ጋዜጠኛ እና የዜማ እና ግጥም ደራሲ ጽጌ ገብረአምላክ አረፈ

ጋዜጠኛ እና የዜማ እና ግጥም ደራሲ ጽጌ ገብረአምላክ አረፈ ፥ ፀሐዬ ደመቀች በሚለው የዜማ እና ግጥም ድርሰቱ ይታወቃል ከ1970ዎቹ ጀምሮ በጋዜጠኝነት እና በዜማ ግጥም ደራሲነት የሚታወቀው ጽጌ ገብረአምላክ ዛሬ መስከረም 27 2016 ማረፉ ተሰማ። በ1977 በውጭ ቋንቋ እና ስነ ጽሁፍ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተመረቀው ጽጌ ለታዋቂ ድምጻውያን የዜማ ግጥሞችን በመስጠት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱ ይነገራል ።

የዜማ ግጥም ከሠጣቸው ድምጻውያን መካከልም ጥላሁን ገሠሠ፣መልካሙ ተበጀ፣ተሾመ ወልዴ፣ነጻነት መለሠ ይገኙበታል ። ጽጌ ለጥላሁን ገሠሠ ,”ይህቺ ናት ጨዋታ ፣ ለነጻነት መለሠ ደግሞ እንደ ሀምሌ ፀሀይ የተሰኘውን የዜማ ግጥም ሰጥቷቸዋል። ገና በወጣትነት ፒያሳ አካባቢ በሚገኙ የቀበሌ ኪነት ውስጥ መሳተፍ የጀመረው ጽጌ ይህን ዝንባሌውን የበለጠ በማዳበር ቀጥሎበታል። ጽጌ በ 1985 ወደ ኢቲቪ በመዛወር ለ 3 ዓመታት በእንግሊዝኛ ክፍል ሀላፊነት አገልግሏል ።

በመቀጠል ፣ ወደ ኢትዮጵያን ሄራልድ በመግባት ለ4አመታት በዋና አዘጋጅነት ሙያዊ አደራውን ሲወጣ ነበር ። ከ1990ዎቹ ወዲህ በሌሎች ድርጅቶች ውስጥ በትጋት ሲያገለግል የነበረ ባለሙያ ነበር ። ጋዜጠኛ እና የዜማ ግጥም ደራሲ በ1951 ዓ.ም በመቀሌ የተወለደ ሲሆን በህይወቱ መጨረሻ አካባቢ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሲያገለግል ነበር ። የጋዜጠኛ ጽጌ ገብረአምላክ የቀብር ስነ-ስርአት ነገ ሰኞ መስከረም 28 2016 ሲኤምሲ በሚገኘው ሳህሊተ ምህረት ቤተ -ክርስቲያን ከቀኑ 9 ሰዓት ይፈጸማል ።

የመረጃ ምንጭ ጌጡ ተመስገን መረጃ ጥንቅር ተወዳጅ ሚድያ (እዝራ እጅጉ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *