ሀይሉ ወንድሙ

ሀይሉ ወንድሙ

ከካሜራ ባለሞያ እስከ ምክትል ሥራ አስኪያጅነት (Deputy Managing Editor) የዘለቀው ፎቶ‐ጋዜጠኛ ሀይሉ ወንድሙ።

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡
በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 200 የሚድያ ፤ የስነጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል የፎቶ ባለሙያ ሀይሉ ወንድሙ ይገኝበታል፡፡ ሀይሉ በፎርቹን ጋዜጣ ላይ ለ 16 አመታት በፎቶ ባለሙያነት እና በምክትል ማኔጂንግ ኤዲተርነት ያገለገለ ሲሆን በሁለ-ገብነቱ ብዙዎች አድናቆት ይቸሩታል፡፡ በአሁኑ ሰአት በኦስትሪያ የሚገኘው ሀይሉ ወንድሙ ለጋዜጣ ስራ ጥልቅ ፍቅር እንዳለው ይገልጻል፡፡ እዝራ እጅጉ እና ሞሊቶ ኤሊያስ የህይወት ታሪኩን ሰንደውታል፡፡

ትውልድ እና እድገት

ህዳር 13 1969 ዓ.ም ነበር በአዲስ አበባ ከተማ ኦሎምፒያ አካባቢ የተወለደው። ሚሊቴሪ ቤት የነበሩት አባቱ መቶ አለቃ ወንድሙ ወርቅነህ ገና በልጅነቱ ነበር ለሀገራቸው መስዋዕት ሆነው ያጣቸው። ከአባቱ ህልፈት በኋላም እሱን እና ታላላቅ ሁለት እህቶቹን እናቱ ወ/ሮ ውጋገን አበበ ብዙ መስዋትነት ከፍለው እንዳሳደጓቸው ሀይሉ ይመሰክራል። ከ 1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል በነፃነት ብርሃን እንዲሁም ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል በቦሌ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሮ አጠናቋል። በልጅነቱ ቴክኒክ ነክ ነገሮች ቀልቡን የሚስበው እና የኤሌክትሪክ ሽቦ ፣ ባትሪ እና አምፖል ነፍሱን የሚያስደስቱ የልጅነት ቁሶቹ ነበሩ።

ካሜራ ጋር የተቆራኘበት አጋጣሚ

ሀይሉ የ12ኛ ክፍል የማትሪክ ፈተና ከወሰደ በኋላ የተለያዩ ዝግጅቶችን እና ሠርጎች ላይ ቪዲዮና ፎቶግራፎችን ያነሳ ለነበረ የቅርብ ወዳጁ ረዳት በመሆን መብራትና ካሜራ በመያዝ ነበር የካሜራን ዱካ መከተል የጀመረው። ሥራውን እያወቀው ሲመጣ ከረዳትነት ወደ ራሱን ችሎ መስራት አደገ። ቀስ በቀስም የሙያው ፍቅር ወደ ውስጡ ገባ። በልምድ እየጎለበተ የነበረውን የሙያውን ፍቅር በትምህርት ማዳበር አለብኝ ብሎ ስላመነም የካሜራ ሙያን ለመማር ወሰነ። ነገር ግን በወቅቱ አሁን ላይ እንዳሉ የካሜራ ሙያ ማሰልጠኛ ማዕከላት እምብዛም አልነበሩምና ያሰበውን የሙያ ስልጠና ለማግኘት ቀላል አልነበረም።

ይሁንና አንዲት መልካም እድል ከፊቱ ቀረበች። በወቅቱም ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት አጠገብ በምትገኝ መዋእለ-ህፃናት ግቢ ውስጥ በምሽት ክፍለ- ጊዜ የፎቶ እና የቪዲዮ ሙያ ማሰልጠኛ ተከፍቶ ነበር። ይህም ማሰልጠኛ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለረጅም ዓመታት በካሜራ ባለሙያነት ያገለገሉና ጡረታ የወጡ አቶ ጨሻ አንደቦ የተባሉ ግለሰብ ሠልጣኞችን የካሜራ ጥበብ ለማስተማር የከፈቱት ማሰልጠኛ ነበር። ሀይሉም 1990 ዓ.ም ወደዚህ ማሰልጠኛ ተቋም በመቀላቀል በፎቶግራፍ እና በቪዲዮ በዲፕሎማ መርሃ ግብር ተምሮ የሁለተኛ ዙር ሰልጣኝ ሆኖ በጥሩ ውጤት ማጠናቀቅ ቻለ።

የካሜራ ስራ ጅማሮ

የካሜራ ሙያ ትምህርት ሳይማር በፊት መብራትና ካሜራ በመያዝ ያገለግል የነበረው ሀይሉ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ሙሉ ሰዓቱን ለሙያው በመስጠት እና በዘርፉ ሰዎችን በመተዋወቅ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራው ዓለም ገባ።

ወደ ጋዜጣ ዓለም የገባበት አጋጣሚ

በዚሁ በካሜራ ባለሙያነት ሥራ ላይ እንዳለ አንድ ዕለተ- ሠንበት ታምራት ነገራ ከሚባል የሰፈሩ ልጅ እና አብሮአደጉ ጋር ይገናኛል። በዚያን ወቅት ታምራት ነገራ ካፒታል በሚባል በእንግሊዝኛ ቋንቋ ለአንባቢያን ይቀርብ ለነበረ ጋዜጣ አንባቢ ፈላጊ (Subscription sales Agent) ሆኖ ይሰራ ነበር። ለሀይሉም ያለበትን የስራ ሁኔታ በመግለፅ አብሮት በኮሚሽን ሰራተኛነት እንዲሰራ ጠየቀው። ገና በለጋ ዕድሜው ለስራ ታታሪ የነበረው ሀይሉም የተሰጠውን ዕድል ወደኋላ ሳይል የካፒታል የሽያጭ ቡድን አባላትን ተቀላቀለ። በወቅቱ ጋዜጣው እምብዛም የማይታወቅ ስለነበር ወደ ተለያዩ ቢሮዎች በማቅናት አንባቢዎችን የመፈለግ ስራውን በትጋት ያከናውን ነበር። ከሰኞ እስከ ዓርብ ይህንን ይሥራ እንጂ እሁድ እና ቅዳሜን የካሜራ ሙያውን ሳይተው ጎን ለጎን ያስኬደው ነበር።

ከካፒታል ወደ ፎርቹን

ሀይሉ ወንድሙ ፣በካፒታል ጋዜጣ ውስጥ ጥቂት ጊዜ እንዳገለገለ በጋዜጣው ሸሪኮች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት የፎርቹን ውልደት ዕውን ሆነና ሀይሉም ከቀድሞ የሥራ ባልደረቦቹ ጋር በመሆን በተመሳሳይ የሥራ ዘርፍ (sales) በቋሚ ሰራተኛነት ተቀጥሮ የፎርቹን ጋዜጣ አሳታሚ በሆነ ድርጅት ውስጥ ማገልገል ጀመረ። በተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወረም የጋዜጣውን አንባቢያን ማፈላለግ የዘወትር ስራው ሆነ።

የህይወት መስመር ቀያሪዋ አስገራሚ አጋጣሚ

ሀይሉ በፎርቹን ጋዜጣ በአንባቢ አሳሽነት ሥራ ላይ እንዳለ ነበር ለጋዜጣው በካሜራ ባለሙያነት ታገለግል የነበረች ልጅ በአንዷ ዕለት ከስራ የቀረችው። በድንገተኛ የካሜራ ባለሞያዋ ከስራ መቅረት አጣብቂኝ ውስጥ የገቡት የጋዜጣው አዘጋጆች ሀይሉን ጨምሮ ቢሮ ውስጥ በሌላ ስራ ላይ ለነበሩት ሰራተኞች ፎቶ በማንሳት እንዲተባበሯቸው እርዳታ ይጠይቃሉ። ሀይሉ ከሁሉም ቀድሞ እኔ ልሄድ ባይልም አብረውት ይሰሩ የነበሩ የስራ ጓደኞቹ ግን «ሀይሉ ይሄድ» ብለው ጮክ ብለው ተናገሩ። የቅርብ ጓደኞቹ የካሜራ ችሎታውን ይወቁ እንጂ የጋዜጣ ዝግጅት ክፍሉ የካሜራ ትምህርት ስለመማሩም ሆነ ስለብቃቱ የሚያውቀው ነገር አልነበረም። እርሱም አልተናገረም።

ለካሜራ ጥልቅ ፍቅር የነበረው ሀይሉ በጋዜጣ ዝግጅት ክፍሉ እሳቤ “ከተበላሸም ይበላሽ”በሚል ስሜት የተሰጠውን ዕድል ሳያንገራገር በመቀበል በዕለቱ ጥሩ የሚባሉ ፎቶዎችን ማንሳት ቻለ። ካነሳቸው ፎቶዎች መሃል ለህትመት ብቁ ናቸው የሚላቸውን ፎቶዎች አሳጥቦ የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ቢሮ አቀረበ። ባልተጠበቀው ብቃቱ የተገረመው የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ሀይሉ ያነሳቸውን ፎቶዎች ጠረጴዛው ላይ ደርድሮ «እንዴት በአንድ ቀን እንዲህ ዓይነት የጋዜጣን መስፈርት ያሟሉ ፎቶዎች ታነሳለህ? ወይስ ልምዱ ከዚህ በፊት አለህ?» ብሎ የማፋጠጥ ያህል ጠየቀው። ያኔ ሀይሉ ስለ ራሱም ሆነ ስለሙያው ተናገረ። የካሜራ ትምህርት መማሩንና ልምዱንም ከዛም አልፎ ጠረጴዛው ላይ ያሉትን ብቁ የጋዜጣ ፎቶዎችን የተመለከተው አዘጋጅ ሀይሉ ዲፓርትመንት ቀይሮ ከኤዲቶሪያል ቡድኑ ጋር አብሮ እንዲሰራ ዕድሉን ሰጠው።

ከአንባቢ ፈላጊነት ወደ ካሜራ ማንነት

በጋዜጣው ኃላፊዎች አይን ውስጥ በዚያች አጋጣሚ መግባት የቻለው ሀይሉ ከአንባቢ ፈላጊነት ወደ ፎቶግራፍ አንሺነት መሸጋገር ቻለ። ከዚህም በኋላ በተለያዩ ትላልቅ ስብሰባዎች እና ቃለ- ምልልሶች ላይ ተመራጭ የፎቶ ግራፍ ባለሙያ ሆነ። ሀይሉ ዛሬ ላይ ሆኖ ወደኋላ ሲያስታውስ የዛሬ ሀያ ዓመት ገደማ ብዙ የመንግስት ባለስልጣናት እና አሉ የተባሉ የከተማው ነጋዴዎች በሙስና ክስ ወህኒ የወረዱበትን ጊዜ «የማይረሳ የሥራ ዘመን» ይለዋል። በወቅቱ ዕለት በዕለት እየተከታተለ የተከሳሾችን የፍርድ ቤት ውሎአቸውን በፎቶ ይዘግብ ነበር። ያን ወቅት እሁድ ደርሶ ፎርቹን ምን ፎቶ ይዞ ሊወጣ ነው? የሚባልበት ዘመን ነበር። ሀይሉ በካሜራ ባለሞያነት ህይወቱ 1997 ዓ.ም ሀገር አቀፍ ምርጫ 97ትን ተከትለው የተከሰቱ ሁነቶችን የመሳሰሉ ታሪካዊ ክስተቶችን በፎቶግራፍ በማስቀረት እና ለጋዜጣው ፊት ገፅነት በማዋል በስራው ተወዳጅነትን ማትረፍ ችሏል።

አድማሱን እና ኃላፊነትን ማስፋት

የሥራ ልምድን የተማርኩት ሳይሆን የወረስኩት ከዋና ኤዲተሬ ከታምራት ገብረ ጊዮርጊስ ነው ብሎ ምስክርነት የሚሰጠው ሀይሉ ሁሌም ስለቀድሞ ኤዲተሩ የጋዜጠኝነት ብቃት አውርቶ አይጠግብም። ጋዜጠኝነት ሥራ ሳይሆን የህይወት መንገድ ነው (Life style) ነው ብሎ ያምናል። ሀይሉ እንደተለመደው የፎቶግራፍ ስራ አሳይመንት ከሪፖርት አድራጊዎቹ የሚቀበል ሳይሆን ራሱ በኤዲቶሪያል ስብሰባ ላይ ተካፋይ ሆኖ ስለሚሰሩት ዜናዎችም ሆነ የፊቸር ታሪኮች ታሪክ አጠንጥኖ ተረድቶ ከመረጃው መነሻ ጀምሮ ታሪኮችን በማጎልበት እና ለታሪኩ የሚመጥን ገላጭ ፎቶግራፎችን በማዘጋጀት ወደ ገፅ ዲዛይን በመተርጎም ጋዜጣው ተጀምሮ ለህትመት እስኪበቃ ድረስ በየፈርጁ አሻራውን ይጥላል። ይህንን ሁኔታ ያለማቋረጥ ከ10ዓመታት በላይ አከናውኖታል። ሀይሉ ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር «እራሴን እጅግ እድለኛ አድርጌ ቆጥረዋለሁ ምክንያቱም ሰለሚያገኙት ደሞዝ ሳይሆን ለአንባቢ ስለሚያበረክቱት ጋዜጣ ከሚያስቡ የስራ ባልደረቦች ጋር መስራቴ የስራውን ክብደት እንዳይሰማኝ ሆኜ ስለኖርኩ ዕድለኝነቴ ዘወትር ይሰማኛል» ይላል።

በጋዜጣው ካሜራ ባለሞያነት የተዋጣለት ሀይሉ ታዲያ አንድ ነገር ላይ ሀሳቡ ተሳበ። ይህም በውጭ ሀገር የሚታተሙ ጋዜጣዎች ከሀገር ውስጥ ጋዜጣዎች አንፃር ለአይን የሚስቡ፣ያልደበዘዙ እና ውበት ያላቸው ሲሆኑ በአንፃሩ እኛ ሀገር የሚታተሙት ጋዜጣዎች ግን ቀለማቸው የጠቆሩ እና የደበዘዙ በመሆናቸው ሀይሉ ውስጥ ቅናት አሳደረበት። የውጭ ጋዜጣዎችን ሚስጥር ለማወቅ ፍላጎት ያደረበት ሀይሉ የተለያዩ ፅሁፎችን ማንበብ እና መመርመር ጀመረ። ራሱን በማስተማር በነበረው መሠረታዊ የኮምፒውተር እውቀትና ልምድ በመጠቀምም በውጭ ሀገር ጋዜጣዎች ላይ ሲያያቸው እና ሲቀናባቸው የነበሩትን አይነት ጥራት ያለው ፎቶ (Photoshop screen print) በመጠቀም ጋዜጣው ላይ የሚወጡ ምስሎችን ለብቻቸው በማተም እና ለህትመት ለመላክ በተዘጋጀው ገፅ ላይ በልኩ ቆርጦ በመለጠፍ ጥራት ያላቸውን ፎቶዎች ለመጀመሪያ ጊዜ አሳትሞ ለህዝብ ማድረስ ችሏል። ከዚህም በኋላ ከፎቶ ግራፍ አንሺነት በተጨማሪ የግራፊክስ ባለሙያ በመሆን የሚያነሳቸውን ፎቶዎችን ጨምሮ የጋዜጣው ማስታወቂያዎችንም ህትመት ጥራት እንዲኖራቸው በሀይሉ ዴስክ ላይ ማለፍ ጀመሩ። ይህ በእንዲህ እንደቀጠለ በአንድ አጋጣሚ በፎርቹን ጋዜጣ የገፅ ዲዛይን ይሰራ የነበረው ሰው በወቅቱ ስራውን በመልቀቁ ሀይሉ ኃላፊነቱን በማስፋት የጋዜጣውን የገፅ ንድፍ ሥራን ከፎቶ ግራፍ እና ግራፊክስ ጋር በማያያዝ መስራት ችሏል።

የማይረሱ አቀበቶች

አንድ ቀን ጠዋት የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ሀይሉን ቢሮ ይጠራውና አንድ ሥራ ያዘዋል «በስተሰሜን የአዲስአበባ መውጫ አካባቢ አንድ ትልቅ ሎቤድ (ተጎታች የጭነት መኪና) አቅጣጫውን ወደ ሰሜን አድርጎ እየሄደ ነው። ይህ መኪና የያዘው ጭነት በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ከሀገሪቱ የድልድይ አቅም ጋር አይመጣጠንም በሱ ዙሪያ የምንሰራው ዘገባ ስላለ ሎቤዱ ርቆ ሳይሄድ ድረስበትና ፎቶ አንሳው» ተብሎ ይላካል። ሀይሉም ይህንን አሳይመንት ተቀብሎ ካሜራውን ሸክፎ የመስሪያቤቱን መኪና ራሱ እየነዳ የተባለውን ጭነት ፍለጋ ወጣ። ጭነቱ እንዳሰበው በቅርብ ርቀት አልተገኘም። ለተሰጠው አሳይመንት ድርድር የማያውቀው ሀይሉ የመኪናውን ቤንዚን ሞልቶ ካላገኘው ላይመለስ ቆርጦ ሱሉልታን አልፎ ሽቅብ ወደ ሰሜን ይነዳ ጀመር።
በየመንገዱ ላይ እየቆመ የአካባቢ ነዋሪዎችን እየጠየቀ መንገዱን ሳያቆም ጫንጮ እና መልከጡሪን አልፎ ደብረ ሊባኖስ ደረሰ።

ይህን ያህል ርቆም ሀይሉ ተስፋ አልቆረጠም ከፊት ለፊቱ ያሉትን ከተሞች እያለፈ ጎአፂኦን አልፎ ቁልቁል ወደ አባይ ድልድይ መንደርደሩን ተያያዘው። እንደ እባብ የተጥመዘመዘውን የአባይ ቁልቁለትን እንደጨረሰ ተፈላጊው ሎቤድ በጥበቃ ሀይሎች የአባይን ድልድይ አትሻገርም ተብሎ ዓባይ በረሃ ውስጥ ቆሞ ተገኛኙ። ያኔ ሀይሉ በረጅሙ ተነፈሰ፡፡ ከስድስ ሠዓታት በላይ በአሰሳ ያደከመውን ታሪካዊ ጭነት በካሜራው እያገላበጠ አንስቶ ለታሪክ አስቀመጠው፡፡ ይህ ከባድ ጭነት የተከዜ ሀይል ማመንጫ ተርባይን አንዱ አካል ነበር። ሀይሉ እንዲህ ያሉ የሥራ ዲሲፕሊንን የሚፈልጉ ስራዎችን እየሰራ ከስሩ ያሉ ተተኪ ፎቶግራፈሮችንም እያሰራ ለ16 ዓመታት የጋዜጣ አንባቢዎችን ሲያገለግል ኖሯል።

ከፎቶ ግራፍ ሙያ ወደ ሚዲያ አመራርነት

ሀይሉ ከፎቶ ግራፍ አንሺነት ባለፈ በጥልቀት ወደ ሚዲያው በመግባት የተለያዩ ኃላፊነቶችን በመረከብ እና በስሩ ጀማሪ ፎቶግራፍ አንሺዎችን በመቅጠር፣በማሰልጠን እንዲሁም ልምዱን በማካፈል ነበር ትልቅ ሚናን መጫወት የጀመረው።

ፎርቹን ጋዜጣ ለ16 አመታት

ለ16 አመታት በፎርቹን ያሳለፈው ሀይሉ በነበረው ትጋት እና የስራ ፍቅር ፈጣን እድገቶችን ማግኘት ችሏል።በመጀመሪያ የፎቶ ግራፍ ኤዲተር በመቀጠልም ሲኒየር ኤዲተር በመሆን ከማገልገሉም በላይ፤ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሀሳቦችን ቅርፅ በማስያዝ፣ታሪኮች በመገንባትና በማዳበር በሚዲያ አመራር ሂደት ባልተለመደ መልኩ የካሜራ ባለሞያ ሆኖ በኤዲቶሪያል አባልነት በመሳተፍ እና ይዘት ላይ ሀሳብ በማዋጣት የድርብ ሙያዎች ባለቤት መሆኑን በተግባር ማሳየት ችሏል።

በተለያዩ የሚዲያ ዘርፍ ሙያዎች በልምድ ራሱን ያዳበረው ሀይሉ በኋላም የፎርቹን ጋዜጣ ምክትል ኤዲተር (Deputy Managing Editor) እስከመሆን በመድረስ በከፍተኛ ኃላፊነት ማገልገል ችሏል። ከጀማሪ የፎቶግራፍ ባለሞያነት ጀምሮ በየደረጃው የተለያዩ ሀላፊነቶች ላይ ቢቀመጥም የፎቶግራፍ ሙያውን ያልተወው ሀይሉ ታሪካዊ ክስተቶችን በፎቶ ለታሪክ በማስቀመጥ በሚዲያው ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከተ ኢትዮጵያዊ ነው።

መዝጊያ

ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የመዝገበ-አእምሮ ቦርድ አባላትን አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡ የፎቶግራፍ ሙያ በህትመት ጋዜጠኝነት ስራ ውስጥ ግንባር ቀደም የተከበረ ሙያ ነው፡፡ አንድ የህትመት ውጤት ላይ ዜናውን አይቶ አብሮ የወጣውን ምስል አለማየት ከቶ አይቻልም፡፡ እዚህ ጋር የፎቶግራፈሮችን ሚና አጉልቶ ማስቀመጥ ግድ ይላል፡፡ ለጋዜጣ ዜና ያለ ምስል ሊታመን አይችሉም፡፡ ሀይሉ ወንድሙ ፎርቹን ላይ ሲሰራ የበለጠ ዜናው ተአማኒ እንዲሆን ገላጭ ምስሎችን እያነሳ ሲያገለግል ቆይቷል፡፡16 አመታትን በዘለቀ የፎርቹን ቆይታው ሀይሉ ፕሮፌሽናሊዝም በተላበሰ የሚድያ ሰውነት አሳልፏል፡፡ ፎርቹን በፊት ለፊት ገጹ ገራሚ እና በተለየ አንግል የተነሱ ፎቶግራፎች ነበሩት ከተባለ ከስራው አጠገብ ደግሞ ሀይሉ አለ፡፡ ሀይሉ ስለሚያነሳው ጉዳይ ቀድሞ ኤዲቶሪያል ገብቶ ግንዛቤ ይወስዳል፡፡ ከዚያም የሚጠበቅበት ማሰብ ብቻ ነው፡፡

እንዲህ አይነት ይዘት አውቀው ፎቶ አለው፡፡ ለስራው አንዱ ያለ አንዱ ሊሳካላቸው አይችልም፡፡ በተለይ ተአማኒ የጋዜጣ ዜና ለማዘጋጀት እውቀት የበራለት ታጋይ እና ታታሪ ፎቶግራፈር የግድ መፈጠር አለበት፡፡ ሀይሉ ሙያውን ይወዳል ብቻ ሳይሆን መለስ ብለን ከ16 አመት ወዲህ የነበሩ የፎቶ ስራዎቹን ስናይ ከግል ጋዜጦች አንጻር የማይረሳ አሻራ ማኖሩን ማስተዋል ይቻላል፡፡ በእኛ እምነት በየዘመኑ ያሉ በጋዜጣ ስራ የነበሩ ባለሙያዎች ስለ አሻራቸው ብዙም አልተነገረም፡፡ የግድ እንዲጻፍላቸው የሮም ግንብን እስኪገነቡ አንጠብቅም፡፡ የሮም ግንብን ለመገንባት እንዲችሉ ግን ዛሬ ጅምር መንገዳቸውን እናቀናለን-እናበረታለን- ታሪካቸውንም ለጥናት ያግዝ ዘንድ እንሰንዳለን፡፡ ይህች ሀገር የወለደችው ልጅ አጠገቧ እያለ ለውጭ ሀገር ሰው የታዋቂነትን ካባ መደረብ የለባትም፡፡ እስቲ አንዱ የሌላውን ታሪክ ይሰንድ፡፡ አውነት ለመናገር አያውቁንም፡፡ ካላወቁን ደግሞ የተሰነደ ታሪካችንን ይመልከቱ፡፡ ሀይሉ ወንድሙ እንግዲህ ከበርካታ የሚድያ እና የጥበብ ሰዎች ጋር ታሪኩ ተሰንዷል? ምን ይል ይሆን? የሰራ ሲሰነድ ያልሰራ ደግሞ አሻራ እስኪያኖር ድረስ ካለበት ይቀመጣል፡፡ ሀይሉ በአሁኑ ሰአት በአውሮፓዊት ሀገር ኦስትሪያ ይገኛል፡፡ ይህ የስነዳ ስራ በጋዜጠኞቹ እዝራ እጅጉ እና በሞሊቶ ኤሊያስ የተከናወነ ሲሆን ዛሬ መስከረም 3 2016 በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ተጫነ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *