አማረ አረጋዊ ወልደኪዳን 

አማረ አረጋዊ ወልደኪዳን 

 የሪፖርተር ጋዜጣ ባለቤት አቶ አማረ አረጋዊ ፤ 

ብዙ አልተነገረለትም፡፡ ብዙ ግን ሰርቷል፡፡ ስራዬ ይናገር ብሎ ስለሚያምን ከወንኩ ብሎ በኩራት አይሞላም፡፡ በሀገራችን 26 አመት የሞላውን ፤ ያለ አንዳች መቋረጥ የታተመውን ሪፖርተርን  ዛሬ ድረስ አዝልቋል፡፡ በቲቪ በሬድዮ ስለ ግለ-ታሪኩ ሲነገር አይሰማም፡፡ በጋዜጣ በመጽሄት አቶ አማረ ይህን አደረገ ይህን ፈጸመ  እዚህ ቦታ አደገ ተብሎ ሲጻፍ አላየንም፡፡ ግን ለሀገሩ ሚድያ እድገት ለአመታት የታገለ ፣በእውቀት ብቻ ተመስርቶ ስለሚሰራው ስለዚህ ሰው ለምን ያልተነገረው? ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን  በአቶ አማረ አረጋዊ ላይ በቂ ጥናት በማድረግ ይህን ለዊኪፒዲያ የሚሆን ጽሁፍ አሰናድቷል፡፡ ከዚህ ቀደም የጥበብ የመረጃ እና የመዝናኛ ሰዎችን ግለ-ታሪክ እየሰነድን እንዳለ ይታወቃል፡፡ አሁን ደግሞ የአቶ አማረን የልጅነት የፎቶ ስብስቦች ፤ 12ኛ ክፍል የጻፈውን ጽሁፍ ይዘን ታሪኩን በዚህ መልኩ አቅርበናል፡፡  ክፍል አንድ እነሆ ፡፡ 

ጃንሆይና ብላቴናዎቹ

በሚድያ ስራ ለ40 አመታት ያገለገለው አቶ አማረ አረጋዊ ወልደኪዳን በገና እለት ታህሳስ 29 ቀን 1947 አ.ም ተወለደ፡፡ እናቱ ወይዘሮ ዘነበች ገብረማሪያም ሲባሉ አባቱ ደግሞ አቶ አረጋዊ ወልደ ኪዳን ይባላሉ፡፡ የትውልድ ስፍራውም መቀሌ ነበር፡፡ በመቀሌ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ይማር በነበረበት ሰአት የትያትርና የስነ-ጽሁፍ ፍቅር ያደረበት አማረ በ1955 ገና የ8 አመት ብላቴና ሳለ እርሱና ጓደኞቹ አንድ አነስተኛ መጽሀፍ ጽፈው ነበር፡፡በጊዜው ንጉስ ሀይለስላሴ መቀሌን ለመጎብኘት የመጡ ጊዜ እነ አማረ የጻፉትን መጽሀፍ አይተው ነበር፡፡ጃንሆይ የብላቴናዎቹን ልዩ ጥረት ተመልክተው ‹‹በዚሁ ቀጥሉ‹‹  ብለው አበረታቷቸው፡፡

እስከ 11 አመቱ ማለትም ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ በመቀሌ ትምህርቱን የተከታተለው ታዳጊው አማረ፣ በ1959 ባገኘው ነጻ የትምህርት እድል የጄኔራል ዊንጌት ተማሪ   ለመሆን ቻለ፡፡ በልጅነቱ የስነ-ጽሁፍ ዝንባሌ ያሳደረው ታዳጊው አማረ ሁለተኛ ደረጃ ሲገባም በዚሁ ዝንባሌ ቀጥሎበት ዊንጌት የድራማ ክበብ ውስጥ የተለያዩ ድራማዎችን በመስራት በተለይ ‹‹ትዌልቭዝ ናይት›› በተሰኘው ቴአትር ላይ በመተወን የኪነ-ጥበብ ፍቅሩን ሊወጣ ችሏል፡፡ በዛን ወቅት ዊንጌት የሚገቡ ተማሪዎች ከየክፍለ-ግዛቱ  የተውጣጡ በትምህርት ውጤታቸውም ከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገቡ ነበሩ፡፡ አማረ ከእነዚህ ጎበዝ ተማሪዎች አንዱ ስለነበር በ12 አመት እድሜው የዊንጌት ተማሪ ቤት ግቢን ረገጠ፡፡

አማረ ፣ዊንጌት ያሳለፈውን ጣፋጭ 4 አመታት ዛሬ ድረስ አይዘነጋውም፡፡ በተለይ መምህሮቹ ተማሪዎቹን ብቁ ለማድረግ ያደርጉት የነበረውን ጥረት ፍጹም የሚረሳው አልነበረም፡፡ አቶ አማረ በ1962 አ.ም የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ በዊንጌት የተማሪዎች መጽሄት ላይ በእንግሊዝኛ የጻፈውን ጽሁፍ በማየት የታዳጊው የቋንቋ ክህሎት ምን ያህል የዳበረ እንደነበር መገንዘብ ይቻላል፡፡ እስቲ ይህን ጽሁፍ በማንበብ የታዳጊውን የኣማረን የልጅነት ትዝታ አብረን እንቋደስ፡፡

እንዴት  አይነት  ማራኪ ስፍራ ነው?

ዊንጌት የመመደቤ ዜና ለእኔ እንደ ትልቅ የምስራች የሚቆጠር ነበር፡፡ የመግቢያ ፈተናውን ሳልፍና አዲስ አበባ እንደምመጣ ሳውቅ በደስታ ቦረቅሁ፡፡አንዳች ታላቅ ኩራት ሲሰማኝ ታወቀኝ፡፡ አዲስ አበባ የደረስኩበትን ወቅት ፍጹም አልረሳውም፡፡ ጊዜው ዝናባማ ፣ መንገዱ ደግሞ ዝናቡ ባመጣው ምክንያት በጭቃ ተሞልቶ ነበር፡፡ልክ የሀምሌ ጨለማ እንደሚባለው አይነት፡፡  የከተማው ነዋሪዎች በክረምቱ ምሬት ቢያሰሙም ለእኔ ግን አንዳች ብሩህ ነገር ይታየኛል፡፡ በዚህ ብሩህ ስሜት  ታክሲ በመያዝ ወደ ምድብ ተማሪ ቤቴ አቀናሁ፡፡

በአንድ እጄ ቦርሳዬን እንዳነገትኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የጄኔራል ዊንጌት ተማሪ ቤትን ደጃፍ ረገጥኩ፡፡ ገና እቅጥር ግቢው እንደደረስኩ ቀስ ብዬ በታላቅ ርጋታ ተሞልቼ መራመድ ጀመርኩ፡፡ እርምጃዬ ሀይል ከተሞላ መሬቱ የሚሰነጠቅ ይመስል አሁንም ቀሰስ በማለት  በጥንቃቄ መራመድ ግድ ሆነ፡፡ተማሪ ቤቱን ልብ ብዬ አጤንኩት ፡፡ እንዴት አይን ማራኪ ስፍራ ነው?

አንድ ሀሳብ በውስጤ ይብላላ ጀመር፡፡‹‹… እዚህ ቅጥር ግቢ ምን አገኛለሁ? ስል ጥያቄውን ለራሴው አቀረብኩ፡፡ ለወደፊቱ ህይወቴ መሰናዶ የማደርገው በዚህ ስፍራ ነው ማለት ነው? በውስጤ መጠየቄን ቀጠልኩ፡፡ ታላላቆች እዚህ ነበር እውቀትን ሲቀስሙ የኖሩት? አሁንም ከራሴ ጋር ማውራቱ ቀጠለ፡፡

ከዚህ ቀደም ተማሪ ቤት አላየሁም ለማለት ሳይሆን የዚህኛው ለየት ያለ ሆኖብኝ ነው፡፡ በልጅነት ሳለን ከጨዋታ በቀር ለሀገር ማሰብ የሚባል የወደፊት ህልም አልነበረንም፡፡ አሁን 2ኛ ደረጃ ስገባ ለሀገር ማሰብ የሚለው ጉዳይ ታወቀኝ፡፡ ምናልባትም ሀኪም አሊያ ሳይንቲስት ሆኜ  የሀገሬን ስም አስጠራ ይሆናል፡፡ እርግጥ ነው ዊንጌት ተማሪ ቤት ነው፡፡  እንደነገሩ የሆነ ተማሪ ቤት አልነበረም፡፡ ብዙ አይነት ህይወት የሚታይበት፤ በአነስተኛ ቅጥር ግቢ ነገር ግን ብዙ ነገር የያዘ ታላቅ ስፍራ፡፡ የወደፊት የሀገር ተረካቢዎችን በዚህ መልኩ አቅፎ መያዝ እንዴት ያለ ድንቅና ታላቅ ነገር ነው?  አንዱ ከሌላው እውቀት የሚቀስምበት መልካም አጋጣሚ፡፡

4 አመት እንደመቆየቴ የተማሪ ቤቱ የትምህርት አሰጣጥ  ገራሚ ነው፡፡ ተማሪዎቹ የወደፊት መድረሻቸውን ጠንቅቀው ስለሚያውቁ  ጠንክሮ ለማጥናት ለንባብ ቅድሚያ ይሰጣሉ፡፡ ለስኬት ዋናው ቁልፉ ነገር ጠንክሮ መማር መሆኑንም  በሚገባ ያውቃሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከዊንጌት ታላቅ ነገር ትጠብቃለች፡፡

በተማሪ ቤቱ የነበረው የጨዋታ እና የስፖርት ክፍለ-ጊዜ በፍጹም አይዘነጋኝም፡፡ የዊንጌቱ ትዝታዬ ፍጹም ከህሊናዬ ጠፍቶ የሚቀር አልነበረም፡፡ ቀኖች ቀስ እያሉ መሄድ ሲጀምሩ ከዊንጌት የመለየቴን ነገር ሳስበው ሀዘኔ ይመጣል፡፡ ያ ያሳለፍኩት መልካም ትዝታ እንዴት ይረሳል?  ልጅ ሆኜ መጥቼ አድጌ የወጣሁበት፤ ታላቅ የእውቀት አድማስ ያገኘሁበት ዊንጌት፡፡

የአብሮ አደጎች ትዝታ

አቶ ሙሉጌታ ለማ አቶ አማረን በልጅነት ከሚያውቁት የቀድሞ የዊንጌት ተማሪዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ሁለቱ ብላቴናዎች ከጀነራል ዊንጌት እውቀት ቀስመዋል፡፡  አቶ ሙሉጌታ እንደሚያስታውሱት አማረ በልጅነቱ ጸባየ ሸጋና ጎበዝ ተማሪ ነበር፡፡  በተለይ የሼክስፒር ድርሰት በሆነው  ትዌልቭዝ ናይት ድራማ ላይ አማረን ሲተውን ያስታውሱታል፡፡

‹‹…. አማረ የጀመረውን ነገር ዳር የሚያደርስ ጠንካራ ሀገር ወዳድ ነው፡፡  በጀነራል ዊንጌት የቀድሞ ተማሪዎች ህብረት ውስጥም  አማረ የጎላ አስተዋጽኦ ያደረገ ነው፡፡ ›› ሲሉ አቶ ሙሉጌታ ለማ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

አቶ ዋቅጋሪ ጎንጆ ከአማረ ጋር ዊንጌት በሚገኘው ብሉ ሀውስ የነበራቸው ትዝታ ተነግሮ አያልቅም፡፡  እርሳቸው በጊዜው ከወለጋ ነበር የመጡት ፡፡ አንዱ ተማሪ ደግሞ ከደቡብ፡፡ ሌላው ደግሞ ከሰሜን ፡፡ አንዱ ከምስራቅ፡፡ በዚህ መልክ ኢትዮጵያ በዊንጌት ውስጥ አንድ ሆና ትገኝ ነበር ሲሉ አቶ ዋቅጋሪ ያስታውሳሉ፡፡  ያኔ የነበረን ፍቅር ልዩ ነበር ሲሉ ትዝታቸውን ያወጋሉ፡፡

አቶ ዋቅጋሪ የአቶ አማረ ጉብዝና ዊንጌት የጀመረ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡  በተለይ ለእንግሊዝኛ የነበረው ዝንባሌ ብዙዎቻችንን ያስደነቀ ነበር ሲሉ በትዝታ ተሞልተው አጫውተውናል፡፡  አማረ ከድሮ ጀምሮ ለነገሮች ምክንያታዊ ነበር ሲሉ ሀሳብ ይሰጣሉ፡፡

‹‹….. ከአማረ ጋር የቤተሰብ ያህል  የአንድ አባት 2 ልጆች ነበርን፡፡  ኢህአዴግ ከጫካ አዲስ አበባ ሲገባ መጀመሪያ ያገኘሁት አማረን ነበር፡፡  እኔ በጊዜው የልጅነት ነገሩ ነው የመጣብኝ፡፡  አማረ ገና የገባ ቀን ነው  ተቃቅፈን ሰላም የተባባልነው፡፡ ሳቅፈው እንባዬ እንደመጣ አስታውሳለሁ፡፡ የልጅነት ትዝታ ምንጊዜም ከህሊና አይጠፋም ›› ሲሉ 50 አመት  ወደ ኋላ ተጉዘው ትዝታቸውን አውግተውናል፡፡

ለ4 አመታት ያህል አንድ ክፍል የነበሩት አማረና አቶ ዋቅጋሪ በእረፍት ጊዜያቸው  እዚያው ዊንጌት አካባቢ ፓስቲ ቤት እየሄዱ ይጫወቱ ነበር፡፡ፊልም ቤት ከመሄድ ይልቅ በጥናት ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ፡፡

አቶ አማረ እና ጓደኞቹ በዊንጌት ሲማሩ ለታላቅ ቁምነገር  ካበቋቸው መምህራን መካከል  የ9ኛ እና የ10ኛ ክፍል የአማርኛ መምህር የነበሩት  አባ ህላዌ ይታወሳሉ፡፡  ግሪክ ሀገር የተማሩት  የግብረገብ መምህር አባ ሲራክም  እነ አማረ በጥሩ ስነ-  ምግባር እንዲታነጹ ካደረጉት መሃል ናቸው፡፡ አቶ ሰለሞን ሙሉነህ ደግሞ የ11ኛ እና የ12ኛ ክፍል  የአማርኛ መምህር ሲሆኑ በኋላ ላይ  የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ለመሆን የቻሉ ነበሩ፡፡ ከአቶ አማረ ጋር በዊንጌት ከተማሩት መካከል ዶክተር ተገኝወርቅ ጌቱ ፤ ካፒቴን ተስፉ፤ አቶ ነጂብ ፤ ዶክተር ታዬ የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡    

የሪፖርተር ጋዜጣ መስራች አቶ አማረ አረጋዊ ወልደኪዳን በ1962 የዊንጌት ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ እንግሊዝ ሀገር ነጻ የትምህርት እድል አግኝቶ ይሄዳል፡፡ እዚያም ለተወሰኑ አመታት ትምህርቱን ሲከታተል ቆየ፡፡ ከ1967-1983 በፖለቲካ ትግል ውስጥ ገብቶ የነበረው አቶ አማረ ከ1983-1985 የኢትዮጵያ ቲቪ መምሪያ ሃላፊ  እንዲሁም ከ1985-1987 የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የስራ መሪ በመሆን አገልግሏል፡፡

 ኢቲቪና አቶ አማረ

አቶ አማረ አረጋዊ ቴሌቪዥን የስራ መሪ በነበረ ጊዜ፣ በርካታ የለውጥ ርምጃዎችን በመውሰድ ለሚድያው ዘርፍ የማይዘነጋ ውለታ ውሏል፡፡ በተለይም በዜና፣ በመዝናኛ እና በቋንቋዎች ላይ መሰረታዊ ለውጥ እንዲመጣ ተመልካችን የሚመጥን፣ ፈጠራ የታከለበት ፕሮግራም አየር ላይ እንዲውል አድርጓል፡፡ አቶ አማረ ፣ የእኔ ዋና ግብ አዳዲስ መዋቅሮች እንዲዘረጉና ሳቢ የፕሮግራም ፎርማቶች እንዲቀረጹ ማድረግ ስለነበር ይህንኑ እውን ለማድረግ ብዙ ጥረት አድርጌያለው ይላል፡፡

በአቶ አማረ አረጋዊ ሀሳብ አመንጪነት ተጀመረው ከቆዩ የመዝናኛ ፎርማቶች አንዱ እሁድ ከሰአት ይቀርብ የነበረው 120 የመዝናኛ ፕሮግራም ነው፡፡ አቶ አማረ ሲኤንኤንን ለመጎብኘት በተጋበዘ ጊዜ ነበር የ120 ሀሳብ ውስጡ የተጸነሰው፡፡ ኋላ ላይ ፕሮግራሙ ከፍተኛ ተቀባይነት በማግኘቱ አማረንም ተመስጋኝ አድርጎታል፡፡ በወቅቱ የነበሩ የመዝናኛ ጋዜጠኞችም አቅማቸውን እንዲያወጡ በር የከፈተ አጋጣሚ ነበር፡፡ ጋዜጠኛን ነጻ በማድረግ ያምን የነበረው አቶ አማረ 120 መሰናዶን ለሚሰራው ባለሙያ እንዲመች አድርጎ የቀረፀው ስለነበር በቶሎ ተቀባይነት አግኝቶ ነበር፡፡

 ባለሙያዎችን በማበረታታት የሚያምነው አቶ አማረ ለ120 መሰናዶ እነማን ምን ሊሰሩ ይችላሉ? የሚለው ቀድሞ ያሰበበት ነበር፡፡ መሰናዶው የመዝናኛ ስለነበር ኮሜዲውን እንደ እነ እንግዳዘር ነጋ ፣ ደረጀ ሀይሌ፣ሀብቴ ምትኩ የመሳሰሉ ሰዎች ቢይዙት የተሻለ እንደሚሆን አቶ አማረ ያምን ነበር፡፡ ደረጀ ሀይሌ ለዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጅ እንደነገረው አቶ አማረ መዝናኛ የገባው ታላቅ ሰው ሲል ይገልጸዋል፡፡ ኮሜዲያን ደረጀ ሀይሌ 120 ከመጀመሩ በፊት በጣቢያው የኮሜዲ ስራ በማቅረብ ይታወቃል፡፡ ሀብቴም እንዲሁ፡፡ አቶ አማረ 120 እንዲጀመር ማድረጉ ለሀብቴና ለደረጀ ጥሩ እድል የፈጠረ ነበር፡፡

ደረጀ‹‹…… ያኔ በነበረው ስራችን ውስጥ በተለይ ከእኔና ከሀብቴ ጋር በተያያዘ የአንበሳውን  ድርሻ የያዘው ጋሽ አማረ ነው.›› ሲል አቶ አማረ ለ120 ማማር የተጫወተውን ሚና ጎላ አድርጎ ያስቀምጠዋል፡፡ በዚያን ጊዜ እነ አለልኝ መኳንን ፤ ጥላሁን ዘውገ እንግዳዘር ነጋ ፤ አበበ  በለው የተለያዩ የኪነ-ጥበብ ስራዎችን ሲያቀርቡ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ደረጀ እና ሀብቴ ወደ እሁድ 120 የኮሜዲ ስራ ይዘው ሲመጡ አቶ አማረ እንደ ስራ መሪ ያስቀመጠላቸው ጥብቅ የስራ ቅድመ-ሁኔታ አልነበረም፡፡ ይሁንና ስራዎቹ ተመልካችን የሚያዝናኑ የሚያንጹ ማህበራዊ ነገሮችን የሚነቅሱ እንዲሆኑ አቶ አማረ ይጠበቅ ነበር፡፡

‹‹….. አቶ አማረ ቲቪ ሳለን ስራ ሰርተን ስንወጣ ደረጃው ላይ ያገኘን እንደሆነ ሞራል ይሰጠናል፡፡ የትናንቱ ብዙም አያስቅም፡፡ ይልቅ በቀጣዩ ሳምንት ጥሩ ስራ ይዛችሁ ቅረቡ፡፡ ይለን ነበር፡፡ ኮሜዲው እኮ አስቆታል፡፡ ነገር ግን የተሻለ ስራ ይዘን እንድንመጣ በማሰብ አላሰቀኝም ይለናል›› ሲል ደረጀ 29 አመት ወደ ኋላ ተጉዞ ትዝታውን አውግቶናል፡፡ ደረጀ እንደሚያስታውሰው፣ አቶ አማረ አረጋዊ በጊዜው የነበሩጋዜጠኞችን  በማበረታታት አቅማቸውን አጎልብተው እንዲያወጡ ያደርግ ነበር፡፡ ቀርቦ እንደ ጓደኛ በማውራትም  ጥሩ የስራ ምህዳር ይፈጥር ነበር፡፡

አቶ አማረ ፣ በ1984 በ120 በተከታታይ ይቀርብ የነበረው ባለጉዳይ ድራማ አየር ላይ እንዲውል የአንበሳውን ድርሻ የተወጣ ባለውለታ ነው፡፡ ይህ በገጣሚና ተርጓሚ ነቢይ መኮንን የተደረሰ የቲቪ ድራማ በአበበ ባልቻ እና በፍቃዱ ተክለማሪያም እንዲሁም በሌሎች የተተወነ ሲሆን ድራማውም የተሰራው በአቶ አማረ አረጋዊ ቢሮ ውስጥ ነበር፡፡ ይህ ድራማ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተንሰራፍቶ የነበረውን የተገልጋይ እንግልት ፤ ብልሹ የሙስና አሰራር የሚያሳይ ነበር፡፡ ዛሬ ድረስ ይህ ድራማ በተመልካች አእምሮ ውስጥ የማይረሳ ለመሆን የቻለ ነው፡፡ በወቅቱ ኢህአዴግ ሀገሪቱን ከተቆጣጠረ ገና አንድ አመቱን ያስቆጠረ ሲሆን ቀርቦ በነበረው ድራማም ደስ ያልተሰኙ የመንግስት ባለስልጣኖች በስራ መሪው በአቶ አማረ አረጋዊ ላይ ጥርስ መንከሳቸው አልቀረም፡፡ አቶ አማረ አረጋዊ ግን በኪነ-ጥበብ ብልሹ የሙስና ስራዎችን ማጋለጥ አለብን ብሎ ያምን ስለነበር በተሰራው ድራማ ደስተኛ ነበር፡፡

አቶ አማረ በመሰረቱ ኢቲቪ የመጣው መሰረታዊ  ለውጥ  ለማድረግ ነው፡፡ ይህ ጥረቱ በከፊልም ቢሆን እንደተሳካለት የሚያምኑ አሉ፡፡ ሌላ አማረ እንዲለወጡ ካደረጋቸው ጉዳዮች አንዱ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተጠሪነቱ ለማስታወቂያ ሚኒስቴር መሆኑ ቀርቶ ለፓርላማ ተጠሪ እንዲሆን ማድረጉ ነበር፡፡ በተጨማሪም የፖለቲካ ፓርቲዎች በመንግስት ሚድያ የመጠቀም መብት እንዲኖራቸው አቶ አማረ ያደረገ ሲሆን ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ችሎ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ቲቪ ከአዲስ አበባ ወጣ እያለ የተለያዩ የበአል የስፖንሰር ፕሮግራሞችን አየር ላይ እንዲያውል ቆራጥ ውሳኔ በማድረግ  ሃላፊነቱን የተወጣው አቶ አማረ አረጋዊ ነበር፡፡ እንዲሁም አቶ ሀብቴ ገመዳ እንዳጫወቱን በኢቲቪ ለመጀመሪያ ጊዜ የማርኬቲንግ ዲፓርትመንት እንዲቋቋም ያደረገው አቶ አማረ ነው፡፡ በተጨማሪም ከ120 ሌላ በትግርኛ እኛ በአፋን ኦሮም ፕሮግራሞች እንዲቀረፁ ያደረገ ጠንካራ የሚድያ መሪ ነው፡፡

ሮማን ተገኝ-ስለ አማረ 

ጋዜጠኛ ሮማን ተገኝ ከ1977 ሚያዝያ ወር አንስቶ በሚድያ ሙያ ያገለገለች ስትሆን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ከ8 አመት በላይ በመዝናኛ ፕሮግራሞች ላይ ሰርታለች፡፡ ሮማን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከሀምሌ 1984 ከዛሬ 29 አመት በፊት የእሁድ 120 የመዝናኛ ፕሮግራም ሲጀመር ከመስራች ጋዜጠኞች አንዷ ናት፡፡ በጊዜው የቀደመ የ7 አመት ልምድ አካብታ የነበረችው ሮማን ተገኝ ከመምሪያ ሃላፊው ከአቶ አማረ አረጋዊ ቀርቦ የነበረውን አዲስ የፕሮግራም ፎርማት ምንነት ለማድመጥ ከቢሮው መገኘቷን ታስታውሳለች፡፡

በወቅቱ የስራ መሪው አቶ አማረ አረጋዊ ማዘጋጃ ቤት ግቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቢሮ ውስጥ ሆኖ 16 በላይ የሚጠጉ ጋዜጠኞችን ሰብስቧል፡፡ በስብሰባው ላይ ከታደሙት የዜና እና የፕሮግራም ጋዜጠኞች መካከል ሰሎሞን አባተ ፣ሰሎሞን አስመላሽ ፣መልካሙ ደምሴ ፣ሮማን ተገኝ፣ዘካሪያስ ኅይለማሪያም፣ግርማ ደገፋ ፣  ደምሰው መርእድ እና ያይኔአበባ አሰግድ ይገኙበታል፡፡

 በወቅቱ አቶ አማረ እሁድ ከሰአት ከ8 ሰአት ጀምሮ ተመልካች ዘና ፈታ የሚልበት አንድ የ2 ሰአት መሰናዶ ልንጀምር ነው ብሎ ሀሳብ ሲያቀርብ በጋዜጠኞች ፊት ላይ አንዳች የተስፋ ብርሀን ተነበበ፡፡ ይህ የተስፋ ብርሀን የመስራት ፤ አዲስ ፈጠራ ለተመልካች የማቅረብ ምኞትን አክሎ የያዘ ነበር፡፡ ከዚያ ቀደም ብሎ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እሁድ ከሰአት ላይ የሚቀርብ የቲቪ መሰናዶ አልነበረም፡፡ ያኔ የኢትዮጵያ ቲቪ 27ኛ አመት የምስረታ በአሉን አክብሮ ነበር፡፡

ሮማን ተገኝ  ጋዜጠኞቹ ላይ ይነበብ የነበረውን አንድ ፕሮግራም የመስራት ፍላጎት ዛሬ ስትገልጸው አቶ አማረ የስራ ሞራልን የማነሳሳት ችሎታው ምን ያህል ከፍተኛ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ ጋዜጠኞቹ እዚያው ስብሰባ ውስጥ ሆነው ይህን ብሰራ ያንን ባነብ እያሉ በውስጣቸው ሀሳብ ያብላሉ ነበር፡፡

‹‹……. ይህ 120 የተሰኘው ፕሮግራም ለብዙዎቻን ጥሩ የመስራት አጋጣሚን የፈጠረ ቢሆንም ምን አይነት ፕሮግራም አየር ላይ ብናውል ነው ተመልካች የሚደሰተው የሚለው ታላቅ ጭንቀት ውስጥ ከትቶን ነበር፡፡ ይሁንና በ15 ቀን ሁላችንም በአንድ ላይ ተረባርበን  ፕሮግራሙን አየር ላይ አዋልን ›› ስትል 120 ከተጀመረ በኋላ ከተመልካች ጥሩ ግብረ-መልስ መገኘቱን ትናገራለች፡፡

አቶ አማረም በተገኘው መልካም ግብረ-መልስ ተደስቶ ባለሙያዎቹን ያበረታታ ነበር፡፡  ማበረታታት የአቶ አማረ የዘወትር ልምዱ ነው፡፡ በማሸማቀቅ አያምንም፡፡  ባልደረቦቹ  ቀርቦ እና አቅርቦ ስለሚያወራቸው ሁሉም ሳይፈሩ ሀሳብ እየሰጡ ይሰሩ ነበር፡፡ ሮማን እንደምትናገረው  አቶ አማረ የስራ መሪ በነበረ ጊዜ ለጋዜጠኛው ጥሩ አመለካከት ነበረው፡፡ ነጻ ያደርጋል፡፡ እንደ አለቃ አይኮፈስም፡፡ ሮማን እንዲህ አይነት የሰውን ሞራል የሚገነባ፣ ለሰዎች ስሜት የሚጠነቀቅ መሪ የኢትዮጵያ ሚድያ ያስፈልገዋል ትላለች፡፡ ሮማን ትዝ እንደሚላት  አየር ላይ አንድ መሰናዶ አውላ ከሆነና በጣም ምርጥ ከሆነ  አቶ አማረ አበረታች ምክር ይለግሳል፡፡‹‹ ማመስገንን በደንብ አድርጎ የሚያውቀው አቶ አማረ አብረውት በሚሰሩት ባለሙያዎች  ተወዳጅ ነበር›› ስትል ሮማን ለዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች አጫውታናለች፡፡

ሮማን ተገኝ ፣አማረ ቲቪ የቆየበት ጊዜ በጣም አጭር እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ከ1983-1985 2 አመት ሰርቶ ዛሬ ድረስ መታወስ የሚችሉ ጉዳዮችን በማበርከቱ ምን ጊዜም ታላቅ ከበሬታ ይቸረዋል፡፡

‹‹ አማረ የኢትዮጵያ ሚድያ ባለውለታ ነው፡፡ አእምሮው እጅግ ክፍት ነው፡፡ ያኔ በ1985 አማረ ኢቲቪን ሊለቅ ነው ሲባል ሁላችንም ማልቀስ ነበር ያማረን፡፡ይሁንና ምክንያቱ ባልታወቀ መንገድ አቶ አማረ ወደ ኢዜአ የመሄዱን ዜና ሰማን.›› ስትል ሮማን አቶ  አማረ 5 አመት እንኳን ቢሰጠው ቲቪ ውስጥ ተጨማሪ ለውጦችን ማምጣት በቻለ ነበር ብላለች፡፡  ክፍል 2 ይቀጥላል.

አማረ በኢዜአ 

አቶ አማረ አረጋዊ ፣የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቆይታው እንዳበቃ  ወደ ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተዛወረ፡፡ በ1985 አ.ም ኢዜአን በመምሪያ ሃላፊነት የተቀላቀለው  አቶ አማረ አረጋዊ ወልደኪዳን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተሞክሮውን መሰረት በማድረግ ኢዜአም ላይ የአሰራር ማሻሻያ ለማድረግ ማሰቡ አልቀረም፡፡ ረጅም አመት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ሁሌም የመንግስትን ሀሳብ ብቻ ከሚያስተናግድ ይልቅ የህዝብ የዜና አገልግሎት መሆን የሚችልበትን ስልት ነበር አቶ አማረ ለመንደፍ ፈልጎ የነበረው፡፡

አቶ ብርሀኑ ተሰማ፣ በ1985 አቶ አማረ የኢዜአ የስራ መሪ ሆኖ በመጣ ጊዜ የኢዜአ የወላይታ ሶዶ ዘጋቢ ነበሩ፡፡ በአሁኑ ሰአት በዜና አገልግሎቱ ውስጥ በምክትል ዋና አዘጋጅነት እያገለገሉ የሚገኙት አቶ ብርሀኑ የአቶ አማረን ኢዜአን የማዘመን ህልምን በበጎ ጎኑ ይመለከቱታል፡፡ በተለይ ከሮይተርስ ባለሙያዎችን በማስመጣት በዜና አሰራር ላይ የዳበረ ስልጠና እንዲሰጥ ማድረጉ አቶ አማረን ያስመሰግነዋል ሲሉ አቶ ብርሀኑ ተሰማ የመምሪያው ሃላፊ ጥረት የደከሙትን ያህል ባይሆንም ለጥረታቸው ትልቅ እውቅና ሰጥተዋል፡፡

የሪፖርተር ጅማሮ

አቶ አማረ አረጋዊ ከበፊት ጀምሮ የራሱን ሚድያ የማቋቋም ህልም ሰንቆ ነበር፡፡ ታዲያ እርሱ ሊጀምረው ያሰበው ሚድያ ነጻ ፕሬስ ነጻ ሀሳብ ነጻ መንፈስ የሚለውን ትልቅ እሳቤ የሚያንጸባርቅ ነበር፡፡  በ1987 ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደለቀቀና የኢህአዴግ አባልነቱን እንደተወ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽንን ለመመስረት ሀሳብ አደረገ፡፡ በጊዜው ወይዘሮ መአዛ ብሩ እና ባለቤቷ አቶ አበበ ባልቻ አንደኛውን ድርሻ ይዘው ከአቶ አማረ ጋር ሪፖርተርን አንድ ላይ መሰረቱ፡፡ መአዛ ብሩና አቶ አማረ በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ የእድገት በህብረት ዘመቻ ላይ መአዛ ውቀሮ የዘመተች ጊዜ የሚተዋወቁ ነበሩ፡፡ በኋላ ላይ አቶ አማረ የቲቪ የስራ መሪ ሆኖ ሲመጣ ይበልጥ ቅርርባቸው እየተጠናከረ መጣ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ለዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጅ ሀሳቡን የሰጠው  የህግ ባለሙያ አበበ ባልቻ ሪፖርተር ሲጀመር አቶ አማረ እንደ አጋጣሚ እኛን አገኘን 50000ብር አዋጥተን ስራውን ጀምርን ይላል፡፡ ነገር ግን ሪፖርተር የሚለውን ስያሜ ከመስጠት አንስቶ በሙሉ የኤዲቶሪያል ስራው ላይ የነቃ ተሳትፎ ሲያደርግ  የነበረው አቶ አማረ እንደነበር ጠበቃ  አበበ ባልቻ ይናገራል፡፡

በወቅቱ የጥብቅና ሙያ ላይ የነበረው አበበ ባልቻ የአቶ አማረን ለፕሬስ ያለውን ቁርጠኝነት ያደንቃል፡፡ እንዴት ይደክም እንደነበር፤ ሪፖርተርን በህዝብ ዘንድ ተአማኒ ለማድረግ የሄደበትን ርቀት  አበበ ባልቻ ያደንቃል፡፡  የአማረን ያህል ለፕሬስ ስራ ያለ አንዳች መታከት የታገለ ሰው አላየሁም ሲል የወዳጁን ጥንካሬ ይገልጸዋል፡፡  ተዋናይ እና ጠበቃ  አበበ ሪፖርተር ጋዜጣ በመጀመሪያው እትም 10000ቅጂ መታተሙን ለተወሰኑ ጊዜያትም ኪሳራ ማጋጠሙን ይናገራል፡፡ ይሁንና አቶ አማረ ሪፖርተር ላይ የጸና እምነት ሰንቆ ስለነበር ያለ እረፍት ይሰራ ነበር በማለት ጠበቃው አበበ ትዝታውን አጫውቶናል፡፡

ተዋናይ እና  ጠበቃ አበበ ባልቻ   እስከ 1990 ድረስ የሪፖርተር የ50 ከመቶ ባለድርሻ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን መአዛ ብሩ ሬድዮ መጀመር ስለነበረባት ሬድዮና ጋዜጣ ደግሞ መስራት ባለመቻሉ ሙሉውን የባለቤትነት ድርሻ ለአቶ አማረ ትተን ወጣን ሲል አቶ አበበ ታሪኩን አጫውቶናል፡፡አቶ አማረ ሪፖርተርን ሲጀምር እርሱ ከሚፈልገው ራእይ ጋር አብረው ሊሄዱ የሚችሉ ጠንካራ ባለሙያዎችን ይፈልግ ነበር፡፡ ከበፊት ጀምሮ ሰው የመቅረብና የማቅረብ ችሎታው ሳቢ ስለነበር ሰው ማግባባቱን እና ማሳመኑን ተክኖበታል፡፡ እናም ለካርቱን ስራ አቶ በቀለ ሀይሌን ለሚድያው ስራ ሰሎሞን አባተን ፤ እሸቴ አሰፋን ፤ ደረጀ ደስታን እንዲሁም ከበደ ደበሌ ሮቢን በመያዝ ስራውን አንድ ብሎ ጀመረ፡፡

ያኔ ሰለሞንን አቶ በቀለንና  እና እሸቴን ከኢቲቪ የወሰዳቸው ሲሆን ከበደ ደበሌ ሮቢን ደግሞ በነጻ ጋዜጦች ላይ በሳል ጽሁፎችን ለንባብ በማብቃት ታዋቂ ነበር፡፡  ይህ ስብስብ በጋዜጠኝነት ቢያንስ ከ10 አመት በላይ ልምድ ያካበተ ስለነበር አማረ ለሚፈልገው ስራ የሚመጥኑ ብርቱ ጋዜጠኞች ነበሩ፡፡ አቶ አማረ የድርጅቱ ባለቤት ነኝ ብሎ ይህን እናንተ ስሩ ብሎ ትእዛዝ አይሰጥም፡፡ ቆይታ የተሰኘውን የቃለ-ምልልስ አምድ ጥሩ አድርጎ ይሰራ ነበር፡፡ ርእሰ-አንቀጹም የግሉ ነች፡፡ ርእሰ-አንቀጽ ከመጻፉ በፊት ብዙ ሀሳብ ያወጣል ያወርዳል፡፡ አቶ አማረ በርካታ ሰዎችን ያውቅ ስለነበር ዜና አይቸግረውም፡፡ ቃለ-ምልልስ የሚያደርጋቸውም ሰዎች በቀላሉ የሚገኙ አልነበሩም፡፡ ይህም የተግባቦት ክህሎቱ ምን ያህል የዳበረ እንደነበር የሚያሳየን ነው፡፡

 የአማረ አረጋዊ ርእሰ-አንቀጾች ከያኔ ጀምሮ በቃላት አወቃቀራቸው አንባቢን ለንባብ የሚጋብዙ የራሳቸውን ጣእም የያዙ ነበሩ፡፡ አቶ አማረ፣ ሚድያና ኮሚኒኬሽን ቢሮን ሲከፍት የመጀመሪያው ቢሮው ኮከብ ሬስቶራንት አጠገብ ሲሆን ቤቱም አንድ ለቀቅ ያለ ቪላ ነበር፡፡  ኮሜዲያን ደረጀ ሀይሌ  ከጓደኛው ሀብቴ ጋር በመሆኑ ያኔ ሪፖርተር ላይ በማስታወቂያ ወኪልነትና በጥበብ አምድ አዘጋጅነት ይሰሩ ነበር፡፡ ደረጀ ኮከብ ሬስቶራንት ግድም ስለሚገኘው የሪፖርተር የመጀመሪያው ቢሮ ሲያስረዳ የመስራት ስሜትን የሚያመጣ ድንቅ ቢሮ ነበር ሲል ትዝታውን ለዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጅ ገልጧል፡፡

አቶ አማረ አረጋዊ፣ አንድን ነገር የመፍጠርና እውን የማድረግ ልዩ ክህሎት የታደለ ብቁ ባለሙያ መሆኑን ብዙዎች ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ፡፡ አቶ አብዱ አሊ ሂጅራ ሪፖርተር ሲመሰረት አንስቶ በብዙ ጉዳዮች ከአቶ አማረ ጎን ነበሩ፡፡ በጋዜጣው ላይ ታዋቂ አምደኛ ነበሩ፡፡ በተጨማሪም ምክትል የጋዜጣው አዘጋጅ በመሆን አገልግለዋል፡፡ አቶ አማረን ሲገልጹት ለፕሬስ ነጻነት ወገቡን ታጥቆ ታላቅ ተጋድሎ ያደረገ በሳል ሰው ነው ይሉታል፡፡ ስለ ኢትዮጵያ የነጻ ፕሬስ ታሪክ ስናነሳ አቶ አማረን አለማንሳት አንችልም ሲሉ አቶ አብዱ የባለሙያውን የአማረን ብቃት ድንቅ ነው ሲሉ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ፡፡

አቶ አማረ አረጋዊ ነጻ ፕሬስ   በኢትዮጵያ ማበብ አለበት ብሎ ያምን ስለነበረ ይህ ለውጥ እንዲመጣ አስፈላጊውን ትግል ያደርግ  ነበር፡፡ ጋዜጣዋ 2ኛ አመቷን ባከበረች ጊዜ አሁንም ነጻ ፕሬስ ነጻ ሀሳብ ነጻ መንፈስ በሚል አይረሴ ርእሰ-አንቀጽ ጽፎ ነበር፡፡  ይህ ርእሰ አንቀጽ በተጻፈበት ጊዜ ከሪፖርተር አማርኛው ባሻገር የእንግሊዝኛው ዘ ሪፖርተር እንዲሁም ሪፖርተር መጽሄት መታተም ጀምረው ነበር፡፡ አቶ አማረ በ1989 በጻፈው በዚህ ርእሰ አንቀጹ እንዳለው ለብቻ ተሁኖ ነጻ ፕሬስ ፤ ነጻ ሀሳብ በሀገራችን ማስፈን ከቶ አይቻልም፡፡አቶ አማረ በዚህ ርእሰ አንቀጹ መገናኛ ብዙሀን መጠናከር አለባቸው ብሎ አጽንኦት ሰጥቶ ጽፏል፡፡ በተለይ መንግስት  የኢንፎርሜሽን ፖሊሲ ማውጣት እንዳለበት አቶ አማረ በርእሰ አንቀጹ ያሳስባል፡፡ መንግስት የራሱን ሚድያዎች ብቻ እንደሚጠቅሙት ማሰብ የለበትም፡፡ የግሉ ሚድያም ሊኖረው ስለሚችለው የጎላ ድርሻ መንግስት ማስተዋል አለበት ሲል አቶ አማረ ይጽፋል፡፡

አቶ አማረ በሚመራው ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ከ150000 በላይ ዜና እና ጽሁፎች የተስተናገዱ ሲሆን ሁሉም በሚባል ደረጃ የህዝብ የመረጃ ጥማት ለማርካት የሚሰናዱ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ሰኞ ጥር 12 1989 በፊት ለፊት ገጽ ከወጡት ዜናዎች አንዱ የክልል 14 አቃቤ ህግ ለችግር ተጋልጧል የሚል ነበር፡፡  ሰኞ ነሀሴ 26 1989 በወጣው ጋዜጣ ላይ ደግሞ ሚኒስትሩ ሳይፈቅዱ መረጃ እንዳይሰጥ ታገደ የሚል ዜና መውጣቱ አይዘነጋም፡፡ 

መንግስት ነጻውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ መመሪያ እየጣሰ ነው ተባለ የሚለውም ዜና መንግስትን  ሸንቆጥ የማድረግ ዝንባሌ ይታይበታል፡፡ መረጃ ከተገኘ እና ታማኝ ምንጭ ከኖረ አቶ አማረ ዜና ያደርገዋል፡፡ በተቻለ መጠን ሚዛናዊ ዜና ለማቅረብ ሲተጉ የነበሩት እነ አማረ በአንባቢ ለመከበር የቻሉትና 26 አመት የዘለቁት ትክክለኛነትን ስለሚከተሉ ነው በሚለው ብዙዎች ይስማማሉ፡፡

አቶ አማረ ጋር ተቀጥረው የሚሰሩ ባለሙያዎች በተለይ ኢዲቶሪያል ላይ ያሉት ለሙያው  ክብር የሚሰጡና አቶ አማረ የሚያራምደውን የነጻ ፕሬስ ሀሳብ የሚያስተጋቡ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ጋዜጠኞቹ ለሙያቸው ታማኝ በመሆን በማስረጃ ላይ ተንተርሰው ዜናቸውን ለማቅረብ ይታትራሉ፡፡

ኤሊያስ አረዳ ስለ አቶ አማረ 

ሪፖርተር ጋዜጣ በተመሰረተ በ2 አመቱ በካርቱኒስትነት አማረን የተቀላቀለው ኤሊያስ አረዳ ዘንድሮ ሪፖርተር የገባበት 23ኛ አመትን አክብሯል፡፡ ኤልያስ እነዚያን አመታት ከወርቅ ጋር ያመሳስላቸዋል፡፡ በወርቃማ ዘመን ላይ አቅሜን ያየሁበት ጊዜ ነው ሲልም በትዝታ ወደ ኋላ ይነጉዳል፡፡ገና ከአርት ስኩል ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ሪፖርተርን የተቀላቀለው ኤልያስ አረዳ በጊዜው ስለ ወቅቱ የፖለቲካ ትኩሳት የላቀ ግንዛቤ አልነበረውም፡፡ነገር ግን ከአቶ አማረ የሚሰጠውን ሃሳብ እየተቀበለ ግንዛቤውን ሊያዳብር ቻለ፡፡ ከ10000 በላይ የካርቱን ስእሎችን በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ እንደሰራ የሚናገረው ኤልያስ  ለዚህ ደረጃ ያበቃኝ አቶ አማረ ስለሆነ ልባዊ አክብሮቴን መግለጽ እወዳለሁ ሲል የአቶ አማረን ስም በጥሩ መልኩ ማንሳት ይፈልጋል፡፡

ኤልያስ አረዳ በ800ብር ሪፖርተርን ከተቀላቀለ በኋላ በርካታ የአቶ አማረን ርእሰ-አንቀጾች በማንበብ ጥሩ እና ገላጭ ፤ አስቂኝ ካርቱኖችን ሰርቶ ለአንባቢ / ተመልካች እንካችሁ ብሏል፡፡ኤልያስ አቶ አማረን ሲገልጸው ራሱን አግዝፎ የማይመለከት ፤ ቀርቦ በእርጋታ የሚያስረዳ ቀና ሰው ነው ይለዋል፡፡

‹‹……. አማረ ካርቱን በምሰራበት ጊዜ ስህተት ስሰራ በቁጣ ቃል አይናገረኝም፡፡  ይልቁንም ቀስ ብሎ እንደ ልጅ ያስረዳኛል፡፡ ይህን እንዲህ ብታደርገው እያለ ሀሳብ ይሰጠኛል፡፡››  ሲል ኤልያስ የአቶ አማረን ሰብእና ይገልጸዋል፡፡ አቶ አማረ በምትፈልገው መንገድ ስራ ብሎ ኤልያስን ይለቅቀዋል፡፡ ኤልያስም የተሰጠውን ነጻነት በመጠቀም ደረጃውን የጠበቀ ካርቱን ለማቅረብ ይሞክራል፡፡

አቶ ኢየሱስወርቅ ዛፉ ስለ አቶ አማረ

አቶ ኢየሱስወርቅ ዛፉ የህብረት ኢንሹራንስ መስራች ናቸው፡፡  አቶ አማረን ከ26 አመት በፊት ያውቁታል፡፡ ያኔ ህብረት ኢንሹራንስ የተጀመረበት ሰሞን ነው፡፡ በጊዜውም አቶ አማረ ሪፖርተርን ለመጀመር ደፋ ቀና የሚልበት ተመሳሳይ ጊዜ ነበር፡፡  እና አቶ አማረ ወደ አቶ ኢየሱስወርቅ ዛፉ ቢሮ አቀና

‹‹….. አዲስ ጋዜጣ ልናቋቁም ስለሆነ ህብረት ኢንሹራንስን በእኛ ጋዜጣ ላይ እንዲያስተዋውቁ ፈልጌ ነበር ›› ሲል አቶ አማረ ጥያቄውን ያቀርባል፡፡አቶ ኢየሱስወርቅም አማረን ልብ ብለው ካደመጡት በኋላ ‹‹….. እኔ ከረጅም አመት ቆይታ በኋላ ነው ሀገሬ የገባሁት ፡፡ በአሁኑ ሰአት በሀገሪቱ ለህትመት እየበቁ ያሉት ጋዜጦች በ2 ወገን የተከፈሉ ናቸው፡፡ ወይ ጭልጥ ብለው መንግስትን የሚደግፉ አሊያ ደግሞ በዚያኛው ጽንፍ ይዘው  መንግስትን የሚተቹ ፡፡ አንተ ከእነዚህ እንደ አንዱ አይነት ጋዜጣ ከሆነ የምትጀምረው ምን ዋጋ አለው? አልኩት ›› ይላሉ አቶ ኢየሱስወርቅ ዛፉ 26 አመት ወደ ኋላ ተጉዘው፡፡

አቶ አማረ  አረጋዊም በመጠነኛ ፈገግታ ተሞልቶ ‹‹ …. ከአንደኛው ወገን ሳይፈርጁኝ እድሉን ይስጡኝ፡፡  ምን አይነት ጋዜጣ ልመሰርት እንዳሰብኩ ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡  ለየት ያለ ሚዛናዊ የህትመት ውጤት ላወጣ እንደምችል ላረጋግጥልዎት እችላለሁ›› ሲል አቶ አማረ በሚሰራው ስራ ተማምኖ ተናገረ፡፡

አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ በዚህ መልኩ ከአቶ አማረ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ተዋወቁ፡፡  በአማረ ላይ ታላቅ እምነት አሳድረው የህብረት ኢንሹራንስን ማስታወቂያ ሰጡት፡፡ ዛሬም ህብረት ከሪፖርተር ጋር አብሮ አለ፡፡ አቶ ኢየሱስወርቅ በሂደት አማረን እየቀረቡት ሲመጡ ለፕሬስ ተሟጋች ሆነው አገኙት፡፡ በዚህም ትልቅ ከበሬታ አለኝ ይላሉ፡፡

ዳዊት ታዬ ስለ አቶ አማረ

ጋዜጠኛ ዳዊት ታዬ አቶ ኢየሱስወርቅ ባሉት ሀሳብ ላይ ሙሉ በሙሉ ይስማማል፡፡ አቶ አማረ ከልቡ የነጻው ፕሬስ ተሟጋች ነው፡፡ ዳዊት በአሁኑ ሰአት የሪፖርተር ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ ነው፡፡  አቶ አማረን ሲያውቀው 18 አመታት አልፈዋል፡፡ ዳዊት ካፒታል ጋዜጣ ላይ ይሰራ በነበረ ጊዜ በአንድ ዘገባ ምክንያት ከአቶ አማረ ጋር ትውውቅ እንደነበረው ይናገራል፡፡  የበለጠ አማረ ማነው? የሚለውን የተረዳው ግን ሪፖርተርን ከተቀላቀለ ወዲህ ነበር፡፡ የአማረ መለያው ነጻ ማድረጉ ነው ይላል ዳዊት፡፡  አማረ፣ ራሱን ነጻ አድርጎ ጋዜጠኛውም በነጻ መንፈስ እንዲመራ መንገዱን ይከፍታል ይህም የትክክለኛ የሚድያ ሰው መገለጫ መሆኑን ዳዊት ያሰምርበታል፡፡

ዳዊት ከ1984 ጀምሮ እይታ፣ አእምሮ፣ኢትዮጵያን ጆርናል  በመሳሰሉ ጋዜጦች ላይ በመስራቱ  በጊዜው የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ የነበረበትን ጠንካራ እና ደካማ ጎን ሊያስተውል ችሏል፡፡ ነጻ ሚድያው በርካታ ሁኔታዎች ባልተሟሉበት ሁኔታ  ህትመት ውስጥ መቆየቱ ቢደነቅም  በርካታ ጉድለቶች ነበሩበት፡፡  በተለይ አንድን ዜና በሚዛናዊነት ልኬት መስራት የወቅቱ ጋዜጦች ትልቁ ክፍተት እንደነበር ዳዊት ያስረዳል፡፡ ዳዊት በ1995 አ.ም የዛሬ 18 አመት ገደማ ሪፖርተርን ሲቀላቀል በቀዳሚነት ነጻነት የሚለውን ሀሳብ ከአቶ አማረ ድርጊት ይማር ነበር፡፡

ዳዊት፣ 18 አመት ሪፖርተር ላይ ሲሰራ አገኘሁት የሚለው ትልቅ ነገር ነጻነትን ነው፡፡  አማረ በጋዜጠኛው ስራ ውስጥ እንደ አሳታሚ ወይም እንደባለቤት ጣልቃ አይገባም፡፡  ዳዊት የአቶ አማረን ነጻ የማድረግ ሁኔታ ሲገልጽም እንዲህ ይላል‹‹…… አንድ ሰው በሰራሁት ዜና  ወይም ጽሁፍ ላይ ቅሬታ ቢኖረው ለአቤቱታ አቶ አማረ ጋር ሊሄድ ይችላል፡፡ አቶ አማረም ማስረጃ ከእጃችሁ ላይ አለ ወይ ብሎ ነው በቀዳሚነት የሚጠይቀው ፡፡ ማስረጃ ካለን ሰዎቹን አሰናብቶ የመስራት ሙሉ መብቱን ለእኛ ነው የሚሰጠን፡፡›› ሲል ዳዊት የአማረ የነጻነት ልክ እምን ድረስ እንደሆነ ያስረዳል፡፡

ብዙ ጊዜ አሳታሚዎች እኔ ያልኩት ይሁን በማለታቸው ይታወቃሉ፡፡ አቶ አማረ ግን ጋዜጠኛው ለያዘው እውነት ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ ዳዊት ፣ በማቴሪያሎች የተሟላ እቃ ይዞ የሚሰራ የሚድያ ተቋም ለስኬት እንደሚበቃ እና ቀጣይነት እንደሚኖረው ያምናል፡፡ በአቶ አማረ የተመሰረተው ሪፖርተርም በሰው ሀይል የተደራጀ ሆኖ በመገኘቱ ለዛሬው ስኬቱ መብቃቱን ዳዊት ይናገራል፡፡

አቶ አማረ በ1987 ሪፖርተርን ሲመሰርት ጥሩ የስራ ስርአት ወይም ሲስተም ዘርግቷል፡፡ አማረ ኖረም አልኖረ  ስራዎች ወግና መልኩን ጠብቀው ይከወናሉ፡፡  ቀደም ሲል ሪፖርተር የተጀመረ ሰሞን አቶ አማረ ርእሰ -አንቀጹንና ቆይታ አምዱን ይሰራ ነበር፡፡ ሪፖርተር የተጀመረ ሰሞን አብዛኛዎቹ ቃለ-ምልልሶች የተደረጉት በአቶ አማረ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ከአንባቢ እኩል አቶ አማረ ጋዜጣውን ማኪያቶ እየተጎነጨ ያነባል፡፡ ይህ ነው የስራ ሲስተም ዘርግቶ መገኘት ማለት፡፡

ዳዊት አቶ አማረ ጋዜጣውን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለፕሬስ ወጥሮ መታገሉን ፤ ፕሬሱን ወደ ስቅላት የሚሰዱ አፋኝ ህጎች ሲወጡም ወገቡን ታጥቆ  ሙግት  መግጠሙን የአቶ አማረ ትልቁ ጠንካራ ጎኑ እና ባለውለታ ያሰኘው ነበር፡፡ይላል አቶ አማረ ብዙ ህልሞችን ሰንቆ ሲነሳ፣ሪፖርተር በራሱ ማተሚያ ቤት እንዲታተምና ጋዜጣውም በየቀኑ እንዲወጣ በማለም ነበር፡፡ ይህ ግን አልሆነም፡፡ የነበሩት ቢሮክራሲያዊ አሰራሮችና በአንዳንድ የመንግስት ሃላፊዎች አሻጥርም ህልሙ እንዳይሳካ ተደርጓል፡፡ አቶ አማረ ግን ተስፋ የሚቆርጥ አልነበረም፡፡ አንዱ በር ሲዘጋ ደግሞ በሌላኛው ይሞክራል፡፡  በአሁኑ ሰአት ሮብ እና እሁድ እየወጡ ያሉ ጋዜጦችን የበለጠ ትክክለኛ ጋዜጣ ለማድረግ የሪፖርተር ኤዲቶሪያል እየጣረ ይገኛል፡፡

ራሄል አለሙ ስለ አቶ አማረ

ራሄል አለሙ ፣ ሪፖርተር ጋዜጣ ሲመሰረት ጀምሮ ከነበሩት መካከል  አንዷ ነች፡፡ ያኔ ከሪፖርተር በፊት እርዳታ ማስተባበሪያ ትሰራ የነበረችው ራሄል አቶ አማረ ጋር በጸሀፊነት በ500 ብር ደሞዝ ተቀጠረች፡፡ ያኔ ራሄል ኮከብ ሬስቶራንት ግድም የነበረው የሪፖርተር ቢሮ ውበት ይላበስ ዘንድ ቀለም ሲቀባ ምንም እንኳን ስራዋ ባይሆን  ቢሮው መስህብ ይላበስ ዘንድ አብራ ቀለም ከቀቡት መካከል አንዷ ነበረች፡፡ ራሄል በጸሀፊነት ስትሰራ አንድ የምታውቀው ነገር አቶ አማረ ደግነትን የተላበሰ ፤ ሰብአዊነት ያለው መልካም አለቃ ነበር፡፡ አቶ አማረ ለሰው ችግር የሚደርስ  በጎ ሰው መሆኑን ራሄል ታስታውሳለች፡፡ ‹‹…ሪፖርተር በሚወጣበት ጊዜ አቶ አማረ ከጋዜጠኞቹ ጋር እየሰራ ያድር ነበር፡፡  በተጨማሪም ጋዜጣው አልሸጥ ብሎ ሲመለስ በትእግስት ተሞልቶ ጠንክረን እንድንሰራ ያደርግ ነበር፡፡

አቶ አማረ ሰዎችን ለማገዝ ወደ ኋላ የማይል ሰው ነው፡፡ ሰይፉ ፋንታሁን ሆሊውድ ጋዜጣን ሲጀምር በ1988 ገደማ ርዳታ ያደረገለት አቶ አማረ ነበር፡፡ በጊዜው ለሰይፉ 3000 ብር ለግሶት እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በጊዜው አቶ አማረ ሰይፉን እንዴት እንዳበረታታው አስታውሳለሁ፡፡ ደረጀ እና ሀብቴም በአማረ ይታገዙ ነበር፡፡ ሰው ሳያውቅ ደግሞ የሚረዳቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ አቶ አማረ ለሰራተኞቹ እድገት በመስጠት ይታወቃል፡፡ በጊዜው የሚከፍለውም ደሞዝ ቀላል አልነበረም ›› ስትል ራሄል ትዝታዋን አውግታለች፡፡

ራሄል በጸሀፊነት የስራ መደብ ስራዋን ትጀምር እንጂ በኋላ ላይ በሴልስ ባለሙያነት ሪፖርተርን አገልግላለች፡፡ከ1987-2002 ለ15 አመታት ሪፖርተርን ያገለገችው ራሄል የማርኬቲንጉን ስራ በኃላፊነት  በመስራት የአቅሟን ያህል ሰርታለች፡፡ ራሄል የሎ ፔጅ  ላይ፣ መጽሄቱ ላይ እንግሊዝኛው ላይ ልዩ ልዩ ማስታወቂያዎችን ስታመጣ 10 ከመቶ ኮሚሽን ይከፈላት ነበር፡፡ ትዝ እንደሚላት አቶ አማረ ጋዜጠኞቹ እንዲጠቀሙ የማያደርገው ነገር አልነበረም፡፡ ውጭ ሀገር ሲሄድ ሽቶ ይዞ ለሰራተኞቹ በስጦታ መልክ ያበረክታል፡፡ ራሄል ይህን ሁሉ ስታስታውስ  ሪፖርተር በአቶ አማረ አማካይነት ጥሩ ትዝታ ትቶላት ያለፈ የሙያ ቤት ነው፡፡ ታዲያ ትላለች ራሄል እንደ አቶ አማረ አረጋዊ አይነት በሳል ሰው ኢትዮጵያ ማሞገስ ፤ ማድነቅ አለባት ስትል ራሄል ለአቶ አማረ እና ቤተሰቡ መልካሙን ሁሉ ተመኝታለች፡፡

 አ ፍሪካ ደበበ ስለ አቶ አማረ

ከአቶ አማረ አረጋዊ ጋር የተዋወቅነው በ 1989 ም የሚዲያ እና ኮምዩኒኬሽን ሴንተርን በሰራተኝነት በተቀላቀልኩበት ጊዜ ነበር፡፡ አቶ አማረ ሰራተኞቹ ስራችውን በነፃነት እንዲሰሩ የሚፈቅድ በጣም መልካም አለቃ ነበር፡፡ እኔ አብሬው በምሰራበት ጊዜ አማረ ጠንካራ እና የማይደክመው ሰራተኛ ነበር፡፡ እኛንም እንደሱ ሳይደክመን ረጅም ሰዓት መስራትን አስተምሮናል!! አቶ አማረ ላመነበት ነገር ወደኋላ የማይል ሰው እንደሆነ አብረን በሰራንባችው ጊዜያቶች በገጠሙን ሁኔታዎች ተረድቻለሁ፡፡ አቶ አማረ ትክክለኛ የሚዲያ ሰው የሚያስብለው አንደበተ ርቱእነቱ፣ ሃሳቡን ጠቅለል አድርጎ በፅሁፍ መግለፅ መቻሉ ዋና ዋና ሲሆኑ፤ የሪፖርተር ጋዜጣ ርዕሰ አንቀፅ ይህንኑ ይመሰክራል፡፡

ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ ስለ አቶ አማረ

ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ ፣ አቶ አማረ አረጋዊ ባለፉት 26 አመታት ለኢትዮጵያ ሚድያ ያበረከተውን የጎላ ሚና በጥሩ መነጽር ይመለከተዋል፡፡ ሀገራዊ የሆኑ አጀንዳዎችን  ቀርጾ በማውጣት ፣ ጠንካራ ጋዜጠኞች ብቁ ሆነው ሙያው ላይ እንዲቆዩ በማድረግ  አቶ አማረ የበኩሉን ድርሻ መወጣቱን ረዳት ፕሮፌሰሩ ይናገራል፡፡ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ተቋም ውስጥ መምህር የሆነው  ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ  በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ በርካታ  ተማሪዎች የንጽጽር ጥናት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ያስረዳል፡፡

አቶ አማረ ዜናዎችን በማነፍነፍ  የሚታወቅ፣ ለዜናም የተለየ አይን ያለው መሆኑን በቅርበት የሚያውቁት ሁሉ ይመሰክራሉ፡፡ ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻም  በዚህ ሀሳብ ሙሉ በሙሉ ይስማማል፡፡ በተለይ ደግሞ አቶ አማረ ከውዳሴ የወጡ በሂስ መነጽር የሚመለከቱ  ርእሰ-አንቀጾቹ እጅግ ተወዳጅ ፣ ሳቢ ለመሆን ችለዋል ሲል መምህሩ ለአቶ አማረ አረጋዊ ያለውን ጥልቅ አክብሮት ይገልጻል፡፡

የአቶ አማረ ርእሰ-አንቀጾች በአንድ በኩሉ መንግስት ላይ የሰላ ሂስ ይሰነዝራሉ፡፡ ማህበረሰቡም ራሱ ቆም ብሉ ሀገሩን እንዲያይ እድል ይፈጥራሉ፡፡  የአቶ አማረ የርእሰ-አንቀጽ አጻጻፍ ዘዴ ለንባብ የሚጋብዝ ስለነበር ብዙዎች ደግሞ ሪፖርተር በዛሬው ርእሰ-አንቀጹ ምን አለ? ብለው ጋዜጣውን ከእጃቸው ለማስገባት ይጓጉ ነበር፡፡

ከዚህ ቀደም አንድ የጋዜጣ አንባቢ ስራዬ ብሎ የጋዜጣን ርእሰ-አንቀጽ አያነብም ነበር፡፡  ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ የመንግስት ሚድያዎች ርእሰ-አንቀጾች መንግስትን አወዳሽና የመንግስትን ፖሊሲ ትክክለኛነት የሚሰብኩ ስለነበሩ ነው፡፡ አቶ አማረ ግን  ለጽሁፎቹ ስነ-ጽሁፋዊ ለዛ እያላበሰ  ርእሰ-አንቀጹ ከቀን ወደ ቀን እየተወደደ እንዲሄድ አድርጓል፡፡

ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ የአቶ አማረ ርእሰ-አንቀጾች ለተማሪዎች ማስተማሪያ መዋላቸውን   ሲገልጽም ‹‹……  አብዛኛውን ጊዜ ወደ ክፍል ስገባ  የሪፖርተርን ርእሰ -አንቀጾች በመያዝ ተማሪዎች እውቀት እንዲቀስሙ አደርጋለሁ፡፡  እነዚህ ርእሰ-አንቀጾች  ጠያቂ መሆናቸውን የአጻጻፍ ለዛቸው የተዋዛ መሆኑን ለተማሪዎቼ እነግራቸዋለሁ፡፡ ››በማለት ረዳት ፕሮፌሰሩ ርእሰ አንቀጾቹ ትልቅ አብዮት መፍጠራቸውን ይናገራል፡፡ አቶ አማረ በአንድ ወቅት የሰላሌ ቆንጆ በሚል ርእስ የፕሬስ ነጻነትን አስመልክቶ የጻፈው ርእሰ-አንቀጽ ከብዙዎች አእምሮ የሚጠፋ አልነበረም፡፡

የአቶ  አማረ ርእሰ -አንቀጽ ጽሁፎች ላይ  ተጨማሪ ሀሳቦች

አቶ አማረ ርእሰ-አንቀጽ ሲጽፍ  ቀጥተኛ ነው፡፡ አብረውት የሰሩት እና በአርታኢነት የሚታወቁት  አማረ የርእሰ- አንቀጽ ሀሳቦችን በጽሁፍ ሲያሰፍር በቀጭን ገመድ ላይ ይሄዳል ይሉታል፡፡ የጀመራትን ሀሳብ መልክ አሲዞ ይቀጥላል እንጂ እዚያ እዚህ አይረግጥም፡፡ የሚፈልገውን ጉዳይ ወዲያው ይገልጻል፡፡ አንባቢን ዙሪያ ጥምጥም አያስኬድም፡፡ ታዲያ የአቶ አማረ ርእሰ-አንቀጾች ቀለል ብለው በማይከብዱ ቃላት ቢገለጹም ይዘታቸው ግን ከባድ እና ታላቅ ርእሰ‹ ጉዳዮች ናቸው፡፡  ስለሆነም አቶ አማረ ከበድ የሚል ጉዳይን በቀላል ቋንቋ መግለጽ የሚችል ሰው መሆኑን እዚህ ጋር መደምደም ይቻላል፡፡ አቶ አማረ ጥሩ የንባብ ክህሎትያለው ስለነበርም ርእሰ-ጉዳይ አይቸግረውም፡፡  አንዳንዴ ለርእሰ-አንቀጽ የሚሆኑ ሀሳቦችን  የማይጽፍ ከሆነ በቃሉ እየነገረ ያጽፋል፡፡ ጽሁፉ ሲያልቅ አንድም መዛባት አይኖርም፡፡ አእምሮው ላይ ጽሁፉን አጠናቅቆ ስለሚገኝ ለሚጽፈው ሰው ስራው ቀላል ይሆንለታል፡፡

የካርቱን ሀሳብን በተመለከተ አቶ አማረ ትልቅ ሚና ነበረው፡፡ ብዙዎቹን የካርቱን ሀሳቦች አማረ ያመነጫል፡፡ ካርቱኒስቱ ስኬቹን ያቀርባል፡፡ አማረ ሀሳብ ያክልበታል፡፡ ታትሞ ሲወጣ የማዝናናት ፤ ነገርን እያዋዙ የመንገር አቅም  ያላቸው ርእሰ አንቀጽና ካርቱን አንባቢ ዘንድ ይደርሳሉ፡፡  ነገርን አዋዝቶ የመግለጽ ልዩ ክህሎትን  የተላበሰው አቶ አማረ ይህ ባህሪው በብዙዎች ይወደድለታል፡፡

አቶ መላኩ ደምሴ ስለ አቶ አማረ

አቶ መላኩ ደምሴ  በሚድያ ስራ ከ 30 አመት በላይ የዘለቀ ነው፡፡  በአሁኑ ሰአትም የሪፖርተር ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር ሲሆን  አቶ አማረ የፕሬስ ስራ በሀገራችን እድገት እንዲያሳይ በህይወቱ ሳይቀር ዋጋ የከፈለ  ባለውለታ ነው ይለዋል፡፡  ላለፉት 20 አመታት በሪፖርተር ላይ ያገለገለው አቶ መላኩ፣  አቶ አማረ ከመንግስት የስራ ሃላፊነት ላይ ተነስቶ ነጻ ፕሬስ ብሎ ጠቃሚ ሀሳብ ማመንጨቱ ራሱ ድንቅ ይለኛል ይላል ፡፡

አቶ አማረ አዲስ ነገር መፍጠር ይቻላል የሚል የጸና እምነት ያለው ሲሆን  በተለይ ኢትዮጵያ ሀገራችን የ3000 ዘመን ታሪክ ባለቤት የሆነች ታላቅ ሀገር መሆኗ ያኮራዋል፡፡  ለፈረንጆቹ አዲስ የሆኑ በአክሱም ስልጣኔ ጊዜ የተሰራባቸው ናቸው፡፡ ዛሬ በአዲስ  አስተሳሰብ ዳግም በስልጣኔ መገስገስ አለብን ብሎ  የሚያምነው አቶ አማረ ቴክኖሎጂ ወደ ስልጣኔ የሚያራምድ አንዱ መንገድ እንደሆነ ያስባል፡፡

አቶ መላኩ እዚህ ጋር የአማረን የቴክኖሎጂ ፍቅር ያደንቃል፡፡  ትናንት ጋዜጣ ላይ የነበረው ሪፖርተር  ዛሬ ደግሞ በዲጂታል ሚድያ 2 ሚሊዮን አንባቢያንን ለማፍራት ችሏል፡፡  ይህ አንዱ የአማረ እርካታ ነው፡፡

 አቶ መላኩ ከአቶ አማረ ምን ነገር ተማርክ ተብሎ ሲጠየቅ  ሚድያን ከልብና የእውነት  መውደድ ሲል ምላሽ ይሰጣል፡፡  አቶ አማረ ብዙ ጊዜ አብረውት የሚሰሩ ጋዜጠኞችን ሰብሰብ አድርጎ ‹‹….. አንድን ዜና ጥሩ አድርጋችሁ መስራት ከፈለጋችሁ የምትጠይቁትን ሰው ላብ ላብ እስከሚለው ድረስ ሀሳቡን ውሰዱ›› ይላቸው እንደነበር አቶ መላኩ ያስታውሳል፡፡

ከዚህ በኋላ  በአቶ አማረ አረጋዊ ላይ የስንዱ አበበን የታምራት ሀይሉን እና የደመቀ ከበደን አስተያየት እንዳለ እናቀርባለን 

ታሪክን መሻማት አለብሽ-ከስንዱ አበበ 

የሪፖርተር ጋዜጣ ባለቤት አቶ አማረ አረጋዊ መጀመሪያ ጋዜጠኝነትን ስንማር ካስተማሩኝ ሰዎች አንዱ ነው ።

ከሱ ትምህርት የሸመትኩት ቁምነገር ዋነኛው :- ” ጋዜጠኛ ታሪክን መሻማት አለበት ።  ዜጎች ታሪክ ሲሰሩ በቦታው ቀድሞ በመድረስ የባለታሪኩን ገድል በማውሳት ለመጪው ትውልድ የማቀበል ሀላፊነትን መወጣት አለበት ” ብሎ ያባነነኝ ባለውለታዬ ነው ። ለዚህ በረከቱ ታላቅ ምስጋና ና አክብሮት አለኝ ። ከብዙ አመታት በኋላም የጋዜጣው ባልደረባ ለመሆን በአንድ የስልክ ጥሪ ነው የተቀጠርኩት ። ለዚህም ትልቅ አክብሮት አለኝ ። አትሌት ፋጡማ ሮባ ማራቶን አሸንፋ ስትደምቅ ታሪክን ልሻማ ( በተመከርኩት መሰረት ) ቃለመጠይቅ አረኩላት ።

ፋጡማ ግዙፍ እንደ ጭላሎ የዋህ እንደ እርግብ ! ብዬ ዘገብኩ ።( ያኔ ሌላ ጋዜጣ ውስጥ ነበር ተቀጥሬ እምሰራው ።)የሪፖርተሩ ጋዜጠኛ ምንም ዕውቅና ለኔም ሆነ ለዘገብኩበት ጋዜጣ እውቅና ሳይሰጥ ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ የራሱ ዘገባ አስመስሎ አተመው ። ተበሳጭቼ አቶ አማረ ጋ ደውዬ ጮህኩ ። አጣርቶ እርምጃ ወሰደ ። ደግሞ ከየፈኝ ።እሱ ጋ ስሰራ በነበር ዘመን ” ስሟ ይበቃኛል ። አትንኳት ” እያለ ማሞላቀቁን አልክድም ።

ትዝታዬ ! 17

ሚዲያና ኮምኒኬሽን ሴንተር ( MCC ) አማርኛና እግሊዝኛ ጋዜጦችና ረፖርተር መፅሔት ዝግጅት ክፍል ሳሪስ መንገድ ካዲስኮ አካባቢ የተንጣለለ ግቢ ነው ። ( ድሮ ናይት ክለብ ነበር ሲሉ ሰምቻለሁ ) ለስራ ምቹ የሆነ ፤  በጣም ተግባብተው በደስታ እሚሰሩ ፣ አብሮ በመክረም እዛው አድገው ጥሩ ቦታ የደረሱ ያሉበት ፤ ሻይ ና ቡና በነፃ ለሰራተኞች እሚያቀርብ ዘመናዊ ቢሮ ነው  ።  አዳኑዬ እምታፈላልን ቡና ዛሬም ውል ይለኛል ።

አቶ አማረ አረጋዊ በጣም ቀልጣፋ ፣ ነቄ ፣ የሰዎችን የግል ችሎታ እሚገነዘብ ዘና ያለ አለቃ ነው ። ሳቅ ጨዋታም ይወዳል ። ክሽ ሲልበትም ይጋብዘናል ። ቢሮው በተጠና መልኩ የተደራጀ ነው ። ብዙ ልምድ ያላቸውንም ፣ ወጣቱንም ፣ ገና ጀማሪውንም ጋዜጠኛ አሰባጥሮን ያሰማራናል ።

ሪፖርተር ቢሮ እማይመጣ ሰው የለም ። ፖለቲከኞች ፣ ጋዜጠኞች ፣ አቤቱታ አቅራቢዎች ፣ ምስጢር አቀባባዮች — ይንጋጋሉ ። አርብ አርብ ማምሻውን ግቢውን እየተሽከረከረ ሀሳብ ሲያመነዥግ ” ርዕስ አንቀፅ እያማጠ ነው ” እንላለን ።  ርዕስ አንቀፅ የግል እርስቱ ነች ። ጋሽ መስፍን ሀብተማርያምም ከቤተመፅሀፍቱ የጀመረውን ፅሁፍ አቋርጦ ግቢውን እየተሽከረከረ እሚያምጥ ሁለተኛው ሰው ነው ። ግቢውን መሽከርከር !

የአማርኛው ጋዜጣ ክፍል ሀሙስና አርብ ስራ ይበዛበታል ። ብዙ አርቦችን አድረን ጭምር ነው እምንሰራው ። ለምሽቱ ስራ በየተራ ኤዲተር እየተደረግን ለከባድ ሃላፊነት እንመደባለን ። ጋዜጣው ወደማተሚያ ቤት ከመላኩ በፊት በተቀመጠው መመሪያ ጥንፍፍ ብሎ የመሰራቱ ነገር በሀላፊነት ለተመደበው ተረኛ ያስጨንቃል ።

 ከቢሮ ውጭ ብዙ ፀሀፊዎችን እሚያስተናግድ ቢሮ ነው ። በተለይ እኔ በነበርኩ ዘመን እስራኤል ዘካሪያስ የተባሉ ፀሀፊ እጅግ ገራሚ ነበሩ ። የሳቸው ፅሁፍ በኮምፒውተር ተፅፎ ለእርማት ስንሻማ አስታውሳለሁ ። ብሄራዊ ባንኩንና ኤኮኖሚያዊ ነገሮችን ይበልታሉ ።

አሁንም ይፅፉ ይሆን ? ( አድናቂያቸው ነኝ )

ሪፖርተር ሳልቀጠር በፊትም ፅሁፎቼ ታትመውልኛል ። በተለይ የቅዱስ ላሊበላ አፎሮ አይገባ መስቀል የተሰረቀ ግዜ  በራሴ ወጪ ቦታው ድረስ ተገኝቼ የሰራሁትን ዘገባ ስለታተመልኝ ( ምናልባትም መስቀሉን ለማስመለስ ትልቅ ጫና ፈጥሯል ) ለቢሮውም ለመምህሬ አቶ አማረም ትልቅ ክብር ነበረኝ ። በስራ ጉዳይ ግጭት መፈጠሩ አይቀሬ ነው ። አንድ ቀን የቅርብ አለቃዬ ከበደ ደበሌ ሮቢ ” የመስክ ስራ አሰማራ ተብያለሁ ተዘጋጂ ” አለኝ

‘ከማን ጋር’ ? አልኩ

” ጋዜጠኛ አይደለሽም እንዴ ? ብቻሽን ፣ አንችም መታሰቢያ ተሾመም የተለያየ ቦታ ተመድባችኋል የትራንስፖርትና የቀን ቀለብ ተሰፍሮላችኋል ” አለ

‘ለብቻዬማ መስክ አልሄድም’ ። ስለው ብልጭ አለበትና ተንደርድሮ ለአማረ ሪፖርት አደረገ ።

አቶ አማረ ሁለታችንንም ጠራና ” መስክ አልወጣም  ብለሻል ? ” አለኝ ።

‘ብቻዬን-  አዎ አልወጣም ‘  ።

“‘ለምን ?”

‘ይደፍሩኛል ! ‘ አልኩት ።

ነገር አለሙን ትቶት በሳቅ ተንፈራፈረ ።

” ፖሊስ ያለበት ቦታ ነው እምትሄጅው ” ብሎ ተቆጣ  ከብዬ

‘ ፖሊስ ነው እምፈራው ! ‘ አልኩ ።

አቶ አማረ ‘ በቃ – በቃ ሴቶቹን አትላኩ ። እ ራሳችሁ ተሰማሩ ‘ ብሎ አሰናበተን ።

ከዛሬ ይልቅ ነገን አርቆ የሚያይ –  የታምራት ሀይሉ ሀሳብ 

‹አቶ አማረ በሀገራችን የግል ሚዲያ ዘርፍ ላይ ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ አማራጭ የሚዲያ ተቋም መስርቶ ለሚዲያ አንዱስትሪው የራሱን አስተዋፅኦ ያበረከተ ባለሙያ ነው፡፡ ማንም ለመረጃ ቅርብ መሆን የሚፈልግ ሰው ዘወትር እሑድ የሚወጣውን ሪፖርተር ጋዜጣ የማገላበጥ ልምድ ማዳበሩ እሙን ነው፤ ላለፉት 26 ዓመታት ሪፖርተር እንደ ተቋምም ሆነ አቶ አማረ በግሉ በፕሬስ ስራ ላይ ቀላል የማይባሉ የሙያ ውጣ ውረዶችንና መስዋዕትነቶችን ከፍሏል፤ በተለይም የግሉን ፕሬስ ወደ ስቅላት ለመውሰድ የህግ ማዕቀፍ ሲዘጋጅ አቶ አማረ መገናኛ ብዙሃን አይነተኛ የፖሊሲ ምንጭ የመሆን አቅማቸውን የሚያመላክቱ በር ከፋች ርዕሰ አንቀፆችን በመፃፍ ለመረጃ ነፃነት ያለውን ቀናኢነት አሳይቷል፤ ከዚህ በተጨማሪ ሚዲያው ራሱን በራሱ የማረም ስርዓት እንዲመሰርትም ከአራት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት እንዲመሰረት ጊዜውን፤ እውቀቱንና ገንዘቡን በመመደብና በመምራት መሠረት የጣለ ሰው ነው፤ ከምንም ነገር  በላይ ሀገርና ህዝብን የማስቀደም ጋዜጠኝነትን የሚሰብከው አቶ አማረ ከዛሬ ይልቅ ነገን አርቆ የሚመለከት የሚዲያ መሪ ነው

መታሰቢያ ተሾመ ስለ አቶ አማረ አረጋዊ

መታሰቢያ ተሾመ በአሁኑ ሰአት መኖሪያዋን በአሜሪካን ሀገር ያደረገች ሲሆን ከሪፖርተር የቀድሞ ጋዜጠኞች መካከል አንዷ ናት፡፡መታሰቢያ ገና የጋዜጠኝነት ትምህርቷን  በመማር ላይ ሳለች ነበር  አንድ ዜና ሰርታ ሪፖርተርን  ያወቀችው፡፡ ዜናውን ትጽፍ ዘንድ ያበረታታትም እስክንድር መርሀጽድቅ ነበር፡፡ እናም መታሰቢያ በ1989 በኮሞሮስ ደርሶ ስለነበረው የአውሮፕላን አደጋ ነበር የዜናዋ ትኩረት፡፡ በዚህ ሰአት ነበር የሪፖርተር ጋዜጣ ባለቤት የሆነውን አቶ አማረን የተዋወቀችው፡፡ አቶ አማረ ያመጣችው ዜና በጥሩ መልኩ የተሰራ ስለነበር ያልጠበቀችው ገንዘብ እንዲከፈላት አደረገ፡፡ ይህ መታሰቢያን አበረታት፡፡በጊዜው የሬድዮ ጋዜጠኝነት ታጠና የነበረችው መታሰቢያ ዜናውን ለመስራት እንጂ ለክፍያው ብላ አልነበረም፡፡ ቀጥላ ትምህርቷን ስትጨርስ ሪፖርተርን ተቀላቀለች፡፡ መሰረት ለገሰ እና መታሰቢያ ተሾመ በ1990  የሪፖርተር ባልደረቦች ነበሩ፡፡ መታሰቢያ አቶ አማረን ስትገልጸው ደግና እንደ አባት የሚታይ መልካም ሰው ነበር ትለዋለች፡፡ መታሰቢያ ሪፖርተርን ለቅቃ ወደ እለታዊ አዲስ ስትሄድ ምንም ቅር ቢላት መሄዱዋ ግድ ስለነበር ወደ እለታዊ አዲስ አቀናች፡፡  እለታዊ ተዘግቶ ተመልሳ ስትመጣ ግን አቶ አማረ በደስታ ነበር የተቀበላት፡፡ መታሰቢያ የአቶ አማረን በጎ ነገሮች ስታነሳ ሰውን ይሰማል፤ ልጅ ነው ብሎ አይንቅም ስትል በጊዜው አድናቆቷ ከፍ ያለ እንደነበር ትናገራለች፡፡ አማረ ጠያቂ ፍጡር ነው ትላለች፡፡ መልሶም ደግሞ ይህን እንዴት አድርገሽ ሰራሽው እያለ ይፈትናል፡፡ እንዲህ አይነት መሪ ይከበራል ትላለች መታሰቢያ፡፡ እኔ ያልኩት ይሁን ብሎ የማይጫን አለቃ ነው አማረ ስትል መታሰቢያ ትዝታዋን አውግታለች፡፡

ደመቀ  ከበደ ስለ አማረ 

አማረ አረጋዊን በቅርበት የማውቀው ከዩኒቨርሲቲ ተመርቄ ስራ ስጀምር ነው። የሪፖርተር ጋዜጣ የባህልና ኪነ- ጥበብ አምድ ባልደረባ ሆኘ ነው የተቀላቀልኩት። ሪፖርተር በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች በመፅሄትና በጋዜጣ፣ እንዲሁም በኦንላይን የሚቀርብ ዘመናዊ አደረጃጀት ያለው ተቋም ነው። ዩኒቨርሲቲ ጋዜጠኝነትን ስማር እንደነበረው ዓይነት ታላላቅ የሚዲያ ተቋማት ያላቸውን ቅርፅና አደረጃጀት ይዞ ማግኘቴ አስገርሞኝ ነበር። በወቅቱ ምንም እንኳን ዋና ስራ አስኪያጅ በመሆኑ የቅርብ አለቃዬ ባይሆንም እያንዳንዱን የተሰሩ ዘገባዎች በጥልቀት እያነበበ አስተያየት ይሰጥ ስለነበር እኔንም ያበረታታኝ ነበር። ይህ ተግባሩ ለሁሉም ጋዜጠኛ የሚያደርገው በመሆኑ ጠንካራ ዘገባዎች እንዲዘጋጁ ምክንያት ነበር። እርሱ ራሱም ዜናም ሆነ መጣጥፎች ይሰራ ነበር። ጋዜጠኞች ክስ ሲያጋጥመን ፍርድ ቤት ድረስ ሄዶ ይከራከር እንደነበር አውቃለሁ።

አማረ ጥሩ የሚዲያ መሪ ነው። ድክመትህን እያረመ የሚያጎለምስ እንጅ የሚያሸማቅቅ አለመሆኑ፣ እንደ ዋና አለቃና ባለቤት ሳይሆን በቅርበት እየሰራ መምራቱ፣ የሚሰራን በፋይናንስም እንዲጠቀም የሚያደርግ አሰራር በመዘርጋቱ ብሎም ለረጂም ጊዜ በጠንካራ አደረጃጀት የሚመራ ተቋም ፈጥሮ እስካሁን ለብዙ ባለሙያዎች መፍሪያ ተቋም ለኢትዮጵያ ሚዲያ ኢንዱስትሪ ማበርከቱ ትልቅ አስተዋፅኦው ነው።

ተፎካካሪ እንጂ ጠላቶች አይደሉም

አቶ አማረ ከዛሬ 18 አመት በፊት በግንቦት 1995 ታትሞ ለወጣው ኢንፎቴይንመንት መጽሄት  እንዳለው ከስራ ሃላፊነቱ የወጣው  ባለመስማማት እንደሆነ ይናገራል፡፡  አቶ አማረ ያኔ እንደገለጸው  የኢትዮጵያ የፖለቲካ  ችግር አለመስማማት ማለት በአረዳዱ  እንደጥላቻ ተደርጎ ስለሚወሰድ ይህም ትክክል እንዳልሆነ ያብራራል፡፡

አቶ አማረ በ1995 በሰጠው ቃለ-ምልልስ እንዲህ ብሎ ነበር ‹‹……. በእኔ አመለካከት  ተቃዋሚ አመለካከት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ሆኑ ግለሰቦች  ተፎካካሪ እንጂ ጠላቶች አይደሉም›› ብሎ ነበር፡፡ አቶ አማረ ከዚህ ጋር በተያያዘ ሀሳቡን ሲያስቀምጥ አንድን ነገር ሊተቸው ይችላል እንጂ አይጠላውም፡፡ መጥላት የሚባል ነገር ከአማረ ጋር እንደማይሄድ ራሱ ተናግሯል፡፡

አቶ አማረ እንደሚያምነው ለዴሞክራሲ ፣ ለቢዝነስ ለኢንፎርምሽን ለሁሉም ነገር ዋስትና የሚኖረው  የግል ሚድያ ሲስፋፋ ነው፡፡  በአማረ ቅኝት በመንግስት ሚድያ ብቻ የሚመጣ መፍትሄ የለም፡፡ አቶ አማረ ይህን ሁኔታ ሲያስረዳ  የአለምን ሁኔታ  ጠቅሶ ነው፡፡  በአሁኑ ሰአት በአለም ላይ መንግስት ከሚድያው እየወጣ  የግል ሚድያው እያደገ እንዳለ የምናየው ሀቅ ነው፡፡

አቶ አማረ ነጻው ፕሬስ ላይ በዚህ መልኩ ሲታገል አንድ ወቅት የግድያ ሙከራ ተደርጎበት ለጥቂት ከሞት ተርፏል፡፡  7 ኮንቴነር ሙሉ የማተሚያ ማሽን ለማስገባት ቅድመ-ሁኔታዎችን አሟልቶ  ሊጀምር ሲል እንዲስተጓጎል ተደርጎበታል፡፡  አማረ እንደሚለው ሙሰኛውን ስታጋልጠው ይጠላሀል፡፡  አብረኸው የምትሰራ ከሆነ ደግሞ ይወድሀል፡፡ ቢሆንም ግን በሁሉም ሁኔታዎች ውስጥ አልፈን ሳይሞቀን ሳይበርደን  ሚድያውን ወደ አንድ የእድገት ደረጃ ከፍ ለማድረግ ጠንክረን እየሰራን ነው ይላል፡፡

በአሁኑ ሰአት የመገናኛ ብዙሀን ካውንስልን በመስራችነትና በመሪነት እያገለገለ የሚገኘው አቶ አማረ  በተለይ የስነ-ምግባር ደንብ ማውጣት ላይ አጽንኦት ይሰጣል፡፡ በአቶ አማረ ምልከታ የሚድያን የስነ-ምግባር ደንብ  መቆጣጠር ያለበት ራሱ ሚድያው እንጂ መንግስት መሆን የለበትም፡፡

 አቶ አማረ በኢትዮጵያዊነቱ አንድም ድርድር የማያውቅ ቆራጥ ሀገር ወዳድ መሆኑን ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡  የአቶ አማረ ቤተሰቦች ከዶጋሊ ጀምሮ  በ1928ቱ ጦርነት ሀገርን ከጠላት ለማዳን ብዙ ተጋድሎ የፈጸሙ ነበሩ፡፡  የአቶ አማረ እናት  የወይዘሮ ዘነበች ገብረማሪያም ሁለት ወንድሞች  መስዋእት የሆኑት ጣሊያንን በመዋጋት ነበር፡፡ አድዋም ላይ ቢሆን የአቶ አማረ አያቶች    መስዋእትነት በመክፈል የሀገራቸውን ነጻነት አስከብረዋል፡፡

ከልጅነቱ ጀምሮ ስለ እናት ሀገሩ ፍቅር እየሰማ ያደገው አቶ አማረ ዊንጌት ሲመጣ ደግሞ  ከልዩ ልዩ ጠቅላይ ግዛቶች ከመጡ ልጆች ጋር ሲገናኝ ኢትዮጵያን አወቃት፡፡ ወደዳትም፡፡  ገና የ16 አመት ታዳጊ ሳለ የጀነራል ዊንጌት ተማሪ ቤት ቆይታውን ሲያጠናቅቅ  የጻፈውን ጽሁፍ እንዳየነው  ብላቴናው በልጅነት እድሜው  የኢትዮጵያ ፍቅር አድሮበት ነበር፡፡

 አቶ አማረ ለሀገር የታገሉ ኢትዮጵያውያን ታሪክ ይመስጠዋል፡፡  የዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጅ በታህሳስ 2010 የጸሀፌ-ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድን ግለ-ታሪክ በዘጋቢ ፊልም ያወጣ ጊዜ  ለአቶ አማረ የዶክመንሪውን ስራ አሳየው፡፡  አቶ አማረ የጸሀፌ-ትእዛዝ አክሊሉ ስም ገና ሲነሳ በታላቅ ተመስጦ ውስጥ ገብቶ ኢትዮጵያ እነ አክሊሉን የመሰሉ በምንም የማይተኩ ዲፕሎማቶች ነበሯት ሲል  ለባለውለታው አክሊሉ ያለውን ፍቅርና አክብሮት ገልጾ ነበር፡፡ አቶ

አማረ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን በመምሪያ ሀላፊነት ሲመራ  36 አመቱ ነበር፡፡ ሪፖርተርን ሲመሰርት ደግሞ 40፡፡

‹‹…. የስራ ሃላፊ ሆነህ እነዚህን ሁሉ ለውጦች ስታመጣ  ገና 40 አመት ሳይሞላህ ነበር፡፡  በወጣትነቴ ብዙ ሰርቻለሁ ብለህ ታስባለህ ? ›› የሚል ጥያቄ ከዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጅ ለአቶ አማረ ተነስቶ ነበር፡፡

አቶ አማረ ሲመልስም‹‹….. የፌስቡክ መስራች በ21 አመቱ ነው ማህበራዊ ትስስር ገጽን የፈጠረው ፡፡ እነ ስቲቭ ጆብስ  ቢልጌትስ እነዚያን ታላላቅ ድንቅ ራእዮች እውን ያደረጉት ከ40 አመት በጣም ባነሰ እድሜ ነው፡፡  እኔ ደግሞ ከእነርሱ አንጻር  እድሜዬ ትልቅ ከሆነ በኋላ ነው የጀመርኩት፡፡›› በማለት አቶ አማረ ምላሽ ሰጥቶ ነበር፡፡

አቶ አማረ አረጋዊ በሚድያው ዘርፍ ላበረከተው አስተዋጽኦ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ምክር ቤትና ዋቤ የኣሳታሚዎች ማህበር በ2009 እውቅና ሰጥተውታል፡፡ በዚህ የእውቅና ስነ-ስርአትም የወቅቱ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ክቡር ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ለአቶ አማረ የእውቅና ስጦታውን  አበርክተው ነበር፡፡ በመቀጠልም በ2011የበጎ ሰው የሚድያ ዘርፍ ተሸላሚ ለመሆን ችሎአል፡፡አቶ አማረ ባለትዳር ሲሆን የ4 ልጆች አባትም ነው፡፡

መዝጊያ

የአቶ አማረ ታሪክ መሳጭ ነው፡፡ ብዙ የለፋ ነው፡፡ ታሪኩ ግን በዝርዝር አይታወቅም፡፡ ኢትዮጵያን ይወዳል፡፡ የዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጅ አቶ አማረን ሲያውቀው 23 አመት ሞላው፡፡ በ1990 የዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጅ ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ለ 7 ወር የበጎ ፍቃድ አገልጋይ  ሆኖ በሚድያ ስራ ላይ ሰርቷል፡፡ እናም አቶ አማረን በቅርበት የማወቅ እድሉን ገና በልጅነት ያገኘ ነበር፡፡ እና አቶ አማረ የእውነትም ለወጣት የሚመች፤ ሞራል ገንቢ ነው፡፡ የገባው ነቄ የሚሉት ቀና ሰው ነው፡፡ በአንድ በኩል ደግሞ ፈታኝ በሆነው የሚድያ ስራ ውስጥ ይታገላል፡፡ ይሮጣል፡፡ ግን ማን አወቀለት? አማረን በደንብ የሚያውቀው ምን ያህል ሰው ነው? ለሀገር የለፉ እየተዘነጉ ፤ ሀገር የሚያጠፉ ታዋቂ በሆኑበት ሀገር ስለ አማረ ትውልድ  በወጉ ማወቅ አለበት፡፡ ይህ ሰው ሚድያን ከእነ ሙሉ ክብሯ ያውቃታል፡፡ የተካነ ነው፡፡ ፍጹም ነው ብለን ለማሞገስ ሳይሆን አንድ ያልተዘመረለት ስላገኘን ለአዲሱ ትውልድ ባለ ታሪክ  ልናቀብል ፈልገን ነው፡፡ አማረ አረጋዊ  ወልደኪዳን በሳል የሚድያ ሰው ነው፡፡ የዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች 13 ሰዎችን ቃለ-መጠይቅ በማድረግ ራሱን አቶ አማረን በማነጋገር በርካታ የሪፖርተር ቅጂዎችን በማጥናት ስለ አቶ አማረ ይህን 5600 ቃላት የፈጀ ግለ ታሪክ ስንሰራ ታላቅ ርካታ ይሰማናል፡፡ ለአቶ አማረ መልካሙን ተመኘን ፡፡ / የዚህ ጽሁፍ ሙሉ የጥናት የቃለ-መጠይቅ እና የአርትኦቱ ስራ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የተከናወነ ሲሆን ዛሬ ሀምሌ 28 2013 ዊኪፒዲያ ላይ ወጣ፡፡ ይህ ጽሁፍ አስፈላጊው ማሻሻያ እየተደረገበት በየጊዜው ይወጣል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *