ቀኝ አዝማች ያሬድ ገብረሚካኤል /1908-1966/
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡
ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 200 የሚድያ ፤ የስነ-ጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል ቀኛዝማች ያሬድ ገብረሚካኤል ናቸው፡፡
ቀኝ ዝማች ያሬድ ገብረሚካኤል የጋዜጠኝነት ስራ የጀመሩት ከዛሬ 79 አመት በፊት በ1936 አ.ም ነበር፡፡ በጊዜውም የብርሀንና ሰላም ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነበሩ፡፡ ከ25 በላይ መጽሀፍትን የደረሱት ቀኛዝማች ያሬድ ገብረሚካኤል በ1966 በ58 ዓመታቸው ነበር ያረፉት፡፡ እዝራ እጅጉ የህይወት ታሪካቸውን እንደሚከተለው ሰንዶታል፡፡
ትውልድ እና ልጅነት
ቀኝ አዝማች ያሬድ ገብረሚካኤል በያኔው ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ተብሎ በሚጠራው በተጉለት እና ቡልጋ አውራጃ በጅሩ ወረዳ በጉበላ ሚካኤል ቀበሌ በ1908 ዓ.ም ከመሪ ጌታ ገብረሚካኤል ይመኑ እና ከወይዘሮ ደስታ ወልደ ዮሃንስ ተወለዱ። ቀኝ አዝማች ያሬድ እድገታቸው በቤተክርስቲያን አካባቢ ሲሆን በተለይም በአጎታቸው በብላታ ወልደጊዮርጊስ በመንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን ከነበሩት የቅኔ መምህር ከአለቃ በላይ ዘንድ ቅኔ የቆጠሩ ሲሆን በ10 አመታቸው ሰም እና ወርቁ የተስተካከለ እና ምስጢሩ እና ዘይቤው የተቀነባበረ ቅኔ በመቀኘታቸው ብዙዎች ሲያደንቁዋቸው በተለየም በአንድ ወቅት ሊቃውንት በተገኙበት ከጃንሆይ ፊት በመቀኘታቸው ጃንሆይም የቅኔውን ብስለት የቀኝ አዝማች ያሬድን የልጅነት መጠን አይተው ሊቁን ዶክተር አለቃ አየለን አስጠርተው የመፅሃፍትን ትርጉም አስተምረው ስለኑሮው ስለቀለቡ እና ስለልብሱ ከቤተመንግስቱ እንዲሆን ሲሉ አዘዙላቸው። ቀኝ አዝማች ያሬድ እንደተባለው ከሊቁ ዶክተር አለቃ አየለ ዘንድ ጠንክረው በመማር ሃዲሳቱን ሊዘልቁ መቻላቸው ይነገርላቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ወደ ዳግማዊ ምኒሊክ ት/ቤት ገብተው የዘመናዊ ትምህርትና የተለያዩ ቋንቋዎችን አጥንተዋል። በጠላት ወረራ ጊዜ ችግር ስለገጠማቸው ትምህርታቸውን አቋርጠው ቤተክርስቲያንን እያገለገሉ ቆይተዋል።
ግርማዊ ንጉሰ- ነገስት በድል አድራጊነት እንደተመለሱ ወዲያው በ1933 ዓ.ም በጦርነቱ ጊዜ መጠኔ ሳይፈቅድልኝ ቀርቶ ወደ ዘመቻ ሄጄ የፈፀምኩት ግዳጅ ስለሌለ በዚያ ፈንታ አሁን ወታደር መሆን አለብኝ ብለው የጦር ሀይሎች ባልደረባ ከመሆናቸውም በላይ በጦር ሰራዊት የፈረሰኛ ክፍል መቶ አለቃ ሆነው አገልግሎታቸውን ሲያበረክቱ በድንገት ታመው በሆስፒታል በመዳረጋቸው ከውትድርና ለመውጣት ተገደዋል፡፡
ወደ ጋዜጣ ስራ
ከዚያም በ1937 ዓ.ም በጋዜጣ እና ማስታወቂያ መምሪያ ቤት ተቀጥረው በጋዜጦች ክፍል ያገለግሉ ጀመር። ገና በመጀመሪያ ባፃፃፍም ሆነ በአመራር ችሎታቸውን ስላሳዩ በዚያ ጊዜ የነበሩ የመስሪያ ቤቱ ባለስልጣኖች በከፋ ጠቅላይ ግዛት ጅማ ላይ የጋዜጣ ንባብ ፍቅር እንዲስፋፋ በማለት አዘዋቸው ሄደው ከታሰበው በላይ ስራውን በማከናወናቸው መስሪያ ቤቱ አመስግኗቸዋል ። እንዲያውም ለዋናው መስሪያ ቤት ያስፈልጋሉ ተብለው ብርሃን እና ሰላም ለተባለው ታላቅ መፅሄት ዋና አዘጋጅ ሆነው እንዲሰሩ ስለተደረገ በዚህ ስራ ላይ እስከ 1940 ዓ.ም ድረስ ቆይተዋል።
ከዚያም በሰንደቅ አላማችን እና በአዲስ ዘመን ጋዜጦች ክፍል በምክትል አዘጋጅነት እና በዋና አዘጋጅነት እንዲሁም በዲሲፕሊን ጉባኤ ከስራ ተካፋዮቻቸው ጋር ባልተቆጠበ ድካም ሲያገለግሉ የቆዩ ናቸው። ከዚያም የማስታወቂያ ሚንስቴር ፣ የጋዜጣ እና የማስታወቂያ ሚኒስቴርነት መስሪያ ቤት እየተባለ በሚጠራበት ጊዜ መስሪያ ቤቱን ይመራ የነበረው ሰባት ሰዎች የሚገኙበት ቦርድ አባል ሆነው ሰርተዋል። ቀኛ አዝማች ያሬድ በማስታወቂያ ሚንስቴር በቆዩበት ጊዜ ለሬዲዮ ፕሮግራም ዲያሎግ በማዘጋጀት ፣ የልዩ ልዩ ጋዜጦች አዘጋጅ በመሆን ከፈጸሙት አገልግሎት በላይ በመስሪያ ቤቱ እና በግል በመፅሃፍ ቅፅ ያዘጋጇቸውና ለመንግስትም ያበረከቷቸው ድርሰቶች እጅግ ብዙ ናቸው። ቀኛአዝማች ያሬድ በደራሲነት ካበረከቷቸው 25 መጽሀፎች ውስጥ ጥቂቶቹ የእንስሳት አገልግሎት ፣ የመወለድ ሙያ ፣ የአዲስ አበባ ከተማ መስታወት ፣ የፍቅር ምርኮኛ ፣ ይምጡ በዝና ፣ አዲስ አበባ እና የሰው ልጅ ስንክሳሮ ይገኙበታል።
ቀኝ አዝማች ያሬድ በተለይ ሰንደቅ አላማችን ጋዜጣ ባንዳንድ ችግር ምክንያት ስራውን እስከተዉ ድረስ በእርሳቸው አማካኝነት በቅንነት በታማኝነት ፣ በትጋት እና በጥንቃቄ በዋና አዘጋጅነት ከፍ ያለ የስራ ፍሬ አበርክተዋል። ቀጥሎም የአዲስ ዘመን ጋዜጣ አዘጋጅ ሆነው እስከ ህይወታቸው ፍፃሜ ድረስ ሙሉ አገልግሎት ያላቸው ታላቅ ደራሲ እና ጋዜጠኛ ነበሩ። ቀኛ አዝማች ያሬድ ከዚህ ከተዘረዘረው አገልግሎት እና ሙያ በተጨማሪ ለሃገራቸው ተቆርቋሪ እና አሳቢ በመሆናቸው በእነዋሪ እና በጁሁር ት/ቤት ካቋቋሙት ማህበርተኞች አንደኛው ናቸው። በተለይም “የእንስሳት አገልግሎት” የተባለው መፅሀፋቸው ላይ ለጁሁር እና ለእነዋሪ ት/ቤቶች ለልጆች ማስተማሪያ እንዲሆን ብዙ መፅሀፍት በነፃ ስለሰጡ መልካም ስም አትርፎላቸዋል። በሰላሳ ሶስት ዘመን አገልግሎት ጊዜያቸውም ውስጥ የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ የፈረሰኛ ደረጃ ኒሻን የ1933 ዓ.ም ድል 25ኛ ዓመት መታሰቢያ የኦሜድላ ኒሻን እንዲሁም የዘውድ ኢዮቤልዩ መታሰቢያ በአል ኒሻን ተሸልመዋል።
ልጃቸው ተሰማ ያሬድ ስለ አባቱ የተናገረው
አባቴ በህይወት በነበሩበት ጊዜ ጨዋታ አዋቂና ከሰዎች ጋር በቀላሉ የሚግባቡ ነበሩ፡፡ አባቴን በቅርበት የሚያውቋቸው አቶ መርስኤሀዘን አበበ ሙሻዘር በተባለው መጽሀፋቸው ገልጸዋቸዋል፡፡ ምናልባትም ‹‹ይምጡ በዝና›› በተባለ መጽሀፋቸው የአዲስ አበባ ከተማን አመሰራረት በማስረጃ አስደግፈው ያቀርቡ ነበር፡፡ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ህይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ አዘጋጅ እና በተለያዩ ክፍሎች አገልግለዋል። በትምህርትም የቤተክህነት ትምህርት የተማሩ ሲሆን ያሬድ የሚል ስም የወጣላቸው በ10 አመታቸው ነበር ። በቋንቋ ደረጃ ፈረንሳይኛ ፣እንግሊዘኛ ቋንቋን ይናገራሉ። የእቴጌን ሙሉ ታሪክ በእንግሊዘኛ ፣ ኢዬቤልዮ የተሰኘው የንጉሳውያኑን ቤተሰብ የህይወት ታሪክ የያዘ ፅሁፍ ፣ የፍቅር ምርኮኛ ፣ የእንስሳት አገልግሎት ለህፃናት በረከት የሚለውን መፅሀፍ ትምህርት ሚኒስቴር ወስዶት የሶስተኛ ክፍል አማርኛ መፅሀፍ ማስተማሪያ ነበር ። ከ25 እስከ 28 የሚደርሱ መፅሀፍትን የፃፉ ናቸው፡፡
ቀኝ አዝማች ያሬድ ገብረሚካኤል በ1908 ዓ.ም የተወለዱ ሲሆን በ1966 ዓ.ም አርፈዋል።
መዝጊያ
ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የመዝገበ-አእምሮ ቦርድ አባላትን አቋም የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ ቀኝ አዝማች ያሬድ ገብረሚካኤል በኢትዮጵያ ታሪክ ስማቸው ጎልቶ ሊወጣ የሚገባ ሰው ናቸው፡፡ በ28 አመት እድሜያቸው ነበር ወደ ጋዜጣ ስራ የገቡት፡፡ በጊዜው በሀገራችን ታሪክ ከ1933 በኃላ ለህትመት የበቁትን ህትመቶች ካዘጋጁት ባለሟሎች መካከል ቀኛዝማች ያሬድ ገብረሚካኤል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እኒህ ታላቅ የሀገር ባለውለታ ከጋዜጠኝነት ስራቸው ባሻገር የንባብ ፍላጎትን የሚያረኩ 25 መጽሀፎችን ወደ አንባቢ አድርሰዋል፡፡ ይህም ከደራሲነት ተርታ የሚያስመድባቸው ናቸው፡፡ በሀገራችን መጽሀፍ የሚደርሱ ሰዎች ቁጥራቸው በጣት በሚቆጠርበት በዛን ዘመን ቀኛ ዝማች ያሬድ ያወቁትን ለማሳወቅ ጉጉት በማሳደራቸው በተከታታይ መጽሀፎችን አሳትመዋል፡፡ ሀገራችን ባለፉት 80 አመታት በሺህ የሚቆጠሩ የስነጽሁፍ እና የሚድያ ባለሙያዎች የነበሩ ሲሆን ቀኛዝማችም ፈር ቀዳጅ ከሚባሉት ተርታ የሚመደቡ ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያ እንደ እርሳቸው አይነት ሰዎችን በየጊዜው መዘከር አለባት፡፡ ይህ ታሪክ ራሱ ከዚህ ቀደም በቀላሉ የሚገኝ አልነበረም፡፡ ማለትም ስለ ቀኛዝማች ያሬድ ስማቸውን ከመጥቀስ ባለፈ ዘርዘር ያለ መረጃ አይገኝም፡፡ አሁን ግን ቤተሰቦቻቸው ፈቅደው ይህን የህይወት ታሪክ ለመሰነድ በቅተናል፡፡ ይህን ታሪክ ስናወጣ ለልጃቸው ለአቶ ተሰማ ያሬድ የከበረ ምስጋናችንን ማቅረብ እንወዳለን፡፡