ኤፍሬም እንዳለ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ በስነጽሁፍ በቴአትርና በፊልም ዘርፍ ያሉ የተወሰኑ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የስነዳው ስራ ተጠናክሮ እየቀጠለ ሲሆን ይህም 2ኛው ዙር መሆኑ ነው፡፡ እኛ በአቅማችን የሰሩ ሰዎችን እያፈላለግን ያኖሩትን አሻራ ለምርምር ግብአት እንዲሆን አድርገን እያስቀመጥን ነው፡፡ በዚህ ስራችንም እንቀጥላለን፡፡

በተወዳጅ ሚድያ ቦርድ አጽዳቂነት የህይወት እና የስራ ታሪካቸው ሊሰራ ይገባል ያልናቸውን በተወዳጅ ሚድያ የዲጂታል መገኛዎችና በማህበራዊ ድረ-ገጽ ላይ እያስቀመጥን እንገኛለን፡፡ ትልቁ አላማችን በመረጃ እና በመዝናኛው ኢንዱስትሪ ላይ እነማን አሉ እነማንስ ነበሩ ብለን በጨረፍታ ለማሳየት ነው ትልቁ ሙከራችን፡፡ ያለቀለት ወይም የሁሉንም አሊያ የአብዛኛውን በዘርፉ ላይ ያለን ሰው ታሪክ ለማካተት ብንሞክር እንኳን ስራውን ከባድ ያደርገዋል፡፡ በመሆኑም በዚህ አመት በ2015 መጨረሻ በምናሳትመው መዝገበ-አእምሮ ከ120 በላይ የመረጃ እና የመዝናኛ ዘርፍ ላይ ያሉ ሰዎችን ታሪክ ጠብቁ ፡፡ ከእነዚህ አንዱ ኤፍሬም እንዳለ ሲሆን ባለፉት 43 አመታት በስነጽሁፍ በትርጉም ስራ እና በልቦለድ ስራዎቹ ከአንባቢ ጋር ለመተዋወቅ የበቃ ነው፡፡ ኤፍሬም እንዳለ ስለራሱ ለመናገር ባይወድም የቅርብ ሰዎቹን በማነጋገር የኤፍሬምን አበርክቶ ለማየት እንሞክራለን፡፡ ይህን ጽሁፍ በቀዳሚነት እንድንጽፍ መነሻ ሀሳቡን የሰጠን ወዳጃችን ጀሚል ይርጋ ሲሆን እዝራ እጅጉ እና ቅድስት ወልዴ ደግሞ ሙሉ ታሪኩን አጠናክረው ሰንደውታል፡፡

‹‹ጋዜጠኛ፣ ተርጓሚና ደራሲ ነው – ። አለቀ። ከዚህ ውጪ ስለ እሱ ግላዊ ሕይወትና ማንነት፣ ጥረትና ልፋት በሕትመትና ብሮድካስት ሚዲያዎች ሲነገር ሰምቼ አላውቅም። የእሱም ፍላጎትም፣ ግድም አይመስለኝም አደባባይ መውጣቱ። ደም ለመመለስ ቤቱን አቃጥሎ የሸፈተ ሰው፣ መልኩን አይደለም ጥላውን ሳያሳይ ጫካና ጥሻን ተከልሎ ወደ ዒላማው ጥይቱን እንደሚልከው ሁሉ ፣ እሱም ካለበት ጥጋት ተሰትሮ በብዕር ከመተኮስ ውጪ በታይታ ሰውነቱ አይታወቅም ››ሲል ጀሚል ይርጋ በፅሁፉ ኤፍሬም እንዳለን ያወሳዋል፡፡

ልጅነት እና ትምህርት

በመሀል ፒያሳ ሰራተኛ ሰፈር ተወልዶ አድጓል፡፡አባቱ አቶ እንዳለ ገ/ፃዲቅ በብርሃን እና ሰላም ድርጅት ወስጥ በኃላፊነት ያገለገሉ ሲሆን የትላልቅ ደራሲያን መፅሃፍትንም የሰሩ ሰው ናቸው፡፡ለቤተሰቡ አራተኛ ልጅ የሆነው ኤፍሬም ቤተሰቡ አንባቢ ነበሩ፡፡ እርሱም ከልጅነቱ የተከተለው ልምዱ ንባብ ነበር ፡፡በስልሳዎቹ መጨረሻ በሰባዎቹ መጀመሪያ መጽሀፍ ሊገዛ ሲመጣ የተዋወቅነው የሚለው አቶ ክብሩ ክፍሌ (የክብሩ መፅሀፍት ባለቤት) ኤፍሬም እንዳለ ዛሬም የመፅሀፍት ደንበኛው ነው፡፡ ክብሩ እንደሚናገረው ኤፍሬም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ታሪካዊ እና እንግሊዘኛ ልብወለድ መፅሀፍትን ያነብ ነበር፡፡
አብሮ አደጉ ግዛቸው የማነ መኩሪያ ኤፍሬም እንዳለን ከ1970 ጀምሮ ያውቀዋል፡፡አብረው ባደጉበት ፒያሳ ሰራተኛ ሰፈር የልጅነት ጊዜያቸውን አሳልፈዋል፡፡

ኤፍሬም እስከ ስምንተኛ ክፍል በካቴድራል ት/ቤት ተምሯል፡፡በዚሁ ትምህርት ቤት በተለይም ሰባተኛ ክፍል የእንግሊዘኛ ልብ-ወለድ መጽሀፎችን ማንበብ ግዴታ ነበር፡፡ከመጽሀፍቱም ያገኙትን ዋና ሃሳብ ሆነ ጭብጥም ያስረዱ ነበር፡፡ይህ ለኤፍሬም ከንባብ ጋር በእጅጉ አቆራኝቶታል፡፡በጊዜው በትምህርት ቤት ውስጥ በርካታ መፅሀፎችንም በማንበብ ተሸላሚ መሆን ችሏል፡፡ በመቀጠልም የአሜሪካ የሰላም አስከባሪዎች በነበሩበት ወቅት በተፈሪ መኮንን(ቲኤምኤስ)ተምሯል፡፡በጊዜው አለማያ ኮሌጅ ይባል በነበረበት ወቅት ተቀላቅሎ የነበረ ሲሆን በእድገት በህብረትም ምክንያት አቋርጦ በዘመቻው ተሳትፏል፡፡ በአሜሪካ ኤምባሲ አማካይነት የጋዜጠኝነት ስልጠና አግኝቶ ሲጨርስ ወደ ሃገሩ ተመልሷል፤ቡልጋሪያም በሌላ ጊዜ ሄዶ ትምህርት ወስዷል፡፡

የስራ ህይወት

ኤፍሬም ወደ አርባ ለሚጠጉ ዓመታት ጀምሮ በተለያዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ ምፀት – ለበስ ወጎችንና ጨዋታዎችን ሲያስኮመኩመን አሁን ድረስ አለ። ገና ከወጣትነቱ ካቴድራል እየተማረ ጀምሮ ለፅሁፍ ስራዎች እና የንባብ ዝንባሌ የነበረው ሲሆን በ1972 ዓ.ም ስራ የጀመረው በኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ ላይ ነበር፡፡ በአብዛኛው በሄራልድ ጋዜጣ ይፅፋቸው የነበሩ ጽሁፎች በአንጋፋው ጋዜጠኛ በያዕቆብ ወ/ማርያም ይታዩለት ነበር፡፡ኤፍሬምም ቢሆን ዛሬ ለደረስኩበት ደረጃ አስተዋፅኦዋቸው ከፍ ያለ ነው ሲል ያነሳቸዋል፡፡እርሳቸውም ቢሆኑም ኤፍሬም በአማርኛ እና በእንግሊዘኛ የሚጽፋቸው ፅሁፎች ልዩ ናቸው ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ኤፍሬም እንዳለ በዚህ ጋዜጣ ላይም በሕዝብ ዘንድ እጅግ ተወዳጅነት የነበረውን ‹‹ቢትዊን ዩ ኤንድ ሚ››የተሰኘውን አምድ በመጀመር ለጽሁፍ ስራ ያለውን ፍቅር ተወጥቷል፡፡ በአምደኝነትም ሰርቷል፡፡የዚህን አምድ ርዕስ አቶ ያዕቆብ ወ/ማርያም እንደሰጡትም እና ያግዙትም እንደነበር ይናገራሉ፡፡በኢትዮጵያ ሄራልድ ላይም ለ16 ዓመታትም በተለያዩ ደረጃዎች እና አምዶች ላይ በመፃፍ አገልግሏል፡፡ ሄራልድ ጋዜጣ አብረው የሰሩት ሰለሞን በቀለ አቋቁሞት በነበረው ማህሌት መጽሄት ላይም ተወዳጅ የሆኑ ጽሁፎችን በብዕር ስም በመፃፍ ኤፍሬም ይታወቃል፡፡በ”ምዕራፍ” ጋዜጣ ከነ ስብሐት ገብረእግዚአብሄር ጋር በመሆን በዋና አዘጋጅነት ሰርቷል፡፡

ከጓደኞቹ ጋርም ዘሰን የተሰኘ ጋዜጣ አቋቁሞ ይሰራበት ነበር፡፡ኤፍሬም ከዚህም በተጨማሪም በ”ፀደይ” መጽሔት እንጨዋወት አምድ ላይም ታዋቂ የሆኑ ፅሁፎችን ይጽፍ ነበር፡፡ በ1992 ዓ.ም በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ እንጨዋወት የተሰኘውን አምድ በመክፈት፤በዚህ ጋዜጣ ላይም ረዥም ጊዜ ማለትም ለተከታታይ 23 አመት በመፃፍ ቀዳሚው ነው፡፡ ጽሑፎቹ የጨዋታዎቹ ለዛቸውን ጠብቀው የቆዩ ናቸው፡፡ ዕይታዎቹና የሚያነሳቸው ጉዳዮች ጥልቅ እና በሳል ናቸው፡፡ እንዲሁም ብዕሩ ከዘመን ዘመን አልከሸፈም፡፡ የህበረተሰብን ጉዳይ ለዛ ባለው መንገድ በማንሳት ኤፍሬም ተመስክሮለታል፡፡

በ”አዲስ አድማስ” ጋዜጣ ላይ የሚጽፋቸው ጽሁፎች ትናንት አራዳ፣ ዛሬም አራዳ ነገም አራዳ እንደሆነ ስለመዝለቁ ያሳብቃሉ ፡፡ ለወጉ ማዋዣነት ጣል የሚያደርጋቸው አስቂኝ ቀልዶችና ገጠመኞች በአንባቢ ዘንድ በእጅጉ ይወደዳሉ፡፡ ዋሲሁን በላይ ኤፍሬምን ልክ እንደ ታላቅ ወንድሜ እመለከተዋለሁ ይላል፡፡ አንድ ሰፈር ናቸው፡፡‹‹ከኤፍሬም ጋር ከልጅነት ጀምሮ የምንተዋወቅ ሲሆን የሰራቸውን ስራዎች ሙሉውን ትርጉሙንም ወጥ ስራዎቹን እንዲሁም ደግሞ የህፃናት መፅሃፉንም በሙሉ በሚያስብል ደረጃ አውቃቸዋለው። መፅሃፍቶች ከነ ትርጉሞቹ ከ18 በላይ የሚጠጉ ናቸው››ሲል ይመሰክራል፡፡

መጻሕፍትን ለንባብ በማብቃቱም ረገድ፤ሶስት የሲድኒ ሸልደንን መፅሀፍት ተርጉሟል፡፡ እጅግ ተነባቢና ተወዳጅ የነበረውን የሮበርት ሉድለምን መጽሐፍ “ፍንጭ” በሚል ርዕስ ለንባብ አብቅቷል። የቱርካዊውን አዚዝ ኔሲን “እራሴን አጠፋሁ” የተሰኘ መጽሐፍም በኤፍሬም እንዳለ ተተርጉሞ ለህትመት የበቃ ነው። እሱ ያዘጋጀውን “ቤርሙዳ ትርያንግል” የተባለ መጽሐፍም ከብዙ ዓመታት በፊት ለአንባቢያን ደርሷል። “የዘመን ዱካ” እና “ሕይወት በክር ጫፍ” የተሰኙ ሥራዎችም አሉት። በተለያዩ መጽሔቶችና “እፍታ” መጽሐፍ ላይ የወጡ የራሱንና ትርጉም አጫጭር ልቦለዶችን ለአንባቢያን አበርክቷል። “የጉራ ሊቅ”ን ያስታውሷል። “እንግሊዘኛን በቀላሉ”

የተባለች ለእንግሊዘኛ መማሪያነት የምታገለግል በኪስ የምትያዝ ታዋቂ መጽሐፍም ነበረችው። ጋዜጣና መጽሔት ላይ ወጥተው የተነበቡ ሥራዎቹንም በመጽሐፍ መልክ አሳትሟቸዋል። በአብዛኛው መፅሀፎቹ የታተሙት በክብሩ አማካይነት ነው፡፡ ክብሩ ክፍሌ ‹‹ሕይወት በክር ጫፍ››የተሰኘውን የኤፍሬምን ልቦለድ ያደንቃል፡፡ በኢትዮጵያ ሬድዮ “ቅዳሜ መዝናኛ” እና በሸገር ሬድዮ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የአርብ እና የሰኞ ወሬዎችን ተከትሎ ያቀርባቸው የነበሩ ወጎች እጅግ ተናፋቂ ነበሩ፡፡ በተጨማሪ “የጨዋታ” ፕሮግራም ላይ የተላለፉ ተከታታይ እና አጫጭር አዝናኝ ድራማዎችን በመድረስና በመተርጎም ለአድማጮች እንዲደርሱ አድርጓል። ተደንቆበታልም።

በአንድ ወቅት ቢቢሲ አዘጋጅቶት በነበረው የስነፅሁፍ ውድድር በግሉ ተወዳድሮ ከአፍሪካ አራተኛ ወጥቶ ሃገሩንም ማስጠራት ችሏል፡፡ ታዲያ በጊዜው የቢቢሲዋ ጋዜጠኛ በማሸነፉ ምክንያት ቃለ-መጠይቅ እናድርግልህ ስትለው ኤፍሬም እንደ ሁል ጊዜው አቋሙ ፈቃደኛ አይደለሁም ሲል ምላሽ ሰጥቶ ነበር፡፡ ኤፍሬም በአንድ ወቅት “ስካይ ፕሮሞሽን” የሚል የማስታወቂያ ድርጅት አቋቁሞ እንቅስቃሴ ያደርግ ነበር።

ባህርይ

ባህሪውን ሲገልጹትም በጣም ሰው አክባሪ ፣ሰዎችን ለመተቸትም ሆነ ሰውን ለመውቀስ ፈፅሞ የማይሆንለት ነውለለ ትክክል እንኳ እንዳልሰሩ ሆነ እንዳልሆኑ ሲመለከት በተረጋጋ እና አስተማሪ በሆነ መንገድ የሚናገር መሆኑን ነው፡፡ አብሮ አደጉ ግዛቸው የማነ ዛሬ ላይ ኤፍሬምን ሲገልጸው ‹‹ ኤፍሬም ቁጥብ ነው፡፡ለመናገር ሳይሆን ለመስማት ይፈጥናል፡፡ስለምንም ነገር አስተያየት ሲሰጥ በእርጋታ ነው››በማለት ነው፡፡ ኤፍሬም እንዳለ በተለያየ አጋጣሚ ስራውን ከሰራ በኋዋላ ገንዘቡን በጊዜው አልያም ጭራሹኑ ላይከፍሉት ይችላሉ፤እርሱ ግን በቃ ሲመጡ ይምጡ በማለት እንጂ በመጨቃጨቅ አይታወቅም፡፡ከዚሁ ጋር በተያያዘ እነዚህን ሰዎች የማኩረፍም ልምድ የለውም፡፡

‹‹በሰራው ስራ አልተጠቀመም፤በገንዘብ ያን ያህል ተጠቃሚ አይደለም፡፡ወጪውንም አልሸፈነለትም፡፡ለቀረበው ሰው እንደ ኤፍሬም አይነት ጥሩ ሰው የለም፡፡ከዚህ ውጪ ግን ልታይ የማይል ስነ-ስርዓቱ ልዩ የሆነ ፤እርሱ በራሱ ዓለም ነው የሚኖረው ››የሚለው የክብሩ መፅሀፍ ቤት ባለቤት አቶ ክብሩ ነው፡፡ ‹‹ ኤፍሬም እንዳለ ለስፖርት ልዩ ፍቅር ያለው ሲሆን እግር ኳስን ይመለከታል፡፡ሌሊት እስከ 6 ሰዓት ሲፅፍ ያምሽ እንጂ ከዚያ በኋላ እንቅልፉን የሚሻማው ነገር አይፈልግም፡፡ቤተሰብን መንከባከብ ግዴታ ነው ለእነሱ መኖር ያስፈልጋል ሲል ሁሌም ይሰማል፤እናቱ ወ/ሮ በየነች ህይወታቸው ካለፈ በኋላ አባቱን አቶ እንዳለ ገ/ፃድቅን በመንከባከብ በአጠቃላይ ቤተሰቡን በመንከባከብ ኖሯል›› ሲል አብሮ አደግ ጓደኛው ይመሰክርለታል፡፡

ዋሲሁን በላይም ‹‹ኤፍሬም ከሙዚቃ መሳሪያዎች ኪቦርድ እና ጊታር የሚጫወት ሲሆን ከዚህ አኳያ ሁለገብ ሰው ነው። ማንኛውንም ወደ እሱ ሊያማክሩት የመጡት የፅሁፍ ስራዎች እያየ እና መስተካከል ያለበትን እያስተካከለ ለንባብ እንዲበቁ ያደርጋል። በተለይም የእንግሊዝኛ መፅሀፍቶችን ኤዲት ያደርጋል፡፡ የፅሁፍ ስራዎች የሚሰሩ ሰዎችንም ያበረታታል።›› ይለዋል፡፡ ሁሉም የቀረቡት እንደሚመሰክሩለት ኤፍሬም ከማውራት ይልቅ መፃፍን የሚመርጥ፣ከሱስ የፀዳ ፣ገንዘብን ሲያሳድድ ያልኖረ፣እውቅና እና ዝናዬን ሳይል ስራ እና ስራ ሲል ያለውን ለሕዝቡ በማድረስ ሁሌም ለሙያው ተደብቆ መኖርን መርጦ ዛሬም በዚሁ ቀጥሏል፡፡

መዝጊያ

ኤፍሬም እንዳለ በሀገራችን የሚድያ እና የስነ-ጽሁፍ ንቅናቄ ውስጥ ሊደምቅ የሚገባ ስም ነው፡፡ ለ43 ዓመታት በሚድያ ስራ ሲዘልቅ ሙያውን ወዶ እና አስከብሮ ነው፡፡ ኤፍሬም ለሙያው ያለው ታማኝነት ፤ ጽናት ለወጣቶች አርአያ የሚሆን ነው፡፡ ኤፍሬም በአንድ በኩል በእንግሊዝኛ በመጻፍና አርትኦት በመስራት አሉ ከሚባሉት ተጠቃሹ ነው፡፡ ኤፍሬም ግን እወቁኝ ባይ አይደለም፡፡ መታወቅ ቀዳሚ የህይወቱ ግብ አይደለም፡፡ የእርሱ አላማ የማይነጥፍ ብእሩን ማሳየት ብቻ ነው፡፡ ኤፍሬም ታዋቂ የውጭ መጽሀፍትን ይተረጉማል፡፡ ደግሞ የልቦለድ ስራዎችን በማውጣት ድንቅ የመፍጠር አቅም እንዳለው ያሳየናል፡፡ ኡፍሬም ይሰራል እንጂ አይታይም፡፡ ያውቃል እንጂ ለመታወቅ አይጣደፍም፡፡ ቢወድም ቢጠላ ግን አንባቢዎቹ ያውቁታል-ያብሩታል፡፡ ምክር ማግኘት ለሚሹ ደግሞ በሩ ክፍት ነው፡፡ ወጣቶች ሲመጡ ያለ አንዳች ስስት ያከማቸውን እውቀት ይለግሳል፡፡ ይህ ነው ኤፍሬም ማለት፡፡ እኛ እንደ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን እንደ ኤፍሬም አይነት ሰዎች ወደፊት እንዲመጡ እንሻለን፡፡ ለምን ቢባል የስራ ልምዳቸው ለወጣቱ ማሳያ ስለሆነ ነው፡፡ ትህትና የኤፍሬም ዋና መታወቂያው ነው፡፡ ይህን ደግሞ ብዙ ወዳጆቹ ይወዱለታል፡፡ እናም የኤፍሬምን የስራ ታሪክ አዲሱ ትውልድ እንዲያውቀው እነሆ አንብቡት ብለናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *