ዶክተር ጌታቸው ታረቀኝ
ዶክተር ጌታቸው ታረቀኝ- የራሱን መንገድ የፈጠረ ከያኒ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 150 የሚድያ ፤ የስነ-ጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡
በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል ዶክተር ጌታቸው ታረቀኝ ይገኝበታል፡፡ ዶክተር ጌታቸው ታረቀኝ በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቴአትር ጥበባት ተመርቆ ባመጣው ጥሩ ውጤት እዚያው መምህር ሆኖ ቀርቶ ብዙዎችን በእውቀት ያስታጠቀ ነው፡፡ በተጨማሪም በ1985 አ.ም የአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽን በዋና ስራ አስኪያጅነት የመራ እና በቴአትር ቤቱም ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ ያስቻለ ነው፡፡ ዶክተር ጌታቸው ለ27 አመታት መኖሪያውን በአሜሪካ አድርጎ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን ያጠና ሲሆን በዚህ ሙያውም አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ ሀገር ቤት ሳለ ቤጊዮሎጂ ፤ ካሊጉላ ፤ ደራሲው በሰማይ ቤት የመሳሳሉ ቴአትሮችን በመተርጎምና ለእይታ በማብቃት ትልቅ አሻራውን ማሳረፍ ችሏል፡፡ ጌታቸው ታረቀኝ ህይወትን እና ታሪክን በራሱ መንገድ የሚመለከትና የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲመጣ ከሚሹት መካከል አንዱ ነው፡፡ እናም የህይወት ታሪኩን እንዲነግረን ስንጠይቀው በራሱ መንገድ የራሱን እይታ እንዲህ ተርኮልናል፡፡
ጌታቸው ታረቀኝ ስለራሱ
ከመጀመሪያው ከእነኚህ ዉድ አዋቂዎች መሐል ስሜ በመካተቱ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ጭራሽ ከእነኚህ ሰዎች ጋር በእኩል የሚያቆመኝ ነገር እንደሌለኝ ባውቀውም ይሄን እድል በመጠቀም የሚከተለውን ለማለት እወዳለሁ፡፡ ተወልጄ ያደግኩት በአዲስ አበባ ከተማ፤ ልደታ ቤተ-ክርስቲያን አካባቢ ነበር፡፡ አካባቢው ከጦር ኃይሎች እስከ ቄራ ድረስ ብዙ የጦር ካምፖች የነበሩበት ሲሆን መንግስት ከተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ሰዎችን እየመለመለ የሚያመጣበትና የሚቀጥርበት ቦታ በመሆኑ፤ አስተዳደጌም ከብዙ ብሄሮች ከመጡ ልጆችና ቤተሰቦች ጋር ስለነበር ሰፈራችን “ኢትዮጵያ” የሚባለውን ሃሳብ የሚወክል ሰፈር ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በሰፈራችን ያልነበረ “ብሔር” አልነበረም፡፡ ሁላችንም በድብድብና በፍቅር አድገን ነበር፡፡ (ኡጅሉ ኦፋ የሚባል በጣም መልኩ የጠቆረ፤ ረጅም ሰዉ፤ ከጋምቤላ መጥቶ የምድር ጦርን ወክሎ የሚወዳደር ቦክሰኛ ሁሉ ነበር፡፡ ከወሎዬ ጋር የተጋባ፡፡ ብዙዎቻችን ከስራ ሲወጣ ጠብቀን እንላፋው ነበር፡፡
እናም በትምህርት ጎልብቼ አዲሰ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ1979 ዓ.ም ስገባ በህይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን የሚሰድብ፤ ኢትዮጵያዊነትን የሚያጠለሽ “ገተር ሊትሬቸር” ያየሁበት በዩኒቨርስቲዉ ሽንት ቤቶችና፤ ከኬኔዲ ላይብሪረ በምንዋሳቸው መፅሀፎች ላይ የተሞነጫጨሩ ስድቦች ነበሩ፡፡ ነገሩ በጊዜው እንግዳ የሆነና፤ ከመጀመሪያው አስቂኝ የነበረ ቢሆንም ዩኒቨርሲቲዉ ይሄን አይነቱን ተራ ነገር ለማጥፋት አንድም እርምጃ ባለመውሰዱም ያሳስበኝ ነበር፡፡ ሽንት ቤቱን ለምን ቀለም እየቀቡ ስድቦቹን እንደማያጠፉት ይገርመኝ ነበር፡፡ አንዱን ብሔር የበላይ ሌላዉን የበታች አድርጎ የሚያሳየውን ክፍፍሉን እና ጥላቻውን ማበረታታት ፈልገውት ይሆን እንደሆነም አልገባኝም ነበር፡፡
በጊዜዉ ዩኒቨርሲቲዉ የእውቀት መገብያ ተቋም መሆኑ ቀርቶ ይሄን አይነቱን ተራና ወራዳ ሃሳብ ከማስተላለፉ ባሻገር “መምህራን” የሚባሉትም አብዛኛዎቹ ለራሳቸው ክብር (ፍርሃት) ሲሉ ማሰብ የሚችለዉን ተማሪ የሚያስፈራሩና፤ ልመና እና አድር-ባይነትን የሚያስተምሩ ሆነው ስላገኘኋቸዉም “ቤጊዮሎጂ” የሚባል ስራም በመምህራን ማህበር መፅሄት ላይ እና በመድረክም አቅርቤው ነበር፡፡ ሁላችንንም የአይምሮ ስንኩል፤ የነገሩንን ሸምድዶ ከመድገም በስተቀር፤ ማሰብ (ክሪቲካል ቲንኪንግ) የማንችል በሁለት እግራችን መቆም የማንችልና በትንሹም ነገር የማንስማማ “ለማኝ” አድርገውናል ብዬ አስባለሁ፡፡
ዛሬ በአምሳ ስድስት አመቴ መለስ ብዬ ሳስበው የአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ በዚህች የጋራ በነበረችው አገራችን ላይ ያደረሰው በደል በዝምታ መታለፉና በህግ ፊት አለመዳኘቱ ሁሌም ያሳስበኛል፡፡ ለልጆቼ የማሳልፈው አገር አለመኖሩና፤ ያኔ በየሽንት ቤቱ ይሰዳደቡ የነበሩት ደካሞችም፤ ጊዜ ተለዉጦ፤ ባንኩንም ታንኩንም ይዘው፤ አገር ከልለዉና ከፋፍለዉ፤ ነፍስና ንብረት እያጠፉ ስመለከት የአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ ገና በአፍላ እድሜዬ ያደረሰብኝ ስነልቦናዊ ተፅእኖ የተለየ የህይወት ታሪክ እንዳይኖረኝ አድርጎኛል ብዬ አምናለሁ፡፡
“አገሬ” ብዬ ያደግኩባት አገር ዛሬ ባይተዋር ስታደርገኝ ያሳፍረኛል፡፡ ልጆቼ ከተለያዩ “ብሄሮች” የተወለዱና በዛሬው ፎርሙላ “አገር አልባ፤ ክልል አልባ” በመሆናቸው እንደ አባት አሳፍሬአቸዋለሁ፡፡ ያለ አገር አስቀርቼ ባዶ ሜዳ ላይ ጥያቸዋለሁ፡፡ ችግሩ ከከፋም ወደ የት አገር እንደሚሄዱም አላዉቅም፡፡ ልጆቼ “ዉጭ” የሚባለዉ አገር ይወለዱ እንጂ ሁሌም የእኔ የኢትዮጵያም ናቸው፡፡ አድገዉበታል፤ በስነ-ልቦናዊ ማንነታቸዉ ኢትዮጵያዊ ናቸዉ፡፡ ለዚህ ሰጪም አያስፈልጋቸዉም፡፡
አሁን ራሴን በጡረታ አግልዬ የምኖርና ከሠላም በስተቀር ምንም ነገር የማልፈልግ ቢሆንም ቀደም ብዬ እንዳልኩት፤ የህግ እውቀት ያላቸውን ሰዎች ለማሰባሰብና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ላይ የሲቪል ክስ በማቅረብ፤ ዛሬ ለሚፈናቀሉት፤ በግፍ ለሚገደሉት ድሆች ተገቢዉን ካሳ ዩኒቨርሲቲዉ እንዲከፍልና ይቅርታ እንዲጠይቅ፤ የህግ “ትምህርት” ሳይሆን “እዉቀት” ያላቸዉን ሰዎች እርዳታ እየለመንኩ እገኛለሁ፡፡ በሰለጠነው አለም የባርያ ንግድን አስመልክቶ ተሳትፈዉ የነበሩ ባንኮችና ሌሎች ድርጅቶች፤ ትላልቅ ዩነቨርሲቲዎችን ጨምሮ፤ በህግ ፊት ተጠያቂ የሆኑበት ሁኔታ ስላለ፤ ቅንነቱ ካለ በዚህ አገር ለተሰራዉ ግፍና በደል ዩኒቨርሲቲዉን በህግ ፊት ማቅረቡና አስፈላጊዉን ካሳ እና ማሻሻያ እንዲያደርግ ማስገደዱ ብዙም አስቸጋሪ አይመስለኝም፡፡
ስመ ጥሩው ደራሲ አቤ ጉበኛ “አልወለድም” የሚል ስራ በልጅነቴ አስነብቦኝ ስለነበር፤ እኔም እንደ እሱ ጥልቅና አነጋጋሪ ስራ ለመስራት ሁሌም እመኝ ነበር፤ ይሁን እንጂ፤ ዛሬ “ኪነ-ጥበብ” የሚባለዉ ከተራ ፕሮፓጋንዳ የማይሻልና፤ “አርቲስት” የሚባሉትም አብዛኛዎቹ በጣም በከፋ ችግር ዉስጥ የሚኖሩ በመሆናቸዉ፡ “አጤ ምኒሊክ አድዋ ሳይዘምቱ አዲስ አባባ ተደብቀዉ ነበር” የሚል ፅሁፍ አምጡ ቢባሉ የሚሽቀዳደሙ በመሆናቸው፤ የዘመኑን ቅዠት አንዱ ማሳያ ከመሆኑ ባሻገር ስለ ጥበብ እድገት ማዉራት የሚቻልበት ዘመን ላይ ያለን አይመስለኝም፡፡ ጥላቻ በዘጠና ቋንቋ ተተርጉሞ፤ ቀለም እየተቀባ በታላቅ ፍጥነት ስለተሰራጨ ብቻ የሚያቀጭጭ ጥላቻ ከመሆን አያመልጥም፡፡
በተለምዶ “እዉነታ” የሚባለዉ ራሱ ከልቦለድ አልፎ ተአማኒነት የሌለዉ ቀፋፊ ልብ-ወለድ (ዴስቶፒያን ፊክሽን) እንዲሆን ካደረጉት ተቋሞች መሐልም ዋናዉ የአዲስ አባባዉ ዩኒቨርሲቲ በህግ እስከሚዳኝ ድረስም ይሄንን ከቀን ቅዥት የባሰ “እዉነታ” ወደ “ልብ-ወለድ” መቀየር የሚችል ፀሐፊም ከእንግዲህ የሚፈጠር አይመስለኝም፡፡ ለሃያ ስድስት አመታት በስደት ኖሬ ሶስት ልጆችን በትዳር ያሳደግኩ ሲሆን፤ በትምህርቴም (በስተ-መጨረሻዉ) በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የዶክትሬት ዲግሪ “ቴክሳስ ኤ ኤንድ ኤም” ከሚባል ዩኒቨርሲቲ ተቀብያለሁ፡፡ በዉጭም አገር ለተለያዩ የቴሌካም ካምፓኒዎችና፤ ወደ አገሬ ከተመለስኩ በኋም፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በአንድ የግል ባንክ ተቀጥሬ (ኮር ባንኪንግ ኔትዎርክ) በተማርኩት ሙያ የድርሻዬን ግልጋሎት አበርክቻለሁ፡፡
ትምህርት ጥሩ ነገር ነዉ፤ ይሁንና መማር ማለትና “እዉቀት መገብየት” ሁለት የተለያዩ ነገሮች በመሆናቸዉ ዛሬም “እዉቀት” ለመገብየት ጥረት እያደረግኩ እገኛለሁ፡፡ በሃገራችን ብዙ የተማሩ፤ ብዙ የአካዳሚ ዲግሪዎች ያላቸዉ ሰዎች ቢኖሩንም “አዋቂ” የምላቸዉ ሰዎች እጅግ ቁጥራቸዉ ትንሽ መሆኑና በዝምታ እንዲቀመጡ መገደዳቸዉ እንደዜጋ ያሳስበኛል፡፡
እዉቀት ከዩንቨርሲቲዎች ሳይሆን የማህበረሰብን ስነልቦና እና፤ የአካባቢን (ጂኦ-ፖሊቲክስ) ከማገናዘብና ከማዳመጥ የሚመጣ መሆኑ ተዘንግቶ፤ የአገራችንና የዉጭ የመገናኛ ብዙሃን፤ ብዙ ትምህርት ባላቸዉ ዶክተሮች፤ ግና “እዉቀት” በሌላቸዉ ሰዎች ኤኮ ቼምበር እሰጥ-አገባ የተሞላ መሆኑና፤ መደማመጥ በሌለበት ተራ ብሽሽቅ መሞላቱ ያሳስበኛል፡፡ አገራችንን ከዉጭ ወራሪ ጠብቀዉ፤ ልዩነታችንን አቻችለዉ ያቆዩልን ሰዎች ከአይቪ ሊግ ኮሌጅ ተመርቀዉ የወጡ ሳይሆን ማገናዘብ የሚችሉና ሆደ- ሰፊ ምሁራን መሆናቸዉ ተረስቶ፤ ዛሬ በፈረንጅ ቋንቋ የሚናገሩትን ምሁራን አዳምጦ የሚሉትን ነገር መገንዘብ በጣም ከባድ ሆኗል፡፡ (በጣም ከምኮራባቸዉ ምሑራን መሐል ታላቁ የታሪክ ምሑርና ጋዜጠኛ ጳዉሎስ ኞኞ ጭራሽ ዩንቨርሲቲ የሚባለዉን የማያዉቅ ግና ብዙዎቻችንን ያስተማረ ታላቅ ሰዉ ነበር፡፡ ማሞ ካቻ የተባሉ ትምህርት ቤት ያልገቡ ኢንጂነርም፤ በህዝብ ማመላለሻ አዉቶቢስ (ኤሮ ዳይናሚክስ) ቅርፅ ላይ የፈጠሩት ለዉጥ፤ በጊዜዉ በተደጋጋሚ እየተገለበጡ ነፍስና ንብረትን ያጠፉ የነበሩትን የህዝብ ማመላሻ ተሽከርካሪዎች አደጋን በእጅጉ እንዲቀንስ ማድረጉን ስታስተዉለዉ በዘመናዊዉ ትምህርት ላይ ያለህን እምነት የሚሸረሽር ነዉ፡፡)
እዚህ ያደረሰንን የቅዠት ዘመን በተመለከተም በርካታ መፅሐፎች በአማርኛና በእንግሊዝ ቋንቋ የፃፍኩ ሲሆን፤ ብታነቡት እሰየዉ፤ ባታነቡትም ግድ የለኝም፡፡ (በቅርቡ በአለም አቀፍ ደረጃ የመፅሐፍ ማቃጠል ዘመቻ ስለሚኖርም ፍፃሜዉ ሩቅ አይሆንም፡፡) በዩኒቨርሲቲ መምህርነትም፤ በስራ አስኪያጅነትም በዳይሬክተርነትም በኢንጅነርነትም እዚህም እዛም ያገለገልኩ ብሆንም፤ የግል ታሪኬ ግን ከሃፍረት የፀዳ ላለመሆኑ እንደ እኔ ልጆቹን አገር-አልባ ያደረገ ሁሉ እንደሚገነዘበኝ እምነቴ ነዉ፡፡ የህይወት ታሪኬ፤ ለጊዜዉ ፍፃሜዉ ባይታወቅም፤ ባጭሩ የኪሳራ እንደነበርና፤ ያለፍኩበት የድርቅና ዘመንም ለዚሁ ኪሳራ እንደዳረገኝ መመልከቱ አዳጋች እንደማይሆን እገምታለሁ፡፡ በአንድ መስመር ይጠቃለል ከተባለም “ተወልዶ ሞክሮ ነበር፤ ግና ከመክስር አላመለጠም” የሚለዉ በቂ ይመስለኛል፡፡
አመሠግናለሁ፡፡
ጌታቸዉ ታረቀኝ (ዶ/ር)
ስለ ጌታቸው ታረቀኝ / ዶክተር የተሰጡ ምስክርነቶች
የዚህ የህይወት ታሪክ አሰናጅ ይህን ጽሁፍ የተሟላ ለማድረግ ከዶክተር ጌታቸው ታረቀኝ ጋር ከ 4 ሰአት የበለጠ የወዳጅ ጭውውት አድርጓል፡፡ ጌታቸው ታረቀኝ ታሪኩን በዝርዝር ይህን አደረግኩ ብሎ ባይነግረንም የለፋ እና የደከመ ስራው ያሳውቀዋልና ስለ ጌታቸው አንዳንድ ጥናቶችን ስናደርግ ብዙ ጠቃሚ እውነቶችን አግኝተናል፡፡ በተለይ ከ1982-1988 ባሉት 6 አመታት በሀገራችን የቴአትር ታሪክ ጌታቸው አዳዲስ የአጻጻፍ ስልቶችን አስተዋውቋል፡፡ የዚህ ታሪክ አሰናጅ ደራሲው በሰማይ ቤት እና ካሊጉላ የተሰኘውን የጌታቸውን ስክሪፕት እንደተመለከተው ከያኒው ጌታቸው ለአዲስ መንገድ የተፈጠረ ለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡ ይህም ሲባል ከተለመደው መንገድ ወጣ በማለት የራሱን ዳና በመከተል አንድ አሻራ ማስቀመጡን ልብ ይሏል፡፡ ጌታቸውን አግኝተነው የህይወት ታሪክህን ንገረን ስንለው ከላይ የተቀመጠውን ቃል በቃል እንድናወጣ በነገረን መሰረት እነሆ ታሪኩን አስቀምጠናል፡፡ ዋናው የዚህ ፕሮጀክት ግብ የህይወት ታሪክን በባለታሪኩ ፈቃድ ላይ ተመስርተን የምንሰንድ በመሆኑ በዚህ መልኩ የጌታቸውን ሀሳብ አክብረን ይሄ ነው ታሪኬ ያለውን አውጥተናል፡፡
እንደአጠቃላይ ግን ጌታቸው ታረቀኝ ምን አይነት ከያኒ ነበር የሚለውን በወጉ ለመረዳት 9 ሁነኛ ሰዎችን አነጋግረን ነበር፡፡ ዘጠኙም በአንድ ድምጽ ጌታቸው ከበፊት ጀምሮ የራሱን መንገድ መከተል የሚያረካው ሰው ነበር ሲሉ ሀሳባቸውን ለግሰዋል፡፡ ጌታቸው ታረቀኝ ከ1988-2001 ድረስ ለ13 አመታት በባህር ማዶ ኖሮ በአይቲ ሙያ ተመርቆ በአንድ የግል ተቋም ይሰራ ነበር፡፡ ከዚያም ወደ ባህር ማዶ ተመልሶ ለታላላቅ ተቋማት ሲያገለግል ነበር፡፡ ሙያ ቢቀይርም ውስጡ ያለው የጥበብ ናፍቆት ትኩስ ነበርና ስራዎቹን በማሳተምና ዳግም ወደ መድረክ እንዲቀርቡ የተቻለውን አድርጓል፡፡ ወደ ፊት በስራዎቹ ላይ አንዳንድ ነጥቦችን ማንሳታችን እንደተጠበቀ ሆኖ ይህ ጽሁፍ ግን ጌታቸው ታረቀኝን በመጠኑ የሚያሳውቅ ይመስለናል፡፡አብረውት የሰሩ እና የተማሩ የሚያውቁት ደግሞ የሰጡትን ሀሳብ እንከታተል፡፡
ዳግማዊ አመለወርቅ ፈይሳ ስለ ጌታቸው ታረቀኝ
ዳግማዊ የአራተኛ አመት ዩንቨርስቲ ተማሪ እያለ ጌታቸው ታረቀኝ ደግሞ የሶስተኛ አመት ተማሪ ሆነው ትውውቃቸውን ጀመሩት፡፡ በጊዜው አንድ ክፍል ከነበሩት ከነግርማ ደገፋ እና ከሌሎችም ጋር ጌታቸው ጥሩ ፕሮዳክሽን አቋቁሞ ነበር። ዳግማዊ ስለ ጌታቸው በትዝታ ሲያስረዳ ፦‹‹…..ጌታቸው በጊዜው ፈገግታ የማይለቀው ፣ ቀይ ወጣት ፣ ሰው የሚጋብዝ ፊት ያለው፣ ለቲያትር የተሰጠ ሰው፣ ፍጥነት ያለው ቀልጣፋ ተማሪ ነበር ። ተማሪ ሆኖ እነ ጌታቸው ማንጉዳይ በሚያዘጋጁት የቅዳሜ መዝናኛ ፕሮግራም ላይ ድራማ ያቀርብ ነበር። በኢትዮጵያ ሬዲዩ የቅዳሜ ፕሮግራም ላይ ይተላለፉ ከነበሩት ተውኔቶቹ ላይ የመሳተፍ እድል ያጋጠመኝ ሲሆን ከተማሪነቱ ጀምሮ በፅሁፍ ስራዎቹ እንከን የማይወጣለት ስለነበር ብዙዎች አድናቆታቸውን ይቸሩት ነበር፡፡›› ሲል ተናግሯል፡፡
ዳግማዊ እንደሚናገረው ጌታቸው እስክሪፕት በመጻፍ ፈጣን ነበር፡፡ በፍጥነት ሃሳቦችን የማፍለቅም ልዩ ክህሎትም ነበረው፡፡ በዚህ ፍጥነቱም ብዙ የፃፋቸው ተውኔቶች ያሉት ሲሆን ፍጥነቱ ውጤታማ አድርጎታል። አንድ ሰው አንድ ተውኔት ለመፃፍ ከ ስድስት ወር እስከ አንድ አመት የሚፈጅበትን ጌታቸው ግን ፈጣን በመሆኑ በአንድ ቀን እስክሪፕት ፅፎ ሊያመጣ ይችላል። ሁሌም በታየ ቁጥር ከእስክሪፕት እና ከቲያትር ጋር አብሮ ነበር።
‹‹…..ተውኔቶቹ እና ፅሁፎቹ ከሌላው ገንጠል ያሉ እና ለየት ያለ ገፀ- ባህሪያትን የመፍጠር የተለዩ ሃሳቦችን የማንሳት እና ሁሌም ከተለመደው ነገር ወጣ ያሉ ነገሮች ነበሩ። የሳጥናኤል አበሳ ፣ ደራሲው በሰማይ ቤት እንዲሁም ሌሎች ትያትሮቹ ወጣ ያሉ መሆናቸውን ማየት ይቻላል። በቲያትሩ ቢገፋበት እና ቢሰራበት መልካም የነበረ ቢሆንም ከሃገር ከወጣ በኋላ ግን ሙሉ ለሙሉ ትያትርን ትቶ ይገኛል። ከሚያፈልቀው ቲያትሩ ይራቅ እንጂ ጌታቸውን ባሳተማቸው መጽሀፎቹ ማግኘት እንችላለን። በባህሪው በራሱ የሚተማመን ፣ ቁጡ ፣ ቆፍጣና ፣ በመብቱ ጉዳይ ቀልድ የማያውቅ፣ ፊት ለፊት ተናጋሪ የዚህን ያህል ደግሞ ተጫዋች ፣ ዘናጭ ሰው ነው። በቲያትር እና ባህል አዳራሽ ገና በ 26 አመቱ መምራት የቻለ ነው። ጌታቸው በኢትዮጵያ ትያትር ትልቅ አሻራ መጣል የቻለ እና ትልቅ ቦታ ያለው ነው›› ሲል ዳግማዊ ፈይሳ ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡
ጌታቸው ታረቀኝ በአለማየሁ ታደሰ አንደበት
አለማየሁ ታደሰ የ2ኛ አመት የቴአትር ተማሪ እያለ ጌታቸው ደግሞ ረዳት ምሩቅ መምህር ሆኖ ነበር፡፡ያኔ የተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬገሰሰ ረዳት ሆኖ ነበር፡፡ አለማየሁ 30 አመት ወደ ኋላ መለስ ብሎ ያንን ዘመን ሲያስታውስ ‹‹….እነጀማነሽ ሰለሞን ፣ ፍቃዱ ተ/ማሪያም የሚተውኑባቸው ብዙ የሬዲዩ ድራማዎች በቅዳሜ ከሰአት በኢትዮጵያ ሬድዮ ይተላለፉ ነበር። ደራሲ ጌታቸው ታረቀኝ በድራማዎቹ ይታወቅ ስለነበር በጊዜውም በመድረክ ዝግጅት በድርሰት የመጣበት ወቅት ነበር። እኛም በሬድዮ ድራማዎቹ በዝና እናውቀው ስለነበር መምህራችን መሆኑን ስናውቅ ደስታ ተሰማን›› ሲል አለማየሁ ነግሮናል፡፡
አለማየሁ የትወና ችሎታዬን ያረጋገጥኩት የጌታቸው ስራዎችን በመስራቴ ነው ብሎ ያምናል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደኮርስ የሰጣቸው ‹‹የመድረኩ ራእይ›› የተሰኘውን የአብዬ መንግስቱ ግጥም ነበር፡፡ ይህን ግጥም ወደ ተውኔት ቀይሮ ሰጥቷቸው ነበር። ከዛም ደራሲው በሰማይ ቤት ፣ ቤጊዮሎጂ፣ እስረኛው ንጉስ ፣ ካሊጉላ እና ሌሎችም ነበሩበት፡፡
ጌታቸው ታረቀኝ በጨዋታ ጊዜ የሚያወራቸው ነገሮች አብረውት ለነበሩት ሰዎች ምቾት የሚሰጡ ነበሩ፡፡ አለማየሁ ትዝ እንደሚለው ጌታቸው ተማሪዎቹ ፊት ብዙም ማካበድ የማይወድ እና ተማሪዎች ነገሮች ቀለል ብሏቸው እንዲሰሩ መንገድ የሚያመላክት መምህር ነበር፡፡
ደራሲው በሰማይ ቤት ትያትር በድርሰት ወጣ ያለ የሞቱ ገፀ-ባህሪያት ሰማይ ቤት ሲገናኙ አይነት ይዘት ያለው ነው፡፡
አለማየሁ እንደሚናገረው የትርጉም ስራው ካሊጉላም ለየት ባለ አቀራረብ የተመደረከ ነበር፡፡
ደራሲው በሰማይ ቤት ብዙ ሀሳቦች አሉት፡፡ አለማየሁ እንዲህ ይላል‹‹…. አብዛኛው አሁን ላይ ያለው ቲያትር ከማስለቀስ እና ከማሳቅ ወጣ ያለ ጭብጥ ሊኖረው ይገባል ሲል ጌታቸው ይነግረን ነበር፡፡በሚያስተምር ጊዜ እንዲያው በምናብ ሳይሆን በተግባር የሚያሳይ ሲሆን ሲያስተምርም ለየት ባለ እና ለሌሎች እድል በመስጠት የሚታወቅ ነበር፡፡ ከሌሎች መምህራን የተለየም ነበር። ›› ሲል አለማየሁ ታደሰ ለጌታቸው ታረቀኝ ያለውን ጥልቅ አክብሮት ነግሮናል፡፡
ጌታቸው ታረቀኝ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እያስተማረ የአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ ስራ አስኪያጅ ሆኖ ሄደ፡፡ አለማየሁም ትምህርቱን አጠናቅቆ ማዘጋጃ ቤት ገባ፡፡ ያኔ ተማሪና አስተማሪ የመገናኘት እድል ገጠማቸው፡፡ አለማየው ሲናገር አሁን ካለሁበት ደረጃ የደረስኩት ከጌታቸው ጋር አብሬ በማሳለፌ ነው ይላል፡፡ ያኔ የቀሰመው እውቀት ለአለማየሁ ዛሬ ድረስ ስንቅ ሆኖታል፡፡ ለዚህም ውለታውም ጌታቸው ታረቀኝን ማመስገን ይፈልጋል፡፡
ጌታቸው ማንጉዳይ ስለ ጌታቸው ታረቀኝ
ጌታቸው ታረቀኝ በፀባዩ ትጉህ ፣ ጨዋ ፣ታታሪ እንዲሁም በትምህርቱ ጎበዝ ነበር። በድራማዎቹ የተለያዮ የሬዲዮ ድራማ ህግጋቶችን እየተማረ ራሱንም ድራማዎቹንም እያሳደገ ቴክኒኮቹን እያወቀ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ በማድረግ የተሣካለት ሰው ነበር። ድራማ ይጽፍ የነበረው ገና የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለ ነበር፡፡ ብዙዎቹ ድራማዎች በቅዳሜ መዝናኛ ፕሮግራሞች ላይ የቀረቡ ናቸው። ገና በጀማሪነቱ ራሱን ከትላልቅ ደራሲያን ተርታ ማሰለፍ የቻለ ሲሆን በስራው እጅጉን ታታሪ ሰውም ነበር። ወደ ሬድዮ ሲመጣም ድራማ በመጻፍ አቅሙን እንዲያጎለብት ብርታት ሰጥቻለሁ፡፡ ከሃምሳ በላይ የሚሆኑ ወጣቶች በዚህ ፕሮግራም የወጡ ሲሆን ጌታቸው ግን በሬዲዮ ድራማ ፀሀፊነቱ በወጣትነቱ እጅግ የተከበረ ትልቅ ሰው ነበር።ከዚህ ባሻገር አስተማሪ ቲያትር አዘጋጅም ነበር። በወቅቱ ከነበሩት ሬዲዮ ድራማ አዘጋጆች ግን ቦታውን ጠብቆ ህዝቡንም አስደስቶ ያገለገለ ወጣት ድራማ ፀሀፊ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በድራማዎቹ ያልተዳሰሰ ሃሳብ አልነበረም። ጌታቸው የራሱን የአፃፃፍ ዘዴ እና መንገድ ይዞ ከመምጣቱም ባሻገር በትያትሩ አለም በነበረበት ወቅት ሽልማት ቢኖር ቀደምትነትን ይዞ ይሸለም ነበር።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር
“ካሊጉላ”
ድርሰት :- አልበርት ካሙ
ተርጏሚ:- ጌታቸው ታረቀኝ
ዝግጅት :- ተዋንያን በህብረት
ተዋንያን :- ተስፋዬ ገ/ሃና(ስለ ካሊጉላ):መዓዛ ብሩ(ስለ ካሶንያ)ጫንያለው ወ/ጊዮርጊስ(ስለ ሲሲፒዩ):እንድሪስ አህመድ(ስለ ኦክታቫስ):ቴዎድሮስ ተስፋዬ(ስለ ሉሲየስ):ፍቃዱ ፈዬ(ስለ ኦክፒቨስ):ተስፋዬ ገ/ማርያም(ስለ ሄሊከን):ጌትነት እንየው(ስለ ሊፒደስ):ኃይሉ ከበደ(ስለ ፓትሪከስ):ተክሌ ደስታ(ስለ ቼርያ):ሰለሞን ሙላት:እስቲፋኖስ አድማሱ:ሉሌ አሻጋሪ(ስለ አጃቢ ሴት)አስቴር ጣሰው(ስለ አጃቢ ሴት):ትዕግስት ባዩ(ስለ አጃቢ ሴት):ሰለሞን ተካ(ስለ ባለ ቅኔ):ጌታሁን ኃይሌ(ስለ ባለ ቅኔ):መሰለ አደቆ(ስለ ባለ ቅኔ):ገበያው ገሠሠ(ስለ ጠበቂ/ዘበኛ):መስፍን እንግዳሸት:ሰለሞን ጋሻው:ነጋሲ አምባዬ:ቅድስት ገ/ማርያም:አዲሱ ፈለቀ:ሙሉጌታ ገ/መድህን እና መላኩ አለማየሁ::
የድምፅ ግብዓት:- ኃይለመስቀል ዲሳሳ እና መስፍን አርጋው::
የብርሃን ግብዓት:- ተክለማርያም አወቀ:ቅጣው ክፍሌ እና ተሾመ አዳነ::
የመድረክ ፖስተር ዲዛይን:- ደምሴ ሽፈራሁ(ነፍስ ይማር!)::
የመድረክ ግንባታ:- መላኩ ካሣ:ግርማ ወርቄ እና አጥናፋ ልሳነወርቅ::
ቁሳቁስ:- ውብዓለም መንግስቱ::
ገፅ-ቅብ:- አልማዝ ኃይሌ::
የተመደረከበት ዓ.ም :- 1984
ማስታወሻ(Notes)
በቴአትሩ ውስጥ የተሳተፉ ተዋንያን ስም ዝርዝር ከነ ገፀ-ባህርያቸው የተዘረዘሩት የሁሉም ፎቶ(ምስል) ተካቶ ቀርቧል::
ፋሲካ ለገሠ እባላለሁ
ጌታቸው ታረቀኝ (ዶክተር) የማውቀው በቅርብ ጊዜ ነው። የሱ ድርሰት የሆነውን እስረኛው ንጉስ የተሰኘውን ተውኔት ላይ በትወና እንድሳተፍ እድሉን አገኘሁና በዝና እና የተወሰኑ የቴአትር ስራዎቹን የማውቀው የነበረውን በዚሁ ቴአትር አዘጋጅ ሆኖ ስለነበር ተዋወኩት።
መጀመሪያ ቀን ልምዳችን ላይ እንዳገኘኝ ስለምጫወተው ገፀ – ባህርይ ጠይቆኝ እያስረዳኝ እኔም ቃለ – ተውኔቱን እያልኩ አባባሉን እያረመኝ ከሰራን በኋላ ያስረዳኝን ነገሮች እንዳልረሳ አሳቦኝ በተረፈ አጀማመሬ ጥሩ እንደሆነ ነገረኝ። በቀጣይ የልምምድ ቀኖች ቀድሞ እየደወለልኝ የጨመራቸውን ነገሮች እየነገረኝና እያሳየኝ ስለ – ገፀባህሪውም ተጨማሪ ገለፃዎችን እየሰጠኝ እንሰራ ነበር በዚህ ውስጥ ታዲያ በዝግጅት ወቅትም ሆነ ስለባህሪው ያስተዋልኳቸውን ነገሮች እንደሚከተለው አቀርባለሁ።
ልምምድ ከመጀመራችን በፊት ብዙ ግዜ የአካል እንቅስቃሴ እና የቴአትር ቮካል ያሰራናል ።አንዳድ ጊዜ ሞቅ ባለ የባህር ማዶ ኦልዲስ ሙዚቃ ተዝናኖት እንዲሰማን የቴአትር አባላቱ ሁሉ ዳንስ በሚመስል እንቅስቃሴ የተወዛወዝንበትም ጊዜ አለ። ሌላው ደሞ ቮካል ሲያሰራን የተለያዩ ድምፆችን ዘለግ ባለ ድምፅ እንድናወጣ በተለይ ” መሀበሉሉ መሾንጌ ” የሚለውን ቃል እሱ ስሜቱን እየነገረን በደስታ ፣ በሀዘን ፣ በፍቅር ፣ በንዴት . . . ስሜቶች እንድንገልፅ የሚያደርግበት ሁኔታ አይረሳኝም። በልምምድ ወቅት የተዋናዩን ንቃትና ትኩረት ይፈልጋል ።በደንብ ተዋናዩ ሲቀበለው ለእሱም ተነሳሽነቱን ይጨምርለታል። በቀጣይ ልምምድ አስቦ የሚጨመሩ ነገሮችን ይዞ ይመጣል። ተነሳሽነት ከሌለ ግን ስሜቱ ይቀየራል (ይደብረዋል) ።
ጌታቸው (ጌች) ብዬ ነው እኔ የምጠራው እሱን ከማወቄ በፊት የሳልኩት ሰውና ካወኩት በኋላ ያገኘሁት የተራራቁ ነበሩ። ምክንያቱም ኮስታራ ለማናገር የሚያስፈራ ሰው አድርጌ ነበር የሳልኩት። ግን ሳውቀው ቀለል ብሎ እንደጓደኛ የሚቀርብ ተጫዋች አይነት ሰው ነው። ግን ይሄ ሲባል በልምምድ ሰአት የሚያረፍድና የሚጠበቅበትን ሚና የማይወጣ ሰውን አይታገስም። ቆራጥ ነው ለተዋንያን ደግሞ ተቆርቋሪ ነው። ተዋናዩ መብቱ ተጠብቆለት እንዲሰራ ይፈልጋል ይሄንንም በተግባር ያደርገዋል። አንዳዴ ከራሱም ኪስ ሊያወጣ ይችላል። በአጠቃላይ አርቲስቱ ከሙያው የሚጠቀምበትን መስመር እንዲዘረጋ ማህበር ተቋቁሞ መብቱ የሚከበርለት እንዲሆን ሲታመም ለመታከም የሰው እጅ የሚያይበት ሁኔታ እንዲቀር በተቋርቋሪነት ስሜት ይነግረናል።
በባህሪው ታይታ አይወድም ኢሄን ሰራው ኢሄን አደረኩ ብሎ ሚዲያ ላይ መቅረብም አይፈልግም። ለዚህም ይመስለኛል ብዙ ሰዎች በሰራቸው ስራዎቹ እንጂ በአካል አያቁትም። ሌላው ጥረትህን የሚያበረታታው ነገር ነው የሚገርመኝ እኔ የሞከርኳቸውን የተለያዩ ስራዎቼን እልክለትና ካየው በኋላ ደውሎ አስተያየቱን ሳይደብቅ በአውንታ ይነግረኛል። በቴአትር ዘርፍ አ.አ. ዩንቨርሲቲ እንደተማረና ከዛ በመምህርነት ተቀጥሮ እንደሰራ በወቅቱም የቴአትር እንቅስቃሴ ከፍ ያለ ስለነበር የተለያዩ ፔሌዩችን በዩንቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ያሳዩና አስተያየትም በቀረበው ፕሌይ ላይ ይሰጥባቸው እንደነበርና በዛ ውስጥ እሱም ይሳተፍ እንደነበር አጫውቶናል። አዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ (ማዘጋጃ ቴአትር) በስራ አስኪያጅ ሀላፊየት እንዳገለገለና በተጨማሪም ብዙ ዘርፎች ላይ እውቀት እንዳለውና እንደሰራ ከንግግሩ ማወቅ ችያለው የአለምን ታሪክ በተለይ የኢትዮጵያን ታሪክ ፤ ስለ ህክምና ባህላዊ የሆነውንም ፤ አሁን ያለውን (ዘመነኛ) ህክምና ፤ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (IT) ላይ ደግሞ በስፈት እንደሰራ ተረድቻለሁ።
መጀመሪያ ከምንም በላይ ሰው ሁን። የፈለገ በቃላት ብትራቀቅ ሰው ካሎንክ ዋጋ የለውም ያለኝ ነገር ትዝ ይለኛል። በአጠቃላይ እኔ ባየሁት መጠን ጌች ታዋቂ ሰውም ሁን አትሁን ሁሉንም በተግባሩ ( በስራው) እኩል የሚዳኝና ለሚያዳምጥ ፤ጥረት ለሚደርግ ፤የተሰጠውን በአግባቡ ለሚወጣ ሰው ልዩ ክብር የሚሰጥ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
ነሃሴ 2015 ዓ.ም.
መዝጊያ
ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የመዝገበ-አእምሮ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው ፡፡ የሰው ልጅ ህይወቱን በብዙ መልክ ይገልጻታል፡፡ ወይ ነጭ አሊያ ጥቁር፡፡ ካልሆነ ደግሞ ቀለም አልባ፡፡ ሰዎች የኖሩበትን መንገድ ካላቸው ወቅታዊ እሳቤ ጋር አሰናስለው መግለጽ ይችላሉ፡፡ ታሪኩን የሰነድንለት ዶክተር ጌታቸው ብዙም ስለራሱ መናገር የማይመርጥ ይልቁንም በስራ ኑሮን ለማሸነፍ የሚተጋ ታጋይ ነው፡፡ ሲናገር ያምርበታል-ያውቅበታል-ብዙ ሀሳቦቹ ሚዛን ይደፋሉ፡፡ በሀገራችን የቴአትር ታሪክ ውስጥ በተለይ 1980ዎቹ ካነሳን በጉልህ ከሚጠቀሱት ውስጥ አንዱ ነበር፡፡ በአጭር አመታት መልካም እና በጎ ነገር ከሰሩት መሀል አንዱ ነው፡፡ የእኛ የሰናጆች የህዝብን ታሪክ አጣርቶ መሰነድ ስለሆነ ይህንኑ ሚናችንን እየተወጣን ነው፡፡ በእኛ እምነት የዶክተር ጌታቸው ታሪክ ብዙ ያስተምራል- ችግሩ ግን እንዴት የበለጠ መማር ይቻላል? የሚለው ይሆናል፡፡ ህይወት ታሪክ በጨረፍታ ማስቀመጥ አንዱ ማስተማሪያ መንገድ ሲሆን ሌሎች መንገዶችም ይኖራሉ፡፡
በእኛ እምነት ባለሙያ ከስሙ በዘለለ መታወቅ መከበር መወደስ መመስገን አለበት፡፡ ከዚህ ቀደም ድርጅታችን ተፈሪ አለሙን እናክብር ብሎ ትልቅ የምስጋና መሰናዶ እውን ሲያደርግ መልእክቱ አንድ ነበር፡፡ በቁም ሳለን አንዳችን ስለ አንዳችን የምስጋና ቃል እንወርውር ለማለት ነው፡፡ በመሆኑም በየቤቱ የጠፉብን የትናንት ባለውለታዎችን ለምን ወደ እኛ የስነዳ መድረክ አናመጣቸውም? ሰው በህይወት ሳለ ህይወት ታሪኩን ሲያነብ ፈጣሪውን ማመስገኛ መንገድ አይሆነውምን? ለዚህ ስላደረስከኝ ተመስገን አያስብልምን? የእኛ አላማ ይህ ብቻ ነው፡፡ ደርሻለሁ ማለት አንድ ነገር ሆኖ ታሪክን ወይም በጎነትን ለትውልዱ ማስተላለፍ ደግሞ ሌላው ነገር ነው፡፡
ሰዎች በህይወት ሳሉ የሰሩትን ጽፈው ማስቀመጥ ግዴታቸው ነው፡፡ የመኖር አንዱ ግብ ምን ትቼ አለፍኩ ነውና፡፡ እኛ ባደረግነው ጥናት ጌታቸው በተዋናዩም በአዘጋጁም ፤ በቴአትር መምህራንምይወደዳል-ይመሰገናል፡፡ ስሙም በመልካም ይነሳል፡፡ ታዲያ ስለ ጌታቸው ካልተሰነደ ስለማን ይሰነዳል? ስነዳው እና ታሪክ ማጠናከሩ ግን ይቀጥላል፡፡ ሌሎች ጌታቸውን የሚያውቁ ደግሞ ሌላውን መልክ ቢነግሩን ስራችንን ቀላል ያደርገዋል፡፡ ወንድማችን ጌታቸው …… እናመሰግናለን፡፡ ታሪክህ በመዝገባችን ላይ እንዲሰነድ በመፍቅድ ከትህትና ጋር እናመሰግናለን፡፡ ይህ ጽሁፍ በተወዳጅ ሚድያ ዲጂታል ሚድያዎች ላይ ቆየት ብሎም በመዝገበ-አእምሮ ቅጽ 2 ላይ ታትሞ ይወጣል፡፡ የዚህ ጽሁፍ የስነዳ ስራ ዛሬ ነሀሴ 2 2015 በእዝራ እጅጉ ተከናወነ፡፡