ተመስገን ያለው
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በኪነ-ጥበብ እና በመዝናኛው ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ያልተነገረላቸው ባለሙያዎችን በአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ ላይ ሲያወጣ ነበር፡፡ ወደፊትም ያወጣል፡፡ መዝገበ-አእምሮ አንዱ ስራ ነው፡፡ ሀገር የምታድገው የሰራ ሰው ልምድና ታሪኩን ሲያካፍል ነው ብለን እናምናለን-እንደ ተወዳጅ፡፡ ያለ አንዳች እረፍት የሰራ ሰው ለብዙዎች አርአያ እንደሚሆን ስለሚታመን ታሪኩ ይሰነዳል፡፡ ከእነዚህ ታሪካቸው ከሚሰነድላቸው የቴአትር ባለሙያዎች መካከል ተመስገን ያለው አንዱ ነው፡፡ ተመስገን፣ ከ9 አመት አስቀድሞ ወደ ባህርማዶ ያቀና ሲሆን ዛሬም ለጥበብ ታላቅ ፍቅር ያሳደረ ነው፡፡
ትውልድ እና ልጅነት
ተመስገን ያለው ህዳር 27 ቀን 1965 ተወለደ፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በነፃነት ብርሀን 1ኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ቤት፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በአብዮት ቅርስ ትምህርት ቤት ተከታትሏል፡፡ በአዲስ አበባ ዪኒቨርስቲ የቲያትር ጥበባት ትምህርቱን አጠናቅቆ በ1986 በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቋል፡፡ ተመስገን ያለው በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቆይታው ልዩ ልዩ ልቦለዶችን በማንበብ ለስነጽሁፍ ያለውን ፍቅር በሚገባ ማሳደግ ችሏል፡፡የበለጠ ወደ ቴአትር የተሳበው ግን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከገባ በኋላ ነበር፡፡
በመድረክ 75ብር
ተመስገን የ3ኛ አመት ተማሪ እያለ ነበር ወደ ፕሮፌሽናል መድረክ በተዋናይነት ለመስራት የበቃው፡፡ የተወዳጁ ደራሲ በአሉ ግርማ ከአድማስ ባሻገር ቲያትር ደራሲ ኃይለማሪያምን በመወከል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር ከአንድ አመት በላይ ተውኗል፡፡ ይህን ስራ ከመጽሀፍ ወደ ቴአትር የቀየረው ነቢዩ ተካልኝ ነበር፡፡ በተመሳሳይ ጊዜ በእውቁ የቴአትር ሰው አባተ መኩሪያ የተዘጋጀውን ታላላቅ ተዋንያንን ባሳተፈው የኤዲፐስ ንጉስ ቲያትርም ላይ በትወና አቅሙን አሳይቷል፡፡ በመቀጠልም በሀገር ፍቅር ቲያትር በአዲስ አበባ ማዘጋጃና በራስ ቲያትር የበላይነህ አቡኔ ውርስ ትርጉም የሀይማኖት አለሙ ዝግጅት በሆነው ‹‹ተውኔቱ›› ቲያትርና በፍሰሀ በላይ ቲያትሮች ላይ በመተወን ለሙያው ያለውን ፍቅር ለማሳየት ችሏል፡፡
ተመስገን ገና የ3ኛ አመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር በመድረክ 75ብር እየተከፈለው ይሰራ ነበር፡፡ በሳምንት 2 መድረኮች ስለነበሩት በወር ገና ሳይመረቅ 600 ብር ኪሱ ይገባ ነበር፡፡ ያኔ ዲግሪ የጫነ የሚያገኘውን ተመስገን ያገኝ ነበር፡፡
ወደ ሙያ መሳብ
ከአዲስ አበባ ዪኒቨርስቲ ተመርቆ ከወጣ በኋላም በራስ ቲያትር በተዋናይነትና በቲያትር ኤክስፐርትነት ተቀጥሮ ሰርቷል፡፡ በራስ ቲያትርም የመሀን ትሩፋት፣ ዲዳይቱ ወይዘሮ፣ የደም ባለ ሳምንት ፣ቁርጥ ቀን : እንዲሁም ማክቤዝ ቲያትር ላይ በተዋናይነት ተሳትፏል፡፡ በዚህ ጊዜም ተመስገን ለፊልም ጥበብ ባለው ከፍተኛ ፍላጎት በከፍተኛ ችግርና ውስብስብ ሁኔታዎች በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ በጊዜው በኢትዮጵያ የፊልም ታሪክ ውስጥ በጣት ከሚቆጠሩት ቀደምት የቪኤች ኤስ ፕሮዳክሽኖች አንዱ የሆነውን የእሳት ራት የቪዲዮ ፊልም ደርሶ በማዘጋጀትና በመተወን ለህዝብ አቅርቧል ፡፡
በቲቪ የ5 ደቂቃ ድራማ
ይህ የተመስገንን የፊልም ፍላጎትና አቅም ከተማሪነቱ ጀምረው ይገነዘቡ የነበሩት አቶ ነቢዩ ተካልኝ ተመስገን በቴሌቪዥን የመዝናኛ ፕሮግራሞች ላይ የተሳካ ስራ ሊሰራ እንደሚችል ያቀረቡት ምክረ ሀሳብን ተከትሎ የባህል ቢሮው ተመስገን ከራስ ቲያትር ወደ አዲስ አበባ ቴሌቭዥንና ሬዲዮ የመዝናኛ ኃላፊ ሁኖ እንዲሰራ አዛወረው፡፡ በዚህ ወቅትም ለ2 አመታት ሳምንታዊ ፕሮግራሞች ላይ ከ200 በላይ አጫጭር የአምስት ደቂቃ ድራማዎችን ፕሮዲውሰር በመሆን ሰርቷል፡፡ በተጨማሪም በደራሲነትና በአዘጋጅነት እንዲሁም ኤዲተርነትም ተሳትፏል ፡፡በቲቪ የ5 ደቂቃ ድራማ ማሳየት እንደሚቻል መንገዱን በማሳየት ጭምር ተመስገን ትልቅ አሻራ ማኖር ችሏል፡፡ መስኮት በተሰኘው ፎርማት የአዲስ አበባን ጉዳዮች በማንሳት ድራማዎች ወደ ተመልካች እንዲቀርቡ በማድረግ የተመስገን ሚና ጉልህ ነበር፡፡ በጊዜው የቲቪ ድራማ ፍቅር ያላቸው ሰዎች ወደ መድረኩ እንዲመጡ በማደፋፈር በኩል ተመስገን የራሱን ድርሻ ተወጥቷል፡፡ ከ1992-1994 ባሉት ጊዜያት እንደ ፕሮዲዩሰር፤ እንደ ደራሲና አዘጋጅ በመሆን ተመልካችን ለማዝናናት ሌት ተቀን ለፍቷል፡፡በወቅቱ ታገል ሰይፉ በመስኮት ድራማ ላይ የሚሰራቸው የመዝናኛ ጥበባዊ ስራዎች በተመስገን ስር ነበሩ፡፡
ተመስገን ጃፓን ሀገር በመሄድ የዲጂታል ቪዲዮ ፕሮዳክሽን ትምህርት ተከታትሏል፡፡
ተመስገን የተለያዩ የሙዚቃ ክሊፓችንና የዶክመንተሪ ስራዎችን የሰራ ሲሆን በተለይም የቴዲ አፍሮ ያስተስርያል የሙዚቃ ክሊፕንና የመድረክ የሙዚቃ ስራዎችን ዳይሬክትና ኤዲት በማድረግ አቅርቧል ፡፡ እንዲሁም ለረጅም ጊዜ የለፋበት በባህር ዳር ዙሪያ የተሰራ ጌትነት እንየው መስታወት አራጋው ሱራፌል ተካና ልኡል ተፈሪን የመሳሰሉ እውቅ ባለሙያዎች የተሳተፋበትን ቢሰራም ፕሮዲውሰሩ የሜጋ ኪነጥባት ድርጅት በመፍረሱ ስራው ለህዝብ ሳይቀርብ ቀርቷል፡፡ደመና ወራሾች የተሰኘውን የአበረ አዳሙ ድርሰት ታሪኩን በ ማሰደግና ወደ ፊልም ፅሁፍ በመለወጥ አዘጋጅና ኤዲተር በመሆን ሰርቶአል:ደመና ወራሾች የተሰኘው ይህ ስራው በምስል ጥራቱ የተመሰከረለት እንዲሁም በይዘቱም ጠንካራ እንደነበር ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡
‹‹ሰው ለሰው››
በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጨረታ አሸንፎ ለአንድ አመት ድራማ ለመስራት ተዋውሎ ‹‹ሰው ለሰው›› የተሰኘውን ድራማ ለመስራት ጀምሮ ለአንድ አመት የሚሆነውን የታሪኩን አፅመ- ታሪክ በደራሲነት እንዲሁም የተዋናይ ምልመላና የፕሮዳክሽን አደረጃጀቱን ከሰራ በኋላ ስራው ከሚገባው በላይ በተለያዩ ምክንያቶች ሲጓተት ሊሄድ ባለመቻሉ ስራውን አቋርጦ ወደ አሜሪካን ሀገር ለመሄድ ተገዷል ፡፡ ከዛሬ 9 አመት በፊት በ2005 ግድም ወደ ሜሪላንድ ያቀናው ተመስገን ከባለቤቱ ከወይዘሮ አዜብ መንግስቱ ጋር ጋብቻን መስርቶ 2 ልጆችን አፍርቷል፡፡ በዳይሬክቲንግ ፤ እንዲሁም በድርሰትና በትወና ለ18 አመታት አቅሙን ያስመሰከረው ተመስገን አሁንም የጥበብ ፍቅር ውስጡ እንዳለ ነው፡፡ ልጅ የማሳደግ ነገር ቅድሚያ ስለሚሰጠው እንጂ ተመስገን ለሚወደው የቴአትር ሙያ አንድ ነገር ለማበርከት ማቀዱ አልቀረም፡፡ አቅዷልም፡፡ ይህን እቅዱን ከግብ ለማድረስ አንዳንድ ሀሳቦችን እየሰበሰበ ነው፡፡ ሀሳቡ ሲበስልና ነፍስ ሲዘራ ተመስገን ዳግም ያንሰራራል፡፡
አርቲስት አዳነች ወልደገብርኤል ስለ ተመስገን ስትናገር የዳይሬክቲንግ ችሎታው በብዙዎች የተመሰከረ ነው ትላለች፡፡ አዳነችና ተመስገን የተዋወቁት ራስ ቴአትር ነው፡፡ በአዳነች እይታ ተመስገን ከራስ ቴአትር ጀምሮ ድንቅ አቅሙን እያጎለበተ የመጣ ነው፡፡ በአዲስ አበባ መስተዳድር ይተላለፍ በነበረው መስኮት የቲቪ ድራማ ላይም በዳይሬክቲንግ ትልቅ ድርሻ እንደነበረው አዳነች ትመሰክራለች፡፡በአዳነች አባባል ተመስገን ተመስገን ለስራው ቅድሚያ ይሰጣል እንጂ ስሙ እንዲታወቅለት ብዙም የሚሻ ሰው አለመሆኑን አዳነች ትናገራለች፡፡ ‹‹የእሳት ራት ሲሰራ ተመስገን በዳይሬክቲንግ ትልቁን ሚና ተጫውቷል፡፡ በዚህም ምስጋናዬን ልቸረው እወዳለሁ›› ትላለች አዳነች፡፡
መዝጊያ
ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የቴአትር ሰዎች ታሪክ መማክርት ቡድን አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡ ተመስገን በብዙዎች ይወደዳል-ይከበራል፡፡ ይህ የሆነው ግን ያለ አንዳች ምክንያት አይደለም፡፡ተመስገን ሰው በመርዳት ያምናል-ትችላላችሁ ብሎ ማደፋፈር ልዩ መለያው ነው፡፡ ሲሰራም በትጋት ስለሚሰራ ይህ ልፋቱ በብዙዎች ታውቆለታል፡፡ በቀበሌ ደረጃ ቴአትር የሚሰሩ ወጣቶች በቴክኒክ በመደገፍ ተመስገን ብዙዎች አብቅቷል፡፡ ተመስገን ተባብሮ በመስራት ያምናል፡፡ ይህ እምነቱ በብዙዎች አስከብሮታል፡፡ ተወዳጅ ሚድያ ከኋላ እንደ ደጀን ሆነው ሙያቸውን ያስከበሩ ጀግኖችን የዘመናቸው ተተኪ ጀግና ይላቸዋል፡፡ በሙያቸው ላይ ታላቅ ፍቅር ያሳደሩትን ወደፊት እያመጣ ከፍ አድርጎ ስማቸውን በደማቁ ይጽፋል፡፡ ቴአትር ድሮ ቀረ በሚሉት ብሂል አንስማማም፡፡ቴአትረኛ ድሮ ቀረ የሚለውንም አቋም አናራምድም፡፡
ይልቁንም የድሮና የአሁን ትጉሀንን በአንድ መስመር እያሰለፍን የስነዳ ተግባራችንን ማከናወን ለቀጣዩ ትውልድ አንድ ደጎስ ያለ ስራ ማስረከብ ቀዳሚው ተግባራችን ነው፡፡ ተመስገን በዚህ መዝገበ አእምሮ በተሰኘ መጽሀፍ ውስጥ ታሪኩ ቢቀመጥ ለትውልዱ የሚያስተምረው አንድ ነገር አለው፡፡ በአሁኑ ሰአት መኖርያውን በሜሪ ላንድ አሜሪካ ያደረገው ተመስገን በባህር ማዶ ከሚገኙ የቴአትር ሰዎች ጋር እየተገናኘ ከሙያው ላለመራቅ ጥረት ያደርጋል፡፡ ይህ ጥረቱ ደግሞ በጽናት ከቆመ መሳካቱ አይቀርም ›› / ይህ ጽሁፍ ባለታሪኩን ተመስገን ያለውን በማስፈቀድ ፤ በማነጋገር የተሰራ ነው፡፡ ጽሁፉ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የተሰናዳ ሲሆን አስፈላጊ ማሻሻያ ፤ ተገቢ እና ገንቢ ምስክርነቶች እየታከሉበትበየጊዜው የሚቀርብ ይሆናል፡፡ ይህ ጽሁፍ ለመዝገበ-አእምሮ መጽሀፍ ለ12 ወር በኋላ ከሚታተሙ ስብስቦች አንዱ ነው፡፡ በዚህ ሰአት ዛሬ ሀምሌ 3 2014 በዊክፔዲያ ፤ እና በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽእና ብሎግ የወጣ ነው፡፡