እመቤት አንዱዓለም በላይ
የ ዚህ ታሪክ አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡
ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡ ከሚድያ ዘርፍ ታሪኩዋ የሚቀርብላት ጋዜጠኛ እመቤት አንዱአለም በላይ ናት፡፡
ቅጽል ስም ( ሄለን )
እመቤት በጋዜጠኝነት ሙያዋ ለ13 አመታት ሰርታለች፡፡ ሆኖም ብዙ እንደሚጠበቅባት ስለምታምን መስራቷን በሙሉ ልብ ለመግለፅ ይቸግራታል፡፡ አብልጣ ለመስራት እቅድ ማኖሯም ለዚሁ ነው።
ዉልደት- እድገትና -ትምህርት
እመቤት አንዱዓለም በ ግንቦት 1 1977 ዓ.ም ነው የተወለደችዉ፡፡ በአዲስ አበባ ልዩ ስሙ መካኒሳ ቆሬ(ሁለት ቁጥር ማዞሪያ ) የሚባል ሰፈርም አድጋለች፡፡ ጊዜን ባግባቡ እንደምትጠቀምበትና ፣ይሄ ነገር አልፎኛል ብላም የምትቆጨው ነገር እንደሌለ ትናገራለች። ሁሉም በጊዜው ውብና የተማረችበት ነበር ፡፡
የቄስ ትምህርት ቤት ና አንደኛ እና 2ኛ ደረጃ
እርሷ ባደገችበት አካባቢ ፊደል የሚያስቆጥሩት የኔታ አባ ገብረማርያም ነበሩና እስከ ወንጌል ለሁለት አመት ያህል ተምራለች ፡፡ ሀሁን፤ አቦጊዳን፤ መልእክተንና ፤ወንጌልን ተምራለች፡፡ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርቷን በብሩህ ተስፋ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት፤ ሁለተኛ ደረጃ አየር ጤና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ተከታትላላች፡፡ የመሰናዶ ትምህርቷን ደግሞ በከፍተኛ 23 የመሰናዶ ትምህርት ቤት አጠናቃለች፡፡
ዩኒቨርሲቲና ሌሎች ስልጠናዎች
የመጀመርያ ዲግሪ በ1999 ዓ.ም በባህርዳር ዩኒቨርስቲ በጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ያገኘችው ጋዜጠኛ እመቤት አንዷለም ባህርዳር ዩኒቨርስቲ ህይወትን ጭምሮ አብሮ መኖርን የመሰለ ክህሎት የተማረችበት እንደሆነ ትናገራለች፡፡ .በ2006 የአንድ አመት በአማኑ ልብስና ዲዛይን ማሰልጠኛ ተቋም በልብስ ስፌትና ዲዛይኒግ ሰርተፍኬት አግኝታለች ፡፡
በ2012 ከቶም ፎቶግራፊና ቪዲዮግራፊ ማስልጠኛም ፤ በካሜራ በቪዲዮ ኤዲቲንግ ፤ በዳይሬክቲንግ እና በስክሪፕት ጸሀፊነት ለአን ድ አመት በመሰልጠን ሰርተፍኬት አግኝታለች፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በመካነየሱስ ሊድርሽፕ ኮሌጅ ( organizational leadership and management ) የማስተርስ ድግሪዋን እያጠናቀቀች ነው፡፡ በጋዜጠኝነት ሞያን በተመለከተ በርካታ አጫጭር ስልጠናዎችን የወሰደች ሲሆን ሰርተፍኬትም አግኝታበታለች፡፡
- በ2001 ዓ.ም በፋና ራዲዮ በሬዲዮ ጋዜጠኝነት -በ2003 ዓ.ም ( sexual reproductive health training for journalists ) በማሪስቶፕስ ኢንተርናሽናል
- በ2004 ዓ.ም (infection privation and patient safety) በዩ. ኤስ. አይዲ በ2004 ዓ.ም. (Audience based health communication) በዲኬቲ ኢትዮጵያ
- በ2011 ዓ.ም (building resilience and adaption to climate extremes and disasters ) በቶምሰን ሮይተርስ ፋዉንዴሽን -በ2012 ዓ.ም (በስደት እና በፍልሰት አዘጋገብ ) በአይ ኦ ኤም
- በ2013 ዓ.ም (conflict sensitive reporting and election reporting inclusive reporting ) በኢንተርኒዉስ አጫጭር ስልጠናዎችን ወስዳለች።
ከዚህ በተጨማሪ በመንፈሳዊ ትምህርት በኢትዮጵያ ኦርቶድክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን በሰንብት ትምህርት ቤት የሚሰጠዉን የሶስት አመት ኮርስ በቀዳማይ ፤ካላይ እና ሳልሳይ ተከታትላ አጠናቅቃለች፡፡
ልጅነት
ልጅነትዋ የነፃነት ጊዜዋ ነው። ሁሉን ሞክራ አሁንም ድረስ ከማትረሳቸው የልጅነት ጓደኞቿ ጋር ከነአመለወርቅ ፣ ፍሬህይወት ፤መአዛሽ እና ቅድስት በወቅቱ ከነበሩ ጓደኞች ጋር በነጻነት ተጫውታ ማደጓ የልጅነት ትውስታዋ ነው። በሰፈሩ የተቸገሩ አዛውንቶች ፤ ልጆች የሌላቸ ዉ እንዲሁም የአእምሮ ህመም ላጋጠማቸዉ ሰዎች ቤታቸዉን በማዘጋጀት ምግብ በማብሰል እገዛ ታደርግም ነበር።
የምትኖርበት አካባቢ በሚገኝ የካቶሊክ የሳሊሲያን ሲስተርስ በጎ አድራጎት ድርጅት በመሄድም የእጅ ሞያ ( ጥልፍ የተማረችው እመቤት አንዷለም በተማሪነት ጊዜ ባሀላዊ አልባሳትን በመጥለፍ ገንዘብ ታገኝበት ነበር፡፡የዩኒቨርስቲ ተማሪ እያለች ደግሞ በክረምት የጥልፍ ሞያዋን በደንብ በመጠቀም ራሷን ደግፋበታለች፡፡
ደራሲ መሆን የልጅነት ፍላጎቷ ስለነበር ጓደኞቿን በመሰብሰብ የፃፈቻቸውን አጫጭር ልቦለዶች ታነብላቸው ነበር ፡፡ በዚህ ፍላጎቷም በ2000 ዓ.ም ግን “ስራ ፍለጋ “የሚል አጭር ልቦለድ በማጻፍ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ሊታተምላት ችሏል። በፋና ኤፍ ኤም 98.1 እና በሸገር 102.1 ላይም ተተርኮላታል።
የስራ ህይወት
በ2000 ዓ.ም በፋና ኤፍ ኤም 98.1 በሪፖርተርነት በመቀጠር ስራ ጀምራለች ፡፡ ከዚሁ አመት ጀምሮ አስከ 2010 መስከረም ድረስ ከ9 አመት በላይ በፋና ብሮድካስቲነግ ኮርፖሬት በጋዜጠንነት ሰርታለች፡፡ ከ2000-2006 ..በኤፍ 98.1 በዜና ፤በፋና 90 እንዲሁም በዉይይቶችን በማዘጋጀት ቀጥታ ስርጭት የቅዳሜ መዝናኛ ሆስት በመሆንም ለረዥም ጊዜ ሰርታበታለች፡፡ በ2005 ዓ.ም አሜሪካን ሀገር ለሚተላለፈዉ ለማህበረ ቅዱሳን ሬድዬም በሳምንት የአንድ ሰዓት ፕሮግራም ለሶስት ወር አዘጋጅታለች።
ከ2006 በኋላ ደግሞ በፋና ፕሮግራም ክፍል በመዛወምር ፤ ትምህርታዊ የሬዲዮ ዝግጅቶችን አዘጋጅታለች፡፡ ሆስት በመሆን የእርሶ ቢሆኑና ቤተሰብ ሰአትን በማወያየትና ክፍሉ እንዲሰራለትየ ሚፈልጋቸዉን ስራዎች በብዛትም በጥራትም ለመስራት ጥረት አድርጋለች፡፡ ከ2010 ጀምሮ ደግሞ ለ10 ወራት በኢትዮ ኤፍኤም 107.8 በዜና ክፍል ሀላፊነት ወይም ዋና አዘጋጅ በመሆን የሰራችው ጋዜጠኛ ከ2011 ጀምሮም በአርትስ ቲቪ በዜና ከፍል በማስተባበርም እንዲሁም በዜና ኤዲተርነት አገልግላለች፡፡ በደስታ የተሞሉ 9 የስራ አመታት በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት
እመቤት ከተመረቀች በኋላ ኤፍ ኤሴች ለተባለ በጎ አድራጎት ድርጀት በሞያዋ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እየሰጠች ባለበት ወቅት ፋና ራዲዩ ማስታወቂያ በመዉጣቱ ተወዳድራ በሪፖርተርነት ተቀጠረች ፡፡ በፋና ለ1 ወር የሬድዮ ጋዜጠኝነት ስልጠና በመወሰድ ስራ ጀምራለች። በወቅቱ ፋና ኤፍ ኤም 98.1 ተደማጭ የነበረበት አሁን ድረስ በሬዲዮ ጋዜጠኝነት ስኬታማ የሆኑ ጋዜጠኞች የነበሩበት ክፍል ውስጥ በመመደቧ ሙያን ስነምግባርን እና ጠንካራ ሰራተኝነትን ከፋና ተምሬያለሁ ትላለች።
በፋና ራዲዮ ከታላለቆች በመማር በፍጥነት ከሪፖርተርነት-ወደ ከፍተኛ ሪፖርተርነት በመቀጠል ወደ ረዳት አዘጋጅነት እና አዘጋጅነት በማደግ ከ2004 ጀምሮ አስከ 2010 መስከረም በአዘጋጅነት ሰርታለች፡፡
በፋና የምትፈልገዉን በነጻነት በራሷ ዕቅድ በመስራቷ ዕቅድ የማመንጨት አቅሟን እንድታሳድግ ብሎም በነፃነት በመስራቷ አቅሟን እንድታጎለብት አግዟታል። አብረዋት የሚሰሩ ሰዎች አንድ እቅድ የማመንጨት ልዩ ክህሎቷን ያደንቃሉ፡፡ በተለይ ልትሰራ ያሰበችውን አንድ የስራን እቅድ ወይም ጉዳይ በሚገባ ስለምታውቀው አለቆችን አሳምናም ቢሆን የሀሳቧን ትክክለኛነት ታሳያለች፡፡ ጋዜጠኛዋ በዚህ ልዩ ክህሎቷ በመጠቀም በርካታ ማህበራዊ እና ጥበባዊ ስራዎችን አየር ላይ አውላለች፡፡
ጉዞ ወደ ኢትዮ ኤፍኤም 107.8
በ2010 ዓ.ም ኢትዮ – ኤፍኤም 107.8 ሲቋቋም የተደረገላት ጥሪ እና ጣቢያው ኢትዮጵያዊ አንድነትን የሚሰብክ በመሆኑ በሀሳቡ በመስማማት በደስታ ተቀብላ በዜና ክፍል ሀላፊነት ሰርታለች፡፡ እጅግ በጣም ትልቅ ክብር ከምትሰጠው የአናዶሉ ጋዜጠኛ ስለሺ ተሰማ ጋር መስራት በመቻሏ ሙያዋን እንድታዳብር እድል ፈጥሮላታል። በኢትዮ – ኤፍ.ኤም በነበራት ቆይታም ከፋና ሬዲዮ በቀሰመችው ልምድ መሰረት ቢሮው ውስጥ ጠንካራ ስነ-ምግባርና የስራ ባህል እንዲኖር ለማድረግ ችላለች።
ጣቢያዉንም በባለቤትነት አብሮ በመምራም ልምድ ከነበራቸዉ አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ እና ሰይፉ ፋንታሁን እንዲሁም የጣቢያዉ ስራ አስኪያጅ ወሰንየለህ ጥላሁን ጋር ጥሩ የስራ ግዜን በማሳለፏም ጥሩ ልምድን አካብታለች።
አርትስ ቲቪ
ከ 2011 እስከ አሁን አፍሪካን ሬኔሳንስ ቴሌቭዥን ሰርቪስ ከተቋቋመ በኋላ ባገኘችው አብሮ የመስራት እድልም በዜና ክፍል ኤዲተርነት በመስራት ላይ የምትገኝ ሲሆን ዜና በማንበብ ዜና በመስራት እንዲሁም አስፈላጊ ሲሆንም በዉይይትና ፕሮግራም በመስራት እንዲሁም የኦንላይን ዜናዎችን በማዘጋጀት ለአየር ታውላለች፡፡ በአርትስ ቴሌቭዥን ፤ የቴሌቭዥን ጋዜጠኝነትን ከቴክኒካል እዉቀት ፤ ከካሜራ ኦፕሬቲንግ፤ የላይት ሴት አፕ ዳይሬክቲንግ ።፣ስክሪፕት ራይቲንግና ቪዲዮ ኤዲቲንግ በመማር ራሷን ከስራው ጋር በእውቀት ለማዋሃድ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡
በጋዜጠኝነት ህይወት ከማትዘነጋቸው ውጤቶቿ ለአብነት:- 1. የኢራንን ታሪክ በ3 ክፍል የተሰራ መሰናዶ ከኢራን ኤምባሲ የአውሮፓዊያንተጽዕኖ የሌለበት በተደራጀ መረጃ የተሰራ እና ሚዛናዊ የሆነ በመሆኑ ለተቋሙ ምስጋና ለእርስዋ ደግሞ የኢራንን ባህልና ታሪክ የሚያጠናዉን የኢራኖሎጂ ትምህርት እንድትማር እድል ያገኘችበት ነበር፡፡ የኤምባሲውን ሰዎች ያስደሰታቸው ጉዳይ ሚዛናዊ ፕሮግራም መሆኑ ነበር ፡፡ 2. በደብረብርሃን አካባቢ ገጠራማዉ ክፍል ሚኖሩ አባወራ አርሷደሮች ወንዶች የሚጠቀሙበትን ቫዚክቶሚ የሚባለዉን የቤተስብ እቅድ አገልግሎቶች ተጠቅመዉ ባለቤቶቻቸዉን ካለባቸዉ ጫና የገላገሉ አባወራዎችን በማነጋገር የሰራችው ነበር፡፡ አባወራዎቹ ፤የባለቤቶቻቸዉ ህይወት እንዴት እንደተሻሻለች ያወሩት ፡ደስታቸዉ ፤ባህሉን እንዴት እንደተቋቋሙት ቡና ጠጡ በተሰኘዉ ፕሮግራም የተሰራጨ ድንቅ ዝግጅት የሚታወሰ ነው። 3. ስለ ጉዲፈቻ ፤ ስለኤች አይቪ ኤድስ በተከታታይ ለአመታት የሰሯቻቸዉ ፕሮግራሞችም እንዲሁ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የግል ህይወት
ጋዜጠኛ እመቤት ከ2004 ዓ..ም ጀምሮ ከአቶ ዳሳለኝ መንግስቱ ጋር ጋር ጋብቻየፈጸመች ሲሆን ማቴዎስ ደሳለኝ እና የማርያም ደሳለኝ የተሰኙ ሁለት ልጆችን አፍርታለች ፡፡ የህይወት መርህ በተቻለ መጠን አዲስ ነገር መፈለግ ለለዉጥ ሁሌም መማር መማር ፤ መሞከር መሞከር ካልተሳካም ያለዉ እንዳማረበት እንዲቀጥል መጣር የሚል ነው።