ሀብታሙ አሰፋ ስሜ
የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡
በ tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡ በሚድያ ዘርፍ በተለይም ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎች በሚያጋጥምብት የግሉ ሚዲያ ዘርፍ ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ ያሳልፈው የጋዜጠኛ ሀብታሙ አሰፋን ታሪክ ዛሬ እንዘክራለን፡፡
ውልደትና የትምህርት ሁኔታ
ሀብታሙ አሰፋ ስሜ ተወልዶ ያደገው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ 22 ማዞሪያ በቀድሞ አጠራር አሥመራ መንገድ የሚባለው አካባቢ በጊዜው ቀበሌ 11 ነበር ።በሰፈሩ በኮስታራነታቸውም ከአደገ ሲያስተውለው ለትምህርት ትልቅ ግምት ይሰጡ የነበሩት ሁሉም ልጆች ጋሽ ዘውዱ የሚሉዋቸው የቄስ ትምህርት መምህር ነበሩ፡፡ ሀብታሙም እዚያ ነበር የተማረው፡፡ በጊዜው ቄስ ትምህርት ቤት ለከተማ ልጆችም ብቸኛ ትምህርት የመገብያ አንዱ መንገድ ነበር፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን መገናኛ በላይ የካ ተራራ አንደኛ ደረጃ ተምሯል። ስድስተኛ ክፍል እንግሊዝ ኤምባሲ አጥር ጋር የሚዋሰነው ራስ አባተ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ቤት ተከታትሏል።ከ7ኛ እስከ 12ኛ ድረስ ኮከብ ጽባሕ ተከታትሏል።
ኮከበ ጽባሕ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ ወደ ጋዜጠኝነት ዝንባሌው አጋደለ።በጊዜው ኮከበ ጽባሕ የቴአትር፣የስፖርት ክበብ ነበረው። ቴአትር ይሰራ ነበር፣ የጠረጴዛ ቴኒስም ለትምህርት ቤቱ ተጫውቷል። የቅርጫት ኳሱንም ሞክሮት እዚያው ኮከበ ጽባሕ ትቶታል።አልገፋበትም።የጋዜጠኝነት ሙያው ግን ዛሬም አለ።
የኮኮብ ጽባሕ ሚኒ ሚዲያን ለአራት ዓመታት ያለማቋረጥ አገልግሎአል።የሙያው ጅማሮ የተለያዩ ፕሮግራሞችን በተማሪዎች የእረፍት ሰዓት ከማቅረብ ጀምሮ የሚኒ ሚዲያው ኃላፊም ሆኖ ሌሎች ተማሪ ባልደረቦቹን የተለያዩ ፕሮግራሞችን በጋራ ሰርተው ያቀርቡ ነበር።ያ ጊዜ የበለጠ የጋዜጠኝነቱን ሙያ ዝንባሌውን አጠናክሮለታል።ልጅ ሆኖ መርማሪ ብጤ መሆን ይመኝ ነበር። ይህ ዝንባሌ እንደዋዛ የመጣ ሳይሆን ከማንበብ ፍላጎቱ ጋር አብሮ ያደገ ነበር፡፡ የወንጀል ታሪኮችን ሲያነብ መርማሪ ሆኖ ወንጀለኛን መያዝ ይመኝ ነበር። ከንባብ ዝንባሌው ባሻገርም ከትምህርት ቤቱም ውጭ በዕሁድ የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ በጊዜው የሚሰማውን ስሜትበአጫጭር ጽሑፎች ይገልጽ ነበር።አልፎ አልፎ ይደመጡልኝ ነበር ሲልም ጊዜውን ያስታውሳል።ለመጀመሪያ ጊዜ ጽፎ የላከው ጽሑፍ «ሶስተኛው ሰው» የሚል እንደነበር ያስታውሳል።
በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ በቋንቋና ሥነ ጽሑፍ በ1990 ዓ.ም ተመርቋል። ከዚያ በኋላ ከጋዜጠኝነት ጋር የተያያዙ የተለያዩ አጫጭር ኮርሶችን በአገር ቤት ወስዷል።በተለይ የአሜሪካ ኤምባሲ የኢንፎርሜሽን ክፍል(USIS) በጊዜው የተለያዩ መምህራንን ከአሜሪካና ከተለያዩ አፍሪካ አገራት ዩኒቨርስቲዎች እያስመጡ ይሰጡዋቸው የነበሩ የአጫጭር ጌዜ ሥልጠኛዎችን ብዙዎቹን ሀብታሙ ወስዷል።ከዚያ ሥልጠና እጅግ ጠቃሚ ነገር አግኝቻለሁ፡ ሲል ዛሬም ያስታውሰዋል። ከመሰረታዊ ጋዜጠኝነት እስከ የምርመራ ጋዜጠኛ ሚና (investigative journalism ),ሕግና ጋዜጠኝነት፣የጋዜጣ ዲዛይን እና በተለያዩ የሙያው ንዑስ ዘርፎች ሥልጠናዎችን ወስዷል።በጊዜው በአገሪቱ የጋዜጠኝነት ትምህርት ራሱን ችሎ በማይሰጥበት ወቅት በመሆኑ በተለይ ለኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች ያን መሰሉ አጋጣሚ ጠቃሚ ነበር።
ከኮተቤ በኋላ የጋዜጠኝነት የዲግሪ ፕሮግራም ለመከታተል በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ሥር እዛው እያለ የተጠቃለለው የቀድሞ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ግቢ ካለው ትምህርት ቤት ትምህርቱን እየተከታተለ ሳለ ምርጫ 1997ን ተከትሎ በመጣው ቀውስ የሁለተኛ ዓመት ትምህርቱን ሳይጨርስ ከአገር የሚወጣበት አስገዳጅ ሁኔታ መጣ።
ጋዜጠኝነቱን እንዴት ገፋበት?
ሚኒ ሚዲያውላይ እየሰራም እየተማረም 12ኛ ክፍል ሲደርስ አንድ ቀን ከዳግማዊ ምንሊክ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚኒ ሚዲያ ክበብ(ዳ.ም.ሬ.ክ) በትምህርት ቤቱ በኩል ጥሪ ደረሰው።እዚያ ሲሄድ ዛሬ በተለያዩ ሚዲያዎች የሚሰሩና በጊዜው ለዛ ስብሰባ ከየትምህርት ቤታቸው የመጡ ተማሪ አማተር ጋዜጠኞች ተሰባስበው አንድ ሀሳብ ጠነሰሱ።በዚያ ሀሳብ መሰረት ከጥቂት ስብሰባ በኋላ ጳውሎስ ኞኞ አማተር ጋዜጠኞች ማህበርን(ጳ.አ.ጋ.ማ) ከመሰረቱት አንዱ ሆነ። ጳውሎስ ቢሞትም ስሙን ሕያው ለማድረግ የተመኘ ስብስብ ነበር።በወጣትነት እድሜያቸው በጊዜው ብዙዎቹ በዚያ ክበብ ትልቅ አስተዋጽዎ አድርገዋል። ዛሬ ራሳቸውን ችለው ትልልቅ ፕሮግራሞች በተለያዩ ጣቢያዎች የሚያዘጋጁ፣የፕሮግራም ኃላፊ እስከመሆን የደረሱም አሉ፡፡
ሀብታሙ ፣ጋዜጠኝነትን በጀማሪነት ተቀጥሮ መስራት የጀመረው አፈሩን ይቅለለውና ከአንጋፋው ጋዜጠኛ ወርቁ አለማየሁ ጋር ነበር፡፡ በጊዜው ወርቁ ያሳትም በነበረው «መብረቅ»ሳምንታዊ ጋዜጣ ላይ ሀብታሙ ጽሑፍ በማቅረብ ተሳትፎውን አሳደገ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ወደ ዝግጅቱ ባልደረባነት አድጎ ጋዜጣው ስሙን ቀይሮ ‹መብሩክ›ም ሲሆንም ለዓመታት ሰርቷል። አልፎ አልፎ በጊዜው ለነበሩ የተለያዩ ጋዜጦች ጽሑፍ ይጽፍ ነበር። ከመብሩክ በኋላ የሩሕ ጋዜጣና መጽሔትን በከፍተኛ ሪፖርተርነት ተቀላቅሎ ለዓመታት ሰርቷል። የፍርድ ቤትና የፓርላማ ዘገባን ከወትሮ በተለየ በስፋት ይዘግብ ነበር። አንዳንዶች ሲቀልዱ አብረው ሲሰላቹበት ከዋሉት የፓርላማ ውሎበ ዜናውን ያወጣው ነበር። ዜና ይወዳል። ሩሕ እያለ በአገሪቱ የፍርድ ቤትና የፍትሕ በታሪክ በውስጥ ዛሬም ድረስ የሚጠቀሱ ጉዳዮችን በአካል ተገኝቶ ተከታትሏል።
ብዙዎች የሚጠቅሱት የእነ አቶ ስዬ ችሎት ብቻ ሳይሆን የቀድሞ የፍትሕ ሚኒስትር ወረደ ወልድ ወልዴም የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ አክብረው ምላሽ ባለመስጠታቸው የአንድ ወር እስራት ሲፈረድባቸው እዚያው አራዳ ሶስተኛ ፍትሐብሔር ችሎት ነበር።የቀድሞው ዳኛ ነጻነት እና ባልደረባው ሚኒስትሩ ላይ የፈረዱት የወቅቱ የኢዴፓ አመራር የነበረውን አቶ ታምራት ታረቀኝን ፖሊስ አስሮ የት እንዳደረሰው ባለመታወቁ ያኔ ፖሊስ በፍትሕ ሚኒስቴር ስር በመሆኑ ሚኒስትሩ ለተከፈተው አካልን ነጻ የማውጣት ክስ ፖሊስ ተገቢውን ምላሽ ባለመስጠቱ ነው።ሚኒስትሩ የፍርድ ቤት ቀጠሮውን ትተው ሚኒስትሮች ም/ቤት ሪፖርት ነበረብኝ ብለው ሳይቀርቡ ይቀራሉ። በ2ኛው ቀጠሮ ፖሊስ አቅርባቸው ተብሎ ቀረቡ።ችሎቱ ሙሉ ቀን ነው የፈጀው።ሙሉቀን
እዛው የዋልንበትን ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ያኔ መውጣት የጀመረው የፍትሕ ጸሐይ ወዲያው እንዲጨልም ባይደረግ ዛሬ የት በደረሰን ብሎ እየተቆጨ ያነሳዋል።
ከሩሕ ወደ አዲስ ዜና ጋዜጣ ገባ።ከዜና አልፎ የፍትሕ አምድ ያዘጋጅ ነበር። ከዓመታት ቆይታ በኋላ ከአዲስ ዜና ለቆ ሪፖርተር ጋዜጣ እና መጽሔት ዝግጅት ክፍልን ተቀላቀለ።በየምዕራፉ ከመብሩክ እስከ ሪፖርተር ብዙ ተምሬበታለሁ ይላል።
በዚህ ሁሉ ሒደት ቀድሞ በአማተር ጋዜጠኝነት ማህበር እስከ ማቋቋም የነበረው ተሳትፎ ኋላም ነጻ ፕሬሱን ሲቀላቀል የለቀቀው አይመስልም።የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች ማህበር(ኢ.ነጋ.ማ) ከአባልነት እስከ ሥራ አስፈጻሚነት አገልግሏል።በጊዜው መንግሥት ማህበሩን እንደ ጠላት በመቁጠር የራሱን መፈንቀለ- ሥልጣን ያለ አባላቱ ፈቃድ ለማድረግ ከሕግ አግባብ ውጭ ከአገዳቸው የማህበሩ አመራሮች አንዱ ነበር።ከመብረክ/መብሩክ ጀምሮ ጓደኛውም የዛሬም ባልደረባውም የሆነው ጋዜጠኛ ታምሩ ገዳን ጨምሮ በጊዜው የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ክፍሌ ሙላትን ጨምሮ ድርጊቱን በመቃወም በመንግሥት ላይ ክስ መስረተው በፍርድ ቤት ፍትሕ ሚኒስቴር ላይ አስፈርደዋል።ከከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ በኋላ ይግባኝ ያልጠየቁት የወቅቱ ሹሞች ምርጫ 97 ማግስት ለደረሰባቸው ሽንፈት አንዱ ተጠያቂ ያደረጉትን ኢ.ነ.ጋ.ማን ወረው ንብረቱን ወርሰው ዘጉት።በኋላ ስሙን ይዞላቸው የሚዞር አንድ የቀድሞ የማህበሩ ጸሐፊ አገኙ።
ስደት
የኢ.ነ.ጋማ የሥራ አስፈጻሚ እያለ ግብጽ ለአጭር ጊዜ የሥራ ልምድ ለመውሰድ በማህበሩ በኩል ተጋብዞ እ.ኤ.አ 2003 ላይ ሄደ። በግብጽ ቆይታው ወደ አገሩ ሲመለስ ‹‹ግብጽ ሔጄ ለአገሬ አልቅሼ መጣሁ ››በሚል በቁጭት የጻፈው የጉዞ ማስታወሻን የሚያስታውሱት አሉ። ግብጽ በአባይ ያን ሁሉ ስታለማ እኛስ የታለን የሚል እና በቆይታው የታዘበውን በጊዜው ሪፖርተር መጽሔት ላይ ያወጣው ትዝብት ነበር።
በምርጫ 1997 ግንቦት 7 የምርጫው እለት አዋሳና ሻሸመኔ እየተመላለሰ ሪፖርተርን ወክሎ ምርጫውን ታዝቧል።የምርጫ ትዝብቱን የሕዝቡን ተስፋ ጽፎታል። ያ የሕዝቡ የነጻነት መንፈስ ከሌሊት ጀምሮ ለድምጹ የነበረው ቀናኢነት ዛሬም ድረስ ያስቀናዋል።መጨረሻው ሳያምር የሕዝቡ ድምጽ ተሰርቆ የሆነውን ወንጀል አይቷል። የንጹሀን ሕይወት ምርጫውን ተከትሎ ሲጠፋና ባልደረቦቹ፣የሙያ አጋሮቹ ሲታሰሩ ስደትን ከመረጡት ተዳበለና አስቀድሞ ለልምድ ወደ ሔደባት ግብጽ ካይሮ አቀና።
ከሪፖርተር ወጥቶ ከአገር ከመውጣቱ በፊት በነበረው አንድ ወር የዛሬው ሰብዓዊ መብት ጉባዔ በጊዜው መጠሪያው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ(ኢ.ሰ.መጉ.) የመብት ጥሰት መርማሪ ሆኖም ሰርቷል። ምርጫውን ተከትሎ ልጆቻቸው የተገደሉ፣ባሎቻቸው የሞቱ፣የደረሱበትን የማያውቁ፣የታሰሩባቸው ብቻ ብዙ መሄጃ ያጡ ዜጎች ብቸኛ ተሰፋ አድርገው ኢሰመጉ ድምጻቸውን እንዲያሰማላቸው ይመጡ ነበር።በዚያ ትንሽ ቆይቼ የተሻለ አስተዋጽዎ ባደርግ ኖሮ ብሎ ዛሬም ሁኔታውን በቁጭት ያስበዋል።
በካይሮ የአንድ ዓምት ከዘጠኝ ወር ቆይታው ትንሽ ጊዜ አጫጭር ኮርሶችን ወስዷል። ለስደተኛ የሚሰጡ የቋንቋ እና የኮምፒዩተር ሥልጠናዎችን ብቻ ሳይሆን በካይሮ አሜሪካ ዩኒቨርስቲ ለጥቂት ጊዜ ሕግ እና ስደተኛ ላይ ያተኮረ ሥልጠና ከተለያዩ አገራት ከተውጣጡ የዓለም አቀፉ ስደተኞች ጉዳይ የሚያዩ ሠራተኞች ጋር እድሉን አግኝቶ ወስዷል።
ስደት ሲወጣ እጮኛውን ትቶ ቢሆንም ካይሮ ከዓመት ቆይታ በኋላ ወስዶዋት እዚያው ተሞሽረዋል። ከግብጽ ወደ አሜሪካ እ.ኤ.አ. በመስከረም 2007 በዓለም አቀፉ ስደተኞች ማህበር ያገኘውን እድል የአሜሪካ መንግሥት በስደተኝነት ተቀብሎ እሱና ባለቤቱ ገቡ። ዛሬ የሁለት ወንዶች እና የአንዲት ሴት ልጅ አባት ነው። ባለቤቴ መርከብ ጸጋዬ ጥሩ እናት ባትሆን እዚህ አገር የጀመርኩትን ሙያ ለኑሮህ ሌላ ነገር እየሰራሁ ከ10 ዓመታት በላይ ሕብር ሬዲዮን ከባልደረባዬ ታምሩ ገዳ ጋር ይዘን መዝለቅ ከባድ ይሆን ነብር ይላል።
ሕብር ሬዲዮ እ.ኤ.አ. በመስከረም 2009 ተቋቋመ። ዛሬም ድረስ አቅም በፈቀደው መጠን ቀጥሏል፡፡ቀድሞ ከቬጋስ አልፎ በብዙ ቦታ እንዲሰማ ከዘሐበሻ ዩቱብ ጋር በትብብር ሲሰሩ መቆየታቸውን ይገልጻል። ዛሬ ሕብር ሬዲዮ በራሱ የዩቱብ ቻናል ጭምር ይሰራጫል።በሕብር ድህረ ገጽም ተክፍቶ አገልግሎት ይሰጣል። በሕብር ለዓመታት በርካታ ጉዳዮች ተዳሰዋል።ከሁሉም ማህበረሰብ በተለይም ያለ ድንበር የአገርና ወገን ፍቅር ጉልበት ነው የሚል አባባል አለው።ሁለቱ ከሌለህ በተለይ በውጭ አገር ከዚያ የዕለት ኑሮ አልፈህ ለማሰብ ጥንካሬ የሚገኝ መሆኑን ይጠራጠራል። ጥቂት ቢሆኑም ለወገኖቻቸው ድምጽ የሚሆኑ ሰዎች በሰልፉም፣በመዋጮውም፣ስለ ወገን አቤት በማለቱም ያ ጥንካሬ ያስፈልጋል ለእኛም ብርታት የሆነን እሱው ነው የሚል ጠንካራ እምነት አለው። ሕብር ሬዲዮን የመሰለ በብዙ አስቸጋሪ ፈተና የሚያሳልፍ ፕሮግራም ከ10 ዓመት በላይ መስራት ከባድ ይሆን ነበር ይላል።ማንም ሰው ሲጠቃ ማየት አይፈልግም።ጥቃት ያመኛል ይላል።በእናቴ እጅ ነው ያደኩት።የሆነ ጽናት እና ጥንካሬ ከሱዋ የወሰድኩ ይመስለኛል።
ሀብታሙ እናቱን ወይዘሮ ብዙነሽን ምንጊዜም ማመስገን ይፈልጋል፡፡
‹‹………. በሕይወት ስላለች እግዚያብሄርን አመሰግነዋልሁ። እናቴ ወ/ሮ ብዙነሽ መንበሩ ትልቅ ባለውለታዬ ነች።የምፈልገውን ሙያ በጊዜው ያለ አንዳች ጫና ማድረግ መቻሌ ምን አልባት ዛሬም ድረስ በዚሁ አቆይቶኛል የመጀመሪያ ልጅ ብሆንም 3 እህቶች እና አንድ ወንድም ሶስቱ ልጆቼ አቤኔዘር፣ናትናኤል እና ሀሴት ይባላሉ።
ሀብታሙ በስተመጨረሻ እንዲህ ይላል
‹‹……..ሰው በአገሩ ሰውነቱ ቦታ አግኝቶ አላግባብ ሕይወቱን ሆነ ንብረቱን የማያጣበት ሥርዓት እስኪመጣ የምንችለውን ሙያዊ አስተዋጽዎ እያደረግን እየቀጠልን ነው።;››ሲል ሀሳቡን ይናገራል፡፡