ሀበነዮም ሲሳይ ታረቀኝ

ሀበነዮም ሲሳይ ታረቀኝ

ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ እስካሁን መስፈርቱን የሚያሟሉ ባለታሪኮች ግለ-ታሪካቸውን እየጻፉ እየላኩልን ነው፡፡ እርስዎም tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡

ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ6 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ከሚድያ ዘርፍ ታሪኩ የሚቀርብለት ሰው ሀበነዮም ሲሳይ ታረቀኝ ይሆናል፡፡

ልጅነትና እድገት

ሀበነዮም ሲሳይ ታረቀኝ መስከረም 25 ቀን 1975 ዓ.ም. በታሪካዊቷ ደሴ ከተማ ላይ ነው የተወለደው፡፡ አባቱ አቶ ሲሳይ ታረቀኝ በቀ/ኃ/ሥላሴ ዘመነ- መንግስት የትራፊክ ፖሊስ የነበሩ ሲሆን የመንግስት ስራቸውን በራሳቸው ፈቃድ ከተው በኋላ ወደደሴ ከተማ በማቅናት“ፎቶ ሸዋ” የተባለ የመጀመሪያውን የንግድ ፎቶግራፍ ቤት ከፍተዋል፡፡ አቶ ሲሳይ ከደሴ በተጨማሪ በአዲስ አበባ፣ ከሚሴ፣ ወልዲያና ሌሎች ከተማዎችም ቅርንጫፍ የነበራቸው ሰው ነበሩ፡፡

አቶ ሲሳይ ታረቀኝ ከነበራቸው ህብትና ዝና በላይ ግን በጨዋታ አዋቂነታቸውና ባልተለመዱ አስገራሚ ፈላስፋዊ ስብዕናቸው የሚታወቁ ሰው ነበሩ፡፡ እናቱ ወ/ሮ መቆያ ለገሠ ደግሞ የደሴ ከተማ ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ በሚያስተዳድረው የመጀመሪያው መዋዕለ- ሕፃናት መምህርት ነበሩ፡፡ በርካታ ሕጻናትን ያስተማሩት ወ/ሮ መቆያ ለገሠ ልጀችን በሥነ- ምግባር ቀርጾ ለቁምነገር በማብቃታቸው ይታወቃሉ፡፡

በተጨማሪም ወላጆቻቸው ጥለዋቸው የሄዱ ህጻናትን በማንሳት ጭምር አሳዳጊ እስኪገኝላቸው ድረስ በመንከባከብ ጭምር ይሰሩ የነበሩት እናቱ በደግና ሩ ህሩህ ልባቸው የሚታወቁ ነበሩ፡፡ በዚህም የተነሳ አባትና እናቱ በደሴ ከተማ ውስጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ ጥንዶች ነበሩ፡፡

በመልካም ቤተሰባዊ ሕይወትና እንክብካቤ ውስጥ ያደገው ሀበነዮም ሲሳይ የልጅነት ጊዜው በወላጆቹ ፍቅር ተከቦ ያደገበት አስደሳች ጊዜ ነበር፡፡ ወላጅ እናቱ ገና በ38 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ የ10 ዓመት ልጅ የነበረው ሀበነዮም ወላጅ አባቱንም ያጣው የ18 ዓመት ልጅ ሆኖ ነው፡፡ በተለይ እናቱን በሕይወት ሳሉ የነበረው የልጅነት ጊዜ በጥሩ ትውሰታ የተሞላ ነበር፡፡

ለምሳሌ እናቱ ማሕበራዊ ጉዳይ ውስጥ በመስራታቸው ምክንያት ገና በለጋነት እድሜው በዘመኑ ለነበሩ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት አበባ በተደጋጋሚ አበርክቷል፤ ከነዚህም ውስጥ አንዱ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የነበሩት ጓድ መንግስቱ ኃ/ማርያም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ይሁን እንጅ የእናቱን በሞት መለየት ተከትሎ ቤተሰባቸው ውስብስብ ችግር ውስጥ በመግባቱ የተነሳ የልጅነት እድሜው በፈተና የተሞላ ሆኗል፡፡

የባለቤታቸውን በሞት መለዬት ተከትሎ ብዙ ነገሩ የጨለመባቸው አባቱ ድርጅታቸውን በአግባቡ ማስተዳደር ስላቃታቸው ከስሮ ተሸጠ፣ መኖሪያ ቤታቸውን አስይዘው ብድር በመውሰዳቸውና መክፈል ስላቃታቸው ቤታቸው በሐራጅ ተሸጠ፤ ይህን ተከትሎም ቤተሰቡ ተበታትኖ መኖር ጀመረ፡፡ በዚህ የተነሳ ደግሞ ቤተሰቡ አይነተ ብዙ ለሆነ አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ችግር የተጋለጠ ሲሆን የሚያግዛቸው ሰው በማጣታቸው ኑሮን በየራሳቸው መንገድ ለማሸነፍ ከባድ መስዋዕትነትን ከፍለው አድገዋል፡፡ ሀበነዮም ሲሳይ አሁን ያለበት ደረጃ የደረሰው ቤተሰቡ የገጠመውን የመበታተንና ሌሎችንም በርካታ ችግሮች ተቋቁሞ በማለፍ ነው፡፡

የወጣትነት ዘመን

ሀበነዮም የወጣትነት ዘመኑ የዕለት ጉርሱን እንኳን ማግኘት ፈተና ሆኖበት ኑሮና ትምህርቱን ለማሸነፍ በየቀኑ ትግል በመግጠም ነው፡፡ በወጣትነቱ የገጠሙትን ችግሮች ለመወጣት ከረዱት ነገሮች ውስጥ በተለያዩ የአማተርና የበጎ አድራጎት ክበባትና ማሕበራት ውስጥ የነበረው ተሳትፎ ከነበረበት የሕይወት ችግር አንጻር ትልቅ መፍትሔ ሰጥተውታል፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር የደቡብ ወሎ ቅርንጫፍ የወጣቶች ክበብ ውስጥ የወጣቶች አስተባባሪ እስከመሆን በመድረስ፣ ሀገራዊ ባህልና እሴቶችን ለማስተዋዎቅ በመላው ኢትዮጵያ ጉዞዎችን ያደርግ የነበረውና “በተጓዝክ ቁጥር እንደርቀትህ መጠን ትሰፋለህ” የሚል መርሕ የነበረው የደሴ ቱሪዝም ክበብ ውስጥ አባል ሆኖ በርካታ የሕይወት ክህሎቶችን በመቅሰም፣ በደሴ ደብረ መዊዕ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት እና ቅዱስ መርቆሪዮስ ቤተ ክርስቲያን በሚገኘው የፍሬ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪ ሆኖ ማለፉ ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡

የትምህርት ሕይወት

ከ1-6ኛ ክፍል ድረስ በደሴ ከተማ በሚገኘው የትግል ፍሬ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ 7 እና 8ኛ ክፍልን በቅዳሜ ገበያ የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምሀርት ቤት ሲሆን 9ኛ ክፍልን ደግሞ በወ/ሮ ስኂን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሯል፡፡ ከዚህ በኋላ 10ኛ ክፍልን በአዲስ አበባ ከተማ የቦሌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማረ ሲሆን ቀሪውን 11 እና 12ኛ ክፍል ግን ወደደሴ ከተማ በመመለስ በወ/ሮ ስኂን የቀለምና ቴክኒክ ሙያ ትምህርት ቤት ተምሯል፡፡

በወ/ሮ ስኂን ትምህርት ቤት በነበረው ቆይታ ስፔሻል ተማሪዎች ይማሩበት በነበረው የቴክኒክና ሙያ እንዲሁም የቀለም ትምህርት አብሮ ይሰጥ በነበረበት ጊዜ ሲሆን የትምህርት ሥርዓቱም ከደርግ ዘመን የቀጠለው ነበር፡፡ ትምህርት ቤቱን ሲቀላቀልም የአዉቶሞቲቭ ቴክኖሎጂ ተማሪ ሆኖ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ የቀለሙን ትምህርት ግማሽ ቀን እየተማረ በቀሪው ግማሽ ዓመት ደግሞ የአውቶሞቲቭ ሙያን በመማር ከሶስት ዓመት በኋላ የሥርዓተ ትምህርቱ የመጨረሻ ዙር ተማሪ ሆኖ 12ኛ ክፍል ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ በአውቶሞቲቭ ቴክኖሎጂ ዲፕሎማ እና የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤቱን አምጥቶ ነበር፡፡

ለዩኒቨርስቲ መግቢያ ባመጣው ውጤት መሰረትም በ1995 ዓ.ም. በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የፖሊ ኢንጅነሪንግ ፋካልቲ ተመድቦ በቴክስታይል ቴክኖሎጂ ሙያ በአድቫንስ ዲፕሎማ በ1997 ዓ.ም. ተመርቋል፡፡ ከዚያም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማታው ትምህርት ክፍል የቴአትር ጥበባት ተማሪ በመሆን በዲግሪ ተመርቋል፡፡ ከዚያም በማስከተል በ2011 ዓ.ም. ከቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ በነገረ መለኮት ትምህርት የዲግሪ ትምህርቱን አጠናቋል፡፡

የአማተርነት ሕይወት

ገና በልጅነቱ ፓይለት ወይም ጋዜጠኛ የመሆን ፍላጎት የነበረው ሀበነዮም ሲሳይ በወ/ሮ ስኂን ትምህርት ቤት ውስጥ በነበረው ሚኒ ሚዲያ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የጋዜጠኝነት ሙያን መለማመድ ጀምሯል፡፡ በተጨማሪም በትምህርት ቤቱ ውስጥ በነበረው የሥነ ጽሑፍና ክርክር ክበብ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ስለነበር በሥነጽሑፍ እጁን ማፍታታት ጀመረ፡፡

በማስከተልም ጽንሰቱን በትምህርት ቤቱ ሚኒ ሚዲያ ውስጥ ያደረገው የኋላው የደሴ ቱሪዝም ክበብ ውስጥ በነበሩ የተውኔት፣ የሥነ ጽሑፍና የተለያዩ የኪነ ጥበብ ዝግጅቶች ላይ በመሳተፍ ራሱን ማሳደግ ቻለ፡፡

ከዚያም በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ውስጥ በቆየባቸው ሶስት ዓመታት ውስጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ በመሆን ከ10 ያላነሱ ክበባትን በመምራትና አባል በመሆን የአማተር የሥነጽሑፍ፣ የጋዜጠኝነትና የተውኔት ሕይወቱን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ችሏል፡፡ የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የፖሊ ካምፓስ ይሳተፍባቸው ከነበሩ ክበባት መካከል የሥነጽሑፍ ክበብ አባል በመሆን ቋሚ የሥነ ጽሑፍና የግጥም ምሽቶችን በግቢው ውስጥ በማዘጋጀት፣ በወቅቱ ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን የተማሪዎች የጥያቄና መልስ ውድድር (Hero Question and Answer Program) አዘጋጅና አቅራቢ በመሆን፣ የግቢውን ሚኒ ሚዲያ በመምራትና ፕሮግራሞችን በማቅረብ፣ የግቢው ፀረ ኤች አይቪ ክበብ አባል በመሆን፣ በወቅቱ የነበሩት 6 ዲፓርትመንቶች የጋራ ሃሳብ ማፍለቂያ የነበረው የMP6 ክበብ (Mission Possible for 6 Departments) አባል ሆኖ፣ የRDL (Redefining Life) የተቸገሩ ሰዎችን የሚረዳ የበጎ አድራጎት ክበብ ደጋፊ በመሆን፣ የተማሪዎች መማክርት እና የምረቃ ኮሚቴ አባል ሆኖ የተሳተፈባቸው ከፊሎቹ ናቸው፡፡

የሥራ ዓለም

የመጀመሪያ ስራውን በ1998 ዓ.ም. የቴክስታይል ፕሮፐርቲ መምህር በመሆን በሲታም የልብስ ስፌትና የፋሽን ዲዛይን ትምህርት ቤት የጀመረ ሲሆን ከአንድ ዓመት በኋላ ድግሞ በኔክስት የፋሽን ዲዛይን ኮሌጅ በተመሳሳይ ትምህርት የማስተማር ስራ ሰርቷል፡፡ በ2000 ዓ.ም. ከመምህርነት ሙያ በመውጣት በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ውስጥ የፍሎር ማናጀር እና የስቱዲዮ ዳይሬክተር ሆኖ ለ2 ዓመት ሰርቷል፡፡

ወደሚወደው የጋዜጠኝነት ሙያ በ2002 ዓ.ም. ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን በሪፖርተርነት በመቀላቀል ስራ የጀመረው ሀበነዮም ሲሳይ በፋና ኤፍ ኤም፣ በፋና ቴሌቭዥን እና በፋና ዲጂታል ሚዲያ ላይ ሰርቷል፡፡ በመጀመሪያ የስራ ዓመታት ውስጥ ለሀገራችን ኤፍ ኤም ሚዲያዎች አዲስ አይነት አቀረራረብ ያስተዋወቀው ፋና90 ሲጀመር ከመጀመሪያዎቹ አቅራቢዎች ውስጥ አንዱ በመሆን ሰርቷል፡፡ ከዚህ በኋላ በግል ሕይወቱ በገጠሙት ምክንያቶች ለሁለት ጊዜ ድርጅቱን ከለቀቀ በኋላ ወደፋና የተመለሰው ሀበነዮም የጋዜጠኝነት ሙያ ሱስ አስያዘኝ የሚለውን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት “ገና ሳልገባ፣ ገብቼም ሆነ ወጥቼ የምወደው ቤት ነው” ይለዋል፡፡

ከፋና በወጣባቸው ዓመታት ሌሎች ሥራዎችንም የሰራው ሀበነዮም ወደኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ተመልሶ በዜና አንባቢነት ለአንድ ዓመት አገልግሏል፡፡ የኢትዮጵያ ስካውት ማሕበር ከኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ጋር በመተባበር ያቀርብ የነበረውን “ዝግጁ” የሬዲዮ ፕሮግራም በዋና አዘጋጅነት ለአንድ ዓመት ከሶስት ወር ሰርቷል፡፡ ከዚያም በዚያው ጣቢያ ላይ “ቴክኖ ላይፍ” የተባለ በቴክኖሎጂ ላይ የሚተኩር የሬዲዮ መዝናኛ ፕሮግራም ከአንድ ዓመት በላይ በዋና አዘጋጅነት ሰርቷል፡፡

ከዚህ ባሻገር በአሐዱ ሬዲዮ 94.3 ላይ በኤዲተርነትና ብራንድ ማናጀርነት የሰራ ሲሆን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቴሌቭዥን ጣቢያ ምክትል ሥራ አስኪያጅ እና ቴክኒካል ዳይሬክተር በመሆንም ሰርቷል፡፡ በሌላ በኩል በተለያዩ ጊዜያት ሶስት የንግድ ድርጅቶችን በግሉና ከጓደኞቹ ጋር በማቋቋም(ኤች ኤ ማስታዎቂያና ፕሮሞሽን፣ ሜሮኤ መልቲሚዲያ የግል ድርጅት እና ሜሮኤ ሚዲያ እና ኮሚዩኒኬሽን ኃ.የተ.የግ.ማ.) የተለያዩ የማስታዎቂያ፣ የዶክመንተሪ፣ የሁነት ዝግጅት፣ ማስታዎቂያ፣ የሬዲዮ ፕሮግራሞችንና የመሳሰሉትን በጊዜው ሰርቶ ለደንበኞቹ እርካታ ሰርቷል፡፡

በተጨማሪም በሁለት የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ምስረታ ታሪክ ውስጥ የራሱን አሻራ ማኖር ችሏል፡፡ በቅድሚያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቴሌቭዥን ጣቢያ ሲቋቋም በሚዲያው ምስረታ ሒደት ውስጥ ባለሙያዎችን በማሰልጠን፣ የሚዲያውን መመሪያዎች በማዘጀት፣ ፎርማቶች በመቅረጽና ለአየር እንዲበቃ በማድረግ በጣቢያው ምስረታ ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በማስከተልም የአሐዱ ሬዲዮ ሲመሰረት የጣቢያውን ሕጋዊ ሒደት ከማስፈጸም ጀምሮ፣ የኤዲቶሪያል ፖሊሲና፣ መመሪያዎችና ፎርማቶችን በመቅረጽ እንዲሁም ጣቢያው በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ የሆነበትን ኢትዮጵያዊ መልኩን እንዲይዝ በማድረግ አሻራውን አስፍራል፡፡

ከዚህ ባሻገር ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በ2012 ዓ.ም. የጀመረውና አንድ ዓመት ዓመት ወስዶ በተጠናቀቀው ተቋሙን በአዲስ መልኩ የመለወጥ ሥራ የተሰጠው የስትራቴጂ ቡድን ውስጥ አባል በመሆን የተቋሙን የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ሰነድ፣ ቢዝነስ ሞዴል፣ መዋቅርና ሌሎች ሰነዶች ውስጥ ከጥናት እስከ ትግበራ በመሳተፍ በመሳተፍ ኮቪድ-19 በተከሰተበት ጊዜ ውስጥ ከቡድኑ አባላት ጋር ከፍተኛ መስዋዕትነት በመክፈል ለሚወደው ተቋም የራሱን ድርሻ ማበርከት ችሏል፡፡

ለቴክኖሎጂያዊ ጉዳዮች ቅርበትና ፍላጎቱ ያለው ሀበነዮም ሲሳይ ከኮቪድ-19 መከሰት ጋር ተያይዞ በፋና ቴሌቭዥን የተጀመረው “ፋና ጤና” ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ፣ በፋና ኤፍ ኤም ላይ ዘዎትር ማክሰኞ ረፋድ የሚቀርበው “ፋና ዲጂታል” የተባለ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ በመሆን እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ በጣቢያው የዲጂታል ሚዲያ ክፍል ውስጥ የዩትዩብና ሞኒተሪንግ ክፍል ረ/ዋና አዘጋጅ በመሆን እየሰራ ይገኛል፡፡

የግል የሕይወትና አመለካከት

ከወ/ሮ ዝናሽ መንግስቴ ጋር ትዳር መስርቶ የሚኖረው ሀበነዮም ሲሳይ የሶስት ልጆች አባት ሲሆን በትዳሩ ደስተኛ አባት ነው፡፡ ከራሱ በላይ ኢትዮጵያ ሀገሩን አብልጦ እንደሚወድ ብዙዎች የሚመሰክሩለት ሀበነዮም በጋዜጠኝነት ሙያው ማሕበራዊ ለውጥ (Social Transformation) ማምጣት የሚፈልግ ሲሆን ለሚወዳት ሀገሩ የተሻለ ስራ መስራት የሁልጊዜም በጎ ሀሳቡ ነው፡፡ “ጤናማ ሀገር የምትወሰነው ባሏት ጤናማ ትዳሮች ልክ ነው” የሚል የግል እምነት ያለው ሀበነዮም አሁን ያለችው ኢትዮጵያ ከገባችበት ውጥንቅጥ ችግር ወጥታ ክብሯ የተጠበቀና ሰላማዊት ሆና ለአዲሱ ትውልድ እንድትደርሰውና በሀገሩ የሚኮራ እንዲሆን ካስፈለገ የሁሉም ነገር መሰረት የሆነው ቤተሰብ ላይ መሰራት አለበት ይላል፡፡

ለዚህም ከራሱና ከቤተሰቡ “ሕይዎት በመማር፣ እንዲሁም በሀገሪቱ በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የፍቺ ቁጥር መጨመርና ወጣቱ ስለትዳር ያለው ዋጋ መቀነስ የሚፈጥሩበትን ስጋት በአዎንታዊ መልኩ ለመቀየር በኢትዮጵያ ውስጥ ጤናማ ትዳርና ቤተሰቦች እንዲበዙ የሚያደርጉ ስራዎችን የመስራት ፍላጎት አለው፡፡

በተጨማሪም የተማራቸው ትምህርቶች የተፈጥሮ ሳይንስ እና የማሕበራዊ ሳይንስ ዘርፎች በመሆናቸው ከሁሉም የትምህርት አይነቶች ያገኘውን እና በግል ንባቡ ያዳበራቸውን “የቴክኖሎጂ እውቀቶችን በመጠቀም ማሕበራዊ ችግሮችን መፍታት” በሚል እሳቤ ሁሉንም ሙያዎቹን አቀናጅቶ ለማሕበራዊ ፋይዳ የመጠቀም እቅድ አለው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *