ም/ኮ ብርቄ ወ/ገብርኤል

ም/ኮ ብርቄ ወ/ገብርኤል

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን፣ በቅርቡ ክምችተ-እውቀት / ኢንሳይክሎፒዲያ / በሚል ርእስ የሚድያ እና የኮሚኒኬሽን ባለሙያዎችን ታሪክ በጠንካራ ሽፋን መጽሀፍ አሳትሞ ያስመርቃል፡፡ ታሪካቸው በመጽሀፉ ውስጥ ከሚሰነድላቸው አሻራ ካኖሩ የሚድያ ሰዎች አንዷ ደግሞ ምክትል ኮማንደር ብርቄ ወልደገብርኤል ናት፡፡ ም/ኮ ብርቄ በተለይ በፖሊስና ህብረተሰብ ፕሮግራም መሰናዶዎቿ እውቅና አግኝታለች፡፡ ታሪኳ እንደሚከተለው ተሰናድቷል፡፡

ጋዜጠኛ ም/ኮ ብርቄ ወ/ገብርኤል በሰሜን ሸዋ ዞን ቀደም ሲል ይፈትና ጥሙጋ ተብሎ በሚጠራው አነስተኛ በሆነችው ካራቆሬ ከተማ ውስጥ ጌሸ ተራ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ሚያዝያ 27/1948 ዓ.ም ተወለደች፡፡ አባቷ አቶ ወ/ገብርኤል ገ/ማርያም እናቷ ወ/ሮ ፋና አንባው ይባላሉ፡፡ አባቷ የተወለዱት በጉራጌ ዞን እዣ ወረደ ሻም ጊዮርጊስ በተባለው ስፍራ ነው፡፡ እናቷ ወ/ሮ ፋና አንባው እዛው ሰሜን ሸዋ ገምዛ ከተባለች የገጠር ከተማ ነው የተወለዱት፡፡

ብርቄ ለወላጆቿ 3ኛ ልጅ ናት፡፡ እድሜዋ 5 አመት ሲሞላ እዛው ካራቆሬ ከተማ መርእድ አዝማች ወሰን ሰገድ አስፋው ወሰን ት/ቤት ገባች፡፡ 4ኛ ክፍል እያለች አባቷ አቶ ወ/ገብርኤል በድንገተኛ ህመም አረፉ፡፡ 5ኛ ክፍል እያለች ገና በ13 ዓመቷ በአካባቢው ባህል መሠረት ተዳረች፡፡የአንድ ወንድና የሁለት ሴቶች ልጆች እናትም ሆነች፡፡ አሁን ሰባት የልጅ ልጆች አግኝታለች፡፡

ባለቤቷ መምህር ስለነበሩ ከካራቆሬ ተዛውረው አጣዬ፣ ደብረሲና፣ ሰንዳፋ፣ በመጨረሻም አዲስ አበባ ተዛዋውረው ሲሄዱ ጋዜጠኛ ብርቄም አብራ ተጉዛ ነበር፡፡ መማር እየፈለገች ልትማር ባለመቻሏ ከባለቤቷ ጋር ዘወትር ሸምግልና ላይ ይቀመጡ ነበር፡፡ በኃላም ባለቤቷ መማሯን ፈቀዱ፡፡ ደብረሲና በነበሩበት ወቅት የማታ በመማር ከ5-8ኛ ክፍል ተምራ በሚኒስትሪ ፈተና 98.4 ውጤት በማምጣቷ የመማር ፍላጎቷ ጨመረ፡፡ በመቀጠል ሰንዳፋ ተዛውረው ሲመጡ ጅማ ሰንበቴ ት/ቤት 9ኛ ክፍል ቀን ከመደበኛ ተማሪዎች ጋር መማር ጀመረች፡፡ በመሃከሉ ሁለተኛ ልጇን በመፀነሷ አቋረጠች፡፡

ለመማር ባላት ፍላጎት በሴትነቷ የደረሰባትን ችግር ተጋፍጣ እየተናነቀች ባል አግብቶ መማር በአካባቢው ባህል እንደነውር ስለሚቆጠር የሚያደርሱባትን የሞራል ጫና ተቋቁማ ልጅ እያሳደገች ስራም ከተቀጠረች በኃላ እየሰራች ትምህርትና የትዳር ጊዜዋን በችግር ነበር ያሳለፈችው፡፡

አዲስ አበባ ተዛውረው ከመጡ በኃላ ዳግማዊ ሚኒሊክ ት/ቤት በማታው ክፍለ ጊዜ 9ኛ ክፍል ተመዝግባ መማር ቀጠለች፡፡ በመሃከሉ ትምህርትሽን አቁሚና ልጆችሸን ያዢ ሠራተኛም መቅጠር አያስፈልገንም በሚል ተጋጩ፡፡ ብርቄም ትምህርቴን አላቋርጥም በማለቷ ግጭቱ ከረረ፡፡ ባልና ሚስት ተለያዩ፡፡ ልጆች በአባታቸው እጅ ቀሩ፡፡ ብርቄም ኮልፌ ከሚኖሩት አጎቷ ሻ/ባሻ ተረፈ አንባው ቤት ተጠግታ እየኖረች ኮልፌ ጳውሎስ ት/ቤት ተመዝግባ መማር ቀጠለች፡፡ በመሃከሉ መምህሩ ባለቤቷ ቀበሌ ተመርጠው ይሰሩ ስለነበር በወቅቱ የፖለቲካ ችግር ተገደሉ፡፡ ልጆቿንም ማሳደግ ባለመቻሏ ወላጅ እናቷ ጋር ወስዳ እንዲያሳድጉላት ተደረገ፡፡

ጋዜጠኛ ም/ኮ ብርቄ ወ/ገብርኤል 1ኛ ደረጃ ት/ቤት በምትማርበት ወቅት በት/ቤቱ ውስጥ የሙዚቃና ድራማ ክፍለ ጊዜ ስለነበር በየሳምንቱ ለተማሪዎች መዝሙርና ድራማ ታቀርብ ነበር፡፡ ግጥሞች አጫጭር ልብ ወለድ ታሪኮች እየፃፈች ሰኔ 30 ት/ቤት ሲዘጋ ለወላጆች ቀን ተወዳዳሪ ሆና ታቀርብ ነበር፡፡ በስራዎቹም ተሸላሚ ናት፡፡ በዛን ወቅት መምህራኖች ያበረታቷት ነበር፡፡ አልፎ አልፎም ለጓደኞቿ አጫጭር ታሪኮችን እየፃፈች በእረፍት ሰዓት ታዝናናቸዋለች፡፡ ማታ ማታም ለቤተሰቦቿ ሲሰበሰቡ ታነብላቸዋለች፡፡ በፃፈችው ነገር ሲስቁ ሲዝናኑ ማየት የበለጠ ያበረታታት ነበር፡፡

ጳውሎስ ት/ቤት ከፖሊስ ማሰልጠኛው ፈጥኖ ደራሸ ካምፕ አጠገብ ነበርና 10ኛ ክፍል እንደጨረሰች የፖሊስ ቀጠራ ማስታወቂያ ወጥቶ ስለነበር ትምህርቷን ትታ ለመቀጠርና ልጆቿንና ቤተሰቧን ለመርዳት ወሰነች፡፡ ታናሽ እህቷ አርቲስት አዳነች ወ/ገብርኤልን ጨምራ ለቀጠራው ተመዘገቡ፡፡ የተሰጣቸውንም ፈተና አልፈው በሙዚቀኝነት ተቀጥረው በ1967 ዓ.ም ስራ ጀመሩ፡፡

በ1968 ዓ.ም ላይ ኤርትራ ፖሊስ ሙዚቃ ክፍል ሙያተኛ ይፈልግ ስለነበር ወደ ኤርትራ መዛወሯ ለብርቄ ይገለፅላታል፡፡ ዝውውሩን ተቃውማ ለፖሊስ ጠ/መምሪያ አመለከተች፡፡ እህቷ አዳነችና ሌሎች አስመራ ሄዱ፡፡ ብርቄ ግን አዲስ አበባ ፖሊስ ሆስፒታል ተመደበች፡፡

በ1969 ዓ.ም ፖሊስ ሬዲዩ ፕሮግራም ሊጀምር ስለሆነ የስነፅሁፍ ችሎታ ያላችሁ የትምህርት ደረጃ ከ10ኛ ክፍል በላይ የሚል ማስታወቂያ ወጣ፡፡ ብርቄም ከመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ህልሟ ልትገናኝ ሆነ፡፡ ፍላጎቷ ከፍተኛ ስለነበር የመጀመሪያዋ ተመዝጋቢ ሆና የተሰጣትን የስነፅሁፍ ፈተናና በድምፅና በአነባበብ ዘዴዋ በአንደኝነት አልፋ በሬድዮ ጋዜጠኝነት በ 1969 ህዳር ወር ላይ ኢትዮጵያ ሬድዮ ለ3 ወር ስልጠና ገባች፡፡

ስልጠናው በእነ አቶ ማእረጉ በዛብህ፣ በእነ ወ/ሮ አለሚቱ፣ በእነ አቶ ታደሰ ሙሉነህ በእነ አቶ ጌታቸው ኃ/ማርያምና አቶ ሙሉጌታ ሉሌ በአቶ ተክሉ ታቦርና በሌሎችም፣ ዜና ምንድን ነው? ዜና እንዴት ይዘጋባል? ዜና ከየት ይገኛል? ዜናና የዜና ሐተታ ልዩነት ስለትረካ አፃፃፍና አዘጋገብ ስለአነባበብ ስልትና የጋዜጠኝነት ስነ-ምግባርና ሌሎች በርካታ ርዕሶች ላይ እንድንማር እንድንወያይ እንድንዘግብና እንድናነብ የሙከራ ስልጠና ተሰጥቶን በቀጥታ ወደ ስራ ገባን ትላለች ጋዜጠኛ ብርቄ ወ/ገብርኤል፡፡

በስልጠናው ላይ የሬዲዮ ክፍሉ ኃላፊ ሆነው የተመደቡት ሻለቃ ተዘራ ብርሃኑ ከፖሊስ ሙዚቃና ቲያትር ክፍል ሌ/ኮ ግርማ ኃይሌና አቶ ካሳሁን ገርማም የአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን አባትና ሌሎችም ለሬዲዮ ጋዜጠኝነት የተመለመሉ አባላት ነበሩ፡፡ ከሁሉም ብርቄ በቀዳሚነት በድምጽ የአነባበብ ዘዴና ቃና ተመርጣ ከጥሩ ምስጋና ጋር በሰርተፍኬት ስልጠናውን አጠናቀቀች፡፡

ስልጠናውን በወሰዱ ጋዜጠኞች የፖሊስና ህብረተሰብ ፕሮግራም መሰናዳት ጀመረ፡፡ ጥቆማ ለአድማጮችና ጥቆማ ከአድማጮች የተሰኘ በወንጀል ጉዳዮች ዙሪያ የሚዘጋጅ አዝናኝና አስተማሪ ፕሮግራም ለአድማጭ መድረስ ጀመረ፡፡ እንዲሁም የትራፊክ ደህንነት ዝግጅት ዜናን አካቶ ስርጭቱ ህዳር ወር መጨረሻ 1969 ተጀመረ፡፡

መሰናዶው ከጊዜ ወደ ጊዜ በአድማጭ ዘንድ ተወዳጅና ተመራጭ ሆኖ የምርመራ ማህበር በተሰኘው ዝግጅት በትረካ ብርቄና ካሳሁን ገርማሞ ኮከብ ሆነው ታዩ፡፡ በየጊዜው የዝግጅቱ አድማስ እየሰፋ ሲሄድ ከጣቢያዎቻችን የተሰኘው የብርቄ ወ/ገብርኤል ዝግጅት ሌላው ምርጥና ተፈላጊ ነበር፡፡ ለጥንቃቄ የተሰኘው ዝግጅትም ለህብረተሰቡ የሌቦችን የአሰራረቅ ዘዴ የሚጠቁምና የሚያስጠነቅቅ ሆኖ በሪፖርት እና በድራማ መልክ የሚቀርብ ስለነበር ይህም ለብርቄ ከፍተኛ እውቅና አስገኘ፡፡ በአጠቃላይ የዝግጅት ክፍሉ ስራ በቡድን የሚከናወን ስለነበር የሁሉም ውጤት የላቀ ነበር፡፡ ሆኖም ስራዋ ሁሉ አልጋ ባልጋ አልነበረም፡፡ አንድ ወቅት የዋቢ ሸበሌ ሆቴል አስተዳደር አንድ ታይፒስት ለመቅጠር በጋዜጣ ማስታወቂያ ያወጣና ተወዳዳሪዎች እንዲቀርቡ ይደረጋል፡፡ በዚህ መሠረት ስራ ፈላጊዎች የትምህርትና የሙያ ማስረጃቸውን ይዘው በመቅረብ ይመዘገባሉ፡፡ መመዘኛውን ያሟሉ ለፈተና እንዲቀርቡ ይደረጋል፡፡

ፈተናው ሙያነክ በመሆኑ ከሆቴሉ ጋር በተደረገ ስምምነት የአሁኑ የንግድ ስራ ኮሌጅ እንዲፈትን ይደርጋል፡፡ ከፈተናው በኃላ ውጤቱ ለሆቴሉ አስተዳደር ይላካል፡፡ የተላከው ውጤት እንደማይሆን ይገለበጥና አንድ የቀድሞ ባለስልጣን ሚስት እህት እንድታልፍ ይደረጋል፡፡ አላስፈላጊውን የቅጥር ፎርም አሟልታ ስራውን ትጀምራለች፡፡ በማለፌ አልጠራጠርም ያለች ተፈታኝ ማመልከቻ ይዛ ፈተናው እንደገና እንዲታረም ለሆቴሉ አቤት ትላለች፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድ በኃላ ፈተናው እንደገና ሲመረመር አመልካቿ በአንደኝነት እንዳለፈች ይደረስበታል፡፡ በውጤቷ መሠረት ለመቀጠር ብትጠይቅ አይሆንም ትባላለች፡፡ መብቷን ለማስከበር ድርጅቱን ትከስና በፍ/ቤት አቁማ በውጤቱ መሠረት እንድትቀጠር ታስወስናለች፡፡

‹‹ይህ ጉዳይ በፖሊስና ህብረተሰብ ሬዲዮ ፕሮግራም ላይ እንዲሰራ በክፍሉ ኃላፊ ታዝዤ ግራና ቀኙን በማነጋገር አቀነባብሬ ለአየር በማብቃቴ የፕሮግራሙ ዋና አዘጋጅና እኔ ተጠርተን በኃላፊዎች ዘንድ ባለስልጣኑን አሳቅላችኋል በማለት ለሰዓታት ታስረን በወቀሳ ተለቀናል፡፡ ያን ጊዜ ታዲያ ሻለቃ ተዘራ ዋና አዘጋጁ ለዳግመኛው እንዲህ አይነት ዝግጅት እንዳናቀርብ የባለስልጣናት ቤተሰቦች ስም ዝርዝር ቢሰጠን እነሱን እየለየን ስራችንን ለመስራት ያመቸናል በማለታቸው የክስ ቻርጅ ተሞልቶ በማህደራቸው እንዲታሰር ተደርጓል፡፡ በስራችን ብዙ ስቃይና እንግልት ደርሶብናል ብዘረዝረው አያልቅም፡፡ ትላለች፡፡

የሬዲዮ ፕሮግራሙ እያደገ መሄድ የቴሌቪዥን የአየር ሰዓት እንዲገኝ እድል ከፈተ፡፡ የወቅቱ የቴሌቪዥን ዝግጅት ክፍል ኃላፊ ሻ/ል ግዛው ዳኜ ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ፕሮግራሙ ተጀመረ፡፡

የቴሌቪዥን ፕሮግራሙም እጅግ ተወዳዳሪ ሆነ፡፡ በርካታ ስራዎችን በማቅረብ ታወቀ፡፡ የሚተላለፉ የወንጀል ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው የበዓል ዝግጅቱ ምርጥና የተለየ ነበር፡፡ ይህ በህዝብ ዘንድ ትውስታው አሁንም ድረስ አለ፡፡

ጋዜጠኛ ም/ኮ ብርቄ በፖሊስና ህብረተሰብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ለ31አመታት ከ1969-1999 በሙያው ላይ ከፍተኛ የስራ ልምድ በማካበቷና ተወደዳሪና ጠንካራ ሠራተኛ በመሆን ጎን ለጎንም ለሙያ ስራዋ እገዛ የሚያደርግላትን የሕግ ትምህርት በቅድስት ማርያም ዩንቨርሲቲ ኮሌጅ በመማሯ ለፖሊስ የወንጀል ነክ ዝግጅቶች ብቃት ያላት በመሆኗ የተወችው አሻራ አሁንም ጎልቶ ይታያል፡፡

ብርቄ በጋዜጠኝነት ስራ ብትታወቅም ሰዎች ሲበደሉና ሲቸገሩ አይታ የማታልፍ የሰዎች መብት ሲጣስ ወይም አስታዋሽ ሲያጣ አይመለከተኝም ሳትል ለቁጥር የማይመቹ ብዙ ስራዎችን ሰርታለች ለምሳሌ ያህል

  1. በፌ/ፖሊስ ውስጥ የሴቶች ጉዳይ ቢሮ እንዲከፈት ኃላፊም እንዲመደብ
  2. መደበኛ ነባር ሴት ፖሊሶች ኮሌጅ ገብተው ስልጠና አግኝተውና በማዕረግ ተመርቀው ለመውጣት እድሉ ስላልነበራቸው የመግቢያ ነጥብ ተስተካክሎ ለስልጠና እንዲገቡ
  3. ቀጥታ ከት/ቤት ፖሊስ ኮሌጅ ለመግባት ለሴቶች እድሉ ዝግ የነበረውን በወቅቱ የነበሩ ሃላፊዎች ሃሳቡን ደግፈውና ራሳቸው ጥረት አድርገው ሴቶች በእኩል የመሳተፍ መብታቸው ተጠቃሚ እንዱሆኑ
  4. የተቸገሩ እናት አባት የሌላቸው ህፃናት ድጋፍ እንዲያገኙና እርዳታ ድርጅቶች እንዲረዷቸው
  5. ከእርዳታ ድርጅት አገር ውስጥ ለማደጎ የተሰጡ ልጆችን አስተዳደግና ሁኔታ በማጥናት ህጋዊ መብት እንዲኖራቸው ጥረት አድርጋ ውጤታማ ሆናለች፡፡ በሬድዮ ክፍል ውስጥ ከሪፖርተርነት እስከ ዋና አዘጋጅነት በኋላም የሶስቱም የሚዲያ ክፍሎች ሬድዮ ቴሌቪዠንና ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልን በሚዲያ አስተባባሪነት ኃላፊ ሆና ከ1988-1999 በመምራት ሰርታለች፡፡

በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ስርአት በሙያ ስራዋ ምክንያት ህግ በማስከበሯና በማክበሯ ብዙ ችግሮችን ተጋፍጣለች፡፡ በህይወቷ አደገኛ ሁኔታ በማየቷ በቅድሚያ ከሙያ ስራዋ መራቅ ስለፈለገች በተማረችው የህግ ትምህርት መስራት ስለወሰነች ወደ ፌደራል ፖሊስ ህግ አገልግሎት እንድትዘዋወር ጠይቃ ጥቂት ጊዜ በነገረፈጅነት ከሰራች በኋላ በራሷ ፍቃድ በጡረታ እንድትሰናበት ጠይቃ 2001 ዓ.ም ሐምሌ መጨረሻ ስራዋን ትታ ወጥታለች፡፡

ከስራ ከወጣች ቡኋላ በF.M ሬድዮ የአየር ሰአት አስፈቅዳ አፍርሳታ የተሰኘ ፕሮግራም ጥሩ ጥሩ ሙያተኞች ይዛ እየሰራች ፕሮግራሙ ምርጥና ተወዳዳሪ ሆኖ ሳለ ችግሩን እዚህ ላይ ለመዘርዘር አስፈላጊ ስላልሆነ በደፈናው እንድትሰራ ስላልተፈለገ ትንቅንቁ ከፍተኛ በመሆኑና ዛቻው ስለበዛባት ፕሮግራሙን ለ 5 ወር ከሰራች በኋላ አቋረጠች፡፡

ጋዜጠኛ ብርቄ ከሙያዋ ላለመራቅ በኢሳት ሬድዮ ፕሮግራም አልፎ አልፎ ወቅታዊ የሪፖርት ስራዎችንና ታሪካዊ መጣጥፎችን በመላክ ትሰራ ነበር፡፡ በኋላ ላይ የወቅቱን የፖለቲካ ችግር በመሸሽ አቋረጠች፡፡ የጋዜጠኝነት ስራዋንም ተወች፡፡

ም/ኮ/ር ብርቄ በአሁኑ ሰአት በደረሰባት ተደራራቢ ችግርና በስራ ምክንያት ለፊልድ ስራ ስትወጣ ልጆችዋን ለዘመድ ለጎረቤትና ለቤት ሠራተኛ እየተወች ለረጅም ዘመን ያልተንከባከበቻቸው፣ የእናት ፍቅሯን በአግባቡ ያልሰጠቻቸው ተቸግራና ተወጣጥራ ያሳደገቻቸው ሁለት ሴትና አንድ ወንድ ልጇ የሚኖሩት ውጭ አገር በመሆኑ በተደጋጋሚ ጊዜ ጣልያንና አሜሪካን ጎብኝታለች፡፡ በግሏም እስራኤልንና ግብፅን የመጎብኘት እድል አግኝታለች፡፡

ብርቄ ምንድን ነው የምትወደውና የምትጠላው ለምትሉ የምትወደው ተፈጥሯዊ የሆኑ ለም ቦታዎች ወንዞች ፏፏቴዎች ባሉበት ዘና ማለት ትወዳለች፡፡ ይህ በሌለበት በቤቷ ውስጥ መፅሀፍ ማንበብ ቤቱን ማዘጋጀት ማፅዳትና ስፖርት መስረት ትወዳለች፡፡ የምትጠላው ለምትሉ ድብቅ ውሸታም አስመሳይ ለሰዎች ያለው አመለካከት ዝቅ ያለ አይመቸኝም ትላለች፡፡

የመዝጊያ ሀሳብ

ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የኢንሳይክሎፒዲያ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡ በብዙዎች ስለሚወደደው ፖሊስና ህብረተሰብ የሬድዮና የቲቪ መሰናዶ ስናስብ ብርቄን አብረን እናስባለን፡፡ ምክትል ኮማንደር ብርቄ ከብዙዎች ህሊና አትጠፋም፡፡ ለሙያዋም የተለየ አክብሮት ያዳበረች ታላቅ ባለሙያ ናት፡፡ በአንድ በኩል ፖሊስ ደግሞ በሌላ ጋዜጠኛ፡፡ ይህች ብርቅ እናት ፤ እንደስሟ ብርቅ ስትሆን በሙያዋ አጋሮቿም በበጎ ትነሳለች፡፡ በተለይ የፖሊስና ህብተተሰብ ፕሮግራም ተጀምሮ ጥሩ ቁመና ላይ እንዲደርስ ካደረጉት ቀዳሚዋ ናት፡፡ ቀዳሚ በመሆን ብቻ ሳይሆን ለሙያዋ እጅግ ታማኝ በመሆን ያገለገለች ስለመሆኗ በስፋት ይነገራል፡፡ ብርቄ ብቻ ሳትሆን ስለ ፖሊስና ህብረተሰብ መሰናዶ ሲነሳ ሻምበል ግዛው ዳኜን የመሰሉ አይተኬ ሰዎችን እናገኛለን፡፡ እነዚህ ሰዎች ምን ሰሩ? ስንት አመት አገለገሉ ?ብለን ብንጠይቅ መልሱ በቀላሉ የሚገኝ አይሆንም፡፡ ቀድሞ በወጉ ያተጻፈና ያልተሰነደ ዛሬ ከወደየትም አይገኝ፡፡ ብርቄ እና አብረዋት ፖሊስና ህብረተሰብ ፕሮግራምን የሰሩ ባለመያዎች ምንጊዜም የማይረሱና ለኢትዮጵያ መልካም ውለታ የዋሉ ናቸው፡፡ እናም ስለእነዚህ ወርቅ የሀገር ሀብቶች ብናወራ በጣም መልካም የሚሆን ይመስለናል፡፡ ብርቄ ግን ብርቅ ናት፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *