ሻምበል ታደሰ ወልደገብርኤል

በል ታደሰ ወልደገብርኤል

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 150 የሚድያ ፤ የስነ-ጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል ሻምበል ታደሰ ወልደገብርኤል አንዱ ነው፡፡ እርሱም በልቦለድ ድርሰት እና በግጥም ስራው የሚታወቅ ነው፡፡ ከ6 ወር በፊት ህይወቱ ያለፈው ሻምበል ታደሰ ሀገሩን የሚወድ ታላቅ ሰው ነበር፡፡ የህይወት ታሪኩንም እዝራ እጅጉ እንደሚከተለው ሰንዶታል፡፡

ሻምበል ታደሰ ወ/ገብርኤል ከአባታቸው ከአቶ ወ/ገብርኤል ገ/ማርያም እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ፋና አንባው መስከረም 17 ቀን 1960 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ዞን በኤፍራታ እና ግድም ወረዳ በካራቆሬ ከተማ ተወለዱ። በመርእድ አዝማች ወሰን ሰገድ አስፋው ወሰን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብተው የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው የሁለተኛ ደረጃን አጣዬ ሁለተኛ ደረጃ ተከታትለዋል።

ሻምበል ታደሰ ወ/ገብርኤል በልጅነት ዕድሜያቸው በካራቆሬ ከተማ በነበራቸው ህይወት የጓደኞቻቸው መሪ በመሆን በውስጣችው በነበረ የኪነ-ጥበብ ዝንባሌ ፊልሞችን በካርቶን አዘጋጅቶ በማሳየት፣ ድራማዎችን በመድረስ እና በመጻፍ በተለያዩ ከተሞች በተለይም እስከ አፋር ክልል ድረስ ቡድኑን እየመሩ በማሳየት ጓደኞቻቸውን በእግር ኳስ እና በሩጫ ቡድን በማደራጀት በመምራት፣ ለአደን በነበራቸው ፍቅር በወስፈንጥር እና በጠብመንጃ ከእንጨት ጠርበው በመስራት የዱር እንስሳትን በማደን እንዲሁም የጓደኞቻቸው የልጅነት ፎቶግራፎችን አደራጅተው በመያዝ ለታሪክ ማስታወሻነት እንዲቀመጥ በማድረግ የማይረሳ ታላቅ ስራ ያከናወኑ ሰው ናቸው።

ሻምበል ታደሰ ወ/ገብራኤል ህዳር 03 ቀን 1975 ዓ.ም በዕጩ መኮንንነት ኮሮስ ሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት ለወታደራዊ ስልጠና ገብተው፤ ጥር 12 ቀን 1976 ዓ.ም በምክትል መቶ አልቅነት ተመርቀው ባስመዘገቡት ከፍተኛ ውጤት በትምህርት ቤቱ ተመድበው በመምህርነት፣ በትምህርት ቤቱ ወታደራዊ ቤተ-መዘክር እና ቤተመፅሐፍት ሃላፊነት በቅንነት፣ በታማኝነት እና በብቃት አገልግለዋል። ሻምበል ታደሰ ወ/ገብርኤል የኪነ-ጥበብ ጊዜያዊ መብት አስከባሪ ኮሚቴ ውስጥ በኦዲዮ ቪዥዋል አሳታሚዎች ማህበር ውስጥ በአመራርነት ተቀምጠው ለአምስት ዓመታት ያህል በነፃ በማገልገል የኪነ-ጥበብ ውጤት መብት እንዲከበር ከፍተኛ አስተዋፆ አበርክተዋል።

ሻምበል ታደሰ ወ/ገብርኤል በጂ.አዲ አርት ፕሮሞሽን ውስጥ ከእህታቸው አርቲስት አዳነች ወ/ገብርኤል ጋር በመሆን በምክትል አዘጋጅነት በየወሩ ታትሞ የሚወጣ ጠብታ መፅሄት ላይ ‘’የዛሬ ጠብታችን የነገ ምንጫችን አካል ትሆናለች‘’ በሚል መርህ ለአንባቢያን ተደራሽ ያደረጉ ነበሩ። በተጨማሪም በዚህ ድርጅት ውስጥ ሳሎን ኢትዮጵያ የተሰኘ ጋዜጣ በኢትዮጵያ ውስጥ በማዘጋጀት በየአስራ አምስት ቀኑ በአሜሪካን ለአንባቢያን ተደራሽ ያደርጉ ነበር። ሻምበል ታደሰ ወ/ገብርኤል ከአያታቸው በወረሱት የባህል ህክምና እውቅና ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ፅ/ቤት የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት በማግኘት ህዝባቸውን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

በኪነ- ጥበብ ሙያ ዘርፍ በተለያየ መስክ ተሰማርተው ያገለግሉ ሲሆን በተለይ በስነ ፅሁፍ ዘርፍ ተሰማርተው ‹‹ቃዘኖ›› የተሰኘ ልብ ወለድ መፅሀፍ፣ ሰዓት እና ዘመን የተሰኘ የግጥም መድብል፣ የብረት ቆሎ የተሰኘ በገነት ጦር ትምህርት ቤት ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን መፅሀፍ ለአንባቢያን ተደራሽ አድርገዋል። ‹‹ቃዘኖ›› የተሰኘውን ልብ ወለድ መፅሀፍን ወደ ፊልም በመቀየር ለእይታ አብቅተዋል። በተጨማሪም ምላጭ እና መርፌ የተሰኘውን የግጥም መድብላቸውን ለህትመት ሳይበቃ ሻምበል ታደሰ ወ/ገብራኤል ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

ሻምበል ታደሰ ወ/ገብራኤል በሰሜን ሸዋ ዞን በኤፍራታ እና ግድም ወረዳ በካራቆሬ ከተማ በኪነጥበብ ሙያ ዘርፍ የተሰማሩ ወጣቶችን በማደራጀት የላቀ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ለማድረግ የበኩላቸውን አስተዋፆ አበርክተዋል። ሻምበል ታደሰ ወ/ገብርኤል የካቲት 3//2015 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ መሳለሚያ ቅዱስ አማኑኤል ቤተክርስቲያን ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት የቀብር ስነስርአታቸው ተፈጽሟል፡፡ ሻምበል ታደሰ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባትና የአንድ የልጅ ልጅ ነበረው፡፡

ስለ ሻምበል ታደሰ ወልደገብርኤል የተሰጡ ምስክርነቶች

ሻምበል ታደሰ ወልደገብርኤልን የቅጂ እና ተዛማጅ መብቶች ትግል በሚደረግበት ጊዜ በቅርበት የማወቅ እድል ነበረኝ፡፡ በእርግጥ ከዚያም ቀደም ብሎ እንተዋወቅ ነበር፡፡ በእኔ እይታ ታዴ የተዋጣለት የግጥምና ዜማ ደራሲ ነበር፡፡ የኪቦርድ የሙዚቃ መሳሪያ ይጫወታል፡፡ የዜማ ድርሰቶቹንም ማህተመ ሀይሌና አሸናፊ ከበደ ተጫውተውታል፡፡በርካታ የዜማ ድርሰቶች በእጁ እንደነበሩ አውቃለሁ፡፡ ግጥም ሲጽፍ ታዴ ፈጽሞ ሀሳብ አያልቅበትም፡፡ የግጥም አጻጻፉም ባህልን መሰረት አድርጎ ነው፡፡ ልቦለዶችንም ገላጭ በሆነ መልኩ የሚጽፍ ነው፡፡ ታዴ ሀገሩን የሚወድ እጅግ አንባቢ ሰው ነው፡፡

ታዴ ሲሰራ የማይደክመው ለታታሪ ባለሙያዎች ተምሳሌት የሚሆን ነው፡፡ እኔ ከእርሱ ብዙ መማር ችያለሁ፡፡ እኔ ታደሰን ቅመሙ ነው የምለው፡፡ ምክንያቱም ሁሉነገርን የማጣፈጥ ችሎታ ስለነበረው ነው፡፡ በባህሪይ ደግሞ ለሰዎች ችግር ደራሽ ነው፡፡ ታዴ ሚስጥር ጠባቂ ነው፡፡ የግለሰብንም ሆነ የሀገር ሚስጥርን ይጠብቃል፡፡ በስራ አለምም ቢሆን ሰርቶ አይጠግብም፡፡ ገንዘብ ኪሱ ካለ ደግሞ ይሄ ሰው አሳዘነኝ ብሎ ያለውን የሚሰጥ ቸር ሰው መሆኑን መመስከር እወዳለሁ፡፡ ፈጣሪ ነፍሱን በገነት ያኑራት፡፡

ትእግስቱ በቀለ / የቅርብ ወዳጅ

ታደሰን ከእነ ቤተሰቦቹ አውቀዋለሁ፡፡ አብሮ አደጎች ነበርን፡፡ ከልጅነት ጀምሮ ህልሙን ለማሳካት የሚጥር ሰው ነበር፡፡ ደግሞም ህልሙን ያሳካ ነበር፡፡ ታዴም ሆነ ቤተሰቡ የጥበብ ፍቅር ያላቸው ናቸው፡፡ ወንድሙ አለማየሁ ፤ እህቱ አዳነችም እና ብርቄ የጥበብ ሰዎች ናቸው፡፡ እና ታዴም ከልጅነቱ ጀምሮ የማስተባበር ችሎታ የነበረው፡፡ ትዝ ይለኛል ድሮ ሬድዮ ይዞ የዘፈን ምርጫ ፕሮግራም ያሰማን እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ጓደኞቹን አስተባብር የእግር ኳስ ቡድን መስርቶ ነበር፡፡ ይህም ከሰው ጋር ያለውን የመግባባት ችሎታ የሚያሳየን ነው፡፡

ሮማን አሰፋ (አብሮ አደግ )

ሻምበል ታደሰ ወ/ገብርኤል የኪነ ጥበብ ባለሙያም፣ወታደርም፣ሐኪምም ነዉ። ሻምበል ታደሰ ወ/ገብርኤልን ከልጅነት እስከ ዕዉቀት በደንብ የማዉቀዉ ተፈጥሮ አብዝታ ለኪነ ጥበብ የቸረችዉ ድንቅ ሰዉ ነዉ። በ1975 ዓም በሆለታ ገነት ጦር ት/ቤት ገብቶ በመሰልጠን ፣ወታደራዊ ዕዉቀትን በመቅሰም የሻምበልነት ማዕረግ ደረጃ ላይ የደረሰ ሲሆን በተጨማሪም ከአያቱ በወረሰዉ የባህል ህክምና ዕውቀት ኢትዮጵያ አዕምሮአዊ ፅ/ቤት የባለቤትነት መብት ተሰጥቶት ብዙዎችን ከህመማቸው ፈውሷል። ሻምበል ታደሰ ወ/ገብርኤል ልብ ወለድ ፅሁፍ ይፅፋል፣ዜማና ግጥም ይደርሳል፣የግጥም መድብልና ለፊልም የሚሆን ስክሪብትን ያዘጋጃል፣ወጣት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችንም አደራጅቶ ይረዳል።በወታደራዊ ሳይንስም የዳበረ ዕውቀት አለው፣በባህል ህክምናውም ዘርፍ የኢትዮጵያ የባህል ሀኪሞች ማኀበር አባል የነበረና ለዘርፉ ከፍተኛ የሆነ አስተዋፅኦ ያበረከተ ሰው ነው። በ2015 ዓም የቀድሞ የፖሊስና የጦር ሰራዊት ማኀበራት ህብረት ዋና ፀሐፊ በመሆን እያገለገለ ሳለ ነበር ህይወቱ በድንገት ያለፈው። ሻምበል ታደሰ ወ/ገብርኤል ማለት ብቃት፤የብቃት ትርጉም ሻምበል ታደሰ ወ/ገብርኤል። ስራዎቹን ሁሉ በጥበብና በብቃት ነበር የሚያከናውነው።

እግዚአብሄር ነፍስህን በገነት ያኑርልኝ።
ቢንያም ዓለማየሁ ወ/ ገብርኤል (ኢንጂነር)

መዝጊያ

ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የመዝገበ-አእምሮ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡ ከ6ወር በፊት ህይወቱ ያለፈው ሻምበል ታደሰ በኖረበት 55 አመታት ውስጥ አቅሙን ሳይቆጥብ ሁለገብ በሆነ መልኩ በጥበቡ አለም ላይ አንድ አሻራ ለማኖር ጥረት አድርጓል፡፡ ይህ ጥረቱ ምናልባት በስፋት ብዙ ሰው ላያውቀው ይችላል፡፡ አጠገቡ ያሉት ግን ምን እንዳደረገ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ስለሚያውቁም ይህ ታሪክ ለትውልድ እንዲቀመጥ አደረጉ፡፡ የእኛም ትልቁ ግብ ላልተዘመረላቸው መዘመር ሲሆን ይህም ቤተሰብን የሚያኮራ ለልጅ እና ለትውልድ የሚቀመጥ ነው፡፡ ባለሙያው ሰርቶ ቢያልፍም ታሪኩ ግን ይቀመጣል፡፡ ምንአልባት ምን ሰርቶ ነበር ቢባል ደግሞ ለእናት ሀገሩ ብዙ መልፋቱን መገመት አያዳግትም፡፡ የእኛ ግብ ይህን ታሪክ ዘመን ተሻጋሪ ማድረግ ነው፡፡ ደግሞም ይሳካል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *