የጥቅምት ማስታወሻ
አቢይ ኤፍሬም ሁሉንም ያስማማ በጎ ሰው
ከእዝራ እጅጉ እንደወትሮዬ ከምሽቱ 7 ሰአት ግድም እየሰራሁ ሳለ አንድ ሰው በሜሴንጀር ደወለልኝ፡፡ ጊዜው ማክሰኞ ጥቅምት 13 2014 ነበር፡፡ ታብሌቱን ሳየሁ አብይ ኤፍሬም ይላል፡፡ መዝገበ-አእምሮን ለማዘጋጀት ሰዎች ጋር ማታ እየደወሉ ማግባባት ልማዴ ነበር፡፡ አቢይ ግን ሊያበረታታኝና እርሱም ታሪክ እንዳለሁ ሊነግረኝ ሲደውልልኝ ውስጤ በደስታ ተሞላ፡፡ ታሪኩን በገዛ ፈቃዱ የሚያካፍል በጠፋበት ሀገር አቢይ ኤፍሬም በደስታ ፈቃደኛ መሆኑን ሲነግረኝ ትህትናው ገዛኝ፡፡ በስም ከመተዋወቅ በዘለለ የተለየ ቀረቤታ የለንም፡፡ በአካልም አልተያየንም፡፡ ከዚያች ሌሊት አንስቶ ግን አቢይ ኤፍሬም በጎ ነገር ያለው ትሁት ሰው መሆኑን አወቅኩ፡፡
ሀዘኔን ልወጣ ሞከርኩ፡
ከዚያም ታሪኩ ተሰርቶ አይቶት ተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ሲወጣ ብዙ ሰዎች ሀሳባቸውን ሰጡ፡፡አቢይም አመስግኖኝ አንድ ቀን ልንገኝ ቀጠሮ ይዘን ነበር፡፡መዝገበ አእምሮ መጽሀፍ ሲመረቅ ሳይመቸው ቀረ፡፡ ብቻ በአንዱም መንገድ አቢይን ሳላውቀው ወደ ዘላላማዊ ቤቱ ሄደ፡፡ እናም አራት ኪሎ በሚገኘው መኖርያ ቤቱ ሄጄ ሀዘኔን ልወጣ ሞከርኩ፡፡ ፈጽሞ አልወጣ አለኝ፡፡ የህይወት ታሪኩን እንደሰነደ ሰው ከዚህ በኋላ አቢይን በምን ልናስበው እንችላለን? ስል አሰብኩ፡፡
አንድ የሚቀሰቅስ ግን ያስፈልጋል፡
የብዙ ታላላቆች የማስታወሻ ዝግጅት እንዳዘጋጀ ሰው አቢይን መዘከር የግድ ነው ስል አሰብኩ፡፡ ይህ ሀሳብ ብዙዎች ጋር ነበር፡፡ አንድ የሚቀሰቅስ ግን ያስፈልጋል፡፡ እናም ለመጀመርያ ጊዜ ጳግሜ 5 2014 በዚህ ጉዳይ ላይ የማገዝ አቅም ያላቸው እና ልባቸው ቀና የሆኑ ሁለቱ ወዳጆቼ ይነገር ጌታቸው እና ሀይለሚካኤል ዴቢሳ ጋር ደወልኩ፡፡ ፈጣሪ ይስጣቸው ነገሩን ቶሎ ተረዱ፡፡ እና አንድ ማስታወሻ ማድረግ አለብን ወደሚለው መንገድ ተጓዙ፡፡ ከዚያም ነገሩን ከፍ ለማድግ አቶ አይሸሹም ተካ የተባሉ ዲፕሎማትና ባለሀብት ይህን ሀሳብ እንዲረዱት አደረግን፡፡ ከዚህ በኋላ ነገሩ በእግዚአብሄር እጅ ገባ፡፡ ለ40 ቀናት ሁሉም በየአቅሙ ደከመ፡፡ከ45 በላይ ሰዎችን ያሳተፈው የአቢይ ኤፍሬም የ40 ቀን ማስታወሻ በጥሩ መልኩ ተከወነ፡፡ ይህም በእግዚአብሄር አይን ቀላል ነበር፡፡
ጥቅምት 8 2015
ሁሉም እኔ ሰራሁ ሳይል በተለይ መድረኩን እውን ለማድረግ፤ መጽሀፉ እንዲታተም መንገዱን ለማመቻቸት አንዳንድ ብርቱ ሰዎች ቀዳሚ ሆነው ተነሱ፡፡ እኔ ባለኝ እውቀት ማን ምን እንደከወነ ስለምረዳ በተለይ ከሁነቱ፤ ከዘጋቢ ፊልሙ፤ ከመጽሀፍ ህትመቱ፤ ከገቢ ማሰባሰቢያ ቡድኑ ጀርባ ማን ምን አይነት ሚና እንደነበረው በዝርዝር መናገር ይቻላል፡፡ ለነገሩ ታሪክ ሰናጅ በመሆኔ ዝርዝር ማወቄ ብዙም አይደንቅም፡፡
አቶ አይሸሹም ተካ
እኒህ ሰው የአቢይን ቤተሰብ በወጉ ያጽናኑ ለቀናት በሁሉም ነገር ያልተለዩ ናቸው፡፡ በዚህም ብቻ ሳይወሰኑ የአቢይም የማስታወሻ መሰናዶ እውን ለማድረግ ስናስብ ለእኛ ከበድ የሚሉ የአዳራሽ ፤ የገቢ ማሰባሰቡን እና ኮሚቴውን በቶሎ ማደራጀቱ ላይ የቀደመ ሚና ያላቸው ሰው ናቸው፡፡ አቶ አይሸሹም ሞራል በመስጠት አብረው ስለነበሩ እና ስራው እንዲሰራ ነገሮች ቀለል ስላደረጉ መመስገን አለባቸው፡፡በእለቱም ታድመው ነገሮችን በወጉ እንድናስኬድ የጀርባ ሰው በመሆን የተጉ ናቸው፡፡ ብዙ እንዲነገር ባይፈልጉም ታሪክ ላይ መስፋራቸው አይቀርም፡፡
ይነገር ጌታቸው
ይነገር ጌታቸው በእኔ እይታ ጥሩ ልብ እና ጥሩ የጽሁፍ ችሎታ ያለው ሰው ነው፡፡ለዚህ ስራ ‹‹ከነገ ልበደር ›› የሚለው መጽሀፍ ሲታተም ቀዳሚ የማሰባሰቡን ስራ ከጓደኛው ከብርሀን እያየሁ ጋር የተወጣ ነው፡፡ ይነገር የመጽሀፉ ሙሉ አርታኢ ነው፡፡ አርትኦት ምን ያህል አድካሚ እንደሆነ የነበርንበት የምናውቀው ነው፡፡ በዚህ ብቻ ሳይወሰን ዶክመንተሪው ላይ 3 ሰዎች በወጉ ቃለ-ምልልስ ያደረገ ነው፡፡ ይነገር በየጊዜው በምናደርጋቸው ስብሰባዎች በመገኘት ጠቃሚ ሀሳብ የሰጠ ብርቱ ባለሙያ ነው፡፡ ሁነቱ እንዲያምር፤ ስራዎች በመልክና በወጉ እንዲሄዱ ታላቅ ተጋድሎ አድርጓል፡፡ ይኔ ታላቅ ሰው መዝገበ-አእምሮ ላይ ጠብቁት፡፡
ብርሀን እያየሁ
ብሬ የተረጋጋች ብሩህ አእምሮ ያላት የኢቲቪ ጋዜጠኛ ነች፡፡ ብሬ ታላቅ ሰው ደስ ሲል እርጋታው፡፡ አንቺ የምለው ቅርበቴ ነው፡፡ የአቢይ ኤፍሬም የ12 አመት ወዳጁ ስለሆነ ብዙ የፎቶ እና የሰነድ መረጃዎችን እንካችሁ ያለን ብሬ ነው፡፡ ብርሀን እያየሁ ከዶክመንተሪው ጀምሮ በሁሉም ስራ ውስጥ እየገባ በሚያደርገው ክትትል የተደነቀ ነው፡፡ በተለይ ዛሬ በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል በተደረው የማስታወሻ መሰናዶ ላይ ተፍ ተፍ ሲል አቦ ሲያምርበት ፡፡ ትጉህ ልጅ … የኢቲቪ ብርቱ የቢዝነስ ዘጋቢ ……መዝገበ አእምሮ ላይ መርጠነዋል፡፡ አብሮ እና ተባብሮ መስራት ይችላል፡፡ ሀሳብ ይሰጣል፤ ይቀበላል…. ነገሮች እንዲያምሩ በመመኘት ብዙ አስቦ ደግ ሀሳቦችን ያክላል፡፡ ብሬ ባለህበት ተመስገን፡፡
ሀይለሚካኤል ዴቢሳ
ሀይልሽ የፋና ወዳጄ … አሁን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሙያ ነው፡፡ ሀይሌ ዘጋቢ ፊልሙን ተቀብሎ አስተካክሎ ፤ ማየት ለሚገባቸው ሰዎች አሳይቶ የፍጻሜ አስተያየቱን ይዞ ዶክመንተሪው ላይ ነፍስ የዘራ ፕሮዲዩሰር ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ሀይሌ ክቡር አቶ ደመቀን መኮንንን ቃለ-ምልልስ በማድረግ ሚናውን የተወጣ ነው፡፡ ዋፋዎች የኤዲቲንጉን ስራ ቢሰሩ ይሻላል የሚለውንም ሀሳብ ያመነጨ ሀይሌ ነው፡፡ ሀይሌ ትጉህ ነው፡፡ በውጭ ጉዳይ በኩል የሚጠሩ ሰዎችን በመለየት ሳይደክመው የሰራ ነው፡፡ በሁነቱ ዕለት ጥቅምት 8 2015አ.ም ላይም ሁለገብ ሆኖ የሰራ በጎ ሰው ነው፡፡ ሀይልሽ ተመሰገኚ……….. ቅልጥፍናሽ ሲመች ተባረኪ ……
ናትናኤል ግርማ እና ማርታ በላይ
ናቲ ደግሞ ገና ከመጀመርያው ቀን አንስቶ ይህ ሀሳብ በጥሩ መልኩ እንዲከናወን የአቅሙን የጣረ ነው፡፡ የራሱን ካሜራ በመመደብ በምርጥ ካሜራ ጥሩ ምስል እንድናይ የጣረ በጎ ሰው ነው፡፡ ናቲ በዚህ ብቻ አይወሰንም፡፡ ስራው ከተባለው ጊዜ ቀደም ብሎ እንዲፋጠን የጣረ ነው፡፡የሜልባ ፕሪንቲንግ ፐብሊሺንግ ኤንድ ፓኬጂንግ ዋና የስራ መሪ ማርታ በላይም የአቢይ መጽሀፍ በቶሎ ታትሞ ለህትመት እንዲበቃ ጥራለች፡፡ ብዙ ፍጥነት ከማተሚያ ቤቶች ተጠባቂ ነው፡፡ማርታ እና ናትናኤል የትዳር አጋሮች ሲሆኑ የአቢይ የማስታወሻ መሰናዶ መልከኛ እንዲሆን የደከሙ፤ ከአንድ ቤት ወጥተው ድንቅ በጎነታቸውን የቸሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ናቲ ባለህበት ምስጋናው ይድረስህ ተባረክ ልበልህ ………..ደረጀ ሀይሌ ጋር ግን ደውለህ አገናኘኝ ባክህ?
አብርህም በላይነህ
አብርሀም በላይነህ አቢይ የደረሰውን ግጥም ዜማ አቀናብሮ ለማስታወሻ መሰናዶው አፍጥኖ ያደረሰ ጀግና ባለሙያ ነው፡፡ ይመስገን
አቶ ሞላልኝ አስፋው
አቶ ሞላልኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጽ/ቤት ሃላፊ ሲሆኑ በየጊዜው እያገኙን የሚያበረቱን …. በየጉዳዩ ጣልቃ ሳይገቡ ፕሮፌሽናል ስራ እንድንሰራ የረዱን ባለውለታ ናቸው፡፡ በተለይ በአቶ ደመቀ መኮንን ቢሮ በኩል ያሉ ሰዎችን በማስተባበር ፤ የክልል የስራ አመራሮችን በማሰባሰብ የአቶ ሞላልኝ ሚና በቀላሉ የሚነገር አልነበረም፡፡ በተጨማሪም ሁነቱ ፕሮቶኮሉን የጠበቀ እንዲሁም ወግና ስርአት ያለው እንዲሆን ሙሉ ሀይላቸውን ተጠቅመዋል፡፡ በዚህም ጥረታቸው መመስገን አለባቸው፡፡
በተጨማሪም ለዚህ ስራ ሙያዊ እገዛ ስጡ ሲባሉ ያለ ምንም ክፍያ የሰሩ ተቋማትና ግለሰቦች የሚከተሉት ናቸው፡፡
- ዋፋ ማርኬቲንግ እና ፕሮሞሽን ወይዘሮ ፋንታዬ ጌታነህ
- ከዚራ አድቨርታይዚንግ
- ኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል
- የካቢኔ ሚኒስትሮች
- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰራተኞች
- የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ.ቤት ሰራተኞች
- የጥበብ ሰው ተፈሪ አለሙ
- ገጣሚ ምስራቅ ተረፈ
- ደራሲ ህይወት እምሻው
- ረዳት ፕሮፌሰር መኩርያ መካሻ
- ረዳት ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬ
- አቶ ሰለሞን ሙሉጌታ
- ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን