ዶክተር ተሻለ አሰፋ

ዶክተር ተሻለ አሰፋ

ሊሻል ብቅ ያለው ተሻለ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 150 የሚድያ ፤ የስነ-ጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡

በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል ዶክተር ተሻለ አሰፋ አንዱ ነው፡፡ ዶክተር ተሻለ አሰፋ በ1984 ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቴአትር ጥበባት ተመርቆ ባለፉት 31 አመታት በመምህርነት ፤ በቴአትር አዘጋጅነት ፤ በደራሲነት በተዋናይነት ያገለገለ ብዙዎች የመሰከሩለት ባለሙያ ነው፡፡ ዶክተር ተሻለ አሰፋ የበአሉ ግርማን ህይወት ወደ መድረክ በመቀየር ጥሩ ስራ መድረክ ላይ ለማሳየት የበቃ ነው፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የዶክተር ተሻለን የህይወት ታሪክ ለመስራት ፈቃድ ጠይቆ ዶክተር ተሻለም ሙሉ ፈቃደኝነቱን ሰጥቶን ታሪኩ እንደሚከተለው ተሰንዷል፡፡ እዝራ እጅጉ እና አማረ ደገፋው ታሪኩን አጠናክረውታል፡፡

በ1964 ዓ.ም.ከሻሸመኔ ወደ ባሌ በሚወስደው መንገድ ከ20 ኪሎ ሜትሮች በኋላ በምትገኝ መንደር ኮፈሌ በኢትዮጵያ የቴአትር ጥበብ የተሻለ ነገር ሊያመጣ ተሻለ አሰፋ ተወለደ። በመጀመሪያና በሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ቤት ቆይታው የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶች ላይ ያለውን ጉብዝና ያየ ማንም ‘መሀንዲስ ወይ ሀኪም ይሆናል’ ብሎ ይወራረድ ይሆናል እንጂ ‘ቴአትረኛ ይሆናል’ ብሎ የሚገምት አይኖርም። የእርሱም የልብ መሻት እንዲያ ነበር፤ ሲሆን ሲሆን የጤና ሳይንስን ቢማር ካልሆነለት ሲቪል ምህንድስናን ቢያጠና ይወድ ነበር።

በ1981 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ሲቀላቀል ግን ወደ ማህበራዊ ሳይንስ ተመደበ። “ለህይወት የቀረበ” ብሎ ቴአትርን መርጦ መማር የጀመረ ቢሆንም የመጀመሪያው ዓመት በተለይ አስቸግሮት እንደነበር ዛሬም አይረሳም። ለማቋረጥ ዳድቶት እንደነበርም ይናገራል። አስቀድሞም ቢሆን ከሰዎች ጋር የተገደበ ግንኙነት የነበረውና ዝምተኛው ተሻለ የክንውን ጥበብና ከሌሎች ሰዎች ጋር ደጋግሞ እንዲነጋገር የሚያደርገውን ጥናት መምረጡ ግር ቢያሰኝም ከሁለተኛ ዓመት የትምህርት ዘመኑ ጀምሮ ይሄው እስከዛሬ ድረስ ተመችቶት በጥበብ ከፍ ብሏል።

ከዩኒቨርሲቲ ከመመረቁ አስቀድሞ ሀገር ፍቅር ቴአትር ውስጥ በተጋባዥ ተዋናይነት ሲሰራ ቆይቶ ከምርቃቱ በኋላ ተወዳድሮ በተቀጠረበት ህፃናትና ወጣቶች ቴአትር አንድ ሳምንት ብቻ ነበር የሰራው። ባህልና ቱሪዝም ያወጣውን ማስታወቂያ ተከትሎ ወደ ጂንካ አቅንቶ በዚያ አንድ ዓመት ከዘጠኝ ወራት ቆየ። በጂንካ ከቴአትር የራቀውን ማህበረሰብ ቴአትር አስተዋውቆ፣ ህፃናትና ወጣቶችን አሰልጥኖ፣ ለሌላ ስራ በቦታው የተገኙ ሰዎችን አስተባብሮ ቴአትር አሰርቶ፣ የመጀመሪያውን አማተር የቴአትር ክበብ መስርቶ ያሳለፋቸውን ሃያ አንድ ወራት ዛሬም ድረስ ይናፍቃቸዋል። በትዝታ ሆኖ ‘ካስተማርኩት የተማርኩት ይበልጣል’ ይላል።

ከጂንካ ቆይታው በኋላ ዲላ ዘልቆ ዓመት ሲቆይ የቴአትር ስልጠና መስጠቱን አላቆመም ነበር። ስልጠና በመስጠቱ መሀል ስለናፍቆቱ ደብዳቤ ወደ ጂንካ ፅፎ እንደነበር ያስታውሳል።ለዓመት እረፍት ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ሳለ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ለባህልና ቴአትር አዳራሽ በወጣ ክፍት መደብ የተመዘገቡትን ለፈተና የሚጠራ ማስታወቂያ አንብቦ ያልተመዘገበውን ልፈተን ብሎ ደጅ ጠና፤ ተፈቀደለት። እድሉን በሚገባ ተጠቅሞ አለፈ። ዝምተኛው ቴአትረኛ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ። በጂንካና ዲላ የተለያዩ ቴአትሮችን ለተመልካች ያደረሰው አበባ ወዳጁ ቴአትረኛ አዲስ አበባ ገባ። ዘውዱ አበጋዝ የተረጎመውን “ቆንጆዎቹ” ለማዘጋጀት በወጣ ውድድር ለመሳተፍ ሲያመለክት ‘ተው’ ያሉትም የሳቁበትም እንደነበሩ ያስታውሳል። ተወዳድሮ አሸነፈና “ቆንጆዎቹ” በአዲስ አበባ መድረክ የመጀመሪያ ቴአትሩ ሆነ። ተመልካች ተሰለፈ፣ አዳራሽ ሞላና የመጀመሪያው ስኬታማ ሆነለት።

ቀጥሎ ወደ ጥናትና ምርምሩ ለማዘንበል ፈልጎ ባህልና ማስታወቂያ ቢሮ ገባ። ቴአትር ቤቶች እየገጠማቸው ስለነበረ የጽሑፍ ድርቅ እና ስለ ባለሙያዎች የእርስ በእርስ ግንኙነት ጠለቅ ያለ ጥናት አጥንቶ የመፍትሄ ሀሳቦችንም አስቀመጠ። በመፍትሄ ሃሳቦቹ ላይ የተመሰረቱ ስልጠናዎችንም ለወጣቶች ሰጠ። በኢትዮጵያ ቴአትር የተሻለ ሁኖ ለመገኘት እየለፋ ያለው ተሻለ ራስ ቴአትር ተፈጥሮ የነበረውን ችግር እንዲቀርፍ ወደዚያው ተላከ። ከውጭ ሁኖ የተነገረውና ውስጥ ሲገባ ያገኘው ችግር አልገጥም ቢለውም የማንም መሳሪያ ከመሆን ይልቅ ከባለሙያዎቹ ጎን ሁኖ ለቴአትር ለፋ። “የአንድ ቀን እስረኞች” የሚል ቴአትር አዘጋጅቶ ቴአትር ቤቱ ተዳከመ ከተባለ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ተመልካች ማሰለፍ ቻለ።

ባለሙያዎች “መልቲ ሚዲያ” የሚሉት ዓይነት የሆነው የአንድ ቀን እስረኞች በሀገራችን በዚህ ዘርፍ የመጀመሪያው እንደሆነ ሲጠየቅ ‘እንዲያ ለማለት ጥናት ይጠይቃል’ የሚል ትህትና ላይ ያርፋል። ቴአትር ለዓይን እንደሚሰራ አጥብቆ የሚሞግተው ተሻለ “መልቲ ሚዲያ”ን “ቅጥልጥል ኮኮቦች”ም ላይ እንደተጠቀመበት አይዘነጋም። ከዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ሀገር ፍቅር ተመልሶ ትወናና ዝግጅት ላይ አተኮረ። በተለይም ትንሿን አዳራሽ ለሙከራዊ ቴአትር(Experimental) ትሁን ብለው ከወዳጆቹ ጋር መከረ። አሁን ለምን እንደቀረ እየቆጨው ከአስታጥቃቸው ይሁን ጋር ራሱ አስታጥቃቸው የፃፈውን ባለ ሁለት ተዋንያን የእንግሊዝኛ Experimental ቴአትር ማቅረባቸውን ያስታውሳል።

ተሻለ (በ Development Studies)፤ MA እና MSc ውን (ማስተርስ ዲግሪውን)፤ PHDውን (ዶክትሬት ዲግሪውን)፤አግኝቷል። እንኳን የመማሪያ ክፍል ውስጥ ሲናገሩና ሲንቀሳቀሱ ያስተምሩኝ ነበር የሚላቸው የቀድሞ መምህሮቹ ፍሰሃ በላይ ይማም እና ነቢዩ ተካልኝ ከፍ ያለ ተፅዕኖ እንዳደረጉበት ይናገራል። በመምህርነት ዘመኑ የቴአትር ትምህርት ክፍል ሀላፊ ሁኖ ለ7 ወራት ካገለገለ በኋላ እርሱ “በቂና ገፊ” በሚላቸው ምክንያት ኋላፊነቱን ሊቀጥል አልቻለም። ሃላፊነቱን ይተው እንጂ ቴአትር ቤቶች ከሰራቸው የላቁ ቴአትሮችን ለትምህርት ቤቱ መድረክ አብቅቷል። ‘ቁጡ ነህ ይሉሃል’ ተብሎ ሲጠየቅ “ለስሜቴ ተገቢውን ምላሽ ስለምሰጥ ጤነኝነት ይሰማኛል” ይላል። ከቁጣ ይልቅ ለመሸለም የፈጠነ መሆኑን ለማስረዳት “ሁሌም በቀኝ እጄ ቀይ አበባ በግራ እጄ የተጠቀለለ ጅራፍ እይዛለሁ” ይላል። ቁጣውን የወከለ ጥቅልሉ ጅራፍ እስኪፈታና ግራ እጁ የቀኙን ያህል ስለማይቀናው ቁጣው የዘገየች ናት። ይሁን እንጂ የተዋናይ ስነ ምግባር ላይ ኮስታራ ነው።

ቴአትር ላይ የበረታው ብርታት ይዞ የሬዲዮ ድራማውም ላይ ብቅ ብሏል። የየኛ ድራማ ላይ አምስቱን ተዋናዮች ከማሰልጠን ጀምሮ እስከ ዝግጅት ተሳትፏል። “ቴአትር ለዓይን ነው የሚሰራው” የሚል መርሁን የሬዲዮ ድራማውም ላይ ይዞት መጥቶ የተሳኩና ለዓይን የተሰሩ ክፍሎችን አስደምጦናል።
(Participatory Action for Development)፤ ትያትርን አንድ የመናገርያ ስልት አድርጎ (መልዕክቶችን ከሚያስተላልፍ ድርጅት ፤ጋርም በመስራት ሙያዊ ሃላፊነቱን ተወጥቷል፡፡ ዶክተር ተሻለ”የአና ማስታወሻ” ትያትርን አዘጋጅቶ በአሁን ሰዓት በብሔራዊ ቴአትር በመታየት ላይ ይገኛል።
ከዚህ ቀደም ከፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር ጋር በመተባበር “የሳቅ ጀምበር” የተሰኘ የውድነህ ክፍሌ ተውኔት አዘጋጅቶ በሀገር ፍቅር ቴአትር አቅርቦአል።

“የኛ” የሬድዮ ድራማ ያዘጋጀሁ DFID (Department For International Development) እና GirlHub ከሚባሉ የውጪ ድርጅቶች ጋር ነው። ዶክተር ተሻለ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ አማካይነት በቅርቡ የሚታተም የተውኔት ዝግጅት መጽሐፍም አለው። ዶክተር ተሻለ ሁል ጊዜ በጥረት ያምን ስለነበር ገና በተማሪነቱ ታሪካዊ እና ብሉይ የኪነጥበብ ስራዎችን በመምረጥ ቴአትሮችን ዳይሬክት ያደርግ ነበር፡፡ከእነዚህም ውስጥ ንጉስ አርማህ ፤ንጉስ ሊር ፤ኦቴሎ ፣ ሀምሌት ይገኙበታል፡፡ ዶክተር ተሻለ አሰፋ ከመምህርነቱ እና ከዳይሬክተርነቱ ባሻገር በትወናም ላይ አቅሙን አሳይቷል፡፡ደራሲው በሰማይ ቤት ፣ካሊጉላ፣የከርቸሌው ዘፋኝ ፤ እና ጥምዝ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በልዩ ልዩ ርእሰ-ጉዳዮች ላይ ጥናታዊ ስራዎችን በማበርከት ምሁራዊ ሚናውን ተወጥቷል ዶክተር ተሻለ ። ዶክተር ተሻለ አሰፋ ለቴአትር ተማሪዎች ማስተማሪያ የሚሆን መፅሀፍ በቅርቡ ለንባብ ያበቃል ።

የቴአትር እና የስነ-ጽሁፍ ክበቦች ሙያዊ እገዛ በፈለጉ ጊዜም ዶክተር ተሻለ እውቀቱን አንድም ሳይሰስት ሲለግስ ኖሯል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ውድነህ ክፍሌ የፃፈውና ስለእውቁ ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ የሚያትተው (በዓሉ ግርማ – ቤርሙዳ)፤ቴአትርን አዘጋጅቶ በሀገር ፍቅር መድረክ ላይ እያሳየ ይገኛል።
ተዋናይ ኩራባቸው ደነቀ ስለ ዶክተር ተሻለ ሲናገር በስራና በሰዓት ጉዳይ ላይ ቀልድ አያውቅም ለዛ ነው ስኬታማ የሆነው ይላል። ስለሰው ምስክርነት መስጠት ከባድ ነው የሚለው ደራሲ ቴዎድሮስ ተክለአረጋይ ስለተሻለ መመስከር ግን ቀሎት ታይቷል። ብዙ ተማሪዎቹ ጥሩ ቢባሉ ቀድመው የሚጠሩት ሰው እንደሆነም ያስቀምጣል።

ውድነህ ክፍሌ በበኩሉ “ወደ ተማሪዎቹ ሲመጣ ምን ማቅረብ እንዳለበት አውቆ የሚመጣ እና በእውነት የማይደራደር መምህር መሆኑን ይናገርለታል።የስራም የስምም ሞክሼው ተሻለ ወርቁ ደግሞ ” ሞክሼዬ ለሁሉም ነገር የተመቼ ነው” ሲል ይገልፀዋል። “ተሻለ ጋር እየሰራህ ሙያው የሚጠይቀውን ዝግጁነት ካልተወጣህ ትጋጫለህ…. ለዛ ነው ተሻለን አስቸጋሪ የሚሉት” የሚለው ደግሞ የሀገር ፍቅር ቴአትር ስራ አስኪያጅ አብዱልከሪም ጀማል ነው። ተሻለ ስራና ትምህርት ላይ የሚፈጥረው ግጭት ግን እዚያው ተጀምሮ በቦታው የሚያልቅ እንጂ ከስራ ውጭ እንደማይደርስ የምታስረዳው ደግሞ ተዋናይት ሸዊት ከበደ ናት። ህንደኬን አብሮት የሰራው ተዋናይ ይገረም ደጄኔም በሸዊት ሃሳብ ይስማማል። “ዝግጅት ላይ ነፍሱ በጣም ስለምትመሰጥ ስሜታዊ ሁኖ ሊናገር ቢችልም የስራው መጨረሻ ላይ ግን የተቆጣሁት ለስራው ማማር ነው ብሎ ይቅርታ ይጠይቃል” ይላል። ይገረም፡፡

መዝጊያ

ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የመዝገበ-አእምሮ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡ ዶክተር ተሻለ የተሻለ ስራ ይዞ ብቅ ለማለት ሁሌም የሚታትር በሳል ባለሙያ ነው፡፡ የመዝገበ-አእምሮ የጥናት ቡድን ይህን በተግባር ማረጋገጥ ችሏል፡፡ ሰዎች ያኖሩት አሻራ የትም ሊደበቅ አይችልም፡፡ በግልጽ የሚታይ ነው፡፡ ባለሙያው ላለፉት 31 አመታት ሙያውን ወደ አንድ ከፍታ ለማሳደግ ብሎም በልህቀት ለመስራት የተቻለውን አድርጓል፡፡ይህ የሚያስመሰግን ነው፡፡ ታሪክን የምንሰንደው አንድ ታላቅ አሻራ ላኖረ በመሆኑ ይህም እኛን ያኮራናል፡፡ ዶክተር ተሻለ በአንድ አስተዋጽኦ ብቻ ሳይወሰን ሙሉ አቅሜ ለዚህች ሀገር ይዋል ብሎ ያለውን አካፍሏል፡፡ ይህን እኛ ብቻ ሳንሆን አብረውት የሰሩት ፤ ተማሪዎቹና ያቀረባቸው ስራዎች ይመሰክራሉ፡፡ በቴአትር ዘርፍ ከ1980 በኋላ ከተነሱ በሳል መምህራን ወይም የቴአትር ባለሙያዎች አንዱ ሆነው ዶክተር ተሻለ ለስራ ቅድሚያ መስጠቱ እና ለነገሮች ምንም አይነት ድርድር አለማቅረቡ ሊያስከብረው ይገባል፡፡ እኛም የሰዎችን ታሪክ ለትውልድ እንደሚያቀብል ሰናጅ የዶክተር ተሻለ አይነት ሰዎች ወደ መድረኩ ይምጡ ማለት እንወዳለን፡፡ ይህ የስራ ታሪክ ብዙ ማሻሸያዎች የሚደረጉበት ሲሆን ወደ ፊት ባለታሪኩ ዶክተር ተሻለ አዳዲስ ስራዎች ሲያክል የሚጨመሩ ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ ለዛሬ ግን ለዶክተር ተሻለ መልካሙን ተመኝተን መዝጊያውን እንቋጫለን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *