ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በግለ-ታሪክና ባለሙያዎችን በማመስገን ዙሪያ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ከጀመረ አመታት ተቆጥረዋል፡፡
ልክ የዛሬ 5 አመት የክቡር አቶ ተሾመ ገብረማሪያም ፤ የጸሀፌ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድን ፤ የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትን የመሳሰሉ የ44 ሰዎችን ታሪክ በሲዲ በድምጽና በምስል አቅርቦ አስመርቆ ነበር፡፡
ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በዚህ አመት የሪፖርተር ጋዜጣ ባለቤት የአቶ አማረ አረጋዊን እንዲሁም የአንጋፋውን የብእር አርበኛ የሙሉጌታ ሉሌን ግለ-ታሪክ በሲዲ ድምጽና በጽሁፍ ሰንዶ ለተመራማሪ ምቹ እንዲሆን ማድረጉ ይታወሳል፡፡
ድርጅቱ በቅርቡ አሳትሞ በሚያወጣው የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ / መዝገበ– አእምሮ ./ ከ1950-2000 ያሉና የነበሩ የሚድያ ሰዎችን ታሪክ አሰባስቦ ለህትመት ዝግጁ አድርጓል፡፡ 
ከእነዚህ ታላላቆችና እንደ ፈርጥ ከሚታዩት መካከል አንዷ ጋዜጠኛ ጸሀይ ተፈረደኝ ስትሆን ዛሬ መጋቢት 10 2014 በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር ‹‹ጸሀይ ተፈረደኝን እናክብር›› የተሰኘ መሰናዶ እውን ሆኖ ነበር፡፡ ይህን መሰናዶ ከጸሀይ ተፈረደኝ ቤተሰቦች ጋር በትብብር ያዘጋጀው ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ሲሆን የድርጅቱ መስራች እና ዋና ስራ አስፈጻሚ እዝራ እጅጉ እንዲህ በማለት ንግግር አድርጎ ነበር ‹‹…..ጸሀይን ለኢትዮጵያ ሚድያ ለዋለችው ውለታ እናመሰግናለን ልንል ይህን መሰናዶ አዘጋጅተናል፡፡ የሰሩ ሰዎች፤ የመልካም ሰብእና ባለቤቶች እንዲህ በአደባባይ ይመሰገናሉ፡፡ በየጓዳው ያሉ ትጉሀን ‹‹…ደግሞ እኔ ምን ሰርቼ ታሪኬ ለወግ ማእረግ ይበቃል? የሚሉበት ዘመን ያከትማል፡፡›› በማለት ሀሳቡን ገልጾ ነበር፡፡
ዛሬ መጋቢት 10 2014 በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር በተደረገው ‹‹ጸሀይን እናክብር›› በተሰኘው ታላቅ ስነ-ሰርአት በእቴጌ ጣይቱ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ድራማ የቀረበ ሲሆን አጭር ዘጋቢ ፊልምም ቀርቧል፡፡ በእለቱ ከ250 በላይ ሰዎች በስነስርአቱ ላይ የታደሙ ሲሆን ወደ 90 የሚጠጉ ሰዎች ለጸሀይ ተፈረደኝ በተዘጋጀ የክብር መዝገብ ላይ ለጸሀይ ያላቸውን አክብሮት አኑረዋል፡፡ ከጸሀይ ተፈረደኝ ጋር አብረው የሰሩ የሚድያ ባለሙያዎች አባይነሽ ብሩ ፣ እሸቱ ገለቱ ፤ መስፍን አሰፋና ደረጀ ተክሌ ስለ ጸሀይ ተፈረደኝ ምስክርነታቸውን የሰጡ ሲሆን የጋዜጠኛዋን ጠንካራ ሰብእና አብራርተው ገልጸዋል፡፡ በእለቱ ጸሐይ ተፈረደኝ ለተሰጣት አክብሮት አድናቆቷን ገልጻለች፡፡ የጸሀይ ተፈረደኝ ልጆችም ባደረጉት ንግግር እናታቸው ለብዙዎች አርአያ የምትሆን ታላቅ ሴት መሆኗን በዚህም ታላቅ ኩራት እንደሚሰማቸው ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በምድር ጦር የቅጥር ስነ-ስርአት በተሟላበት ሁኔታ ከተቀጠሩት 62/ሴት ወታደሮች ውስጥ አንዷ ፀሐይ ተፈረደኝ ነበረች፡፡ፀሐይ ተፈረደኝ የውትድርና ስልጠናውን ጨርሳ ከተመረቀች በኋዋላ በምድር ጦር በጽህፈት ስራ ላይ ተመደባ እየሰራች ባለበት ወቅት ለጦር ኃይሎች ሬድዮ ጋዜጠኝነት ሴቶች ይፈለጋሉ ሲባል ተመርጣ ለውድድር ቀረበች፡፡ ፀሐይ ውድድሩን ሶስተኛ በመውጣት ለስልጠና ወደማስታ ወቂያ ሚኒስቴር ተላከች፡፡ በጊዜው እነ ጌታቸው ኃ/ማር ያም፤ታደሰ ሙሉነህ፤ልኡል ሰገድ ኩምሳ፤ እና ሌሎችም እውቅ የጋዜጠኝነት ባለሙያ ዎች ለሶስት ወር የጋዜጠኝነትን ሙያ ሰለጠነች፡፡ በመሆኑም የጦር ኃይሎች ሬድዮ ጋዜጠኛ በመሆን ሙሉ በሙሉ መስራት የጀመረችው ከ1978 ዓ/ም ጀምሮ ሲሆን እስከ 1983/ዓ/ም ማለትም ኢህአዲግ አገሪቱን እስከተቆጣጠረበት ጊዜ ድረስ አገልግላለች፡፡ የጦር ኃይሎች ራዲዮ በሳምንት ሁለት ቀን ማለትም ረቡእና እሁድ ይተላለፍ የነበረ ሲሆን በተለይም የረቡእ እለት ፕሮግራሙ አዘጋጅ በመሆን ነበር የሰራችው፡፡ በኢትዮጵያ ሬድዮ በህይወት ዙሪያ እና ኢትዮጵያን እንቃኛት በተሰኘው መሰናዶ ትልቅ አሻራ ያኖረችው ጸሀይ ተፈረደኝ ዛሬም በ68 አመት እድሜዋ የጋዜጠኝነትን ሙያ በፍቅር በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡