ዘላለም ጌታቸው (ዶ/ር)

ዘላለም ጌታቸው (ዶ/ር)

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ሥራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡

ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ? የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡

ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 185 የሚድያ ፤ የስነ-ጽሁፍ የቴአትር የፊልም ሰዎች ታሪክን አሰባስበናል። በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከሚሰነድላቸው መካከል የሥነ-ጽሁፍ ባለሙያ እና ደራሲ ዶክተር ዘላለም ጌታቸው ይጠቀሳል፡፡ ዶክተር ዘላለም የተለያዩ የልቦለድ ስራዎችን ከመስራቱ ባሻገር በተለይ የልጆች ስነጽሁፍ ላይ ባበረከተው ልዩ አስተዋጽኦ ይታወቃል፡፡ የዶክተር ዘላለም ጌታቸው የሕይወት ታሪክ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

ዘላለም ጌታቸው (ዶ/ር) ህዳር 23 ቀን 1968ዓ.ም. ከእናቱ ወ/ሮ ውልታ ሰይፉ እና ከአባቱ ከአቶ ጌታቸው አትከልከል በአዲስ አበባ ከተማ ተወለደ፡፡ ለቤተሰቦቹ የመጨረሻ ልጅ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለውም ተወልዶ ባደገባት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ዘላለም፣ በአማርኛ ቋንቋ እና ሥነጽሑፍ የመምህርነት ዘርፍ ዲፕሎማ እና የመጀመሪያ ዲግሪውን ከኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ካገኘ በኋላ በግል ኮሌጆች ውስጥ በአማርኛ ቋንቋ እና ሥነጽሑፍ መምህርነት እና በተለያዩ የስራ ኃላፊነቶች አገልግሏል፡፡ ከ2000ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ በዲላ ዩኒቨርሲቲ በአማርኛ ቋንቋ እና ሥነጽሑፍ መምህርነት እያገለገለ ሲሆን፣ በትምህርት ዘርፍም በአማካሪነት ይሰራል፡፡ ትምህርት እና ሥነጽሑፍ፣ በተለይ የልጆች ትምህርት ይበልጥ የሚሳብበት መስክ ነው፡፡

ዘላለም፣ የሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአማርኛ ቋንቋ ማስተማር ዘርፍ ያገኘ ሲሆን፣ የሶስተኛ ዲግሪ ጥናቱን ያከናወነው በሥነጽሑፍ ተጠቅሞ ማስተማር ለልጆች የቋንቋ ክህሎት መዳበር ባለው ጠቀሜታ ላይ ነው፡፡ በእዚህም ይበልጥ የሚሳብባቸውን የትምህርት እና የሥነጽሑፍ መስኮችን አስተሳስሮ ለማጥናት በር ከፍቶለታል፡፡ በጥናቱ መነሻነትም የሥነምግባር ትምህርትን በሥነጽሑፍ ተጠቅሞ ለማስተማር የሚረዱ እና ከ1-4ኛ ክፍል ለሚማሩ ተማሪዎች የሚያገለግሉ አራት የሥነምግባር የመማሪያ መጻሐፍትን አዘጋጅቷል፡፡

ዘላለም ተወልዶ ባደገበት ሰፈር የነበረ ቤተመጽሐፍ የማንበብ ፍቅርን እንዲያዳብር እንደረዳው ይናገራል፡፡ በህጻንነቱ የቤተመጽሐፍ ሰራተኞቹ የሚሰጡትን መጻሐፍት በቤተመጽሀፉ ውስጥም ሆነ ቤት ወስዶ ዘወትር ማንበቡ የማንበብ ክህሎቱን ጭምር እንዳዳበረለት ይናገራል፡፡ የማንበብ ልምዱና ክህሎቱ በልጅነቱ የድርሰት ሙከራዎችን እንዲያደርግ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለ ለመጽሔቶች የፈጠራ ስራዎችን እንዲያቀርብ እንደረዳው ያስታውሳል፡፡ የ11ኛ ክፍል ተማሪ እያለ ከእዚሁ ከሚጽፋቸው የፈጠራ ስራዎች በሚያገኘው ገንዘብ መጽሐፍ የመግዛት ልምዱን እንደጀመረ፣ ይህ ልምዱ አሁንም እንደቀጠለ እና አንድ የግል ቤተመጽሐፍ ቤቱ ውስጥ እስከማደራጀት እንደረዳው ይገልጻል፡፡ ማንበብ በጣም ከሚያስደስቱት ጉዳዮች አንዱ እንደሆነም ይናገራል፡፡

የዘላለም ጌታቸው የመጀመሪያው የህትመት ውጤት “ሽርፍራፊ ሰከንዶች” በሚል ርእስ በ1997ዓ.ም. የታተመ የአጭር አጭር ልቦለድና የግጥም መድብል ሲሆን፣ ከእዚያ በኋላ የጻፋቸው የልጆች መጻሐፍትን ነው፡፡ በስፖትላይት አሳታሚዎች የታተሙ እና በግሉና እና በቡድን የተጻፉ ከ68 በላይ የልጆች መጻሐፍትን የጻፈ ሲሆን፣ መጻሐፍቱ በሥነምግባር እና በጠቅላላ እውቀት ላይ መሰረት ያደረጉ ናቸው፡፡ እንደዘላለም አባባል፣ የልጆች ሥነጽፍ ከመዝናኛነቱ ባሻገር ሌሎች ፋይዳዎችም እንዳሉት ታሳቢ ተደርጎ መጻፍ አለበት፡፡ ልጆች በሥነጽሑፍ አማካይነት ዘላቂ በሆነ መልኩ ዕውቀትና ባህሪያቸውን ሊያዳብሩ እንደሚችሉ ይገልጻል፡፡ በእዚህም እምነቱ ምክንያት የሚጽፋቸው የልጆች መጻሐፍት ከማዝናናት ተግባራቸው ባሻገር የማስተማር ሚናም እንዲኖራቸው ይዘቶችን ከሚማሩት ትምህርት እና ካላቸው የልጅነት የእድሜ ደረጃ አኳያ በጥንቃቄ እንደሚመርጥ ይናገራል፡፡ በእስካሁኑ ጥረቱም ሥነምግባርን፣ ሒሳብን እና ሳይንስን በልጆች መጽሐፍ ዝግጅቱ አዝናኝ በሆነ መልኩ ለልጆች ለማቅረብ ሞክሯል፡፡

ዘላለም ከድርሰት መስክ ባሻገር በመጽሐፍ ህትመት ዝግጅት በሰፊው ተሳትፏል፡፡ በአሳታሚ ድርጅት ውስጥ በአርታኢነት እና በቴክኒካል አድቫይዘርነት ለአምስት ዓመታት ሰርቷል፡፡ በመጽሐፍ ህትመት በአማካሪነትም አገልግሏል፡፡ በእዚህ ልምዱ በተለይ በህጻናት መጽሐፍ ዝግጅት፣ የትርጉም እና የአርትኦት ስራ በቂ ተግባራዊ እውቀት አግኝቷል፡፡

ከሥነጽሑፍ አበርክቶ ባሻገር፣ ዘላለም የማንበብ ልማድ እንዲዳብር በሚሰራበት ተቋም እና በሚኖርበት ከተማ የተለያዩ እንቀስቃሴዎችን ያደርጋል፡፡ “አንዱ ጥሪዬ መምህርነት ስለሆነ፣ ይህ ተግባር የመምህርነት አንዱ መንገድ ነው” ብሎ ያስባል፡፡ በእዚህ ረገድም፣ የተለያዩ የሥነጽሑፍ ባለሙያዎችን በዲላ ዩኒቨርሲቲ እየተገኙ ልምዳቸውን እንዲያጋሩ ከትምህርት ክፍሉ አባላት ጋር በጋራ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ከእዚህም ባሻገር በሚኖርበት ሀዋሳ ከተማ አንባቢ ትውልድን ለመፍጠር 60ሻማ በሚል መጠሪያ ከብሩክ ተስፋዬ ጋር የተለያዩ ደራሲያንን በግል ወጫቸው በየወሩ በመጥራት ወጣቶችን አነቃቅተዋል፡፡ በርከት ያሉ የከተማው ወጣቶችም የራሳቸውን ስራዎች እንዲያሳትሙ በር ከፍተዋል፡፡ ይህ የ60ሻማ ዝግጅታቸው፣ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር፣ ተስፋዬ ገሰሰ፣ ሥዩም ተፈራ፣ የሻው ተሰማ፣ ፍቅረማርቆስ ደስታ፣ ዓለም እሸቱ፣ እንዳለጌታ ከበደ (ዶ/ር)፣ አንዷለም አባተ (ዶ/ር)፣ በሀይሉ ገ/እግዚአብሔር፣ በዕውቀቱ ስዩም፣ ሜሮን ጌትነት እና ሌሎችም ደራሲዎች በመገኘት ለሥነጽሑፍ አፍቃሪያን ልምዳቸውን እንዲያጋሩ በር ከፍቷል፡፡ ለእዚህም በከተማው ከሚገኝ ተቋም የምስጋና ሰርተፍኬትና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የልጆች መጽሐፍ ህትመት 100ኛ ዓመት መታሰቢያ በወመዘክር በተከናወነበት ወቅትም፣ ከ2000ዓ.ም. በኋላ በርከት ያሉ የልጆች መጽሐፍን በመጻፍ አበርክቶ ካላቸው 8 ደራሲያን አንዱ በመሆንም በሆሄ የሥነጽሑፍ ሽልማት እና በኢትዮጵያን ሪድስ አዘጋጅነት በተከናወነ መርሃግብር ከኢፌድሪ የባሕል ሚኒስቴር ዴኤታ የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶለታል፡፡

ዘላለም ጌታቸው እንደርሱ በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ የአማርኛ ቋንቋ እና ሥነጽሑፍ መምህርት ከሆነችው ሒሩት አምሃ ጋር ትዳር የመሰረተ ሲሆን፣ ሁለት ልጆችም አፍርተዋል፡፡ ሴት ልጃቸው ማርካን ዘላለም፣ ወንድ ልጃቸው ደግሞ ናታን ዘላለም ይባላሉ፡፡ ሁለቱም እንደወላጆቻቸው በልጅነታቸው ከፍ ያለ የማንበብ ፍቅር ያላቸው ሲሆን፣ ይህንን የማንበብ ፍቅር ለመላው የኢትየጵያ ልጆች እንደሚመኝ ዘላለም ይገልጻል፡፡ በቀጣይ ህይወቱም በተለይ በልጆች ትምህርት እና መጽሐፍ ዙሪያ የተሻሉ ስራዎችን ለመስራት እርሱና እና ባለቤቱ ልጆቻቸውን አንባቢ ለማድረግ የሄዱበት መንገድ እና ያገኙት ውጤት የበለጠ እንደሚያነሳሳው ይገልጻል፡፡ ባለቤቱ ሒሩት አምሃ በመስኳ በክልል አቀፍ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ በተደረጉ የምርጥ መምህራን ሽልማቶች በተደጋጋሚ ጊዜ አሸናፊ የሆነች ሞዴል መምህር መሆኗ፣ በመማሪያ መጽሐፍ ዝግጅትና አማካሪነት እንዲሁም በሬዲዮ ትምህርት አዘጋጅነት የሰራች ጎበዝ ባለሙያ መሆኗ ስራውን እንዳቀለለት በመግልጽ፣ “ቤቴ ጎበዝ አርታኢ ስላለችኝ ስራዎቼ ለልጆች ጠቃሚ እንደሚሆኑ አልጠራጠርም” በማለት የባለቤቱን አስተዋጽኦ ከፍ አድርጎ ይገልጻል፡፡

ዘላለም እና ባለቤቱ በአሁኑ ወቅት ከመደበኛ ስራቸው ባሻገር የልጆች የትምህርት ዌብሳይት በማበልጸግ ለቀጣዩ የትምህርት አመት የኢትዮጵያ ልጆች እንዲጠቀሙበት ግብአቶችን በማሟላት ላይ ይገኛሉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *