ትዕግስት አለማየሁ ጊዮን

ትዕግስት አለማየሁ ጊዮን

ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በፊልም ፤ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እናስተዋውቃለን፡፡ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ5 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ከቴአትር ዘርፍ ታሪኳ የሚቀርብላት ሰው ትዕግስት አለማየሁ ጊዮን ናት፡፡

ትውልድና ልጅነት

ትዕግስት አለማዬሁ ጊዬን ፣ የጤና መኮንን ከነበሩት አባቷ አቶ አለማየሁ ጊዮን እና የግብርና ቢሮ ሰራተኛ ከሆኑት እናቷ ወ/ሮ ያለምዘርፍ ጎንደር በቻግኒ ከተማ መጋቢት 16 1979 ተወለደች፡፡ ለቤተሰቦቿ 5ኛ ልጅ ስትሆን አንድ እህት እና ስድስት ወንድሞችም አሏት፡፡የልጅነት ጊዜዋን በወላጆቿ የስራ ሁኔታ ምክንያት በተለያዩ የመተከል እና አዊ አካባቢዎች አሳልፋለች፡፡ ትምህርት ቤት ከመግባቷ በፊት ማንዱራ እና ፓዌ የተባሉ ከተሞች ውስጥ ከሳለፈች በኋላ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን መንታ ውሃ አንደኛ ደረጃ እና ቻግኒ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተከታትላለች፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በዳንግላ ከተማ በሚገኙት መንገሻ ጀንበሬ እንዲሁም ዳንግላ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ እና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች ተከታትላለች ፡፡

የዩኒቨርሲቲ ቆይታ

የ”ፕሪፓራቶሪ” ትምህርቷን አጠናቃ የዩንቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ከተፈተነች በኋላም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ትምህርት ክፍልን ተቀላቅላ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ተቀብላለች፡፡ በዚህ ወቅት የመመረቂያ ወረቀቷን የሰራችው በሜጀር ጀነራል ደጀኔ መሸሻ ህይወት ላይ ነበር፡፡ ትእግስት በነበራት የኪነ-ጥበብ ልዩ ፍላጎት የተነሳ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ቤት የማታውን መርሃ-ግብር ተቀላቅላ ተጨማሪ ዲግሪ ከቴአትር ጥበባት ትምህርት ቤት ለማግኘት በቅታለች፡፡

የቴአትር ትምህርቷን በማታው መርሃ-ግብር በመማር ላይ እያለችም የማስተርስ ዲግሪዋን በቀኑ መርሃግብር በኢትዮጵያ ስነ-ጽሁፍ እና ፎክሎር ዘርፍ ተምራ በአንድ ቀን ሁለተኛ ዲግሪዋን እና የማስተርስ ዲግሪዋን በመመረቅ አርአያነቷን አሳይታለች፡፡ በዚህ ጊዜም ከፍተኛ የገንዘብ ችግር ይገጥማት ስለነበር ቤት ለቤት ህጻናት ልጆችን በማስጠናት ገቢ ታገኝ እንደነበር ትናገራለች፡፡ ይህም የሚያሳየን አንድ ሰው ካለመበት ግብ ለመድረስ የትኛውንም አይነት ስራ ሊሰራ መቻሉን ነው፡፡ ትእግስት በቴአትር ጥበባት ስትመረቅ የመመረቂያ ጥናቷን የሰራችው ‹‹ የቴአትር ጥበባት፤ የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤትና አለ የስነ-ጥበባት ተማሪ ቤት በአንድ ኮሌጅ ስር መሆናቸው ያለው ፋይዳ በሚል ርእስ ነበር፡፡ የማስተርስ መመረቂያዋ ደግሞ የአዊ ማህበረሰብ የማንነት ቃላዊ ዝርው ተረኮች ፋይዳ የሚል ነበር፡፡

የዩኒቨርሲቲ መምህርት

ከ2005 ዓ.ም ጀምሮም ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴአትር ጥበባት ትምህርት ቤት በመምህርትነት ተቀጥራ በማገልገል ላይ ትገኛለች፡፡ በትምህርት ቤቱም ከማስተማር ስራዋ ባሻገር የተለያዩ የስራ ሀላፊነቶችን ተረክባ በማገልገል ላይ የምትገኝ ሲሆን የመጀመሪያዋ የትምህርት ቤቱ ሴት ዳይሬክተርም ናት፡፡ ያስተማረቻቸው ተማሪዎች እንደሚናገሩት ትእግስት ወደ ተማሪዎቿ ከመግባቷ በፊት በቂ ቅድመ-ዝግጅት ታደርጋለች፡፡

ይህም ጥሩ እውቀት ለተማሪዎቿ እንድትሰጥ አስችሏታል፡፡ አንድ ሰው በቂ ምርምር ማድረግ አለበት ብላ የምታምነው ትእግስት ተማሪዎቿም ይህን ፈለግ እንዲከተሉ ትፈልጋለች፡፡ ለአንድ ተማሪ ግሬድ ከመስጠቷ በፊትም ተማሪው ያቀረበውን የጥናት ወረቀት በጥልቀት ለመረዳት የተቻላትን ታደርጋለች፡፡ በዚህም አብዛኛዎቹ ተማሪዎቿ አድናቆትን ይቸሯታል፡፡ ያላትንም ጥሩ የመምህርነት ስነ-ምግባር ሁሉም ያደንቃሉ፡፡ባለፉት 8 አመታት የቀንና የማታ ተማሪዎችን ጨምሮ ከ900 በላይ ተማሪዎችን ያስተማረችው ትእግስት ተማሪን በመቅረብና በማቅረብ የምታምን ወጣት ምሁር ናት፡፡

የድርሰት ና የምርምር ስራዎች

ትእግስት ‹‹የአንድ ሰው ቴአትር ቅኝት›› በኢትዮጵያ በሚል ርእስ በ2008 ኮንፈረንስ ላይ ጥናት ያቀረበች ሲሆን በመቀጠልም የመጀመሪያው የቴአትር ፌስቲቫል ላይ የወጋየሁ ንጋቱ ስራና ህይወቱ ላይ በሳል ምሁራዊ ጥናት አቅርባለች፡፡ ኢየሩሳሌም ጸጋው ከምትባል ሰው ጋርም የከበደ ሚካኤል የቴአትር ስራዎች ሞራላዊ ፋይዳ በሚል ርእስ የጥናት ወረቀት አቅርባለች፡፡ በዚህ አመት ደግሞ ማርች 8 2021 ደግሞ በሀዋሳ የከፍተኛ ትምህርት ጽንሰ-ሀሳብና አካታችነት በሚል ርእስ በብዙዎች ለመደነቅ የቻለ ጥናት ለታዳሚያን አቅርባለች፡፡ ከ2 አመት በፊት በ2011 ደግሞ የቻይና መንግስት ለኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች በሰጠው የ21 ቀናት የስልጠና እድል ልምድ ቀስማ ተመልሳለች ፡፡

ትዕግስት ከቴአትር ጥበባት መምህርነት ስራዋ በተጨማሪ ፤ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን አቅርባለች፡፡ ከእነዚህም መካከል “የመጨረሻው ንጉስ-ቀ.ኃ.ሥ” የተሰኘ የሙሉ ጊዜ ተውኔት ጽፋ ያሳተመች ሲሆን በተለያዩ መድረኮች እና በሬድዩ ለመቅረብ ችሏል፡፡ ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ ጋር ተያይዞ “ጃንሆይ እንዳስተማሩን” በሚል ርዕሥ አጭር ቴአትር ጽፋ በማዘጋጀት በብሄራዊ ቴአትር ሌሎች ባለሙያዎች ካዘጋጇቸው ዝግጅቶች ጋር በግንቦት 19 2011 ለማቅረብ ችላለች፡፡ ይህ ‹‹ጃንሆይ እንዳስተማሩን›› የተሰኘ የባለ አንድ ሰው ተውኔት የቴሌኮሙዩኒኬሽን የመጀመሪያው ስራ አስከያጅ በሆኑት በኢንጂነር በትሩ አድማሴ ህይወት ላይ ያተኮረ ሲሆን የህይወት ታሪኩም አዘጋጅ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ነው፡፡

ትእግስት አለማየሁ ፤ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽንን በቅርበት የምታበረታታ እና ሙያዊ ምክሯን የምትለግስ ስትሆን በተለይ በግንቦት 1 2011 የገጣሚ ደበበ ሰይፉ ኦድዮ ሲዲ በባህል ማእከል በተመረቀ ጊዜ ልባዊ እና በትህትና የታጀበ ምክሯን የለገሰች ናት፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከአንድ መቶ ሃያ ባለሙያዎች በላይ የተሳተፉበት “የክብር ወሰን /አድዋ” የተሰኘ ተውኔት ጽፋ በማዘጋጀት የካቲት 23 ቀን 2013 ዓ.ም በወዳጅነት አደባባይ አቅርባለች፡፡ ይህም በወዳጅነት አደባባይ የቀረበ የመጀመሪያው የቴአትር ስራ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ አሳታፊ ቴአትሮችን ከተማሪዎቿ ጋር ለመስራት እድሉን ያገኘች ሲሆን ከእነዚህም መካከል “የቆሻሻው ተራራ”፤”ትምህርት በታችን” እና በሀገር ፍቅር ትንሿ አዳራሽ የመቅረብ እድል ያገኘው “ድምጹ ተበክሏል” ቴአትር ይጠቀሱበታል፡፡

ቤተሰባዊ ሁኔታ የንባብ ህይወት እና የዶክትሬት ትምህርት

ትእግስት ባለትዳር እና የአንድ ልጅ እናትም ነች፡፡ ማንበብ የእውቀት አድማስን የማስፋት ሀይል አለው የምትለው ትእግስት የህይወት ተፈራ ስራ የሆነውን Tower in the sky የተሰኘውን መጽሀፍ ትወዳለች፡፡ እንደዚሁም የአዳም ረታ ግራጫ ቃጭሎች ልዩ ስሜት የሚሰጣት መጽሀፍ ነው፡፡ ትእግስት ሁል ጊዜ ለራሷ እንዲህ ብላ ትነግራለች፡፡ ‹‹የቻልሸውን ያህል ከመስራት አትስነፊ፤ በቅንነት ኑሪ፤ ተስፋሸ በፈጣሪሸ ላይ ብቻ ይሁን።›› ትላለች፡፡

ትዕግስት በአሁኑ ጊዜ የዶክትሬት ትምህርቷን በጣም በምትወደው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አፍሪካ እና የእስያ ጥናት ማዕከል ውስጥ በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡ ለኢትዮጵያ ታላቅ ፍቅር ያላት ትእግስት አለማየሁ ማስተማርን ሁል ጊዜ እንደ መማር ትቆጥራለች፡፡ እናም ዛሬም ነገም መማር የህይወቷ ዋና መርህ እንደሆነ ይቀጥላል፡፡ አሁን 34 አመቷን የያዘችው ትእግስት ስለሰራችው ስራ ቆም ብላ ስታስብ ይህን ባደርግ ኖሮ ብትልም ነገር ግን ወደፊት በውስጡዋ ያሉትን ሀሳቦች ተግባራዊ ማድረግ ስትጀምር ያኔ የልቧ ይሞላል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *