበራቸውን ጋዜጠኞች ፤ የሚዲያ ቴክኖሎጂ የቴክኒክ ባለሙያዎች የሚዲያ መምህራን እና የማስታወቂያ ሚኒስቴር የስራ መሪዎች ( ሃላፊዎችን ) እያፈላለገ የህይወት ታሪካቸውንና ተሞክሮዋቸውን እየሰነደ ይገኛል ፡፡ ይህ የተሰነደ ታሪክ መዝገበ- አዕምሮ መጽሀ,ሃፍ ቅጽ 2 ላይ የሚወጣ ሲሆን ቅጽ 1 በመዝገበ አዕምሮ ከፍተኛ ተቀባይነትና አድናቆት ማግኘቱ ይታወቃል ፡፡ አሁን በዚህ መጽሃፍ ታሪኩን ሰንደን የምናቀርብለት ሰው አለም ብርሃኔ ደስታ ይባላል ፡፡
አለም ብርሃኔ ደስታ ከውልደት እስከ ዕድገት ድረስ ያለፈውን ታሪክ አሁን ለደረሰበት ትልቅ ስኬት መሠረት በመሆኑ በህይወት ዘመኑ የበርካታ ታሪክ ባለቤት በመሆኑ በተለይም በሃገራችን ቀዳሚና አንጋፋ ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ ያለው የቀድሞ የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቭዥን ድርጅት አለም ሐምሌ ወር 1993 ዓ.ም በሙያው ተቀላቅሎ ከጀማሪ ቴክኒሽያን እስከ ከፍተኛ ቴክንሽያን በሬድዮ ዘርፍ በቀጥታ ስርጭትና መስክ ቀረጻ ስራ በቴሌቭዥን ዘርፍም በስቱድዮ ሲስተምና ሳተላይት ፤ በጥገና ስራዎችን ጨምሮ በቴክኒክ ሙያ ዘርፍ ለ17 ተከታታይ ዓመታት ከማገልገሉም በላይ የኢቢሲ ታሪካዊ የሚዲያውን ታሪክ የሚዘክሩ የሚዲያ ቴክኖሎጂ ቴክኒክ መሳሪያዎችን ፤ ፎቶግራፍ ዶክመንቶችን በክፍለ ዘመናቸው በዓይነት በማሰባሰብ ፤ በክብር በቅርስነት ተጠብቀው ለትውልድ እንዲቆዩ ለማድረግ በተቋሙ ሙዚየም ከጽንሰ ሃሳቡ ጀምሮ በተግባር ግንባታ ቅርሶችን በማደራጀት ለእይታ በማቅረብ ፤ በተለይም ዓለም አቀፍ የሬድዮ ቀን በየዓመቱ የካቲት 06 ሲከበር እና የኤፍ ኤም አዲስ 97.1 22ኛ ዓመት ሲከበር የጣቢያው ታሪክ በሚዘክር መልኩ ኤግዚቭሽን በማዘጋጀት አለም የአንበሳውን ድርሻ ተወጥቷል ፤ ስለዚህም እንደ አለም ብርሃኔ ዓይነት ብርቱና ታታሪ ሰዎች ያለፉበትን መንገድ ያስተምራል በሚል እሳቤ የህይወት ታሪኩን እዝራ እጅጉ እንደሚከተለው አሰናድቶታል ፡፡
ከልደት እስከ ዕድገት
አለም ከአባቱ ከአቶ ብርሃኔ ደስታ ከእናቱ ወ/ሮ ሄዋን ተድላ የካቲት 25 / 1969 ዓ.ም በቀድሞ ትግራይ ክፍለ ሃገር በምስራቃዊ ዞን ደብረ ዳሞ ገዳም አካባቢ እንትጮ ወረዳ ጉሎ ምካዳ መንደር ተወለደ ፡፡ አለም በተወለደ በሁለት ዓመቱ ከእናቱ ጋር ወደ ኤርትራ ክፍለ ሃገር አስመራ ከተማ በመሄድ ዕድገቱ ገና ሀ ብሎ ጀመረ ፡፡ በመስከረም ወር 1975 ዓ.ም ወደ ትምህርት አለም ተቀላቅሎ አንደኛ ደረጃ ትምህርቱ ከ1ኛ እስከ 2ኛ ክፍል በመምህር ሐዱሽ ት/ቤት እና ከ3ኛ እስከ 6ኛ ክፍል በአግአዚያን አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ፤ ሁለተኛ ደረጃ ከ7ተኛ እስከ 8ተኛ ክፍል ደግሞ በዶግዓሊ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም 9ኛ ክፍል በቀዳማዊ ኃይሌ ስላሴ ( ቀኃስ ) ( ቀይሕ ባሕሪ ) ትምህርት ቤት ተምሯል ፡፡
በወቅቱ በደርግና በሻዕቢያ መካከል ከባድ ጦርነት ስለነበረ ከአስመራ ከተማ በአውሮፕላኝ ከወላጅ እናቱ ጋር ነሐሴ 22 / 1982 ዓ.ም በታላቅ ወንድሙ መልካም ፈቃድ ሁለተኛውን ምዕራፍ ኑሮውን ለመጀመር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከ10ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርቱ በአብዮት ቅርስ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ( ጂስኤ ) ተምሯል ፡፡
ከልጅነት ዕድሜ እስከ ወጣትነት ዕድሜ ድረስም በተለይም የልጅነት ጊዜውን በአስመራ ከተማ ከሰፈር አብሮ አደጎቹ ጋር ድብብቆሽ ፤ መተዛዘል ፤ ቀስት ውርወራ ፤ እሽክርክሮሽ ፤ ሩጫ በመሳሰሉት ጨዋታዎች እንዲሁም እግር ኳስ በሰፈር ከጨርቅ እስከ ካፖርቲኖ ኳስ በበረኛ ፤ በተከላካይና በአጥቂ መስመር በመጫወት ፤ ወወክማ ስፓርት ተከታታይ ስልጠና በመውሰድ በፕሮጀክት ፤ በስታዲየም የአገር ውስጥ እግር ኳስ ፤ የክለቦች ብስክሌት ውድድር በተለያዩ ስፖርታዊ ትዕይንት ከተጫዋችነት እስከ ተሳታፊነት በተጨማሪም በስነ ስዕል ጥበብ ፤ በዕደ ጥበብ ሙያና በሽቦ ፤ ቆርኪ ፤ የከረሜላ ወረቀት የፈጠራ ስራዎች ክህሎትና ችሎታ ነበረው ፡፡
አለም በስራ ዓለም
በ1985 ዓ.ም 12ኛ ክፍል አገር አቀፍ መልቀቄያ ( ማትሪክ ) ፈተና ወስዶ ለከፍተኛ ትምህርት የሚያበቃ ውጤት ስላልነበረው ፤ ወዲያው ታላቅ ወንድሙም ድንገት በሞት ሲለየው ፤ ተስፋ ሳይቆርጥ ወዲያው ደካማ አይነስውር ወላጅ እናቱ ለመርዳት ለመንከባከብ ፤ ኑሮውን ለማሸነፍ ሲል መርካቶ ጎማ ተራ በግለሰብ ንግድ ተቀጥሮ የመኪና ጎማ በመሸጥ በሚከፈለው ዕለታዊ ክፍያ ብር እናቱን ቤት ተከራይቶ ኑሮውን በግል በመምራት ከስራ መልስ በማታ ክፍለ ጊዜም በኤሌክትሮኒክስ ሙያ ዘርፍ በአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ት/ቤት በመማር በከፍተኛ ውጤት በማዕረግ ሓምሌ 1992 ዓ.ም በዲፕሎማ ተመርቋል ፡፡ ነገር ግን ታህሳስ 1992 ዓ.ም እናቱ በህመም ድንገት በሞት ቢለዩትም ህልሙን ለማሳካት እንደወትሮው ጉዞውን ወደፊት በመቀጠል በተማረበት ሙያ ዘርፍ ስራ ለማፈላለግ ለአንድ ዓመት ያህል ከቆየ በኃላ ሓምሌ 01 / 1993 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሬድዮ ድርጅት ባወጣው ክፍት የስራ መደብ ተወዳድሮ በቴክኒክ ሙያ ዘርፍ በጀማሪ ቴክኒሽያን መደብ በ472 ብር ወርሃዊ ደመወዝ በቋሚነት ተቀጥሮ ስራውን ጀመረ ፡፡
አለም በቀጥታ ስርጭትና መስክ ቀረጻ ክፍል ተመድቦ ፤ የተሰጠውን ስራ በብቃት ለመወጣት በተለያዩ ማህበራዊ ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሁነቶች ከጋዜጠኛ ጀርባ በመሆን ፤ በተንቀሳቃሽ ሬድዮ ስቱድዮ ( ኦቢቫን ) ቀጥታ ስርጭትና እና በመስክ ቀረጻ በከተማና ገጠር በናግራ ሪል ቴፕ ቀረጻን በጥራት ይህም በፓርላማ መደበኛ ስብሰባዎች ፤ በከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ጠቅላይ ሚኒስትርና ሚኒስትሮችን ንግግርና ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅታዊ ሁነቶች ፤ የሃይማኖታዊና ሃገራዊ ክብረ በዓላት የሙዚቃ ቀረጻዎች በተለይም በሳምንት ዓርብ ቀን የሚተላለፈው የሊቀ ናይል የተማሪዎች ጥያቄና መልስ ውድድር በጀማሪነት ከሪል ቴፕ ቀረጻ ጀምሮ እስከ አዶቬ እና ፍላሽ ቀረጻ ድረስ በግንባር ቀደምትነት እንዲሁም በሬድዮ ስቱድዮ በቴክኒክ ቀረጻና በሲስተም ቴክኒክ ጥገና በሙያው አገልግሏል ፡፡
ከጥቅምት 01 / 2001 ዓ.ም ጀምሮ በሚዲያ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ሬድዮ ሲስተም በመቀጠልም በቴሌቭዥን ሲስተም ስራ ክፍልም በርካታ የመስክ ቀረጻ ፤ የቀጥታ ስርጭትና የጥገና ኢንስታሌሽን ስራዎችን ማከናወን ውጤታማ የጤክኒክ ባለሙያ የነበረ ሲሆን ይህም በስቱድዮ ኢንስታሌሽን ስራዎች በዋናው መ/ቤት እንዲሁም አዲስ በተሰራው የኢቢሲ ባህዳር ጊዜያዊ ስቱድዮ ኢንስታሌሽን ስራ ፤ ብሎክ ዲያግራም ስራ ፤ የተለያዩ የአርቴክት ስራዎችን በአቅሙ ሰርቷል ፡፡ በተጨማሪም በግል እሳቤ በስቱድዮ ሲስተምና ሳተላይት ዘመናዊ የቴክኒክ ጥገና ማዕከል እንዲኖር ከጽንሰ ሃሳብ ( ፕሮፖዛል ) ጀምሮ እስከ ጥናታዊ ስነ ጽሁፍ በማዘጋጀትና የቴክኒክ ባለሙያዎችን በማስተባበር የልምድ ልውውጥ ከተመረጡ ተቋማት ማለትም ከኢትዮ ቴሌኮም ፤ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮምፒውተር ጥገና ማዕከል ( CRTC ) እንዲወስዱ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ተግባራዊ አድርጓል ፡፡ በተለያዩ የመስክ ቀጥታ ስርጭትና ቀረጻ ስራዎችን በማከናወን ፤ በተለያዩ የቴክኒክ ጥገናና ቁጥጥር ስራዎችን በመሳተፍ ውጤታማ ስራዎችን በመስራት ሙያዊ ግዴታውን አበርክቷል ፡፡
አለምና የኢቢሲ ታሪካዊ ሙዚየም
አለም ብርሃኔ ከጅምሩ በነበረው የቴክኒክ ሙያዊ ብቃትና ክህሎት በቁጭት ራዕይን ሰንቆ የተቋሙ ዘመን ተሻጋሪ የሚዲያ ታሪክ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ያለውን ከአድማስ ባሻገር የሚዲያ ቴክኖሎጂና ይዘት ዘርፍ በውስጡ ያሉትንና ያለፉትን አንጋፋ ጋዜጠኖችና የቴክኒክ ባለሙያዎች ታሪካቸውን ለትውልድ በታሪክ ተሰንዶ በሙዚየም በቅርስነት በክብር እንዲቀመጥ በማሰብ የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቭዥን ድርጅት ሚዲያ ታሪክ ከየት ? ወዴት ? በሚል አጭር ፕሮፖዛል በማዘጋጀት በምናባዊ አዕምሮ ያለውን ሃሳብ በወረቀት በማስፈር ለቀጣይ ምዕራፍ ዝግጅት በማድረጉ ምክንያት ይኸው ከየካቲት 2008 ዓ.ም ጀምሮ አዲስ በተቋቋመው የኢቢሲ ሚዲያ ታሪካዊ ሙዚየም ከጽንሰ ሃሳቡ ጀምሮ ባደረገው ጥረት የሙዚየም ቡድን መሪ በመሆን በተሰጠው ሃላፊነት በርካታ ቅርሶችን በአይነታቸው በማሰባሰብ ፤ ለግንባታ የሚሆኑ ቁሳቁሶችን በማሰባሰብ ፕሮፖዛልና የስትራክቸር ፕላን በማዘጋጀት የግንባታ ስራዎችን ጀምሮ በተግባር በመጨረስ በሬድዮና በቴሌቭዥን ኮርነር የተለያዩ ተቋሙን በይዘትና በሚዲያ ቴክኖሎጂ የሚዘክሩ ሁነቶችን በፎቶግራፍ ፤ በሚዲያ ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ፤ በኦዲዮ ቪዥዋል እና በስክሪን በማዘጋጀት ለዕይታ አቅርቧል ፡፡
አለም ባለው የወደፊት ዕቅድና ራዕይም ሙዚየሙን በሁሉም መስክ አቅሙን በማሳደግ ዘመናዊና ተደራሽ ለማድረግ ከብሔራዊ ሙዚየም ጋር የስራ ግንኙነት በመፍጠር ሙያዊ እገዛ ማግኘት ችለዋል ፡፡ በተጨማሪም ሙዚየሙን በከፍተኛ የቅርስና ጥበቃ ኤክስፐርቶች እንዲጎበኝና እንዲገመገም አድርጓል ፡፡ ከሰኔ 20 / 2008 ዓ.ም ጀምሮ በሙዚየምና ቤተመጻህፍት ቡድን መሪ ሃላፊነት በመስራት ከሙዚየም ስራዎች ጎን ለጎን ቤተመጻህፍትንም በዘመናዊ መልክ በማደራጀት ተደራሽና የመረጃ አቅሙን ለማሳደግ ዕቅድን በመንደፍ በከፍተኛ ሞራል ዘመናዊ ቤተመጻህፍት አውቶሜሽን የመረጃ ማዕከል እንዲኖር ፕሮፖዛል በማዘጋጀት ፤ ስራውን ሳይንሳዊ በሆነ ጥናት እንዲደገፍ ከተለያዩ ተቋማት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፤ ከብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻህፍት ኤጀንሲ ፤ ከስራ አመራር ኢንስቲትዩት ጋር ሙያዊ ግንኙነት በማድረግ ጥናታዊ ጽሁፍ ፤ ዝርዝር የበጀት ስፔስፊኬሽን ዶክመንት በማዘጋጀት ስራውን ለመጀመር በሂደት ላይ እያለ በበጀት እጥረት ምክንያት ስራው ሳይሳካ ቀርቷል ፡፡
ከሰኔ 01 / 2010 ዓ.ም ጀምሮ በተቋሙ በተሰራው አዲስ የአደረጃጀት መዋቅር በዋና ላይብሬሪያን የስራ መደብ እስካሁን ድረስ በማገልገል ላይ የሚገኝ ሲሆን ፤ የተሰጠውን የስራ ሃላፊነት ፕሮፌሽናል በሆነ መንገድ ለመምራት ታህሳስ 2011 ዓ.ም ከብሄራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻህፍት ኤጀንሲ የቤተመጻህፍት ሙያ የአሰልጣኞች ስልጠና ተከታትሎ የምስክር ወረቀት አግኝቷል ፡፡ በስልጠና ባገኘው ሙያዊ ክህሎት ስራውን ውጤታማ ለማድረግ እስካሁን ድረስ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል ፡፡ በአጠቃላይ አለም ብርሃኔ ከሐምሌ 01 / 1993 ዓ.ም እስከ የካቲት 2008 ዓ.ም ለ17 ዓመታት ያህል ከጀማሪ ቴክንሽያን እስከ ከፍተኛ ቴክንሽያን ሙያ ፤ እንዲሁም ለ5 ተከታታይ ዓመታትም በሙዚየምና ቤተመጻህፍት በቡድን መሪነትና በዋና ላይብሬሪያን ሙያ በማገልገል ላይ ይገኛል ፡፡
መንፈሳዊ ህይወት ግልጋሎትና ትምህርት
አለም ብርሃኔ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት እምነት ተከታይ ሲሆን ከልጅነቱ ጀምሮ ከቤተሰብ ባገኘው ሃይማኖታዊ ትውፊት በክርስትና እምነት ታንጾ በማደጉ ምክንያት ከልጅነቱ ጀምሮ አሁን ለደረሰበት ከፍተኛ መንፈሳዊ ደረጃ ማዕረግ ያለፈበትን የህይወት ውጣ ውረድ በእግዚአብሔር ሃይል በእምነት ሁሉን በመሻገር መሆኑ እውነት ነው ፡፡ አለም ብርሃኔ ባለፈበት ህይወት በነበረው ጽኑ ሃይማኖታዊ እምነት ለልጆቹና ለመጪው ትውልድ አብነት ለመሆን መልካም ጅማሮ በመሆኑ በእግዚአብሄር ቃል በጥበብ ታንጾ በመንፈሳዊ ጥበብ በዕውቀት ለማደግ በነበረው ህልምና ራዕይ ገና መንፈሳዊ ትምህርት በነሃሴ 1984 ዓ.ም በመካነ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስ ቤተክርስቲያን ውልደ ብርሃን ሰንበት ት/ቤት በአባልነት ተመዝግቦ ፤ የ8ኛ ዙር ተከታታይ መንፈሳዊ ትምህርት በሚገባ ተከታትሎ ፤ በሰንበት ትቤቱ በተለያዩ የኮሚቴ አደረጃጀት በሰባሳቢነትና በአባልነት በትምህርት ፤ በልማት ፤ በቅርስና ጥበቃ ፤ በወጣቶች ማስተባበሪያና በመዝሙር ኮሚቴ ከማገልገላቸው በተጨማሪ በሰንበት ት/ቤቱ በሚሰሩት የኪነጥበብ ስራዎች በራሄል ዕንባ ፤ በደም ድምጽ ትልልቅ የመድረክ ተውኔቶች በረሃብ ጥሪ ፤ በመንግስተ ሰማያት ፤ በጌታ ልደት ፤ በቆሎ ተማሪ አጫጭር ድራማማዎች በተለያጡ ገጸ ባህሪያት በመወከል በተዋናይነት ሰርቷል ፡፡
እንዲሁም በሰንበት ት/ቤቱ መንፈሳዊ ተከታታይ ኮርስ በስነፍጥረትና የእግዚአብሄር ህልውና ፤ የመንፈስ ፍሬዎች የቅዱሳን መላዕክት ባህሪያትና አማላጅነት ፤ በዜማና መዝሙር የትምህርት ዓይነት በአስተማሪነት አገልግሏል ፡፡ አለም ብርሃኔ ፈጣሪውን እርሱ በሰጠው ጸጋ ለማገልገል በነበረው ከፍተኛ እሳቤ የአብነት ትምህርት ከአባ ልብሰ ወርቅ ዘንድ ውዳሴ ማርያም ፤ አንቀጸ ብርሃን ፤ መልክዐ ኢየሱስ ፤ መልክዐ ማርያምና መልክዐ ቂርቆስ በመማር እንዲሁም የንባብ ትምህርት ከአባ ክፍለ ዮሃንስ ከመልዕክተ ዮሐንስ ጀምሮ የተለያዩ መንፈሳዊ መጻህፍት ንባብ በመማር ፤ በታህሳስ 10 / 1991 ዓ.ም ከሊቀ ጳጳስ አቡነ መቃሪዮስ መልካም ፈቃድና ቡራኬ እጅ በመንበረ ፓትርያሪክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተክርስቲያን የዲቁና ማዕረግ ተቀብሏል ፡፡
ዲያቆን አለም ብርሃኔ እግዚአብሔር ለማገልገል መንፈሳዊ ሩጫውን ለአፍታ ሳያቋርጥ ትልቅ ራዕይ ስለነበረው መንፈሳዊ ዕውቀት በስፋት ተምሮ ለማስተማር ከቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በሃምሌ 3 / 1996 ዓ.ም በዲፕሎማ እና በሰኔ 05 / 2002 ዓ.ም በባችለር ዲግሪ በስነ መለኮት ( ቲኦሎጂ ) በብቃት ትምህርቱን ተከታትሎ ከፓትሪያሪክ ከብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቡራኬ እጅ የመጀመሪያ ዲግሪና ዲፕሎማ ከነሙሉ ክብሩና ማዕረግ አግኝቷል ፡፡
መምህር ዲያቆን አለም ብርሃኔ ከሰማያዊ አባት ከልዑል እግዚአብሔር ባገኛው ባለ ዘርፈ ብዙ መንፈሳዊ ዕውቀትና ጥበብ ቅድስት ኦርቶቶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ለማገልገል ፤ ምዕመናንን በመንፈሳዊ ትምህርት ለማነጽ ለተከታታይ በርካታ ዓመታት በተለያዩ ገዳማትና አድባራት ፤ በማታ መርሃ ግብር ስብከተ ወንጌል ፤ በመንፈሳዊ ማህበራትና ሰንበት ትምህርት ቤቶች ፤ በመንፈሳዊ ጉዞዎች በማስተማር በስብከት በትሩፋት አገልግሏል በማገልገልም ይገኛል ፡፡
የትዳር ህይወትና ቤተሰብ
መምህር ዲያቆን አለም ብርሃኔ ወደ ትዳር ዓለም ለመግባት በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ቅዱስ ጋብቻውን ከወ/ሮ ለምለም ስለሺ በስርዓተ ቤተክርስቲያን በተክሊልና በቅዱስ ቁርባን ህዳር 07 / 2001 ዓ.ም በመካነ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስ ቤተክርስቲያን በመንፈሳዊ አገልግሎት ፈጽሟል ፡፡ በትዳር ህይወትም አራት ሴት ልጆች ሶሊያና አለም ፤ ኑሃሚን አለም ፤ ዮስቲና አለም እና አሜን አለም ወልዷል ፡፡ ከመልካም ቅዱስ ጋብቻ የተገኙ ልጆችም ወደፊት ሀገርንና ቅድስት ቤተክርስቲያንን በሃላፊነት በሙያቸው በመልካም ስነምግባር በቅንነት በታማኝነት ለማገልገል በፈሪሃ እግዚአብሔር በመንፈሳዊ ጥበብ በዕውቀት ኮትኩቶ እያሳደገ ይገኛል ፡፡
አለማዊ ትምህርትን በተመለከተ
- ከመስከረም 1990 ዓ.ም እስከ ሃምሌ 1992 ዓ.ም በኤሌክትሮኒክስ ሙያ ዘርፍ ለ3 ዓመታት ዲፕሎማ ከአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ትምህርት ቤት
- መስከረም 1997 ዓ.ም እስከ ሰኔ 2000 ዓ.ም በአድቫንስድ ኤሌክትሮኒክስ ለ4 ዓመታት ዲፕሎማ ከአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ኢንዱስቲሪያል ኮሌጅ ፡፡
- ከመስከረም 2010 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 2013 ዓ.ም በማኔጅመንት ለ4 ዓመታት ባችለር ዲግሪ ከኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርስቲ
- ከመስከረም 2011 ዓ.ም ጀምሮ በማይክሮ ሊንክ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኮሌጅ የ5ኛ ዓመት ኮምፒውተር ኢንጀሪንግ መርሃ ግብር በመማር ላይ ይገኛል ፡፡