ምርጫ ከጃንሆይ እስከ ብልጽግና

ምርጫ በንጉሱ ጊዜ /ከ1949-1965/

በ1949 በሀገራችን የእንደራሴዎች ምርጫ በሚል ስያሜ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚወክለውን ለመምረጥ እድሉን አግኝቶ ነበር፡፡ በ1964 ለህትመት የበቃውና መብት ምርጫ፣ ሃላፊነት የተሰኘው መጽሄት ላይ እንደሰፈረው ስለ መምረጥና መመረጥ ስለ የጋራ ሃላፊነቶች ፤ እንዲሁም የህዝብ እንደራሴዎች በምክር ቤት ምን ሊሰሩ እንደሚገባ በዝርዝር ሰፍሯል፡፡ ይሄው የዛሬ 49 አመት ለህትመት የበቃ መጽሄት የውድድር ስርአት በሚል ርእስ ፣‹‹ስነ-ስርአትን ማወቅ ለማንኛውም ስራ አፈጻጸም ቀና ይሆናል›› ሲል ሀሳብ አስፍሯል፡፡

በተጨማሪም ለመናገር የተለየህ ሁን ለመስራት የፈጠንክ ሁን ሲል ከወሬ ይልቅ በአድራጎት ማሳየት የተሻለ ነው ሲል ለእንደራሴዎች የሚሆን መልእክት አስፍሮ ነበር፡፡ ምርጫ በሀገራችን የ64 አመት ታሪክ ያለው ሲሆን በተለይ በንጉሱ ጊዜ እንደራሴዎች በመኪና እየዞሩ ቅስቀሳ ያደርጉ ነበር፡፡ ምስላቸውንም እያኖሩ ህዝብን ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ አድርገው ነበር፡፡ በ1957፣ 3ኛው የህዝብ እንደራሴዎች ምርጫ በተደረገ ጊዜ ከመካከለኛው ወረዳ እጩ ሆነው ቀርበው የነበሩት ወይዘሮ ያይኔአበባ ሸዋንግዛው ሴቶች ግዴታቸውን እምብዛም አልተገነዘቡም ብለው ያምናሉ፡፡ ሴቶች በባህል ምክንያት ፊት ለፊት ከመጋፈጥ ይልቅ ከኋላ ሆነው መርዳትን ይመርጣሉ ሲሉ ከዛሬ 56 አመት በፊት ተናግረው ነበር፡፡

‹‹………..የኢትዮጵያ ሴቶች በምክር ቤት ስራ በሰፊው እንዲወከሉ ምኞቴ ነው፡፡ የህዝብ እንደራሴ የሚሆነውን ለመምረጥ ሴቱም ወንዱም በመብቱ መጠቀም አለበት፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ መብቱንና ግዴታውን አውቆ በሃላፊነቱ ከተጠቀመ የሀገር ልማትና እድገት የተደላደለ ይሆናል፡፡ የተማሩ ሴቶችና ወንዶች በምርጫ ስራ በይበልጥ ካልተሳተፉ የተሻሉ የህዝብ እንደራሴዎች ሊገኙ አይችሉም ›› ሲሉ ወይዘሮ ያይኔ አበባ ተናግረው ነበር፡፡

43 ገጽ ያለውና በ1964 ለህትመት የበቃው መጽሄት በዛን ጊዜ ስለነበረው የምርጫ ሁኔታ ዝርዝር ሀሳቦችን አስፍሮ ነበር፡፡ የውድድር ስርአት በሚል ርእስ የቀረበው ጽሁፍ የሚከተለው ሀሳብ ሰፍሮበት ነበር፡፡ ‹‹……ጤናማ ውድድር ለማንኛውም የስራ ክንውን ይመቻል፡፡ የውድድሩን አላማ ሳያውቁና ለይስሙላ የሚወዳደሩ ሁሉ የራሳቸውን ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም እድል ያሰናክላሉ፡፡ የውድድርን ስርአት ጠንቅቆ ማወቁ የሚጠቅመው እጩውን የህዝብ እንደራሴ ብቻ ሳይሆን መራጩንም ጭምር ነው፡፡ ተመራጩ በዲሞክራቲክ ስርአት ለመወዳደር ልበ-ሰፊ መሆን አለበት፤፡ በዱላ በስድብ ስም በማጥፋት የምርጫ ካርዶችን በመጣል መራጮችን ግራ በማጋባት የሚወዳደር እጩ ተመርጦ ምክር ቤት ቢገባም አይጠቅምም፡፡ የተንኮልና የማታለል ልማድ ያለው ሰው በነጻ ውድድር ሊጠቀም አይችልም፡፡ ›› የሚል ሀሳብ መጽሄቱ ላይ ሰፍሮ ነበር፡፡

ምርጫ በደርግ ጊዜ /ከ1979-1983 /

‹‹1979 አዲስ መንግስት የመቋቋም መርሀ ግብር ይዞ መጣ፡፡›› ይላሉ አቶ ገስጥ ተጫኔ ነበር በተሰኘው መጽሀፋቸው ላይ ፡፡ በዛን ጊዜ የኢሰፓና የመንግስት አካላት በሙሉ ሀይላቸውን አሰባስበው መንቀሳቀስ ጀመሩ፡፡ በ17 ምእራፎች ተከፋፍሎ 119 አንቀጾችን ይዞ የተረቀቀው እና የህዝብ አስተያየት የተሰጠበት ረቂቅ ህገ-መንግስት ከወራት መታሸት በኁላ ህዳር 20 1979 በተቋቋመ ኮሚሽን አማካይነት ጥር 24 1979 ውሳኔ ሀሳብ አረፈበት፡፡ የህዝብ እንደራሴዎች ሸንጎ ለመፍጠርም የምርጫ ኮሚሽን ሚያዝያ 14 ቀን 1979 ተቋቋመ፡፡ ይህ ኮሚሽን በዚያ መልኩ ቢቋቋምም የስራውን ሙሉ ሃላፊነት የያዘው ኢሰፓ በመሆኑ ዋናው የስራ ጫና ያረፈው በክልል ፓርቲ ኮሚቴዎች በተለይም በአውራጃና ወረዳ ፓርቲ ኮሚቴዎች ላይ ነበር፡፡

በ1979 የዛሬ 34 አመት የእጩ እንደራሴዎች ቅድመ-ዝግጅት እንደተጠናቀቀ 150000 አባላት ያሏቸው የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴዎች በመላ ሀገሪቱ ተቋቋሙ፡፡ በእነርሱም አማካይነት የምርጫ ጣቢያዎች ተሰናዱ ፡፡ የምርጫ ኮሚሽኑም ቅድመ-ዝግጅቱ ያለቀለትን የእጩ እንደራሴዎች ዝርዝር ተረክቦ አጸደቀው፡፡ የምርጫ አፈጻጸምና የእጩዎች ማስተዋወቂያ መመሪያዎችም አዘጋጀ፡፡ ለእያንዳንዱ እጩ ‹‹ ዝሆን አንበሳና ጎሽ ብሎ የምርጫ ምልክቶችንም አደለ፡፡

ገስጥ ተጫኔ በጻፉት ነበር መጽሀፍ ላይ እንደሰፈረው የእጩዎች ትውውቅ አብቅቶ ምርጫው ሰኔ 7 1979 ከንጋቱ 12 ሰአት እስከ ምሽቱ 12ሰአት ድረስ በመላ ሀገሪቱ ተካሄደ፡፡ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጋዜጠኞችም ሲዘግቡት ዋሉ፡፡
መመረጣቸውን ገና በእጩነታቸው ወቅት ያወቁት ዕጩዎች የህዝብ እንደራሴ መሆናቸውን በካርድ ቆጠራ አረጋገጡ፡፡ በዚህ አይነት ሁኔታ የብሄራዊ ሸንጎ መስራች ጉባኤ ዻግሜ 4 ቀን 1979 አ.ም ተከፈተ ፡፡

ምርጫ በኢህአዴግና-በብልጽግና

የ1987 ዓ.ም. ሀገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ በ1987 ዓ.ም. በሀገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ በሁሉም ክልሎች እና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተከናወነ ሲሆን በአጠቃላይ ሃያ አንድ ሚሊዮን ሦስት መቶ ሰላሣ ሰባት ሺህ ሦስት መቶ ሰባ ዘጠኝ (21,337,379) ሕዝብ ለመራጭነት ተመዝግቧል፡፡ አዲስ አበባ ላይ የተመዘገበው መራጭ ህዝብም 400000 ይጠጋል፡፡ እሁድ ሚያዝያ 29 1987 በተደረገው ምርጫ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምርጫውን የሚታዘቡ 80 ታዛቢዎችን መድቦ ነበር፡፡

በመላው ሀገሪቱ ባሉ 547 የምርጫ ክልሎች ላይ ሃያ ዘጠኝ ሺህ ሁለት መቶ ሃያ አንድ (29,221) የምርጫ ጣቢያዎች ተቋቁመው የነበረ ሲሆን በእነዚህም የምርጫ ጣቢያዎች ለይ ከተመዘገበው መራጭ ውስጥ ሃያ ሚሊዮን ስልሳ ስምንት ሺህ አምስት መቶ አስራ ሦስት መራጮች ድምፃቸውን መስጠት ችለዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎች እና የግል ተወዳዳሪዎችን ጨምሮ አምስት መቶ ሰላሳ ስድስት (536) ወንዶች እንዲሁም አስር (10) ሴቶች የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መቀመጫ ማግኘት ችለዋል፡፡ ከነዚህም መሀከል አስሩ (10) የግል ተወዳዳሪዎች የነበሩ ሲሆን የተቀሩት የፖለቲካ ፓርቲዎችን በመወከል የተወዳደሩ እጩዎች ነበሩ፡፡

የክልል ምክር ቤቶችን በተመለከተም አንድ ሺህ ሶስት መቶ ሃምሳ አምስት (1,355) ወንዶች እና ሰባ ሰባት (77) ሴቶች የክልል ምክር ቤቶችን ምርጫ በማሸነፍ በዘጠኙ ክልሎች ባሉ የክልል ምክር ቤቶች ውስጥ መቀመጫ ማግኘት ችለዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ አርባ ሰባቱ (47) የግል ተወዳዳሪዎች ነበሩ፡፡ በ1987 ሀገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ ላይ በአጠቃላይ አርባ ሶስት (43) የፖለቲካ ድርጅቶች የተወዳደሩ ሲሆን ሃያ አንዱ (21) ድርጅቶች ኢህአዴግ እና አጋር ድርጅቶቹ ነበሩ፡፡ በ1987ቱ ምርጫ ራሳቸውን ለማስተዋወቅ ከተመዘገቡት 238 ተወዳዳሪዎች ውስጥ በአጠቃላይ 1410 ደቂቃዎችን የሚድያ የአየር ሰአት ለመጠቀም ችለዋል፡፡

የ1992 ዓ.ም. ሀገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ

በ1992 ሀገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ በመላው ሀገሪቱ ለመራጭነት የተመዘገቡ ዜጎች ብዛት ሃያ አንድ ሚሊዮን ስድስት መቶ ሃምሣ አምስት ሺህ ሰባት መቶ አምሳ ሁለት (21,655,752) ሲሆን ከዚህም ውስጥ አሥራ ዘጠኝ ሚሊዮን ስድስት መቶ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ሰማንያ ሦስት(19,602,783) መራጮች ድምጻቸውን ሰጥተዋል፡፡ በወቅቱ በአምስት መቶ ሃያ አራት (524) ዞኖች ላይ የተቋቋሙ የምርጫ ጣቢያዎች ብዛት ሃያ ስድስት ሺህ አንድ መቶ አሥራ ሁለት (26,112) ነበር፡፡

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎች ውስጥ ኢህአዴግ በአራቱ የግንባሩ አባል ፓርቲዎች አማካይነት ማለትም ሕወኃት/ኢህአዴግ ሰላሳ ስምንት (38) መቀመጫዎች፣ ኦህዴድ/ኢህአዴግ መቶ ሰባ ስድስት (176) መቀመጫዎችን፣ብአዴን/ኢህአዴግ አንድ መቶ ሃያ አራት (124) ደኢህዴን/ኢህአዴግ ሁለት (2) መቀመጫዎችን ማግኘት ችሏል፡፡ የግል ተወዳዳሪዎች አስራሶስት (13) መቀመጫዎችን ሲያገኙ ቀሪዎቹ መቀመጫዎች በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተይዘዋል፡፡

የክልል ምክር ቤቶች መቀመጫዎች ኢህአዴግ አንድ ሺህ አንድ መቶ ሁለት (1,102) መቀመጫዎችን በሁሉም ክልሎች እና የክልል አስተዳደሮች ሲያገኝ ሃያሰባት (27) የግል ተወዳዳሪዎች በተለያዩ ክልሎች ላይ መቀመጫዎችን ማግኘት ችለዋል፡፡ በ2ኛው ሀገራዊ ምርጫ ለመታዘብ የተገኙ ተንቀሳቃሽ ታዛቢዎች 1697 ሲሆኑ ምርጫውም የተደገረው እሁድ ግንቦት 6 1992 ነበር፡፡

የ1997 ምርጫ

ግንቦት 07 ቀን 1997 ዓ.ም. በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች እና የክልል ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ ላይ ሃያ ስባት ሚሊዮን ሶሰት መቶ ሰባ ሁለት ስምንት መቶ ስማንያ ስምንት (27,372,888) ሰዎች በመራጭነት የተመዘገቡ ሲሆን ከዚህም ውስጥ ሃያ ሁለት ሚሊዮን ስድስት መቶ አስር ሺህ ስድስት መቶ ዘጠና (22,610,690) መራጮች ድምፅ መስጠት ችለዋል፡፡ በዚህም ምርጫ ኢህአዴግ ሶስት መቶ ሃያ ሰባት (327) መቀመጫዎችን ሲያገኝ ቅንጅት ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ አንድ መቶ ዘጠኝ (109) መቀመጫዎችን፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሀይሎች ህብረት ሃምሳ ሁለት (52) መቀመጫዎችን፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ አስራ አንድ (11) መቀመጫዎች ማግኘት ችሏል፡፡ የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች እና ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች የተቀሩትን መቀመጫዎች ማግኘት ችለዋል።

የክልል ምክር ቤቶች ምርጫን በተመለከተም በትግራይ ህወሐት አንድ መቶ ሃምሳ አንድ (151) መቀመጫዎች ሲያገኝ፣ በአፋር አብዴፓ ሰማንያ አራት (84) መቀመጫዎችን በአማራ ክልል ምክር ቤት ብአዴን አንድ መቶ ሰማንያ ሰባት (187) መቀመጫ እንዲሁም ቅንጅት አንድመቶ ሰባት (107) መቀመጫዎችን አግኝተዋል፡፡ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ሶማሌ እና ሀረሪ የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች አብዛኛውን ድምፅ ሲያገኙ ቅንጅት (በሦስቱ ክልሎች ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል እና ሀረሪ ክልሎች) ባሉ ምክር ቤቶች ስድስት (6) መቀመጫዎችን አግኝቷል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ም/ቤት ኢህአዴግ/ኦህዴድ ሶስት መቶ ሰማንያ ሰባት (387) መቀመጫዎችን ኢዴኃን አንድ መቶ አምስት (105) መቀመጫዎችን ኦፌዴን እና ቅንጅት ደግሞ አርባ ሶስት (43) መቀመጫዎችን ማግኘት ችለዋል፡፡ በደቡብ ክልል ምክር ቤትም በተመሳሳይ ደኢህዴን ሁለት መቶ ሰባሁለት (272) መቀመጫዎችን ሲያገኝ ቅንጅት እና ኢዴአህ ሰባ አምስት (75) መቀመጫዎችን አግኝተዋል፡፡ በዚህ ምርጫ197ሺህ የምርጫ አስፈጻሚዎች ሲኖሩ ለ65 የሀገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞችም መታወቂያ ተሰጥቷል፡፡ በዚህ በ3ኛው ምርጫ 1103 የሀገር ውስጥና የውጭ ዜጎች በታዛቢነት የተገኙ ሲሆን 350ሺህ የምርጫ አስፈጻሚዎችም ነበሩ፡፡ አጠቃላይ የምርጫ ጣቢያዎች ብዛትም 36ሺህ ነበር፡፡

የ2002 ዓ.ም. ሀገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ
በግንቦት 15 ቀን 2002 ዓ.ም. በመላው ኢትዮጵያ የተካሄደው አራተኛ (4ተኛ) ዙር ጠቅላላ ምርጫ በሁሉም ክልሎች እና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ተከናውኗል፡፡ በዚህ ምርጫ ስልሳ ሶስት (63) የፖለቲካ ድርጅቶች የተሳተፉ ሲሆን በአጠቃላይ ሁለት ሺህ አንድ መቶ ሰማንያ ስምንት (2,188) ዕጩዎችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሁም አራት ሺህ ሰባት መቶ አርባ ስድስት (4,746) ዕጩዎችን ለክልል ምክር ቤቶች አቅርበዋል፡፡

ከነዚህም በተጨማሪ ለተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ሰላሳ አራት (34) የግል ዕጩዎች በተወዳዳሪነት ቀርበው ነበር፡፡ ለክልል ምክር ቤቶችም እንዲሁ አስራ አንድ (11) የግል ዕጩዎች ለመወዳደር ቀርበው ነበር፡፡ በምርጫው ላይ ለመምረጥ የተመዘገበው የመራጭ ሕዝብ ብዛት ሠላሳ አንድ ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ሃያ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ሃያ (31,926,520) ሲሆን ከዚሁ ውስጥ ድምፅ የሰጠው መራጭ ቁጥር ደግሞ ሃያ ዘጠኝ ሚሊዮን ስምንት መቶ ሠላሳ ሁለት ሺህ አንድ መቶ ዘጠና (29,832,190) ነው፤ በመቶኛ ሲሰላ ከተመዘገበው ሕዝብ ዘጠና ሶስት ነጥብ አራት (93.4%) በመቶ የሚሆነው ተመዝጋቢ ድምፁን መስጠቱን ያሳያል፡፡

በአጠቃላይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ምርጫ በተካሄደባቸው አምስት መቶ አርባ ሰባት (547) የምርጫ ክልሎች፣ ኢህአዴግ በአራቱ የግንባሩ ድርጅቶች እና አጋር ድርጅቶች በኩል ዘጠና ዘጠኝ ነጥብ ስድስት (99.6%) በመቶ መቀመጫዎች አግኝቷል፡፡ ቀሪው በአንድ ፓርቲ ተወካይ እና በግል ተወዳዳሪ ተይዟል፡፡

የክልል ምክር ቤቶችን በተመለከተ ኢህአዴግ እና አጋር ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ መቀመጫዎችን አግኝተዋል፡፡ በምርጫው ውስጥ የነበረ የሴቶች ተሳትፎን በተመለከተ ድምፅ ከሰጠው ህጋዊ መራጭ ውስጥ አርባ ሰባት ነጥብ ስድስት (47.6%) በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ሲሆኑ ከቀረቡት ዕጩዎች መካከል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስራሁለት ነጥብ አራት (12.4%) በመቶ እንዲሁም ለክልል ምክር ቤት ምርጫ አስራ አምስት ነጥብ ሶስት (15.3%) በመቶዎች ሴቶች ነበሩ፡፡

በዚህ ምርጫ 220ሺህ የምርጫ አስፈጻሚዎች ተሰማርተው የነበረ ሲሆን በአንድ የምርጫ ጣቢያም 1000 ሰው እንዲመርጥ ተደርጓል፡፡ የዛሬ 11 አመት በ2002 በተደረገው ምርጫ መንግስት 38ሚሊዮን ብር በጀት መድቦ ነበር፡፡ በ2002ቱ ምርጫ ፓርቲዎች 90 ሰአት በቲቪ 95 ሰአት በሬድዮ ወስደው መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ 849 የጋዜጣ አምድም አግኝተው ነበር፡፡ ምርጫውንም እንዲታዘቡ ከ850 በላይ ለሚሆኑ ጋዜጠኞች የእውቅና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡40ሺህ ታዛቢዎችም ነበሩ፡፡

የ2007 ዓ.ም. ሀገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ

ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. በመላው ኢትዮጵያ በተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ሠላሳ ስድስት ሚሊዮን ስምንት መቶ ሃምሳ አንድ ሺህ አራት መቶ ስልሳ አንድ (36,851,461) ሕዝብ በመራጭነት የተመዘገበ ሲሆን ከዚህም ውስጥ ሠላሳ አራት ሚሊዮን ሦስት መቶ ሃምሳ አንድ ሺህ አራት መቶ አርባ አራት (34,351,444) ወይም በመቶኛ ሲሰላ ዘጠና ሶስት ነጥብ ሁለት (93.2%) የሚሆነው ህዝብ ድምፅ ሰጥቷል፡፡

በዚሁ ምርጫ ላይ የተወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብዛት 58 ሲሆን በእነዚህ ፓርቲዎች አማካይነት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንድ ሺህ ስምንት መቶ ሃያ ስምነት (1,828) ዕጩዎች እንዲሁም ለክልል ምክር ቤቶች ሶስት ሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና አንድ (3,991) ዕጩዎች ቀርበዋል፡፡ በተጨማሪም በግል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዘጠኝ (9) እና ለክልል ምክር ቤቶች ሶስት (3) ዕጩዎች ቀርበዋል፡፡

በዚህ ምርጫ ላይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጠቅላላው ሃምሳ ሁለት (52) የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ዘጠኝ (9) የግል ዕጩዎች ተካፍለዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ኢህአዴግ አምስት መቶ (500) ወንበሮችን ማለትም በመቶኛ ሲሰላ ሰማንያ ሁለት ነጥብ አራት (82.4%) ያገኘ ሲሆን ከነዚህም መካከል ሁለት መቶ አስራ ሁለቱ (212) ወይም በመቶኛ ሲሰላ ሰላሳ ስምንት ነጥብ ስምንቶቹ (38.8%) ሴቶች ናቸው፡፡

የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች የተቀሩትን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበሮችን አግኝተዋል፡፡ የክልል ምክር ቤቶችን በተመለከተም ኢህአዴግ እና የተለያዩ አጋር ድርጅቶች ሁሉንም መቀመጫዎችን ያገኙ ሲሆን ለክልል ምክር ቤቶች መቀመጫ ካገኙ ዕጩዎች መካከል ስምንት መቶ (800) ወይም በመቶኛ አርባ ነጥብ ሶስት (40.3%) የሚሆኑት ሴቶች ናቸው፡፡ በሀገሪቱ ለዚህ ምርጫ ተብሎ 44454 ጣቢያዎች የተከፈቱ ሲሆን 250000 ታዛቢዎችም ነበሩ፡፡ ለፖለቲካ ፓርቲዎችም 56ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብር የፋይናንስ ድጋፍ ተደርጎ ነበር፡፡

6ኛው ምርጫ

ዘንድሮ ሰኞ በሰኔ 14 2013 በሚደረገው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር 38ነጥብ 2 ነው፡፡ በዚህ ምርጫ ላይ 1804 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ያሉ ሲሆን 547 የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት መቀመጫዎች እንዳሉ ታውቋል፡፡ በዚህ ምርጫ 46 የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸውን ያዘጋጁ ሲሆን 148 የግል እጩዎች 17 አገራዊ ፓርቲዎች እንዲሁም 29 ክልላዊ ፓርቲዎች የሚሳተፉ ሲሆን 18 ፓርቲዎች ይወዳደራሉ ፡፡ በመላ ሀገሪቱ 637 የምርጫ ክልሎች ያሉ ሲሆን 48000 በላይ የምርጫ ጣቢያዎች አሉ፡፡

በ2013ቱ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ አጠቃላይ የእጩዎች ብዛት 9505 ሲሆን በተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩ እጩዎች ብዛት 99 ነው፡፡ በግል የሚወዳደሩ ደግሞ 148 ናቸው፡፡ በዚህ ምርጫ አጠቃላይ የሴት እጩዎች ብዛት 1987 ነበር፡፡ በዚህ የ2013 ምርጫ ለ68 የሚድያ ተቋማት እውቅና የተሠጠ ሲሆን ከ1400 በላይ ጋዜጠኞች የምርጫ ዘገባ ፈቃድ ወስደዋል፡፡ 46000 በላይ ታዛቢዎችም ይተኛሉ፡፡
ም ንጭ- አዲስ ዘመን ከ1987-2007
የምርጫ ቦርድ ድረ-ገጽ
መብትና ምርጫ ሃላፊነት መጽሄት 1964
ነበር ክፍል 2 በገስጥ ተጫኔ ከገጽ104-121

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *