ሻለቃ ግርማ ይልማ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡
ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 150 የሚድያ ፤ የስነ-ጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል ሻለቃ ግርማ ይልማ ናቸው፡፡ ሻለቃ ግርማ ይልማ በደርግ ጊዜ የማስታወቂያ እና መርሀ-ብሄር ሚኒስትር በመሆን ሰርተዋል፡፡ በተጨማሪም የባህል ሚኒስትር በመሆን ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡ ከ1970-1983 በኢትዮጵያ በሚድያ እና በቴአትር እንቅስቃሴ ላይ ቁልፍ የመወሰን ስልጣን የነበራቸው ሰው ነበሩ፡፡
ሻለቃ ግርማ ይልማ አብረዋቸው በነበሩ ሰዎች የሚከበሩ እና የእሁድ ጠዋት የኢትዮጵያ ሬድዮ የመዝናኛ ፕሮግራም እንዲጀመር መሰረት የጣሉ ናቸው፡፡ በብእር ስማቸውም ይጽፉ ነበር፡፡ ሻለቃ ግርማ ይልማ ከዛሬ 30 አመት በፊት መኖሪያቸውን በሲያትል አሜሪካ ያደረጉ ሲሆን ለተወዳጅ ሚድያም ታሪካቸው እንዲሰራ ፈቃደኝነታቸውን አሳይተዋል፡፡ ሻለቃ ግርማ ይልማ ብዙም ስለራሳቸው መናገር የማይወዱ በትህትና የተሞሉ ሰው ናቸው፡፡ እዝራ እጅጉ እና ዘቢባ ሁሴን የህይወት ታሪካቸውን እንደሚከተለው ሰንደውታል፡፡ የሰውነት ተምሳሌት ።የመልካም ስብእና መገለጫ ። ባለተሰጥኦ አንባቢ አድማጭና ተመልካች እንዲሁም የጽሑፍ ሰው የረዥም ጊዜ የሕይወትና የሥራ ልምድ ባለቤት ። ከመኮንንነት እስከ ሚኒስትርነትና አምባሳደርነት የዘለቀ ሃገርን የማገልገል ጥበብ የተቸራቸው ናቸው ። ሚኒስትርነት ቀላል ሥልጣን አልነበረም፣አይደለምም። እርሳቸው ግን ቀለል ያሉ ነበሩ፣ ፈረንጆቹ “Simple” የሚሏቸው አይነት። ዛሬም ናቸው። ሻለቃ ግርማ ይልማ
ውልደትና እድገት
ሻለቃ ግርማ ይልማ ሀይቆችና ቡታጅራ ቆንዳልቲቲ ጭብጭባ በምትባል መንደር በ1936 ዓም በጷግሜ ቀናት ተወለዱ። አስተዳደጋቸው እንደማንኛውም በገጠር የሚያድግ ልጅ የቄስ ትምህርትን ተምረው ነበር። ሻለቃ ትምህርት ቤት ከመግባታቸው በፊት ወላጅ አባታቸው በተሰማሩበት የንግድ ስራ ምክንያት ወደ ቢሾፍቱ በኋላም ለተሻለ የንግድ ስራ ወደ ዲላ ከተሞች ይዘዋቸው ተንቀሳቅሰዋል። ሻለቃ ግርማም ልክ እንዳባታቸው በተንቀሳቀሱበት ሁሉ ወደ ንግዱ አዘንብለው የተዋጣላቸው ነጋዴ ነበሩ።
የትምህርት ጅማሮ
ትምህርት ሳይማሩ ንግዱ ላይ ብቻ ያተኮሩት ሻለቃ በ1948 ዓም ጓደኛቸው በነበረ ግርማ በቀለ ጋባዠነት የተማሪዎች የትምህርት መዝጊያ ፕሮግራም “የወላጆች” ቀን ላይ ተገኙ። በዚህ ቀን በትናንሽ ልጆች አጫጭር ድራማዎች ሲቀርቡም ተመለከቱ ። በጣም የተደሰቱ። በእነዚህ ተማሪዎችም መንፈሳዊ ቅናት አደረባቸው። ወደ ትምህርት ፊታቸውን በማዞር የቀለም ትምህርትን ጠንክረው መማር እንዳለባቸውም ወሰኑ። ምንም እንኳን የንግድ ስራው እየተጠናከረ ቢሄድም እርግፍ አድርገው ትተውት በ1949 ዓም 3ኛ ክፍልን በመቀላቀል “ሀ” ብለው ትምህርታቸውን መማር ጀመሩ። በእድሜ ከፍ ብለው ትምህርት መጀመራቸው የራሱ የሆነ ስነ-ልቦናዊ ጫና ቢኖረውም ውሳኔው ትክክል ነበርና ሁሉን በመቋቋምና ደብል በመምታት በ3 ዓመት ውስጥ በ1952 ዓም በጥሩ ውጤት የመጀመሪያ ደረጃ የ8ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ማጠናቀቅ ቻሉ።
ኮከበ ፅባህ
በቅርብ የሚያውቋቸው የተሻሉ ሰዎች መምህራን ነበሩና መምህር መሆንን ሰንቀው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የነበሩት ሻለቃ ግርማ ይልማ በ1953 ዓ.ም ከ8ኛ ክፍል በቀጥታ ወደ አዲስ አበባ “ኮከበ ፅባህ” መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም በመግባት ለተከታታይ አራት አመታት ከ1953- 1957 የመምህርነት ሞያን ተምረው በዲፕሎማ መመረቅ ችለዋል። ሻለቃ ግርማ በኮከበ ፅባህ እያሉ በተማሪዎች እንቅስቃሴዎች ላይ ንቁ ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን በዘመኑ ከ3000 በላይ ተማሪዎች በሚማሩበት የተማሪዎች መማክርት ኮሚቴ እና የተማሪዎች ፕሬዚደንትም ነበሩ። ትምህርት ቤቱን በበላይነት ይመሩ የነበሩት አካላት አብዛኞቹ የውጭ ሃገር ዜጓች ነበሩ፡፡ ካናዳውያኑ በወቅቱ በነበሩ ተማሪዎች ላይ ጭቆና ያደርሱ ነበር። ይህንን ለመከላከል ከፍተኛ ተጋድሎም ያደርጉ ነበር፡፡ የተማሪዎች ፕሬዚደንት ሻለቃ ግርማ። ሻለቃ ከኮከበ ፅባህ ተመርቀው እንደወጡ በምደባ ወደ ሲዳሞ ተጉዘው መምህር ሆነው ሰርተዋል። በሲዳሞ ለአንድ አመት ያህል ብቻ ያስተማሩ ሲሆን በዚያች አንድ አመት ቆይታቸው በሞያሌ አቅራቢያ ሜጋ : አባያታ እና ኦናጎ አካባቢ ባሉ ትምህርት ቤቶች ተዘዋውረው አስተምረዋል።
የሚሊተሪ ቤት ቆይታ
ሻለቃ ግርማ ይልማ ፖሊስ ሆነው የሃገራቸውን ዳር ድንበር ማስከበር ሌላው ህልማቸውና የልብ መሻታቸውም ነበር ፡፡ይህ ተዳፍኖ የኖረ ፍላጎት የተቀሰቀሰው በኮከበ ፅባህ ትምህርት ላይ ሳሉ ነበር። ምንም እንኳ ወደ አዲስ አበባ የመጡት የመምህርነት ሙያን ለመማር ቢሆንም በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ በዚያኑ አመት የፖሊስ ሰራዊት 12ኛ ክፍል ያጠናቀቁና 11ኛ ክፍል ላይ ያሉ ተማሪዎችን ይመለምል ነበርና ሻለቃ ግርማም አመልክተው በወቅቱ የአፍሪካ አንድነት ፅ/ቤት ተብሎ በተሰራው የፖሊስ ኮሌጅ ተፈትነው በማለፍ በ1958 ዓ.ም የአባዲና ፖሊስ ኮሌጅ እጩ መኮንን በመሆን ስራቸውን መጀመር ችለዋል።
ሻለቃ ግርማ በፖሊስ ኮሌጅ ሳሉ በእጩ መኮንኖች መካከል በተደረገ የስነ-ግጥም ውድድር ላይ ተሳትፈው ” በትምህርት የወለደኝ” የሚል ርዕስ ያለው ግጥም ፅፈው በንጉሰ- ነገስቱ ፊት አቅርበው ነበር። ይህ ወደ ስነ-ፅሁፍ ያንደረደራቸው መንገድ ሲሆን በዘመኑ ተቀርፆ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የመተላለፍ እድልም ነበረው። ሻለቃ ግርማ ይልማ ንባብን እጅግ የሚያፈቅሩ ሰው ነበሩ። ከእጃቸው መፅሀፍ ተነጥሎ አያውቅም።የነመሀተመ ጋንዲን የአብርሃም ሊንከንና የሌሎችንም ታላላቅ ሰዎች የግለ-ታሪክ መጽሀፍ ማንበብ ይወዱ ነበር። ማንበብ ብቻ ሳይሆን ገና ተማሪ ሳሉ ነበር በመንግስት ጋዜጦችና መፅሄቶች ላይ በብዕር ስም ይፅፉ የነበሩት።
የኤርትራ ጠቅላይ ግዛት ፖሊስ
ሻለቃ ግርማ ይልማ ከፖሊስነት ምረቃ በኋላ በኤርትራ ክፍለ -ሀገር የማስታወቂያና የህዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ በመሆን ሰርተዋል። ከኮሎኔል አለምሰገድ ቦጋለ ጋር በመሆንም የኤርትራ ፖሊስ መፅሄትንም ያዘጋጁ ነበር። በ22 ዓመታቸው የኤርትራ ጠቅላይ ግዛት ፖሊስ አባል ውስጥ የመቶ አለቃነት ማእረግን ይዘው ሃገራቸውን በማገልገል ላይ የነበሩት ሻለቃ ግርማ “ኤርትራ ወይ ሞት” ” የሃገር ፍቅር ማህበር” ብለው ከኢትዮጵያ ጋር የቆሙና ለኢትዮጵያ የታገሉትን በርካታ ኤርትራዊያን ከህዝቡ ጋር የሚያስተዋውቁበትን የመጀመሪያ መፅሄትን አዘጋጅተው ለህዝብ አድርሰዋል። ስለዘመናዊ ፖሊስ ምንነትም እንዲሁ ለህዝቡ ይፅፉ ነበር። በንጉሱ ዘመን በትንሹ ለስምንት ዓመታት ያክል አገልግለዋል፡፡ ከ22 ዓመታቸው 30 እስኪሞላቸው ድረስ። በዚህ የስራ ዘመናቸው በተለይ የፖሊስነትን ስራን : ህግ የማስከበር ተግባርንና ሌሎችንም በህትመትና በማስታወቂያው ዘርፍ ከህዝቡ እና ከአባላቱ ጋር እጅና ጓንት በመሆን ሰርተዋል። ኃላፊነታቸውንም ተወጥተዋል።
በዘመነ ደርግ
ሻለቃ ግርማ ይልማ የንጉሱ ዘመን አብቅቶ የደርግ መንግስት ሲተካ የ31 ዓመት ወጣት ነበሩ። በ1962 ዓም ከኤርትራ ተመልሰው በአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ስር በፖሊስና እርምጃው ጋዜጣ ክፍል ሻለቃ ጌታቸው መንግስቴ በዋና በአዘጋጅነት ሻለቃ ግርማ ይልማ ደግሞ በተባባሪ አዘጋጅነት ተመድበውም ሰርተዋል። በዚህ ወቅት ወደተለያዩ የሃገራችን አካባቢዎች በመዘዋወር ወንጀል ነክ የሆኑ ፕሮግራሞችን በመፃፍ በጋዜጣ ላይ እንዲወጡም ያደርጉ ነበር። በዚህ መሀል በመልካም የስራ አፈፃፀማቸው የፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ባመቻቸላቸው የትምህርት እድል ተጠቅመው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ተምረው ተመርቀዋል። በዘመኑ አራተኛ ክፍለ ጦር የነበሩ ሰራዊቶችን ለማስተባበር ሁለት ጊዜ የደርግ አባል ሆነው እንዲሰሩ ተመርጠው ነበር። ነገር ግን በምርጫው ወቅት ሻለቃ ግርማ በስፍራው ባለመኖራቸውና የተመረጡት ሰዎች በቂ ስለነበሩ እዚያው በፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ውስጥ እንዲያገለግሉ ሆኗል።
ሹመት
ሻለቃ ግርማ በደርግ ውስጥ የማስታወቂያ ኮሚቴ ሲቋቋም በ1967 ዓም የደርግ ማስታወቂያ ኮሚቴ ሆነው ተመርጠው ሠርተዋል። አጠቃላይ የመርህና የድርጅታዊ አመራር የሚሰጠው በዚህ ኮሚቴ ውስጥ ነበርና በዚህ አጋጣሚ የማስታወቂያና መርሀ ብሄር ሚኒስቴር ሚኒስትር እንዲሆኑ ከጓድ ሊቀመንበር መንግስቱ ሃይለማርያምና ከዋና ፀሃፊያቸው ጥያቄ ቀረበላቸው። የሻለቃ ግርማ መልስ ግን እኔ ለዚህ ስልጣን ብቁ አይደለሁምና አልፈልግም የሚል ነበር። ይህ ምላሽ በዘመኑ ብዙዎችን ያስደነቀም ነበር።
ሹመት አያሻኝም ቅድሚያ ልማር : ልወቅ : ልብቃ ያሉት ሻለቃ ግርማ ወደ ሶቪየት ህብረት ተጉዘው ለ6 ወር ያህል የፖለቲካ ትምህርት ተምረው ተመለሱ። ከዚህ በኋላ ግን በ1970 ዓ.ም እንደገና የሹመት ጥያቄ ቀረበላቸውና የማስታወቂያና መርሀ-ብሄር ሚኒስቴር ሚኒስትር ለመሆን ችለዋል። ሻለቃ ግርማ ይልማ በየካቲት 1975 ዓ.ም ከማስታወቂያ ሚኒስትርነት ወደባህልና ስፖርት ጉዳይ ሚኒስትርነት በሹመት የተዛወሩ ሲሆን ከሰኔ ወር 1982 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በሶቪዬት ኅብረት የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ሃገራቸውን አገልግለዋል።
ሻለቃ ግርማ ይልማ የቀድሞው የፖሊስ መኮንን አባልነት እንዲሁም የማስታወቂያና መርሀብሄር ሚኒስቴር ሚኒስትር ከሆኑበት ከነሐሴ 1970 ዓ.ም በፊትና በኋላም በመደበኛ ስማቸውም በተለያዩ የብዕር ስሞችም ይጽፉ ነበር። በተለይ በተወዳጁ የእሑድ ጠዋት የራዲዮ ፕሮግራም በ”ቡልቡላ ዘመርካቶ” ስም ጉልህ ተሳትፎ አድርገዋል። “በተለይ የሩሲያው አብዮትና አሜሪካዊዉ ጋዜጠኛ” በሚል ርዕስ የፃፉትንና ንጉሴ አክሊሉ በኢትዮጵያ ቴሌቪዠን ያነበበውን ፅሁፍ መቼም አይዘነጉትም።
በዘመነ ቀይና ነጭ ሽብርም በፈጠራ ክስ ሕይወታቸው አደጋ ላይ ወድቆ የነበሩ ጋዜጠኞችን በፅሁፋቸው ታድገዋል። ሌሎችንም ፅሁፎች በጋዜጦችና በመጽሔቶችም ላይ አዘውትረው ይጽፉ ነበር። “ነፃውን ፕሬስ በተመለከተ ደግሞ የምንጊዜም ተባባሪና የሚያውቁትን ሁሉ ለማካፈል ማወላወል የማያውቁ ነበሩ። አንድ የኪነጥበብ ጋዜጣ ለሥራው ስኬታማነት ጉዳዮችን መፈተሽ ሲያስፈልግ የሻለቃን ስልክ ሁሌ መደብደብ፣ የቤታቸውንም በር “መቆርቆር” የግድ ነበር።
ነፃ ፕሬሶች ተጠናክረዉ ከማየትና ሕዝቡም ማወቅ ያለበትን ያለማጣቱን ከማየት በላይ እኔን የሚያጠግበኝ አንዳችም ዓይነት ሌላ ዋጋ የለም” ሲሉ አብዝተዉ ይደመጣሉ። ከ1970-1975 ዓም የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ባሉ ግዜ አጠቃላይ የቴሌቪዠንም ሆነ የሬድዮ ጋዜጠኞች በስራቸው ነበሩ። እነ ሙሉጌታ ሉሌ እነ በአሉ ግርማና ሌሎችም ። በዚህ ወቅት ሙያው እንዲያድግ በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሃገራት የትምህርት እድል ሲገኝ ባለሙያዎች እንዲማሩ እንዲያነቡ ያደርጉ ነበር።
ሻለቃ በዘመኑ አብረዋቸው ይሰሩ የነበሩ ታላላቅ ሰዎችን እንዲህ ይገልፃሉ። ሙሉጌታ ሉሌ በጣም ፈጣን ። ሃሳብ ያለው። ቋንቋው ምሉዕ የሆነ ሰው ነው። በአሉ ግርማ እጅግ የማከብረውና የማደንቀው የስነ ፅሁፍ ሊቅ ነው ገዳሙ አብርሃ ደግሞ በአማርኛም ሆነ በእንግሊዘኛ የሚፅፍ ብቁ ሰው ነው።
ብርሃኑ ዘሪሁን በደራሲነቱ እንዲሁም በጋዜጠኝነቱ የሚያደንቁት ሰው ነው ። ሻለቃ ግርማ ታላላቅ አማካሪዎች ነበሯቸው እነ አፈወርቅ ተክሌ እነ ፀጋዬ ገብረመድህን እነ አቶ ተክለፃዲቅ መኩሪያን የመሠሉ ። አሁንም ድረስ ከእነርሱ ጋር ያደርጉት የነበረውን ውይይት የነበራቸውን የሀገር መቆርቆር ስሜት በመልካም የሚያስታውሱት ነው።
ዘመነ ኢህአዴግ
ሻለቃ ግርማ ይልማ በሞስኮ የኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው እያገለገሉ ሳሉ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የደርግ መንግስት ወደቀና አዲሱ የኢሕአዴግ መንግስት ሥልጣን ያዘ። ኢህአዴግም በየሃገራቱ ያሉ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ሁሉ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱም ጥሪ አደረገ። ብዙውን ጊዜ በእርሳቸው ደረጃ ብቻ ሳይሆን ከዚያም ዝቅ ባለ የኃላፊነት ቦታ ያሉ ሁሉ በወጡበት መቅረቱን እንደሚመርጡ የታወቀ ነው። ለወትሮውም ተመላሹ ጥቂት ነበር።
በሚኒስትርነት የሥልጣን መንበር ላይ ቢቆዩም፣ የኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እንደነበሩ ቢታወቅም፣በንጽሕናቸው የሚተማመኑት አምባሳደር ግርማ ይልማ ግን ጥሪውን ተቀብለው ከሞስኮ ወደሃገራቸው ተመለሱ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም በክብር ተቀበላቸው። “ሻለቃ ግርማ ይልማ ጎበዝ አንባቢ ጥሩ ተመልካችና አድማጭ ብዕራቸው ደግሞ የሰላ ነው። ትልቅ አርአያቸው ደግሞ ጓድ መንግስቱ እንደሆኑ ይመሰክራሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ላይ ሳሉ ምንም እንኳ ሚኒስትር ቢሆኑም የዩኒቨርሲቲውን ቅጥር ግቢ ሲረግጡ ራሳቸውን እንደማንኛውም ተማሪ ነበር የሚቆጥሩት። ያደረሳቸውን ሾፌር አሰናብተው ደብተራቸውን ይዘው፣ አስፈላጊም ሲሆን ወንበራቸውን ራሳቸው ተሸክመው እያመጡ ይማሩ ነበር።
ቤተሰባዊ ህይወት
ሻለቃ ግርማ ይልማ ባለትዳርና የሶስት የልጆች አባት ሲሆኑ ከባለቤታቸው ሲስተር አለሚቱ ገዳ ጋር በ1949 ዓም የሶስተኛ ክፍል ተማሪ ሳሉ ነበር የሚተዋወቁት። ከዚህ ጀምሮ እስከ 1963 ዓም ድረስ ለ14 ዓመታት ወዳጅ ሆነው ቆይተዋል። በኋላም በ1963 ዓም በትዳር ተሳስረዋል። አሁንም በትዳር 52 ዓመታትን በፍቅርና በመተሳሰብ እየኖሩ ይገኛሉ። የመጀመሪያ ልጃቸው ዘየደ ግርማ ሁለተኛ ልጃቸው ትዕግስት ግርማ የመጨረሻ ልጃቸው ደግሞ ንቢቱ ግርማ ይሰኛሉ። ልጆቹ የተማሩት በራሽያ ነበር። ሻለቃ ግርማ ይልማ አሁን ላይ ኑሯቸውን ያደረጉት በአሜሪካን ሃገር ሲያትል ሲሆን ከኢትዮጵያ የወጡት በዲቪ ነበር።
ሻለቃ ግርማ ምንም እንኳ ከሃገራቸው የመውጣት ፍላጎት ባይኖራቸውም በጡረታ ከተገለሉ በኋላ ምንም አይነት ስራን ባለማግኘታቸው ስራ ለመቀጠር በርካታ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ሊሳካላቸው አልቻለምና ተስፋ በመቁረጥ ውስጥ ሳሉ እመቤት እንዳለ የምትባል የባለቤታቸው የወንድም ልጅ በሞላችላቸው የዲቪ ሎተሪለአላማ ነውና አንዷን ልጃቸውን ይዘው ወደ አሜሪካን ሃገር ተጓዙ። ባለቤታቸው ከጥቂት ዓመታት በኋላ ተከተሏቸውና አብረው መኖር ጀመሩ።
ሻለቃ ግርማ ይልማ “ቡልቡላ ዘመርካቶ” “ዜግነት ክብሬ” ” ዘላለም ኢትዮጵያ” በሚሉ የብእር ስሞች እነ አሸናፊ ዘደቡብና ታደሰ ሙሉነህ በሚፅፉበት ዘመን ሁሉ የሚፅፉት በእጃቸው ነበር። ዛሬም ድረስ ሲፅፉ ከታይፕ ይልቅ እጃቸውን ይመርጣሉ። ሻለቃ ግርማ ይልማ አሁን ካሉበት አሜሪካን ሃገር ሆነው በርካታ የትርጉም ሰራዎችን ሰርተዋል። አሁንም በመስራት ላይ ናቸው። ፅሁፎቹንም ወደ ህትመት ለማምጣትም በዝግጅት ላይ ይገኛሉ። ሻለቃ ግርማ ይልማ ለሃገራችን ኢትዮጵያ ላበረከቱት አስተዋፅኦ ሁሉ ክብርና ምስጋና አለን። ረጅም እድሜንም እንመኛለን።
የፀሀፊ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ ምስክርነት
ከሻለቃ ግርማ ይልማ ጋር የምንተዋወቀው እኔ ከአውሮፓ ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለስኩ ነበር። ዘመኑ የአብዮት ነበርና በውጭ ሃገር በትምህርት ላይ ለነበርነው ሁሉ የጮሀችሁለት አብዮት ፈንድቷልና ወደሃገራችሁ ተመልሳችሁ የሃገራችሁን ኪነ ጥበብ አሳድጉ የሚል ጥሪ በዘመኑ የባህል ቋሚ ተጠሪ በነበረው ጋሽ ፀጋዬ ገብረመድህን የቀረበን ጥሪ ተከትዬ እንደመጣሁ ለመጀመሪያ ግዜ ያገኘኋቸው ሻለቃ ግርማን ነበር።
ሻለቃ ግርማ በወቅቱ ይመሩት የነበረው የማስታወቂያ ሚኒስቴርን ሲሆን እኔ ደግሞ ስራ የጀመርኩት ባህል ሚኒስቴር ውስጥ ነበር። ባህል ሚኒስቴር የሚተዳደረው በሻለቃ ግርማ ስር ስለነበር መልካም ቅርርብ ነበረን። ሻለቃ ግርማ ሚኒስቴር እንደመሆናቸው በባህልና ኪነጥበብ ዙሪያ ለሚያጋጥሙን ጉዳዮች አማካሪያችን ነበሩ። ሻለቃ ግርማን ሳውቃቸው የወታደር መንፈስ ያልተላበሱ ። ከሚገባው በላይ ታጋሽ የሆኑ። ባልተረጋጋች ሃገር ውስጥ ፍፁም የተረጋጋ ማንነት ያላቸው። ለሰው ልጅ ከፍተኛ ፍቅርና አክብሮት የሚቸሩ ። በጣም በጥንቃቄ የሚጓዙ ሰው ናቸው።
በናይጄሪያ በተካሄደው የመላው አፍሪካ የባህል ፌስቲቫል ላይ እኔ በወቅቱ የባህል ሚኒስተርና የትያትር ጥበባት ድርጅት ሃላፊ እንደመሆኔ ሁለት ቡድኖችን ይዤ ወደ ናይጄሪያ በሄድኩበት ወቅቱ የተሳካ ስራን ሰርተን እንድንመለስ ትልቁን አስተዋፅኦ ያበረከቱት ሻለቃ ግርማ ነበሩ። ይህን ያደረጉት ደግሞ ገና የደርግ ፅ/ቤት አባል ሳሉ ነበር። የኢሰፓ ሪዮታለም መምሪያ ባዘጋጀው የኪነጥበብ ጉዞ ላይም በኮሚቴነት: በአስተባባሪነትና በአዘጋጅነት ታላቅ ተሳትፎ እንደነበራቸው አስታውሳለሁ።
ሻለቃ ግርማ ደፋር ። የማይሆንን አይሆንም የሚሆንን ይሆናል ለማለት የማይወላውሉ ላመኑበት ሁሉ እስከጥግ የሚታገሉ ሰው ናቸው። በርካታ ለሃገር የሚጠቅሙ ጉዳዮችን እያከናወኑ እንኳ ማንም እንዲያውቃቸው አይፈልጉም። ይህ ደግሞ የምደነቅበት ሌላው ባህሪያቸው ነው። ሻለቃ ግርማ በጣም ታታሪና ትጉህ የነበሩ። በዘመኑ ውስብስብ የነበረውን የባህል ሚኒስተርነትን ስራ ኮሽ ሳይል ለዘመናት የመሩ ብርቱ ሰው ናቸው።
በራሺያ የኢትዮጵያ የሙሉ ስልጣን አምባሳደር በሆኑበት ዘመን ወደሩሲያ ሄደው የሚማሩ ተማሪዎች ባህሪ እጅግ አስቸጋሪ ቢሆንም እርሳቸው ግን አምባሳደር ብቻ ሳይሆኑ ቤተሰብም ጭምር ሆነው እየረዱ የሃገር ፍቅር እንዲያድርባቸው እያደረጉ የነበሩ ትልቅ ሰው ናቸው። ኢህአዴግ ሲገባ ምንም አይነት እስርም ሆነ እንግልት ካልደረሰባቸው ሰዎች መካከል ሻለቃ ግርማ አንዱ ነበሩ። ለዚህ ትልቁ ምክንያት ደግሞ በወቅቱ ይሰሩት የነበረው ሃገራዊ ስራ ስለነበር ነው። ከሙስና ነፃ የነበሩ በመሆናቸውና በሃገር ፍቅር ስሜታቸው የሚመሠከርላቸው ሰው ስለነበሩ ነው። ሻለቃ ግርማ ለሃገር ብዙ ለፍተው ግን ራሳቸውን ደብቀው የሚኖሩ ሰው ቢሆኑም ተወዳጅ ሚዲያ ግን ለሃገር ያበረከቱትን አስተዋፅኦ ለህዝብ ሊያስተዋውቅ ፈልጎ ስላገኛቸው ከፍተኛ ክብር አለኝ ። አመሠግናለሁ።
መዝጊያ
ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የመዝገበ-አእምሮ የቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡ በየዘመናቱ ጥሩ አለቆች ይፈጠራሉ፡፡ በየዘመናቱ ደግሞ ስማቸው ሁሌም በመልካም የሚነሱ ትልልቅ የስራ መሪዎች ይኖራሉ፡፡ የዚህ የመዝገበ-አእምሮ ዋና ግብ እና አላማ በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ አስተዋጽኦ ያበረከቱ በተለይ የማይረሳ አሻራ ያኖሩ ወሳኝ ሰዎችን ማስታወስ ነው፡፡ ሰዎቹ ጋዜጠኛ ወይም ቴአትረኛ አሊያ ደራሲ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በመሪነት የስራ ድርሻ ላይ ካሉ የሁሉም የተጠቀሱት ከያኒዎች አለቃ ይሆናሉ፡፡ ሻለቃ ግርማ ይልማ በደርግ ዘመን የነበራቸው ስልጣን ደግሞ የሀገሪቱን የመረጃ እና የመዝናኛ ዘርፍን መምራት ነው፡፡ ሻለቃ ግርማ በብዙዎች ዘንድ ስራ ወዳድ እና አርቆ አስተዋይ የስራ መሪ ለመሆናቸው በስፋት ይመሰከር ላቸዋል፡፡ በጊዜው በደርግ ዘመን በተለይ በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ እንዲህ አይነት ከፍተኛ የስልጣን ማማ ላይ መውጣት ፈታኝ ቢሆንም ሻለቃ ግርማ ግን በሁሉ ተመስግነው ዛሬም ትውልድ እያመሰገናቸው ይገኛል፡፡
ሻለቃ ግርማ ይልማ ብእር ከወረቀት ጋር አዋህዶ ለመጻፍ ማንም አይቀድማቸውም፡፡ ይህም ውስጣቸው ያለ ጥሪ ነው፡፡ በአሁኑ ሰአት በሲያትል ነዋሪነታቸውን ያደረጉት ሻለቃ ግርማ ከመጻፍ እና ከማንበብ ወደ ኃላ አላሉም- ማንበብ ከፍተኛ ርካታ ይሰጠኛል ብለውናል፡፡ እና እንዲህ አይነት የስራ መሪ በደርግ ዘመን ነበር፡፡ ሁሌ ሰዎችን ከዘመኑ ፖለቲካዊ እሳቤ ጋር ብቻ ማቆራኘት አያስፈልግም፡፡ ይልቁንም በተሰጣቸው የስራ ሃላፊነት ምን ሰሩ ብሎ በመስፈርቱ መሰረት መመዘኑ የተሻለ ነው እንላለን፡፡ እንደ ሻለቃ ግርማ ይልማ አይነት በ1970ዎቹ ስመጥር ባለስልጣን የሆነ ሰው ታሪኩ ሲነገር ዘመንን ጥርት አድ ርጎ ማየት ይቻላል፡፡ የእኛ የሰናጆቹም ግብ ይህና ይህ ብቻ ነው፡፡ አንድን ሰው የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ይግባ ዋናው የሚጠየቀው በተመደበበት ስፍራ ጥሩና አርአያ የሚያደርገው ስራ ሰርቷል ወይ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ሻለቃ ግርማ ሁሉም በአንድ ድምጽ የተስማማባቸው ሰው ስለሆኑ የእርሳቸውን የህይወት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመሰነድ በመቻላችን ታላቅ የመንፈስ ርካታ ይሰማናል፡፡ እኛም ለእኒህ ጉምቱ ሰው መልካሙን ሁሉ ተመኘን፡፡ ይህ ጽሁፍ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ እና በጋዜጠኛ ዘቢባ ሁሴን የተጠናከረ ሲሆን በተወዳጅ ሚድያ ዲጂታል ሚድያዎች ላይ የሚቀመጥ ነው፡፡ ይህን የሻለቃ ግርማን ታሪክ ስንሰራ ትብብር ላደረጉልን ለልጃቸው ለዘየደ ግርማ እና ለቴዎድሮስ ንዋይ ምስጋናችንን ማቅረብ እንወዳለን፡፡
What an amazing individual. Honest humble and caring.i have thousands of stories about him. But he is real.