ታየች ኡርጊቾ

ታየች ኡርጊቾ

ትውልድና እድገት

ታየች ኡርጊቾ የመጀመሪያዋ የአዲስ ልሣን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ናት፡፡ ታየች የተወለደችው በ1957 ዓ.ም በቀድሞው የወላይታ አውራጃ፣ ሶዶ ከተማ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷንም በዚያው በወላይታ አውራጃ በዴሳ ከተማ፣ የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በቦዲቲ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በሶዶ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቃለች፡፡

ወደ ጋዜጠኝነት

ታየች ጋዜጠኛ ለመሆን አስባም፣ አልማም እንደማታውቅ ነው የምትናገረው፡፡ ትምህርት ከመውደዷ በስተቀር አፍ ሲፈቱ ፓይለት እሆናለሁ፤ ዶክተር እሆናለሁ እንደሚሉት እንደአሁኖቹ ሕጻናት የምትሆነውን አውቃ አይደለም ሕይወትን የጀመረችው፡፡ ወደ ጋዜጠኝነት ያደረሰኝ እግሬ ነው የምትለው፡፡ ይሁን እንጂ በኋላ ከጋዜጠኝነት መውጣት የሞት ያህል ከብዷት እንደነበርም አልሸሸገችም፡፡ ጋዜጠኝነት አልጋ በአልጋ የሆነ ሥራ ስለሆነ ሳይሆን ፍቅር ስለሚያስይዝ፡፡

ጋዜጠኛ እሆናለሁ ብላ ባታስብም መጽሐፍ ማንበብ ግን የጀመረችው ገና ከልጅነቷ ነው፡፡ በተለይ የፖለቲካ ይዘት ያላቸው የታሪክ መጻሕፍት ይማርኳታል፡፡ የየትኛውም አገር ታሪክ ቢሆን ማለት ነው፡፡ ስላለፉት ትውልዶችና ስለፈጸሟቸው ሥራዎች ማወቅ ያስደስታታል፡፡ የመጀመሪያውን መጽሐፍ ያነበበችው የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ሆና ነው፡፡ ያገኘችውን መጽሐፍ እያነበበች የቤት ውስጥ ሥራ ችላ ስትልባት አክስቷ መጽሐፍ ትበያለሽ? እያለች ትቆጣት እንደነበር በፈገግታ ታስታውሳለች፡፡ በሮዴዥያ ስለነበረው ስለኢያን ስሚዝ የቅኝ አገዛዝ ግፍ በሚያወሳውና “ኦ ሰላም ሰላም በስምሽ ስንት ግፍ ተሠራ?” በሚለው የሳህለ ሥላሴ ደስታ መጽሐፍ ነበር ንባብን ሀ ሁ ያለችው፡፡ አሁን ታሪኩን ሙሉ በሙሉ ባታስታውስም መጽሐፉን በእንባ አንብባ እንደጨረሰች ትናገራለች፡፡ በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸመውን ግፍ የልጅነት አእምሮዋ መሸከም አቅቶት፡፡ ያም ሆነ ይህ የንባብ ፍቅር ያደረባት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡

ታየች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በቋንቋና ሥነ ጽሑፍ የመጀመሪያ ዲግሪ በማግኘት ተመረቀች፡፡ በ1979 በአዲስ አበባ አስተዳደር ሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት ሥራ ጀመረች፡፡ በሥነ ጽሑፍ እጇን ያፍታታችው በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ ነው፡፡ ጋዜጠኝነትን የጀመረችው ግን “የከነማ ልሳን” በሚል ርዕስ ይታተም በነበረው የአዲስ አበባ ምክር ቤት ወርሃዊ ጋዜጣ ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ሕዝብ ግንኙነት በባለሙያዎችን በአደረጃጀትም ጠንካራና በርካታ ኅትመቶች የሚወጡበት ስለነበር ለታየች ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮላታል፡፡ የመንጠቆ ቴአትር ተርጓሚ የሆነው ደራሲ ሙላቱ ገብሩ ከእነዚህ መካከል አንዱ ነበር፡፡

በ1985 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማስታወቂያ ቢሮ በመግባት በመጀመሪያ “አዲስ” የተባለ ወርኃዊ መጽሔት፣ ቀጥሎም ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1994 ጥር ወር ድረስ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በመሆን ሰርታለች፡፡ ታየች ከመጀመሪያዎቹ የማስታወቂያ ቢሮ፣ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ፣ የአዲስ ቴሌቪዥን እንዲሁም የአዲስ ሬድዮ መሥራቾች አንዷ ናት፡፡

“አዲስ ልሳን”ና የመጀመሪያ ልጄ እኩል ስለተወለዱ አብረው ነው ያደጉት በማለት ትናገራለች፡፡ ምንም እንኳን ልጅ ማሳደግ ጊዜ የሚጠይቅ ቢሆንም ታየች ግን አብዛኛውን ጊዜዋንና ኢነርጂዋን የምታውለው ለ”አዲስ ልሳን” ነበር፡፡ የግድ ስለሆነባት፡፡ ጋዜጠኝነት ለራስ ጊዜ እንዲተርፍ ከማይፈቅዱ ሥራዎች አንዱ ነው፡፡ በሳምንት ሁለት ጊዜ፣ በሀያ አራት ገጽ ይታተም የነበረ ጋዜጣ ደግሞ በዓልን፣ ቅዳሜንና እሑድን ጭምር አይምርም፡፡ እስከ ምሽቱ 3፡00 ድረስ መሥራት የተለመደ ነበር፡፡ “እናትነትነት ክፉኛ የተፈተነበት ጊዜ ቢኖር አዲስ ልሳን ላይ የሰራሁበት ወቅት ነበር” በማለት ታስታውሳለች፡፡ ያም ሆነ ይህ ሁሉም ሥራ የራሱ ተግዳሮቶች አሉት፡፡ የጋዜጠኝነትን ተግዳሮቶች ተሻግራ ዛሬ የሶስት ልጆች እናት ለመሆን በቅታለች፡፡

ዜና አነፍናፊዎቹ

አዲስ ልሣን ታየች መቼም የማትረሳቸው ዜና አነፍናፊ ጋዜጠኞች እንደነበሩት ታስታውሳለች፡፡ ጋዜጣው ሲጀመር የዜና ምንጭ ሥርዓት ስላልነበረው ዜና እያሸተቱና እያነፈነፉ ማምጣት የግድ ነበር፡፡ የእርሷም ሆነ የአዲስ ልሳን ሪፖርተሮች ዓይንና አእምሮ ዜና በማሽተትና በማነፍነፍ ላይ የተጠመደ ነበር፡፡ በኋላ ግን በቁልፍ ቦታዎች ሪፖርተሮችን በመመደብና በየዞኑ የማስታወቂያና የህዝብ ግንኙነት ሥራዎች ሲደራጁ ሥራው እየቀለለ መጣ፡፡

በአዲስ ልሳን ቆይታዋ እንደአረፈ ዓይኔ ሀጎስና፣ መኩሪያ መካሻ ካሉ ምርጥ ጋዜጠኞች ጋር መሥራቷ በብዙ መልኩ ለሙያዋ እገዛ እንዳደረገላት ትናገራለች፡፡ የአሁኑ የሸገር ሬድዮ ጋዜጠኛ እሸቴ አሰፋ ሞዴሏ እንደነበርም ታስታውሳለች፡፡

ታየች ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅነት ከለቀቀች በኋላ በአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የአካባቢ ትምህርትና ግንዛቤ ጽሑፎች ኤዲተር፣ በመቀጠልም የጽሑፍና ኅትመት ማደራጃ ቡድን መሪ በመሆን ሰርታለች፡፡ በአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ቆይታዋ በአካባቢ ጉዳዮች ላይ ያተከሩ በርካታ ኅትመቶች ላይ ሰርታለች፡፡ በመሥሪያ ቤቱ ሰነዶች የአርትኦትና ትርጉም ሥራዎችንም ስታከናውን ቆይታለች፡፡ ለምሳሌ፣ በ2003 የወጣውን የኢትዮጵያ የአርንጓዴ ኢኮኖሚ ራዕይ ወደ አማርኛ ተርጉማለች፡፡ የባለሥልጣኑ ዳይሬክተር ጀነራል ዶ/ር ተወልደብርሃን ገብረ እግዚአብሔር እና ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ደሳለኝ መስፍን ለጽሑፍና ለአርትኦት ሥራ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጡ ነበር፡፡ ስለዚህም ቁጥራቸውን የማታውቃቸውን የድርጅቱን ሰነዶች አርትኦት እና ትርጉም መሥራቷን ትናገራለች፡፡

ታየች በ2001 ዓ.ም ወደ ኔዘርላንድስ በመሄድ በዋግንኒንገን ዩኒቨርሲቲ (Wagningen University) ሥር ከሚገኘው ከቫንሆልላርነስቴይን ዩኒቨርሲቲ (Van Hall Larnestien) በሶሻል ኢንክሉዥን ጀንደርና ላይቭሊሁድ (Social Inclusion Gender and Livelihood) የማስተሬት ዲግሪ በማግኘት ከተመለሰች በኋላ በዚሁ መሥሪያ ቤት የሥርዓተ ጾታና አካባቢ ዳይሬክተር በመሆን ለ5 ዓመታት ያህል አገልግላለች፡፡

ታየች በባህላችን ስለሴቶች እና ወንዶች ያለው የአመለካከት ልዩነት መላውን ኅብረተሰብ ምን ያህል ወደ ኋላ እንዳስቀረ የተገነዘበችው ከልጅነቷ ነው፡፡ ሴቶች በትምህርት፣ ሙያን በማሻሻል ወደ ፊት እንዳይሄዱ የሚያግዷቸው ብዙ እንቅፋቶች አሉባቸው ትላለች፡፡ ከወንዶች እኩል እድል ቢያገኙ ኖሮ እስካሁን ድረስ አንደ አገር፣ እንደ ሕዝብ የትና የት እንደርስ ነበር በማለትም ትቆጫለች፡፡ አሁን ግን ዘገምተኛ ቢሆንም መሻሻሎች መኖራቸው ያስደስታታል፡፡ አዲስ ልሳን ላይ “የሴቶች” ዓምድ በመክፈት ቀደም ሲል ለጋወርቅ አሰፋ፣ ቀጥሎም ሌሎች አዘጋጆች ስለሴቶች ብዙ መጣጥፎች ተጽፈዋል፡፡

በአስቸጋሪ ወቅት ሳቅ

የአዲስ ልሳን ቆይታዋ አስደሳችም፣ አስቸጋሪም እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ ለሥራ ምቹ ሁኔታዎች አልነበሩም፡፡ የአዲስ ልሳን ሪፖርተሮችና ምክትል አዘጋጆች ግን የነበራቸው የቡድን ስሜት ደስ የምትሰኝበት እንደነበር በኩራት ትናገራለች፡፡

ታየች ድንቅ በማለት የምትገልጻቸው እነዚህ የቀድሞ የአዲስ ልሳን ሪፖርተሮች ዛሬ የአንዳንድ ትላልቅ መጽሔትና ጋዜጣ ዋና አዘጋጆች ናቸው፡፡ ለነገሩ ብዙ ጋዜጠኞች በአዲስ ልሳን አቆራርጠው ነው ወደ ሌሎቹ ሚዲያዎች የሚሻገሩት፡፡ ለምሳሌ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን መምህር መኩሪያ መካሻ፣ “የቁም ነገር መጽሔት” ዋና አዘጋጅ ታምራት ኃይሉ፣ ታዋቂው ገጣሚ ታገል ሰይፉና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡ አንዳንዶቹ በአገር ውስጥና በመላው ዓለም በተለያየ ሥራ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ ሥራን በቡድንና በፍቅር መሥራትን፣ በችግርና በአስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ መሳቅን ላስተማራችሁኝ የቀድሞ የአዲስ ልሣን ጋዜጣ ጋዜጠኞች የላቀ አክብሮት አለኝ ትላለች፡፡ ታየች በአሁኑ ወቅት በአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን በከፍተኛ አማካሪነት በመሥራት ላይ ትገኛለች፡፡

መዝጊያ

ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን አቋም የሚንጸባረቅበት ይሆናል፡፡ ታየች ኡርጌቾ ጎበዝ አርታኢ ስለመሆኗ አብረዋት የሰሩ በሙሉ አንደበታቸው ይመሰክራሉ ፡፡ ታየች በዚህ ልዩ ክህሎቷ ዛሬም በርካታዎች ይመሰክሩላታል፡፡ በተለይ በ1990ዎቹ አብረዋት ያገለገሉ አለቃቸው ሆና የመራቻቸው ሲመሰክሩ አስደናቂ አርታኢ ይሏታል፡፡ ይህ የታየች ክህሎት እንዲህ በቀላሉ የመጣ አይሆንም፡፡ በብዙ ልፋት ብሎም በብዙ ድካም ነው፡፡ በተለይ ገና በወጣትነት እድሜዋ ራሷን በንባብ ያዳበረችው ታየች ወደ ሚድያው ዘልቃ ስትገባ ስራው ብዙም አዳጋች አልሆነባትም፡፡ ታየች ኡርጌቾ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ የመጀመሪያዋ ዋና አዘጋጅ ነች፡፡ በተለይ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ዋና አዘጋጅ ሆና በሰራችበት ጊዜ ደስ ብሏት ብዙዎችን ለማብቃት እንደቻለች ይመሰከራል፡፡ ታየች አሁንም ቢሆን በምትሰራበት ስፍራ ያለአንዳችመታከት እየሰራች ትገኛለች፡፡ ታየች በአሁኑ ሰአት በህትመት ሚደያው ላይ በጣም የምታስፈልግ ባለሙያ ናት፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያ ሚድያ የሚፈልገው ክህሎት ያዳበረን ለሙያው ብቻ የሚተጋን ታታሪ ሰው ብቻ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ሰዎች ናቸው ሰው ለማስተማር የሚችሉት ፡፡ ታየች በሚድያ አለም በተለይ በህትመት ዘርፉ ያበረከተችው ሚና ቀላል አይባልም፡፡ እኛ ሀገር በአንድ ወቅት የሰራ ብዙዎች የሚያመሰግኑት በቆይታ ይዘነጋል፡፡ እከሌ ለመሆኑ አለ ይባላል፡፡ እውነትም አንዳንድ ሰዎች ጠፍተዋል፡፡ ታሪካቸው ግን እንዳይጠፋ ትውልድም እንዲያመሰግናቸውና ቀጣይነት ያለው ምርምር እንዲያደርግ ታሪካቸውን አውጥተናል፡፡ ከእነዚህ ባለታሪኮች አንዷ ደግሞ ታየች ናት፡፡/ የዚህ ጽሁፍ የምርምር እና የስነዳ ስራው በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የተከናወነ ሲሆን ዛሬ ቅዳሜ ጥር 28 2014 በተወዳጅ ሚድያ የግለ-ታሪክ ገጾች ላይ የወጣ ነው፡፡ አስፈላጊው ማሻሻያ ተደርጎለትም በየጊዜው እንዲወጣ ይደረጋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *