ተስፋዬ ማሞ ወንድም አገኘሁ

የዕጸ-በለስ ደራሲ

ተስፋዬ ማሞ ወንድም አገኘሁ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡

ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡

በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 150 የሚድያ ፤ የስነጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡

በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል ተስፋዬ ማሞ አንዱ ነው፡፡ ተስፋዬ የልጅነት ህልማቸውን ካሳኩ ሰዎች አንዱ ነው፡፡ በይፋ የጥበቡን አለም ከተቀላቀለ 34 አመት የሞላው ሲሆን ገና በወጣትነት ብእር ከወረቀት እያዋሃደ ለጊዜው ህትመቶች ይልክ ነበር፡፡ ተስፋዬ ማሞ የልቦለድ ደራሲ ነው፡፡ ደግሞ በሌላ መልኩ የፊልም ስክሪፕቶችን በመጻፍ አቅሙን ያሳየ ነው፡፡

ይህ ከያኒ በግጥምና በሬድዮ ፕሮግራሙም ይታወቃል፡፡ ተወዳጅ ሚድያ የቤተሰብ ሰው ወይም ልጆቹን እና ባለቤቱን ከሚያከብሩ የጥበብ ሰዎች አንዱ አድርጎ ተስፋዬን ይቆጥረዋል፡፡ እንዲህ አይነት ሰዎች ቢነበቡ ብዙ ገጽ አላቸው፡፡ በመሆኑም የተስፍሽ ታሪክ ለትውልዱ ይጠቅማል ብለን ሰንደነዋል፡፡ የህይወት ታሪኩን መነሻ ጽሁፍ ከባለታሪኩ ያገኘን ሲሆን የስነዳ ተግባሩን ደግሞ እዝራ እጅጉ አከናውኖታል፡፡

ተስፋዬ ማሞ የተወለደው መጋቢት 23 ቀን 1949 ዓ.ም ነው። የትውልድ ቦታው ወሎ ክፍለሀገር ኮምቦልቻ ከተማ ሲሆን፤ አባቱ አቶ ማሞ ወንድም አገኘሁ ወይም በአገሬው አጠራር ማሞ ኢሣ የአውራጎዳና ባለስልጣን መካኒክ፤ እናቱ ወ/ሮ ጣይቱ አሊ አማኑ ደግሞ እስከ 1960 ድረስ የቤት እመቤት የነበሩና በዚሁ አመት በኮምቦልቻ በተቋቋመው ሶፕራል የሥጋ ፋብሪካ ተቀጥረው ዕድሜአቸው ለጡረታ እስከ ደረሰ ድረስ ያገለገሉ ለፍቶ አዳሪ ወዛደር ነበሩ።

ተስፋዬ የቤተሰቡ የበኩር ልጅ ሲሆን ገና በጨቅላነታቸው ለአፈር ከተሰጡ ሁለት ህጻናት ሌላ ከእሱ በታች ሁለት ወንድሞችና እህቶች ነበሩት።

ልጅነትና ትምህርት

ተስፋዬ እንደማንኛውም የዚያ ዘመን የኢትዮጵያ ልጅ ዕድሜው 4 + 4 + 4 አራት አመት ከአራት ወር ከአራት ቀን ሲሆን ፊደል ይቆጥር ዘንድ፤ በአካባቢው ስመ-ጥር ከነበሩት መሪጌታ ከበደ ይመር ዘንድ ገብቶ የቄስ ትምህርቱን (የአብነት ትምህርቱን) ከፊደል ተራ ጀምሮ መዝሙረ- ዳዊትን በቃሉ ሸምድዶ እስከመድገም ደርሷል። በዚያም ወቅት በነበረው ንቃትና ከፍ ያለ የትምህርት አቀባበል መምህሩ በዚያው እንዲቀጥልና የቤተክርስቲያን አገልጋይና ሊቅ እንዲሆን ከፍተኛ ግፊት ቢያደርጉም በአባቱ ተቃውሞ በ1957 ዓ.ም. በወቅቱ አስኳላ የሚባለውን የዘመናዊ ትምህርቱን ጀምሯል።

የአንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በኮምቦልቻ ከተከታተለ በኋላ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደሴ በሚገኘው የወይዘሮ ስኅን አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በመከታተል ላይ እንዳለ፤ ባላቸው አቅም አቀማጥለው ያሳድጉት አባቱ በጡረታ በመገለላቸው፤ የልጅነት ህልሙ በኪነ-ጥበብ ሙያ ላይ መሠማራት ወይም ጋዜጠኛ መሆን የነበረ ቢሆንም አቅጣጫው በድንገት ተለውጦ፤ ዕድገት በህብረት ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የጤና ረዳትነት ትምህርት ስልጠና ቁጥራቸው ከ400 ከሚበልጡ ወጣቶች ጋር ተወዳድሮ ከተመረጡት 8 ተማሪዎች አንዱ በመሆን፤ የህክምና ትምህርት ለመከታተል ወደ ጎንደር ጤና ጥበቃ ኮሌጅ በመግባት በዲፕሎማ ተመረቀ።

ተስፋዬን በቅርብ የሚያውቁት ቤተሰቦቹና አብሮ አደጎቹ በልጅነቱ ያሳያቸው ከነበሩ እንቅስቃሴዎቹ፤ ከአንዱ የኪነጥበብ ዘርፍ ላይ እንደሚያርፍ እርግጠኞች ቢሆኑም፤ ይህንን ይሆናል ብለው ለመተንበይ ይቸገሩ ነበር። ግጥም ሲጽፍ ፣ የጻፈውን በመድረክ ሲያቀርብ፣ በወላጆች ቀን ወይም ከአብሮ አደግ ጓደኞቹ ጋር ሰብሰብ ብሎ ሲተውን፣ በተሰበሰቡ ሰዎች መካከል ሃሳቡን በድፍረት ሲገልጽ፣ የአነጋገር ችሎታው፣ ሲሻው ደግሞ በእርሳስና በቾክ የሚሞነጫጭራቸው ስዕሎቹ ነፍሱ የት ጋ እንደሆነ ለመተንበይ አስቸጋሪ ይሆንባቸው ነበር።

በልጅነት የትምህርት ቤት ቆይታው በተለይ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ሆኖ ዴስክ ውስጥ በመደበቅ ራሱን እንደራዲዮ አድርጎ ዜና ሲያነብ የሚያውቁ፣ ወይም ክፍል ውስጥ በተማሪዎች ፊት የሚነበብ ነገር ሲኖርና “ማን ያንብብ?” ሲባል ክፍሉ ሁሉ በአንድ ድምጽ “ተስፋዬ ማሞ” ብሎ የሚስማማበትና በአነባበብ ፍጥነትና ችሎታው ይደመሙበት የነበሩ፣ ገና የአራተኛ ክፍል ተማሪ በነበረበት ጮርቃነቱ “ምንታምር ወረደ” በተሰኘው የአቶ ተስፋዬ እሸቱ የቲአትር ድርሠት ውስጥ ያለውን “አንተነህ” የተሰኘ ገጸ-ባህሪ በመሪ ተዋናይነት ሲጫወት የተመለከቱ፤ ከልጅነት መንገድና ህልሙ ውጭ ድንገት አቅጣጫው ወደ ህክምና ሙያ ሲሆን የተገረሙ ብዙዎች ነበሩ። እርሱም ቢሆን “ከችግር ለመሸሽ ስል የገባሁበት የቀን ማሳለፊያዬ” ይለዋል የህክምና ትምህርቱን። በዚያም ምክንያት የእህል ውሀ ነገር ሆኖ ህክምና የተስፋዬ የመጀመሪያ ሙያ ሆኖ ተመዘገበ።

የሥራ አለም አሃዱ

ተስፋዬ የሥራ ዓለሙን ሀ ብሎ የጀመረው በህክምና ዘማችነት ኤርትራ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ምድቡ አሰብ ሆስፒታል ነበር። አሰብ ሆስፒታል ለአንድ አመት ከስምንት ወር ያህል ከሠራ በኋላ ወደ አሥመራ በመመለስ ፣ ሃዘሃዝ በሚገኘው የፖሊስ ሆስፒታልና በመካነ-ህይወት ሆስፒታሎች ለጥቂት ጊዜያት በህክምና ዘማችነት ካገለገለ በኋላ የህይወቱን አቅጣጫ እስከአሁን ወደቀየረ ያልታሰበ አቅጣጫ ተሳበ። ይሄውም አሰብ በነበረበት ጊዜ ፍጹም ባልዋለበት፣ ባልነበረበትና ባልተሳተፈበት ሁኔታ “ኢህአፓ” ነህ ተብሎ መታሠሩና ለጥቂትም ከቀይሽብር ግድያ መዳኑ በፈጠረው አጋጣሚ፤ ከማርክሳዊ ርዕዮት ንድፈ-ሃሳብ ጋር መተዋወቁ ነበር። በዚህም አሥመራ ከተመለሰ በኋላ ያሳይ በነበረው እንቅስቃሴ፤ የወቅቱን የፖለቲካ ሰዎች ትኩረት በመሳቡ ወደ የካቲት 66 የፖለቲካ ት/ቤት ተልኮ ለ 6 ወራት ልዩ የርዕዮተ-ዓለም ትምህርትን እንዲከታተል ተደረገ። ይህም የተስፋዬን የወደፊት አቅጣጫ ሁሉ የሚለውጥ ሆነ። በስልጠናው ወቅትም እጅግ ከሳበው የማርክሲስት ፍልስፍና ጋር መተዋወቁና በፍልስፍናውም ከመማረኩ በተጨማሪ በራስ መከላከል ረገድ ከወሰደው ወታደራዊ ስልጠና በተጨማሪ፤ በኪነ-ጥበብ ዘርፍም በወቅቱ ዝናቸው ከፍ ካለው ከነወጋየሁ ደግነቱ፣ ውብሻው ስለሺ፣ ብርቅነህ ኦርጋና ተሾመ ሲሳይ ከመሳሰሉት የሙዚቃ ሰዎች እንዲሁም ከእነ ሊቀ ምዕመራን አበባው ይግዛው ከመሳሰሉ ሊቃውንት ጋር በመሆን በበርካታ መዝሙሮችና የሥነ-ጽሑፍ ክዋኔዎች ላይ መሳተፍ መቻሉና በተሳትፎም ያሳየው ብቃት ትኩረት እንዲሰጠው ያደረገ ነበር።

ከየካቲት 66 የ 6 ወራት ስልጠና በኋላም ወዲያውኑ ቀድሞ ከነበረበት ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ወደ ህዝብ ድርጅት ጉዳይ ጽ/ቤት ተዛውሮ እንዲሠራ ደብዳቤ ደረሰው። ከዚህ በኋላም ተስፋዬ ጤና ጥበቃንና የህክምና ሙያን በይፋ ለቆ አዲሱ መሥሪያ ቤቱን ተቀላቀለ።

በአዲሱ መሥሪያ ቤቱም መጀመሪያ ህዝብ ድርጅት በኋላም ብሄራዊ አብዮታዊ ዘመቻ መምሪያ በአሥመራ፣ በመንደፈራና አዲኳላ በልዩ ልዩ ኃላፊነቶች እየተማረም፣ እየታሠረም፣ እየተፈታም ካገለገለ በኋላ ኤርትራን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተሰናብቶ ጳጉሜ 2 ቀን 1973 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ መጣ።

ከ 1974 እስከ 1979 ጥቅምት ወር ድረስ በአቃቂ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ተመድቦ በልዩ ልዩ የሥራ መደቦች ያገለገለ ሲሆን ከዚህ ጊዜ ውስጥም 1978 ዓ.ምን በሀገራችን ተከስቶ በነበረው ድርቅና ረሀብ ምክንያት በነበረው የሠፈራ ፕሮግራም ላይ ተሳታፊ ለመሆን ወደ መተከል ሠፈራ ጣቢያ በመዝመት ለ 11 ወራት በሠፈራ ጣቢያው የጤና አስተባባሪ ኃላፊ በመሆን ታላቅ ኃላፊነትን በመወጣት ከአክብሮትና ምስጋና ጋር ተመልሷል። ተስፋዬም ይህንን ጊዜ ሲያስታውስ “በህይወት ዘመኔ ሁሉ ከሠራኋቸው ሥራዎች በእጅጉ የምደሰትበትና ውጤታማ የነበርኩበት ዘመን ነበር” በማለት ይገልጸዋል።

በመተከል ሠፈራ ጣቢያ በነበረበት ጊዜ ባገኘው የጥሞና ጊዜና ሌሎች ምክንያቶች ጭምር ከዘመቻ እንደተመለሠ የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ በማቅረብ በራሱ ፈቃድ የመንግስት ሥራንና የመንግሥት ሠራተኛነትን ተሰናብቶ አዲስ የህይወት መንገድን መከተል ጀመረ።

ከመንግሥት ሥራ ለቆ በራሱ ለመቆምና አዲስ ህይወት ለመምራት የነበረው ሽግግር እጅግ በጣም አስቸጋሪና ፈታኝ ነበር። ተስፋዬ ለችግርና ጊዜያዊ ፈተና እጁን ላለመስጠት በጥንካሬና በውሳኔ ጽናት አንድ አመት ያህል ችግሩን ተቋቁሞ በመቆየት፤ መተከል ሠፈራ ጣቢያ በነበረበት ጊዜ በነበረው የስራ ቅልጥፍናና፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ መተከል ሠፈራ ጣቢያ ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ያደርግላቸው በነበረ ያልተቆጠበ ድጋፍና እገዛ የተማረኩት የጣና በለስ ፕሮጄክት የሥራ ኃላፊዎች በቀረቡለት የአብረን እንሥራ ጥያቄ መሠረት፤ ከጥቂት ጊዜ መጉላላት በኋላ በ1980 ጥቅምት ወር፤ የጣና በለስ ፕሮጄክት አማካሪ መሃንዲስ በሆነውና “ስቱዲዮ ኢንጂኔሪንግ ጆርጆ ፔትራንጀሊ” በመባል የሚታወቀው ኩባንያ ባልደረባ በመሆን፤ ጎጃም አቸፈር ወረዳ በሚገኘው ቁንዝላ ሳይት ሥራውን ጀመረ። ይሁንና የሥራ አካባቢው በወቅቱ “አያልነሽ” እየተባለች በምትጠራው የኢህአፓ አንድ ክንፍ የሚመሩ የመንግሥት ተቃዋሚዎች በጣሉት ድንገተኛ ጥቃት ምክንያት ለጥቂት ሲተርፍ ሥራ ከጀመረ ሁለት ወር ያልሆነው ፕሮጄክቱም ፍጻሜም በዚያው ሆነ።

ከቁንዝላ በኋላም ቀድሞ በዘማችነት ከሠራበት ፓዌ የግልገል በለስ ግድብን ከቅየሳ ጊዜ ጀምሮ ግንባታው ከግማሽ በላይ እስከሄደበት ድረስ የካምፕ አስተዳዳሪ በመሆን ለ አንድ አመት ከአራት ወር ያህል ከሠራ በኋላ ጥቂት ገንዘብ አጠረቃቅሞ፤ የበረሀውን ሥራ እርግፍ አድርጎ በመተው ኑሮውንና ቀጣይ ህይወቱን የልጅነት ህልሙን ለመኖር በመወሰን ወደ አዲስ አበባ ተመለሠ።

ወደ ልጅነት ህልም

የተስፋዬ የልጅነት ህልም ገጣሚነት፣ ደራሲነት፣ ጋዜጠኝነትና ሠዓሊነት ቢሆንም፤ የሠዐሊነት ፍላጎቱ ‘እንደጠይም ንቅሳት’ ቀስ በቀስ ሲደበዝዝ፤ በተለይ በሥነጽሁፍ ረገድ የነበረው ፍላጎት ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የሚሄድ ነበር። በዚህም አሥመራ በነበረበት ጊዜ፤ ህብረትና ኢትዮጵያ በተባሉ ጋዜጦች ላይ በመጻፍ ይሳተፍ ነበረ። አቃቂ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ይሠራ በነበረበት ጊዜም፤ ጽሑፎቹና ግጥሞቹ በአዲስ ዘመንና ኢትዮጵያ ጋዜጦች ላይ ወጥተውለታል። ከብዙዎቹ ጽሑፎቹና እሱም እስከ አሁን ከሚያስታውሳቸው መካከል “እሰይ ፖሊሳሪዮ” በሚል ለፖሊሳሪዮ የነጻነት ንቅናቄ ድጋፍ የጻፈው ግጥምና “የባህር ውስጥ ጋብቻ” በሚል ርዕስ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ /Underwater Marriage/ የሚል ኹነትን ተርጉሞ የወጣለትን ያስታውሳል።

ተስፋዬ አቃቂ ጨርቃ ጨርቅ ተመድቦ በሚሠራበት ወቅት የነበረው ኪነታዊ ተሳትፎ የላቀ ነበር። ግጥሞችን ይጽፋል፣ ከፋብሪካው የኪነት ቡድን ጋር በቅርበት ይሠራል፣ ፋብሪካው ለተለያዩ ኹነቶች በሚያወጣቸው መጽሄቶች ላይ ይሳተፋል፣ በዓላት በሚኖሩበት ወቅት የፋብሪካውን ግቢ በማሸብረቅ ረገድ ድርሻው ከፍ ያለ ነበር። መድረኮች ሲኖሩ መድረኮችን ይመራል። ከነዚህና ከማይረሱት መድረክ የመምራት እንቅስቃሴዎቹ አንዱ፤ የሩማኒያ መሪ የነበሩት ፕሬዝዳንት ኒኮላይ ቻውሴስኩ አቃቂ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካን ለመጎብኘት ከፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ጋር በመጡበት ጊዜ መድረኩን “ጉድ” እስኪባል ድረስ በድምቀት ይመራው የነበረው ተስፋዬ ማሞ ነበር።

በ 1977 በኢሠፓ ምስረታ ወቅትም፤ አቃቂ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ የኢትዮጵያ ሠርቶ አደሮች ፓርቲ (ኢሠፓ) የመሠረታዊ ድርጅት የመሥራች ስብሰባውን ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃ/ማርያም በተገኙበት ሲያካሂድም በልዩ ችሎታው ተመርጦ መድረኩን ይመራ የነበረው እሱ ነው።

እዚህ ላይ የመድረክ መምራት ሥራን ከኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ዘመን ጀምሮ እስከ ዶ/ር ዐብይ አህመድ ድረስ የነበሩ ሁሉም የኢትዮጵያ መሪዎች ባሉበት መድረክ በመምራቱ ምናልባትም ተስፋዬ ማሞን በታሪክ ልዩ ቦታ ላይ የሚያስቀምጠው ሊሆን ይችላል።

የተስፋዬ የአቃቂ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ቆይታ፤ በኪነጥበብ ረገድ ዐይኑን እንዲገልጥና ልምምድ እንዲያደርግ፣ እንዲሁም የወደፊት ተስፋውን አቅርቦ እንዲመለከት፣ በርካታ አስተዋጽኦዎችን አድርጎለታል። ለዚህም ከሚጠቀሱት መካከል በ 1975 የኢትዮጵያ ሠርቶ አደሮች ማህበር (ኢሠአማ) ሀገራዊ የሠራተኛ ማህበርት መሪዎች ምርጫ ያካሂድ ስለነበር፤ ይህንን ሁኔታ አስመልክቶ ለቅስቀሳ የሚሆን የቴሌቪዥን ድራማ የተሠራው በአቃቂ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ውስጥ ነበር። የድራማው ዳይሬክተር የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዕውቅ ዳይሬክተር አፈወርቅ ማና ሲሆን ከተዋንያኑ መካከልም አንጋፋው ተዋናይ ተክሌ ደስታ ይገኝበታል። ተክሌ ደስታና አፈወርቅ ማና በዚያ ዘመን (1974) ከእነ ዓለምጸኃይ ወዳጆ፣ አይናለም ተስፋዬ፣ ንጉሡ ዘውገና ሌሎች ጋር በመሆን የሠሩት “ያልተከፈለ ዕዳ” የተሰኘው የይልማ ሃብተዬስ በወንጀል ላይ የተመሠረተ ድራማ፤ እጅግ የተወደደበትና የእነሱም ዝና ከፍ ያለበት ዘመን ነበር። ተስፋዬም ለመጀመሪያ ጊዜ፤ ከእነዚህ ዝናቸው ከገነነ ባለሙያዎች ጋር ካሜራ ፊት በመቆም የተሰጠውን ቃለተውኔት አጥንቶ መተወኑ ቀጥሎ ለመጣበት ሙያው ከፍ ያለ መንደርደርያ ሆኖለታል።

ከዚህ በኋላ ተስፋዬ ጓዙን ጠቅልሎ ወደ ኪነጥበቡ አለም የገባው 1981 ላይ ነው። ይህ ዘመንም ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ አጫጭር ታሪኮችንና ግጥሞች ያለማቋረጥ እየጻፈ እራሱን የሚፈትሽበትና ብዕሩን የሚያሟሽበት ጊዜ ነበር። ፈራ ተባ በሚልበትና ሥራውን ወደ አደባባይ ይዞ ለመውጣት፣ ድፍርቱንም መንገዱን ባጣበት ጊዜ፤ በሥራው ደፍሮ እንዲወጣና ወደ እውቅናው ማማ እንዲጠጋ ታላቅ ውለታ የዋለለት በወቅቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነጽሁፍ መምህር የነበረው ወዳጁ አሠፋ አረጋሃኝ እንደነበር ተስፋዬ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሲያወሳው ይሰማል።

ይህም የሆነው አሠፋ አረጋሃኝ “ትሁት” የተሰኘውን የተስፋዬን አጭር ልቦለድ ጽሑፍ ካነበበ በኋላ በመገረም “ትችላለህ….ከዚህ በኋላ መቆየት የለብህም” በማለት ስላበረታውና ጽሑፉንም ራሱ አሰፋ አረጋሃኝ ወስዶ፤ ኢትዮጵያ ራዲዮ ለታዋቂው ጋዜጠኛና የሥራ ኃላፊ ታደሠ ሙሉነህ ስለሰጠለት፤ በተወዳጁ ዕሁድ ጠዋት ፕሮግራም ላይ “ትሁት” በታዋቂው ተዋናይ ጥላሁን ጉግሣ አንደበት መተረኳ ነው። ተስፋዬ የመጀመሪያ ሥራውን የሰማ ቀን የተሰማውን ስሜት “መሬት ጠበበችኝ፣ በፍጹም የኔ ጽሑፍ እስከማይመስለኝ ነበር የተገረምኩት” ይላል። ከዚያ በኋላ በኢትዮጵያ ራዲዮ የዕሁድ ጠዋት ፕሮግራምና ቅዳሜ ከሰዓት ፕሮግራሞች ላይ በትረካ፣ በግጥምና ወግ ተስፋዬ ማሞ የሚለውን ስም መስማት የተለመደ ሆነ። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ያን ዘመን በአባታቸው ሰመ ሞኩሼ የሆኑ እንደ አማረ ማሞ፣ ጥሩነህ ማሞ፣ ዝናሽ ማሞ እና ሳምሶን ማሞ የመሳሰሉ ስሞች ተደጋግመው የሚሰሙበት ዘመን ስለነበር የሱም ስም ሲጨመር ለመታወቅ ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም። ያለማቋረጥ ይጽፋል። በተለይ በሀገራዊ ሁኔታዎች ዙሪያ ድራማዎችና የቅስቀሳ ጽሑፎች ሲያስፈልጉ ተስፋዬ ተፈላጊው ሰው ሆነ። ርዕሰ ጉዳይ ይሰጠዋል…. ሳይውል ሳያድር በተሰጠው ርዕሰ ጉዳይ ላይ እንደሁኔታውና ጭብጡ ድራማ፣ ወግ፣ አጭር ልቦለድ ወይም ግጥም ጽፎ ይመጣል። ይሁንና ይህ አዝማሚያ ለተስፋዬ ከሚፈልገው መስመር የሚያስወጣውና ረዥሙን ጉዞ የሚጎዳበት መስሎ ስለተሰማው፤ ከዕውነተኛ ስሙ ውጭ በብዕር ስም መጠቀምን ጀመረ። በዚህም “ሳተናው ከግንባር” በሚል መጠሪያ እሱ ከጦር ሜዳዎች የሚጽፍ ወታደር ሲሆን፤ ከመሃል ደግሞ የፍልውሀው ጀሚል “ደጀኑ መኩሪያ” በሚል እየተቀባበሉ ለረዥም ጊዜ ያለማቋረጥ ይጽፉ ነበር።

ተስፋዬ በዚህ ዘመን በስሙ ከጻፋቸው የራዲዮ ድራማዎቹና ጽሑፎቹ “የበረሐው ሙሽራ፣ ለእናት አድልቶ እናት ማጣት፣ ስብሰባው፣ ቀጠሮው…..ወዘተ የሚባሉና ሌሎች በርካታ ሥራዎችን አበርክቷል።

የተስፋዬን የብዕር በረከት ከፍ ካደረጉለትና በህዝብ ዘንድ እጅግ ከታወቁለትና ከተወደዱለት ሥራዎች ውስጥ “ዕጸ-በለስ” በሚል ርዕስ የጻፈውና በዕሁድ ፕሮግራም በተከታታይ በጥላሁን ጉግሣ ተራኪነት ይደመጥ የነበረው ጽሑፉ ነው። ትረካው ከመወደዱ የተነሳ በርካታ አድማጮች ታሪኩን ቀድመው ለመጨረስ ገና ሳይታተም “መጽሐፉ የት ይገኛል” እያሉ በብዛት መጠየቃቸውና በየሣምንቱ የሚሰጠው አስተያዬት፤ ተስፋዬን ለራዲዮ ብቻ አስቦ የሠራውን ታሪክ፤ አቃቂ ከሚገኘውና ከኤርትራ አብሮት ከመጣው በዕደማርያም አበራ ከተባለ ጓደኛው ቤት ለስድስት ቀናን ሌሊት ከቤት ሳይወጣ መሽጎ በመጻፍ “ዕጸ-በለስ”ን ለመጽሐፍ ትሆን ዘንድ አዘጋጃት። ለማሳተምም ተስፋዬ እንደብዙዎቹ ደራስያን ብዙ አልወጣም፣ አልወረደም፣ አንተንከራተተም። የሳንሱር ጣጣውን በአጭር ጊዜ ጨርሶ፤ መጀመሪያ የሄደባቸው ብሄራዊ ቲአትር ፊለፊት ዛሬ ከፈረሰውና ላዬን ባር መደዳ የሚገኘው “ደስታ ስቴሽነሪ” ጋር የዕለቱ’ለት ውል ፈጽሞ “ዕጸ-በለስ” በአርቲስቲክ ማተሚያ ቤት ባለ 132 ገጽ መጽሐፍ ሆና ግንቦት 1982 ላይ ብቅ አለች። ተስፋዬ ይህንን ቀን በህይወቱ ከመዘገባቸው ታላላቅ የደስታ ቀኖች ሁሉ “ቀዳሚው የደስታ ቀኔ ነው” ይላል።

“ዕጸ-በለስ” በ 10 ሺህ ኮፒ ታትማ ለማለቅ ሶስት ወር አልፈጀባትም። በ 5 ብር ሂሳብ “እንደትኩስ ኬክ” ተሸጠች። እንደገና ለማሳተም ግን አልተቻለም። የህትመት ዋጋ በአንድ ጊዜ ከ 130% በላይ መጨመሩ በተነቃቃው የመጽሐፍ ማሳተም ሥራ ላይ ቀዝቃዛ ዉሀ ቸለሰበት። ይሁንና ተስፋዬ መጻፉን አላቆመም “ዕጸ-በለስ” ለገበያ በዋለች በአመት ከመንፈቋ “የጨረቃ ጥሪ” የተባለ ረዥም ልቦለድ መጽሐፍን በመጻፍ በመጋቢት 18/1984 ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ፤ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የምርመራ አገልግሎት ሳንሱር ማለፏን የሚያረጋግጥ ማህተም አስመትቶ በእጁ አስገባ።

ከጆሮ ወደ ዐይን / ከራዲዮ ወደ ቲቪ

ተስፋዬ “ዕጸ-በለስ”ን ለአንባቢ ካቀረበ በኋላ አዲስ ነገር ፈላጊ ስሜቱ በ1974 በቴሌቪዥን በተመለከተው “ያልተከፈለ ዕዳ” የተሰኘ የቴሌቪዥን ድራማ ውስዋስ ዐይኑን ወደ ቴሌቪዥን አዞረ። ለዚህም በወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሚኒስትር የነበሩትና በየካቲት 66 የፖለቲካ ት/ቤት መምህሩ የነበሩት፤ አቶ አብዱልሃፊዝ የሱፍ ውለታ ቀላል አልነበረም። “የሥነጽሑፍ ሙያዬን በቴሌቪዥን ማሳደግ እፈልጋለሁ” ብሎ ሲያማክራቸው በ“ዕጸ-በለስና” ልዩ ልዩ የሥነጽሑፍ አላባዎቹ ችሎታውን ያስመሰከረበት ጊዜ ስለነበርና ድምጹም ለራዲዮና ቴሌቪዥን የሚመረጥ ባለግርማ ሞገስ ድምጽ በመሆኑ፤ በወቅቱ ለነበሩት የቴሌቪዥን ኃላፊዎች “ከፍ ያለ ችሎታ ስላለው በቴሌቪዥን ቢቀጠር ይጠቅማል” የሚል ማስታወሻ ደብዳቤ አስይዘው ላኩት። የወቅቱ የቴሌቪዥን የሥራ ኃላፊዎች ግን እንደሱ ፍላጎትና እንደሚኒስትሩ ቃል አልተቀበሉትም።

ላለመቀበላቸው የሰጡት ምክንያትም ግንባሩ የሸሸ (መላጣ) በመሆኑ ለቴሌቪዥን screen appearance አይሆንም” የሚል ነበር። ተስፋዬ በመልሳቸው አልተከፋም። እንዲያውም ስሜቱ ልክ ናቸው ወደሚል ከማዘንበሉም ሌላ ፍላጎቱ በቴሌቪዥን መታዬት ሳይሆን፤ በቴሌቪዥን ድራማ መሥራት ነበርና ሙሉ ትኩረቱን ከዜና ወይም ፕሮግራም አቅራቢነት ውጭ በማድረግ ውሳኔውን በጸጋ ተቀበለ።

ትኩረቱንም በድራማ ጽሑፍ ላይ በማድረግ የቴሌቪዥን ድራማ አጻጻፍ ቴክኒኮችን ለማወቅ ውሎውን በብሪቲሽ ካውንስል ቤተመጻሕፍትና ሌሎች የዕውቀት አውዶች በማሳለፍ ራሱን በንባብ አዳበረ።

በ1983 በራዲዮ ድራማነት ያሟሸውን “ስብሰባው” የተሰኘ ታሪክ ለቴሌቪዥን እንዲሆን አድርጎ በማዘጋጀት ወደ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲወስደው በደስታ እጁን ስመው ተቀበሉት። ዘመኑም እገሌ የሚባል የቴሌቪዥን ድራማ ጸሐፊ ጎልቶ የወጣበት ዘመን ባለመሆኑ፤ ለተስፋዬ ምቹ ሁኔታን ፈጠረለት። “ስብሰብው”ን በዘካርያስ ኃይለማርያም ዳይሬክተርነት ራሱን ጨምሮ እነ ፍቅርተ ጌትሁን፣ ጌታቸው አበራ፣ የወይንሸት አስፋው የመሳሰሉ ተዋንያንን በመያዝ የመጀመሪያው የሆነውን የቴሌቪዥን ድራማ ለዕይታ አበቃ። ይህንን ጊዜ ተስፋዬ ከቴሌቪዥን ድራማ ጸሐፊነት በተጨማሪ ራሱን በተዋናይነት ለመሞከር ዕድሉን የተጠቀመበት ወቅት ነበር።

ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ በመምጣቱ፤ ነገሮች ቶሎ ቶሎ የተለዋወጡበት ጊዜ ነበር። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንንም በበላይ ለመምራት አቶ አማረ አረጋዊ ተመደበ። አማረ አረጋዊ ቀና፣ ለውጥ የሚፈልግ፣ ትኩስ ጉልበት ያለው ስለነበር፤ ለሥራ እግጅ የተመቸ ሁኔታ ተፈጠረ። በመሆኑም ተስፋዬ ይህንን የተመቸ ሁኔታ ለመጠቀም፤ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ታሪክ ሲበዛ አራት ክፍል ብቻ የነበረውን የቴሌቪዥን ድራማ ልማድ በመቀየር 12 ሣምንት እርዝመት ያለውና በወንጀል ታሪክ ላይ የተመሠረተውን “ትንቅንቅ” የተሰኘ ድራማ ለመሥራት በቃ። ይህ በተስፋዬ ፈርቀዳጅነት የተጀመረው ሥራ ብዙዎችን በማነቃቃት፤ እንደ “የህሊና ዕዳ!” የመሰሉ ግሩም የቴሌቪዥን ድራማዎች እንዲመጡና ከ 12 ሣምንትም በላይ ዘልቀው እንዲሄዱ አግዟቸዋል።

ከዚህ በኋላ ተስፋዬ እሰከ 1990 ድረስ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር በመዝናኛ ዝግጅቶች በፍሪላንስ ሠራተኛነት በርካታ የራሱና የሌሎች ጭምር የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ በጸሐፊነትና በአዘጋጅነትና ሠርቷል። ከነዚህም ውስጥ በጥቂቱ ስብሰባው፣ ትንቅንቅ፣ መላ፣ ትዝታ፣ ይቅርታ፣መንትያ፣ ዐውዳመት፣ የንዋይ ሰለቦች፣ ሶስቱ የፍቅር ታሪኮች (በቴሌፕሌይ ጽሑፍ፣ በትወና፣ በአዘጋጅነት) የመሳሰሉት ሊጠቀሱ ይችላሉ።

ከዚህም በተረፈ በ1986 የተቀረጸውና በ1987 በአምባሠል ሙዚቃና ቪዲዮ አሳታሚነት ሙሉ በሙሉ በባህርዳርና ዙሪያው፣ከአዲስ አበባ አንድም ተዋናይ ሳይወስድ እዚያው ባሉ፣ ባህሉን በሚኖሩና ታሪኩ የሚፈልገውን የቋንቋ ዘዬ የሚናገሩ ተዋንያንን በማሠልጠን (የአዲስ አበበ ዩኒቨርሲቲ የቲአትር ምሩቅ የሆኑትን አለማየሁ ገ/ህይወት፣ ዘለአለም ብርሃኑ፣ እስጢፋኖስ አድማሱና ወንድምኩን አላዩ በስተቀር) ባህርዳር ያሉ ወጣትና ጀማሪ ተዋንያን በማሰልጠን በVHS የተሠራውና “ፍቅር መጨረሻ” የተሰኘው የቪዲዮ ፊልም ለኢትዮጵያ የቪዲዮ ፊልም ሥራ ከፍተኛ መነቃቃትን በመፍጠር ከቀዳሚዎቹ ውስጥ የሚጠራ ሥራን አበርክቷል።

በቪዲዮ ፊልም ረገድ ከ”ፍቅር መጨረሻ በተጨማሪ ብዙም ያልተነገረለት “ፊርማ” የተሰኘ ርዝመቱ አንድ ሰዓት የሆነና ስዩም ተፈራ፣ ዕንግዳዘር ነጋ፣ አሰፋ በዬነ፣ አቢሎ ካሣና ሌሎች የተሳተፉበትን ድራማ፤ እንዲሁም ከ VHS ዘመን ወዲህ የዲጅታል ቪዲዮ ቴክኒዮሎጅ ሲመጣም “ዕጣ ፈንታ” የተሰኘ ተወዳጅ የቪዲዮ ፊልም በመሥራት ለሙያው ዕድገት የበኩሉን አስተዋጻኦ አድርጓል።

ተስፋዬና ማስታወቂያ

ተስፋዬ በ1992 አካባቢ ከወንደላጤነት ህይወት ተሰናብቶ ወደ ትዳር ጉዞ ሲጀምር፤ በመጣበት መንገድ በመጓዝ ቤተሰብ ማስተዳደርና መምራት የሚያስቸግር መሆኑን በመገንዘብ፤ ቀደም ብሎ ከአድማስ አድቨርታይዚንግ መስራችና ባለቤት ከአሰፋ ጎሳዬ ጋር በነበራቸው የቀረበ ግንኙነት በተለይ የ ፒ ኤስ አይ ኢትዮጵያን “የህይወት ብስክሌተኞች” የተሰኘ የኮንዶም ማስታወቂያ፣ የቤርሻኮ ኢትዮጵያን ሳምራ የጸጉር ቅባት አይነት ማስታወቂያዎችን በድምጽ ሲሠራ ባገኘው የማስታወቂያ ሥራ ልምምድ፤ በቂ ጥናትና ዝግጅት በማድረግ የማስታወቂያ ሥራ ፈቃድን አውጥቶ ወደ ሥራው ገባ።

ተስፋዬ በማስታወቂያ ሥራ ተሠማርቶ የራሱን የገበያ ድርሻ ለመያዝ ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም። በብዙዎች ዘንድ በስፋት የሚታወቁትን እንደአንበሳ ሻይ፣ ጉድ ሞርኒንግ ሻይ የመሳሰሉትን ሥራዎች በመስራት በአጭር ጊዜ ተፈላጊ የማስታወቂያ ሠራተኛ ለመሆን ቻለ። በዚህም የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኒዮሎጅ ግሩፕ ማስታወቂያዎችንና ዶኪዩመንታሪ ፊልሞችን በብቸኝነት የመሥራት ዕድልን አገኘ። በኢስት አፍሪካን ሆልዲንግም ሁሉንም በሚባል ደረጃ እንደነ ፋስት የዱቄት ሳሙና፣ ዱከም ብስኩት፣ ጉድሞርኒንግ ኮፊ ብስኩት አንበሳ ዱቄት የመሳሰሉ ማስታወቂያዎችን በመሥራት፤ የገበያ ድርሻውን ማስፋት ቻለ። ቀስ በቀስም ከሀገር ውስጥ ምርት ባለፈ፤ ዓለምአቀፍ ብራንዶችን የመሥራት ዕድል በማግኘት T3 የተሰኘ የማሌዚያ ምርት የሆነ የብጉር ማጥፊያ ቅባትና ክሬም ማስታወቂያ በሚፈለገው ደረጃ በማዘጋጀት ለተስፋዬ ከፍ ያለ ጥቅም ያሰገኘለት አጋጣሚ ተፈጠረ።

ይህ አጋጣሚ ተስፋዬን ዐይን ውስጥ በማስገባቱ በሱ ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ማስታወቂያ ሥራ ላይ ጥላ ያጠላና ከፍ ያለ ጉዳት ያስከተለም ሁኔታን ፈጠረ።

ተስፋዬ “ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በእግሩ ወጥቶ በመኪና ገባ” ተባለ። የማስታወቂያ ኮሚሽን ክፍያ የቆመውም ከዚህ ጊዜ በኋላ ነበር።

የማስታወቂያ ኮሚሽን ቢቆምም፤ ህይወት አይቆምምና ተስፋዬ ለልዩ ልዩ ተቋማት ከ 20 በላይ የሚሆኑ ዶኪዩመንታሪ ፊልሞችን ሠርቷል። ከዚህ በተጨማሪም ለዲኬቲ ኢትዮጵያ በአማርኛ በትግርኛና በኦሮሚኛ ቋንቋ ለማስተማሪያ የሚሆኑ አጫጭር ስፖት ደራማዎችን አዘጋጅቷል። በዚህም የሥራና የገቢ አድማሱን ለማስፋት በሌሎች ልዩ ልዩ የፕሮዳክሽን ሥራዎች ላይ በመጠመድ ኑሮን የማሸነፍና ቤተሰብ የመምራት ኃላፊነቱን መወጣቱን ቀጠለ።

ከዚህም ወጭ ተስፋዬ በ1992 ክረምት ላይ በዓለምአቀፍ የፊልም ሥራ ተሳትፎ ከፍተኛ ልምምድን ባገኘበት፤ በደቡብ አፍሪካው የፊልምና ቴሌቪዥን ኩባንያ Mnet አማካኝነት በሀገራችን በተሠራው “አባትዬው” /The Father/ የተሰኘ የማንያዘዋል እንደሻው ድርሰት፤ በኤርሚያስ ወ/አምላክ ዳይሬክተርነትና በአብረሃም ኃይሉ ብሩ ሲኒማቶግራፈርንነት በተሠራው የ35 ሚሊሜትር ባለ ቀለም ፊልም ላይ በአርት ዲፓርትመንት በአልባሳትና ቁሳቁስ ዝግጅት /Costume & props management/ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት በመሥራት ከፍተኛ ልምድን አትርፏል። በዚህ ሥራ ላይ ሓምሌ 19 መናፈሻ ውስጥ በነበረ ቀረጻም የሥራ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ በነበረበት ሁኔታ በደረሰበት ከባድ አደጋም በቀኝ እጁ ላይ የስብራት ጉዳት ደርሶበት ያለ አንዳች የመድህን ሽፋን ለሚወደው ሙያ ከፍ ያለ ዋጋ አስከፍሎታል።

ከዚህ በኋላ ተስፋዬ በ 1997 ከሠራው “ዕጣፈንታ” የተሰኘ ተወዳጅ ሥራውና፣ በ2010 በባለቤቱ በየውብዳር አንበሴ ጸሐፊነት በእሱ ቴሌፕሌይ ጸሐፊነት፣ በእሷ ዳይሬክተርነትና በሱ ፕሮዲዩሰርነት ከሠሩት “ምልሰት” የተሰኘ በፋና ቴሌቪዥን ለ28 ሣምንታት ተላልፎ በኮቪድ አስገዳጅነት ከተቋረጠው ተከታታይ የቴሌቪዥን ሥራና በ2005 ከታተመው “የጨረቃ ጥሪ” ከተሰኘ ሥራው ውጭ፤ ሙሉ ትኩረቱን በማስታወቂያ ሥራ ላይ በማድረጉ በኪነጥበብ ሥራ ረገድ ብዙ የሚጠቀስ ሥራዎችን አልሠራም። ይህ ማለት ግን ተስፋዬ ሙሉ በሙሉ ከጥበባዊ ሥራዎች ወጥቷል ማለት አይደለም።

ወደ ራዲዮ

2004 ዓመተ ምህረት ተስፋዬ ማሞ ከዕለታት በአንዱ ቀን በተጋባዥ እንግድነት በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ላይ በየሳምንቱ ማክሰኞ በሚተላለፍ ፕሮግራም ላይ በእንግድነት ይጋበዛል። ጋባዡ የፕሮግራሙ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተስፋዬ ሽመልስ ነበር። በዕለቱ ግሩም ቆይታ በማድረጋቸው ከአድማጮች የሚመጡ አስተያየቶችም የሚያበረታቱ ነበር። ሞክሼው ተስፋዬ በሁኔታው በመነቃቃት ደጋግሞ ተስፋዬን የስቱዲዮ ዕንግዳ እንዲሆን ይጋብዘዋል። ተስፋዬም ያለ ብዙ ችግር ጋባዡን ተቀብሎ ስቱዲዮ ይገባል። ይህ ሁኔታ እያደር እያደገ በመምጣቱ ተስፋዬ ከተጋባዥ ዕንግድነት ወደ ተባባሪ አዘጋጅነት አደገ። አልፎ አልፎ ረ/ፕሮፌሠር ነብዩ ባዬም ስለሚኖር ለሶስት ስቱዲዮ ይገባሉ። እንዲህ እንዲህ እያሉ ባለበት ሁኔታ ዋና አዘጋጁ ተስፋዬ ሽመልስ፤ የብሔራዊ ቲአትር ተ/ዳይሬክተር ሆኖ ይመደባል። ለጥቂት ሳምንታት ሁለቱን ሥራዎች ጎን ለጎን ለማስሄድ ቢሞክርም መዝለቅ ሲያቅተው ተስፋዬን በዋና አዘጋጅነት እንዲይዘው ይጠይቀዋል። ነብዩ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቲአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ዳይሬክተር ስለሆነ ተስፋዬ ኃላፊነቱን ተቀብሎ የጥበብ መንገድ ዋና አዘጋጅ ሆነ።

ከረ/ፕ ነብዩ ባዬም ጋር በጥሩ ስሜት ለ 6 ዓመታት አብረው እየሠሩ ከቆዩ በኋላ “ተስፋዬ ማሞ የሹመት ገድ አለው” እስኪባል ድረስ ነብዩም በሹመት ወደዚያው ወደ ብሄራዊ ቲአትር ሄደ።

እነሆ በዚህም ተስፋዬ የጥበብ መንገድ የራዲዮ ፕሮግራምን የተለያዩ ፎርማቶችን በማበልጸግ ተወዳጅ እንዲሆን በማድረግ እስከ አሁን ዘልቋል። በራዲዮ ፕሮግራም ዝግጅቱም በየሳምንቱ ሳይቋረጥ የሚቀርቡት ፕሮግራሞቹ በአድማጮቹ ዘንድ እጅግ የተወደዱ ሆነዋል። በተለይም በማህበራዊ ሂስ ላይ የሚያተኩረው “የድባቤ ውሎ” የተሰኘው ዝግጅት ተናፋቂና ተወዳጅ የፕሮግራሙ መለያ እስከመሆን ደርሷል።

ተስፋዬና ትዳር

ተስፋዬ ማሞ ከባለቤቱ ከየውብዳር አንበሴ ጋር ከ1992 ጀምሮ ጎጆ ቀልሰው ሁለት ወንዶችና አንዲት ሴት ልጅ በማፍራት ኑሯቸውን በፍቅርና በሠላም የሚመሩ፣ ለብዙዎች የሚያስቀናና አርአያ የሆነ ቤተሰብ መመስረት ችለዋል። ትልቁ ልጃቸው ናኦል ተስፋዬ በአሁን ሰዓት በአሜሪካን ሀገር የሁለተኛ አመት የሳይበር ሴኪዩሪቲ ትምህርቱን በማጠናቀቅ ላይ ያለ ሲሆን መካከለኛው ዳግማዊ ተስፋዬ ደግሞ በቱርክ ኢስታንቡል የአለማቀፍ ንግድና ቢዝነስ የሁለተኛ አመት ተማሪ ነው። የቤቱ መቋጫና የመጨረሻ ልጃቸው ፌኔት ተስፋዬም የአሥረኛ ክፍል ተማሪ ናት።

ተስፋዬ በአሁን ሰዓት መተዳደሪያውን ከ23 አመታት በፊት ተስፋዬማሞ ፊልም ፕሮዳክሽንና ማስታወቂያ በሚል ባቋቋመው ድርጅቱ የማስታወቂያ፣ የፊልም ፕሮዳክሽንና፣ የራዲዮ ፕሮግራም ሥራዎቹን በማከናወን በረጋና በደስታ ስሜት በመሥራት ላይ ይገኛል።

በአሁን ሰአት በሥነ-ጽሁፍ ረገድ የራሱን በከፍተኛ ውጣ ውረድ የተሞላ የህይወት ጉዞ አንጓዎች የሚተርክ መጽሐፍን በ65ኛ አመት የልደት ቀኑ ላይ ለማበርከት በከፍተኛ ትጋት ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ከልጅነት እስከ እውቀት የጻፋቸው ግጥሞቹ መድብል እንዲሁም የአጭር ልቦለድና ወግ ስብስቦቹን የያዙ መጻሕፍቱ ለመታተም የጊዜን ፈቃድ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።

ተስፋዬ ስለቀሪ ዘመኖቹ ሲጠየቅ “የአምላክ ቸርነት ከታከለበት” ይላልና የአምላክ ቸርነት ከታከለበት፤ እየጻፈ፣ እያሳተመ፣ ልምዱንና ህይወቱን እያካፈለ፣ በበጎ ሥራዎች ላይ እየተሳተፈና ማህበረሰቡን እያገለገለ መኖርን ይመኛል።

ዕድሜ ከጤና ሰጥቶት የልቡ ይሞላ ዘንድም ምኞታችን ነው።

የተሰጡ ምስክርነቶች

ተስፋዬ ማሞ ከተማረው የህክምና ሙያ ኮብልሎ በጥበብ መንገድ በስኬትና በደስታ ለመጓዝ የበቃ ብርቱ ሰው ነው። እስከ ዛሬ በስነ-ጽሁፍ፥ በፊልምና በግጥም ዘርፍ ያኖራቸው ቱሩፋቶቹ እንዳሉ ሆነው በቅርቡ ደግሞ የማስታወቂያ ሥራን ጥበብ በማጎናጸፍ ለሙያው አዲስ ጣዕም ለመስጠት የቻለ ባለሙያም ነው። ተስፋዬ ለቃላት፥ ለስነቃሎች፥ ለአገር በቃል ውብ የዘፈን ስንኞችና አገራዊ እሳቢዎች ልዩ አክብሮትና ፍቅር ያለው፥ የአገር ፍቅሩ አደባባይ የሚያቆመው፥ ስሜቱንም በሚንፎለፎል የቃላት ሃብቱ ለመግለጽ የሚችል መሆኑን ያሳየ መሆኑን ከሚመሰክሩለት የሩቅ ወዳጆቹ አንዱ ነኝ።

ተስፋዬ ድረሴ

ዕፀ በለስ መፀሃፉን ያነባብኵት በልጅነቴ 6ኛ ክፍል እያለሁ ነው እና ይህንን መፃሃፍ ያበረከተልንን ተስፋዬን በአገኘሁት ቁጥር ልጅነቴን ያስታውሰኛል ። የመዝናኛውን ኢንድስትሪ ለማገዝ ያለዉ ፍላጎት ይህ ነው አይባልም።

ወይዘሮ ሀቢባ ፋሪስ

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ስራ አስፈጻሚ

፨፨፨፨፨፨፨

እኔ ደግሞ ታላቅ የሰብዕና መገለጫው ከሆኑት በትንሹ ልጨምር።

1 ወዳጅነትን አክብሮና ጠበቆ የሚያቆይበት ፍቅሩ

2 ሰውን እንጅ የሰው ማህበራዊ ደረጃ ግድ እማይሰጠው

( ከሀብቱ፣ ከስልጣኑ ፣ ከዝናው ፣የሚጠብቀው ስለሌለ )

3 ለማገዝና ለመተጋገዝ ቅንነቱ

4 ለተሰራ እና ለተጨበጠ ነገር ስስት አልባ አድናቆቱ

5 ንባብና እና እውቀት ላይ ሲያድግ ማደሩ

6 አባዎራነቱ በባለቤቱና ልጆቹ ደስታና ጉዞ መታየቱ

7 ሚዛናዊነት ፣ ትህትና ፣እውነትና ማስረጃ ያለባቸው ሀሳቦቹ

8 ፍፁም ልክ ሆኖ ለመኖር መትጋቱ

9 አመስጋኝነቱና የማስታወስ አቅሙ

ምን አልባትም ከ18 አመታት ላላነሱ ጊዜያቶች ፊት ለፊት

ያየኋቸው የማንነቱ መልኮች ናቸው ። እናም ለኔ ተስፍሽ ከማከብራቸው ሰዎች መካከል አንዱና አብሬው ስሆን የማተርፍበት ጥቅሜ ነው።

ጃን ዋሴ

መዝጊያ፤ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የመዝገበ-አእምሮ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡ ይህ ጽሁፍ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የተጻፈና ትውልዱን ያስተምራል በሚል እሳቤ በተወዳጅ ሚድያ ዲጂታል ሚድያዎች የተሰነደ ነው፡፡ ዛሬ ሀምሌ 21 2015 ይህ ጽሁፍ ተሰነደ፡፡

በቅድሚያ ተስፋዬ ማሞ በታላቅ ትህትና ታሪኩን ለማካፈል ፈቃደኛ በመሆኑ አክብሮታችን መግለጽ እንወዳለን፡፡ ይህን የስነዳ ፕሮጀክት አንድ ካልንበት ሰአት አንስቶ ሙሉ ተባባሪ እዚህ ልንደርስ እንደምንችል ቀድሞ ያየ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ሰዎችን ለትውልዱ ማቀበል ይገባል፡፡ የህይወት ታሪካቸው ልዩ አበርክቷቸው ደግሞ ለስራ የሚያነሳሳ ነው፡፡ ታሪኩን እንዳየነው ህልሙን ያገኘ አንድ ሰው ማለት እርሱ ተስፋዬ ነው፡፡ በልቦለድ ስራዎች በፊልምና በማስታወቂያ ስራዎች ላይ 1980ዎቹ ሲነሳ ተስፍሽ ቀድመው ከሚነሱት መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህ የጥበብ ሰው ብዙ ሞክሯል ብቻ ሳይሆን ራሱን በማስተማር እውቀትን የገበየ በመሆኑ ዛሬ ከእርሱ የጥበብ ውሀ ይቀዳል፡፡ በብዙ የህይወት መልኮች አልፏልና ገራሚ እይታዎችን ይዟል፡፡

ነገሮች እንዴት መሆን እንዳለባቸው ያወቀ በመሆኑም ጥሩ ቤተሰብ አፍርቶ ልጆቹን ለወግ ማእረግ ያበቃ ነው፡፡ ይህ በቀላሉ አይመጣም፡፡ ዋናው ተመስጋኝ እግዚአብሄር ቢሆንም የባለታሪኩ የውሳኔ ሰው መሆን ጠቅሞታል፡፡ ስኬት የሚለካው ሰዎች በሚወስኑት ውሳኔ ነውና እርሱ የመወሰኑ ውጤት ነው፡፡ ከእንዲህ አይነት ታሪኮች የኪነጥበብ ሰዎች እንዲማሩ እንሻለን፡፡ በ3000 እና በ2500 ቃላት የተሰነዱ የሰዎችን ታሪክ አንብቦ መንቃት ይቻላል፡፡ መንቃት ከማንበብ መንቃት ልምድ ከመቃረም የሚገኝ በመሆኑ ይህ ታሪክ ተነቦ አንዳች ቁምነገር እንዲጨበጥበት እንሻለን፡፡ የሀገራችን ሰዎች የራስን ታሪክን በመንገር ሌሎችን ከሞት መታደግ እንደሚቻል ማመን አለባቸው፡፡ መድሀኒትን ይዞ ረጅም ጊዜ ማቆየት አያሻም፡፡ ፍቱን እንዲሆን ለወጣቱ ቶሎ መስጠት ነው፡፡ እንደ ተስፋዬ አይነቶቹ እነሆ እንዲህም ተኑሯል ብለው የህይወታቸውን ገጽ አካፍለዋል፡፡ ተከታዩ ሀገር ተረካቢ ደግሞ በተመሳሳይ መልኩ የተደረገለትን ያደርጋል፡፡ እንዲህ እንዲሆን ስለምንመኝ ነው ቀን ከሌት ታሪካችሁ ይሰነድ እያልን የምንሞግተው፡፡ እንደ ተስፍሽ አይነቶች ደግሞ ሲተባበሩ ብዙዎች ከተደበቁበት ብቅ እያሉ መድሀኒት ይሰጣሉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *