ግራዝማች ተስፋይ አብርሃ /1911-1982/
የትግርኛ ጋዜጠኝነት አሻራ ያኖሩ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን፣ በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
እስከ ዛሬ 310 ሰዎችን ኣፈላልገን ታሪካቸውን ሰንደናል፤ ለወደፊትም በዚህ ስራችን ጠንክረን እንቀጥላለን፡፡ በ 2014 “የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ” በማለት ታሪኮችን ዳጎስ ያለ ጥራዝ የወጣውን መጽሀፍ አሳትመን ያሰራጨን ሲሆን፤ ባለታሪኮቹን ጨምሮ፤ ብዙ ሰዎች ማጣቀሻ ሰንድ እያደረጉ እንደሚጠቀሙበት መረጃ አለን። በዚህም ተበረታትተናል። ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ “ምን ታሪክ አለኝና?” የሚሉና ታሪካቸው በስፋት ተደራሽ ያልነረ፤ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን፤ የህይወት ገጽ እያስነበብን እንገኛለን፡፡
የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ የበርካታ ባለመልካም ተሞክሮ ዜጎችን ታሪኮችን መሰነዳችንን እንቀጥልበታለን፡፡ በህይወት የማይገኙትን አበርክቶም ለማስነበብ የተቻለንን እናደርጋለን፤ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ነው ብለን ስለምናምን፡፡ መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 200 የሚድያ ፤ የስነ-ጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ ከባለታሪኮቹ መካከል ግራዝማች ተስፋይ አብርሀ አንዱ ናቸው፡፡ ግራዝማች ተስፋይ በትግርኛ ጋዜጠኝነት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ከ30 አመት በፊት ህይወታቸው ያለፈ ባለውለታ ናቸው፡፡ እዝራ እጅጉ የህይወት ታሪካቸውን እንደሚከተለው ሰንዶታል፡፡
ግራዝማች ተስፋይ አብርሀ፡ካባታቸው አቶ ኣብርሃ በራኺ፣ከእናታቸው ወ/ሮ ጨረቃ ሃብተጽዮን በ1911ዓ.ም፡በሐማሴን አውራጃ፡በተከላ ዓገባ ልዩ ስሙ ጸዓዘጋ መንደር ተወለዱ።
የትምህርት ደረጃ-በጥንት ስርዓት የሚሰጥ የነበረው የትምህርት ስርዐት፡ከቤተ ክርስትያን የቆሎ ትምህርት ቤት ገብተው ተምረዋል፡፡ በዚያን ጊዜ ለአበሾች በጣልያን ወራሪ መንግስት ይሰጥ የነበረው የትምህርት ደረጃ እስከ 4ኛ ክፍል ብቻ ነበር።እርሳቸውም እስከ 4ኛ ክፍል ተምረዋል። ከዛ በኋላም ለትምህርት በነበራቸው ትልቅ ፍላጎት ተነሳስተው-በእንግሊዝ ወታደራዊ መንግስት ኤርትራ ላይ ይሰጥ የነበረው ሻል ያለ የትምህርት ደረጃ እና ዓይነት በመፈጠሩ ገብተው ተምረዋል። ከዛም በተመሳሳይ ትልቅ ህልምና ራእይ አንግበው ስለ ነበር-በግል ጥረታቸው በማታ ክፍለ ጊዜ የትምህርት እድል ይሰጥ ስለ ነበር-እዛም ገብተው ተምረዋል። በዚህም፡ለ3 ዓመት የሕግ ትምህርት ተማሩ።በማስከተልም ለ3 ዓመት በንግድ የትምህርት ዘርፍ ላይ ተምረዋል።
በስራ አለም ደግሞ ከ1938-1948 ዓ/ም፡ለድፍን አስር ዓመት በቅድስት ማርያም ትምህርት ቤት፡ አስተምረዋል።
ከህዳር 14፡1948 ዓ.ም በህዝብ ግንኙነት ተቋም (Public Relation) የተባለው የመንግሥት መስሪያ ቤት “ዘመን” በተባለው በትግርኛ ቋንቋ የሚዘጋጀው ጋዜጣ ላይ እንደ ምክትል አዘጋጅ፡ለ7 ዓመታት ሙያዊ አገልግሎት ሰጥተዋል። ከዛ በኋላም ከሚያዝያ 1955 ዓ.ም፡ጀምረው ደግሞ የ “ህብረት” ጋዜጣ ላይ እንደ ዋና አዘጋጅ በመሆን በ1967 ዓ.ም በጡረታ እስከተገለሉበት ድረስ፡በቅንነት እና በታማኝነት ህዝባቸው እና መንግስታቸውን አገልግለዋል።
ግራዝማች ተስፋይ፡በአገር ፍቅር በነበራቸው የፀና አቋምና ፍቅር ተነስተው-የሀገር ፍቅር ማሕበር፡በ1934 ዓ/ም ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮው፡የሐማሴን አውራጃ የሀገር ፍቅር ማሕበርም ፡ምክትል ዋና ጸሓፊ በመሆን ኤርትራ ከአካልዋ ከሆነችው ኢትዮጵያ በፌዴሬሽን በ1945 እስከ ተወሀደች ድረስ በጽናት አገልግለዋል። ከዚያ በመቀጠልም፣ “ኢትዮጵያ ወይ ሞት” በሚል ዓላማ አንግበው ከፍ ያለ አስተዋፅኦ እንደፈጸሙ ይታወቃል። ግራዝማች ተስፋይ፡በፍኖተ-ብርሀን ጋዜጣ ላይም እንደ መስራች ብቻ ሳይሆን እንደ ዋና ኣዘጋጅ በመሆንም ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ እንደ አባል ይሁን እንደ ሥራ አስፈጻሚም በመሆንም ለጋዜጣ ስራው ትልቅ ሚና አበርክተዋል።
ፍኖተ-ብርኃን ጋዜጣ በቅድስት ማርያም ቤተ ክርስትያን ስር የምትተዳደር ጋዜጣ ነበረች። ባጭሩ፡ግራዝማች ተስፋይ አብራሃ በመምህርነት እና በጋዜጠኝነትን ሞያ ተሰማርተው ለአገራቸው እና ለህዝባቸው እስከ ህይወታቸው ፍጻሜ ድረስ አገልግለዋል። በተለይ በ2ኛው የአለም ጦርነት የተሳተፉ ወደ ትምህርት ቤት ያልሄዱ የኤርትራ ተወላጆች፡በጦርነት ያሳለፉትን የሕይወት ተሞክሮ እንዲጽፉ ይወተዉቱ ነበር።
በሳቸው ምክር እና ሀሳብም ማንበብና መጻፍ ካለመቻል ተነስተው መጽሓፍ የጻፉ ሰዎች አሉ። ሌላም በባህልና ቋንቋ በነበራቸው እውቀት እና የካበተ ልምድ ለደራስያን እና ጸሓፍያን በሙያቸው አስተዋጽኦ ያደርጉ እንደ ነበር-ከ32 ዓመት በፊት የታተሙትን መጽሀፎች መመልከት ይቻላል፡፡
በ20ኛው ክፍለ-ዘመን የነበሩ የትግርኛ ጋዜጦችን በተመለከተ የተወሰነ ጥናት እና ምርምርን ያደረጉ ሰዎች እንደሚያስረዱት የግራዝማች ተስፋይ ዉለታ ትልቅ ነው፡፡ ግራዝማች ተስፋይ ኣብራሃ፡ያልተዘመረላቸው ትልቅ ጋዜጠኛ መሆናቸውን ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡ ጋዜጠኛ እና ጸሐፊ ግራዝማች ተስፋይ ኣብራሃ አንጋፋ ከሚባሉ ጋዜጠኞች አንዱ ነበሩ። በአስመራ ዩኒቨርሲቲ ተምረዋል፡፡በማስታወቂያ እና መርሐ ጽህፈት ቤት እስከ ከፍተኛ አዘጋጅ በመሆን ሰርተዋል።
ምክትል ዋና ኣዘጋጅ በመሆንም በህብረት ጋዜጣም ሰርተዋል። ግራዝማች ተስፋይ ጋዜጠኛ ከመሆናቸው በፊትም አስተማሪ ሆኖው ይሰሩ ነበር።በተለይ በአስመራ ከተማ የሚገኘው፡ማርያም ጽዮን ቤተ ክርስትያን ስር የሚተዳደረው-ቅድስት ማርያም ትምህርት ቤትም አስተምረዋል። ከወይዘሮ ሉል ጎይቶኦም ተጋብተው 7 ልጆች አፍርተዋል።ከወለዷዋቸው 7 ልጆች 3 ቱም በህይወት የሉም።ሌሎቹም እና እናታቸው ግን በህይወት እንዳሉ በ2022 ያደረግነው ጥረት ያስረዳል። ታመው በ1982 ኣስመራ ከተማ እንደ ሞቱም በትውልድ አገራቸው፡በሰራየ አውራጃ፣በድባርዋ ወረዳ በሚገኘው ዓዲ ገዳ በሚባል መንደር ተቀብረዋል። የግራዝማች የቀብር ስነ ስርዓት ሕዳር 29፡1982 ዓ/ም ነበር በ71 እድሚያቸው ታመው ከዚህ አለም ድካም በሞት ነው የተለዩት።
የሞቱበትም ቀን ሕዳር 28፡1982 ዓ/ም ነው። በህልፈታቸውም ጊዜ የማስታወቂያ ሚኒስቴር በኤርትራ ክፍለ- ሀገር ጨንፈር መስርያ ቤት፡የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል።
መዝጊያ
ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የመዝገበ-አእምሮ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡ በሀገራችን የጋዜጠኝነት ሥራ በትግርኛ ቋንቋ ሲሰራበት ኖሯል፡፡ እንደ ህብረት ያሉ ጋዜጦች ብዙ ዜናዎችን በትግርኛ ሲያስተናግዱ ከርመዋል፡፡ ይህ የጋዜጠኝነቱ አንዱ መልክ ሲሆን በሙያው ያለፉ ሰዎችም እንደ ትልቅ ባለታሪክ የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ከእነዚህም አንዱ ግራዝማች ተስፋይ አንዱ ናቸው፡፡ እርሳቸው በትግርኛ ቋንቋ ሲጽፉ ኖረዋል፡፡ የሀገራችን የጋዜጠኝነት ስራ ከአማርኛ ባሻገር በትግርኛ ቋንቋ ሲሰራበት እንደነበር አንዱ ማሳያ የግራዝማች የሙያ አበርክቶ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ታሪክ ከአማርኛ በዘለለ ሲሰራባቸው የነበሩ ቋንቋዎችንም ማጥናት ይኖርበታል፡፡