ወሰኔ በሻህ
ላለፉት 38 አመታት፣ በአፋን ኦሮሞ ወደ 50 የሚጠጉ መጽሀፍትን ለህትመት ያበቃው መምህርና ደራሲ ወሰኔ በሻህ በ65 አመቱ መጋቢት15 2010 አረፈ፡፡የቀብሩም ስነ-ስርአት በአዳማ ከተማ ተፈጽሞአል፡፡በ1967 በቁቤ መጻፍ የጀመረው ደራሲ ወሰኔ በሻህ በአርሲ ዞን ነበር የተወለደው፡፡ የደራሲ ወሰኔ መጽሀፎች ሁሉም ትኩረታቸውን በቋንቋ እና ባህል ላይ ያደረጉ ነበሩ፡፡
የመምህርነትን ስራ ከልቡ እንደሚወደው የሚናገረው ተመራማሪ ወሰኔ ለመጀመሪያ ጊዜ የአንደኛ ደረጃ መምህር ሆኖ ማስተማር እንደጀመረ ይነገራል፡፡ ባሌ ጎባ ለ3 አመት በሁለ-ገብ አስተማሪነት ካስተማረ በኋላ ወደ አርሲ በቆጂ በማቅናት ለ9 አመት አስተምሯል፡፡ በጭላሎ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ቤትም ለ4 አመታት በርካታዎችን ለቁም-ነገር ማብቃቱ ይነገርለታል፡፡
ከ1966 አንስቶ በመምህርነት ህይወቱን ያሳለፈው ደራሲ ወሰኔ፣ ለተወሰኑ ጊዜያት በትምህርት ቢሮ ውስጥ ማገልገሉን ይናገራል፡፡ ነገር ግን ‹‹ ወደምወደው ሙያ ብገባ ይሻላል›› የሚል እምነት ስለነበረው ወደ ቢሾፍቱ ሞዴል 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በማቅናት ማስተማር ጀመረ፡፡
በዛን ጊዜ ከነበረው የመምህራን ማሰልጠኛ የተመረቀው ወሰኔ ህይወቱን ሙሉ በማስተማር ያሳለፈ፣ ፈጽሞ ደከመኝን የማያውቅ ሰው እንደነበር ይነገራል፡፡
በ1984 የአፋን ኦሮሞ በቁቤ መጻፍ ሲጀመርና፣ የመጀመሪያዎቹ መጽሀፍቶች ሲዘጋጁ በብቃት ካሰናዱት አንዱ ወሰኔ ነበር፡፡ በተለይ ከ1ኛ ክፍል እስከ 6ኛ የተማሪዎች መማሪያዎች በቁቤ ሲሰናዱ ወሰኔ ከአዘጋጁት ውስጥ አንዱ ነበር፡፡የሁለተኛ ዲግሪውን የያዘው ወሰኔ በመማር ያምናል፡፡ማስተማር ደግሞ ከልቡ የሚወደው ሙያ መሆኑን አጽንኦት ሰጥቶ ይናገራል፡፡
ወሰኔ ‹‹ወደ 50 የሚጠጉ መጽሀፍትን እንዴት ልትጽፍ ቻልክ?›› ተብሎ ተጠይቆ በሰጠው መልስ አስተማሪ መሆኑ በርካታ መጽሀፍትን እንዲያሳትም እንደረዳው ይናገራል፡፡ በደራሲ ወሰኔ እምነት አንድ መምህር ከተማሪው ይማራል፡፡ ‹‹እኔም ከተማሪዎቼ ብዙ መማር በመቻሌ ብዙ ለመጻፍ ቻልኩ›› ሲል ተናግሯል፡፡
ህይወቱ ሲያልፍ የ65 አመት ሰው የነበረው አንጋፋው የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ተመራማሪ ወሰኔ በሻህ፣ መደበኛ ትምህርቱን የጀመረው በ10 አመቱ ነበር፡፡ በትምህርቱ ጎበዝ የነበረው ወሰኔ አንደኛ ደረጃን በ3 አመት ውስጥ ሊያጠናቅቅ ችሏል፡፡ወሰኔ ከዚህ ባሻገር፣ በርካታ የምርምር ወረቀቶችን ከማቅረቡ ሌላ ‹‹ ቀቤ›› የሚል ርእስ ያለውን በአፋን ኦሮሞ የወጣ መጽሄት ማዘጋጀቱ ይታወቃል፡፡
ይህ ታላቅ የሀገር ባለውለታ በትናትናው እለት ማለትም መጋቢት 15 2010 ህይወቱ ሊያልፍ ችሏል፡፡ ደራሲና መምህር ወሰኔ በሻህ የቀብር ስነ-ስርአቱ ዛሬ መጋቢት 16 2010 በአዳማ ከተማ ፣ መድሀኒአለም ቤተ- ክርስቲያን ከቀኑ -6 ሰአት ላይ የተፈጸመ መሆኑ ታውቆአል፡፡ ደራሲና ተመራማሪ ወሰኔ በሻህ የ5 ልጆች አባት ነበር ፡፡ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን ለመላ ቤተሰቦቹና አድናቂዎቹ መፅናናትን ይመኛል